Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

በአርበኞች ግንቦት 7 ሕዝባዊ ትግል ላይ ከየአቅጣጫው እየተሰነዘሩ ያሉ ፈተናዎችና ማርከሻ መድኃኒታቸው!

$
0
0

Birhanu nega photo

እግዚአብሔር ይመስገንና አሁን የነገዋን ነጻይቱን ኢትዮጵያ ለማየት መንገዱ ላይ ቆመን መራመድ የቻልንበት ሰዓት ላይ ደርሰናል፡፡ ይሄ ትልቅ ትልቅ እመርታ ነው፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ ራሱ ወያኔ ተሸንፎ እንደወደቀ መቁጠር ይቻላል፡፡ የቀረው የባለሥልጣኑ የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡ ነገ የሚሆነው ነገ እንጅ ዛሬ ስለማይሆን ብቻ ነው፡፡ ነገ ግን ዛሬ መሆኑ አይቀርምና ነገ የምንጨብጠውን ዛሬ እንደጨበጥነው መቁጠር ይቻላል፡፡

ይህ ታላቅ እመርታ እንዳይመዘገብ ወያኔ የሀገር ክህደት በመፈጸም ለጎረቤት ሀገራት ሉዓላዊ የሀገሪቱን መሬት እየቆራረሰ ከመስጠት ጀምሮ በተለያየ ጥቅም በመያዝ መሸሻ መሸፈቻ መደራጃ መንቀሳቀሻ መንደርደሪያ እሱ ሱዳንን ይጠቀምባት እንደነበረውና ከሱዳን ያገኝ የነበረውን ድጋፍና ምቹ ሁኔታዎች የሚሰጠን ጎረቤት ሀገር እንዳይኖርና እንዳናገኝ ለማድረግ ያላደረገው ነገር ያላስቀመጠው መሰናክል ያልቆፈረው ጉድጓድ አልነበረም፡፡ ይሄንን ዕድል ልናገኝ የምንችልበት አንድ ቦታ ከተገኘ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሶተኛ ከመሆኑና ይሄንን አጋጣሚ የሚጠባበቅ ከመሆኑ የተነሣ አርፎ ተቀምጦ የነበረውም አማራጭ ስላጣ ብቻ እንደሆነ ይሄንን ዕድሉን ባገኘ ጊዜ ግን ወያኔ ዕድሜ እንደማይኖረው በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚያልቅለት ጠንቅቆ ያውቀዋልና፡፡ መሸሻ መሸፈቻ ለማሳጣት ይሄንን ያህል ርቀት የተጓዘው ወያኔ ይህ አሁን ከባሕረ ምድር (ኤርትራ) ላይ ያገኘነውንም ለማሳጣት ለማበላሸት ይሄም አልሆን ሲለው ሐሰተኛ የፈጠራ ወሬና ሴራ በመጠንሰስ እንድንሸሽና እንዳንጠቀምበት ለማድረግ በከፍተኛ ደረጃ ሲጥር ነበር እየጣረም ይገኛል፡፡ እውነቱን መለየት ማወቅ መረዳት እስኪያቅተን ድረስ ባሕረ ምድር የመሸጉትን የነጻነት ታጋዮችን ትግል ሊያደናቅፍ ሊያሰናክል ሊያጨናግፍ የሚችሉ የሆኑና ያልሆኑ ነገሮችን መሠረት ያደረጉ ስሞታዎችን ስም ማጥፋቶችን ድምዳሜዎችን የያዙ መጣጥፎች አሁን ማንነታቸው ይበልጥ ግልጽ እየሆኑ እየታወቁ በመጡ ግለሰቦች ቀደም ሲል ግን በጣም ተአማኒነት በነበራቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ድረ ገጾች ላይ እየተለቀቁ እየቀረቡ ትግሉን እንድንጠራጠር እንዳናምን እንድንሸሽ ከዚያም አልፎ በጠላትነት እንድንፈርጅ ለማድረግ ከባድ ከባድ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡

ከዚህ በኋላም ወያኔ እስካለ ድረስና የዕጣ ፈንታው የመጨረሻ መጨረሻ ሰዓት የደረሰ መስሎ እስከታየው ድረስ አያደርገውም የሚባል ነገር ሳይኖረው ሊያደርገው የማይችለው ምንም ዓይነት ነገር ሳይኖር እስከ የመጨረሻ ህቅታው ድረስ የጣረሞቱን በመንፈራገጥ አቅሙን አሟጦ በመጠቀም የተቻለውን ሁሉንም ዓይነት ጥረቶች በማድረግ ይቀጥላል እንጅ ይቆማል ብላቹህ አታስቡ፡፡ አሁን አሁን ከእነዚያ ስም ማጥፋቶች የተጋነኑ ስሞታዎችና የፈጠራ ውንጀላዎች ትክክለኛ የተፈጸሙ ከሆኑትም ጀርባ የወያኔ እጅ እንዳለ ግልጽ እየሆነ መጥቷል፡፡ እኔ በእርግጥ ጥርጣሬው የነበረኝ ቢሆንም አብዛኞቻችን ይሄንን አለመገመታችን አለመጠርጠራችን ምን ያህል የዋሆች ብንሆን ነው እያሰኘኝም ነው፡፡

እነኝህን ጽሑፎች ይጽፉና በድረ ገጻቸው ይለጥፉ የነበሩ ግለሰቦችና ድረ ገጾች አንዳንዶቹ አስቀድሞ በነበረው ማንነታቸው በወያኔነት የምንጠረጥራቸው አልነበሩም፡፡ አንዳንዶቹ ግን ወያኔ በስውር ለዚሁ ዓላማው አስቀድመው ተአማኒነትን አግኝተው እንዲቆዩ አድርጎ ያዘጋጃቸው ናቸው፡፡ ቀደም ሲል በወያኔነት የማንጠረጥራቸው ወይም ወያኔ ያልነበሩትም ቢሆኑ ትናንት አልነበሩም ማለት ዛሬ አይሆኑም ማለት አይደለም፡፡ ወያኔ የመጨረሻው መጨረሻ የደረሰ መስሎ ከታየው እራሱን ለማዳን የሚቆጥበውና የሚሰስተው ምንም ነገር የለም፡፡ እንዳልኳቹህ የሀገርን ካዝና አራቁቶም ቢሆን ገንዘብ ይረጫል፣ ፍላጎታቸው ገንዘብ ሳይሆን ጉዳዮች እንዲፈጸምላቸው ለፈለጉት ጉዳዮቻቸውን ይፈጽምላቸዋል፣ ፍላጎታቸው እነዚህ ሁቱም ያልሆነና ሥልጣን ለሚፈልጉትም ከሚንስትርነት እስከ ዲፕሎማትነት (አቅናኤ ግንኙነት) ድረስ ሥልጣን እየሰጠ ይደልላል፡፡ ሌላው ቀርቶ አያገኝም እንጅ እንዲህ አድርገሀል እንዲህ ብሎ ለፍርድ ላቅርብህ ሳይለው ከሀገር ክህደት እስከ የዘር ማጥፋት ለፈጸመው ወንጀል ላይጠይቀው አስተማማኝ ዋስትና የሚሰጠው አካል ቢያገኝ የመንግሥት ሥልጣንን ሁሉ አሳልፎ በመስጠት እራሱን ለማዳን ዝግጁ ነው፡፡

photo file

photo file

አሁን በዚህ ዘመን በእነዚህ ወያኔ ያንዣበበበትን አደጋ ለማስቀረት ሳይሰስት በሚያቀርባቸው መደለያወች የማይለወጥ የማይደለል ሰው ማግኘት በጣም ከባድ እየሆነ ከመምጣቱ የተነሣ ብዙዎች ያውም በቀላል በቀላል ነገር እየተደለሉ ሕዝብን እንደካዱ ስናይ ቆይተናል፡፡ አብሶ ደግሞ ሀገርና ሕዝብ ነጻ ሆነው ማየት ቁርጠኛ ዓላማ ይዞ ሳይሆን ከግል ጥቅሙ ከዝናና እውቅና ፍለጋ አኳያ እንዲሁም ወያኔ ተወግዶ እሱም ሥልጣን ይዞ በተራው ባለ ሥልጣን ለመባል፣ ለመኮፈስ፣ ሕዝብን ከጫማው ስር ለመርገጥ፣ በግል ጉዳዩ ለገጠመው ችግር የተጣላውን ለመበቀል፣ ለማዘዝ ለመናዘዝ ወይም ደግሞ ለመብላት ምኞትና ፍላጎት ይዞ በተለያዩ የሕዝባዊ ትግል ዘርፎች ተሰማርቶ ወያኔን እየተገዳደረ እየተሯሯጠ ያለ ሰው ከሆነ እንዲህ ዓይነቱን ሰው የያዘውን ሕዝባዊ ትግል በማስካድ ወያኔ የሚፈልገውን ነገር አቅርቦለት አድርጎለት ደልሎ መጠቀሚያው አገልጋዩ እንዲሆን ለማድረግ አይቸግረውም፡፡ አሁን እያስቸገሩ ያሉ ግለሰቦች የተደለሉበት ገንዘብ ወይም ሌላ የመደለያ ነገር መጠንና ዓይነት ይለያይ እንደሆነ ነው እንጅ ከላይ የጠቀስኩትን ዓይነት ፍላጎቶች ይዘው በተለያየ መስክ ሕዝባዊ ትግል ያደርጉ የነበሩ ግለሰቦች እንደነበሩ አሁን ላይ እርግጠኛ መሆን ይቻላል፡፡

በዚህ ጽሑፍ ላይ እኛ ሳናውቃቸው ቀርተን እራሳቸውን ሰውረው ወያኔ ደልሎ ለራሱ ጥቅም እንዲያድሩ ያደረጋቸው ግለሰቦች አሳቢ መስለው የተለያየ ነገር በማውራት የትጥቅ ትግሉ እንዳይታመን እንዳይጠነክር ከግብ እንዳይደርስ ለማድረግ ይጠቀሙባቸው በነበሩ ሐሳቦች ላይ አተኩረን ዕናያለን፡፡ ወደ መሀሉም ወያኔ ገዝቷቸው ካልሆነ በስተቀር ሌላ አሳማኝ ምክንያት ስላላቸው እየተደረገ ያለውን ሕዝባዊ ትግል የሸሹ እንዳልሆኑና ምንም ዓይነት አሳማኝ ምክንያት አቅርበው ሊሸሹ ሊቃወሙ የማይችሉበትን አመክንዮም ዕናያለን፡፡

የትጥቅ ትግሉን የሚቃወሙ ወገኖች የትጥቅ ትግሉን ተአማኒነት ለማሳጣት የሚያነሡዋቸው ነጥቦች ምን ምን ናቸው? የሚለውን ቀድመን ዕንይ በአምስት ዋና ዋና ሐሳቦች ይጠቀለላሉ፡-

