የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001
የተመለከተውን በመተላለፍ የተከፈተ ክስ
የቀ/ቁ/ 001/2006
የወ/መ/ቁ. 01/0001/06
ለኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ
በመላው ዓለም
ከሳሽ ….. ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች (የህዝበ ሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ)
ተከሳሾች… 1/ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግስት
የሽብር ቡድኑ አጠቃላይ አስፈጻሚ
2/ የህውኃት/ኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ
የሽብር ቡድኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ
3/ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ (በሌሉበት)
የሽብር ቡድኑ የቀድሞ አመራር
4/ ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ
የሽብር ቡድኑ አመራር
5/ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን
የሽብር ቡድኑ ወታደራዊ ክንፍ
6/ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ቢሮ
የሽብር ቡድኑ መረጃ ክፍል
7/ የኢ.ፌዲ.ሪ የፌዴራል ጉዳዮች ሚነስቴር
የሽብር ቡድኑ የስልጠናና ምልመላ ክንፍ
8/የኢ.ፌዲሪ. የፍትህ ሚኒስቴር
የሽብር ቡድኑ የህግ ሽፋን ሰጭ ክፍል
9/ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴር
የሽብር ቡድኑ ተባባሪ
10/ የኢ/እ/ጉ/ጉባኤ (መጅሊስ
የሽብር ቡድኑ ተቀዳሚ ተባባሪና ኃይማኖታዊ ሽፋን ሰጭ ተቋም
11/የፌዴራል ወንጀል ምርመራ (ማዕከላዊ)
የሽብር ቡድኑ ቶርቸርና ማወጣጫ (inquisition) ክፍል
12/ አቶ ጌታቸው አሰፋ
የሽብር ቡድኑ መረጃ ክፍል ሃላፊና አመራር
13/ ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም
የሽብር ቡድኑ የስልጠናና ምልመላ ክፍል ሃላፊና አመራር
14/ አቶ ጸጋዬ በርሄ
የሽብር ቡድኑ የፀጥታ ክፍል ሃላፊና አመራር
15/ አቶ ሬድዋን ሁሴን
የሽብር ቡድኑ ቃል-አቀባይ
16/ አቶ አህመዲን አብዱላሂ ጨሎ
የሽብር ቡድኑ ተቀዳሚ ተባባሪና የኃይማኖታዊ ሽፋን ሰጭ ተቋሙ አመራር
17/ ፕሮፌሰር ሃጋይ ኤርሊኽ (በሌሉበት)
የሽብር ቡድኑ ዋና አማካሪ
18/ ዶ/ር ሰሚር አል-ሪፋዒ (በሌሉበት)
የሽብር ቡድኑ አማካሪና የአይዲዮሎጂ ክፍል ተጠሪ
19/ ፔትራም ኃ/የተወ/የግል ማህበር
የሽብር ቡድኑ የፋይናንስ ድጋፍ ሰጭ ክንፍ
20/ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
21/ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ድርጅት (ኢ.ቲ.ቪ)
የሽብር ቡድኑ የድምጽ-ከምስል ስርጭት ክፍል
1ኛ ክስ
(ከ1ኛ እስከ 21ኛ ተከሳሾችን ይመለከታል
ወንጀሉ
በ1996 የወጣውን የኢ/ፊ/ዲ/ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/(1)(ሀ)(ለ)፣ 38(1) እነ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3፣4፣5፣6፣7፣8፣10፣እና 11 የተመለከተውን በመተላለፍ ወንጀል ተከሰዋል፡፡
የወንጀሉ ዝርዝር
ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋ በመሆን እና የወንጀል አድማ ስምምነት በማድረግ በመላ ሃሳባቸው እና አድራጎታቸው የወንጀል ድርጊቱን እና ወንጀሉ የሚሰጠውን ውጤት ሙሉ በሙሉ በመቀበል እነ የራሳቸው በማድረግ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግስት አንቀጽ——— ከተረጋገጠው የእመነት ነጻነት በመቃረን ከራሳቸው “አህባሽ” የተሰኘ አክራሪ አስተሳሰብና አስተምህሮት ውጭ በኢትዮጵያ ውስጥ ሌላ የእስልምና አስተሳሰብና አስተምህሮት መኖር የለበትም የሚል ፖለቲካዊ ዓላማ በማንገብ እና የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጉባዔን (መጅሊስን ) ፖለቲካዊ ዓላማን ለማስፈፀም የተቋቋመ ኃይማኖታዊ ተቋም እንዲሆን እቅድና ግብ በማስቀመጥ መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም የሚለውን የህገ-መንግስቱን አንቀጽ 11ን በመቃረን ቀኑና ወሩ በውል ባልታወቀ 1987 ጀምሮ ህውኃት /ኢህአዴግ በተሰኘው የሽብር ቡድን በመሠባሰብ የረጅም፣ የመካከለኛ እና የአጭር ጊዜ እቅድ በማውጣት እና ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ተንቀሳቅሰዋል፡፡
ተከሳሾች “አህባሽ” የተሰኘው አንጃ በእርስ በርስ ጦርነት በምትታመሰዋ ሊባኖስ ውስ የሚንቀሳቀስ ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው የኃይማኖት ሴክት መሆኑን እያወቁ፣ እንዲሁም የቀድሞውን የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ረፊቀስ ሀሪሪን ግድያ የሚያጣራው የተባበሩት መንግስት የወንጀል አጣሪ ቡድን “አህባሽ” የተሰኘው አንጃ ግድያውን እንደፈፀመ ሪፖርት ያወጣ መሆኑን እያወቁ፤ የአህባሽ አንጃ መስራች የሆኑት ሽህ ዐብደላህ አልሃረሪ ሀረር የሶማሊ አካል ነች የሚል ፀረ-ኢትዮጵያ አቋም ያላቸው መሆኑን እያወቁና ይህንን አቋም የሚገልፀውን መጽሀፍ በመጅሊስ በኩል እያሰራጩ፤ ይህንን በሀገር ሰላም ላ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችልን አንጃ ህዝብ የሰጣቸውን ስልጣን በመጠቀም ወደ ኢትዮጵያ አስመጥተዋል፣ በዚህም ከህዝብና ከሀገር ደህንነት ይልቅ ጊዜያዊ ፖለቲካዊ ጥቅምን በመምረጥ ስልጣናቸውን ለሽብር ዕቅዳቸው ማስፈፃሚያነት ተጠቅመዋል፡፡
ይህን አክራሪ አስተሳሰብ የተጠናወተው “አህባሽ” የተሰኘውን አንጃ ከ1996 ጀምሮ በጦር-ኃይሎች ሦስት ቁጥር ማዞሪያ በሚገኘው ተቋሙ አክራሪ አስተሳሰቡን እንዲያስፋፋ በህቡዕ ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ከዚህም አልፎ ዕለቱና ወሩ ባልታወቀ 2003 ላይ በቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ፊርማ በቦሌ ክ/ከተማ የሚገኝ አንድ መቶ ሺህ (100000) ካሬ ሜትር ቦታ እንዲሰጣቸውና ለአንጃው ማሰልጠኛ ተቋ ግንባታ ይሆን ዘንድ የፔትራም ኩባንያ ስራ አስኪያጅ አቶ ዐብዱልከሪም በድሪ እንዲከታተለው ትዕዛዝ ሰጥተዋልል፡ በዚህም ተግባራቸው ህዝብ የሰጣቸው ስልጣን ለሽብር ዕቅዳቸው ማስፈፀሚያ ተጠቅመዋል፡፡የሽብር ቡድኑ ከሐምሌ ወር 2003 ጀምሮ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ይህንኑ “አህባሽ” የተሰኘ አክራሪ አስተሳሰብ እንዲቀበሉ በማስገደድ፣ ማንኛውም ሙስሊም እነርሱ ከሊባኖስ ካስመጡት የአስተሳሰብ መስመር ውጭ መከተል የማይቻል መሆኑን በአደባባይ በመግለፅ እና የእምነት ነፃነታቸውን ለማስከበር የተንቀሳቀሱ የኃይማኖት መምህራን፣ ዑለማዎችና ምሁራንን ለሥነ-ልቦና እነ ለአካል ጉዳት በመዳረግ እስር ውስጥ በማዋል፣ የህገ-መንግስት ጥሰታቸውን በተቃወመው ህዝበ-ሙስሊም ላይ የህይወት፣ የአካልና የንብረት ጉዳት አድርሰዋል፡፡
ቀደም ሲል ባቀዱት መሰረትም መጅሊስ (የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጉባኤ) ውስጥ ከእነርሱ አክራሪ አስተሳሰብ ውጭ የሆነ ወይም የሽብር ቡድኑ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆነ ግለሰብ በየትኛውም የመጅሊሱ አስተዳደራዊ እርከን እንዳይሳተፍ አግደዋል፡፡ ህዝብ የማያውቃቸውና የኃይማኖትም ይሁን የአካዳ ዕውቀት የሌላቸው ግለሰቦችን የመጅሊሱ አመራር አድርጎ በመሾም ተቋሙ ህዝበ-ሙስሊሙ ላይ ለሚፈፀመው የሽብር ድርጊት ኃይማኖታዊ ሽፋን እንዲሆን ለማድረግ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ይህንንም ለማሳካት የመንግስት መዋቅርን በመጠቀም በትጋት ሰርተዋል፡፡ በተለይም የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ቢሮው ሙሉ ኃይሉን ለዚህ እኩይ ጉዳይ በማዋል በንፁሃን ዜጎች ላይ የእስር፣ የእገታ፣ የድብደባና የግድ ወንጀል ፈፅሟል፡፡ መጅሊሱን ለሽብር ዓላማቸው ማስፈፀሚያነት ለማመቻቸት ይችሉ ዘንድ ህዝበ-ሙስሊሙ ባልተሳተፈበትና የህዝበ-ሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ በፌ/ወ/ምርመራ (ማዕከላዊ) ኢ-ሰብዓዊ ግፍ እየተፈፀመባቸው (እፈፀሙባቸው) ባሉበት ሁኔት ህገ-ወጥ ምርጫ- የመንግስት ተቋም በሆነው ቀበሌ ውስጥ-አካሂደዋል፡፡ በሂደቱም ህገ-ወጥ የመጅሊስ አመራሮችን በሌላ ህገ-ወጥ አመራሮች ተክተዋል፡፡ በዚህም የሽብር ቡድኑ ተሳታፊዎች በኃይማኖት ጉዳይ ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነታቸውን አሳይተዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ የሀገሪቱን መንግስታዊ ተቋማት በመጠቀምና የሀገሪቱን የፀጥታ ኃይል ሙሉ በሙሉ ለህገ- ወጥ ዓላማቸው በማዋል በ “ህገ-መንግስት ማስተማር” ስም አዲሱን አክራሪ አስተሳሰብ በኃይል ጭነዋልል፡ የግዳጅ ስልጠና ሰጥተዋል፡፡ ስልጠናቸውን ለመሳተፍ ፈቃደኛ ያልሆኑና የፀጥታ ኃይላት ማስፈራሪያና ዛቻ ያልበገራቸው የመስጅድ ኢማሞች ከኢማምነታቸው (ከስግደት መሪነታቸው አባርረዋል፡፡ በኃይማኖት ጉዳይ በቀጥታ ጣልቃ በመግባት የመስጅድ ኢማሞችን ሾመዋል፤ እነርሱ የሾመዋቸውን ኢማሞች “ተከትለን አንሰግድም” ያሉ በርካታ ሙስሊሞችን ዘብጥያ ወርውረዋል፣ ለህገ-ወጥ ድርጊታቸው ማስፈፀሚያ ያቋቋሟቸውን ፍ/ቤቶች በመጠቀም በ “ዋስትና” ስም በርካታ ሚሊዬን ብር ከህዝበ-ሙስሊሙ መዝብረዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች በሀገራቸው ሙስሊም ሆነው የመኖር ነፃነታቸውን ነፍገዋል፡፡
የሽብር ቡድኑን ህገ-ወጥ ድርጊት በመቃወም ህገ-መንግስት ይከበር! የሚል ድምፃቸውን ለማሰማት አደባባይ የወጡ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችን “ጥቂቶች” ሲሉ አሸማቀዋል፤ የነፃነት ጩኸታቸውን ለሚመለከተው የመንግስት አካል ያደረሱላቸውና ለመብት ጥያቄያቸው መፍትሄ ያፈላልጉላቸው ዘንድ በፊርማቸው አረጋግጠው ውክልናቸውን የቸሯቸውን የህዝብ ልጆች የሽብር ቡድኑ ራሱ በሚፈፅመውና ግዙፍ የወንጀል ድርጊት በሆነው በሽብር በመወንጀል አሰቃቂ ግፍ ፈፅመዋል፡፡ ይህንኑ የሽብር ዕቅዳቸው አካል የሆነውን ህገ-ወጥ ተግባር የህግ ሽፋን ለመስጠት የኢ/ፌ/ዲ/ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የተሰኘ ክፍላቸውን በመጠቀም የህዝብ ወኪሎችን ከሃያ ወራት ያላነሰ በእስር ቤት አጉረዋል፡፡ በተጨማሪም በሺህዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞችን “በሁከትና በብጥበጥ” በመወንጀል ተመሳሳይ ወንጀል ፈፅመዋል፡፡ መረጃ ለህዝብ እንዳይደርስ ለማገድ በማሰብ በሙስሊሙ ህ/ሰብ ጉዳይ ላይ በማጠንጠን የሚዘግቡ ሃይማኖታዊና ማህበራዊ ጋዜጦችንና መጽሔቶችን አግደዋል፤ አዝዘግተዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ አባስት ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችን በተለያ ስያሚዎች በመከፋፈል፣ አክራሪ አስተሳሰባቸውን በኃይል በመጫን፣ ይህንን ህገ-ወጥ ተግባራቸውን በተቃውሙ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል፤ በርካታ የኃይማኖት መምህራንና ምሁራን ሀገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ አድርገዋል፡፡ ህዝብ የሰጣቸውን ስልጣን ህዝብን ለማሸበር ተጠቅመዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ በኮፈሌ፣ በአሳሳ፣ በሀረር፣ በሀርጉ፣ በደጋን፣ በአዲስ አበባ አወሊያ መስጂድ፣ በአንዋር መስጅድና በአዲስ አበባ ስቴድዮም በህዝበ-ሙስሊሙ ላይ የህይወት፣ የአካልና የንብረት ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡ጰ፡
ተከሳሾች የሽብር ቡድኑን ዓላማ ለማስፈፀም በማሰብ አክራሪ አስተሳሰባቸውን የማቃባሉ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችን በኢኮኖሚ ለማዳከም የተለያዩ እቅዶችን ነድፈው ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች በሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ብልጽግና የሚጨበጥ ተሳትፎ ማድረግ የሚያስችላቸውን ከወለድ ነፃ ባንክ ማቋቋም እንዳይችሉ ከልክለዋል፡፡ ከወለድ ነፃ ባንክ ማቋቋም የሚፈቅድ አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀ ቢሆንም የሽብር ቡድኑ አመራሮች በሰጡት ቀጭን ትዕዛዝ ከ6800 (ስድስት ሺህ ስምንት መቶ) አባላት በላይ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችን ያቀፈውን ዘምዘም ባንክ በብሔራዊ ባንክ ፕሬዝዳንት ፊርማ አዋጁን በመጣስ በኃይል በትነዋል፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ያላቸውን የትምህርት ተሳትፎ ለማቀጨጭ በማቀድ ሆን ብለው ከህገ-መንግስቱ ጋር የሚቃረንና የእምነት ነፃነትን የሚጋፋ አግላይ ደንብ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል በማውጣት ከፍተኛ ጫና አሳድረዋል፡፡ ይህንኑ ህገ-ወጥ ደንብ የተቃወሙ ሙስሊም የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን አንድም ለእስራት አሊያም ከትምህርት ገበታ ለመገለል እንዲደረጉ አድርገዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ ዓላማውን ለማስፈፀም ባቋቋማቸው የመገና ብዙሃን የሽብር ቅስቀሳ አድርጓል፡፡ አባላቱ መረጃን አዛብቶ በማቅረብ የጠወሰነን የህበረተሰብ ክፍል በተወሰነው ላይ የማነሳሳት ወንጀል ፈፅመዋል፡፡ ህዝበ-ሙስሊሙ ያነሳቸውን የእምነት ነፃነት ጥያቄዎች በመቀልበስ ሙስም ላልሆኑ ወገኖቹ ስጋት እንደሆነ አድርገው በመሳል ለርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ በዚህም ድርጊታቸው ለዘመናት ተከባብሮ የኖረውን የኢትዮጵያ ህዝብ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ለማስገባት በማስብ ያልተሳካ ሙከራ አድርገዋል፡፡ ቀስቃሽ የመገናኛ ብዙሃናቸውን በመጠቀም በእስር ላይ ያሉ ንፁሃን የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎችን እና የኃይማኖት መምህራንን በ “ሽብር” በመፈረጅ “ጅሃዳዊ ሀረካት” የተሰኘ ከእውነት የራቀና የተቀነባበረ ዘጋቢ ፊልም በማሰራቸት ህዝብን በህዝብ ላይ አነሳስተዋል፡፡ የሽብር ቡድኑ አባላት በደሴ ከተማ በሸህ ኑሩ ኢማም ላይ ግድያ በመፈፀም የመገናኛ ብዙሃናቸውን በመጠቀም የህዝበ-ሙስሊሙን የመብት ጥያቄ እንቅስቃሴ ለማጠልሸት ተንቀሳቅሰዋል፡፡ የተዛባ መረጃ በመስጠትና በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ያደራጇቸውን ዜጎች በጥቅም በመደለል አሊያም በማስፈራራት በመላ ሀገሪቱ የሀሰት የድጋፍ ሰልፍ እንዲወጣ በማድረግ ህዝብን ለማታለል ሞክረዋል፡፡ በግድያው ማግስትም በርካታ ንፁሃን ሙስሊሞችን ለእስር በመዳረግ በሽብር ወንጅለዋል፡፡
በአጠቃላይ ተከሳሾች የሽብር ቡድኑን ዓላማ ለማስፈፀም በማቀድ በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ በመግባት እነርሱ ከመረጡት አክራሪ አስተሳሰብና አይዲዮሎጂ ውች ያለን ለማጥፋት በመንቀሳቀሳቸው፣ የተወሰነን የህብረተሰብ ክፍል በማስፈራራታቸው በህይወት፣ በአካልና በንብረት ላይ ጉዳት በማድረሳቸው፣ እገታ በመፈጸማቸው፣ የሽብር ድርጊት ለመፈፀም በማቀዳቸው፣ በመዘጋጀታቸው፣ በማሴራቸው፣ በማነሳሳታቸው እና በመፈፀማቸው በግዙፍ የወንጀል ድርጊት ተከሰዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ አባላት የወንጀል ተሳትፎ እንደሚከተለው ተዘርዝሯል፡-
1ኛ. ተከሳሽ – የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግስት
የሽብር ቡድኑን እቅድና ዓላማ ለማስፈፀም በመዋቅሩ ተዋረድ ያሉ መስሪያ ቤቶች እንዲንቀሳቀሱ መመሪያ ሰጥቷል፡፡ የሚፈፅማቸውን የሽብር ድርጊቶች ህጋዊና ትክክለኛ ለማስመሰል የሀገሪቱን የፍትህ ስርዓት እንደ ሽፋን ተጠቅሟል፡፡ ለዚህም ከ8ኛ ተከሳሽ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ንፁሃንን ለእስርና ለኢ-ሰብዓዊ ግፍ ከመዳረጉም በተጨማሪ በሺዎች ከሚቆጠሩ ሙስሊሞች በዋስትና ማስጠበቂያ ስም በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር መዝብሯል፡፡ ለሽብር ዓላማው መደለያ ይሆን ዘንድ በአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ በማደራጀት ለ2005 የበጀት ዓት ብቻ 350,000,000.00 (ሦስት መቶ ሃምሳ ሚሊዮን ብር) በመመደብ ተንቀሳቅሷል፡፡ ለሽብር ዓላማው የሚገለገልባቸውን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ድርጅት (ኢቲቪ) እና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን (አዲስ ዘመን ጋዜጣን) በመጠቀም የሀሰት መረጃ ለህብረተሰቡ በማሰራጨት ህዝበ-ሙስሊሙን ሙስሊም ካልሆነው ወገኑ ጋር ለማጋጨት ተንቀሳቅሷል፡፡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ላይ የተፈፀመውን የሽብር ድርጊት በፊታውራሪነት የመራና ያስፈፀመ በመሆኑ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግስት በፈፀመው የሽብር ድርጊትን ማቀድ፣ ማሴርና መፈፀም ወንጀል በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3 እና 4 የተመለከተውን በመተላለፍ ተከሷል፡፡
2ኛ. ተከሳሽ የህውኃት/ ኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ
የሽብር ቡድኑ ስራ-አስፈፃሚ በመሆን ሰርቷል፡፡ የሽብር ድርጊቱን በማቀድ፣ በማሴር እና አመራር በመስጠት ተሳትፏል፡፡ ቀኑና ወሩ በውል ባልታወቀ 1996 ዓ.ል ጀምሮ በሽብር ድርጊቱ ዙሪያ በህቡዕ በመወያትና የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ እቅድ በማውጣት የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችን መሪ ድርጅት የኢ/እ/ጉ/ጉባኤ (መጅሊስን) የፖለቲካዊ ግባቸው ማስፈፀሚያ ኃይማኖታዊ ተቋም እንዲሆን ተንቀሳቅሰዋል፡፡ በህገ-መንግስት አንቀጽ 11 እና አንቀጽ 27 የተደነገገውን የእምነት ነፃነት በመቃረን በእምነት ተቋና በኃይማኖት ጉዳይ በቀጥታ ጣልቃ ገብተዋል፡፡ ይህን ህገ-ወጥ ድርጊት በተቃወሙ ንፁሃን ላይ የኃይል እርምጃ በመውሰድ የሽብር ድርጊት እንዲፈፀም ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡ ስለሆነም ለሽብር ድርጊት በማሴር፣ በማቀድና አመራር በመስጠት ወንጀል በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4 እና አንቀጽ 7(2) የተመለከተውን በመተላለፋቸው ተከሰዋል፡፡
3ኛ. ተከሳሽ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ (በሌሉበት)
