Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

”የምታስፈራው የታማኝ ኢትዬጲያ!” – ከኤርሚያስ ለገሰ

$
0
0

ባልጠበኩት ሁኔታ ሰሞኑን ፋታ ካጡ ግለሰቦች መደዳ ተሰልፌያለሁ። ሳይቸግረኝ ” የኢትዬጲያ አየር ሀይል” ከሚባል የታሪክ ባህር ውስጥ ገብቼ እየዳከርኩ ነው። በየቀኑ በበርሜል እየጠጣሁ እንኳን ልረካ አልቻልኩም። ርግጥም የኢትዬጲያ አየር ሀይል ከጥግ እስከ ጥግ ሊቀዘፍ የማይችል ባህር ነው። መስመጥ ያልፈለገ እንዲጀምረው አይመከርም!!…እንደ ታማኝ በየነ እንባውን ባደባባይ አፍሶ መጠነኛ ትንፋሽ መውሰድ ካልተቻለ በስተቀር።

tamagn
ስለ ኢትዬጲያ አየር ሀይል በዝርዝር ለማወቅ የገፋፉኝ ምክንያቶች በርካታ ናቸው። የመጀመሪያው አለማወቄን ማወቄ ነው። በተለይም ከታማኝ ጋር በነበረኝ ተደጋጋሚ ጉዞዎች ስለ ቀድሞው መከላከያ ሰራዊት ( ምድር ሀይል፣ አየር ሀይል፣ ባህር ሀይል…ወዘተ) ያለው ተዝቆ የማያልቅ መረጃ እራሴን እንድፈትሽ አግዞኛል። ታማኝ ስለ ኮንጐ ዘማች ኢትዬጲያውያን ገድል በመረጃ ተደግፎ ሲናገር አፍ ያስከፍታል። እነዚህ መረጃዎች ምን አልባት የአሜሪካው ኮንግረስ ላይብረሪ ይገኙ ይሆናል እንጂ፣ ኢትዬጲያ ( ያውም በታቀደ ሁኔታ ታሪክ በሚወድምበት ዘመን) ለማግኘት የሚቻሉ አይደለም። የኢትዬጲያ መከላከያ ሰራዊት ጦር መሳሪያ እስከ አፍንጫው የታጠቀውን የዚያድባሬ ጦር አሳፍሮ ለመመለስ ያደረገውን ተጋድሎ በቪዲዬና ኦዲዬ አስደግፎ ሲያቀርብ መመልከት ከእግር እስከ ጥፍር ይነዝራል። ስለ ጀነራል ፋንታ፣ ጀነራል ለገሰ፣ ኮረኔል በዛብህ ጴጥሮስ የጦር ሜዳ ጀብዱ ሲተርክ ለሰማ ሰው ” የታማኝን ኢትዬጲያ” ለመረዳት ጊዜ አይወስድበትም። 

በነገራችን ላይ ዛሬ ይህቺን አጭር ማስታወሻ በውድቅት ለሊት እንድጵፍ የገፋፋኝ ከአንድ ወዳጄ ጋር ያደረግነው ጨዋታ ነው። ለወዳጄ ሰሞኑን ስለተጠመድኩበት የቀድሞው የኢትዬጲያ አየር ሀይል ታሪክ በተመስጦ ሳጫውተው ከአፌ ተቀብሎ፣
” በል እንደ ታማኝ እንባህን እንዳትዘራ!” አለኝ።
እኔም ” እውነትን መርምሮ ማወቅ ከእንባ በላይ ያስኬዳል!” አልኩት።
ወዳጄ እንደመቀለድ እያለ፣
” የአንዳንዶች በተለይም እንደ ታማኝ ያላችሁ ሰዎች የምታስቧት ኢትዬጲያ ታስፈራለች!” አለኝ።ይህንን ቃል ከሌላም ሰው ሰምቼው ስለነበረ ብዙም አልገረመኝም። ለምላሹም ማሰብ አልጠየቀኝም። በአጭሩ፣
” እውነትህን ነው ወዳጄ በጣም ታስፈራለች ” አልኩት። ለምን እንደምታስፈራም እንዲህ በማለት በአጭሩ ነገርኩት፣

የታማኝ ኢትዬጲያ መሰረቷ ” በኢትዬጲያ አምላክ ይዣችኃለሁ እንዳትሸሹ!” የሚለው የጀነራል ፋንታ በላይ ተማጵኖ ያቆያት በመሆኑ ታስፈራለች!…የታማኝ ኢትዬጲያ በአየር ላይ እንደ ንስር አሞራ እየተገለባበጠ በአንድ ጊዜ አራት የሱማሊያ ተዋጊ አውሮፕላኖችን ከጥቅም ውጪ ያደረገው ጀነራል ለገሰ ሀገር በመሆኗ ታስፈራለች!…የታማኝ ኢትዬጲያ የአዶልፍ ፓርለሳክ እውነተኛ ታሪክ የሆነውን ” የአበሻ ጀብዱ” መጵሀፍ ውስጥ የአቢቹን ገድል የያዘች ስለሆነ ታስፈራለች!…የታማኝ ኢትዬጲያ ” የህውሀት ማኒፌስቶ” ፣ ” የኤርትራ ህዝብ ትግል ከየት ወዴት!” የሚለውን የህውሀት ውስጠ ሚስጥር ተገንዝባ ያለሞሞዳሞድ አምርራ የምትታገል በመሆኗ ታስፈራለች!!…የታማኝ ኢትዬጲያ ገዥዎች ባንዲራ ጨርቅ ነው ባሉ ማግስት በመቶሺዎችን በመስቀል አደባባይ ሰብስባ ” ባንዲራችን የአባቶቻችን ደምና አጥንት ነው! ” በማለት የምትናገር በመሆኗ ታስፈራለች!…የታማኝ ኢትዬጲያ የስልጣን እና የሀብት ክፍፍል ፍትሀዊ እንዳልሆነ በመረጃ ላይ ተደግፋ የምታጋልጥ፣ ” ይሄ ነወይ ፌደራሊዝም?” ብላ የምትጠይቅ በመሆኗ ታስፈራለች!!…ወዘተ።
( የጀነራል ለገሰ ተፈራን ቪዲዬ፣ የአበሻ ጀብዱ መጱሀፍ፣ የህውሀት ማኒፌስቶ/ ኦርጅናል/፣ ” የኤርትራ ህዝብ ትግል ከየት ወዴት” የሚለውን መጵሀፍ ራሱ ታመኝ እንዳነብ የሰጠኝ መሆኑን ከምስጋና ጋር መጥቀስ እፈልጋለሁ!”)


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>