ፍቅር በምትባል አገር ውስጥ አንድ ሽፍታ ይኖራል። ሽፍታው በየግዜው እየዘረፈ እና እየገደለ አስቸገረ። ዛሬ እዚኛው መንደር ከገደለ ነገ እዛኛው መንደር ይገድላል ዛሬ እዚኛው መንደር ከዘረፈ ነገ እዛኛው መንደር ይዘርፋል። ዛሬ እዚህ መንደር እሳት ነገ እዛ መንደር እሳት ሁሉም መንደር በየተራው የሽፍታው ጅራፍ ያላረፈበት የለም። የፍቅር ነዋሪዎችም ሽፍታው ከዛሬ ነገ ይለወጣል ሽፍታነቱንም ይተዋል ወደ ፍቅር ኑሮ ይመለሳል በሚል ተስፋ ቢጠበቅም ይባሱኑ ሽፍታነቱ ብሶበታል። በጥባጭ ካለ ጥሩ ጠላ አይጠጣም እንደሚባለው ሁሉ ህዝቡ በፍቅር አገሩ መኖር እስከሚያስጠላው ተበጠበጠ ዛሬ እዚህ መንደር ነጋ እዛ መንደር አዘን ነው እንደ ክረምት እና በጋ አዘን ገባ አዘን መጣ መባባል ከተጀመረ በፍቅር አገር ሰነበተ። ገዳይ ካለ ሟች እንዳለ የተረዳው የፍቅር ነዋሪዎች በመሰባሰብ ተማከሩ ለሁሉም ነዋሪ መልዕክት አስተላልፈው ምክክር ያዙ። እንዲህም በሚል፡-
ሽፍታ አገራችን ከገባ ሰንብቷል ዛሬ የኛን መንደር አምሶት ገድሎ ከሄደ ሌላ ግዜ ሌላው መንደር እንደዚሁ ያደርጋል ሃዘን ያልገባበት መንደር ችግር ያላጋጠመው አካባቢ የለም የሚያደርሰው ጉዳት እየከፋ ስለመጣ በአገራችን ሃዘን እንዳይኖር ጥፋትም እንዳይከሰት ይህንን ሽፍታ ማጥፋት አለብን ሽፍታው እስካልጠፋ ድረስ ሃዘናችን እየጨመረ ጉዳታችንም እየከፋ ይመጣል እንጂ ሰላም አይኖረንም በሚል ተወያዩ። የተለያዩ ሃሳቦች መንሸራሸር ጀመሩ።
ከአንዱ መንደር የመጣው ከመሃል ተነስቶ እንዲ አለ፡- ሽፍታው መሳሪያ ታጥቋል ብዙ ሰራዊቶችም አሉት ነካክተነው መንደራችንን በሙሉ እንዳያጠፋው አሉ።
ከሌላ መንደር የመጣው አንዱ ከመሃል ተነስቶ እንዲ አለ ፡- አሁን መቼ እየኖርን ነውና አገሬው እየተገደለ መንደራችን እየታመሰች አይደል እንዴ? እሱ የታጠቀውን መሳሪያ እኛ የማንታጠቀው ምን ስለሆነ ነው? ትሰማለህ አሉ ወደ አስተያየት ሰጪው ዞወር ብለው ቁጣ በተሞላበት አነጋገር በታሪክም ሆነ በእውነቱ ህዝብን ተዋግቶ ያሸነፈ ማንም የለም! ይልቅስ ሽፍታው እየገደለን እኛ እያለቀስን ከምንኖር ገዳያችንን በህብረት ተነስተን ገድለነው በሰላም መኖር አሉ። የሁሉም ሃሳብ በሚመስል ሁሉም የአዎንታ ስሜት አሳዩ።
ከሌላው መንደር የመጣውም ተነስቶ እንዲ አለ፡-ለሽፍታው ጉልበት የሆነው እኛው የምንመግበው እኛ የምናጠጣው እኛ የምንሞተውም እኛ እሱ ምን ያድርግ የፈለገውን አንስቶ ሲወስድ ዝም የፈለገወን ገድለ ዘርፎ ሲወስድ ዝም የፈለገውን ሲያስር የፈለገውንም ሲፈታ ዝም ታዲያ ምን ያድርግ በአገሩ ወንድ የሌለ መሰለው ወንድ እራሱ ብቻ እንደሆነ አድርጎ እየተዘዋወረ ይጨርሰን እንጂ…. እንግዲህ ባገራችን በፍቅር ለመሮር የሁሉም መንደር ሽፍታውን ላለመመገብ ውሃም ላለማጠጣት ሊገድለን ሲመጣ ሽፍውን በመግደል ሞት ሽፍታ መንደር እንደሚገባ ማሳየት አለብን አሉ።
ከሌላ መንደር የመጣውም ሌላኛው ተነስቶ እንዲህ አለ፡- መጥረቢያ የተባለች አንዲት ትንሽ ብረት ዛፎቻችንን ጨፍጭፋ ጨረሰች ስለዚህ ለፍርድ ትቅረብልን ብለው ዛፎች ሁሉ ሰልፍ ወጡ እናም መጥረቢያ ለፍርድ ቀረበች ዳኛውም ስለምንድን ነው ዛፎችን የምትጨፈጭፊው ብለው ጠየቋት መጥረቢያም ስትመልስ መቼ እኔ ሆንኩኝና የምጨፈጭፋቸው ከነርሱ መሃል ጠማማ እንጨት እጀታ ሆናኝ ነው እንጂ እኔ መቼ ሃይል አለኝ አለች ይባላል። ለሽፍታው ሃይል ሆነው ህዝባችንን የምናስጨርስ ከኛ መሃል እጅ የሆኑት አሉና ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ወደ ፍቅር አገራቸው ሳይመሽባቸው እንዲቀላቀሉ እንጠይቃለን አለበለዛ ግን ሽፍታው በሚጠፋበት ግዜ እነሱም አብረው እንደሚጠፉ ማወቅ አለባቸው ፍቅር ወደ ቤቷ እንድትመለስ ሰላም ወደ መንደራችን እንዲገባ ለሽፍታው እጀታ የሆናችሁ በሙሉ ስለእውነት፣ ስለ ሰላም፣ ስለነጻነት፣ ከህዝቡ ጎን እንድትሆኑ ጥሪያችን ነው አሉ። የዚህን ግዜ የተሰበሰበው ህዝብ በሙሉ በጭብጨባ አጀባቸው። ለሽፍታ እጅ በመሆን ወገኑን የሚያስጨፈጭፍ እና በደልን የሚያደርስ ሁሉ ቆም ብሎ የሚያስብበት ግዜ ነው። ሽፍታው በሚያዝበት ግዜ እና በሚጠየቅበት ግዜ መቼ እኔ ሃይል ነበረኝ ከእናንተ ውስጥ የበቀሉ ጠማማ ሰዎች እጅ ሃይል ሆነውኝ ገደልኩኝ እንጂ ብሎ እንዳይመሰክርብን የሽፍታ አገልጋይ ከመሆን ወጥተን ወደ ፍቅር አገራችን እንቀላቀል። ያኔም ገዳዩን በመግደል ሞት ባገራችን እንዳይኖር እናደርጋለን። የሞት ንጉስ እስከመጨረሻው ተገርሰስ፡ የፍቅር ንጉስ ባገራችን ንገስ ብለን ፍቅርን እናነግሳለን።
ከተማ ዋቅጅራ
23.07.2015
Email- waqjirak@yahoo.com