  1. ሸአቢያ ራሱ ስላልቻለ አቅም ስለሌለው በእኛ ተጠቅሞ ወያኔን ለመበቀል ለማስወገድ ነው እንጅ በፍጹም በፍጹም ሸአቢያ ለኢትዮጵያ በማሰብ ይሄንን ድጋፍ ሊያደርግ አይችልም፡፡ ሸአቢያ በዚህ ዓላማው ምክንያት በሚያደርግልን ድጋፍ ውጤት ቢመጣ እሱ እንጅ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ አትሆንም፡፡
  2. የወያኔና የሸአቢያ ፀብ የውሸት እንጅ እውነተኛ አይደለም እዛ ብንሔድ መልሶ ነው አሳልፎ ለወያኔ የሚሰጠን ወይም የሚፈጀን፣ ፀባቸው የእውነት ቢሆንም ወያኔና ሸአቢያ ቀደም ሲል ከነበራቸው ጥምረት ቁርኝትና ዝምድና አንጻር ለሸአቢያ ከወያኔ ይልቅ እኛ ቀርበነው ይሄንን ያህል ውለታ ሊውልልን አይችልም፣ ሊታመንልን አይችልም፣ ሸአቢያ ለኢትዮጵያ ከወያኔ የባሰ ሸረኛ ጠንቀኛ ጠላት ነው ብሎ ከመጠራጠር፡፡
  3. የታጠቀ ኃይል የምንፈልገውን ዓይነት ለውጥ ሊያመጣ አይችልም፣ በአፈሙዝ የሚገኝ ዲሞክራሲ (መስፍነ ሕዝብ) የለም፣ የታጠቀ ኃይል የራሱን እንጅ የሕዝብን ፍላጎት አያሟላም፡፡ ከሚል ዓለም አቀፋዊውን ነባራዊ ሁኔታ ካልተገነዘበ አስተሳሰብ፡፡
  4. በዘመነ ደርግ ወያኔና ሸአቢያ ደርግን ሲታገሉ በነበረበት ወቅት የስንቅና ትጥቅ (logistics) ሌላም ድጋፍ ያደርጉላቸው እንደነበሩ ሀገራትና አንዳንድ አካላት በዚህ ዘመን ለእኛ ሊያደርግልን የሚችል ባለመኖሩ በቂ ስንቅና ትጥቅ ሊገኝ ስለማይችል ከንቱ ድካምና ከንቱ መሥዋዕትነት ነው ከሚል፡፡
  5. ሸአቢያ እኛን ይዞ ወያኔን ለማስፈራራትና ከወያኔ የሚፈልገውን ለማግኘት እንጅ የምናደርገው ትግል ፍሬ እንዲያፈራ ለስኬት እንዲበቃም በፍጹም አይፈልግም፡፡ የሚሉ ምክንያቶችን ያቀርባሉ፡፡

እነኝህ ሥጋቶች ጥርጣሬዎችና ስሞታዎች ተጨባጭና ትክክለኛ ስለመሆናቸው መፈተሽ ይኖርብናልና እንደ ቅደም ተከተላቸው እንፈትሻቸው፡-

  1. “ሸአቢያ ራሱ ስላልቻለ አቅም ስለሌለው በእኛ ተጠቅሞ ወያኔን ለመበቀል ለማስወገድ ነው እንጅ በፍጹም በፍጹም ሸአቢያ ለኢትዮጵያ በማሰብ ይሄንን ድጋፍ ሊያደርግ አይችልም፡፡ ሸአቢያ በዚህ ዓላማው ምክንያት በሚያደርግልን ድጋፍ ውጤት ቢመጣ እሱ እንጅ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ አትሆንም” የሚባለው ነገር ሸአቢያ እንዲህ ዓይነት ሐሳብ ሊኖረው ቢችልም እንኳን የእኛ ጠላት የሆነው ለሸአቢያም ጠላት መሆኑ ጥሩ ዕድል መፍጠሩን በመረዳት የጋራ ጠላትን አንድ ግንባር ፈጥሮ ወይም ተረዳድቶ ማጥቃቱ ማጥፋቱ ስልታዊ አኪያሔድ እንጅ ጉዳቱ ምኑ ላይ ነው? ይሄንን ሥጋት የሚያነሡ ወገኖች ይሄንን ያላቸውን ሥጋት በደፈናው ከመናገር በስተቀር ወያኔ በዚህ ጥምረትና መረዳዳት ቢጠፋ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ የማትሆንበትን ምክንያት በግልጽ እንዲህ እንዲህ ነው በማለት አያስረዱም፡፡ በደፈናው ከመጠራጠር በስተቀር የሚሉት ነገር የላቸውም፡፡ ስገምት ግን የእነሡ ሥጋት “ወያኔ ሲወድቅ በወያኔ ቦታ ሸአቢያ ይቀመጥና ውጤቱ ጉልቻ መለዋወጥ ነው የሚሆነው” የሚሉ ይመስላል፡፡ ይሄም ቢሆን ግን ሥጋቱ ተጨባጭ አይደለም፡፡ ከኢትዮጵያ ተገንጥላለች የተባለችው ባሕረ ምድር (ኤርትራ) ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንደ አንድ ሀገር አውቄሻለሁ ብሏታል ከተባለ በኋላ ሸአቢያ አዲስ አበባ ገብቶ ሥልጣን ሊይዝ የሚችልበት ምንም ዓይነት ሁኔታ አጋጣሚ አሠራር የሌለና ሊታሰብም የሚችል ባለመሆኑ ተደርጎ ቢገኝም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሕግ መሠረት “ወረራ” ተብሎ የሚወገዝና ወረራው በአባል ሀገራት የትብብር ጥቃት እንዲቀለበስ የሚደረግ በመሆኑ ሥጋቱ ተጨባጭ ያልሆነና ሊገመትም የሚገባ አይደለም፡፡
  2. “የወያኔና የሸአቢያ ፀብ የውሸት እንጅ እውነተኛ አይደለም እዛ ብንሔድ መልሶ ነው አሳልፎ ለወያኔ የሚሰጠን ወይም የሚፈጀን፣ ፀባቸው የእውነት ቢሆንም ወያኔና ሸአቢያ ቀደም ሲል ከነበራቸው ጥምረት ቁርኝትና ዝምድና አንጻር ለሸአቢያ ከወያኔ ይልቅ እኛ ቀርበነው ይሄንን ያህል ውለታ ሊውልልን አይችልም፣ ሊታመንልን አይችልም፣ ሸአቢያ ለኢትዮጵያ ከወያኔ የባሰ ሸረኛ ጠንቀኛ ጠላት ነው ብሎ ከመጠራጠር” ይሄ ደግሞ በጣም አስቂኝ ነው፡፡ ሰው አይጠርጥር አይጠንቀቅ አይባልም በተለይ በእኛ ሁኔታ መጠራጠርና መጠንቀቅ ተገቢና አስፈላጊም ነው፡፡ ነገር ግን የጠረጠርነውን ነገር ሊያስወግዱ ሊቀርፉ የሚችሉ ያሉና የሚታዩ ተጨባጭ ኩነቶች ባሉበት ሁኔታ አንድ ሰው በዚህ ደረጃ ተጠራጥሮ የማይመስል ነገርን ሲያስብ ብታገኙት ይሄ ሰው በጤነኛና ትክክለኛ የአእምሮ ጤና ውስጥ እንዳልሆነ እርግጠኛ ልትሆኑ ትችላላቹህ፡፡ ለእንደዚህ ዓይነት መስመር የሳተ አስተሳሰብ የሚዳረጉ ሰዎች እንዲህ ሊሆኑ የሚችሉበት ምክንያት ሲመረመር እንዲህ ብለው በሚጠረጥሯቸው በሚያስቧቸው አካላት ከባድ የሥነልቡና ጫና መታወክና መረበሽ የደረሰባቸው ሆነው ይገኛሉ፡፡ ከዚህም የተነሣ እነዚያን የሚጠረጥሯቸውን አካላት በተመለከተ ሊያደርጉትና ላያደርጉት ሊችሉትና ላይችሉት ሊሠሩትና ላይሠሩት ይችላሉ ብለው የሚያስቡት የሚገምቱት ሲመረመር ከሞላ ጎደል ትክክለኛ ሆኖ አይገኝም፡፡ ሥጋቶቻቸውና ጥርጣሬዎቻቸው ከታወከ ሥነልቡናቸው የሚመነጩና ከገሀዱ ዓለም ተጨባጭ እውነታዎች የራቁ ሆነው ይገኛሉ፡፡ ያሉ ነገሮችንም በተጨባጭ ካሉ ከተፈጸሙ መሬት ላይ ከሚታዩ ነገሮች አንጻር መመዘን መለካት የሚፈልጉ አይደሉም፡፡

ይሁንና ምናልባት ያሉበትን ተጨባጭ ያልሆነ ምናባዊ አስተሳሰብ ማሰብ ማገናዘብ መረዳት ያስችላቸው እንደሆነ ከሚል እንዲህ ለሚሉ ሰዎች ላነሣቸው የምፈልጋቸው ጥያቄዎች አሉኝ፡- ሀ. የሸአቢያና የወያኔ ጸብ የውሸት ከሆነ የዚህ የውሸት ጸባቸው ምክንያት ዓላማና ግብ ምንድን ነው? ለ. ጸባቸው የውሸት ከሆነ ወያኔና ሸአቢያ ለ17 እና ለ30 ዓመታት ደርግን ሲታገሉ ከእያንዳንዳቸው ወገን ካለቀባቸው ሠራዊት በላይ በዚያች በአጭር ጊዜ ጦርነት ባደረጉት ጦርነት ብቻ ከእያንዳንዳቸው ወገን ሰባ ሰባ ሽህ የሚገመት ሠራዊት ላለቀበት አስከፊ ጦርነትስ እንዴት ሊዳረጉ ቻሉ? ሐ. ከዚያ አሰቃቂ ጦርነት በኋላስ ባሕረ ምድር (ኤርትራ) ከዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ ተነጥላ በማዕቀብ ስር ሆና ሕዝቧም ለአስቸጋሪ የድህነት ኑሮ ተዳርጎ እስከ አሁንም ድረስ በከባድ ችግር ለማለፍ እንዴት ልትገደድ ቻለች? የሚሉ ጥያቄዎችን ለራሳቸው ለመመለስ ቢሞክሩ ጭንቅላታቸውን ወደ ትክክለኛውና ጤነኛው አስተሳሰብ ለመመለስ ይረዳቸው ይሆናል ብየ አስባለሁ፡፡ አንዱ እንዲህ ዓይነት ችግር ያለበት “ጋዜጠኛ” እማ ጭራሽ ምን አለ? “ጸባቸው የውሸት ነው” ካለ በኋላ “የውሸት መሆኑንም የሚያረጋግጠው ኢትዮጵያ ለኤርትራ በየዓመቱ 250 ሚሊዮን (አእላፋት) ዶላር ትረዳለች” በማለት ያለበትን የሥነልቡናና የሥነ አእምሮ የጤና መታወክ ደረጃ ቁልጭ አድርጎ ሊያሳየን ቻለ፡፡ ወይም ደግሞ የትጥቅ ጥግሉን ለማክሸፍ ለስውር ተልእኮ ወያኔ ከቀጠራቸው ቅጥረኞች አንዱ መሆኑን እንዲህ በል ተብሎ ሊሆንም ይችላል፡፡ ምክንያቱም ይህ ያለው ነገር የፈጠራ መሆኑን የሚያረጋግጠው አስቀድመን ከጠቀስናቸው የሸአቢያና የወያኔ ፀብ የውሸት አለመሆኑን ከሚያረጋግጡት ነጥቦች አኳያ የማይመስል ነገር መሆኑና ለወሬው መረጃውን ወይም ምንጩን መጥቀስ ያልቻለ መሆኑ ነው፡፡

ሌላው “ሸአቢያ ታማኝ አይደለም ሸአቢያ ለኢትዮጵያ ከወያኔ የባሰ ሴረኛ ሸረኛ ጠንቀኛ ጠላት ነው” ለሚለውን የዋሀን ወገኖቻችንም ይሄንን አጥብቀው ያነሣሉ፡፡ ለነገሩ እነሱን ጨምሮ የወያኔ ካድሬዎችም ጭምር ሸአቢያ ከወያኔ የባሰ ጠላት ለመሆኑ የሚጠቃቅሷቸው ነገሮች አሉ፡፡ በሸአቢያ በኩል ደግሞ እነኝህ የሚጠቀሱ ነገሮች ሐሜቶችና የወያኔ የፈጠራ ወሬዎች መሆናቸውንና እሱ ግን ከድሮ ጀምሮ ለኢትዮጵያ በማሰብ ቀና ቀና ነገሮችን ሲያደርግ እንደቆየ ቢናገርም እንዲያው አንዳችም የፈጸመብን ክፉ ተግባር የለም ማለት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ምንስ ቢሆን ሲዋጋ የኖረው ከእኛ ጋር መሆኑ ቀረ እንዴ! ጠላቱ አድርጎ የሚያስበንን ለመጉዳት ለማጥቃት ለማዳከም የማይመኘን የማይጥርብን ምን ያህል ታጋሽ አርቆ አሳቢ በሳል ይቅር ባይ ቢሆን ነው? እንኳንና የሚጠቀሱ ነገሮች እያሉ የቱንም ያህል ደግ አሳቢ ቅኖች የነበሩ ቢሆኑም እንኳ የዚህን ያህል ሊያመጻድቅ የሚችል ሥራ ሊኖራቸው እንደማይችል መገመት የሚቻል ይመስለኛል፡፡

ነገር ግን ይህ የሸአቢያ መልካም ሥራ እውነት መሆኑን ማጣቀሻዎችን እያነሡ የመሰከሩ የአንዳንድ ወገኖች ምስክርነትንም ሰምተናል፡፡ እንደኔ እንደኔ ሠራው የተባለው ክፋት እውነት ቢሆንም እንኳን ሊያስደንቀን የሚገባ አይደለም፡፡ በጠላትነት ተፈራርጀን ስንተላለቅ የኖርን ሰዎች ሆነን እያለ አንዳችም ክፉ ነገር እንዲያደርግብን መጠበቅ የኛን የዋህነት ሊያስይ ቢችል እንጅ ሊሆን የባይገባው ነገር መደረጉን የሚያሳይ አይመስለኝም፡፡ ምን ነካቹህ? በቀንደኛ ጠላትነት ተፈራርጀን ለ30 ዓመታት እኮ ነው ጦርነት ስናደርግ የኖርነው! እኛ እነሱን ልናጠፋ እነሱም እኛን ሊያጠፉ፡፡ ዛሬ ላይ ግን ያ ትግላቸው ለስኬት አብቅቷቸው የትግላቸውን ፍሬ እየለቀሙ ያሉበት ደረጃ ላይ በመሆናቸውና ትግላቸው “ያተረፉበት ወይስ የከሰሩበት? መሆን መደረግ የነበረበት ወይስ ያልነበረበት?” የሚል ጥያቄን ለራሳቸው እንዲያነሡ የተገደዱበት ወቅት ላይ ያሉ በመሆኑና ለትግል ያስወጣቸው ችግሮች የነበሩ ከሆነም እንኳን እነዚያን ችግሮች በሌላ መንገድ መፍታት ይቻል የነበረበትን አማራጭ መፈለግ የተሻለ እንደነበር የተረዱበት ወቅት ላይ ያሉ በመሆናቸው እድሜ የማያስተምረው የማያበስለውም የለምና ከዕድሜና ከተሞክሮም በመማራቸው ከዚህ አንጻር በዚያ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ የሠሩት የፈጸሙት ሸር ሴራ ወንጀል ተንኮል ክፋት ቢኖርም እንኳን የሚጸጸቱበት እንጅ የሚኮሩበት ባለመሆኑ እንደቀድሟቸው ሁሉ አሁንም እንደዚያው ያደርጋሉ ያስባሉ በማለት ፍጹም አትጠራጠሩ ባልልም ድምዳሜ ላይ መድረሱ ግን የሚገባ ነው ብየ አላስብም፡፡

የወያኔ ካድሬዎች ተቀጣሪዎችና የዋሀን ወገኖች የፈለጉትን ሲያወሩ ለሸአቢያ የነበረን ሥዕል ከድሮው መጥፎ መሆኑ ስለ ሸአቢያ መጥፎነት ምንም ነገር ቢባል በቀላሉ እንድናምን እያደረገን ወደ እውነቱ እንዳንደርስ የተጫነን መስሎ ይሰማኛል፡፡ እኔ እንዲያውም አሁን አሁን እየተረዳሁት የመጣሁት ነገር ቢኖር በሸረኝነት በክፋተኝነት በጠንቀኝነት በሴረኝነት በጠላትነት ወያኔ ሸአቢያን እጥፍ አስከንድቶ የሚበልጠው መሆኑን እንጅ የሚያንሰው አለመሆኑን ነው፡፡ በግልጽ አማርኛ ከመጀመሪያውም ጀምሮ ከሸአቢያ ይልቅ ወያኔ እጅግ በጣም የከፋ ሸረኛ ሴረኛ ክፉ ጠላት ነው፡፡

ይሄንን ልታረጋግጡ የምትችሉበትን አንድ ሁለት ነገሮችን ላንሣላቹህ፡፡ ከ1990ዓ.ም. የወያኔ ሸአቢያ ጦርነት በኋላ እነ አቶ ኢሳይያስ ከዓለሙ ማኅበረሰብ የተነጠሉ መሆናቸውን ታውቃላቹህ፡፡ ለምዕራባዊያን ከኢትዮጵያ ይልቅ ባሕረ ምድር (ኤርትራ) ስልታዊ (strategic) ጠቀሜታ ያላት ነች፡፡ የወያኔ ሸረኝነት ሴረኝነትና ዋሽቶ የማሳመን ችሎታ ከሸአቢያ እጅግ የላቀ መሆኑ ባሕረ ምድር እንዲህ ዓይነት ስልታዊ ጠቀሜታ ያላት መሆኗ በቀላሉ ምዕራባዊያንን ከጎኗ ማሰለፍ የሚያስችላት ሆኖ ሳለ በጠቀስነው ችሎታ ወያኔን ስላልቻሉትና በዲፕሎማሲው (በአቅንኦተ ግንኙነቱ) ላይ የበላይነቱን በመያዙ ከጨዋታ ውጪ እንዳደረጋቸው ዓይተናል፡፡ ይሄው እስከዛሬም በአሳዛኝ ተሸናፊነት ተገልለው እንዲቀሩ አድርጓቸው ቀርቷል፡፡ ከሸአቢያ ያየነው ብቃት ቢኖር የዘመኑን የፖለቲካ ጨዋታ ባለመረዳት ከሁኔታዎች ጋር እንደወያኔ እየተጣጠፈ በብልጠት ጥቅሙን ማስከበር ሳይችል በግትርነት በድርቅና መጽናቱን ብቻ ነው፡፡

ይሄ ሽንፈት በድንበር ዳኝነቱ (ኮሚሽኑ) ውሳኔ ጊዜም ተደግሟል የዳኝነቱ ውሳኔ ትክክል ባይሆንም የድንበር ኮሚሽኑ (ዳኝነቱ) ይግባኝ በሌለው ውሳኔ ባድመን ለባሕረ ምድር የወሰነ ሆኖ እያለ ከሸአቢያ ችሎታ ማነስና ደካማነት ከወያኔ መሠሪነት ሸረኝነት የተነሣ ውሳኔው ተፈጻሚ መሆን እንዳይችል አድርጎታል፡፡ እንግዲህ ሸአቢያ ሊጠቀምባቸው መብቴ ነው የሚለውን ሊያስጠብቅበት የሚያስችለው ዕድሎችና አንዳንድ ነገሮች ቢኖሩትም ከደካማነቱ የተነሣ ጥቅሙን ማስጠበቅ ያልቻለ አካል ነው፡፡ ከእነዚህ ሁለት ሁኔታዎች የምንረዳው የወያኔንና የሸአቢያን በጣም የተራራቀና የማይመጣጠን የብቃትና የችሎታን አቅም ነው፡፡ እንደምናስበውና ከየዋሀን ወገኖቻችን ከወያኔ ቅጥረኞችና ካድሬዎች በሰፊው እንደሚወራልን ሸአቢያ ከወያኔ የላቀ የበለጠ መሠሪ ሸረኛ ብቃትና ችሎታ ያለው ቢሆን ኖሮ አይደለም ከወያኔ በበለጠ በተሸለ በምዕራባዊያኑ ተመራጭ ተፈላጊ ሊያደርገው የሚችሉ ነገሮች እያሉት ቀርቶ ባይኖረውም እንኳ የበላይነቱን ይዞ ልናየው በቻልን ነበር፡፡ የሆነው ግን የተገላቢጦሹ ነው ስልታዊ ጠቀሜታ እንደሌለውና በድንበር ኮሚሽኑ እንደተሸነፈ ሆኖ ከዓለም ዓቀፉም ኅብረተሰብ ተነጥሎ ተገልሎ ይሄ ሳያንሰው ማዕቀብ ተጥሎበት በማዕቀብ እየታሸ ለመኖር የተገደደ መሆኑ ነው፡፡

