ከሥርጉተ ሥላሴ 04.08.2015 /ሲዊዘርላንድ — ዙሪክ /
እናፍቅሻለሁ ስለእናት ወለላ – የሚስጢር ወላባ!
ጤና ይስጥልኝ የማከብራችሁ ወገኖቼ – እንዴት ሰነበታችሁልኝ ደህና ናችሁ ወይ? የሃሳብ ልዩነት ተፈልጎ አይገኘም። ማደግ የሚቻለውም በዚህ መስመር ነው። ነገር ግን ሆነን ያለፍነበትን ሌላው ሲሆን ወንጀል መሆኑ አይመችም። ዛሬ አርበኛው የሚያደርገው ተጋድሎ „የአማራውን ህዝብ ለማስጨረስ ሆን ብሎ የታሰበ ትልም ነውን?“ ሌላው የማሌ ርዕዮት ጽንሰ ሀሳቡና መሬት ላይ በህዝብ ውስጥ ያተረጓጎም ክህሎቱ ደግሞ በፍጹም ሁኔታ የተለዬ ነው። ርዕዮት ዓለሙን ተኖረበት፤ ነገርግን የጽንሰ ሃሳቡን ተግባራዊ ለማድረግ ዕድሉ በህጋዊነት – አጋጣሚ አላገኘም፤ ዘመኑም … የሆነ ሆኖ —-“የዛሬ 40 ዓመት ኢህአፓ ጎንደር ላይ ነበር – እነኝህን የምታዮዋቸው የተፈጥሮ ምሽጎች ነበሩ ደጀኖቹ፤ ኢዲዩም ጎንደር ላይ በዚኸው ነበር ዱር ቤቴ ያለው፤ ዬአርበኞች ግንባር ጥንስስም ጎንደር ላይ ነበር አህዱ ያለው፤ ከፋኝም ቢሆን /አንዱ የአርበኛ ክንፍ/ ነውና የጎንደርን ጫካዎች ነበር ልዩ ባዕቱ ያደረገው፤ ወያኔም የማጥቃት ዘመቻው ለስኬት ያበቃለት፤
በዛሬው ጹሑፌ የተንጠለጠሉ ዕሳቤዎችም እግረ መንገዴን ይኬድባቸውል – „ባዶዎች ናችሁ፤ በምንም ትኮፈሳላችሁ፤ ሥልጣን ቀረብን ብላችሁ ታሳድማላችሁ“ ይሉናል፤ ድሮ ድሮ በሀሜት በአሽሙር – ጎሸም ነበር። ዛሬ ግን አደባባይ እዬወጣ ነው። ምን ያለው ገመና ተገኝቶብናል? ለረጅም ጊዜ በመንግሥት ምሥረታ ታሪክ ውስጥ ለነበረ ማህበረሰብ ዬ/heredity/ ጉዳይ መሆኑን በአዎንታዊነት በጽሞና ቢታይ ለትውልዱ ጠቃሚ ነው። ሌላው ግን ባዶን ማን ፈልጎት ያውቅና? ምን – አጥተን? ምን እንዳለን – ምን እንደምንችል – ምን እንደምንፈልግ አቅማችን አሳምርን ስለምናውቅ የበታችነት ለሚያናውዛቸው፤ የመንደርተኝነት ስሜት ላለባቸው የሚፈልጉትን ሸልመን እኛ የ /cosmopolitan city/ መናህሪያ ልጆች ወደ – ሥራችን። በተለይ ዛሬ ብልህ አደራ አለብን! አደራ ማውጣት የበቃ ትውፊታችን ነውና ለዚያ መትጋት ግሎባላዊ ጥሪያችን ነው። በሌላ በኩልም ይህን ተግባራችን ብላችሁ የያዛችሁት አበክሬ ልገልጸው እምሻው ቁምነገር የነፃነት ናፍቆትን እዬጠቀመችሁትም አለመሆኑን ነው። አሉታዊ የፍላጎት ኃይልን እያባባላችሁም ነው። የዘመቻውን ተክለ ቁመና ስገመግመው – የተወላጆችን ልብ ለማሸፈትም – ይመስላል። ትግሉን የጠቀምን እዬመሰለን መንፈስ እዬበተን ነው። ለማንኛውም ትንሽ እሰቡ – ማይካችሁ – የነፃነት ራህባችን በእጅጉ መቅኖ ይውጣልና – እስታግሱት! አደብ ግዙ እንላለን፤ የነፃነት ትግላችን ዬሁሉንም ተሳትፎ በእኩልነት – በጥራት ይፈልጋል። ሁሉም እንደ ችሎታው ያደርግ ዘንድ መጋኛ አትሁኑ። ፓርቲዎች፤ ንቅናቄዎች ደንብና ህግ አላቸው። መንፈሱን ማዋህድ ያስፈልጋል። ማንበብ!
የሆነ ሆኖ ከምታብጠለጥሉት ማህጸን የበቀሉ ቤተኛ ማገዶዎችም ከእኛ ወዲያ ላሳር በምትሉት የትግል መሥመር የፊት ረድፈኞች ናቸው – አሉበት። ማተበ ቢስም መሆን አይገባም። እንዚህ ጡቶች ናቸው ቀደም ባለው ጊዜም ቢሆን ልጆቻችሁን፤ ወንድሞቻችሁን፤ እህቶቻችሁን፤ ትዳራችሁን ጠብቀው – ለአደራ ያበቁት። ለዛሬው የሚሊዮን አለኝታ – ያበቁት። የዛሬው ትሩፋት የትናንት የጎንደር ንጡርና ቅዱስ ውለታ ነው። ለተባው ቅርሳዊ ኢትዮጵያዊ ተሳትፏችን ሆነ ተስፋነታችን – አናፍርበትም። ወርቅ ለሰጠ ብርት ግን እንደ ማተበ ቢሱ ወያኔው – አይገባም። እግዚዬሩም ያያል – ቢያንስ እሱን ፍሩ። አንደበታችሁን ሰብስቡ – ተከወኑ እንላለን! ተውንም እንላለን! ቀደም ባለው ጊዜም ቢሆን እዛው ኤርትራ ድረስ ተሂዶ ተስፋውን ለማምከን – ተሴረ፤ በግልባጭ ካርቦን ከአዲሱ ጋር ደግሞ ለተሰወረ ደባ ቦታው በእሽቅድም – ተያዘ። በባለጊዜነት ሽፋንነት ብዙ ቡቃዬዎች – ደረቁ። ዛሬ ደግሞ ፈጣሪ ደግ ነውና ያ የተናቀ ቁምጣ ለበሽ ባለገር የተባለው ለብቁ አመራር – ታደል። በክፉ ቀን ጥቃትን ሳይቀበል አብሮነትን ከማንም በማስተዋል ቀድሞ ፈቀደ። ይታደሉታል እንጂ አይታገሉት የሚባለውም ለዚህ ነው። እነ የውስጥ አርበኞች ከእሳት እንደገባ ፕላስቲክ ኩፍፍትርትር – አላችሁ። ለዚህም ነው እንደተለመደው ሌላ ሴራ – የጠነሰሳችሁት። እንተዋወቃለን። የሆነ ሆኖ ከጥንትእስከ ዛሬ ሚስጢር ይቀዳል በዚህ – ባዕት። ጸጉራችሁ ቢቆምም ዕውነቱ ይኼው ነው። የትግራይ ትግርኝ እሿኽማ ህልም ቀድሞ የተረዳ ብልህነትም ነው። ስለሆነም ዛሬ በዚህ ዙሪያ የመጨረሻዬ ስለሆነ ተጋባቢ ዕይታዎችን ሁሉ ነው መልክ ማስያዝ እሻለሁ።
ክብሮቼ – የሀገሬ ልጆች አሁን ወደ ተነሳሁበት – ታዲያ ከላይ ያነሳኋቸው በተለያዬ ጊዜ የተፈጠሩ የነፃነት ፍለጋ መንፈሶች ዕውን የአማራውን ህዝብ ለመጨረስ ነበርን?! ነው ቁምነገሩ። አሁን የሰሙኑ ዳንኪራ ቅርንጫፉም ሆነ ቅጠሎቹም ረግፈው መለመላውን ቁሞ እንደምታዩት ልብ ልክ ነው። ኢህአፓ የመሸገው ጎንደር ላይ ለዛ ነበርን – ከቶ የአማርን ህዝብ ለማስደምሰስ ነበርን?! እንደገናስ የሱማሌ ወረራን ያጸደቀውና የወደደው „አትዋጉ¡“ እያለ የለፈፈው ዘመቻስ ፈቃድ አግኝቶ ቢሆን ዛሬ የአልሸባብ መጨፈሪያ ኢትዮጵያ አትሆንም ነበርን?! ሌላም የወርቅ እንክብል አለ – ብቸኛዋ በቅኝ ያልተገዛች አፍሪካዊት ሀገር ኢትዮጵያ ቀለማሙ የሺህ ዘመናት ታሪክ እንዲህ አንገቱን ቀና አድርጎ ይቀጥል ነበርን?! የቀስተዳመና ቅኔ በዓለሙ መሪ በልበ ሙሉነት ይዘረፍበት ነበርን?! በተጨማሪነት – „የብሄረሰቦች መብት እስከ መገንጠል“ መርኽ ግንባር ቀደሙ ተልዕኮስ የኢትዮጵያን አንድነትና ልዑላዊነት ክብር አስጠባቂ ነበርን?! ከዚህ የነጠረ ሃቅ ጋር ትውልዱ ማን ለዬትኛው ጎራ ተሰላፊ እንደሆነ – ይፍረደው። የ20ኛው ምዕተ ዓመት ጀግኖቻችን ሱማሌን አመድ ያደረገው ክብርንስ ማን ተቀብሮ እንዲቀር – አደረገው?! ወያኔ ሃርነት ትግሬ ብቻ – እእ፤ የቀድሞውን የኢትዮጵያ ሠራዊት፣ የአዬር ኃይላችን፤ የባህር ኃይላችን፤ የምድር ጦርችን ያን ሳይንስን ጥበብ የዋጠ ብቁ ታሪክ ቁጭ ብለው ከመስማት ሞታቸውን ይመርጣሉ እነ እንቶኔ። የአድዋው የጥቁሮች ገድል ዳግሚያ ትንሳኤን ትውፊት ማደመጥ – ያንገሸግሻቸዋል። ይመራቸዋል። ይኮሰኮሳቸዋል። በዚያ ጦርነት ገድላማ ጀግንነትን ያሳዩትን የአደራ አርበኞች ማዬት አይሹም። ኢትዮጵያ የገድል ሐገርነቷ ዛሬም – አይዋጥላቸውም። ዘመንን – ይዘላሉ። ታሪክን – ይጸዬፋሉ። ነገር ግን ዛሬም ከእኛ ወዲያ ላሳር ይላሉ። ኢትዮጵያ ስተወደድ ከነመከራዋ መሸከምን ይጠይቃል። በስተቀረ የተቃጠለ – ካርቦንነት ነው!
