Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ከፕሬዝዳንት ኦባማ ጉብኝት ማግስት ….. ግርማ ሠይፉ ማሩ

$
0
0

 

girmaseifu32@yahoo.com , girmaseifu.blogspot.com

Girma  Seifuኦባማ ኢትዮጵያን መጎብኘት አለበት? የለበትም? የሚለው አጀንዳ ማከራከሩ መቆም ያለበት ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ መጥተዋል በቃ!! በእኔ እምነት ኦባማ ኢትዮጵያ የመጡት ኢትዮጵያ ባሳየችው ፈጣን ዕድገት ተመስጠው፣ ይህ ዕድገት ካፈራው ፍሬ የአሜሪካን ህዝብ እንዲቃመስ (ብዙዎቹ እንደሚሉት ቦይንግን እየገዛንም ቢሆን) ብለው አይደለም፡፡ በእኔ እምነት ኦባማ ከስልጣን ከመልቀቃቸው በፊት የአባታቸውን ሀገር ኬኒያን መጎብኘታቸው በብዙ መመዛኛ የግድ አስፈላጊ ነገር ነበር፡፡ ለዚህ አንድ መናጆ በቅርብ ያለች ኢትዮጵያ እንድትሆን የግድ የሚሉ ነጥቦች ተገኝተዋል፡፡ በዋነኝነት ደግሞ ሁሉቱ ሀገሮች በግንባር ቀደምትነት እየተፋለሙት የሚገኘው አልሸባብ የሚባለው የሽብር ቡድን ነው፡፡ በአሜሪካ መንግሰት ዘንድ ይህ ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት የኦባማ ጉብኝት ፈቃድ እንዲያገኝ ይሁንታ ሊያስገኝ የሚችል ነጥብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በተጨማሪ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ በመሆኗ ኦባማ በፀረ ሽብር ህጉ ህብረት አፍሪካዊያን በጋራ እንዲቆሙ በአፍሪካ ህብረት ፅ/ቤት በኩል ማስተላለፍ አንዱ መንገድ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚቻለው የሁሉም አፍሪካ ተወካዮች የሚገኙባት ሀገር ኢትዮጵያ እንደሆነች የሚስት የለም፣ ይህ ኢትዮጵያ ሀገራችን በዓለም ቁንጮ በሆነች ሀገር መሪ እንድትጎበኝ ዕድል ሰጥቷታል፡፡ እንዲህም ሆኖ ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም በጎ ነገር የለም የሚለው ነገር በፍፁም የለኝም፡፡

በእኔ እምነት ኦባማ አፍሪካን መጎብኘት ካለባቸው እና አምስት ሀገር መመርጥ ካለባቸው ኢትዮጵያ አንድ መሆን እንዳለባት አምናለሁ፡፡ ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ካለኝ ግምት እንጂ ሀገሪቱን የሚመራው መንግሰት ኢህአዲግ ስለሆነ አይደለም፡፡ ለማንኛውም ፕሬዝዳንት ኦባማ ኢትዮጵያ የምትባል የሰው ዘር መገኛ የሆነች ድንቅ ሀገር ጎብኝተው ተመልሰዋል፡፡ ከዚህ ጉብኝት ምን ጠበቀን? ምን አገኘን? የሚለው ነገር በቅጡ መታወቅ አለበት፡፡ ይህ ጉዳይ ወደፊት በደንብ የሚፈተሸ ሲሆን አሁን ግን ካለብኝ ስጋት አንፃር አሳቤን ላጋራችሁ፡፡

እጅግ ብዙ የሚባሉ ምን አልባትም በፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ አለን የሚሉ ሰዎች ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ መጥተው ይህን አንባገነን መንግሰት በአደባባይ እንዲያውግዙ እና ይህን የመሰለ ድርጊታቸውን የማያቆሙ ከሆነ ዲፕሎማሲያዊም ሆነ ከዚያ የዘለለ እርምጃ ሊወስዱ እንዲሚችሉ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጡላቸው ነበር፡፡ ከዚያ በመነሳት ኦባማ በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት “በዲሞክራሲያዊ አግባብ የተመረጠን መንግሰት በሀይል ማውረድ ተገቢ አይደለም” የሚለውን ቁንፅል ሃሳብ ይዘው ለምን አሉ በሚል ቡራ ከረዩ ሲባል ታዝቢያለሁ፡፡ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ እንኳን ሰው ሀገር ለጉብኝት ሄደው አይደለም በሀገራቸው ቤተ መንግሰት (ኋይት ሀውስ) ተቀምጠው እንዲህ ዓይነት ከዲፕሎማሲ መስመር የወጣ የአንድን ሀገር መንግሰት ለማዘዝም ሆነ ለማስጠንቀቅ አይችሉም፡፡ በተለይ ኦባማ ከሚከተሉት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ አንፃር ይህ በፍፁም የሚያስኬድ አይደለም፡፡ ለምሳሌ በሪፐብሊካን ዘመን ወዮልሽ ስትባል ከነበረችው ኢራን ጋር የተሻለ የሚሉትን መቀራረብ እና መነጋገር እንጂ ማስፈራራት ተገቢ አይደለም ብለው ይስራሉ፡፡ ኦባማ አሁንም ኢትየጵያ መጥተው ያስተላለፉት መልዕክት የኢትየጵያ መንግሰት አንባገነን ነው ብሎ በመራቅ ሳይሆን ቀርቦ በማነጋገር ማለዘብ ይቻላል ነው፡፡ ከቻይና ጋርም እንስራለን ሲሉን መልዕክቱ ግልፅ ነው፡፡ ኦባማ “በርማ” የሄዱት መንግሰቱ ዲሞክራሲያዊ ስለሆነ አይደለም፡፡ ኢትየጵያም የመጡት እንደዚሁ፡፡

የኦባማ ጉብኝት የአባታቸውን ትውልድ ሀገር ለመጎብኘት ካላቸው ቁርጥ አቋም ጋር መናጆ ተደርገን ነው የምንል ሰዎችም ብንሆን የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት ምንም የሚያመጣው ፋይዳ የለም የሚል እምነት የለንም፡፡ ይህን ፋይዳ ግን ገዢው ፓርቲ እና መንግሰት እንዴት ይጠቀሙበታል የሚለው ነው፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ ገዢው ፓርቲ በዋነኝነት ይህን ጉብኝት መጠቀም የጀመረው ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ እና ይህን ጉብኝት የተቃወሙትን በተለይ ግልፅ ተቃዎሞ ሲያሰሙ የነበሩትን በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ለማውገዝ እና ለማሸማቀቅ ነው፡፡ ይህ ትርፍ ከአስገኘም የአጭር ጊዜ እንጂ ዘላቂ ትርፍ ሊያመጣ የሚችል ሳይሆን መቃቃርን የሚያፋፋ አካሄድ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የኦባማ ጉብኝት ትርፍ በአፍንጫችን ቢወጣ ይሻለን ነበር፡፡ ከዚህ መንግሰት ባህሪ አንፃር ከኦባማ ጋር በሚስጥር በተደረገ ውይይት መነሻ የሚደረጉ ፈጣን የፖሊሲም ሆነ የአስራር ለውጥ በግሌ አልጠብቅም፡፡ ምክንያቱም “ኦባማ እንዲህ አድርጉ ብሎ አደረጉ” መባል አይፈልጉም፡፡ በሌላ ፅንፍ ያሉትም ቢሆኑ “ኦባማ አዟቸው አደረጉ” ማለታቸው አይቀርም፡፡ ይህ በኢትዮጵያዊ ስነ ልቦና ሲታይ ፊት ለፊት ያለው ሲሆን ይህ ደግሞ ለለውጥ እጅግ ደንቃራ የሆነ አስተሳሰብ እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ይህን ሊሰብር የሚችል መሪ ያለን አልመሰለኝም፡፡ አግኝተን ግምቴ ልክ ባይሆን ደስ ይለኛል፡፡

ሌላው ከፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ጉብኝት ከፍተኛ ጥቅም ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው በገፅታ ግንባታ እና እርሱን ተከትሎ የሚመጣው የግል ባለ ንዋዮች የሚያደርጉት ኢንቨስትመንት ነው፡፡ ከፕሬዝዳንቱ ጋር እጅግ ብዙ ጋዜጠኞች ትክክለኛውን የኢትዮጵያ ገፅታ በሚችሉት መስመር ሁሉ ለማግኘት እንደሞክሩ ይታመናል፡፡ እነርሱን መሰረት አድረገው መረጃ የሚተነትኑ እና የሚያወጡ አካላት የሚሰጡት ግመገማ ውጤት ለኢንቨስተሮች ውሳኔ መሰረት ሆኖ ያገለግላል፡፡ የአሜሪካና የቻይና መሪዎች በሀገሮች ጉብኝት ሲያደርጉ ጉልዕ ልዩነት አለ፡፡ የቻይና ፕሬዝዳንት መጥተው ጉብኝት አድርገው ቢሄዱ አንድ ቃል ሊገቡ የሚችሉት ነገር ይኖራል፡፡ መንግሰታቸው ከሚመሯቸው ተቋማት የተወሰኑትን በኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት አድርጉ ብለው ትዕዛዝ ሊስጡ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ፕሬዝዳን ባራክ ኦባማ ይህን ለማድረግ እድልም መብትም የላቸውም፡፡ የአሜሪካ ባለሀብቶች ከመንግሰታቸው ጥበቃን እንጂ የት ኢንቨሰት እንደሚያደርጉ መመሪያ አይሰጣቸውም፤ አይቀበሉም፡፡ የሚገርመው በራሳቸው ውሳኔ ባደረጉት የኢንቨስትምንት ውሳኔ ግን መንግስታቸውን በቂ ጥበቃ እንዲያደርግላቸው ያስገድዱታል፡፡ ይህ ነው የአሜሪካ ስርዓት፡፡

የኢትዮጵያ መንግሰት ከኦባማ ጉብኝት ውጤት ይጠብቅ ከሆነ ያለ ምንም ይሉኝታ በሀገራችን የግል ኢንቨስትመን (በተለይ የውጭ) እንዳይመጣ ማነቆ የሆነውን የውስጥ ሰላምን (ፀጥታ አላልኩም) ማምጣት አለበት፡፡ ይህ ማለት በጠምንጃ ታፍኖ ዝም ያለ ህዝብን መፍጠር ሳይሆን በዲሞክራሲያዊ ሰርዓት ውስጥ የሚገኝ ስላምን መፍጠር ይጠበቅበታል፡፡ ለዚህም ዋነኛ ግብዓት ሆነው የሚያገለግሉትን ነፃ ሚዲያ፣ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታን፣ በህገ መንግሰት ላይ የተደነገጉትን የስብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታት፣ ልዩነቶች በህጋዊ አግባብ መፍታት የሚቻልበት የፍትሕ ሰርዓት መዘርጋት፣ ወዘተ እጅግ በጣም አስፈላጊ ናቸው፡፡ እነዚህ ሲሟሉ የአውሮፓና አሜሪካ ባለሀብቶች ይመጣሉ፣ ኦባማም ኢትዮጵያን ባይጎበኙም፡፡

ኦባማ በአፍሪካ የስልጣን ገደብ ማጣት፣ ሙስና፣ የነፃው ፕሬስ እመቃ ወዘተ ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ካንሰር መሁኑን አበክረው ገልፀዋል፡፡ የሚገርመው መሪዎቻችን ያጨበጭቡ ነበር፡፡ ታመሃል ሲባል የሚያጨበጭብ ታማሚ አንባቢ ልብ ሊለው ይገባል፡፡ በአኔ እምነት በካንሰር የተያዘ የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ በሚገኝ ኢኮኖሚ ውስጥ መዋለ ንዋይ ለማፍሰስ የሚመጣ ይኖራል ማለት የሚታሰብ አይደለም፡፡ ከኦባማ ጋር የመጡት የልዑካን ቡድኖች ውስጥ የሚገኙት የንግድ ማህበረሰብ ተወካዮች በኢትዮጵያ ውስጥ የአንድ ፓርቲ አንባገነን ስርዓት እንዳለ አይሰሙም፣ በሲቪክ ማህበረስብ ውስጥ እየተደረገ ስለ አለው እመቃ አይረዱም፣ ከሲቪል ማህበራት ጋር የተደረገው ውይይት በሚዲያ ሳይገለፅ በሚስጥር ውይይት ይደረግበት ማለቱ ምን ማለት እንደሆነ አይገባቸውም ማለት እነዚህ ባለ ሀብቶች በሚወስዱት ውሳኔ ሳይሆን በድንገት ባለሀብት የሆኑ ያስመስላል፡፡ ኢቲቪ ማታለል የሚችለው በኢቲቪ መረጃ መሰረት አድርገው ውሳኔ ለሚያሳልፉ ብቻ ነው፡፡