እዚህ ላይ አንዳንድ ሰዎች ምናልባት ሸአቢያ ምዕራባዊያኑን ከጎኑ ሊያሰልፍ የሚችልበት ጥቅም እያለው ምዕራባዊያኑ ከሸአቢያ ጎን ሊቆሙ ያልቻሉበትና ከወያኔ ጎን ሊቆሙ የቻሉበት ምክንያት “ወያኔ አልሸባብን አጥፍቶ ሱማሌን የተረጋጋችና መንግሥት ያላት ሀገር እንዲያደርግላቸው ስለሚፈልጉ እዚያ ላላቸው ጥቅም ወያኔን ስለሚፈልጉት ነው” የሚሉ ሊኖሩ ይችሉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን እውነት እንነጋገር ከተባለ የምዕራባዊያኑ ፍላጎትና ጥቅም እውን ሶማሊያ የተረጋጋች ሀገር እንድትሆን ነው ወይ? እንዳልሆነ ሊቢያ ላይ ምን ብለው ምን አድርገዋቸው እንደቀሩ የታየውና የምናውቀው ነው፡፡ አፈራርሰዋት የአሸባሪዎች መፈንጫ አድርገዋት ቀሩ እንጅ ቃል የገቡትን የመልሶ ማቋቋሚያ ገንዘብ ሰጥተው መስፍነ ሕዝባዊ (ዲሞክራሲያዊ) መንግሥት እንዲመሠርቱ ሲረዷቸው ፈጽሞ አልታዩም፡፡ በመሆኑም የምእራባዊያኑ ጥቅምና ፍላጎት ሶማልያን ማረጋጋትና ባለመንግሥት ማድረግ ሆኖ ባሕረ ምድር ካላት ስልታዊ ጠቀሜታነት አንጻር ከሷ ሊያገኙት የሚችሉት ጥቅም ወያኔ ሱማሌ ላይ ከሚሰጣቸው ጥቅም በልጦባቸው አይደለም ከሸአቢያ ይልቅ ወያኔ በልጦባቸው ከወያኔ ጋር ሊቆሙ የቻሉት፡፡

እናም አትጠራጠሩ የከፋው የባሰው የላቀው መሠሪ ሸረኛና ሴረኛ ወያኔ እንጅ ሸአቢያ አይደለም፡፡ ሸአቢያ እንኳንና ፈጥሮ ፈልስፎ አሲሮ ጥቅሙን ሊያስጠብቅ ይቅርና በያዘው ጥቅሙን ሊያስጠብቅ የሚያስችሉትን ዕድሎች በመጠቀም ሌላው ቀርቶ ያንተ ነው የተባለለትን ውሳኔ ጥቅሙን ማስጠበቅ ያልቻለ ምስኪን ተሸናፊ ነው፡፡ ይህ ነገር ስለ ሸአቢያ መጥፎነት የመሠሪነት ብቃትና ችሎታ ሲወሩ ሲነገሩን የነበሩ ነገሮች ሁሉ እውነትነታቸውን እንደገና መለስ ብለን እንድናይ እንድንፈትሽ የሚያስገድደን ይመስለኛል ይገባልም፡፡ ቢያንስ የተባለው ሁሉ እውነት እንዳልሆነ የሚያረጋግጥ ይመስለኛል፡፡ ጥቂቱ እንኳ እውነት ሊሆን ቢችል አስቀድሜ እንደገለጽኩት ለምን እንዴት ብሎ መጠየቅ ድርጊቱንም ማውገዝ ተገቢ ቢሆንም ከነበሩ የጦርነት ነባራዊ ሁኔታዎች አንጻር በምንም ተአምር መፈጸም አልነበረበትም ማለቱና በዚህም ላይ ተመሥርቶ የመጨረሻ ድምዳሜ ላይ መድረሱ ግን እጅግ እጅግ የዋህነትና እጅግም አለመብሰል ነው፡፡ በቤተሰብ መሀከል በጥቅም ምክንያት ወንድም በወንድሙ እኅት በእኅቷ ወንድም በእኅቱ ልጆች በወላጆቻቸው ወላጅ በልጆቹ ክህደት እየፈጸመ በሚባላበት ዘመን ጠላት ተደራርገው አንዱ ሌላውን ለማጥፋት በሚታገል በታጠቀ ሠራዊት መሀከል አንዳንድ ነገሮች መፈጸማቸው አይቀርምና ይሄና ያ እንዴት ለምን ማለትና ምንም ነገር እንዲፈጸም አለመጠበቅ ያንን የተፈጸመውን ጉዳይም የነገሮች መጨረሻ አድርጎ መቁጠር አሁንም እላቹሀለሁ እጅግ የዋህነትና አለመብሰል ነው፡፡ ምን ነካቹህ እቃቃ ስናጫወት እኮ አይደለም የኖርነው በጦርነት እሳት ስንለባለብ እንጅ፡፡ በፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ የሚታየው ዛሬ እንጅ ትላንት አይደለም በዓለማችን ትላንት ሲባሉ ሲቧጨቁ ሲጠፋፉ የነበሩ ዛሬ ላይ ግን እፍ ያለ ፍቅር ውስጥ የገቡ በርካታ ሀገራትንና ቡድኖችን መጥቀስ ይቻላል፡፡

የሆነ ሆኖ ይሄንን ሁሉ እንዳለ ተውትና ያልገባቸው ወገኖችም ሆኑ ወያኔ የገዛቸው ቅጥረኞች የሚናገሩት ክስ አንድም ሳይቀር ሁሉም እውነት እንደሆነ እንቁጠረውና ለወያኔ ከተገዙትና ከወያኔ ካድሬዎች በስተቀር የኢትዮጵያ ሕዝብ ለወያኔ የተገዙና የወያኔ ካድሬዎች የሚያወሩትን ሳይሰማ ትግሉን ተቀላቅሎ ለድል የሚበቃበትን መንገድ ስናገር የሚከተለውን ይመስላል፡- የነጻነት ትግል ማለት ምንም ዓይነት መሰናክልና የፈተና ዓይነት እንቅፋት የሚያግደው የሚያደናቅፈው የሚገታው እንዲያግደው እንዲገታው እንዲያደናቅፈውም የማይፈቅድ ሁልጊዜም በተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ ሳይሆን ባልተመቻቸና እንቅፋት መሰናክሎች ፈተናዎች በበዙበት ሁኔታ የሚደረግ የማይመቹ ሁኔታዎች ስላሉ በፍጹም ከመደረግ የማይቆም የማይቀር፤ ያለው ዕድል ከጠጉር የቀጠነ ዕድልም እንኳ ቢሆን በከፍተኛ ጽናት ትዕግሥትና ብልጠት እሱን ተጠቅሞ ዓላማውን ለማሳካት ከፍተኛ ትግልና ትንቅንቅ የሚደረግበት ሌላው ቀርቶ ምንም ዓይነት ዕድልም እንኳ ባይኖር ራሱን ዕድሉን ፈጥሮ ግቡን ለማሳካት የሚደረግ መራራ ትግል እንጅ እንደ ሽርሽር ምቹ ሁኔታዎች የሚጠበቁበት የትግል ዓይነት አይደለም፡፡

እናም አኔ የምላቹህ የወያኔ ቅጥረኞችና ካድሬዎች እንደሚያወሩት ሸአቢያ ከወያኔ የከፋና የኢትዮጵያ ቀንደኛ ጠላት ቢሆንም እንኳ ትግላችን የነጻነት ትግል በመሆኑና በምንም የሚመለስ ሊመለስም የሚገባ ባለመሆኑ እንኳንና ይሄንን ያህል ዕድል ተፈጥሮ ቀርቶ ምንም ዓይነት ዕድል ባይኖርም ራሱ ዋሽተን ወስልተን ቀጥፈን ሌሎች የብልጠት መንገዶችን ተጠቅመንም ቢሆን ዕድሉን ፈጥረን ግባችንን የማሳካት ግዴታ ያለብን በመሆኑ ሸአቢያ እንዳሉት ቢሆንም እንኳ ባለፈው ጊዜ እንዳልኳቹህ የልባችንን በልብ አድርገን መዋሸት ካለብን እየዋሸን “ቃል ግቡልኝ ፈርሙልኝ ማሉልኝ እንዲህ እንዲህ ታደርጉላኛላቹህ” ቢልም በፍጹም እንደማታደርጉት ልባቹህ እያወቀም አንኳ “እሽ ምን ችግር አለው! የፈለከውን እናደርጋለን! እኛ ሎሌህ ደጋፊዎችህ አጋሮችን ነን! ላንተ የማንሆነው የማናደርገው ነገር የለም!” እያልን ግጥም አድርገን በዐሥር ጣታችን በመፈረም እርኩስ ክፉ መሠሪ መሆኑን ብናውቅም “ደግ ቅንና ቅዱስ ነህ!” እያልን “ሸአቢያ ሽህ ዓመት ይንገሥ በሉ!” ቢል “ለምን ሽህ ዓመት ብቻ ለዘለዓለም ኑርልን!” እያልን ሥራችንን በመሥራት ይሄንን ክፉ ቀናችንን ዛሬን ተሻግረን ግባችንን አሳክተን ከነጻነቱ ቀን ነገ ላይ መድረስ ግድ ይለናል፡፡ ዕድል ባይኖርም ዕድል መፍጠር ይሉሀል ይሄ ነው፡፡ እንዲህ የምናደርገው ለምንድን ነው? እውነት ከሆነ ሸአቢያ የማይወደውን አቋም በመያዛችን በሸአቢያ እንዲጠፉ ተደርገዋል እንደተባሉት ወገኖች ከመጠቃት ለመዳን ነው፡፡ በዚህ የትግል ዘመን እውነት ብቻ ተናግረን ፈተናዎቻችንን ማለፍ መሻገር በፍጹም በፍጹም አንችልም፡፡ የልብን በልብ አድርገን ማስመሰልን መዋሸትን መቅጠፍን በሚገባ ልንካንበት ይገባናል ለምን ሲባል? ለዚህች ውድ ሀገራችንና ለውዱ ሕዝባችን ህልውናና ነጻነት ስንል፡፡ ተስፋ አደርጋለሁ አሁን ነገሩ የሚገባቹህ የሚገለጥላቹህ ይመስለኛል፡፡ በመሆኑም ወያኔ ወይም የወያኔ ቅጥረኛ ካልሆንን በስተቀር ሀገራችንን የምንወድ የሀገራችንንና የሕዝባችንን ነጻነት ፈላጊ ሆነን ከዚህ ሕዝባዊ ትግል ልንሸሽ ጭራሽም ትግሉት ልንቃወም የምንችልበት ምንም ዓይነት ምክንያት እንደሌለ በሚገባ በመረዳት እያንዳንዳችን እንደየችሎታችን ትግሉን በመደገፍ የትግሉ አካል መሆን አማራጭ የሌለው መሆኑን አውቀን መንቀሳቀስ ይኖርብናል፡፡