አሁንም ይህን የተቃጠለ አውሎ በዚህው መከወን ስላለብኝ ተያያዥ ነገሮችን ማንሳትን – ወደድኩኝ። አለ ሌላም – የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ከግንቦት ሰባት ጋር ሲዋህድ „የኢትዮጵያ ህዝብ“ የሚለው ቀርቷል ነው አንዱ። 40 ዓመት ሙሉ ትግል ላይ ያለው ዬኢህአፓ ሥያሜ „ኢትዮጵያ“ በዚህ ነው የሚጀምረው። ሥሙ ብቻውን የተነሳበትን ዓላማ አሳክቷል ወይ?! ከሆነስ ስለምን በጎጥ አስተዳደር 24 ዓመት ሙሉ ኢትዮጵያ ፍዳውን – ከፈለች?! የታገለው የቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት ስለነበር ሲወድቅስ እሱ ለመሆኑ የት ነበረ?! ሥያሜው ብቻውን ድል ከሆነ። እንደገናም አሜሪካን ሀገር /Republican – Democratic – Independent/ ጀርመን ከ(SPD በስተቀር ሌሎቹ (CDU – ‘90 GREEN – FDP)፤ ሲዊዝም ከ(SVP/UDC በስተቀር ሌሎቹ SPS /PSS/ – FDP/ PLR/ – CVP/ PDC/ PPD/) እያለ ይቀጥላል። ዬዬሐገሮች ፖለቲካል ፓርቲዎች ሰፊው እጁ ከሀገራቸው ሥያሜ አልተነሱም። ከፓርቲያቸው ፕሮግራም ዓላማ – ራዕይና ፕሮግራም – እንጂ። ስለሆነም ክርስትያን – ሶሻል – ሊብራል – ዩኒቲ – ዲሞክራት፤ ሪፓብሊክ፣ አረንጓዴ እዬተባሉ ነው የሚጠሩት። የፓርቲዎች የማሸነፍን አቅም ውጤታመነታቸው ስኬቱ የሚለካው ደግሞ ሥልጣኔያቸው፣ ያሰገኙት ትሩፋት፣ ተርፈው አዳሪነታቸውን በተግባር ደረጃ ያለንበት ህይወት ነው።
ሌላም ተጨማሪም አለኝ። የወቅቱ ፓለቲካ መጠለያ በቦሌ ጫካ እንደሆነ ነው – የሚደመጠው። ጉልሆቹ የሰላማዊ ትግል ፓርቲዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትም ቢሆኑ መድረክም ሆነ ሰማያዊም „ኢትዮጵያ“ ብሎ ሥያሜያቸው አይጀምርም። ስለለሆነም የህውከቱ አንጎል አሳማኝነት ከተጨበጠ ነገር (fact) ውጪ ነው። ለነገሩ ሰማያዊም ፓርቲም እኮ ግጥማቸው አይደለም /ውቃቤዬ አልወደደውም ሲሉ ነበር – ሲያንገሸግሻቸውም አስተውለናል/ የሆነ ሆኖ እያደቡ የሚነሱ አጀንዳዎቻቸው ለእውነት አምክንዮዊ ክስተትም ዕጣ ፈንታው – እስረኛ ነው፤ ተተኪ ሆነ ተከታይ የማፍራት ቁመናው መሃን – ይሆናል። ምክንያቱም የመከራከሪያው ክስተታዊ አምክንዮ /phenomenological/ ወይንም ዬማዕከላዊ መዋቅሩ ቁልፍ የሆነውን የመከራከሪያ ሥርዓት ወይንም ህገ ደንብ ስለሚተላለፈው። ስለሆነም የሂደቱ ግብዕት በፍልስፍና ሥያሜው /Phenomenology/ በእውነቱ ምድረ በዳ ነው። ተሸነፊም ነው። ሽንፈትን መቀበል ደግሞ ደካመነት – አይደለም። ከተጨበጠ ነገር /fact/ ለተፈጠረ ሰብዕና። የአዕምሮ ብቃትም መለኪያው መሸነፍና – ማሸነፍን እኩል የማስተናገድ አቅም ይመሰለኛል። ሃሳብ ለማቅናት ሸማች – ያስፈልጋል። የሸማቹ ፍላጎት የሚገዛው በሥነ – ህሊናው ካለው ጥሪት ጋር አቅርቦቱ የሚመጥን ሆኖ ሲያገኘው ብቻ ነው። በስተቀር ከገብያ ውጪ ይሆናል /inflation/ ማለት የመሸመት አቅሙ expired – ያደርጋል።
በዬጊዜው የሚነሱት ገራራ ነጥቦች ቁጭ ብሎ ለመከራከር ወይንም አንፃራዊው አመክንዮ በተደራጀ ሁኔታ ለማስተዳደር አቅም የላቸውም። ስለሆነም በዚህ ዙሪያ የሚነሱት አውሎዎች ለመሸነፍ በጣም የተጋለጡ የሚያደርጋቸው ዓብዩ ጉዳይ እንደ ዕድሜ ጠገብ ልምዱ፣ የታለፈበት የመስዋዕትነት ሂደት፣ የሙያ ብቃቱ ሆነ የቀለም ዕውቀቱ ደረጃ ከፍተኛነት ብቻውን ለሚቀርቡ የተቃውሞ ጭብጦች ወይንም ምክንያቶች /objection/ የሚመጥን አቅም ያላቸው ብልህ ቁምነገሮችን መሆን አለመቻላቸው ነው። በሁሉም አቅጣጫ ጦርነት ያስነሳሉ፤ ግን ፍልሚያውን ሊቋቋሙ የሚችል የሚመጥን አቻዊ አቅም ያጥራቸዋል – ስለሆነም የጦር አቀጣጣይ ሃሳቦች ትንፋሻቸው የተቆራረጠ ሆኖ የሚታዬውም ለዚህ ነው። የማጥቂያ ትልሞቹ አዘውትረው አቋራጭ መንገድ ስለሚሹ በዬጊዜው ተዋጊ ሃሳቦችን አዝለው እንደተንጠለጠሉ ጠውልገው መንገድ ላይ – ይቀራሉ። ለተቀናቃኝነት የሚቀርቡት አጀንዳዎች የፍላጎትን መሠረተ ሃሳብ ወይንም ፍሬ ነገር /substance/ እናጠቃዋለን ብለው የሚነሱበትን ሃሳብ አቅምና ተጨባጭ ህይወት በአግባቡ የመተርጎም መቅኖም በእጅጉ ያጠራቸውም – ናቸው። በአቻነት መሳ – ለመሳ የመቆም ጉልበት እንኳን የላቸውም እንኳንስ ማሸነፍ። ስለምን? ተዘውትሮ የሚታዬው በበቀሉ ወይንም በአቆጠቆጡ ሰብሎች የሚሰነዝሩት የማጥቂያ ዘመቻዎች ተጨባጭ ሁኔታን ሆነ የህዝብን ቅርባዊ ሙቅ ስሜት ያላደመጡ በመሆናቸው ቶሎ – ይበጠሳሉ። ለጦርነት የሚሰማሩት ሃሳቦች እንደ ተመክሮ ማሳው ሆነ እንደ ዕድሜ ጠገብነት ድርጁ መሆን ሲገባቸው ሽብርክና ተሰባሪ ሆነው – ይታያሉ።
እንዲህ ከውስጥነት ያልበቀሉ ተናካሽ ጀውጃዋ አጀንዳዎች አቅመ ቢሱች በመሆናቸው፤ ዬዕድሚያቸው ቁጥር ለሂሳብ እንጂ የተግባርን መዳፍ በማሰብል ልቅና በቀላሉ መረታት አለመቻላቸው የተሸናፊ ዕጣ እንዲቀበሉ – ያስገድዳቸዋል፤ አሸናፊው ተመክሮን ልምድን የዕውቀት ደረጃን ከአደገ ደረጃ የሚያደርስለት ዬተጨባጩ ሙቀታዊ ስሜትን በብልህነት ከማድመጥ ጋር ስለሚጋባ ብልጫ ያለው ባለሙሉ አቅም ሆኖ ያሸንፋል። ለዚህ ነው በዬወቅቱ ጅጉድጉድ ብለው ከአንዱ መረብ ወደ ሌላው በፍጥነት እንደ ፌንጣ የሚዘሉ ሃሳቦቹ እርጋታ ያነሳቸው፤ ክልፍልፍና ሸውሻዋና ተናዳፊ – የሚሆኑት። የመንፈስ አቅም ብልጫ ሆነ – የሥነ ልቦና የበላይነት ገብያ ተሂዶ – አይሸመትም። መሪና አሸናፊ ኃሳቡ ፈተናን የመታደግ ሂደቱ ችሎታን፣ ሙሉዑ ሥነ ምግባርን /አለመተላለፍን ደንበር አለመጣስን/ የብስለት ደረጃ ልቅና ዘላቂነትን፣ የምራቅ መዋጥ – መደርጀትን፣ ወቅትን በጥሞና የማድመጥና የመተርጎም ሥልጡንነትን እንዲሁም ችግርን ለመፍታት በአጅ ያለን አቅም በአግባቡም በመሳትዳደር እረግድ ሥልታዊ የሆነ ብልህ መብቃትን ይጠይቃል። /god handling problems/ እንግዲህ አቶ መልኬ መንግሥቴ መደባቸው የት ላይ እንደሆነ ዳኝነቱን – ለክብረቶቼ። ስለሆነም ዛሬ በምልሰት ጥቂት ተወራራሽ ታሪክ ቀመስ ነገሮችን ስለማነሳሳ ትእግስታችሁንም አብዝቼ – እሻለሁ። አመሰግናችኋለሁም።በቅድሚያ ግን እንዴት ሰነበቱ አቶ መልኬ መንግሥቴ ደህና ነዎት ወይ? ለክብርት ባለቤተዎት የከበረ ሰላምታ አቀርባለሁ። ልዩዬ ናቸውና እጅም – እነሳለሁ።