የሽብር ቡድኑ የቀድሞ አመራር በመሆን ሰርተዋል፡፡ የሽብር ድርጊቱን በማሴር፣ በማቀድና አመራር በመስጠት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ከ17ኛ ተከሳሽ ሃጋይ ኤርሊኽ የተሰጣቸውን ምክር ከልብ በመቀበል ያላቸውን የግል ክህሎት በማከል የሽብር ቡድኑን ዓላማ በመቅረፅ የቡድኑን ጥንስስ ጥለዋል፡፡ በሚያዚያ 9/2004 ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባደረጉት ንግግር በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችን ለመከፋፈል ሞክረዋል፡፡ የሽብር ዘመቻው ለመጀመር የነበራቸውን እቅድ የመብት ጥያቄ ያነሳውን ህዝበ-ሙስሊም “ጥቂቶች” በማለት ከማሸማቀቅ አልፈው “በእንጩጩ ማስቀረት” ሲሉ ዝተዋል፤ አስፈራርተዋል፡፡ ይህንኑ የፓርላማ ንግግራቸውን ተከትሎ 5ኛ ተከሳሽ የፌ/ፖሊስ ኮሚሽን በሚያዚያ 2004 በአሳሳ ከተማ በንፁሃን ሙስሊሞች ላይ የህይወትና የአካል ጉዳት አድርሷል፡፡ ምንም እንኳን የሽብር ድርጊቱን ከመፈፀማቸው በፊት እርሳቸው ራሳቸው በእንጩጩ የቀሩ ቢሆንም የሽብር ቡድኑ በእርሳቸው የተዘረጋለትን የአፈፃፀም እቅድ በመከተል ከፍተኛ የህይወት፣ የአካልና የንብረት ጉዳት አድርሷል፡፡ ግለሰቡ በአዋጅ የፀደቀውን የወለድ ነፃ ባንክ የመመስረት መብትን በመንጠቅ በኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችና በክርስቲያን ወንድሞቻቸውም ተሳትፎ የተቋቋመውን “ዘምዘም ባንክ” እንዲበተን ቀጥተኛ ትዕዛዝ በመስጠት በትነዋል፡፡ በዚህም የሽብር ቡድኑ ዓላማ አንዱ የሆነውን የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችን የኢኮኖሚ ተሳትፎ ማኮሰስን ለማሳካት በማሰብ አዋጅን በመመሪያ ጥሰዋል፡፡ ግለሰቡ በ2004 ለአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት በተፃፈ ደብዳቤ ለአህባሽ ማሰልጠኛ ተቋም ግንባታ የሚውል በቦሌ ክ/ከተማ የሚገኝ 100ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ እንዲሰጥ በፊርማቸው አዘዋል፡፡ በዚህም የህዝብ ስልጣንን ለራሳቸው የሽብር ዓላማ ማሳኪያ ተጠቅመዋል፡፡ ስለሆነም ግለሰቡ የሽብር ድርጊትን በማቀድ፣ በማሴር፣ በማነሳሳትና በመፈፀም ወንጀል በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4 እና 7(2) የተመለከተውን በመተላለፍ ወንጀል በሌሉበት ተከሰዋል፡፡
4ኛ ተከሳሽ -ጠ/ሚኒስቴር ኃ/ማርያም ደሳለኝ
ተከሳሽ የቀድሞውን ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊን (3ኛ ተከሳሽን) የእግር ኮቴ ያለምንም መጨመርና መቀነስ በመከተል የሽብር ቡድኑን መርተዋል፡፡ የሽብር ድርጊቱን የተቃውሙ ሙስሊሞች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡ በሀገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ- 21ኛ ተከሳሽ እና በአልጀዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ ህዝበ-ሙስሊሙን “ጥቂቶች” ሲሉ አሸማቀዋል፡፡ ለሚፈፀሙ የሽብር ድርጊቶች ሁሉ አመራር ሰጥተዋል ባባልም የሀገሪቱ የበላይ አመራር ከመሆናቸው አንፃር በይሁንታ በማለፍ በቀጥታ አመራር የመስጠት ያህል ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ ስለሆነም ሀገሪቱ ውስጥ የተፈፀሙ የሽብር ድርጊቶችን በሙሉ በማቀድ፣ በመፈፀምና አመራር በመስጠት ወንጀል የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 2 እና 7(2)ን በመተላለፍ ወንጀል ተከሰዋል፡፡
5ኛ. ተከሳሽ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን
የሽብር ቡድኑ ወታደራዊ ክንፍ በመሆን በዜጎች ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት አድርሷል፡፡ በሚያዚያ 2004 በአሳሳ፣ በሀምሌ 2005 በኮፈሌ፣ ቀኑና ወሩ ባልታወቀ በ2005 በሀርቡ፣ በ2004 በሀረር፣ በሀምሌ 06/2004 በአወሊያ መስጅድ፣ በሐምሌ 14/2004 በአንዋር መስጅድ እና በሐምሌ 2005 በአዲስ አበባ ስቴዲዮም ዙሪያ በኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ላይ የህይወት፣ የአካልና የንብረት አሰቃቂ ጉዳት አድርሷል፡፡ በሐምሌ 06/2004 በሌሊት አወሊያ መስጅድ ውስጥ ለምፅዋት የሚሆን ምግብ ሲያዘጋጁ የነበሩ ሙስሊሞች ላ እገታ በማድረግ፣ በተዘጋ መስጅድ ውስጥ ባሉ ሙስሊሞች ላይ አስለቃሽ ጥይት ወደ ውስጥ በመተኮስ በህዝብ ጤና ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡ በሐምሌ 2005 የዒድ አልፊጥር ባዕልን ለማክበር በአዲስ አበባ ስቴዲዮም በመገኘት የ1ኛ ተከሳሽን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግስትን በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ ገብነት በመቃወማቸው በሺህዎች በሚቆጠሩ ሙስሊሞች ላይ አሰቃቂ ድብደባ እና እስር ፈፅሟል፡፡ በዕለቱ ከአስር ሺህ በላይ ሙስሊሞችን ለእስርና እንግልት ዳርጓል፡፡ በመሆኑም ከ2ኛ ተከሳሽ ህውኃት/ኢህአዴግ በተሰጠው አመራር የሽብር ድርጊቱን በቀጥታ የፈፀመ በመሆኑ በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3(1)(2)(4) የተመለከተውን በመተላለፍ ተከሷል፡፡
6ኛ. ተከሳሽ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ቢሮ
የሽብር ቡድኑ መረጃ ክፍል በመሆን ለቡድኑ አመራሮች ሀሰተኛ መረጃን በመስጠት የሽብር ድርጊቱን አቀጣጥሏል፡፡ የሽብር ቡድኑ አመራሮችን ከጀርባ ሆኖ በመምራት ሆን ብሎ በኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ላይ ሽብር እንዲፈፀም አበረታቷል፡፡ የተለያዩ በህቡዕ የተፈፀሙ ግድያዎችን አሲሯል፣ አቀነባብሯል፣ ፈፅሟ፡፡ በ2005 በደሴው ሸህ ኑሩ ኢማም ላይ የተቀነባበረ ግድያ ፈፅሟል፡፡ ይህን በማድረግም የህዝበ-ሙስሊሙን የመብት ጥያቄ እንቅስቃሴ ለማኮላሸት ንፁሃንን አስሯል፤ በሀሰት የከሰሳቸውን ዜጎች ከኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች “ህገ-መንግስት ይከበር” እንቅስቃሴ ጋር ለማዛመድ ጥረት አድርጓል፡፡ ቢሮው ከ5ኛ ተከሳሽ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ዜጎችን የማገት፣ የማሰር፣ ቶርች የማድረግና የመግደል ወንጀል ቀጥተኛ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ በተጨማሪም ቢሮው በሐምሌ 08/2004 በተወሰኑ የህዝበ-ሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ላይ የመኪና እገታና ጠለፋ ሙከራ አድርገዋል፡፡ በሀሰት በተወነጀሉት የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴና በተለያዩ ምድብ ችሎት በቀረቡ ንፁሃን ሙስሊሞች ላይ ከ11ኛ ተከሳሽ የፌዴራል ወንጀል ምርመራ ጋር በመሆን ለሽብር ድርጊታቸው የሚሆኑ የሀሰት ምስክሮችን በማባበል አሊያም በማስፈራራት አዘጋጅተዋል፡፡ ስለሆነም የሽብር ድርጊት ቀጥተኛ ተሳታፊ በመሆን እና ምስክር በማባባል ወይም በማስፈራራት ወይም ማስረጃ በማጥፋት ወንጀል በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3(1)(2)(3)(4) እና 10(1) የተመለከተውን በመተላለፍ ተከሷል፡፡