  1. “የታጠቀ ኃይል የምንፈልገውን ዓይነት ለውጥ ሊያመጣ አይችልም፣ በአፈሙዝ የሚገኝ ዲሞክራሲ (መስፍነ ሕዝብ) የለም፣ የታጠቀ ኃይል የራሱን እንጅ የሕዝብን ፍላጎት አያሟላም፡፡ ከሚል ዓለም አቀፋዊውን ነባራዊ ሁኔታ ካልተገነዘበ አስተሳሰብ” ይህ የሥጋት ሐሳብ ላይ ላዩን ሲያዩት እውነት ይመስላል፡፡ በተለይ ደግሞ ምሳሌ ይሉና ደርግንና ወያኔን ምሳሌ አድርገው ሲያቀርቡ እውነት ይመስላቹሀል፡፡ ትንሽ ልትጠረጥሩ የምትችሉት “ታዲያ ምን ይሻላል?” ብላቹህ ስትጠይቋቸው መልስ ሲያጡ ወይም የሚሰጡት መልስ አጥጋቢ ያልሆነና ወያኔን የሚጠቅም ሆኖ ስታገኙት ነው፡፡ ምናልባት እነኝህ ቅጥረኞች የሚያነሡትን ይሄንን የሥጋት ሐሳብ የሚያነሡ ሌሎች የዋሀን የሕዝብ ወገኖች ካሉ ለነሱ ላነሣው የምፈልገው ጥያቄ ቢኖር፡- ይሄንን የሚሉ ሰዎች ለሀገርና ለሕዝብ ታማኝ ከሆኑና ይሄንን ቅን ዓላማቸውን ይዘው የሚታገሉ ከሆነ ወያኔን አባራሪዎቹና እንደተመኙት ሁሉ ሕዝብን የሥልጣን ባለቤት የሚያደርጉት እነሱው አይደሉም ወይ? ሌላ ከማርስ የሚመጣ አብሯቸው የሚገባና አንባገነን ካልሆናቹህ ብሎ የሚያስገድዳቸው አካል አለ ወይ? ዋናው የዓላማ ጽናትና ታማኝነት ነው እንጅ መሣሪያው አይደለም፡፡ ታማኝ ያልሆነ ግለሰብ ወይም አካል ካለ ሲቪል (ሕዝባዊ) ሆኖም ከሀገርና ከሕዝብ ጥቅም በተጻራሪ በመቆም ሕዝብን የሚጨቁን የራሱን ወይም የቡድኑን ጥቅም የሚያስጠብቅ ለራሱና ለቡድኑ ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥ ከመሆን እንደማይድን የብዙ ሀገራት ተሞክሮ በሚገባ ያሳየናል፡፡

በዓለማችን በጦር ኃይል የተመሠረቱ መንግሥታት አንባገነን የሆኑ እንዳሉ ሁሉ የተደላደለ ሕዝባዊና ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊ) መንግሥት እንዲመሠረት እንዲፈጠር ያደረጉም አሉ፡፡ ዋናው የዓላማ ጽናትና ታማኝነቱ ነው፡፡ በዚህ ላይ አርበኞች ግንት 7 ዓላማው ምን እንደሆነ በግልጽ አስታውቋል “የምታገለው ሕዝብ የፈለገውን የወደደውን መሾም ያልፈለገውን ያልወደደውን መሻር የሚችልበት ሥልጣን እንዲኖረው የሥልጣን ባለቤት እንዲሆን ማድረግ ነው እንጅ ወያኔን አውርጀ ሥልጣን ለመያዝ አይደለም፡፡ ወያኔን ደምስሰን የኢትዮጵያ ሕዝብ የፈለገውን የወደደውን መርጦ መንግሥት ያቋቋመ የመሠተረ ጊዜ የኛ ትግል ይጠናቀቃል” በማለት፡፡ ስለሆነም እንግዲህ እውነተኛ የሕዝብ ልጅ ካለ ለግል ጥቅም ለሥልጣን ሳይሆን ለዚህች ሀገርና ለሕዝቧ ነጻነት ለፍትሕ ለእኩልነት እታገላለሁ የሚል ካለ ቦታው አርበኞች ግንቦት 7 ነው ሔደህ ግባ፡፡

እንዲያው ነገሩን አልን እንጅ እውነተኛና ትክክለኛ ለራሱ ቡድናዊና ግላዊ ጥቅምና ፍላጎት ሳይሆን ለሕዝብ የታመነ ኃይል ታግሎ መጥቶ ይሄንን ማድረግ ቢችልና ሕዝብ የወደድከውን የፈለከውን ምረጥ ተብሎ ሙሉ መብት ቢሰጠው ከባድ መሥዋዕትነት ከፍሎ ለዚህ ክብር ያበቃውን፣ ነጻነት ያቀዳጀውን፣ የሥልጣን ባለቤት ያደረገውን፣ ለሀገሩና ለወገኑ እስከ ሞት ድረስ ራሱን የሰጠለትን ትቶ እዚህ ከሞቀ ቤቱ ቁጭ ብሎ ሲያበግነው የኖረውን፣ እንቅፋት እንኳን እንዳይመታው እራሱን ሲጠብቅ የኖረውን፣ ከሕሕብና ከሀገር ይልቅ ራሱን የሚወደውን እራሱን የሚያስቀድመውን፣ ለሕዝብና ለሀገር ሲል ምንም ዓይነት ዋጋ ለመክፈል የማይፈቅደውን፣ ድፍረት ቁርጠኝነት ጽናት የሌለውን፣ ታማኝነቱን ሀገር ወዳድነቱን ከወሬ ባለፈ በተግባር መሥዋዕትነትን እስከመክፈል ድረስ ታምኖ ዋጋ ከፍሎ ማሳየት የማይችለውን፣ የጭርታ የሰላም ጊዜ አርበኛ ተሽታሻ ተሸታሻውን የሚመርጥ ይመስላቹሀል? በፍጹም!

ወያኔ እኮ መሥዋዕትነትን እንደመክፈሉ እስከዛሬ ድረስ በተደረጉት 5 “ምርጫዎች” በኢትዮጵያ ሕዝብ ሊመረጥ ያልቻለው እኮ ወያኔ ካፈጣጠሩ ኢትዮጵያዊ ባለመሆኑ፣ ዓላማና አስተሳሰቡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሽዎች ዓመታት የገነባው የታሪኩ የአንድነቱ የማንነቱ የሥልጣኔው የእሴቶቹ ጠላት ሆኖ ከሚያውቀውና ከሚያምንበት በተጻራሪ ቆሞ ታሪኩን በማጉደፉ፣ ለማፈራረስ ጥረት በማድረጉ፣ በስንት ድካም የገነባውን አንድነቱን ጨርሶ ለማጥፋት በዘር በሃይማኖት እየከፋፈለ ለማባላት በመጣጣሩ በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ተናቀ ተጠላ፤ ከትግሬና ከትግራይ ውጪ ኢትዮጵያን ለማየት ለማሰብ የሚችልበት አቅም አልባ በመሆኑ፣ አስተሳሰቡ ዓላማው ሩጫው ሁሉ ጎጠኛ በመሆኑ ኢትዮጵያ የምትባልን ሀገር ሥዕል በጭንቅላቱ የሌለች ከሌሎቻችን ልቦናም እንድትጠፋ የሚፈልግ በመሆኑ፣ ጭራሽም ሊያፈራርሳት ነገር የሚያሴር ክፋት የሚሸርብ በመሆኑ፣ ባጠቃላይ ለታሪኳ ለማንነቷ ለሥልጣኔዋ ለእሴቶቿ ሁሉ ጠላት በመሆኑ የሀገር ክህደት በመፈጸም ከመሬቷ ጀምሮ ሌሎች ብሔራዊ ጥቅሞቿን አሳልፎ የሚሰጥ የጠላት ቅጥረኛና ባንዳ በመሆኑ ለመንግሥትነት አይደለም ለዕድር አሥተዳዳሪነት እንኳን የሚበቃ አቅም ብቃት ችሎታ ቅንነት የኃላፊነት ታማኝነት ተጠያቂነት ግልጽነት ዕውቀት ተወዳጅነት የሌለው የወንበዴ ጥርቅም ስለሆነበት እንጅ መሥዋዕትነትን ለመክፈል ቆርጠው እንደመታገላቸውማ ቢሆን ማጭበርበር ማስገደድ ማስጨነቅ ማወናበድ ሳያስፈልጋቸው ዕድሜ ልኩን ያለ እነሱ የሚመርጠው ባልነበረ ነበር፡፡ ምክንያቱም ሕዝብ የሚወደውን እስከ ሞት ድረስ የሚታመንለትን ዋጋ የሚከፍልለትን የሚያከብረውን ይወዳልና፡፡ እሱም በተራው የመጨረሻውን ክብር ሰጥቶ ያከብራልና፡፡ የዛኑ ያሕል ደግሞ እስከ ሞት ድረስ መሥዋዕትነትን ለመክፈል የታመነ ቢሆንም እንኳ እንደወያኔ ሁሉ ለጥፋትና ለወረደ ለጠባብ የጥፋት ዓላማ መሥዋዕትነትን የከፈለ ሲያጋጥመው እጅግ ይንቃል ይጠላል ያወግዛል ይረግማል ያገላል ያዋርዳል ይጸየፋል ያንቋሽሻል ያበሻቅጣል እንደ መርገም ጨርቅ ይመለከታል፡፡

  1. “በዘመነ ደርግ ወያኔና ሸአቢያ ደርግን ሲታገሉ በነበረበት ወቅት የስንቅና ትጥቅ (logistics) ሌላም ድጋፍ ያደርጉላቸው እንደነበሩ ሀገራትና አንዳንድ አካላት በዚህ ዘመን ለእኛ ሊያደርግልን የሚችል ባለመኖሩ በቂ ስንቅና ትጥቅ ሊገኝ ስለማይችል ከንቱ ድካምና ከንቱ መሥዋዕትነት ነው” ለሚለው፡- እርግጥ ነው በዚያን ዘመን ወያኔና ሸአቢያ ሲያገኙት የነበረውን ዓይነት ድጋፍ ከእነኛው ሀገራት ማግኘት አንችል ይሆናል፡፡ ይሁንና በዚህ በኩል ያለውን ክፍተት ሸአቢያ ጦርነቱ የእኛ ብቻ ሳይሆን የራሱም መሆኑን በሚገባ ስለሚያውቅ ከምንም በላይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከወያኔ ነጥለው አርቀው ብቻውን ማስቀረት የሚችሉና የኢትዮጵያን ሕዝብ ድጋፍ ማግኘት ከጎናቸው ማሰለፍ የሚችሉ እንዲህ ዓይነት አጋዥ ኃይል ማግኘቱን ቢሳልም የማያገኘው ወርቃማ ዕድል መሆኑን ጠንቅቆ ስለሚያውቅ በስንቅና ትጥቅ በኩል ያለውን ክፍተት ሸአቢያ ለእኛ ብሎ ሳይሆን ለራሱ ብሎ የሚያደርገው የሚያቀርበው በመሆኑ ይሄ የሚያሳስብ ጉዳይ አይደለም፡፡ እነ አቶ ኢሳይያስ በግልጽ እንዳስታወቁት “ላደረኩላቹህና ለማደርግላቹህ ድጋፍ ምንም ዓይነት ምላሽ አልፈልግም የተረጋጋች የበለጸገች እኩልነትና ፍትሕ የሰፈነባት ሰላማዊት ኢትዮጵያን ብሎብ የተረጋጋና ሰላማዊ የቀጠናው ሀገራት እንዲኖሩ ካለኝ ጽኑ ዓላማ ያደረኩትና የማደርገውም በመሆኑ” በማለት ያስታወቁና ለመካስም ካላቸው በጎና ቁርጠኛ አቋም በመነሣት የተዋሐደችና ጠንካራ ምሥራቅ አፍሪካን ለመፍጠር ካላቸው የተቀደሰና ታላቅ ርእይ አንጻር ይሄንን ለማሳካት ያስችል ዘንድ መሠራት ያለባቸውን ሥራዎች እየሠሩ እንደሆነ አምነው ታሪክ ሠርቶ ለማለፍ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ዓላማቸውን ከረጅም ጊዜና ከአጭር ጊዜ አቅድ አኳያ ግልጽ ያደረጉ በመሆኑ “እነ አቶ ኢሳይያስ ለዚህ ሁሉ ውለታ ምላሽ ሳይፈልጉ ይሄንን ሁሉ ነገር ሊያደርጉልን አይችሉም ላደረጉትና ለሚያደርጉት ምን ልንመልስ ምን ልንከፍል ነው?” የሚያስብልና የሚያሳስብ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሁላችንም መወጣት ያለብንን ግዴታና ኃላፊነት የሚጠበቅብንንና ማድረግ ያለብንን ሥራ ነው እየሠራን ያለነው፡፡

ይሁን እንጅ ለሀገራችንና ለሕዝባችን በማሰብ ታጋይ ወገኖቻችን የማይሆን ውለታ (commitment) ውስጥ እንዳይገቡ የምንሠጋና እንዲገቡም የማንፈልግ ከሆነ ለእኛ ነጻነትና ጥቅም ሲሉ ሁለንተናቸውን አሳልፈው የሰጡ እነሱ እንኳን እንዳሉ በማሰብ እያንዳንዳችን ከተረፈን ሳይሆን ምቾታችንን ቆጠብ በማድረግ “ለእኛ ይቅርብን! እኛን ይቸግረን!” ብለንም ቢሆን ትርጉም ያለው ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ በወሬና ከንፈር በመምጠጥ ወይም በማጨብጨብ ብቻ የሚገነባ የሚሠራ ምንም ነገር የለም፡፡ ተግባር ያስፈልጋል ሀገርን መውደድ በተግባር ከምናደርገው አንዳች ነገር ውጭ በምንም ሊገለጽ አይችልም፡፡ ይሄንን ማድረግ ሳይችል ወሬ ብቻ የሚያወራ ካለን ሊያመጣው የሚችለው ለውጥ ካለመኖሩም በላይ ለወያኔ ዕድሜ መርዘም የራሱን እገዛ በማበርከቱ በሀገር ላይ የሚደርሰው ጉዳትና ኪሳራ ከወያኔ በማይተናነስ መልኩ በታሪክ ተጠያቂ እንደሆንን ልንገነዘብ ይገባል፡፡

በተለይ በተለይ ሀገር ብዙ ወጪ አውጥታባቹህ ሳይማር አስተምሮ ተቸግሮ አሳድጎ ነገር ግን በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች (push factors) ከሀገራቹህ ተሰዳቹህ እናንተ እዚህ እንድትደርሱ ሽራፊ ሳንቲም ያላወጣባቹህን የባዕድ ሕዝብና የባዕድ ሀገር በማገልገላቹህ ሀገራቹህን ሕዝባቹህን ባለማገልገላቹህ ውለታውን ለመክፈል ባለመቻላቹህ ቁጭት የሚያንገበግባቹህ የሚቆጫቹህ የሚከነክናቹህ ዕረፍት የነሳቹህ ወገኖች ካላቹህ በተለያየ ምክንያት በረሀ ወርዳቹህ ትግሉን በአካል መቀላቀን ባትችሉም ለዚህ ሕዝባዊ ትግል ትርጉም ያለው ድጋፍ በማድረግ ሀገርራቹህን ልታገለግሉ ባለመቻላቹህ የተሰማቹህን ቁጭት ጸጸት በዚህ መወጣትና ሀገር ወገናቹህን መካስ እንደምትችሉ እንዲሁም ደግሞ  ጉልበታቹህን ዕውቀታቹህን ችሎታቹህን በባዕድ ሀገራት በማፍሰስ ዕድሜያቹህን የፈጃቹህና በዕድሜ መግፋት ምክንያት ከዚህ በኋላ በዕውቀታቹህ በጉልበታቹህ በችሎታቹህ ሀገራቹህንና ሕዝባቹህን ማገልገል የማትችሉ ጡረተኛ ወገኖች ሁሉ ካፈራቹህት ካላቹህ ገንዘብና ንብረት ቁጭታቹህን ጸጸታቹህን ሊያስወግድላቹህ ሊያስወጣላቹህ የሚችል መጠን ያለውን ገንዘብ ለትግሉ በማበርከት መንፈሳዊ እርካታን እንድታገኙ ይንን አጋጣሚ እንድትጠቀሙበት ላመለክታቹህ እወዳለሁ፡፡

የሞቀ ቤታቸውን ቅንጡ ኑሯቸውን ከፍ ያለ ደረጃቸውን ሁለነገራቸውን ጥለው ለእኔና ለእናንተ ለሚወዷት ሀገራቸው ሲሉ ነፍሳቸውን እስከመስጠት ታምነውና ቆርጠው በረሀ የገቡ ፕሮፌሰር ዶክተር ኢንጂኒየር… ወገኖቻችን ግንባር በግንባር ተፋጠው ዕላያቸው ላይ የሚወርድባቸውን ዝናብና ፀሐይ ሳይማረሩ ከሞት ጋር ተፋጠው ለማሸለብ ፋታ አጥተው ያገኟትን ተቃምሰው በረሀብ እየተፈተኑ እነኝህንና ሌሎችንም ሁሉ ዋጋ እየከፈሉ ያሉ መሆናቸውን እያወቃቹህ ከሞቀ ቤታቹህ ሆናቹህ ይህንን ማድረግ ይከብዳቹሀል ለማለት እጅግ ይከብደኛል፡፡

  1. “ሸአቢያ እኛን ይዞ ወያኔን ለማስፈራራትና ከወያኔ የሚፈልገውን ለማግኘት እንጅ የምናደርገው ትግል ፍሬ እንዲያፈራ ለስኬት እንዲበቃም በፍጹም አይፈልግም” ይሄንን የሚሉ ሰዎች ምን ይጠቅሳሉ ለምሳሌ ይሉና “የአርበኞች ግንባር ትግል ከጀመረ 16 ዓመታት ሆኖታል፡፡ ይሄንን ሁሉ ዓመታት ሲቆይ አንድም የሚጠቀስ ተግባር ለመፈጸም አልቻለም እንዲዋጋ አልተፈቀደለትም ዝም ብለው ነው እንዲቀመጡ ያደረጋቸው” ይላሉ፡፡ ይመስለኛል እንዲህ እንዲሉ ያደረጋቸው ስለትግል ስለጦርነት በቂ ግንዛቤ አለመያዛቸው ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን ባለው ሁኔታ ውጤት ያለው ጦርነትም ሆነ ሽምቅ ውጊያ በቂ ኃይል ሳይያዝ፣ በቅጡ ሳይደራጁ፣ ሕዝባዊ ዕውቅናና ድጋፍ በበቂ ደረጃ ሳይገኝ ማድረግ ታይቶ ለመጥፋት ካሆነ በስተቀር ዘለቄታ ያለው እንቅስቃሴ ለማድረግ አይቻልም፡፡ ይሄንን ቅሬታ እንደሚያነሡ ሰዎች አስተሳሰብ ቢሆን ኖሮ የአርበኞች ግንባር ባለው አነስተኛ ኃይል እንደተመሠረተ ተንቀሳቅሶ ቢሆን ኖሮ ገና ድሮ ጠፍቶ ነበር፡፡ እንደሚመስለኝ ሸአቢያም ይሄንን እንዳያደርጉ የከለከለበት ምክንያት የተጠናከረ ኃይል እስኪኖራቸው እስኪይዙ መኖራቸው መደራጀታቸው በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ በቂ ግንዛቤ እስኪያዝበት ድረስ መጠበቅ አስፈላጊ ስለሆነ ነው፡፡ በመሆኑም ይሄንን ቅሬታ የሚያቀርቡ የትግሉ አካል የነበሩ አሁን ላይ በዚህ ቅሬታቸው ምክንያት ከዓመታት በፊት ትግሉን ጥለው የወጡ ግለሰቦች በወቅቱ ሸአቢያ ይሄንን ባለመፍቀዱ ያነሡበት ቅሬታ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ሸአቢያን በጣም በጥርጣሬ ዓይን ስለምናይ ብቻ እያንዳንዷን ነገር በክፋት እየተረጎምን ለተሳሳተ ድምዳሜዎች እየተዳረግን እንደሆነ ልብ ብንል መልካም ነው፡፡ ይህ ችግር በሥራችን ላይ የራሱ የሆነ እንቅፋት ሊፈጥር ይችላልና በማስተዋል ብንራመድ መልካም ነው፡፡

አሳቢ የመሰሉ ወገኖች የሚሰጡትን ምክር ሐሳብና ተቃውሞ አሳቢ ሆነው ሳይሆን ወያኔ ገዝቷቸው ቅጥረኞች ስለሆኑ እንደሆነ በምን ልናውቅ እንችላለን?

ይሄን ለመለየት በተለይ በአሁኑ ጊዜ ብዙም የሚያስቸግር አይመስለኝም ለማንኛውም እነኝህ ነጥቦች ይጠቅማሉ ብየ አስባለሁ፡-

  1. የሚናገሩትና የሚጽፉት ነገር ከረጅም ጊዜና ከአጭር ጊዜ አኳያ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ሀገርንና ሕዝብን ሳይሆን ወያኔን የሚጠቅም ከሆነ፡፡
  2. የሚናገሩትና የሚጽፉት ነገር ትግሉን ወደኋላ ለመሳብ ለማሰናከል የሚያሴር ከሆነ፡፡
  3. አሳቢ መስለው እኩይ ሥራቸው የሚከውኑት ወሳኝና አንገብጋቢ ወቅትን (timing) እያዩ ከሆነ ማለትም ወያኔ ሥጋት በተጋረጠበት ሰዓትና አጋጣሚዎች ላይ ከሆነ፡፡ ለምሳሌ ባለፈው አርበኞችና ግንቦት ሰባት ውሕደት በፈጸሙ ወቅት፣ ሰሞኑን ማጥቃት በመጀመሩ ትግሉን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ወሳኝ ወሳኝ ምእራፎች በሚመዘገብበት ወቅቶች ላይ ማለት ነው እነኝህ ቅጥረኞችም ይሄንን እመርታ ሊቀለብስ የሚችል ሥራን በመሥራት እራሳቸውን ጠምደው ታይተዋል፡፡
  4. እነዚህ አሳቢ መስለው የቀርቡ ግለሰቦች ሕዝባችን ነጻ እንዲወጣ የሚያቀርቡት ተጨባጭና ጠቃሚ አማራጭ የሌለ መሆኑና “ዝም ብለን አርፈን በወያኔ መገዛት ነው የሚሻለን” የሚል ዓይነት ከሆነ፡፡

እነዚህ እነዚህ ነጥቦች ቅጥረኞችን ለመለየት ይጠቅማሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ እነዚህ ኅሊናቸውን ብቻ ሳይሆን ሁለንተናቸውን ለሆዳቸው የሸጡ ምንደኛ ግለሰቦች ለወያኔ ያደሩ ሳይመስሉ መርዘኛ ሐሳቦቻቸውን ሳይፈሩና ሳያፍሩ በነጻነት ለመናገር ለመጻፍ የሚጠቀሙበት አንድ ሽፋን አለ “ሐሳብን በነጻነት የመግለጽን መብት ከመጠቀምና ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ” በሚል ሽፋን ነው፡፡ እንዳሉትም በትክክል ሐሳብን በነጻነት ከመግለጽና ይሄንን ዲሞክራሲያዊ መብት ለመጠበቅና ለማስጠበቅ ከሚል አንጻር ያደረጉት ከሆነ ሚዛናዊነትን ሲጠብቁ ከሁለቱም አቅጣጫዎች ጠንካራ ጠንካራ ሐሳቦችን ሲያስተናግዱ ታገኟቸዋላቹህ፡፡ ነገር ግን ከሁለቱም አቅጣጫዎች ያሉ ጠንካራ ጠንካራ የመከራከሪያ ሐሳቦችንና ተሟጋቾችን የማያስተናግዱና ሚዛናዊነትንም የማይጠብቁ ወያኔን ተጠቃሚ ወደሚያደርግ ወገን የማድላት ዝንባሌ የሚታይባቸው ከሆነ ይሄንን “ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ተግባራዊ ከማድረግ” የሚለውን መብት ሥውር ተልእኮዋቸውን ለማሳካት ለሽፋን እየተጠቀሙበት ነውና ቅጥረኞች መሆናቸውን ልታረጋግጡ ትችላላቹህ፡፡

ለምሳሌ የቪኦኤው “ጋዜጠኛ” ሔኖክ ሰማእግዜር አቶ ኃይለማርያም ከተማሩበት ዩኒቨርስቲ ሊያገኙት ስለነበረውና በተቃውሞ ምክንያት እንዳያገኙ የተደረገውን ሽልማትና እውቅና ዘገባ በሠራበት ጊዜ ዘገባውን የሠራበት መንገድ ግልጽ በመሆኑ ማንነቱን ለመለየት አስቸጋሪ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ሆን ብሎ የጋዜጠኝነትን መርሖዎች ግልጽነትንና ሚዛናዊነትን ባለመጠበቅ ወያኔን ለመጥቀም በማሰብ ትክክለኛ መረጃወች እንዳይካተቱ በማድረግ ዕውነትን ያዛባ ዘገባ ሠርቷል፡፡

ይህ ሰው ይሄንን ዐይን ያወጣ ስሕተት ረዳት አብራሪ ኃይለመድኅን አበራ ቦይንግ 767 የመንገደኞች አውሮፕላንን (በረርትን) በመጥለፍ አውሮፓ ጥገኝነት የጠየቀበትን ዘገባም በተከታታይ በሠራበት ወቅት ወያኔ “አብራሪው ለረጅም ጊዜ የአእምሮ ጭንቀት ላይ ነበረ ይሄንን ያደረገው ሕመሙ ተባብሶበት ከዚህ ችግሩ የተነሣ ነው” ብሎ የደረሰበትን የፖለቲካ ኪሳራ ለመሸፋፈን ጥረት በማድረግ የሰጠውን ሐሰተኛ ስም አጥፊ መግለጫ እውነት ወይም ትክክለኛ ለማስመሰል በማሰብ አሁንም ሚዛናዊነትን ያልጠበቀና የወያኔን ጥቅም ለማስጠበቅ የጣሩ ዝግጅቶችን አቅርቦ ነበር፡፡ እናም ማንም ጋዜጠኞችም ሆኑ የብዙኃን መገናኛዎች ግልጽ የሆኑ የሞያዊ አሠራር ግድፈቶችን ሲፈጽሙ ስታዩ ያ ሰው ወያም ያ አካል ለሚከላከልለት ሀቁን ለደበቀለት (ለወያኔ) ያደረ የተገዛ የሱን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚጥር እንደሆነ ልታረጋግጡ ትችላላቹህ፡፡ እንዲህ መሆኑ በግልጽ የታወቀ ሰው በዚያ የጥፋት ዲርጊቱ ቢገለልና ቢወገዝ ተወገዝኩ ተገለልኩ ጥቃት ደረሰብኝ ብሎ ሊከስ ሊያማርር ሊወቅስ አይችልም መብትም የለውም፡፡

ምክንያቱም ጉዳይ ከሞያዊ ግድፈት አልፎ ሞያውን በማርከስ ኃላፊነትና ግዴታውንም ለግል ዓላማውና ጉዳዩ በመተላለፍ ሞያው የጣለበትን ኃላፊነት አላግባብ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ በመጠቀም ማለትም ወያኔ ወይም የወያኔ አባል በመሆኑ ሆን ብሎ የወያኔን ጥቅም ለማስጠበቅ በመሞከር ጉዳዩን ወደ የመደብ ትግል ፍትጊያ አሻግሮታልና ወይም እንዲለወጥ ያደረገ በመሆኑና የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ በወያኔ ላይ ተስፋ ቆርጦ ትጥቅ ያነሣበት ሁኔታ ላይ ያለ በመሆኑ ይህ ሰው ከመወገዝም አልፎ ቦታና ሁኔታዎች ቢፈቅዱና እርምጃ ቢወሰድበትም እንኳ ድርጊቱ ሕገ ወጥ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ የለም፡፡ ምክንያቱም በጋዜጠኝነቱ ያለውን ከለላ በሠራው ወንጀል አጥቶታልና፤ እራሱን ከጋዜጠኝነት አውጥቶ እንደ አንድ የወያኔ ታጋይ ሁሉ የወያኔ ጥቅም አስከባሪ አድርጓልና፡፡

ይህ እርምጃ ቢወሰድበት “ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ይከበር! እያሉ እነሱ ራሳቸው ይሄንን የሚያደርግን ሰው ያጠቃሉ” ተብሎ ሊገለጽ በፍጹም በፍጹም አይደባም፡፡ ይሄ ብየና አለመብሰልና አለማገናዘብም ነው፡፡ ምክንያቱም የሰውየው ሥራ ሆን ብሎ ከሞያዊ ሥነምግባሩ ውጭ በፈጸመው ስሕተት ምክንያት ሐሳብን በነጻ ከመግለጽ ጋራ ምንም የሚያገናኘው ነገር የሌለ በመሆኑና ይህ የፈጸመው ስሕተትም እራሱን እንደ አንድ የወያኔ ወታደር አድርጎ ስላቆመ ያለውን የጋዜጠኝነትም ሆነ የሌላ መብት ከለላውን ስለሚያሳጣው፡፡ ይህ ሰው ሚዛናዊነትንና ከሁለቱም ወገኖች ጠንካራ የሆኑትን ሐሳቦች ለማስተናገድ የፈቀደ ባለመሆኑ ይልቁንም ትክክለኛ መረጃዎችን ሆን ብሎ የሰወረ በመሆኑ ሐሳብን በነጻ የመግልጽ መብትን ለቅጥፈቱ ሽፋን ሊያደርግ ስለማይችል፡፡

ይሄ “ጋዜጠኛ” ሆነ ሌላ ማንነቱ የታወቀ ሰው ኢትዮጵያዊያን በሚያደርጉት ማንኛውም ኩነት ተገኝቶ ልዘግብ ቢልና ሕዝብ የሚያውቀው በወያኔነቱ በመሆኑ ከወያኔ ጋርም ልዩነታችንን በውይይትና በሌሎች ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊ) መንገዶች ልንፈታ የምንችልበት መንደግ ዕድል ተጠርቆሞ የተዘጋ በመሆኑና በቀረልን ብቸኛ አማራጭ በኃይል እርምጃ ለመፍታት መብታችንን ለማስከበር የተገደድንበት ሁኔታ ውስጥ ያለን በመሆኑ እንዲህ ዓይነቱን ሰው ሕዝቡ በራሱ ዝግጅቶች እንዳይገኝ የመከልከል የማስወገድ መብት አለው፡፡

“እነዚህ የሚከለከሉ (ከዚህ ዞር በሉልን አንያቹህ!) የተባሉ ጋዜጠኛም ሆኑ ሌሎች ግለሰቦች የወያኔ ደጋፊ ወይም ወያኔ እንኳን ቢሆኑ በመነጋገር ነው እንጅ ልዩነቱ መፈታት ያለበት ለምን በኃይል ይሆናል?” ከተባለ በመነጋገር ልዩነትን ለመፍታት 24 ዓመታት ለምነን ተማጽነን አይሆንም አይቻልም ተብለን መብታችንን ተነጥቀን ተነጋግሮ ልዩነትን የመፍቻው ዘመን አልፎ ሳንወድ በግድ ተገፍተን ወደ ሌላኛው የተተወልን ብቸኛ አማራጭ ማለትም በትጥቅ ትግል የኢትዮጵያን ሕዝብ ነጻነትና መብት የማስከበር አማራጭ የገባንበት ወቅት ውስጥ በመሆናችን እንደዚህ ዓይነት ሰዎችን ካጠገባችን እንዳይደርሱ መከልከል ማራቅ እንችላለን መብታችንም ነው፡፡ ሌላ እርምጃ በእነሱ ላይ ለመውሰድ ያሉበት ሀገር ሕግና ሁኔታዎች አይፈቅዱም እንጅ እንደጠላትነታቸው ሁሉ ሁሉንም ዓይነት እርምጃ በእነሱ ላይ ለመውሰድ የያዝነውና የገባንበት ሕዝባዊ ትግል ያስገድደናል፡፡

ሌሎችም ድረ ገጾችና የብዙኃን መገናኛዎችም ቢሆኑ የመጻፍ፣ የመናገር፣ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ሲባል የሕዝብን የጋራ ጥቅም የሀገር ደኅንነትንና ህልውናን ለመጠበቅ ለመንከባከብ የተለየ ሐሳብ ካለ እሱን ለማስተናገድ የተሰጠ መብት እንጅ ሀገርንና ወገንን የሚጎዳ ወይም ሀገርንና ወገንን የሚጎዳን አካል ጥቅም ለመጠበቅ የሚነገር የሚጻፍ ሐሳብን ለማስተናገድ የተሰጠ መብት አይደለም፡፡ በግልጽ አማርኛ ወያኔ የዚህች ሀገርና የሕዝቧ ቀንደኛ ጠላት እንደመሆኑ ማንም ሰው የወያኔ ቅጥረኛ ሆኖ የወያኔን ጥቅም ለማስጠበቅ ማለትም ከድሮ ጀምሮ የራሱን ቡድናዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ሲል የሀገርን ሕልውናንና የሕዝብን ደኅንነትና ጥቅሞች ለመጉዳት ለማጥቃት ለአደጋ ለመዳረግ የሚያሴረውን የወያኔን ጥቅሞች ለማስጠበቅ የተሰጠ መብት አይደለምና በዚህ ሽፋን ይሄንን ሊያደርጉ እንደማይችሉ ጠንቅቀው ሊያውቁት ይገባል፡፡ የትም ሀገር ቢሆን ያለው አሠራር ይህ ነው፡፡ አሜሪካም ብትሆን ዜጋዋ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም የሚጎዳ ሥራ ሠርቶ “ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ነው” ቢል አትሰማውም “ብሔራዊ ጥቅሜን ለአደጋ ዳርጓል የሀገርንና የሕዝብት ደኅንነት ለአደጋ አጋልጧል ወይም ለጠላት ተቀጥሮ በመሥራት” ወንጂላ እንደ ስኖውደን ታሳድደዋለች እንጅ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ነው ብላ አትምረውም፡፡

እነኝህ አካላት ሞያዊ ሥነምግባራቸውን በመጣስ የሀገራችንን ጠላት የወያኔን ጥቅም ለማስጠበቅ ከወያኔ ጋር በማበር የወያኔ ቅጥረኛ በመሆን መረጃን በማዛባት እንደሚንቀሳቀሱ ባወቅን ጊዜ ይሄንን መብት አጥተዋልና ይሄንን መብት ለሽፋን መጠቀም አይችሉም፡፡ አሜሪካ ጥቅሟን የሚጎዳባትን ሰውና ዘገባ የሀገርና የሕዝብ ጠላት አድርጋ እንደፈረጀችና እንደምታሳድድ ሁሉ እኛ ኢትዮጵያዊያንም የሀገራችንንና የሕዝባችንን ብሔራዊ ጥቅሞች የሕልውናችንና የደኅንነታችን ጠላት የሆነው ወያኔን ያገለገለ ወይም የደገፈ ጋዜጠኛንም ሆነ ማንኛውንም ሌላ አካል ሁሉ የሀገራችንና የሕዝባችን ጠላት እንፈርጃለን እናሳድዳለንም፡፡ በግልጽ አማርኛ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉም ዕድሎች ተዘግተውበት መብቶቹን ለማስከበር ተገዶ የትጥቅ ትግል ውስጥ የገባበት ሁኔታ ውስጥ ያለ በመሆኑ ማንኛውም ሰው ወዶና ፈቅዶ የወያኔ አባልና ደጋፊ የሆነ ካለ ይህ ሰው ሊሸሸግበትና ሊታደገው የሚችል ምንም ዓይነት ዋስትና እንደሌለው ጠንቅቆ ሊያውቅ ይገባል፡፡

ይመስለኛል በሌላም በኩል ወይ ድፍረት ቁርጠኝነት አጥተው ይሁን ወይ ደግሞ ቅድሚያ የሚሰጡት ቤተሰባዊም ሆነ ሌላ ጉዳይ ኖሮባቸው ብቻ በአንድም በሌላም ምክንያት በትጥቅ ትግሉ መሳተፍ የማይችሉ ከመሆናቸውና የትግሉ አካል ካለመሆናቸው የተነሣም “የሚመጣው ለውጥ በግል እኔን አያካትተኝም በተዋናይነት ቦታ ሰጥቶ አያሳትፈኝም” ከሚል ሥጋትና “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ከሚል ለራሳቸውም ለወለዷቸው ልጆችም ለሀገር ለወገንም ፈጽሞ የማይጠቅም የደነቆረና በሽተኛ የሆነ የራስወዳድነትና የምቀኝነት ጠንቀኛ አስተሳሰብ ወያኔ ወይም የወያኔ ደጋፊም ሳይሆኑ እየተደረገ ያለውን የትጥቅ ትግል የሚቃወሙ ወይም የማይደግፉ ያሉ ይመስለኛል፡፡ እንዲህ የሚያስቡ ግለሰቦች የማሰብና የማገናዘብ ችሎታ በጣም የወረደ ነው፡፡ ከተቆጣጠራቸው ክፉ የምቀኝነት መንፈስ የተነሣ እንደ ዜጋ እራሳቸውን ጨምሮ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው አስመስጋኝና አስከባሪ ሥራ በሌሎች ሲደረግ ሲያዩ ዐይናቸው ደም ይለብሳል፡፡ ዜጋ እንደመሆናቸው የዜግነት ግዴታ እንዳለባቸው ተረድተው እንደ ዜጋ ለሀገሬ ምን ማበርከት ይጠበቅብኛል? ሀገሬ ወገኔ ከኔ ምን ይጠብቃሉ? ብለው ራሳቸውን በመጠየቅ የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት አስበው በቅንነት ተንቀሳቅሰው የሚያውቁ አይደሉም፡፡ ከተንቀሳቀሱም ለዝና ወይም ድብቅ የሆነ ሌላ የግል ጥቅማቸውን ለማስከበር ለማግኘት እንጅ ለሀገርና ለወገን በማሰብ አንዳች ነገር አድርገው አያውቁም፡፡

እነኝህ ግለሰቦች በሚቃወሙበት ጊዜ ለመቃወማቸው ምክንያት ሲጠየቁ ብዙ ጊዜ ሊያቀርቡት የሚችሉት ምንም ዐይነት ምክንያት የላቸውም፡፡ ካቀረቡም የረባ አይሆንም፡፡ ወይ እራሳቸው አይሠሩትም ወይ ደግሞ ሌላው እንዲሠራው አይፈልጉም አይፈቅዱም፡፡ ሌላው ሠርቶት ሲደነቅ ሲከበር ሲያዩ በሰይጣናዊ የቅናትና የምቀኝነት መንፈስ ቆሽታቸው ይደብናል፡፡ እንኳንና ለልጆቻቸው፣ ለሀገር፣ ለወገን ለራሳቸውም እንኳን ቢሆን ምን ቢሆን እንደሚበጅ በቅጡ የሚያውቁ ሰዎች አይደሉም፡፡ የሚገርመው ለምን እንዲህ እንደሚሆኑ ራሳቸውም እንኳን አያውቁትም፡፡ የሚያደርጉት ነገር ከግል ሕይዎታቸው ጀምሮ እስከ ሀገር ድረስ እንደሚጎዳ እንደማይጠቅም እንኳንና እራሳቸው ሊያስቡት ተነግሯቸውም እንኳ አይገባቸውም እንዲገባቸውም አይፈልጉም፡፡ በጣም የሚገርመው እንዲህ ዓይነት ክፉ የቅናትና የምቀኝነት መንፈስ ተማሩ በሚባሉት የሚብስ መሆኑ ነው፡፡ ችግሩ ግን የተማረ ከሚባለው ጀምሮ መሀይም እስከሚባለው ዜጋ ድረስ በየቦታው አለ፡፡ ሥራ እንዳይሠራ ብዙ ያውካሉ፡፡ በተለይ የተማሩ የተባሉቱ ተቃውሟቸውን የትም ሲያቀርቡ ተቃውሟቸው በቂና አሳማኝ ምክንያት ይኖረው ይሆናል በሚል ግምት ብዙ ጊዜ ሕዝብ ይሰናከልና ድጋፍ መስጠት ላለበት አካል ድጋፍ ይነፍጋል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ችግር ምክንያት የተቀደሰ ዓላማ ተይዞ ስንት ሊሠሩ የሚሞከሩ በርካታ ሥራዎች ከንቱ ሆነው ይቀራሉ፡፡ የእነዚህን ችግር ያለባቸው ግለሰቦች ፈተና ተቋቁሞ ሥራ መሥራት የተቀደሰን ዓላማ ከግብ ማድረስ እንደ ዕድል አልፎ አልፎ የሚገኝ እንጅ በብዛት የሚታይ አይደለም፡፡ እናም ከዚህ ችግራቸው የተነሣ ሕዝባዊ ትግሉን የሚቃወሙ ወገኖች ሊኖሩ እንደሚችሉ እገምታለሁ፡፡ የሆነ ሆኖ የሚያቀርቡት ተቃውሞ ከወያኔነት አንጻር ባይሆንም ቅሉ በሕዝባዊ ትግሉ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ከቅጥረኞች የማይተናነስ እንዲያውም የባሰ በመሆኑ እነሱንም እንደ ወያኔ ሁሉ የሀገርና የሕዝብ ጠላት አድርጎ መቁጠርና የሚፈጽሙትንም ጥቃት መከላከል ግዴታ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡

የተያያዝነው ትግል የሞት ሽረት ትግል ነው፡፡ ጨዋታ አይደለም የተያዘው ሀገርንና ሕዝብን ከጠባብ ጨካኝ ደንቆሮ አንባገነን አገዛዝ መዳፍ ፈልቅቀን ነጻ ለማውጣት ነው እየታገልን ያለነው፡፡ የግድ የሚወሰዱ ቆራጥ አቋሞች ይኖራሉ፡፡ የመረጥነውን የማውረድ መብቱ እያለን የመረጥነውን መንግሥት በኃይል ለማውረድ መሥዋዕትነት የምንከፍልበት ምንም ምክንያት የለንም መርጠን ያስቀመጥነውን መንግሥት ማንም በኃይል እንዲያስወግደው አንፈልግም አንፈቅድምም፡፡ አገዛዙ ያልመረጥነው በመሆኑና በኃይል የተጫነን ይህንን አገዛዝ በምርጫ ልናወርደው ልናስወግደው የሚያስችለን ሥርዓት በፍጹም የሌለ ስለሆነ እንጅ፡፡ ከተረባረብን በእርግጠኝነት ተሳክቶልን በቅርብ ጊዜ ሀገርንና ሕዝብን ነጻ እናወጣለን፡፡ ባለመብሰላችን እየሆነና ሊሆን ያለውን በማስተዋል አቅቶን አርቀንና ግራ ቀኝ መመልከት ተስኖን እያንዳንዳችን መወጣት ያለብንን ግዴታና ኃላፊነት መወጣት ቸግሮን መረባረብ መተባበር ካልቻልን ደግሞ ወያኔ እንደሚለው ለ60 ዓመታት ብቻ አይደለም ለዘለዓለሙ ባልመረጥከውና በኃይል ጫንቃህ ላይ ተጭኖ በነፍስ በሥጋህ እየተጫወተብህ ባለው አገዛዝ በወያኔ የጭቆና ቀንበር ስር ተጠፍንገህ ሰብዓዊ ክብርህን አተህ እየተዋረድክ የባርነት ኑሮህን እየኖርክ ይንንም የውርደት ኑሮ ለልጅህ እያወረስክ ፍዳህን ትቆጥራታለህ! በእርግጠኝነት ይህ እንዲሆን የሚወድና የሚደቅድ ኢትዮጵያዊ አይኖርምና ያለን ብቸኛ አማራጭ መረባረብ ነው እንረባረብ ወገን!!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>