እኔ እንደ ሥርጉተ – ለአቶ መልኬ የተሰጠውን ተቀጥላ ክብር ሳዳምጥ በእውነት – አዘንኩኝ። „ክቡር“ ለማለትም ያልደፈርኩት እኒያ አዛውንት – አባት፤ ባለ ግራጫማ ፀጉር፤ ብዙ ነገር ያዩ – እንደ አባት አዳሩ የእሳቸው ያለሆነው „ክብር“ እንደ ቶፋ /እንስራ/ ሲደለዝላቸው፤ እንደ ቁሮ ከሰል ሲንጠለጠልላቸው የእኔ አይደለም ብለው ሊጸዬፉት ሲገባ አጋጠመኝ በማለት ደልደልና ኮራ ብለው በአዎንታዊነት በደስታ ስለተቀበሉት ነበር። ከዚህ ባሻገር ገዳዳ የሆነውን የሰብዕና ምስክርነትም ሲሰጡ ታዛቢውን ሰፊ አድማጭ ዘንግተውታል። ያልተገባ „ክብርን“ መቀበለዎት ብቻ ሳይሆን ያልተገባ „የሃቅ ጥነትም“ አዳምጨበታለሁ ቃለምልልሱን። ያልበቀለ ክብርን ተቀብሎ ያልተገባ ክብርን መስጠት ጂዋጂዊት ነው። ቢያንስ ሁላችንም በመንታዘበው ዕውነት ላይ ቀጥ ያለ አቋም ሊኖረወት አለመቻሉና የሄዱበት እጅግ የወረደ ከንቱ ውዳሴ ባለቤቱ እራሱ በውስጡ ደረጃዎትን እንዲይበት – ያደርገዋል። ያው ህሊና የሚባለው ከኖረ – ካልተነነ። በተረፈ በአርበኞች ግንባር ላይ የነበረዎት የተሳትፎ ደረጃ አርበኛ ባያሰኘዎትም አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ዬሚችለውን፤ የድርሻውን ለማድረግ ለወቅቱ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት መትጋት መልካም ነው። እኔ አርበኞችን በተገባ ሁኔታ ያግዙና ለአርበኛው ተግባር ቅርብም የነበሩ ከኮሎንቦስ – ኦሃዩ ወንድሞቼ መረጃውን ከማደምጠው በስተቀር፤ ቦቦታው ስላልነበርኩኝ፤ ይህን ዘልዬ እርእሴ ወደ ሆነው አብረን እላለሁ – በትህትና። ዕውን አቶ መልኬ መንግሥቴ የአርበኞች ግንባር መንፈስ መሥራች አባል ነበሩን? መልሱ ህዝብ ይዳኘው ዘንድ ትቼ ለመነሻ የሚሆኑ ነጥቦችን – አነሳሳለሁ።
መነሻ – የአርበኞች ግንባር መንፈስ አህጉራዊ ብቻ ሳይሆን ዓለምአቀፋዊም – ነው። መነሻውም ዬአብዛኞቹ ብሄራዊ – ነበር ማለት ይቻላል። ለዛሬው ዬአርበኞች ግንባር ጥንስስ ጎንደር ለታላቋ ትግራይ ትግርኝ ቅዠት ስትከለል አሻም ዬህወሓትን ማንፌስቶ ያሉት የጎንደር ልጆች ሃቁን ካወቁበት ዕለት ጀምሮ አፈንግጠው በመውጣት እራሳቸውን እንደ አባት አደሩ በሽምቅ ውጊያ አደራጅተው ትግል የጀመሩት በዘመነ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ሳይሆን፤ አስተውሉት ወገኖቼ – በወደቀው ብሄራዊ መንግሥት ወቅት በዘመን ደርግ ነበር። ከዚህም ባሻገር በወቅቱ ያላፈነግጡት – ዬአካባቢው ተወላጆችም ቢሆኑ፤ በነበረው የውይይት ክፍለ ጊዜ ሲታገሉት የነበረ – ሲሆን፤ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ለድል ሲበቃ ለእስር ተዳርገው ዛሬ ውጭ ሀገር የሚገኙ ወንድሞች አሉ። ስለሆነም – የፍሬ ነገሩን ልብ ለማግኘት ከቃሉ ፍቺ መነሳት አስፈላጊ – ይሆናል።
መሠረት …. ማለት ምን ማለት ነው? መሠረት ማለት መነሻ – መጀመሪያ – መጠንሰሻ – መወጠኛ፤ የጅምሩን ንድፍ ብቻ ሳይሆን የግቡንም አናት መንፈሱን ዬመሸከም ሙሉ አቅም ያለው የግንባታው አስኳል ማለት ይሆናል፤ ቃሉ በአውራነት በቤተ ሥምነት ሲራባ መሠረትነት – መነሻነት – መጀመሪያነት – መቅድምነት ማለት ሲሆን፤ የሐረጋማ እርባታው በጊዜ ሲታይ ደግሞ ሊመሠረት፤ እዬተመሠረተ – ሲመሠረት – ተመሠረተ – ተመስርቶ – ይሆናል። ዬሂደቱ እርባታ ቅኝት ደግሞ አመሠራረት – ምሥረታ – ተመሥራች — መሥራችነት – እያለ ይተማል። ስለዚህ „ምሥረታ“ እንደ አለ በቁሙ ሲተረጎም አዲስ በህሊና የተወጠነ ግኝተ – ዬሃሳብ ፍልስፍና መሬት ላይ ዕውን ሆኖ ሲታይ ይሆናል። ጸሐይ ያለዬው ወይንም ያልሞቀው፤ ቀድሞ በሌላ ሰው ያልታዬ የአመክንዮ ይዘታዊ ቀንበጥ ፍሬ – ነገር እንደ ማለት፤ ወይንም በሌላ ወገን ያልተጀመረ የመንፈስ አዲስ ውልደ፣ – ዕንቡጥ በኽር፣ የብቻ ጥሪት ሲሆን፤ ውጥኑ በአጭር ታጥቆ ለተወሰነ ዒላማ ወይንም ረጅምና ቋሚ ዓላማን ይዞ መርህ ነድፎ፤ አህዱነትን /ጀማሪነትን/ በአካልነት ሲሆኑበት ወይንም ሲገኙበት ማለት ነው። ከዚህም አለፍ ተደርጎ ሊታይ የሚችልበትም ሁኔታዎችም – ይኖራሉ። በይዘትና በቅርጽ ልዩነት እና አንድነትንም በዘርፉ ማዬት – ይቻላል። የሆነ ሆኖ በምንም መሥፈርት „መሥራችነት“ በውክልና ወይንም በትውስት ወይንም በአጃቢ ወይንም በደጋፊነት – ወይንም በተለጣፊነት ወይንም በተጨማሪነት – አይለካም። በአህዱነት ውስጥም ቢሆን በአምልኮ እንደ ድንጋይ ሐውልትነት ሳይሆን እራሱ ሰብዕናው፤ የአዲስ ሃሳብ ፈጣሪ አፍላቂ – ፈላስፋው ወይንም አስገኝው ኃይል በቀዳሚ ተዋናይነት ሆኖ ሲገኝበት ብቻ ነው። ከዚህ አንፃር ስለምን አቶ መልኬ መንግሥቴ ከአርበኞች መንፈስ ጋር ተያያዥነት ባላቸው እውነቶች፤ በቅርብም ሆነ በሩቅም ዝምድናቸው፤ እንዲሁም በእትብታዊ ሃዲድነት ከሰመሩት ብሄራዊ ተደሞዎች ጋር በመሥራችንት አባል ሊያደርጋቸው እንደማይችል፤ የተሰጣቸው ያልሆኑት ሥያሜ መሻገሪያው ሰባራ መሆኑን ጹሑፌ ያመለክትና፤ ፍርድና ዳኝነቱን ከወቅቱ ትኩስ የሚሊዮኖች ፍላጎትና ተስፋ ጋር ብዙኃኑ ይዳኘው ዘንድ በክፍትነት እተወዋለሁ …. ሸበላ – የመደማመጥ ጊዜ – በአክብሮት።
የዘመናች ዬአርበኝነት ብሄራዊነት፤ ዕትብታዊ ሃዲድ ምሥረታ፤ ይዘታዊ ውህድነት፤ በአኃቲ መሥመር – አካልነት።
- በታችና ላይ አርማጭሆ ቆላማ ቦታዎች በዛ ጀግና አርበኛ አበጀ በለው የጎበዝ አለቃነት ሌሎችንም አክሎ ትግሉ ሁሉንም መከራ ተቀብሎ – ሲቀጥል፤ አርበኛው በነበረው የኢትዮጵያ መንግሥትም ደስተኛ ስላልነበረ ግራ – ቀኙን ነበር የሚታገለው። ማለትም በወቅቱ የነበረውን የኢትዮጵያ መንግሥትና የጫካውን የወያኔ ሃርነት ትግራይን። አርበኛው ዱር ቤቴ በማለት በደፈጣ ውጊያ በጥምር ሁለቱንም ይፋለም ነበር። ይህ መረጃ የደረሳቸው የወቅቱ የስሜን ጎንደር ክ/ሀገር አስተዳዳሪ የተከበሩ አቶ ሽፈራው እንቁባህሬ እና የተከበሩ ጓድ ገዛህኝ ወርቄ የፓርቲው አንደኛ ጸሐፊ ከትግራይ መለቀቅ ጋር የወያኔ ሃርነት ትግራይ ይዞታውን እያሰፋ ሲመጣ በሀገር ሽማግሌ ተደራድረው አርበኛው የማጥቃትና የመከላከል ትግሉን እንዲቀላቀል ጥሪ – አቀረቡለት። ከዛ በኋላ ጥሪውን ተቀብሎ ሙሉ የትጥቅና የስንቅ ድጋፍ ተደርጎለት ዱር ቤቴነቱን – ቀጠለበት። እኔ በተፈጥሮዬ ከሥራ ሰዓቴ ቀድሜ ነበር ቢሮ እምገባው። ሀገሬ ሥራ ነውና። አንድ ቀን ጥዋት ወደ ቢሮዬ ስገባ ያዬኋቸው ጸጉረ ልውጦች መልካቸው – ቁመናቸው – የትጥቃቸውና የመንፈሳቸው ብቃትና ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን ጽዳታቸው፤ ዬቆፋጣናነታቸው ቅልጥፍና ወዙና – ጠረኑ እስከ ዛሬ ድረስ ከዓይኔ – አይጠፋም። የበረኃ ሰው ሆነው ግን የጀግንነት ዘመናት አገናኙ ተብለው የተፈጠሩ የአደራ ልዩ ውሎች – ድልድዮች ነበሩና። በተመስጦ ቀጥ ብዬ ቆሜ ሰላምታ ሰጥቻቸው በማስተዋል – ቃኘኋቸው። እኔ ጀግና እወዳለሁ። እነኛ ጸጉረ ልውጦች – እንግዳ ማረፊያው ወንበሮች ላይ ቆርጠጥ – ቆርጠጥ ብለው በመደዳ ተቀምጠው – ነበር። የሥራ ሰዓት ሲደርስ መረጃ ክፍሉን ጠይቄ – ዝርዝር ታሪኩን – ተራዳሁ። የእኔ የተግባር መስክ ሲቦክስ ማህበራትን ማደራጀት ስለነበረ ከጉዳዩ ጋር የተያያዘ አቅም ወይንም ኃላፊነት – አልነበረኝም። ደረጃዬም – አይፈቅድም።
እንዲህም ሆነ – … ትግሉ እዬከረረ ሲሄድ ትግራይ የነበረው 604ኛ ኮር ወደ ጎንደር ተዛውሮ – ነበር። እንደገናም 7ኛ ክ/ጦር አዘዞ ላይ 603ኛ ክ/ጦሮች ጨዋሰፈር ጎንደር ከተማ ላይ ነበሩ። በማዕከላዊ ወታደራዊ ትእዛዝ ጎንደር የነበረው ሠራዊት ጥርግርግ ብሎ ወደ ጎጃም እንዲሄዱ ተደረገና ጎንደር ብቻዋን – ቀረች። እንደሚመስለኝ ተለዋጭ ሠራዊት ይመጣል በሚል ነበር እንጂ፤ አመራሩ እሺ ብሎ የሚቀበለው ውሳኔ አልነበረም እንዲሁ ሳስበው። ምክንያቱም እኛም በከፋ ቀውጢ ሁኔታ ላይ ነበርን እና። ደባው ሳይታወቅበት ሹልክ ብሎ ገብቶ ሰላማዊ ሽግግሩን ሸውዶ ከወነ። ብቻ በወሳኝ ወቅት የድል ግልበት – ስለነበር የታሪክ ትውከት – ልበለው። ደንቀዝ ላይ በከባድ መሳሪያ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ሠራዊት እንደ ጉድ ይለቀው የነበረው ድብዳባ ባለማቋረጥ አካባቢውን ሰላም – አሳጣው። በዛን ጊዜ አንዲት ቀን ነፃ ነበረች። ጎንደር ጭስ – ለበሰች። ስታሳዝን።
