ከአካደር ኢበራህም ( አኩ አፋር )
ሓምሌ 28/2007 ዓ.ም
የዛሬ ሶስት አመት ገደማ በአወሊያ ትምህርት ቤት የሙስሊም ተማሪዎች ባነሱት ቀላል፣ ህጋዊና ህግ-መንግስታዊው ጥያቄን ተከትሎ የኢትዮጲያ ሙስሊሞች እስከ ዛሬ በሰላም እና በትዕግሰት የተጓዝነውን የትግል መንገድ ምንም እንኳን መንግስት ለሰላም ያለው አመለካከትና ለህዝብ ያለው ንቀት ገና ከጅምሩ ያሳየበት ቢሆንም የህዝበ ሙስሊሙ አርቆ አሳቢነት እና በበሳል አመራር የድምፃችን ይሰማ መሪነት እሰከዛሬ በሰላም ድምፃችን ይሰማ!!፣ መብቴን ይከበር!!፣ ህገ መንግስቱ ይከበር!! ብንልም ወያኔ «ህዝብን የሚሰማበት ጆሮ የለኝም» ብሎ ትናንት በራሱ ሚዲያዎች ሳይቀር ሲደራደራቸው የነበረው የህዝበ ሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ለሶስት አመታት በእስር ቤት ? ( በማሰቃያው ) በዚህ ባለንበት ክፍለ ዘመን የሰው ልጅ በሰው ልጅ ላይ ይፈፅማል ተብሎ የማይታሰበው በደሎች ሲፈፅምባቸው እና በመንግስት መገናኛ ብዙኃኖች ድራማ ሲሰራባቸው እና ከፍርድ ቤት በፊት በሚዲያ ሲፈርድባቸው ከቆየ በኋላ ዛሬ የድራማው የመጨረሻው ክፍል በተጻፈላቸው መሰረት በካንጋሮ ፍርድ ቤት ተነቧል።
ዛሬ በካንጋሮ ፍርድ ቤት የተፈረደው በ18 ሰዎች ወይም 20 ሰዎች ላይ ብቻ አይደለም። በግማሹ የኢትዮጲያ ህዝብ ላይ የተፈረደ እና በማንኛውም ህልም ያለው ኢትዮጲያዊ ተቀባይነት የሌለው፣ ወያኔ ለውድቅት የተቃረበ ሽብር እና አመፅን የናፈቀ በቤተመንግስት የሚኖር የሽብር ቡዱን መሆኑን በራሱ አንደበት ለመላው የኢትዮጲያ ሙስሊሞች ያሳወቀበት ፖለቲካዊ ፍርድ ነው። በሌላ አነጋገር ዛሬ እነ አቡባከርን በ22 አመት ፅኑ እስራት ቀጥቻለሁ የሚለው የወያኔ ቡድን ለራሱ ይህን ያህል አመታት በህዝብ ላይ እንደፈለገ እየፈረደ ለመቆየት ዋስትናው ምንድነው? የሚል ጥያቄ ያስነሳል… በነገራችን ላይ ዛሬ ይህን ፖለቲካዊ ፍርድን ለማውገዝ ሙስሊም መሆን ግዴታ አይደለም!የሰው ልጅ መሆን ብቻ በቂ ነው። በኢትዮጲያ ሙስሊምም ክርስቲያኑም ጭቆና ውስጥ ይገኛል። የሚገርሞው ግን ሰዎች የፈለጉትን ኃይማኖት የመከተል፣ የመደራጀት፣ ሃሳባቸውን በነፃነት የመግልፅ ወዘተ… መብቶች እያላቸው መንግስት እራሱ ህገ-መንግስትን በመጣስ፣ በሃይማኖት ጣልቃ በመግባት ስልጣኑን በመጠቀም ለሚያስራቸው ሁሉ አሸባሪዎች በማለት ሲፈሪጃቸው እና ሲፈርድባቸው ይታያል።
ለመሆኑ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጲያ በመላው ህዝብ የሚደገፈው ሽብር ምን ዓይነት ሽብር ቢሆን ነው? የአገሪቷን የበላይ ህገ-መንግስትን በመጣስ የህዝብን መብት በአደባባይ ከመርገጥ በላይስ ምን ሽብር አለ? የተከበራችሁ የአገሬ ጉዳይ ያገባኛል ብላችሁ በኢትዮጲያ በሰላማዊ ትግል ለውጥ እናመጣለን ብላችሁ የምትታገሉ በሙሉ ሰላም ለሁሉም ቀዳሚ ምርጫ ቢሆንም አለመታደል ሆኖ እኛ ሰላም ብንፈልግም ወያኔ ሰላም እየነሳን አንድ ባንድ እስኪጨረሰን ድረስ መጠበቅ ያለብን አይመስለኝም። እኔ በበኩሌ ካሁን በኋላ ከህይወቴ በላይ ለአትዮጲያ የምሰጠው ነገር ባይኖረኝም ህይወቴን ለውድ ሃይማኖቴና ለውዲቷ ሀገሬ ኢትዮጵያ ለመስጠጥ ተዘጋጅቻለው።