ከፋሲል የኔዓለም
(የኢሳት ጋዜጠኛ)
ወንድሞቼ ዳንኤል፣ አብርሃም፣ የሽዋስና ሃብታሙ ይፈታሉ በመባሉ በጣም ደስ ብሎኛል። በመፈታታቸው ደስ እየተሰኝን የአገዛዙን ፖለቲካዊ ጨዋታ ማየቱም አይከፋም። ከዚህ ቀድም እንዳልኩት ነው፤ አገዛዙ እድሜውን የሚያራዝመው በሰላማዊ ትግል እና በትጥቅ ትግል መካከል ያለውን የሃሳብ ልዩነት በማራገብ ነው። ሰላማዊ ትግልን የሚያቀነቅኑ ሃይሎች እየጠነከሩ ሲመጡ፣ የትግሉን መሪዎች ያስርና ህዝቡ “ሰላማዊ ትግል አያዋጣንም” ብሎ ወደ ትጥቅ ትግል ፊቱን እንዲያዞር አድርጎ አደጋውን ይቀንሰዋል። የህዝቡ ትኩረት ወደ ትጥቅ ትግል ሲዞር ደግሞ፣ የታሰሩ ሰላማዊ ታጋዮችን ይፈታና የፖለቲካ ምህዳሩንም ትንሽ ከፈት አድርጎ ” አዲስ የተስፋ ዳቦ” ይሰቅላል ። ህዝቡም እንደገና በሰላማዊ ትግል ተስፋ ያደርግና ትጥቅ ትግሉን ለመቀላቀል ልቡ ያመነታል- የታጋዩን ልብ እየከፋፈሉ የመግዛት ፖለቲካ ። የእነ አብርሃን መፈታት “ሃሳብን ከፋፍሎ በመግዛት የፖለቲካ ስልት ” ካየነው ስሜት ይሰጣል።
የተፈቱትም ሆነ ለወደፊቱ የሚፈቱት ታጋዮች ቆራጥ የሰላማዊ ትግል አቀንቃኞች ናቸው፤ ከመጀመሪያውም የታሰሩት ሰላማዊ ትግሉ በምርጫው ላይ ተጽኖ እንደሚፈጥር ስለታወቀ ነው። ከምርጫው በሁዋላ፣ በተለይም ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ጓዙን ጠቅልሎ የትጥቅ ትግል ወደሚደረግበት በረሃ ሲወርድ፣ ህዝባዊ ንቅናቄው በከፍተኛ ደረጃ አድጓል። ይህን ህዝባዊ ንቅናቄ ለመቀልበስ አገዛዙ ፣ ሰላማዊ ታጋዮችን በመፍታትና የፖለቲካ ምህዳሩን ትንሽ ገርበብ በማድረግ የህዝቡን ልብ ለመከፋፈል የተለመደ ስልቱን ተግባራዊ ለማድረግ አቅዷል። ይህ ስትራቴጂ የተበላ እቁብ በመሆኑ ከእንግዲህ ውጤት ያመጣል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው። አንደኛው የትግል አማራጭ ( የትጥቅ ትግሉ) ጉልምስና እድሜ ላይ ደርሷል፤ አገራችን በውጭ ስትወረር ካልሆነ በስተቀር ህዝቡ በዚህ ደረጃ ተነቃንቆ ትጥቅ ትግሉን ለመቀላቀል ፍላጎት ሲያሳይ ስመለከት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ” ትግሉን መቀላቀል እንፈልጋለን” እየተባለ ከአገር ቤት በየቀኑ የሚደወለው ስልክ አስገራሚ ነው፤ እንዲያውም ስልክ የምታነሳው ባልደረባዬ ” የኢትዮጵያ ህዝብ በመሉ ጫካ ከገባ ነጻ አውጪዎች ነጻ የሚያወጡት ማንን ነው? በማለት በጣም ተገርማ ጠይቃኛለች ። ከአገር ቤት ስለሚደወሉ ስልኮች ደግሞ አገዛዙ በቂ መረጃ አለው፤ የህዝቡንም ስሜት ያውቀዋል። ይህን የተባለበትን ቁማር እንደገና ለመቆመር የተነሳውም ለዚህ ነው። እኔ ሁለቱም የትግል ስልቶች በስልት ከተካሄዱ ተደጋጋፊ ናቸው ብዬ አምናለሁ። ስርዓቱን በውስጥም በውጭም በመወጠር፣ ልክ እሱ የታጋዮችን የትኩረት አቅጣጫ በመከፋፈል የነጻነት ትግሉን ለማዳከም እንደሚሞክረው ሁሉ፣ ታጋዮችም በተመሳሳይ ስልት የእሱን የትኩረት አቅጠጫ በማሳት ሊያዳክሙት ይችላሉ። የእነ ዳንኤል መፈታት ትግሉን ወደፊት ይገፋዋል እንጅ አያዳክመውም።