ከዬት የመጣ አቧራ እንደሆንም አላውቅም፤ በአውሎ ታጅቦ ሰሞናቱን በጭስ አባልነት እርሰ ከተማዋ ጉም ለበሰች፤ ከጢሱ ጋር ቀናቱ ድብዛቸው የጠፋ ጭስ ለበስ ድንብስ ነበሩ። ሰው ለሰው መንገድ ላይ ይተላለፍ ነበር። ቀኑ አስቀድሞ – ጨለመ። እንደ ጨለመም ይኼው የጎንደር ሱዳን አዋሳኝነት፤ ዬጎንደር ከከተማነት „ከሜተሮፖሊታን ከተሞች ዝርዝር ህዉሓት መሰረዙን“ ተያያዥ የውጭ ኢንቬስተሮች እድገት መሰላሎች ሁሉ መምከናቸውንም እያዳመጥ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ዓይኑ የከፈተለት ሁሉ መዶሻውን ያው ጎንደር ላይ። አዬ! ነገረ – ጎንደር! ብቻ በዛ ወቅት ለዳኮታ ሰፊ ቦታ ያስፈልጋል ተብሎ እዛው አቧራ ተለብሶ እዬተዋለ እዬታደረ የአዬር ማረፊያ ነዋሪዎች ስንት ደሃ ከኑሮው የተፈናቀለበት አውሮፕላን ማረፊያ መሰናዶም ሳይሰረባት ባክኖ ውሃ በልቶት – ቀረ። ለነዋሪዎቹ ካሳም – አልተሰጣቸውም። አንዲት ቀን ሠራዊት በዳኮታ ማሳረፍ የሚቻልበት አጋጣሚም ውሃ ብልቷት – ቀረ። የራዲዮ መልዕክቱ „ለአጋሰሱ ስንቅ ልከናል የሚል“ እንደ ነበር ሹክ አሉኝ። ብቻ ተስፋው ካለ ይግባኝ – ሞተ። ለአገሰሱ ተላከ የተባለውም ስንቁም ቢሆን አቀባበል ለወያኔ ሃርነት ትግራይ ሠራዊት እንዳይቸገር ተግባሩን ቀለል ለማድረግ ታስቦ ነበር። የመንግሥት ሠራዊቱ ቀድሞ – መሸኘቱን ቀደም ብዬ አጫውቻችኋለሁ። ነገር ግን ጎንደርን አናስደፍርም ያሉ እነዛ ቀደምት የሽምቅ አርበኞች ከቦታቸው ተነስተው ወደ ጎንደር ገሰገሱ፤ በሶስት እጥፍ ተዘጋጅቶ በነበረው የውጊያ መስመር ጉድብ ውስጥ ሆነው 18 ቀን ሙሉ ከሀገሬው ጋር አቧራ ለብሰው ውጊያውን አስከ መጨረሻው ድረስ – ተጋፈጡት።
ሌላው ቀርቶ እኔ በአለፋ ጣቁሳ በር ከነበረው ቡድን ጋር ስለነበርኩ፤ ክፍትም ነፃ ቦታ ደንቢያ ላይ ይሁን በአዋሳኙ ተንከል ላይ አዬር ወለድ የማሰረፍ ሰፊ ዕድል – ነበር። ቦታው ምቹ ለጥ ያለ ሜዳማ – ነበር። በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ከእግረኛው ባላነሰ ጀርመንን ከናዚ ያወጣው ታላቅ ኃይል አዬር ወለድ ነበር ከታሪክ – እንዳነበብኩት። እኛ ላይ ግን ያ የነፍስ ደራሹ ኃይል ዕቀባ – ተደረገበት። የሆነ ሆኖ ከተማ ላይ ጦርነቱን ማካሄድ ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን፤ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እንዳሉትም ጎንደር በውጭ ከሚታዩት ሃብታት ይልቅ ዬማይታዩት የቅርስ ዲታነቷን ያሰተዋሉት መሪ ቅኑ ጓድ ገዛህኝ ወርቄ ስልታዊ ማፈግፈግ አድርገው ወደ ላይ አርማጭሆ ኮማንድ ፓስቱን – አዛወሩት። እንደ ጓድነታቸው ዕሳቤ ሴራው ማዕከላዊ ድጋፍ መኖሩ የተረዱት – አልመሰለኝም፤ እንመለሳለን በሚል ተስፋ ነበር ወደ አርማጭሆ – የሄዱት። እርግጥ ከዛ በፊት ኤሊኮፍተር ተልኮላቸው ከጎንደር ህዝብ ጋር ነው እምሞተው ብለው ስለቀሩ እንዳሉት ሆነው – ተገኙ። ለመጨረሻ ሳላያቸው ሰንብቼ ኮሪደር ላይ – አገኘኋቸው። እንደ ተለመደው በዛ ትሁት መምህር ፊታቸው ከመንገዳቸው ገታ ብለው ቆም ብለው – ጠበቁኝ። በጥልቀትም – አዩኝ። ያ የሚያበራ ግንባራቸው ተለውጧል፤ አንድም ቀን ሱሪ ለብሼ ለዛውም በሙሉ ትጥቅ አይተውኝ ስለማያውቁ በተመስጦ – ቃኙኝ፤ እኔ ብቻ ነበርኩኝ – ሴት። „ጥሩ ነው አይዞሽ!“ አሉኝ – በራዲዮን ጩኽት ብዛት ጉሮሯቸው ዝግት ብሎ – ነበር። የሆነ ሆኖ ከእሳቸው ዕልፈት በኋላ አርበኛው እራሱን እንደገና አደራጅቶ ትግሉን በባዕቱ – ቀጠለ።
የጓድ ገዛህኝ ወርቄ ዕልፈት ተመሳሳይ ግድፈት እንዳይፈጸም ትንሽ ልበል። መዘግዬት ጸጸት ተከል ነውና። እጅግ ወቅታዊና በጣም ተፈላጊም ስለሆነ። እኔ በቁስቋም በር ነበር ብቻዬን – የወጣሁት። እኔ የወጣሁበት መሥመር በሰማይም በምድርም ዬተቃጠለ የጦርነት ቀጠና ነበር። እነሱ ደግሞ አንፃራዊ ሰላም በነበረው በወገራ በር ሆኖ ተገንጥሎ ወደ አርምጭሆ በሚወስደው መንገድ ነበር፤ ቀን ግዳጅ ላይ አብረን እንሰማራለን በዬቡድን መሪዎቻን – ሌሊት ግን ከፍተኛ የመንግሥት፣ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አካላት እንዲሁም የህዝብ ድርጅት መሪዎች ብቻ የሚያድሩት ቦታ በተጠናከረ ጥበቃ በተለዬ ሁኔታ ነበር። ቦታውን እኔ እራሴ አላውቀውም። አውሮፕላን ማረፊያው አዘዞ በወያኔ ሃርነት ትግራይ ቆጥጥር ሥር ሲውል እንዳሉ በጋራ ነበር የተጓዙት። ስለዚህ እኔ በተመቸኝ ቦታ ወጥቼ መሬት ከያዝኩ በኋላ ወደ እነሱ መቀላቀል ነበር – ዓላማዬ። የእኔ ትልቁ ጸጋዬ መዋጋት ሳይሆን ከዬት እንደመጣ አላውቅም አስቸጋሪ በሆነ ጉዳይ ወይንም አጀንዳ ተልኬ ግን ገበሬዎችን በፍቅር አሳምኜ የመምጣት የተለዬ አቅምና ሥጦታ ነበረኝ ማህተም ነው ማለት እችላሁ። ለዚህም ነበር ጫካ የወጣሁት፤ እናም መልዕክተኞችን – ላኩኙ። ዘርፉን በባለቤትነት ለመያዝ የበዛ ፍላጎት – ነበረኝ። አለቆቼም ይህነን ጸጋዬን ስለሚያውቁ፤ ስለሚያከበሩትም አይነፍጉኝም – ነበር። መልዕክተኞች ሲመለሱ መርዶ ይዘውልኝ – መጡ። ጓድ ገዛህኝ ወርቄ እስከ ልጃቸው ማለፈቸውን። ድርብ ሃዘን ነበር ለእኔ። የተግባር ሰው ነበሩ። የሌሎች ልጆች በቦሌ ለከፍተኛ ትምህህርት የጓድነታቸው ግን በብሄራዊ ውትድርና በኋላም ከአባቱ ጋር ተሳዋ። በምንም ተልካሻ ግለኝነት ሆነ ትዕቢትም የማይጠረጠሩ ነበሩ። የሆነ ሆኖ ምክንያቱ ምን እንደሆን ገበሬዎቼን ስጠይቃቸው የነገሩኝ ጀግና አበጀ በለው ትግሉን ከተቀላቀለ በኋላ በተሳሳተ መረጃ በጀርባ ሊያስወጋ ነው በሚል እርምጃ እንዲወሰድበት በመደረጉ ምክንያት መሆኑን ነገሩኝ። ይህም እጅግ በጣም አሳዘነኝ። መልዕክተኞች እንደነገሩኝ ጎንደር ላይ በጀግንነት አብሮ ሲዋጋ የነበረው አርበኛ ከእሳቸው ጎን የነበረ ሲሆን፤ የሀገሬው ህዝብ ጉዳዩን ቀድሞ መረጃው ደርሶት – ቀን ይጠብቅ ስለነበር፤ መተላለፊያ በሩን ዘግቶ በተደራጀ ሁኔታ ገዢ መሬቱን ይዞ አናሳልፍም ብሎ ተዋግቶ እንደገደላቸው ነበር የሰማሁት።
ለዚህ ነው ብዙ ሰዎች በጎንደር ላይ ያነጣጠረ የማያውቁትን ሥነ ልቦና ውስጥ ሲዳፈሩት ሳይ አልፎ አልፎ አንዳንድ ነገሮችን – እምጠቋቁመው። በተከታታይም የጻፍኳቸው ጹሑፎች ነበሩ „ጎንደር ከክፍል አንድ እስከ አራት“ ይህ ታላቅ ተቋም ነው ለዬትኛውም ዘመን። የአካባቢው ህዝብ አንቴናው ከዘመን አመጣሹ ኔት በላይ ሆኖ የኖረ ነው። አሁንም በአርበኛው አያያዝ ስምሪት ድልድል ላይ አርበኛውን የማይመቹ ነገሮችን ላይ የተደረጃ የህሊና መሰናዶ – ያስፈልገዋል። ሞትን የፈቀደው አርበኛው ቢቀበለው እንኳን የአካባቢውን ሥነ – ልቦና የሚገዙ የሃቅ መንገዶች አትኩሮትና ክብር ሊሰጣቸው ይጋበል – እላለሁ። በተለይ የአካባቢው ሰው በሥም በሚያውቃቸው መሪዎቹ አርበኞቹ ላይ ነቁጥ ናት የምትባለው ጉድፍ ግድፈት ግዙፍ ችግር – ትወልዳለች። ምክንያቱን አሁንም በዚህ ዙሪያ ጥንቃቄ ዬሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ሊኖሩ ይችላሉ። በወቅቱ የነበሩ ያን ጊዜ ዘመቻውን የተጋሩ እንዳሉ – አውቃለሁ። ነገር ግን ለደህንነታቸው ስል ሥማቸውን መስጠት ግን – አልችልም።
- እኔ አብርሃም ነው የምለው በክርስትና ሥሙ አሁን ያለውን አቋሙን ስለማላውቅ፤ እኔ በምጠራው ሥም ይሆናል መረጃውን – እምሰጣችሁ። አብርሃም እና እኔ ለዬካቲት 66 ፓለቲካ ኢንስቲቲዩት የመግቢያ ፈታና ለመውሰድ ከታጩት ውስጥ ነበርን። ጎጃም ባህርዳር ላይ የመግብያ ፈተናው ይሰጥ ስለነበር አብረን – ተጓዝን። ፈተናው ቅይጥ aptitude test ዓይነት – ነበር። ብዙም ከባድ ባይባልም ቀላል – አልነበረም። በውጤቱ አብርሃም አልፎ እኔ እንደወደቅኩኝ – ተነገረኝ። ከልጅነቴ ጀምሮ ህልሜ በሀገር ውስጥ መማር እና እዬሩሳሌምን ማዬት ነበር። የሆነ ሆኖ እኔ ከፍቶኝ አሱ በወቅቱ ደስ ብሎት አብረን – ተመለስን። አብርሃምን ብዙም እምቀርበው – አልነበረም። እርግጥ ለተለያዬ ሁኔታ ወደ ማህል ሀገር ሲሄድ ከተለያዩ ክ/ሀገራት የሚያገኙት ጓዶቻችን ሲተዋወቃቸው መጀመሪያ የሚጠይቁት እኔን በመሆኑ፤ ይህ ነገርም ሁልጊዜ ስለሚገጥመው እኔ የማልሰጠውን እሱ አብዝቶ ያከብረኛና – የታደልሽም ይለኝ ነበር። የሆነ ሆኖ ስለማልቀርበው ፈተናውን አልፎ መሄዱ እንደ ሌሎቹ ውስጤን ባዶ አላደረገውም – ነበር። እኔ ከግብርና ሚ/ር ሠራተኝነቴ ነው በጥዋቱ ኢሠፓ ቀለብ – ያደረገኝ። የመስክ ሠራተኛ በመሆኔ ጓደኞቼ በሙሉ ወንዶች – ነበሩ። ፓርቲው ውስጥም funktionary ስሆንም ያው ወደ ቀልቦቼ ነበር የታደምከት። ነገር ግን አብርሃም – አልነበረም። የሆነ ሆኖ አብርሃም የካቲት 66 ኢንስቲቱዩት ሲመረቅ ጎጃም ውስጥ – ተመደበ። ጭንቅ ሰዓት ነበር። ለትምህርት መላኩም ሆነ የተመደበበት ኃላፊነት – አላረካውም። ኩርፊያ – ነገር። እንዲያውም ሁላችንም ከተሰደድን በኋላ ሲነግረኝ አንቺ ወሳኝና ተፈላጊ ብርቅም ስለሆንሽ እኔ ደግሞ ስለማልፈለግ ለወቅቱ ተገፋሁ – ብሎኛል። ይህ ይመስለኛል የወያኔ ሃርነት ትግራይ መጣሁ መጣሁ ይል በነበረበት ወቅት መደበኛ ሠራተኛ ሆኖ በውስጥ የአርበኛ አንጃ ነገር – ያስፈጠረው።
አጋጣሚው ደግሞ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ሠራዊት ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር የኢትዮጵያን ሰንድቅ ዓላማ የእግሩ ገንባሌና ስንቅ መቋጠሪያ ከረጢት አድርጎ /በዓይኔ ያዬሁት/ ይንቀሳቀስ የነበረበት ጊዜ ነበር። ወያኔ ሃርነት ትግራይ ተሳካለትና መላ ኢትዮጵያን – ተቆጣጠረ። በዚህን ጊዜ አብርሃም አዲስ አባባ ውስጥ ሆኖ በጎጃምና በሽዋ ጫካዎች የአርበኝነት ትግል – ጀመረ፤ በኋላም ወደ አሳደገው ጫካ ወደ ጎንደር አመራ። አዲስ አበባ ውስጥ እያለ የትውልዱ ዓራት ዓይናማ የቤተ ክርስትያን ሊቃውንት አባትን በህወሓት የተገለሉ /አሁን በህይወት የሉም – ነፍስ ይማር/ የትግሉ አካል እንዲሆኑ መጠዬቁን፤ ግን አዎንታዊ ምላሽ እንዳለገኘ፤ ከአዲስ አባባ ከተማ ሳይቀር መሳሪያዎችን በድፈረት በመኪና ወደ ትጥቅ ትግሉ ያጓጉዝ እንደነበር እራሱ በአንደበቱ – ነግሮኛል። ከዛ የወያኔ ሃርነት ትግራይ መረጋጋት ሲጀመር ተነቃበትና በጋዜጣ በራዲዮን መፈለግ – ተጀመረ። እኔ ሥራ ዓለም እያለን „ላንቁሶ – ሞልፋጣው“ የምለው አብርሃም የሽዋና የጎጃምን ጀግኖችን ይዞ ጫካ ለጫካ በአርበኝነት ትግሉን – ቀጠለ። በመጨረሻም ሱዳን ውስጥ እግሩ ችግር – ገጠመው። የተባበሩት መንግሥታት የሰደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን በቂ ዕውቅና ሰጥቶት በጥሩ ሁኔታ ሱዳን ላይ ካቆዬው በኋላ፤ ለህክምና ውጪ ሀገር ተለከ። ከዛ በኋለ ሲድን ኮማንድ ፓስቱን ኡጋንዳ አድርጎ የአርበኝነት ትግሉን – ቀጠለ። ጀርመን እንዲሁም ይመስለኛል ኖርወይ ተጨማሪ አስኳላት – ነበሩት። እደገናም ከጋንቤላ የነፃነት ትግሉ አርበኞች ጋርም የሰመረ ግንኙነት እንደበረው አውቃለሁ – ፍቅሩ አክብሮቱ ልዩም ነበር። በስሜንና የደቡብ ሱዳን ማህል ላይ በነበረው የነፃነት ትግልም ልዩ ተመስጦ ነበረው። ምልከታው መንደር ላይ የቆመ አልነበረም፤ ኢትዮ- አፍሪካዊነትን / pan africanism/ አብዝቼ አይቸበታለሁ። ዓይነታ ሥነ ምግባሩ እንደ አርበኛ ድርጅት መሪነቱ ሌሎችን ድርጅቶች ሆነ መሪዎችን ሲዘልፍ ሰምቼው – አላውቅም። ሲያደንቅ ሲያከብር እንጂ። እሱ ዬትጥቅ ትግል እያለ ሰላማዊ ትግልን በሚገርም ሁኔታ ያከብር ነበር። ለጠንካራ ሴቶች ያለው ከበረቴም ዝቀሽ ነው። ለሴቶች የእኩልነት መንፈስ ያለው አመለካከት ቃላት – አይገልጸውም። ግን ዕይታዬን አልነግረውም – ነበር። አድንቄውም – አላውቅም። ይልቁንም ተረብ እያበዛሁ ነበር – እማጫውተው – ውስጡኑም እምጎረጎረው። ውጪ ሁለታችንም ከወጣን በኋላ ከልቤ የገቡ እነዚህን እመሳሳላቸውን ወርቅ ብቃቶችን እነሆ ከድኜ ያቆዬኋቸውን ዛሬ ለነፃነት ትግላችን መምህር ይሆኑ ዘንድ አደባባይ እንዲውሉ – ፈቀድኩኝ። ስለዚህ የእሱም በአርበኞች መንፈስ ምሥረታ ታሪካዊ ዘርፍ የሚካተት – ነው። ጀምሮት የነበረውን ትግሉን የት ደረጃ እንዳደረሰው አላውቅም። … አሁን መረጃ የለኝምና።
….. አልፎ አልፎ ጹሑፎችን ኢትዮ ሚዲያ ላይ – አነባለሁ። ትንሽ ሊብራል የመሆን መንፈስ – አይቸባቸዋለሁ። ምክንያቱም ጹሑፎቹ ድፍረት የበዛባቸው – ከረረ ያለ ጸረ ወኔያዊ ጠረናቸው ሆነ ትችቱ እጅግ ጉልበታም እንደነበሩ – ስለማውቅ። ይህም ምክንያታዊ መሆኑ – ይገባኛል። ታሞ ውጪ ሐገር እንዲታከም ሲላክ፤ ወያኔ የዋዛ፤ በስቃዩ ውስጥ መከራውን በመጋራት በቅርብ እረዳትና ተንከባካቢው የወያኔ ሃርነት ትግራይ እጅ ከእሱ ቀድሞ ነበረበት። እነሱ – ያውቁበታል፤ ጠንከራ መንፈስን የረገበ አልጋ ማድረግ። እርግጥ በልጅነት ያው በተሰጠው ቁመና መዝናናት እጅግ አብዝቶ ይወድ ስለነበር ከእኔ እጅግ የባዛ ዬቁጥብነት ባህሪ አንፃር ዬእሱ መንፈስ ቅርቤም ግጥሜም በፍጹም – አልነበረም። … እኔ ብቻ ሳልሆን የእኛ ጉርፕም – ጭምር ። ያን ጊዜ ቲማችን ተደማጭ – በቂ ተቀባይነት የነበረው፤ ሥልጡንና ትኩስ ነበር። ወጣትነት የማትገኝ የአቅም – ሸጋነት፤ ታዲያንላችሁ ከኮበሌዎቹ ጋር በአባልነት የተመዘገብኩት ሴት ግን እኔ ብቻ ነበርኩኝ – ስለዚህም ብርቅ ነበርኩኝ። ሳቄ የሚናፈቅ – ቀልዴም የሚወደድ – …. ትጋቴ የሚደነቅ … ደከመኝ አልነበረም በእኔ ቤት። በበላዮቼ አመራሮች፣ ባቻዎቼ፣ በምመራቸው የሲቢክስ ማህበራት፤ በተለያዩ አጋጣሚዎች ያገኘኋቸው ታላላቅ ጓዶቼና መሪዎቼ እኔን በሚመለከት ተመሳሳይ ዕድምታ ነበራቸው። ሥርጉተ ማለት በልብ ውስጥ የምትቆዬ ጭራሽም የማትረሳ መሆኗን በህይወት ያሉት – ዛሬም ይመስክራሉ። የተሰጠኝን ምስክርነት ጥበቃዬ ከውስጥ ነበርና። በተዘርክረክ ቦታ ሥርጉተ ዝር ብላ – አታውቀም። ወጣትነቷንም ጭራሽ አስተውሳው አታውቅም፤ በሴትነት /በፆታ/ አቅሜም በቂ አቅም የነበረው ሙሉ እገዛ – ተደርጎልኛል። ያለኝን ጸጋ ሁሉ አበረክት ዘንድ በሮቹ ቧ ብለው የተከፈቱ ነበሩ። የደረጃ እድገቴም እጅግ ፈጣን ነበር። … እንጃ ከዚህ በኋላ ማግኘት አይደለም በህልሜም ያን መሰል የወል ፍቅር፤ ፈጽሞ የማይጠገብ ትስስር የትም ቦታ ማግኘት – አልቻልኩም። ጥንቁቅ የሆነ ግን የበዛ ማህበራዊነት ከግጥሞቼ ጋር – ነበረኝ። አሁን ግን ቁልፍ ነው። ሰላዩ – በዛ።
የሆነ ሆኖ አብርሃም ሌላም ልዩ ድንቅ ጥናካሬ እንዳለው – ታዝቢያለሁ። ከስደትና ከአርበኝነት ውሎ በኋላ — በውጪ ሀገር
- እነዛ አዲስ አበባ ላይ እሱን ሆነ ቤተሰቦቹን እንደ እናት እቅፍ አድርገው ሸሽገው የያዙለትን ባለ ኪዳን ቤተሰቦች ልጃቸውን ውጭ ሀገር በማምጣት እንደ ልጁ አድርጎ እጅግ በሚገርም ፍቅር አቆላምጦ – አሳድጓታል።
- ሌላም ቤተስብ እንዲሁ በዛ ጭንቅ ቀን የተገኙለትን እረዳት ያልነበራቸውን፤ ለቤተሰቡ አጋዥ ይሆኑ ዘንድ ከተለያዩ ቤተሰቦች ሁለት ወንድ ልጆችን፤ ልጆቼ ብሎ ውጭ ሀገር እንዲኖሩ በማደረግ ከቁም ነገር – አድርሷል።
- በተንቀሳቀሰባቸው የገጠር የሽዋ ትናንሽ ከተሞች የረዱትን በፍጹም – አረሳም፤ የፈረሰና ጥገና የሚያስፈልጋቸውን ቤታቸውን – ሠርቷል፤ የታመሙትን – አስታሟል፤ አራሶችን ሽልንጓን እዬለከ – አርሷል፤ እረዳት ያጡትን በተከታታይነት – ረድቷል፤
- እሱ ካለበት ከተማ በጋራ ሰብሰብ ብለው ለጉብኝት የሚሄዱ ኢትዮጵያዊ ወገኖችን በኃላፊነት ስሜት – ያስተናግዳል። ልዩ መስተንግዶም – ያዘጋጃል። ባህልና ትውፊትን በባለቤትነት መፍቀድ ለዛውም ስደት ላይ ተሁኖ ቤት ለእንግዳ ማለት ድንቅ ተግባር ነውና ከምጠብቀው በላይ መልካም ነገር – ፈጽሟል። አድናቆቴ በአክብሮት ይድረስህ – አብርሃም፤
- ኢትዮጵያዊ ወጣት ሴቶች በሞዴልነት ተሳትፎ ሲያደርጉ ግልጥልጥ ብለው ካዬ እጅግ ነው የሚበሳጨው፤ ባህሌ – ትውፊቴ – ታሪኬ፤ ተዛባ የሚል ህመማዊ ስሜት – አይቸበታለሁ። እንኳንስ ሰውነት መጋለጥ አርቲፈሻል ጸጉር በምታደርግ ሴት ይናደዳል። ተፈጥሮን የጣሰ ውበት – ይለዋል። በዚህም እኛነትን በኃላፊነት የመወሰድ ተቆርቋሪነት መሆኑን አስተውዬበታለሁ፤
- እጅግ እማከብርለት እማደንቅለትም ሸበላ ተግባር ደግሞ እሱ በሚኖርበት ከተማ፤ ወጣት ኢትዮጵውያን በት/ቤት በክብር ማዕረግ ሲመረቁ የተለዬ ዝግጅት በማደረግ አድናቆቱን የሚገልጽበት ሥርዓቱ ልቤን እና መንፈሴን አብዝቶ – ይማርከዋል። ለዚህም ነው ግድፈት ግድፈት የሚያሰኛቸውን የአቅም ድሃ ያልሆኑ ወንድሞቼን ብዙ ክፍት ቦታዎች አሉ፤ ቀዳዳችን ብዙ ነው፤ ያልታዩና ያልደረስንባቸውን ቦታዎች ስላሉን ህሊናችሁን ወደዛ ብታሰማሩ በማለት ጠቋሚ ሃሳብ – የማቀርበው።
- ሌላው ሰው የመርዳት አቅሙና ፍላጎቱ ላቅ ያለ ነው። ኬኒያ ላይ ለሞተ ጓዳችን የትዳር አጋሩም ማለፏን ሲሰማ ልጆቹን ወደ ውጪ ለማውጣት ሲያሰተባብር እንደነበረ – አውቃለሁ። ከዚህም ባለፈ አንድ የተዋህዶ አባት እዚህ ሲዊዘርላንድ ውስጥ ከማህበረ ምዕመናን ጋር የበዛ መግባባት የነበራቸው፤ የተግባርም ት/ቤት የነበሩ ነበሩ። እና እሳቸው የሲዊዝ የስደተኛ ቢሮ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ሲወስንባቸው – አማከርኩት፤ የመጡበትን አካባቢ ሳይጠይቀኝ በሚኖርበት ሀገር ካህን የሚፈልጉ ወገኖችን ፈልጎ ካገኘ በኋላ፤ እስፓንሰር ለመሆን ፈቅዶ አግኝቶ በስልክ ሲያነጋግራቸው „ስደት በቃኝ። ከእኔ ይልቅ ግብጽ ውስጥ በእንግልት ያሉ አባት አሉና እርሳቸውን እርዳልኝ አሉት።“ ከዚህ ላይ አንድ ነገር መስታወስ – እሻለሁ። እሳቸው ወደ አገኘላቸው ቦታ ቢፈቅዱ ኖሮ፤ እሱም አብሮ ሽፍት ማደረግ እንደሚችል ነበር – የነገረኝ። ብቸኝነት አባታቸን ሊሰማቸው አይገባም ባይ ነበረ። ከዛም በኋላ ግብጽ ላይ ከነበሩት አባት ጋር ተገናኝቷል – በምን ሁኔታ ጉዳዩ እንዳለቀ – አላውቅም። ሌላው ግን የእሱን አቅም ቀጣይነት ምን በላው ለሚለው፤ ሁለት ነገር ይመስለኛል። አንደኛው – ለአርበኝነት ውሎ የኮማንድ ፖስቱ ማዕከል ከመሬቱ መራቅ ጋና አክራ መሆኑ ተጽዕኖው ቀላል – አልነበረም። በራሱ መንገድና ገቢም ነበር የሚንቀሳቀሰው፤ ለዚህም ነው ብዙ ሰው የማያውቀው፤ ሁለተኛው ደግሞ ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት ውጪ ሀገር ለህክምና ሲሄድ የጠበቀው የታቅደ ወጥመድ – ነበር። እርዳታ ማግኘቱ መልካም ሆኖ ሳለ ያልተጠነቀቀበት ፍሬ ነገር – ያለ ይመስለኛል፤ ብቻ ለመቁረጥ አቅም – አነሰው። ውለታን አላውቅህም ለማለት ለዛውም በባዕድ ሀገር በታማሚነት ዓይን የከበደው – ይመስለኛል። ኢትዮጵያዊ ይሉኝታ „ፈርሃ እግዚአብሄር“ ያጠቃዋል። የሚበልጥበትን መወሰን የሚችል እሱ ብቻ ነው። እርግጥነው አሜሪካ የሚኖሩ ብልህና ጠንካራ ቤተሶቹ ችግሩን ከሥሩ ለመንቀል መላ መተው – ነበር። ታግለዋል – ግን የቻሉ – አይመስለኝም። ይህ ማለት ግን በወያኔ ሃርነት ትግራይ ሀገር አጥፊነት ላይ ይደራደራል የሚል ዕድምታ እኔ በግሌ – የለኝም። የሰንደቅ ዓላማው ሆነ የነገረ ኢትዮጵያ ሚስጢራዊ ክህሎት ጉዳይ ፍቺው ሆነ ትርጉሙም በአብርኃም ህይወት ውስጥ ልዩ መሆናቸውን አሳምሬ አውቃለሁ እና። አብሶ ከተማረ በኋላ በብዙ ነገሮች ተለወጦ እጅግም በስሎ ነበር – ያገኘሁት።
- የሌሎች ነፃነት ፈላጊ ድርጅቶችን አይነቅፍም። አሁን ቅንጅትን እንዴት ይወደው ነበር መሰላችሁ። ተግባራቸውንም ያደንቃል። „ትንሳኤ“ ራዲዮንን ደስ ብሎት ነበር – የሚከታተለው። ይህን ቅንነት በብዙዎቹ የድርጀት መሪዎች – አላይም። አዝናለሁ።
- ብሄራዊ ክብርና የነፃነት ፍላጎት ቀጨጨ በሚልበት ቦታ ላይ ደግሞ የራሳችነን ገመናን ሚዲያ ላይ ሳይዘረግፍ፤ በቀጥታ ለሚመለከታቸው አካላት ደፋር ደብዳቤዎችን፤ ማሳሳቢያዎችን – ይጽፋል። ይህ ደግሞ ድርብ ጥቅም አለው።
- መቸም ወያኔ ሃርነት ትግራይ ሰፊ የሆነ የውጊያ ቀጣና ከገጠመው ቦታ ውስጥ አብዩ ደቡብ ጎንደር ላይ ነበር። ረጅም ጊዜ ነበር የውጊያው ቆይታ። የኢትዮጵያ ሠራዊትና የሀገሬው አርበኞች ቦታቸውን ሳያስደፍሩ ሞጥረው በጀግንነት በሚያኮራ አኳኋን ነበር – የተዋጉት። የፋርጣ አውራጃ አስተዳዳሪ የነበረው ሻ/ አጥናፉ ገላው ያ እናት ሆዱ – ወዳጄም፤ የተግባር አባቴም በውጊያው – ተሰዋ። እና ሌሎችም። የወያኔ ሃርነት ትግራይ የደቡብ ጎንደርን እርእሰ ከተማ ደብረታቦርን ሙሉ ለሙሉ ሲቆጣጠር፤ በወቅቱ የደቡብ ጎንደር ክ/ሀገር ኢሠፓ አንደኛ ጸሐፊ የነበሩት አርበኛ ጄ/ ኃይሌ መለስ ለወያኔ ኃርነት ትግራይ ለሰከንድ ሳይገዙ „አሻምን በተባ ተግባር ታጥቀው – ከፋኝ በማለት“ ትግሉን በጎንደር ጫካዎች – ጀመሩ፤ በወቅቱ ሰፊ የሆነ የማጥቃት እርምጃ መውሰድ ብቻ ሳይሆን የወያኔ ኃርነት ትግራይ እንቅልፍ ያጣበት፤ የተቁነጠነጠበት፤ ስጋት ላይ የወደቀበት ወቅት – ነበር። እኔም በርቀት እዛው ዱር ወስጥ ነበርኩኝና በገብያ ለመረጃ የምልካቸው ገበሬዎች ዜናውን ያመጡልኝ ነበር። ከእሳቸው ጋር ለመገናኘት ግን የሚያመች ሁኔታ ላይ – አልነበርኩም። ከዛም ወደ ሱዳን አርበኞቻቸውን ይዘው መጓዛቸውን – ሰማሁኝ። አሁን በህይወት ኖይዝላንድ ስላሉ ሂደቱንና ዕውነተኛ ታሪኩን አቅርቦ መጠዬቅ የሚቻል – ይመስለኛል። ኢሳትን „እሳት“ ያሉትም እሳቸው ናቸው። አርበኛ ጄ/ ኃይሌ መለስ ጠላትና ወዳጃቸውን የሚለዩ ስለሆነ በአቋማቸው እንደሚጸኑ – አምናለሁ። እኔም ልጃቸው እና የበታቻቸው ያለኝን ዘመን የማይሽረው አክብሮትና አድናቆት በአጋጣሚው – እግልጽላቸዋለሁ። መኩሪያ ናቸውና! በሥራም እሳቸው ግር ሊላቸው ቢችልም እኔ ግን በአካል – አውቃቸዋለሁ … ብዙ ስብሰባዎችን አብረን – ታድመናልና።