7ኛ. ተከሳሽ የኢ.ፌዲ.ሪ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር
የሽብር ቡድኑ የስልጠናና የምልመላ ክፍል በመሆን ሰርቷል፡፡ የህዝብን ሃብትና ጊዜ ለእኩይ ዓላማው በመጠቀም የሽብር ቡድኑን ዓላማ ለማስፈፀም በሙሉ ልቡ ተንቀሳቅሷል፡፡ 10ኛ ተከሳሽን (መጅሊስን) እንደ ኃይማኖታዊ ሽፋን በመጠቀም አክራሪ ስልጠናዎችን አዘጋጅቷል፤ አካሂዷል፡፡ “ህገ-መንግስት ማስተማር” በሚል ስም በኃይማኖታዊ ጉዳዮች በቀጥታ ጣልቃ በመግባት ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት የሚያምኑባቸውን ጉዳዮች በአዲሱ አክራሪ አስተሳሰብ መተካት እንዳለባቸው በ2003 ሐምሌ ወር በሃሮማያ ዩኒቨርስቲ ከ10ኛ ተከሳሽ የኢ/እ/ጉ/ጉባኤ (መጅሊስ) ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የአህባሽ ስልጠና ላይ የ1ኛ ተከሳሽን (የመንግስትን) አቋም አንፀባርቋል የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአክራሪ አስተሳሰቡን ማስፋፋትና በሙስሊሙ ኃይማኖታዊ ጉዳይ ላይ ጣልቃ እየገባ ቀጥተኛ ትዕዛዝና መመሪያ መስጠት የዕለት ከዕለት ተግባሩ በማድረግ ህገ-መንግስታዊ ጥሰት ፈፅሟል፡፡ የሽብር ቡድኑ ለመፈፀም ላቀደውና ለፈፀመው የሽብር ድርጊት የአስተሳሰብ መደላድል በመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ስለሆነም የሽብርተኝነት ድርጊት እንዲፈፀም ስልጠና በመስጠት ወንጀል በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 5(1)(2) የተመለከተውን በመተላለፍ ተከሷል፡፡
8ኛ. ተከሳሽ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር
የሽብር ቡድኑ ለሚፈፅማቸው ህገ-ወጥ ድርጊቶች የህግ ሽፋን በመስጠት ተንቀሳቅሷል፡፡ በስሩ በሚገኘው የፌዴራል ዓቃቢ ህግ በኩል ከ11ኛ ተከሳስ የፌዴራል ወንጀል ምርመራ (ማዕከላዊ) ጋር በመተባበር የሽብር ቡድኑ የሚፈፅማቸውን የህገ-መንግስት ጥሰቶችና የሽብርተኝነት ተግባራት የሚቃወሙና ለህዝብ የሚያጋልጡ የነፃነት ታጋዮችን፣ ጋዜጠኞችንና የፖለቲካ ሰዎችን በሀሰት ውንጀላ በመክሰስ እና የሀሰት የምስክርና ሰነድ በማዘጋጀት ወንጀል ፈፅመዋል፡፡ በተለይም የህዝበ-ሙስሊሙን ህጋዊ ወኮሎች የሽብር ቡድኑ በፈፀመው በሽብር ወንጀል በመክሰስ ለሽብርተኝነት ከለላና ጥበቃ ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም የህዝበ-ሙስሊሙን የመብት ጥያቄ የዓለም ማህበረሰብን ባስደመመ ሰላማዊና ህጋዊ መንገድ የመሩና ያስተባበሩ የህዝብ ልጆችን ያለምንም ሀፍረት ወይም ርህራሄ ለእስርና እንግልት ዳርገዋል፤ የንፁሃንን ቤተሰብ አባወራ አልባ አድርገዋል፡፡ ህፃናቶቻቸውን ያለ አባት እንክብካቤ እንዲያድኑ አድርገዋል፡፡ በአጠቃላይ ሚኒስቴር መ/ቤቱ የሽብር ቡድኑ የዜጎች ዋስትና የሆነውን የፍትህ ስርዓት ለጊዜያዊና ለርካሽ የፖለቲካ ጥቅም እንዲያውል ተባብሯል፡፡ በዚህም የሚ/መ/ቤቱ የህዝብን ደህንት አደጋ ላይ በመጣል የፍትህ ስርዓቱን ለጥቂት የሽብር ቡድኑ አባላት ፖለቲካዊ ጥቅም በማዋሉ እና ለሽብር ድርጊት ከለላና ሽፋን በመስጠቱ በሽብር ድርጊት ተባባሪነት የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 5(2) እና 7(1) የተመለከተውን በመተላለፍ ተከሷል፡፡
9ኛ. ተከሳሽ የኢ.ፌዲ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴር
የሽብር ቡድ በረጅም ጊዜ እቅዱ የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችን የከፍተኛ ትምህርት ተሳትፎ ለማኮሰስ በሚያደርገው ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴርን ሲጠቀም የሚስቴር መስሪያ ቤቱ ለሽብር እቅዱ ስኬት በፈቃደኝነት ተባብሯል፡፡ ተከሳሹ የእምነት ነፃነትን የሚቃረን የተማሪዎች ደንብ በማርቀቅ ተማሪዎች የመማር ማስተማር ሂደቱን በማያደናቅፍ ሁኔታ የሚተገብሯቸውን ኃይማኖታዊ ስርዓቶች ለማገድ ተንቀሳቅሷል፡፡ በዚህም የእስልምናም ይሁን የክርስትና እምነት ተከታዮችን ከኃይማኖተኝነት በማራቅ ለሽብር ቡድኑ አጎብዳጅ ትውልድ የመፍጠር የረጅም ጊዜ የጎድንዮሽ ዓላማ መሆኑን እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው ሆን ብሎ የሽብር ቡድኑ ተባባሪ ሆኗል፡፡ ስለሆነም ሽብርተኝነትን በመርዳት ወንጀል የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7(1) የተመለከተውን በመተላለፍ ተከሷል፡፡
10ኛ. ተከሳሽ የኢ/እ/ጉ/ጉባኤ (መጅሊስ)
የሽብር ቡድኑ ኃይማኖታዊ ሽፋን ሰጭ ተቋም በመሆን ከ1992 ጀምሮ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግና የሽብርተኝነት ድርጊትን ሲረዱና ሲተባበር ቆይቷል፡፡ በህገ-ወጥ መንገድ ስልጣን የተቆናጠጡ አባላቶቹ ህገ-ወጥ ምርቻ በማድረግ ህዝበ-ሙስሊሙ ባስሰጣቸው ውክልና ያለፈቃዱ ሲመሩት ቆይተዋል፡፡ ተቋሙ የ1ኛ ተከሳሽ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግስት አንድ ቢሮ በመሆን የመንግስት ባለስልጣናት በተለይም 13ኛ ተከሳሽ ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም በቀጥታ የሚያዙት በኃይማኖት ሽፋን የፖለቲካ ዓላማ የሚራመድበት ተቋም እንዲሆን ፈቅዷል፡፡ የህዝብን አደራ ወደ ጎን በመተው የመጅሊሱ አመራሮች በከፍተኛ ምዝበራ በመዘፈቅ ከሐጅና ዑምራ ጉዞ የሚገኘውን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ለግል ጥቅማቸውና አክራሪ አስተሳሰባቸውን ለማስፋፋት ተጠቅመዋል፡፡ በተጨማሪም በምዝበራ የተገኘውን ገንዘብም ለ6ኛ ተከሳሽ ለብሔራዊ መረጃና ደህንነት ቢሮ ከፍተኛ ባለስልጣናት በማካፈል የህዝብን ንብረት ህገ-ወጥ ዓላማን ለማስፈፀም አውለዋል፡፡ ያስመጣውን አህባሽ የተሰኘ አስተሳሰብ በኃይል በመጫን የእምነት ነፃነትን ተቃርነዋል፡፡ ተቋሙ ከ7ኛ ተከሳሽ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ጋር በመሆን የግዳጅ ስልጠናዎችን አዘጋጅቷል፡፡ በ8ኛ ተከሳሽ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር ስር ከሚገኙ የፍትህ ቢሮዎች ጋር በመተባበር በግዳጅ ስልጠናዎች ለመሳተፍ ፈቃደኛ ያልሆኑና ከአክራሪ አስተሳሰባቸው ውጭ የሆኑ የመስጅድ ኢማሞችን አባርረዋል፤ በምትካቸውም ምዕመናኑ የማፈልጓቸውን ኢማሞች ሾመዋል፤ በህዝብ በተመረጡ የመስጅድ ኮሚቴዎች የሚተዳደሩ መስጅዶችን ከ6ኛ ተከሳሽ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ቢሮ ጋር በመተባበር ከህዝብ በኃይል ነጥቀዋል፡፡ “መንግስት የሾማቸውን ኢማሞች ተከትለን አንሰግድም” በማለት ስግደታቸውን ለብቻቸው የከወኑ ምዕመናን ለእስርና እንግልት እንዲዳረጉ ምክንያት ሆነዋልል፡ በአጠቃላይ ተቋሙ የሽብር ቡድኑ (ህውኃት/ኢህአዴግ) በህዝበ-ሙስሊሙ ላይ የፈፀማቸውን የሽብር እንቅስቃሲዎች ኃይማኖታዊ ቡራኬ የሰቱ በመሆኑ በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7(1) የተመለከተውን በመተላለፍ ተከሷል፡፡
11ኛ. ተከሳሽ የፌ/ወንጀል ምርመራ (ማዕከላዊ)
የሽብር ቡድኑ ቶርቸር እና ማውጣጫ (Inquisition) ክፍል ሆኖ አገልግሏል፡፡ ዜጎች ያልፈፀሙትን ወንጀል እንዲናዘዙ የአዕምሮ፣ የስነ-ልቦና የአካል ቶርቸር በማካሄድ የሀሰት ሰነድና ማስረጃ በማቀነባበር ከ8ኛ ተከሳሽ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የሀሰት ክስ በመመስረት ንፁሃንን ወንጅሏል፡፡ ያልተፈፀመ ወንጀልን በማውጣጣት ሂደትም እጅግ ኢ-ሰብአዊ የምርመራ መንገዶችን በመጠቀም በከሳሾች ላይ ከፍተኛ የአካልና የስነ-ልቦና ጉዳት አድርሰዋል፡፡ የክፍሉ አባላት የሽብር ቡድኑ የሚፈፅማቸውን የሽብር ድርጊቶች ለመደበቅና ከለላ ለመስጠት ሆን ብለው ንፁሃን ላይ አሰቃቂ ድብደባና የማሰቃያ መንገዶችን በመጠቀም ሽብር የተፈፀመው በእነኝህ ንፁሃን መሆኑን ለማስመሠል ከሞራል ህግጋትም ሆነ ከህገ-መንግስት የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ የተቃረኑ ዘግናኝ ወንጀሎችን ፈፅመዋል፡፡ ተቋሙ በሀሰት በሚወንጅላቸው ንፁሃን ላይም የሀሰት ምስክሮችን በማዘጋጀት፣ በማባባል፣ አሊያም በማስፈራራት የሽብር ድርጊቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረጉ በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 5(1)(ሀ)፣5(2) እና 10(1)(2) የተመለከተውን በመተላለፍ ወንጀል ተከሷል፡፡
12ኛ. ተከሳሽ አቶ ጌታቸው አሰፋ
የሽብር ቡድኑ የመረጃ ክንፍ የሆነውን 6ኛ ተከሳሽ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ቢሮን በበላይነት መርተዋል፡፡ ፍፁም በሆነ አምባገነናዊ አመራራቸው ንፁሃን ዜጎች እንዲታሰሩ፣ እንዲሰቃዩ እንዲታገቱና እንዲገደሉ ቀጥተኛ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡ የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች የመብት ጥያቄ ህጋዊና ሰላማዊ እነቅስቃሴ ለማኮላሸት አቅደዋል፣ አሲረዋል፣ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ የሽብር ቡድኑ ለሚፈፅማቸው የሽብር ድርጊቶች የሚውሉ ግለሰቦችን መልምለዋል ወይም እንዲመለመሉ አድርገዋል፡፡ ስልጣናችውን በመጠቀም በእጅ አዙር እና በቀጥታ የሽብርተኝነት ድርጊት እንዲፈፀም አመራር በመስጠት በወንጀሉ ተሳትፈዋል፡፡ ለሽብር ቡድኑ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት የሽብር ድርጊቱን አፋፍመዋል፡፡ ስለሆነም በሽብር ድርጊቱ ቀጥተኛ ተሳታፊና አመራር ሰጭነት በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3(1)(3) እና 7(2) የተመለከተውን በመተላለፍ ተከሰዋል፡፡
13ኛ. ተከሳሽ ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም
የሽብር ቡድኑን የስልጠናና የምልመላ ክፍል የሆነውን 7ኛ ተከሳሽ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴርን በበላይነት መርተዋል፡፡ የሽብር ቡድኑ ከሊባኖስ ያስመጣውን አህባሽ የተሰኘ አክራሪ አስተሳሰብን በግዳጅ ለማሰልጠን 10ኛ ተከሳሽን (መጅሊስን) እንደሽፋን በመጠቀም ተንቀሳቅሰዋል፡፡ አክራሪ አስተሳሰቡን የማስፋፋት ጥረታቸውን ዋነኛ የቢሮ ስራቸው በማድረግ የህዝብን ስልጣን ያለ አግባብ ተጠቅመዋል፡፡ በግዳጅ ስልጠናውም በተለያዩ ዙር እና በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች 80000 (ሰማንያ ሺህ) ሙስሊሞችን ለማሰልጠን ሞክረዋል፡፡ በተለያዩ የስልጠና መድረኮች በተለይም በሐምሌ ወር 2003 በሐሮሚያ ዩኒቨርስቲ በተካሄደው የግዳጅ ስልጠና በመገኘት ህገ-መንግስቱን በተቃረነ መልኩ በኃይማኖታዊ ጉዳይ በቀጥታ ጣልቃ ገብተዋል፡፡ ህዝብ የሰጣቸውን ስልጣን በመጠቀም የእርሳቸውን አስተሳሰብ ያልተቀበሉ ወገኖችን አስፈራርተዋል፣ ዝተዋል፣ ሙስሊሙን ህ/ሰብ የተለያዩ ስያሜ በመስጠት ለመከፋፈል ጥረዋል፤ 20ኛ ተከሳሽን (አዲስ ዘመን ጋዜጣን) እና 20ኛ ተከሳሽን (ኢ.ሬ.ቴ.ድ፣ ቲቲቪን) በመጠቀም ንፁሃን የመብት ጠያቂ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችን በሽብር ፈርጀዋል፡፡ በአጠቃላይ የሽብር ቡድኑ ስራ-አስፈፃሚ አባል እንደመሆናቸው የሽብር ድርጊት እንዲፈፀም አመራር ሰጥተዋል፡፡ ስለሆነም በፈፀሙት ግዙፍ የወንጀል ድርጊት በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 5(1)(ረ) እና 7(2) የተመለከተውን በመተላለፋቸው ተከሰዋል፡፡
14ኛ. ተከሳሽ አቶ ፀጋዬ ኃ/ማርያም
የሽብር ቡድኑ የፀጥታ ክንፍ በመሆን አገልግለዋል፡፡ የቡድኑን ፀጥታ ለማስከበር በማቀድ የህዝብን ፀጥታ አደፍረሰዋል፡፡ በተለያ የአክራሪነት ስልጠናዎች በአካል በመገኘት ንግግር በማድረግ ለሽብር ቀስቅሰዋል፣ የአክራሪ አህባሽ አስተሳሰብን አበረታተዋል፣ የህዝብን ስልጣን በመጠቀም ዜጎችን አስፈራርተዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች የግዳጅ ስልጠናዎችን እንዲወስዱ አስገድደዋል፡፡ ሙስሊሙን ህ/ሰብ ለመከፋፈል በማሰብና አክራሪ አስተሳሰባቸውን ለማስፋፋት ከ7ኛ ተከሳሽ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ጋር በመሆን በርካታ የግዳጅ ስልጠናዎችን አዘጋጅተዋል፡፡ በተለይም በኢትዮ ቻይና ካምፓስ በመስከረም 2004 የተለያ ስያሜ በመስጠት ሙስሊሙን ለመከፋፈል ሞክረዋል፡፡ በተለይም ከ5ኛ ተከሳሽ የፌ/ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር በኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ላ የሽብር ድርጊት እንዲፈፀም አቅደዋል፤ ለአፈፃፀሙም ተንቀሳቅሰዋል፡፡ በዚህም በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3(1)(2)(4) እና 5(1)(ረ) የተመለከተውን በመተላለፍ ተከሰዋል፡፡
15ኛ. ተከሳሽ አቶ ሪድዋን ሁሴን
የሽብር ቡድኑ ቃል አቀባይ በመሆን ለህዝብ የተዛባ መረጃ አስተላልፈዋል፡፡ በተለይም በሰንደቅ ጋዜጣ 2004 እትም ላይ በሰጡት ቃለ-ምልልስ ህዝበ-ሙስሊሙን በሽብርተኝነት ፈርጀዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችን አደጋ አድርጎ በመሳል ህዝብን በህዝብ ላይ አነሳስተዋል፡፡ ቀደም ሲል የህውኃት /ኢህአዴግ የሽብር ቡድን ፀሀፊ በመሆን ለቡድኑ የሙያ፣ የልምድ እና የሞራል ድጋፍ ሰጥተዋል፡፡ ስለሆነም በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 5(1)(ለ) እና 7(1) የተመለከተውን በመተላለፍ ተከሰዋል፡፡
16ኛ. ተከሳሽ አቶ አህመዲን አብዱላሂ ጨሎ
የሽብር ቡድኑ ኃይማኖታዊ ሽፋን በመሆን በኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ላይ ከፍተኛ ዓለማዊና መንፈሳዊ ክህደት ፈፅመዋል፡፡ ከግብረ አበሮቻቸው ህገ-ወጥ የመጅሊስ አመራሮች ጋር በመሆን የህዝበ-ሙስሊሙ መሪ ድርጅት የሆነውን የኢ/እ/ጉ/ጉባኤ (መጅሊስ ለ2ኛ ተከሳሽ ህውኃት/ኢህአዴግ ፖለቲካዊ ግብ ማስፈፀሚያ ኃይማኖታዊ ሽፋን ይሆን ዘንድ ተንቀሳቅሰዋል፡፤ የህዝበ-ሙስሊሙ ብቸኛ ሚሲዮናዊ ተቋ የሆነውን የአወሊያን ተቋም “ለማፈራረስ” ተንቀሳቅሰዋል፡፡ የሽብር ቡድኑ ለሚያደርጋቸው ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች መሣሪያ በመሆን ህዝበ-ሙስሊሙን ለሽብር ጥቃት ዳርገዋል፡፡ ስሆነም ለሽብር ቡድ በሰጡት ከለላና ለሽብር ድርጊቱ ተቀዳሚ ረዳት በመሆናቸው በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 5(2) እና 7(1) የተመለከተውን በመተላለፍ ተከሰዋል፡፡
17ኛ. ተከሳሽ ፕሮፌሰር ሃገሮ ኤርሊኽ (በሌሉበት)
የእስራኤል ቴልአቢብ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ይሁዳዊው ሃጋይ ኤርሊኽ የሽብር ቡድን አስተሳሰብ በመቅረፅና የአፍሪካ ቀንድ ከባቢያዊ ፖለቲካ ለሀገራቸው እስራኤል ጥቅም አንፃር እንዲቃኝ በማድረግ ከአይሁዶች ጋር ጥብቅ የስራና የዓላማ ትስስር እንዳለው የሚነገርለትን የ “አህባሽ” አስተሳሰብ ማስፋፋት አስፈላጊ መሆኑን ለሽብር ቡድኑ እኩይ ምክር ሰጥተዋ፡፡ በተለይም ከ3ኛ ተከሳሽ የቀድው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር በነበራቸው የግል ቀረቤታ የሽብር ቡድኑ እኩይ ዓላማቸውን እንዲያራምዱ አድርገዋል፡፡ በመስከረም ወር 2004 በ20ኛ ተከሳሽ (ኢቲቪ) “Meet ETV” የእንግዝ ፕሮግራም ላይ በመቅረብ የአህባሽ አስተሳሰብ ለኢትዮጵያ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ስለሆነም ለሽብር ቡድኑ ለፈጠሩት የአስተሳሰብ መደላደልና ባደረጉት የልምድ፣ የሞራል ድጋፍና ምክር በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 5(1)(ለ) የተመለከተውን በመተላለፍ ተከሰዋል፡፡
18ኛ ተከሳሽ ዶ/ር ሰሚር አልሪፋዒ
በሽብር ቡድኑ አመራሮች ጋባዥነትና በ21ኛ ተከሳሽ ፔትራም ኃ/የተወ./የግል ኩባንያ ተባባሪነትና አስተባባሪነት ከሊባኖስ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የተደራጀ የአክራሪዎች ቡድን በማዘጋጀት ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ያደራጃቸው ሊባኖሳዊያን የአህባሽ ግዳጅ ስልጣና ላይ በአሰልጣኝነት እንዲሰሩ አድርገዋል፡፡ ቀኑና ወሩ ባልታወቀ በ2004 በጊዮን ሆቴል ከ13ኛ ተከሳሽ ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም ጋር በመሆን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እርሳቸው ከሚያራምዱት አክራሪ አስተሳሰብ ውጭ ያውን ኢስላማዊ አስተሳሰብ በሽብር ፈርጀዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም ሊታገለው እንደሚገባ በመግለፅ ለህገ-ወጥ እርምጃ አነሳስተዋል፤ ቀስቅሰዋል፡፡ ስለሆነም ለሽብር ቡድኑ የሙያ፣ የልምድና የሞራል ምክርና ድጋፍ በመስጠታቸውና ለሽብር ድርጊት በመስጠታቸው በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4 እና 5(1)(ለ) የተመለከተውን በመተላለፍ ተከሰዋል፡፡
19ኛ. ተከሳሽ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
የሽብር ቡድኑን ዓላማ ለማሳካት የሚያገለግል የህትመትና ስርጭት ክፍል ነው፡፡ የክፍሉ ጋዜጣ የሆነው አዲስ ዘመን ጋዜጣ መረጃን አዛብቶ በማቅረብ የሽብር ድርጊት እንዲፈፀም አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ በርዕስ አንቀፁና በገጽ 3 የፖለቲካ አምዱ ተከታታይ እትሙ ህዝበ-ሙስሊሙ አዲሱን የአህባሽ አክራሪ አስተሳሰብ መቀበል እንዳለበት ዛቻ አዞል ሀተታዎችን አሰራጭቷል፤ የመብት ጥያቄ እንቅስቃሴውን በሽብር ፈርጇል፤ በሀሰት የሽብርተኝነት ድርጊት አስፈራርቷል፡፡ የሽብር ቡድኑን አመራሮች በተለያዩ ጊዜ ቃለ-መጠይቅ በማድረግ ለሽብር ቡድኑ የሚዲያ ድጋፍ ሰጥቷል፡፡ ስለሆነም በፀረ-ሽብረተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 6 እና 11 የተመለከተውን በመተላለፍ ተከሷል፡፡
20ኛ. ተከሳሽ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት (ኢ.ሬ.ድ- ኢቲቪ)
ከህዝብ መገናኛ ብዙሃን አንዱ የሆነው ኢ.ቲ.ቪ. የተቋቋመበትን ዓላማ ወደ ጎን በመተው የሽብር ቡድኑን ዓላማ ለማሳካት የታሰቡና የታቀዱ የተዛቡ መረጃዎችን ለህዝብ በማድረስ ህዝብን በህዝብ ላይ አነሳስቷል፤ የህዝበ-ወኪሎችን በሽብር የፈረጀና በሀሰት ቅንብር ተሞላ “ጅሃዳዊ ሀረካት” የተሰኘ ገዛቢ ፊልም በተደጋጋሚ አሰራጭቷል፡፡ የሽብር ቡድኑ የሚፈፅማቸውን ህገ-ወጥ ድርጊቶች በማስመሰል ህዝብን ለማሳሳት ሙከራ አድርጓል፡፡ የሽብር ቡድኑ አመራሮችና ረዳቶች በተለያዩ ጊዜ ያደረጓቸውን የሽብር ቅስቀሳዎች አሰራችቷል፡፡ በዚህም የሽብርተኝነት ድርጊቱ ተባባሪ ሆኗል፡፡ ንፁሃንንና የሽብር ሰለባዎችን ሽብርተኛ በማስመሰል በሀሰት የሽብርተኝነት ድርጊት ህዝብን አስፈራርቷል፡፡ በተለይም የክርስትና እምነት ተከታዮች በእስልምና ተከታይ ወንድቻቸው ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው በማድረግ የእርስ በርስ ጦርነት ለማስነሳት ያልተሣካ ሙከራ አድርጓል፡፡ ስለሆነም በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 6 እና 11 የተመለከተውን በመተላለፍ ተከሷል፡፡
21ኛ. ተከሳሽ ፔትራም ኃ/የተወ/የግል ማህበር
የሽብር ቡድኑ የፋይናንስ ድጋፍ ሰጭ በመሆን በህግ ከተቋቋመበት የንግድ ተቋም ውጭ የአህባሽን አክራሪ አስተሳሰብ ወደ ኢትዮጵያ በማስመጣት ሂደት ላይ የሎጀስቲክ ድጋፍ ሰጥተዋል፡፡ በዚህም 18ኛ ተከሳሽ ዶ/ር ሰሚር አልሪፋዒይ የተባሉ ሊባኖስዊያንና እርሳቸው ያደራጁዋቸው ሊባኖሳዊያን አሰልጣኞች ወደ ኢትዮጵያ በማስመጣት ሂደት ላይ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ተከሳሹ በ3ኛ ተከሳስ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ፊማ የታዘዘውን በቦሌ ክ/ከተማ የሚገኝ 100000 ካሬ ሜትር (አንድ መቶ ሽህ ካሬ ሜትር) ቦታ ለአህባሽ ማሰልጠኛ ተቋም ግንባታ ይውል ዘንድ ኃላፊነት ወስዶ ተንቀሳቅሷ፡፡ በአጠቃላይ ከፍተኛ የገንዘብ ወጭ በማድረግ ለአህባስ አስተሳሰብ መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረግ የሽብር ቡድኑን ረድተዋል፡፡ ስለሆነም በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 5(1) (ሐ)(መ) እና 7(1) የተመለከተውን በመተላለፍ ተከሷል፡፡
2ኛ ክስ
(16 እና 21ኛ ተከሳሾችን በተመለከተ)
ወንጀሉ
በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብን እና ሽብርተኝነት በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀፅ 31(1)(ሀ)(1) የተመለከተውን በመተላለፍ፡-
የወንጀሉ ዝርዝር
16ኛ ተከሳሽ አቶ አህመዲን አብዱላሂ ጨሎ
ተከሳሽ አህባሽ የተሰኘውን አክራሪ አስተሳሰብ ለማስፋፋት በማቀድ መጠኑ 203000000.00 (ሁለት መቶ ሦስት ሚለዮን ብር) የሆነ ምንጩ ያልታወቀ ገንዘብ በርሳቸው ፊርማ ብቻ እንዲንቀሳቀስ በማድረግ በሽብር ቡድኑ የሚያዘጋጃቸውን የግዳጅ ሥልጠናዎች ወጭ ሸፍነዋል፤ ለ5ኛ ተከሳሽ ለፌ/ፖሊስ ኮሚሽን አባላት የሽብር እንቅስቃሴ የውሎ አበል ክፍያ በመስተት፣ የህዝበ-ሙስሙን እንቅስቃሴ ለማኮላሸት ለተመደቡ ግለሰቦችና የደህንነት አባላት የው አበል በመክፈል፤ በግፍ ለሚወነጀሉ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች የሀሰት ምስክር ለሚሆኑ የአህባሽ አስተሳሰብ አራማጆች አበል በመክፈል የሽብር ድርጊቱ ቀጥተኛ ረዳት በመሆንና ሽብርተኝነትን በገንዘብ በመርዳታቸው በአዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀፅ 31(1)(ሀ)(1) የተመለከተውን በመተላለፍ ተከሰዋል፡፡
21ኛ. ተከሳስ ፔትራም ኃ/የተወ/የግል/ማህበር
የሽብር ቡድኑ የፋይናንስ ድጋፍ ሰጭ ክንፍ በመሆን በህግ ከተቋቋመበት የንግድ ተቋነት ውጭ አክራሪ አስተሳሰብን ከፍተኛ በጀት በመመደብ ረድቷል፡፡ ተከሳሹ ምንቹ ያስታወቀ ግምቱ $30,000,000.00 (ሰላሳ ሚሊዮን) ዶላር ገንዘብ ህጋዊ በማስመሰል ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት የንግድ ተቋሙ ራሱን ከማጠናከር ጎን ለጎን አህባሽን ለማስፋፋት ተጠቅሞበታል፡፡ ከ1996 ጀምሮ በህቡዕ ሲንቀሳቅስ የነበረውንና በጦር ሃይሎች 3 ቁጥር ማዞሪያ የሚገኘውን የአህባሽ ማሰልጠኛ ተቋም ሙሉ በሙሉ ዓመታዊ በጀቱን በመሸፈን ሲረጁ ቆይቷል፡፡ የተከሳሹ ስራ አስኪያጅና ባለቤት አቶ አብዱልከሪም በድሪ ያላቸውን የገንዘብ አቅም በመጠቀም ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ትስስር በመፍጠር አህባሽን ከሊባስ ወደ ኢትዮጵያ በማስመጣት ሂደት ላ የአምባሳደርነት ሚና ተጫውተዋል፡፡ በዚህም ፔትራም ሃ/የተወ/የግል ማህበር በኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ላይ ለደረሰው የህገ-መንግስት ጥሰትና የሽብር ድርጊት የገንዘብ እርዳታ ያደረገ በመሆኑ ተከሳሽ በአዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀፅ 31(1)(ሀ)(1) የተመለከተውን በመተላለፍ ተከሷል፡፡
የማስረጃ ዝርዝር
ሀ/ የሰው ምስክር
- መላው የኢትዮጵያ ህዝብ
ለ/ የሰነድ ማስረጃ
- 10000 ገጽ የተለያ አስረጂ ሰነዶች
ሐ/ የድምፅ ከምስል ማስረጃ
- 15 ቴራ ባይት ማስረጃ
መ/ የፎቶ ግራፍ ገላጭ ማስረጃዎች
- 2000 ፎቶዎች (በቁጥር)
ሠ/ በፍ/ቤት ትዕዛዝ የሚቀርቡ
1. በብሔራዊ መረጃና ደህንነት ቢሮ የሚገኙ ሚስጥራዊ ሰነዶች ከብሔራዊ መ/ደህንነት
2. የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች በማዕከላዊ የደረሰባቸውን ስቃይና የግዳጅ ቃል እንዲሰጡ የደረሰባቸውን ጫና የሚያሳይ የድምፅ ከምስል ማስረጃ፣ ከፌዴራል ወንጀል ምርመራ (ማዕከላዊ)
3. ኢቲቪ በጅሃዳዊ ሀረካት የተሰኘ የሀሰት ዘጋቢ ፊልም ባስተላለፈበት ፊልም ላይ የተጠቀማቸው ፊልሞች ሙሉ ይዘት ከኢቲቪ
4. የህውኃት/ኢህአዴግ የሽብር ቡድን በተለያዩ ጊዜ ያደረጋቸው ህቡዕ ውይይቶች፣ እቅዶች፣ ሴራዎችና ቃለ-ጉባዔዎች፣ ከድርጅቱ ጽ/ቤት
5. የጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አማካሪዎች የሚያቀርቧቸው ጥናታዊ ጽሑፎች ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ
6. የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የግል ማስታወሻ ደብተር ከባለቤታቸው ወ/ሮ አዜብ መስፍን
7. የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችን የመብት ጥያቄ ለመቀልበስ፣ ለማኮላሸትና ለማምከን የተደረጉ ሚስጥራዊ ውይይቶች ቃለ-ጉባዔዎች ከሁሉም የሚኒስቴር መ/ቤቶችና ከመጅሊስ፡፡
©መአኮ