በኦባማ ጉብኝት ምክንያት አንድ የተገኘ ውጤት አለ፡፡ ይህ ውጤት ለአሜሪካም ለኢትዮጵያም እኩል ነው ብለን አናምንም፡፡ የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ መንግስታት ባስማማቸው ጉዳይ ላይ ቃል ኪዳናቸውን አድሰዋል፡፡ ከዚህ በፊት በሚስጥር ተይዞ የነበረው የኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የፀረ ሽብር (በተለይ አልሻባባም በሚመለከት) ኃይል ግንባር መሪ መሆን አሁን በይፋ ታውጇል፡፡ ለዚህም የሚያስፈልገውን ሁለቱም መንግሰታት ለማዋጣት አቅሙ አላቸው፡፡ እኛ ደምና ነብሳችንን እነርሱ ደግሞ ዶላር ሊሰጡን ተሰማምተናል፡፡ በዚህ አጀንዳ ዙሪያ በሁለቱ መንግሰታት ዘንድ ልዮነት የለም፡፡ ይልቁንም ሁለቱ ሀገራት በዚህ አጀንዳ ዙሪያ ባላቸው የጫጉላ ጊዜ ሌሎች አጀንዳዎች እንዲገፉ እና በተለይ የኢትዮጵያን የግፍ ቀን እንዲረዝም በር ከፍተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሰት አልሻባብና መሰሎችን ብቻ ሳይሆን ለዲሞክራሲ የምጮሁ ኢትዮጵያዊያንንም ከእነዚህ ጋር ቀላቅሎ ለመውቀጥ አስፍስፎ ይገኛል፡፡ እሰከ ዛሬ የበላቸውን እነ አንዱዓም አራጌን፣ ናትናኤል መኮንን፣ ሀብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሽን፣ ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮች ወዘተ ጨምሮ ማለት ነው፡፡

የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንበታን በሚመለከት አሜሪካኖች ምክር የሚሰጡ ሲሆን የወዳጅ ምክርን መስማት ያለመስማት ደግሞ በኢትዮጵያ መንግሰት እጅ የሚገኝ ነው፡፡ በኢትዮጵያ መንግሰት አተያየ በተለይ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም አገላለፅ “እንቁላል በአንድ ቅርጫት” አይቀመጥም፡፡ የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ወዳጅ አንድ አይበቃም፡፡ ከቻይናም ከአሜሪካም ያስፈልጋል፡፡ አንዱ ቢያኮርፍ በአንዱ የሚል ዘይቤ ተጀምሮዋል፡፡ ኦባማ ማኩረፍና መራቅ አይጠቅምም- መነጋገር ነው የሚያዋጣው ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሰት ምንም ግልፅ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ቢፈፅም፣ ከዓለም ሁለተኛ ሚዲያ አፋኝ መንግሰት ቢሆኑም ኢትዮጵያን ከሚመስል ትልቅ ሀገር ጋር ጠብ አያስፈልግም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሰትም ቢሆን አሜሪካ ምንም እንኳን ኒዎሊብራል የሆነች ሀገር ብትሆን እና በሀገሯ ኢኮኖሚያዊ ፍትህ የሚያሰፍን መንግሰት ሳይሆን ገበያ የሚመራት ቢሆንም፣ አይንሽን ላፈር ብሎ መሳደብ ጥቅም የለውም፡፡ ሰለዚህ ሁለቱ መንግሰታት የጫጉላ ጊዚያቸውን በሚያስማማቸው ጉዳይ ላይ ያደርጋሉ፡፡ የእኛ ደምና ነብስ እንዲሁም ዲሞክራሲያዊና ስብዓዊ መብታችን አሳልፎ መስጠት፣ የአሜሪካኖች የታክስ ከፋይ ገንዘብ ለጊዜውም ቢሆን ጋብቻ ፈፅመዋል፡፡

ቸር ይግጠመን

 

 

 

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>