- ሌላው የአርበኝነት መንፈስ ኮማንድ ፓስቱ ኬኒያ ላይ የነበረ ከኢትዮጵያ መንግሥት ፍረሰት በኋላ ትውልድ ከቶውንም ሊተካቸው በማይችለው፤ ለወጣት ወገናቸው ችግር እናት ሆዱ በነበሩት፤ በፈላስፋውና በሳይንቲስት ኢንጂነር ቅጣው መሥራችነት ባለ ተስፋ ዬአርበኝነት ውሎም – ነበር። „የኢትዮጵያ አንድነት ብሄራዊ ግንባር“ ‚በሁልአቀፍ‘ መርህ ወቅቱን በተግባር በአርበኝነት መንፈስ – አስጊጦት ነበር። መንፈስን ለወቅቱ – ሰብስቧል። በአጋጣሚ ዕድሌ ውብ ነውና አብሮ ከተጓዛቸው ውስጥ ከሙሉ ሥነ ምግባር ጋር፤ ቀድም ብሎ በአቻነት በክፍል ኃላፊነት ከእኔው ጋር የሠራ፤ በኋላ ከእነ አብርኃም በፊት በነበረው ኮርስ ላይ ታዳሚ የነበረው፤ በየካቲት 66 የፖለቲካል ሳይስንስ ኢንስቲቲዩት የ2 ዓመት ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀው፤ የክ/ሀገር ኢሠፓ ኮሜቴ የድርጅት ጉዳይ ኃላፈ ሆኖ የተመደበው ጓደኛዬ እና እብሮ አደጌም ከሳይንቲስ እንጂነር ቅጣው ጋር ወደ ኤርትራ ከተጓዙት የመጀመሪያዎቹ ውስጥ አንዱ ነበር። ጓድ ገ/መድህን በርጋ እንደ እኔ አብዝቶ ይሳሳለት ነበር። ሙሉውን አቅም ከእርሱ ነበር የወረሰ፤ በዛ ከእሳት ከውሃ ይባልበት በነበረበት የወጣትነት አፍላ ዕድሜ ላይ ቁጥብ – የተረጋጋ – እጅግ የሰነከነ – መቀመጥ የማይሰለቸው – ማድመጥ አድባሩ የሆነ፤ ብሩኽና ሁልአቀፍ የህሊና አቅም የነበረው ጸባይማም ነበር፤ አንድ ቀን ሲበሳጭ ሲቆጣ አይቼው – አላውቅም። ከመናገር የተቆጠበ የተግባር ዓፄ ነበር። የሚገርመው ምክትሉም በኋላ እሱን የተካው እንደ እሱ – ነበር። ዛሬ ሁለቱም ውጪ ሀገር ይኖራሉ። ትግሉን የተውት ይመስለኛል። እንዲያውም በእኔ ደረጃ ከነበሩት እኔ ብቻ ነኝ ያለሁት። ሴትማ ፈጽሞም – አይታሰብም። ለማንኛውም እኔ በሁለገብ ብቃቱ ልምዱና ተመክሮው አርበኛ አንዳርጋቸው ጽጌን መንፈስ የመተካት አቅም ያለው ብቁ አርበኛ ነው የምለው ነው። ያን ጊዜ ወላጅ እናቱ የቅዱስ ገብርኤል የስለት ልጅ ስለነበር ከወሎ ክ/ሀገር ቤታቸውን ትተው፤ ኑሯቸውን አፍረሰው መጥተው ከእሱ ጋር ጎንደር ለመኖር – ወሰኑ። እማ መጀመሪያ ያዩኝ ዕለት ነበር „ጸጋ“ ብለው የጠሩኝ። ዛሬ እኔ እንዲህ በብላቴ ጸጋዬ ገ/መድህን ፍቅር ዙሪያ ስታቀፍ በቅርብ ቀን ነው ትንቢታቸው – የገባኝ። የኢትዮጵያ ሴቶች ብልህነታቸው – ይቀድማል – ጥልቆች! እማ ይህም ብቻ አልነበረም ተልዕኳቸው „ከእኔ ቤተሰቦች ጋር ወሎ አብሮ አድጓል፤ ይህ ግንጥል ጌጥ ነው“ በማለት የአባቱን ቤተሰቦች በጎንደር ገጠሮች አፈላልገው እሱ ሳያውቅ – አገናኙት። የአባቱን የወንድም ልጅም ኃላፊነቱን ወስደው ያስተምሩ – ነበር።
መናሻና መድረሻው ሲገናኙ – የዕድምታዬ።
ሽበት በሆድ የበቀለ ዕለት ክብርን – ይሸልማል። የአቶ መልኬ መንግሥቴ የአርበኞች ግንባር መሥራችነት ሳዳምጥ ከልቤ ነበር ያዘንኩት። አቶ መልኬ መንግሥቴ የአርበኞች ግንባር መሥራች አባልነት ከታሪክም ከእውነትም ጋር ሲታይ በዕብለት የተጀቦነ ለባዶነት – የተመረጠ ስለሆነ። አይደለም በምሥራታው፤ በመንፈሱ በእውነት – አለነበሩበትም። ከሚያድር ነገር ላይ ማረፍ ምንኛ – መታደል ነው። የነገ ሰውስ መሆን ምንኛ – ረድኤት ነው። ውዶቼ የሀገሬ ልጆች – የሚገባነን ክብር ብቻ – እንቀበል፤ የማይገባን ግን የተውሶ ነውና – ልንጸዬፈው ይገባል። አይሰነብትምና። እንትን ታውቃላችሁ? … በረዶ … ስለዚህ ባልዋሉበት ባልነበሩበት የተሰጠው ልብድ ክብር – ቀላጭ ነው ዬጭቃ እራት። የአደራ ተቀባይነት መንፈሱም – ፍልስ ነው፤ ተከታይም አይኖረውም። አብዛኛውን የጎረቤት ሀገሮች በአገኙት አጋጣሚ ያዩት አዛውንት ዕድሜቸው የፈቀደውን፤ መሆን የቻሉትን፤ የዕውቀት ደረጃቸው የመጠነውን ያህል እንደ ዜጋ በሚያምኑበት መስመር ማድረጋቸውን – ግን አከብራለሁ። ትልልፉ ግን – አይመችም። እንደገናም በዚህ ምስቅልቅል ሁኔታ መዳከሩም የውስጥን የራስን ሰላም – ይቀማል። ለምን እንደ መረጡት – በፍጹም አላውቅም። ሌላው ግን በአዲሱ አውሎ የተለጋ መንፈስ በተቃራኒውም ወገንም አድምጫለሁ። ግንቦት 7 ዓላማውን ሲያስተዋውቅ አቅሙን በመመልከት በፍርሃት ተውጠው „ሊሻማ“ ደግሞ መጣ በማለት በቅናት ድብን ብለው ድንኳን ጥለው ሐዘን ላይ የተቀመጡ፤ በመንደርተኝነት ስሜት እያደኑ ሰዎችን ያግባቡ፣ ያስተባብሩ የነበሩ፤ ምስክሮች ተቀምጠን ዛሬ ደግሞ ስለታችን ሰምሮ ግንቦት 7 ቁልፉን ኃላፊነት ወሰደ ብለው ሲፈነጥዙ፤ እነሱ ዘመንተኛ ሌላው ተግባር ላይ ያለው አጥር አልባ የሚማስነው መከረኛ ደግሞ ዕትብቱ ተፈልጎ ተወቃሽ ሲሆን፤ ህሊና ከአካል ቀድሞ ቀብር የተበዬነበት ስለመሆኑ ግራ ቀኙን የምንታዘብ ሰዎች ጉድና ጅራት – ብለናል። አጥቂ ሃሳብን ማድነቅ – መከተል – ተባባሪነትን ማሳዬት፤ አብሮ ለመሆን ከልብ መፍቀድ መልካም ሆኖ ሳለ ከእኔ ወዲያ ላሳር ማለት ግን …. ትናንትን መዝላል – ሽበትንም -ማቃጣል ይሆናል። ስለዚህ ግድፈቱ የእርስዎ ብቻ አይደለም። ማተበኛ ቦታ ተፈጥራችሁ ማተባችሁን ብትጠብቁ መልካም ነው። ከሁሉ የሚከፋው እራስን መዝረፍ ነው።
ምራቂ – መረጃ።
እኔ አቶ መልኬ በአካል – እጅግ በደርበቡ – አውቃቸዋለሁ። በ2008 መጨረሻ ከታህሳስ 18 ጀምሮ እስከ 24 ድረስ የG7 ስበሰባ ኃያላን ሐገሮች ስብሰባ የሄሮድስ መለስ ዜናዊን አስተዳደር የተቃውሞ ሰልፍ ለመሳተፍ ኮፕን ሀገን ዴንማርክ ሄጄ – ነበር። ያን ጊዜ በሙሉ ትጥቅ ነበር – የተገኙት። ዝግጅቱ የሁሉም አውሮፓ አቀፍ ተሳታፊ የአጋርነት መሰናዶና እርዳታ ያስፈልገው – ስለነበር። ለዚህም ክብርት ባለቤታቸው ለነባራቸው የተሟላ ቅናዊ ተሳትፎና ሸግዬ ትህትና የበቃ መሰናዶ ምስጋናዬ የላቀ ነው። የዛሬን አያድርገውና የአቶ መልኬ መንግሥቴ መገኘት ተልዕኳችን ግርማ እንዲኖረው አድርጎት ነበር። ትናንት ለዛሬ እንጀራ እንዳይሆን እርሾውን እንዳለ መድፋት – የተገባ አይደለምና። ሌላው ቀርቶ ድክመቶች ከጥንካሬ በላይ ት/ቤቶችም ናቸው – ከምንጥላቸው ሆነ አያስፈልጉነም ከምንላቸውም ቢሆን እምንማርባቸው ዕንቁ ብልሃቶች – ይኖራሉና።
የዛን ጊዜ ዬገጠሙኝ ደመ ግቡ እና ጠያይም ሁኔታዎች።
ደመ ግቡ – በሐሤት የፈነጠዝኩበት የቤቴን የከረንት አፊርስ ተናፋቂ – ፍቅራቸው የማይጠገበውን እህትና ወንድሞቼን በአካል – ማግኘቴ ነበር። አዬ ከረንት ትንሿ ኢትዮጵያ – የናፍቆት ማዕዶት፤ ፍቅሩ ሁልጊዜ – ያሽታል። ሌሎችንም አውሮፓ አቀፍ የነፃነቱ ትግሉ አባ እና እም ወራ ቤተኞች ጋር በመገናኘቴ – ውስጣቸውን በጥልቀት በማዬትም፤ ለዚህ በመታደሌም፤ ደስታዬ ወደር የለውም። ከሄድኩባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ውስጥ አብዛኞቹ በአዘጋጆች ሙሉ ፈቃድ ተሰጥቶኝ ተልዕኮዬን – አሳክቻለሁ። ድካሜንም በፍሰኃ አወራርጃለሁ – ልበል። ወደ ቤቴ ስመለስ ፍጹም – ሰላም ነበረኝ።
ጠያይሞቹ – የታገሉኝ ሁኔታዎች፤ አንደኛው ይዤያቸው ከነበሩት በርካታ ፓስተሮችና ፍላዬሮች ውስጥ በወያኔ ሃርነት ትግራይ መፈንቅለ መንግሥት ተጠርጥረው የታሰሩት የእነ ጄኒራል አሳምነው ጽጌ እና በተለይም የአርበኛ አንዳርጋቸው ጽጌ አባት ዬአዛውንቱ እስር ሁኔታ ደሜን ነበር – የመረመረው። እንዲሁም የሌሎችንም ወገኖቼም። ስለሆነም ተዘጋጅቸበት ስለነበር – ይህ አልተፈቀደልኝም – ነበር። እስካሁንም ለምን? የሚለው መልስ አላገኘሁም። በእነሱ ዙሪያ ሚዲያ ላይም የማዬው ነገር እንብዛም – የለም፤ ምን አልባት የችግራችን መጫጫን ወይንም በችግራችን በብዛት መዋጣችን ሊሆን – ይችላል። አዳዲስ ችግሮች ፋታ ስለነሱን …. ይሆን? ለነገሩ ሴት ጀግና እህቶቼና ጀግና ጦማርያን ከእሥር ተፈተው እኔ እራሴ እንኳን ደስ አለን ለማለት – አልቻልኩም። በሌሎች ነገሮች – ስለጠመድኩኝ።
– ሌላው ጠይም ገጠመኝ – አቶ መልኬ መንግሥቴ ጊዜ ወስደው በከረንቱ ዬፓልቶክ ተሳትፎዬ ላይ አበክረው በተደጋጋሚ አባታዊ፣ ታላቃዊ፣ አዛውንታዊ ተጽዕኖ ለማሳደር ያደረጉት ሙከራ ነበር። ታስታውሱ ከሆነ በወቅቱ የተከበሩ ኢንጂነር ሃይሉ ሻውል የቅድሚያ ድርድር ፊርማ መሰናዶ ከሟቹ ሄሮድስ መለስ ዜናዊ ጋር ያደረጉትን ዬሂደቱን ጅምር አብዝቼ እታገልም እከራከር – ስለነበር። ይህ አልተመቻቸውም – ነበር። እሳቸው በአካላቸው ማታ ማታ በአርበኞች ግንባር ጉዳይ ላይ ሲከራከሩ ያመሹ ነበር። አንዲያውም ዛሬ በቃለ ምልሱ በኰ/ ታደሰ ሙሉነህ ጉዳይ ተቆርቋሪ ሆነው – አዳምጫለሁ። ያን ጊዜ ደግሞ ድርጊቱን በተከላካይነት በባዕድነት ከአንዲት እህታችን ጋር ሲከራከሩ ያመሹ ነበር። መቼም ግራ ነው – ይህ ሰው የሚባለው ፍጡር። ቀን ላይ ደግሞ በመንፈሳቸው ሌላ ቦታ ላይ ነበሩ። ሁለቱም መብታቸው ቢሆንም የራሳቸው መንፈስ በቂ ሆኖ ሳለ ሌላ ለመዝረፍ ማሰባቸው ተጨማሪ ልብ ዬመፈለግ ስስታምነታቸው ገርሞኝ ነበር። ስለሆነም ልባቸውን ሊያሰገቡልኝ ያደረጉት ጥረት ባክኖ – የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል። በነፃነት የማሰብ፣ የመናገር ነፃነቴን የተጋፋ ዕይታ – ነበራቸው። እንደ ዕድል ሆኖ እኔ በአንድ አጋጣሚ በሆነ መሥመር ሰው ከገኘሁ በኋላ፤ … መንፈሴን መቆጣጠር – ይፈለጋል። ይህ ደግሞ የህልም መንገድ ነው። በታምር ዬማይሆን ነው። እኔነቴን ሳያውቁ ስለሆነ የሚጀመሩት ሙከራው ተኖ – ይቀራል። ለዚህም ነው ዛሬ በእኔ ጉዳይ ላይ ትንሽ ያነሳሳሁት፤ የሆነ ሆኖ አጋጣሚውን ታከው የሚጀመሩ ግንኙነቶች ልደታቸውን ሳያከበሩ በነው ይቀራሉ። የሚቻል ነገር ለማድረግ ተፈላጊውን መንፈስ በጥልቀት የማወቅን አቅም – ይጠይቃል። ይሄ ድንቡልቡል የሥነ -ልቦና ቅኝ ተገዢነት ግጥሜ አይደለም።
በነፃነት ፍለጋ መንገዴ ሆነ በኑሮ መርሆቼ እናቴም አትችልም። … እማምንበትን ብቻ ነው የምሆነው። ነፃነቴ ከእኔ ሰብዕና በላይ ክብር አለው። እርግጥ ነው ሳይሳካ ሲቀር ያው ቻሉኝ የሚል ጦር ይታዘዝብኛል ይህም ሠርጌ ነው – የምፍነሸነሽበት። ለእኔ ዬሚቀር – የለም። እንዲያውም ለጤናዬ ተፈላጊ ነው በቂ እረፍት አገኛለሁ። … ዘመን የሰጠኝ እጅግ ያሰበሉ – የበሰሉ አጋጣሚዎችም …. ወፍ ያወጣቸው ልዩ – ልዩ ተመክሮዎቼ … የተማርኩባቸው ሐዋርያ ብቁ ወገኖቼ፤ ጽሞናዊ አስተዳደጌ፤ የተፈጥረኩበት ዕለትም ለዚህ ሽምቅቅ የትውስት ሰብዕና ቦታ በፍጹም – የላቸውም። የሆነ ሆኖ በአንድ ቤት – በአንድ ማዕድ – እጅግ ከተባረኩ የትዳር አጋር ቤተሰቦች ሰንበትን ዴንማርክ ኮፕን ሀገን …. ግን እኔና አቶ መልኬ – አልቀጠልነም። የተገባም ስንብትም – አላደረግንም — ዬልባቸውን አላደረስኩምና። … እኔን የሚያዘኝ ህሊናዬና የማዬው የእውነት ማህለቅ ብቻ ነው። …. ለእኔ ጉዞ ሹፌሯ እኔው ብቻ ነኝ። ይህ በገጸ በረከትነት ለማንም – አይሸለመም። የፈጣሪዬ የሰውነት ሥጦታ ሥርጉተን ብቻ እንዲተረጎም ሆኖ ነው – የተፈጠረው። ከዚህ ጸጋ ከወጣች ሥርጉተ – መሆኗ … ቀርቶ ቀፎ ብቻ ትሆናለች ወይንም ግፋፎ። እንደ እራስ ለመኖር የፈቀደ ሰብዕና ቀጥ ባለ ግልጽነት፤ በቋሚ ፅናት፤ እራሱን ሆኖ – ይኖራል። ሲያልፍም ሥሙም እሱን እንደ ገለጸ – ይበለጽጋል።
የኔዎቹ ከመሰናበቴ በፊት አንድ የቤት ሥራ ልስጣችሁ – ትፈቅዳላችሁን? አንዲት የዶሮ ላባ ጸጉርን ነቅላችሁ ሚዛን ላይ አስቀምጡና ቁጥሩን የሚዛኑን feedback ለማንበብ – ሞክሩ። ድምስ ነው የሚሆነው። እና አቶ መልኬ በጎንደር ህዝብ ላይ ሊያሳድሩት የሚችሉት ተጽዕኖ ለእኔ ምንም ነው። በልበ ሙሉነት ነው ወገኖቼ – የምነግራችሁ። የሚታወቁ ሰውም – አይደሉም። ወያኔ ኃርነት ትግራይ ከሱዳን አስመጥቶ በእስር የገደላቸው አርበኛ ሻ/ አጣናው ዋሴ ቢሆን ኖሮ አዎን – እርግጥ ነው ይቻላሉ። … ኮከብና ዕውቅ ያላቸው ጀግና ናቸውና – ለማህበረሰቡ። ሞዴልም ናቸው። ሥማቸውም ተፈሪነቱ ዘመን ዘለቅ ነው። ወይንም ጀግና ራስ አሞራው ውብነህ ቢሆኑ ጉልቱ ናቸው – ለአርበኛውም ሆነ ለጎንደር ህዝብ። አቶ መልኬ መንግሥቴ ግን በምን አቅማቸው?! ጫና ያለው ተጽዕኖ ለማሳደር አይችሉም። መጠሪያ ሥማቸው ከቤተሰባቸው ወይንም አብረዋቸው በሥራ ገበታ ከሚያውቋቸው በስተቀር የተቀባይነት ሆነ የዕውቅና አቅም – የለውም። … አሁንም በጣም በእርግጠኝነት። ኤርትራ ላይ በአርበኞች ዙሪያ የነበረውን የተግባር ተሳትፎ ሆነ የቅሬታ ጽንስ – መሬቱን ረግጬው ስለማላውቅ ማን ምን ሠራ? ምንስ ሁኔታ – ተፈጠረ? ለሚለው ዕውቀት – የለኝም። እርግጥ የቀድሞው ዬአርበኞች ዬትግል ሂደት ትርምስን በተደሞ በተለያዬ ሁኔታ ሳዳምጥ ቆይቻለሁ፤ ሊያገኙኝ ለፈለጉትም መልስ በወቅቱ – ሰጥቻለሁ። ጹሑፍ ሲወጣ – አነባለሁ፤ ከዚህ ባለፈ ግን ብዕሬም ሆነ አንደበቴ ቁጥብ ሆኖ ነው – የኖረው። ህውከት፤ የኮፒ ራይት፤ የብቁ መሪ ዕጦት ጉዳይ አብዝቶ ይንጠው በነበረው የቀደመው ዬአርበኞች አቅም ብቅ ጥልቅ … ማለትን በጭራሽ – አልሞከርኩትም። እግዚአብሄር – ይመስገን።
የኔዎቹ – ለነበርን ወግ ያለው ቆይታ ከልብ – አመሰገንኩኝ – ክብረቶቼን። ተሸብልሎ የቀረበውን የነፃነት ፈላጊነት ሸንኮፍ ገለጥለጥ ማድርግ – እንዲህ ይገባል። አቶ መልኬ መንግሥቴ ይህ ዓይነቱን መገለብ አስኝቷቸው ነውና አደባባይ የወጡት፤ ልረዳቸው – አልቻልኩም። ዳኝቱን ለህዝብ – ህሊና። የልቤን አድራሹን ዘሃበሻን እጅግ አመሰግናለሁ። ኑሩልኝ – ውድድድድድ ….
አርበኛነት የዘመን ሥጦታ – የፈጣሪ ምርቃትነቱ ምስክሩ አድሮ የሚገኝ የተግባር ማህደር ብቻ ነው!
አርበኛነት በሙሉ ሥነ – ምግባር የበለጸገ – አብነትነት፤ በሂደቱ የማይታፈርበት፤ የመሆን መቻል – ሰማዕትነት ነው!
ትጥቁን የፈታ አርበኝነት ኑሮ አያውቅም፤ ምክንያቱም ነፍሱ ከሥጋው የተለዬችው ከመፈጠሩ በፊት ሙትቻ ሆኖ ነውና!
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።