እግረ-መንገዴን ስለሚያብከነክነኝ አንድ ነገር ትንሽ ልበል። ሃሳቡን ዮና ብር የተባለ ጎበዝ ጸሃፊ አንስቶት አይቻለሁ ። እንደሚታወቀው በዘፈቀደ እየታፈሱ የሚታሰሩና የሚፈቱ የአገሬ ብርቅዬ ልጆች ይቅርታም ካሳም ተከፍሏቸው አያውቅም። ዘመዶቻቸው እነሱን ለመጠየቅ ሲመላለሱ የገንዘብ ፣ የጊዜና የጉልበት ኪሳራ አጋጥሟቸዋል። ልጆቻቸው የወላጆቻቸውን ፍቅር እንዳያገኙ በመከልከላቸው በአእምሮ እድገታቸው እና በወደፊቱ ህይወታቸውም ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽኖ ይፈጠርባቸዋል። ስራ መስራት ባለመቻላቸው የኑሮ ቀውስ ያጋጥማቸዋል። ሽብርተኛ በመባላቸውም የሞራል ኪሳራ ይደርስባቸዋል። የግል ህይወቴን የተመለከቱ ጉዳዮችን ማንሳት ባልፈልግም፣ ለዚህ ውይይት ስለሚጠቅም ለዛሬ አንድ ነገር አነሳለሁ። ከ5 ዓመታት በፊት፣ ወደ ሆላንድ ከመጣሁ በሁለተኛው አመት፣ የገጠመኝ አንድ ትልቅ ችግር ነበር። ኢሳት እንደተቋቋመ፣ እንደዛሬው በቂ የሰው ሃይል ሳይኖርና በየአገሩ ስቱዲዮዎች ሳይመሰረቱ፣ የሆኑ ሃይሎች “ኢሳትን ማስቆም አለብን” ብለው ተነሱና በእኔ ላይ ክስ መሰረቱ። እነዚህ እኩይ ሰዎች፣ ” ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ይሰራል፤ ህገወጥ ገንዘብ ያገኛል፣ ሰዎችን በህገወጥ መንገድ ወደ አውሮፓ ያስገባል ወዘተ” የሚል ደብዳቤ ጽፈው ለፖሊስ አስገቡ። የተጠቀሱት ወንጀሎች በጣም አደገኛና ከአገር የሚያስባርሩ ወይም የሚያሳስሩ ናቸው። ያው ጥቆማ ቀርቧልና ፖሊስም ምርመራ ጀመረ። ሁለት ጊዜ ተጠርቼ ተጠየኩ፤ መርማሪዎች ቤታችን ድረስ መጥተው አኗኗራችንን አዩት። የባንክ አካውንቴ ተመረመረ፣ ስለኢሳት አጀማመርና የገንዘብ ምንጭ ሳይቀር ተጠየቀኩ፣ የሁዋላ ታሪኬ ሁሉ ተመረመረ። የመንግስት ክፍያም ለሁለት ወራት በግማሽ ቀነሰ። ሰዎች መከሩኝና በነጻ ጠበቃ ወደሚያቆም ድርጅት ሄድኩ። በሳምንቱ፣ ከጠበቃዬ ጋር ፍርድ ቤት ቀረብኩ። ፍርድ ቤቱ ፋይሉን አገላብጦ እንደቆምኩ ውሳኔ ሰጠ። “በአጉል ጥርጣሬ ለተደረገው ምርምራ የይቅርታ ደብዳቤ ይጻፍ፣ ለቃለምልልስ በሚል ሁለት ቀናት ስራ በመፍታቴ ክፍያ ይከፈለው፣ የታገደው የሁለት ወር ክፍያ ይለቀቅለት እንዲሁም በእሱና በቤተሰቡ ላይ ለደረሰው የሞራል ካሳ መዘጋጃው በመስፈርቱ መሰረት ይክፈለው” አለ። አጠቃላይ የገንዘብ መጠኑ ተስልቶ እንደሚነገረኝ፤ በክፍያው ላይ ቅሬታ ካለኝመ ይግባኝ እንድል፣ ስራዬን እንደሚያደንቁ አበረታተው አሰናበቱኝ። በፍጹም ማመን አልቻልኩም። ከቀናት በሁዋላ የይቅርታ እና የገንዘብ ዝርዝር የያዘ ወፍራም ደብዳቤ ደረሰኝ። ጠበቃው ” ገንዘብ አንሶኛል የምትል ከሆነ ይግባኝ እጠይቃለሁ” አለኝ። (እሱም ራሱ ለአንድ ቀን ፍርድ ቤት ስለቀረበ ብቻ ጠቀም ያለ ክፍያ አግኝቷል። ) አይሆንም አልኩት።
የ97ቱን ምርጫ ተከትሎ ከሌሎች ጋደኞቼ ጋር ለአንድ አመት ከ ስምንት ወር ያክል ጊዜ ታስሬ በነጻ ተለቅቄያለሁ። በታሰርኩባቸው ወራት ስራ ብሰራ ኖሮ ላገኝ የምችለውን ገንዘብ እንርሳውና በተለያዩ ምክንያቶች ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ኪሳራ ደርሶብኛል። ባለንብረት የነበርኩ ሰው ንብረት አልባ ሆኜ ተፈትቻለሁ፤ ለዚህ ሁሉ ግን ካሳ ሊከፈለኝ ቀርቶ የተወሰደብኝ ኮምፒዩተር እንኳ አልተመለሰልኝም፤ ስጠይቃቸው ” ገና መቼ ተነካህና ነው” ብለው አሰናብተውኛል። በሰው አገር ለሁለት ቀናት ተጠርቼ በመጠየቄ ብቻ ጠቀም ያለ የሞራል ካሳ ክፍያ ሲከፈለኝ፣ በአገሬ ለረጅም ጊዜ ታስሬ ስፈታ፣ የሞራል ካሳ ሊከፈለኝ ቀርቶ የተወሰደብኝ ንብረት እንኳ በወጉ አልተመለሰልኝም። ልብ በሉ! ለአንድ ቀን ታስሬ ብፈታ ኖሮ የሚሰጠኝ የሞራል ካሳ በዚያው ልክ ይጨምር ነበር። እነርዕዮት፣ የሽዋስ፣ ሃብታሙና ሌሎችም በግፍ የታሰሩት ወገኖቻችን ሁሉ ፍትህ የሚያገኙበት ቀን እሩቅ ባለመሆኑ እንጽናናለን እንጅ፣ የደረሰው ጉዳትስ ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም።