Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የሰላም ትግሉ በኢትዮጵያ (መዝጊያ) –አንዱዓለም ተፈራ –የእስከመቼ አዘጋጅ

$
0
0

ረቡዕ፤ ሰኔ ፲ ቀን፤ ፳ ፻ ፯ ዓመተ ምህቱረት ( 6/17/2015 )

እንዴት ትግሉን በትክክል ወደ ፊት ማስኬድ ይቻላል?
eskemecheበመጀመሪያ ደረጃ ሁላችን መረዳት ያለብን፤ ይህ ትግል በአምባገነኑ ወገንተኛ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርና በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ብቻ ነው። ይህ መነሻና መድረሻ ተደርጎ መወሰድ አለበት። አሁን ሁላችንንም ወጥሮ የያዘን፤ ትግሉን ለምን በአንድነት፤ የሀገራችን የነፃነት ትግል አናደርገውም? የሚለው ጥያቄ ነው። አንዳችን ከሌላችን የተለየ አመለካከት ስለያዝን ብቻ፤ በመካከላችን ጠላትነት ነግሦ፤ “አንተ ወያኔ ነህ!” የሚል ወፍ ዘራሽ ውንጀላ አስቀድሞ መወርወር ትክክል አይደለም። በመደማመጥ በውይይት ሊፈታ የሚችለውን የሃሳብ ልዩነት፤ እንደ የፖለቲካ ውጊያ አድርጎ መበጣጠሱ ጎድቶናል። የተለያየ ሃሳብ ይዞ፤ በሚስማሙበት አብሮ መስራት ይቻላል። የግድ በሁሉም ነገር ሁላችን መስማማት የለብንም። ይህ መሠረታዊ የዴሞክራሲን ሀ ሁ የተቀበሉ ሁሉ የሚስማሙበት ጉዳይ ነው። ታዲያ ለምንድን ነው በመካከላችን መግባባት ያልቻልነው? የዛሬው የማጠቃለያ ጽሑፍ የሚያተኩረው፤ በመካከላችን መግባባትን እንዴት መፍጠር እንችላለን? ምንስ ብናደርግ ትግሉን ወደፊት ማስኬድ እንችላለን? ካለንበት የምስቅልቅል ሀቅ ወጥተን ወደፊት ለመሄድ ከየት እንጀምር? ለሚሉት መልስ በመሥጠት፤ ትክክለኛ አስተባባሪና አስተማማኝ መፍትሔ አቅርቦ፤ ትግሉ በትክክል እንዲመራና ወደ ሕዝባዊ ድሉ ጉዟችን እንዲያቀና መጋበዝ ላይ ነው።

ትግል ወደው የሚገቡበት ክስተት አይደለም። ትግል የሙያ መስክ አይደለም። ትግል ግድ ብሎ የሚመጣ የኅብረተሰብ ክንውን ነው። የአንድ ሀገር ነዋሪዎች፤ በሀገራቸው ያለው ሥርዓት “ትክክለኛ አይደለም!” “ከመስመር ወጥቷል!” ብለው ሲነሱና የሥርዓቱ አራማጅ እንጃላችሁ ሲል፤ ሕዝቡ በእምቢታ ሲነሳ፤ ሕዝባዊ ትግል ነው። ይህ ደግሞ ሁሌ የሚደረግና ለአንዳንዶቹ የሙያ ዘርፍ ሆኖላቸው የሚከርሙበት መኖሪያ አይደለም። በአንድ የታሪክ አጋጣሚ የሚከሰት ነው። አሁን ሀገራችን ላለችበት ሁኔታና ታጋዮች ላለንበት ሀቅ፤ በቂ ምክንያት አለ። ምክንያቱን መርምረን ማግኘት አለብን። ሌሎችን ለዚህ ምክንያት ተጠያቂ ማድረጉ አግባብነት የለውም። ያንን ምክንያት የፈጠርነውና አስተካክለንም ወደፊት መሄድ የምንችለው፤ እኛው ነን። ለየብቻችን መፍትሔ ፈላጊዎች ብቻ ሳንሆን፤ ለየብቻችን ተግባሪዎቹም በመሆን በየበኩላችን ሩጫ ይዘናል። ለምን? ይህ የሀገራችን የሁላችን ጉዳይ አይደለም! ታዲያ ለምን በአንድነት የምንዘምትበትን መንገድ አንፈልግም። በመካከላችን ያለው፤ የትግሉን መንገድ በሚመለከት ያለ ልዩነት አይደለም። በኔ አመለካከት፤ ያሉትን ልዩነቶች በሶስት ከፍዬ አስቀምጭቸዋለሁ።

የመጀመሪያውና ዋናው ማጠንጠኛ፤ የትግሉን መሠረታዊ ምንነት በሚመለከት ያለው ልዩነት ነው። ይህ የትግሉን ሂደት ቅደም ተከተል በሚመለከት የተወሰነ አይደለም። ይህ መሠረታዊ የሆነውን ለምን እንደምንታገል የሚደነግገውን ጉዳይ የሚመለከት ነው። “በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ሀቅ ምንድን ነው?” የሚለውን መመለሱ ላይ ነው። ለዚህ የሚሠጠው መልስ ወሳኝ ነው። ከዚህ ተነስቶ ነው የትግሉ እጅና እግር የሚታወቀው። በሀገራችን ምን ዓይነት ሥርዓት አለ? ምን ዓይነት የፖለቲካ ፍልስፍናና የአስተዳደር መመሪያ ያቀነቅናል። የዚህ ሥርዓት ጉዳቱ ምንድን ነው? የሥርዓቱስ ባለቤት ማነው? በዚህ ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ይላል? የት ነው የምንቆመው? ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ወይንስ ከአምባገነኑ ወገንተኛ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ጋር? እዚህ ላይ፤ ትግሉ የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን ለመፍታት የሚደረግ ሩጫ አይደለም። ትግሉ የነፃነት ጥያቄ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎችን ምርጫ አይደለም የያዝነው። ሁለት ሰፈሮች ብቻ ነው ያሉት። አንደኛው የአምባገነኑ ወገንተኛ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ሲሆን ሌላው የሕዝቡ ሰፈር ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ሆኖ ነው፤ አምባገነኑን ወገንተኛ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር እምቢ ያለው። ስለዚህ አንድ ኢትዮጵያዊነት ብለን፣ አንድ ወገናችን ብለን፣ አንድ ሀገራችን ብለን፣ አንድ ትግል ብለን መነሳት አለብን።

ሁለተኛው ደግሞ፤ የሀገርን ጉዳይ ለድርጅቶች ኃላፊነቱን መሥጠቱ ላይ ነው። ትግሉን አሽከርካሪዎች ድርጅቶች ናቸው ብለን፤ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ኃላፊነቱን በነሱ ላይ ጥለናል። ሀገሪቱ እኮ ለተደራጁት ብቻ አይደለችም። ለሁላችንም እኩል ነች። ታዲያ ኃላፊነቱን ሁላችን እኩል መካፈል የለብንም? በርግጥ በድርጅት የተሰባሰቡ ሰዎች ጠርቀም ያለ ጉልበት አላቸው። እናም ቅድሚያ ይሰለፋሉ። ይህ ማለት ግን፤ ኃላፊነቱ የነሱና የነሱ ብቻ ነው ማለት አይደለም። ይልቁንም በሀገራችን ላይ ባለው ሀቅ፤ ቅድሚያ መስለፉን ዘንግተውታል። እናም በየድርጅቶቻቸው መርኀ-ግብር ተቆልፈው፤ ከመጠጋጋት ይልቅ መራራቁን መርጠው፤ ከመፍትሔ ይልቅ የችግሩ አካል ሆነዋል። ስለዚህ፤ ኃላፊነቱ በሌሎች፤ ማለትም በግለሰብ ባለነው ሀገር ወዳዶች ላይ ተጥሏል። ለሀገር መታገልና ለድርጅት መታገል አንድ አይደለም። በርግጥ ትግል ሳይደራጁ አይካሄድም። ያ ድርጅት ደግሞ ትግሉ ምን ዓይነት መስመር እየተከተልን መሆናችንን ይናገራል። ለድርጅት መታገል ማለት፤ ድርጅትን መነሻና መድረሻ አድርጎ፣ የኔ ድርጅት ትክክለኛ ስለሆነ፤ በኔ ድርጅት ብቻ ተመርታችሁ ትግሉን ቀጥሉ የሚል ቀጭን ትዕዛዝ ማስተላለፍ ነው። በርግጥ ይሄ በብዙ የተለያየ የሚመስል ነገር፤ ነገር ግን መሠረቱ አንድ በሆነ መልክ ይከሰታል። መሠረቱ ደግሞ፤ ለግል ማስብና ለሀገር ማሰብ በሚለው መካከል ያለው ልዩነት ነው። የያዝነው ትግል የግል ትግል አይደለም። የሀገር፣ የነፃነት ትግል ነው።

ሶስተኛውና ማጠቃለያው፤ መፍትሔውን በሚመለከት ያለው ልዩነት ነው። አንድ ሀገር፣ አንድ ኢትዮጵያዊነት፣ አንድ ትግል ብለን ከተነሳን፤ የአንድነቱ ትግል ዋናና አማራጭ የሌለው ነው። አንድነትን ከግል የተግባር እርምጃ ማስቀደም አለብን። አዎ! ትግሉ ተጀምሯል። ሰዎች በተለያየ የትግል መስክና ሁኔታ ከገዥው ቡድን ጋር እየተፋለሙ ናቸው። ነገር ግን ትግሉ ትክክለኛ ስኬት እንዲኖረው መቀጠል ያለበት፤ ከዓላማ ጋር ተቆራኝቶ እንዲቀርብ ሲደረግ ነው። ግቡ አንድነትን የሚመሠርት፣ አስተማማኝ የሆነና፤ ሁሉን ለአንድ ዓላማ አሰባስቦ የሚያታግል እንዲሆን፤ አንድነቱ አሁኑኑ፤ ባለንበት ደረጃ ቅድሚያ ሊሠጠው ይገባል። ይህ ማለት፤ አንድ ሳንሆን የተያዘው ትግል አደጋው ከፍተኛ ስለሆነ፤ ታጋዮች በየደረሱበት የትግላቸው ሂደት፤ ከሌሎች ጋር እንዲሆን ማድረግ ነው። ይህ ግድ የሚለው፤ የሚከተለውን አደጋ ተረድተው፤ የያዙትን ትግል ለአንድነቱ እንዲገዛ አድርው፤ ድሉንም ሆነ ጉዳቱን ለአንድነቱ እንዲያስረክቡ ነው። ይህ ማለት፤ በመሰባሰብ ለሚመሠረተው የአንድነት ድርጅት፤ ሙሉ ተገዥ ሆኖ፤ በሙሉ ልብ በኢትዮጵያዊነት መምጣት ነው። በተደጋጋሚ የተገለጹትን የትግሉ ራዕይና መታገያ ዕሴቶች በመቀበል ወይንም አስፈላጊ የሆኑ ማሻሻያዎችን በማድረግ፤ አንድ ድርጅት፣ አንድ ትግል፣ አንዲት ኢትዮጵያ፣ አንድ ኢትዮጵያዊነት ብሎ መነሳት ነው። መታገያ ዕሴቶቻችን የሚከተሉት ናቸው፤

፩ኛ.   በኢትዮጵያዊነታችን አንድ ነን። በሀገራችን፤ በኢትዮጵያዊነታችን  የፖለቲካ ተሳትፏችን እናደርጋለን።

፪ኛ.   ሀገራችን ኢትዮጵያ፤ ዳር ድንበሯን አስጠብቀን ለኛው ለኢትዮጵያዊያን እናደርጋታለን።

፫ኛ.   በሀገራችን በኢትዮጵያ፤ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን እናደርጋለን።

፬ኛ.   በኢትዮጵያዊነታችን የግለሰብ ዴሞክራሲያዊ መብቶቻችንን እናስከብራለን።

እንግዲህ ከላይ ያሉትን ሶስት ነጥቦች ትኩረት ሠጥተናቸው፤ በቁጥር ፩, ፪, ፫ ትና ፬ የሰፈሩትን መታገያ ዕሴቶች አንግበን፤እና አሁን ያለንበትን የያንዳንዳችንን ሁኔታ ራሳችን መርምረን፤ በግለ ሰብ ደረጃ፤ እኔ በኢትዮጵያዊነቴ ምን ማድረግ እችላለሁ? የሚለውን እኔ በኢትዮጵያዊነቴ ምን ማድረግ አለብኝ? ከሚለው ጋር አቆራኝተን፤ መሰባሰብ አለብን። በድጋሜ፤ እያንዳንዱ ድርጅት የያዘው የራሱን ድርጅት ትግል አንጂ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ የነፃነት ትግል አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ የነፃነት ትግል የሚካሄደው በኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ነው። እናም ለኢትዮጵያ ሕዝብ የአንድነት የነፃነት ትግል ጥረት እናድርግ። የዚያ አካል እንሁን። ይሄን በሚመለከት ለመተባበር ዝግጁ የሆናችሁ ጥሩኝ፤ ወይንም ወደኔ መልዕከት በመላክ ቅረቡ። የዚህ ትግል ባለቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ፤ አንድ ግለሰብ ወይንም አንድ ድርጅት አይደለም።

eske.meche@yahoo.com   http://nigatu.wordpress.com


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles