ከሥርጉተ ሥላሴ 21.08.2015 /ሲወዘርላንድ – ዙሪክ/
„ … በሀገሬ ውስጥ በነፃነት መኖር የሰው ልጅነቴ መለኪያ ነው ብዬ አምናለሁ። ይህን የሚከለክለኝን ማንኛውም ኃይል ከመቃወምና የምችለውን ከማድረግ ወደኋላ አልልም። ይህን ሳደርግ የሚመጣውን ዕዳ ተቀብዬ ነው።“ የሞት ፍርድ በወያኔ ሃርነት ትግራይ ዘራዊ አስተዳደር የተፈረደበት ዬአርበኛ ፕሮፌስር ብርሃኑ ነጋ – ቃል።
ምዕራፍ – ሦስት፤
እንዴት ናችሁ የሐገሬ ልጆች?! ደህና ናችሁ ወይ? በጨለመ የጥላቻ ዋሻ ውስጥ ተሁኖ ተጫባጭ እውነትን ማዬት አይቻልም። ባለገርዶሹን የጥላቻ ጥቁር ዋሻ በመደርመስ ብቻ ፀሐይ ትወጣለች። ጸሐይዋ ስትወጣ ይነጋል – የጥነት ሆነ የቅናት ቅምጥም – ይራገፋል።
የማከብራችሁ – ባለፈው ጊዜ ክፍል ሁለትን በዚህ ነበር የቋጨሁት፤
„ለእኛ ቁርባናችን – ታቦታችን – ጸሎታችን – ስግደታችን – ሳላታችን – የወልዮሽ የባህል ዝክረ ነገራችን – የሃይማኖት ማዕዳችን – ቤተ አምልኳችን ንግሥት ኢትዮጵያ ናት። ለነፃነት ፍላጎታችን ማደሪያ የተመረጠው ደግሞ ሥህነ – ቤዛ ነው። እሱ የእርቅ ጉባኤን ከአድማስ ወዲህና ባሻገር መሳላል – የሥርዬት መክሊት መገናኛ መርከባችን አንባችን – ነው።“
ከብሄራዊ ፍላጎት ጋር መፈጠር – አነባቢ (Vowel።)
ኢትዮጵያዊነትን አሳምሮ ይተርጉመዋል – አናባቢ (Vowel) ስለሆነ፤ ሥህነ – ቤዛ ኢትዮጵያዊነትን አደላድሎ – የማመሳጠር አቅሙ በውስጥነት ውስጡ አድርጎ ነው።
አናባቢ ከሌላ ተነባቢ ቃል አይኖርም። (BCDFGHJK) (ሀለመሰሸቀበተ) አናባቢ ባይኖር ዬዓለም የማድመጫ ዓይኖች እውር በሆኑ ነበር። የኑሮም የማሰቢያ ጭንቅላቱ ትንፋሽ አልቦሽ ግዑዝ በሆነ ነበር። ወንጌላዊው ዮኋንስ „በመጀመሪያ ቃል ነበረ። ቃልም በእግዚአብሄር ዘንድ ነበረ፣ ቃልም እግዚአብሄር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሄር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፣ ከሆነውም አንዳችስ ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም። በእርሱ ሕይወት ነበረች፣ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ይበራል፣ ጨላማም አላሸነፈውም። ዮሐንስ ወንጌል ምዕ. 1 ከቁጥር 1 እስከ 5“ ሲል ያስተማረው የቃልን ህይወት የመፈጠር ሆነ የመነበብን ሚስጢር በመኖር ሲያመሳጥልርን ነው። ያ ቃል ነው ዓለምን፣ ሰማይና ምድርን፣ ህይወት ያላቸውንና የሌላቸውን የፈጠረ። ስለዚህ ለእኔ የኢትዮጵያዊነት ዜግነትን ታማኝ ህዋስ ጥልቅ ሚስጢሩን ተነባቢም – አናባቢም ሆኖ በመገኘት እረገድ ሥህነ – ቤዛ ቤተኛነቱ በመሆን ያከበረ ህብራዊ ቃል – ኢትዮጵያዊ ቋንቋ መሆኑን በጥልቀት – አስተውዬበታለሁ። እንዲህ በተዋርድንበትና በተናቅንበት ዘመን በ እውቀት ላይ የተመሠረተ ንጥር ሁለገብ ብቃቱ – መካሻ! ይህም ብቻ ሳይሆን የሀገሩ የኢትዮጵያ ሁለመና ባለትርጉም መምህር መሆኑንም በሚገባ በጥልቀት – ተርድቻለሁ። መነሻው ኢትዮጵያ መድረሻው ኢትዮጵያ፤ እንዲያውም አለፍ ብሎ አፍሪካንም! ኢትዮጵያ ተኮር ዝንባሌውን እና የአፍሪካዊ ፓለቲካዊ ችግሮች በሚመለከት „ዬአፍሪካ ቀንድ የውይይት ፕሮግራምን“ በአሜሪካን ሀገር በኒዎርክ ከተማ በመስራችነትና በንቁ ተሳትፎ ለአምስት ተካተታይ ዓመት ያደረጋቸው፤ የአዲስ ዓለም ራዕይ የቀደምቶች መንገድ የተከተለ፣ የፓን አፍሪካንዚም ንድፍ ተግባራዊነት – የተመነ መሆኑን ያመሳክራል። በአሜሪካን ሀገር ፊላደልፊያ ላይም „ኢንቢልታ“ መጽሄት የእናቱን ሐገሩን ሁለንትና ችግር ለመጋራት ውስጥነቱን ያሳዬበት መድረክ ነበር። ስለዚህም ጎጥ ላይ ያልተቀረቀረው ውድ ሰብዕናው ፈተናውን በአጥጋቢ ውጤት አልፏል!
በፅሞና በቂ ጊዜ ወስጄ ያለፈባቸውን ሂደቶች፣ ውስጡን የገለጸበት መንገዶችን – በተደሞ፣ ከመሬት ሰቅ ላይ በትክክሉ ሆኜ በአራቱም ማዕዘን በአንክሮ ሁሉን ተመክሮዎቹን – መረመርኳቸው፤ ከኢትዮጵያ ህዝብ ወላዊ ብሄራዊ ጸጋ ሆነ ማዕከላዊ አጀንዳ ማዕቀፍ የወጣበት አንዲት ዬነቁጥ ግድፈት – አላገኘሁበትም። ስለዚህም በተለይ ዬአዲስ አዕምሮ ብቁ ሰለዴ ባለቤቶች የሆናችሁ የእኔ ወጣቶቼ /ጌቶቼና ልዕልቶቼ/ መምህራቸውን ይከተሉ ዘንድ ተግቼ በዚህ ዙሪያ መሥራት እንዳለብኝ – ወስኛለሁ። ግዴታዬም ነው። ለእኔ ነገ ነግቶ – ታይቶኛልና። በአርበኝነት ግንባር ላይ ሆነ በማናቸውም ሁኔታ ያሉት ወገኖቼ ቢሆኑ ሥጦታቸውን ያከብሩት ዘንድ አብክሬ በአፅህኖት ላስገነዝባቸው – እወዳለሁ። ሥህነ – ቤዛ ወላፈኑ በግራ በቀኝ የበዛበት ምክንያቱን እኔ ሳዳምጠው የመዳኛችን ፈውስ መንገድን በመምረጡ ነው። በመልካም ነገሮች ዙሪያ ፈተናው – መጠራቅቁ ያዬለ፣ መንገዱም እጅግ ጠባብ ነው፤ ሲያልፉት ግን ገነት! ሁልጊዜም በግል ህይወት ሆነ በማህበራዊ ህይወት፤ እንዲሁም በፖለቲካ ይሆን በሃይማኖታዊ አቋም፤ በተጨማሪም በሙያዊ መብትና ግዴታም ዙሪያ ቢሆን በተዕቅቦ የሰከኑ ሥነ – ምግባሮች ተፈታታኝ ወይንም ተቀናቃኝ መንፈሶች አዘውትረው ወጆቦችን – ያበራክቱባቸዋል። ስለምን? እራሳቸውን መሆን ዬቻሉ ብስል ወገኖች ያልተገቡትን ሥነ -ምግባሮች – ስለማያስጠጉ፣ ፊትም ስለማይሰጡ። ጥንቃቄያቸው ብልሃት – ዘለቅ፣ ዓላማቸው ስልት – ቀደም፤ ሥልጣኔያቸው መርህ – ገብ ስለሚሆን አውሎው ያዬለ ነው። ቀናዎች ወይንም የአዎንታ አርበኛ መንፈሶች ሥነ – ድንግልና በመንደርተኝነት ዕሳቤ ወይንም በአስተሳሰብ ድህነት ለማስገሰስ ስለማይፈቅዱ። የሰብዕናቸው ሁለንትናው ፀ ———-አዳ፤
ዬመንትዮሹ መስተጋብራዊ ውህድ መንፈስ ከእኛ የሚጠብቀው ብሄራዊ ግዴታ።
የአናባቢነት ውህድ መንፈስ የመንገድ ጠራጊው ዬድርጁው የጀግና አንዳርጋቸው ጽጌ መንፈስ የማያንቃላፋ የማይሞት ስለመሆኑ በፍቅር በመስተጋብር ያዋድዱት ዘንድም በትህትና – ለቅኖቹ ዝቅ ብዬ አሳስባለሁ። ወጣቶችና ቅንነት ያልነጠፈባቸው ወገኖቼ በራሱ የተማመነ ማስተዋልን እንዲፈቅዱለት – አሳስባቸዋለሁ። ከዚህ ላይ ብልህነትን የሚጠይቅ ብሄራዊና ወቅታዊ ግዴታ አለብን። ወያኔ ሃርነት ትግራይ ዬጀግናው አንዳርጋቸው ፅጌ የህዝብ ፍቅር መንፈስ ገናናነት „እራቁት¡“ ለማድረግ በቅናት ድብን ብሎ ስለ አበደ፤ የለመደበትን ዬስውር ደባ ሥራ ማስኬጃ የሆነውን የአቶ መብራቱ ገ/ህይወት ወይንም በበርሃ ሥማቸው የአቶ በረከት ስዕሞንን እውር ራዕይ፤ ቹቻን ተንትርሶ የተዘጋጀውን የኑዛዜ በድን ድምጽ አመድ ማድረግ የቅድሚያ ተግባራችን ሊሆን ይገባል። ይህም ማለት በፈላስማው አንዳርጋቸው ፅጌ ሥም ይወጣል የተባለውን መጸሐፍ ዬኢትዮጵውያንን ክብራችን ገፎ ለውርዴት የዳረገን፤ በእስር ቤት እንኳን ብትን አፈር የነፈገን ሥርዓትን „በቃኝ“ ከምንልባቸው ጉልበታም እርምጃዎች ቀዳሚው በመሆኑ፤ ይህ ደባ የታሪካችን ውርዴም ስለሆነ – አዲሱን የለበጣ ሴራ የበቀል ማዋራረጃ መጸሐፉ ነውና፤ ከገብያ ውጪ በማድረግ የመጋዝን እራት እንዲሆን ቁጣችን – ፀፀታችን – እልሃችን – ቁጭታችን አቅማችነን በማጥገብ „አንገዛውም“ በማለት ተግባር ላይ እንገኝ ዘንድ እንደ አንድ ኢትዮጵያው ዜጋ ጥሪዬን – በአክብሮት አቀርባለሁ። እስኪ ልዬው፣ እስኪ ልፈትሸው ብለን ውርዴታችን በገንዘብ በመሸመት የንጹህ መንፈሳችን ቤተኛ እንዳናድርገው! በነፃ ህወሓት ቢያድለው እንኳን – እንዳናስጠጋው። ያን የጀግና መንፈስ ስቃይ እንዴትስ – አንገዛዋለን? ያ የድብደባ የወገኞቻችን የስቃይ ዬጩኽት መንፈስን በራችን ከፍተን ቤት ለእንግዳ እንዴትስ እንለዋለን?፤! የዛ ዬኢትዮጵያዊነት የማንነታችን ሰቆቃ ረስተን መጸሐፉን ብንገዛው ለብሄራዊ ዕንባችን ድፍረትም ንቀትም ነው። ቢያንስ በገንዘባችን ሀገራዊ ወኔን ሁነኛችን እናድርገው! ይህ ለይደር የሚቀጠር አይደለም። „ቁርጥ ያጠግባል“ ቁርጣቸውን ማሳወቅ – በተባ እርምጃ። ከእነሱ ጋር ሆነ ከጄሌዎቻችው ጋር እራሱን ላልቻለ ጥገኛ መንፈስ ህብረትም ትብብርም ሊኖረን አይገባም። እራሱን ችሎ የቆመ ብቁ ርቁቅ ሥልጡን – ቅዱስ – መሪ መንፈስ አለን- እኛ! የምን ብድር የምን ውሰት – ለባንዳነት ————-?~!
ክብረቶቼ – ኢትዮጵያዊነታችን እምናበለጽገው ቢያንስ በእጃችን በሚገኘው ሙሉ አቅም፣ በተጻራሪ የቆመውን መንፈስ ቅስሙን ለመስበር አሁኑን ተግባርን ስንውጥ ብቻ ይሆናል። „በቃን!“ ቃሉ እራሱ ሁለገብ ነው። የህወሓት ጠረን ሁሉ ድብዛውን ለማጥፋት መዶሻችን ነው „በቃን!“ እርግጥ ነው አሙካ – ደጅጠኝ – ፍርፋሪ ለቃሚ – እፎዎ መንፈሶች ዝቅ ብለው ለአራጃቸው – ያረግሩ ዝል መንፈሳቸውን – ይገበሩ፣ ድብድባ የወጣውን የበታችነታቸውንም – ያቆላምጡ። እኛ ግን ደማችን ውርደትን – ባርነትን – የበታችነትን፤ ሥነ – ልቦናዊ ቅኝ ተገዢነትን ይጸዬፈዋልና ልዩ ቃናችን ኢትዮጵዊነታችነን ድርጊት እናስታጥቀው። ዛሬ እስር ቤት ውስጥ የዱካ ማስቀመጫ ብትን አፈር ቦታ ተነፍጎል፤ አንድ ጆሮውም አይሰማም የጀግናችን ዬጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፤ አካል የሌለው አገልጋይ ቃለ ወንጌል ሳይቀር ፈቃድ ተነስቶ አባ ትርጉም ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ መንፈሱን ጉስቁል ለማድረግ፤ በሥነ ልቦናው እዬትዘናኑ እዬተሳለቁ ይገኛሉ – አራዊቶች፤ ዛሬ የአርበኛ አበበ ካሴ ጥፍር በግፍ ተነቅሎ የመክራ ዝክረ ሙዚዬም እየሆነ ነው፤ የእመቤቴ የጀግኒት ዬወይንዬ ሞላ ማህጸንስ ነገ ፍሬ ያበቅል ይሆን? በካቴና ቃለ ምልስስ ላይ ያዬነው የአርበኛ አቡበክርስ – ዛሬ የወንጀል ቅጥረኞችን በእስር ቤት በማሰማራት ማገዶውን አንዱአለም አራጌን ያስደበድባሉ – ለነፃነት የቁም ሰማዕትነት። ሌሎችንም፤ ምን ዬማያደርጉት አለና …. ምን የማይሰማ መራራ ዜና አለና፤ ይህን መጸሐፍ ከገዛን እኛ ስቃዩን እንደ ፈጸምን አንደ ፋሽስንትም እንደ ተባበርን ያስቆጥራል።
ስለ እስር ቤት ካነሳሁ ትንሽ ምራቂ ነገር ልበል። ወላጅ እናቴ ምህርት ጠይቃ በተሰጠኝ ምህረት የጫካ ኑሮዬን ትቼ አንድገባ አደረገችኝ። እውነት ለመናገርም የግንኙነቴ መስመሩ ስለተቋረጥ ሎጅስቲኩ ሆነ ሁሉ ነገር ከባድ ስለሆነ ግድም ነበር። በምህረት ከገባሁ በኋላ ግን ጎንደር ባታ እስር ቤት ታሰርኩኝ። ሰው በምህረት ገብቶ እንዴት ይታሠራል?! በቬርሙዳ ትርያንግል ሥርአት እኮ ነው ህወሓት የሚመራው። ስፈታ ደግሞ ያን ጊዜ ብዙ ነው በ50000 የኢትዮጵያ ብር ዋስ በቁም እስር ነበር። መንፈሴም አካሌም ሥነ – ልቦናዬም ታስሮ። ዋሴንም የተከበሩ ሸሕ ሲራጅን ሊያስቀምጧቸው ስላልቻሉ ሀገራቸውን – ለቀቁላቸው። ቅብም ቢሆን ፍርድ ቤት፣ ክስ፣ ምስክር የሚበላው በመዲናችን አዲስ አባባ ላይ ብቻ ነው የሚሠራው። የዛሬን ባላውቅም ያን ጊዜ ከክ/ ሀገር ጀምሮ እስከ ነጥብ ጣቢያ አንድ የህወሓት ባለዘር ሜዳሊያ ባለጊዜ ካድሬ ያሰረውን፤ አስተውሉ ወገኖቼ አሳሪው ሀገር ቢለቅ ወይንም ቢሞት ወይንም ከድርጅቱ ቢባረር ሌላው – አይፈታውም። እዛው ተረጅቶ ሞት ብቻ ይጠብቀዋል – ወገናችን። ሌላው ማጣሪያ የሚባለው ነገር ደግሞ የላሜ ወለደች ዓይነት ነው። የእስረኞች ሥም ዝርዝር በከተማ የህዝብ አደባባዮች – ይለጠፋል። በፈለገው ዓይነት በቂም፤ በቅናት፤ በክፋት አንድ ሰው ከጠቆመ ያ እስረኛ መፈቻ የለውም። ምርመራው ደግሞ ታሥራችሁ ልማዳችሁን አንድታቀኑ መገደድ ነው። ግራ እኮ ናቸው። የቬርሙዳ ትርያንግሉ ሥርዓተ አራዊት እንዲህ ነው። በፍጹም ሁኔታ በክ/ሀገርና ከዛ በታች ያሉ የእስረኛ አያያዝ ሁኔታ ከአዲስ አባባ ጋር መወዳደር ቀርቶ – አይቀራረብም። ዓይነቱም ይዘቱም የተለዬ ጭፍን ሸጎሬ ነው። ድፍን ታውቃላችሁን?!
ሚስጢር ዘለቁ – ነገረ ኢትዮጵያዊነት፤
ያደለው ከሚስጢሩ ጋር መፈጠሩ ብቻ ሳይሆን በቁምነገር አብሮ ይኖራል። ነገረ ኢትዮጵያ የሚስጢራት ሁሉ የሥነ – ፍጥረት ሁሉ ነፍስ ነው። ኢትዮጵያዊነት የገድላት – ሩኽ ነው። ኢትዮጵያዊነት የፍጥረት – ህሊና ሥነ – ምግባር ነው። ኢትዮጵያዊነት የጸሎት መንፈስ ነው። ይመራል – ያስተዳድራል፤ ስናጠፋ – ይመክራል ብቁ መካር ነውና። ስናኮርፈው ያቆላምጣል – ሩህሩህ ነው፤ ህጉን አብዝተን ስንተላለፍ ደግሞ ቆንጠጥ አድርጎ – ይገስጻል፤ ስንዳፈረውም ይፈራዳል – ይቀጣል። ዳኝነቱ ሚዛናዊ ከመሆኑ በላይ ራሱን የቻለ ተቋም ነው – ህሊና ላለው፤ ዜግነቱ ውስጡ ለሆነ ሁሉ መዕዋለ ህይወቱ ት/ቤት ነውና – ያስተምራል።
የአትዮጵያዊነት ሥነ – ህግጋቱ የመሆን መቻል ሰማይና ምድር ናቸው። ገሃዱ ዓለም እና መንፈሳዊውን ዓለም ያስማማ በትረ – ዓምድ፤ በፍቅር እያዋዛ ያዋደደ የዘመናት የተደሞ አናት ነው – ኢትዮጵያዊነት። ኢትዮጵያዊነት የቀለሞች ሁሉ አዲስ ቀለም ነው። ኢትዮጵያዊነት የነገዎች ሁሉ አዲስ ቀን ነው። ኢትዮጵያዊነት ሲፈጠር ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ የሚስጢር ሊቀ – ሊቃውንት ነው። ኢትዮጵያዊነት እንደ ወንዝ ዳር ዕጽዋት በጋ ከክረምት፤ መኸር ከጸደይ እዬለመለመ እያሸተ የሚሄድ፤ እርጅና ከቶውንም ዝር የማይልበት ሁልጊዜ ለሁለመና በነፋሻማ ጤናማ አዬር የሚጎበኝ የጤና ፍውሰት ነው። ሙቅ የሆነው ወጣት ፍቅሩ ከቶም አይጠገብም። ቋሚ መንፈሱ ትጉኽ ገበሬ ነው፤ ማራኪ አቀራረቡ በቁሙ የጸደቀ የሁሉዬ በመሆን እኩላዊ፣ ራስነትን የፈቀደ ነው።
ኢትዮጵያዊነት ከኩራት በላይ መኩሪያ፤ ከጋሻ በላይ መከታ፤ ከጥላ በላይ መጠለያ፤ ከመቻል በላይ መቻቻል፤ ከማክበር በላይ መክበር፤ ከማድመጥ በላይ መደመጥ፤ ከሚስጢር በላይ መመሳጠር፤ ከታማኝነት በላይ ታማኝ፤ ከትህትና በላይ ትሁት፤ ከፍቅር በላይ ፍቅራዊነት (Loveism)፤ ከትእግስት በላይ ታጋሽነት፤ ከአብሮነት በላይ ዬአብሮዊነት ልዕልና ነው። ኢትዮጵያዊነት በራስ የመተማመን የደም ማህተም ነው። የነጠረው መንፈሱ ቅኝ ተገዝቶ በፍጹም – አያውቅምና። እራሱን ሆኖ የኖረ ብቻም ሳይሆን ሌላውንም በውስጡ ያኖረ የአደራ ትውፊት ነው። የእኔ የሚለው – ሁሉ ያለው፤ ሁሉንም – የሆነ፤ ለሁሉም ለመሆን የሚችል – ስኩን የመኖር ሥነ – ደንብ ነው – ኢትዮጵያዊነት። ተዝቆ የማያልቀው መክሊቱ የፈለቀው ከእውነት ማህደር ብቻ ነውና። ተመርቆ የተፈጠረ በመሆኑ አስተዳደራዊ ሆነ ጣልቃ ገቢያዊ ፈተና አያጣውም፤ ግን ተቀናቃኙን ድል የመንሳት ተስጥዖው ደግሞ ገድላማ ነው። ዬኢትዮጵያዊነት ድፍረቱ የሚቀደው ከምንጩ ከአለው ረቂቅ ጸጋው – ከራሱ ነው። አለው! ትውስት ክፍሉ አይደለም፤
በሌላ በኩል ኢትዮጵያዊነት ለመንፈስ የርትህ ብሩኽ የችሎት አደባባይ ነው። ኢትዮጵያዊነት በተፈጥሮው የዳኝነት ውሎ ነው። ኢትዮጵያ ሀገራችን ህግ ናት። የተፃፈውም ሆነ ያልተጻፈው ህጓ እሷን ለዬት ብላ፤ እኛ ልጆቿም ኢትዮጵያውያንን ለዬት ብለን ኑሯችን እንድናስተዳድር ይመራል። በኢትዮጵያ ማህጸን ውስጥ የተፈጠረው ኢትዮጵያዊነት አማናዊው ሲሆን በክርስትና እምነት ከዘመነ ብሉያት በፊት በህገ ልቦና አምላኩን የተቀበለ፤ ሃዲስ ኪዳንንም የወደደ ዬፈርኃ እግዚአብሄር ማማ ሲሆን፤ ዬእስልምናም ሃይማኖትን በሚመለከትም፣ ታሪክን የቀደመ፣ የሐዋርያነት ተግባር የፈጸመ የተግባር አንቱ ጉልላት ነው። ለኢትዮጵያዊነት ሃይማኖት አለኝ፤ እማመልከው አምላክ አለኝ ብሎ ማመን ርስተ – ጉልቱ ነው። ተፈጥሮው ነው ማለት ይቻላል። እርግጥ ነው በተፈጥሮ የሚያምኑትንም የራሱን አካላትንም – አይጋፋም። ሳሃ የሌለበት ሥልጡኑ ማንነት – ኢትዮጵያዊነት!
ኢትዮጵያዊነት በግጭቶች ማህል እንኳን ዬስምምነትን ስበት የመወለድ አቅሙ ከጸሐይ ጉልበት በላይ ነው። ኢትዮጵያዊነት ሥርዬት ፈላጊነቱ የመልካም ነገሮች ዓውደ ምህረት እንዲሆን – አድርጎታል። ኢትዮጵያዊነት ነብያትን ቀድሞ ያናገረ፤ ሳይንቲስትን የመራ፤ ቅዱሳንና የፈጠረና ከተለያዩ የዓለም ክፍላት ሰማዕታትን ደናግላንን ሐዋርያትን ሳይቀር በብቃቱ ዬጠራ፤ በብልህነት ያስተናገደ – የገሃዱ ዓለምና የመንፈሳውው ዓለም ፍጹማዊ ዬመርኽ የአብርኃሙ ማዕዶት ነው።
ኢትዮጵያዊነት ጠላቱን የሚያስተምረው ምክንያት ፈልጎ ነው። በዬአጋጣሚዎች እሱን ለማጥቃት የሚነሱትን የዶግ አመድ የሚያደርግበት አቅሙ የሚቀዳው ከሰማዩ ዳኛ ነው። እንሆ የወያኔ ሃርነት ትግራይን በ40 ዓመት ህይወቱ ሉሲ ድንቅነሽን አስቀድሞ ዕውቅና አሰጥቶ፤ ህወሓት በተኛ በ40 ዓመቱ ከእንቅልፉ የቀሰቀሰ፤ የማያልቅ ወይንም የማይቋረጥ ትኩስ ዬአቮል ቡና ፏፏቴ ነው። የማንቃት መዳህኒት በመዳፉ ያለው፤ ቅንኛ – ቀና – ቅኔኛም። ወንዳታ! ዛሬ በጠላቱ በህወሓት መንፈስ አስለፍልፍን አስርፆ ነጋ ጠባ „ኢትዮጵያዊነት፤ ሐገራችን፤ ኢትዮጵያዊ ወገኖቻችን“ እያሰኜ ጠላቶቹ በፖሊሲ ያሰሩትን፤ ገድለን ቀብረነዋል ያሉትን ቅዱስ መንፈስ በልሳናቸው ሲቃጁ ውለው እንዲያድሩ ያደረገ የጀግኖች ቁንጮ፤ አንበሳ ነው ኢትዮጵያዊነት! የመሆን የትጋት – የንጋት ገበሬ!
አዬ! ዓፄ ዘመን እንዴትና እንዴት አድርገህ ነው ኢትዮጵያዊነት – የምትከሰው! ብርሃኑ ሲነጋ በሃቅ – ታታመ። በእንቁላል ውሃ ተገናባ። ዬማግስትነት ክብሩ – ታወጀ። ዘመን ተናገረ – ያደመጠውን በሐዋርያነት ስለ ኢትዮጵያዊነት ልቅና ዓለም መሰከረ ….. ሲፈጠር ከብሄራዊ ፍላጎት ጋር የሆነው ሥህነ – ቤዛችንም እንኳን ደስ አለህ። ትጋትህ ከጥዋቱ ለዚህ ልቅና ነበር፤ … ለጋ ዕድሜህን ለበርሃ የሸለምከው። ዝንፍ ሳትልም በዞግ ንክኪ ከቶውንም ሳትጠመድ በማተብህ የጸናኽው፤ በተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ ብሄራዊ ፍላጎትን ዕውን ለማድረግ አፍላነትህን – የሰጠኽው። ጉልምስናህንም ለሀገርህ ለኢትዮጵያ እንደ ዘመኑ እድገትና ብልጽግና በነፃነትና በዴሞክራሲ አሰራር ያለህን እምነት ውስጥህ በማድረግ፤ የናፈቀህን ዴሞክራሲ ርትህ ዕውን አንዲሆን፤ የምትፈልገውን የእኩልነት ምድር እናትህን ለማድረግ ወደ ኋላ የማትል የኢትዮጵያ ዘላቂ ልጅ። ለአንዲት ሰከንድ በእምስ ዬመንደርተኛነት አጀንዳ ጊዜህን ያለባከንክ የልዕልት ኢትዮጵያ የተቋማት – ምርጥ ተስፋ። …. ኢትዮጵያዊነት ህግህ ያደረክ፤ ለኢትዮጵያዊነት ፍጹም ታማኝ የሆንክ የአዮ ትሩፋት …
ውድ ታዳሚዎቼ – በምዕራፍ ሁለት ጹሑፌ ፕሮፌስር ብርሃኑ ነጋ ሚስጢር ነው ብያለሁ። ስለምን? ሚስጢር መሆኑ ስለተገለጠለት። ስደት ሽርሽርሽር አይደለም፤ ፈተናው ያላችሁበት ነውና – ታውቁታላችሁ። ሁለተኛ ዜግነት መውሰድ – የስደቱን ውሃ ያዘለ ተራራ ለመሸከም፤ ጊዜያዊ ሆነ ዘላቂ ችግር መፍቻ የሚሆኑ ቁልፎችን ለማግኘት፤ ወይንም ቤተሰብ ከተመሰረተ በኋላ በስደቱ መንደር ዬልጆችን የተስፋ ትልም ለማሳካት፤ ቤተሰባዊ ኑሮን በአንድ ለማድረግ፤ ረቂቅና ወስብስብ ፈተናን ለማሸነፍ፤ ባይታዋርነትን ከግንባር ገፋ ለማድረግ ግድ የሚሉ ነገሮች – ይገጥማሉ። ባትወዱትም – ባትፈልጉትም። በማናቸውም ሁኔታ ይህን እርምጃ መወስድን አስፈላጊ የሚያደርጉ የተጽዕኖ ምሽጎች በዬአቅጣጫው ጦርነት – ይከፍታሉ። ታዲያ ትውልደ ኢትዮጵያዊነትን እንደያዙ በተደራቢነት ችግርን ለማስተጋስ ወይንም ለማሸነፍ ወይንም መንፈስን ለመረጋጋት እርምጃው ይወሰዳል – ዬተጨማሪ ዜግነት። ይህ ወንጀል አይደለም። የታህሳስ 10. 1948 ዓለምአቀፍ የሰብዕዊ መብት አስከባሪ ህግ „አንቀጽ 15 እንዲህ ሲል መብት ስለመሆኑ በአጽህኖት – ደንግጎታል።
- እያንዳንዱ ሰው የዜግነት መብት አለው።
- ማንም ሰው ያለፍርድ ዜግነቱ አይወሰድበትም፤ ወይንም ዜግነቱን የመለወጥ መብት አይነፈገውም“። ስደትና መከራውን – በስደት ያለፈ ሁሉ ስለምን ሁለተኛ ዜግነት መውሰድ እንዳለበት፤ ወሳኝና አስፈላጊ እንደሆነ – ይገነዘበዋል።
ወገኖቼ – ይህን ነጥብ ነጥዬ ማንሳት የፈለግኩት መሰረታዊ ምክንያት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን „ኢትዮጵያዊነትን አግላይ“ የሚል ተቀናቃኝ ተቀጥላ ሃሳብ ጎልቶ ስለወጣ ነው፤ ያን ከሥሩ የፈለሰ ሃሳብን በተጨበጠ ዕውነትን fact አቅርቤ እርባና ቢሱን፣ የፋደሰ ከንቱ የላመ አጀንዳ መቅበርም – ስላልብኝ ነው። በሌላ በኩልም ሚስጢር ከሚስጢሩ ጋር ስለመኖሩ የጭብጥ አቅም ያነሳቸው ትችቶች በተያያዥነት ስለ ነበሩ ብኩን ስለመሆናቸውም አስረግጬ ለመግለጽ ነው። እገረ መንገዴን ጠረግ ለማድረግም ጭምር ነው። አንቱው አመክንዮ „ታላቋን አሜሪካን የፈጠረ የኔ ማንነት ነውና እኔ ያለኝ ነገር ሌላው የሌላው ብቻም ሳይሆን፤ ዓለምን ፈጣሪ ስለሆነ ስለምን ብድር እሄዳለሁ? ማንነቴ ኢትዮጵያዊነቴ ይበቃኛል – መቅድም ነውና“ ማለት፤ ለዛውም ሁሉ ነገር እያለው፤ እዬቻለ፤ እራሴን ሆኜ መኖሬ የክብር ክብር፤ የግርማ ግርማ፤ የሐሤት ሐሤት፤ መርሄ ነው ብሎ ኢትዮጵያዊነቱን የፈቀደ፤ ኢትዮጵያዊነቱን የመረጠ፤ ኢትዮጵያዊነቱን የወደደ ከዚህ ጋር የተያያዙ ማናቸውም የስደት ውጣ ውረዶች ለዛውም በወጣትነት ዘመን ብዙ ወጣ ገብ ችግሮች ሳይበግሩት – መልካም ዕድሎችም ሳያታልሉት፤ እንዲህ በውሳኔው መዝለቅ የቀደመ – ሐዋርያነት ነው ለእኔ ለሥርጉተ ሥላሴ። ሥህነ – ቤዛ የትኛውም የስደት ፈተና አላሸነፈውም። ችግሮችን ተጋፈጦ ገዢ መሬቱን – ተቆጣጥሯል።
በዚህ ውስጥ ድፍረቱን፣ ቁርጠኝነቱን፣ ውሳኔ የመስጠት ጉልበታም አቅሙን፤ እራሱን ለመምራት ያለውን አቅም ወቄትም ማዬት ይቻላል። እራስን ማሸነፍ የወርቅ አንክብል ነው። እንዲህ ያለውን በውስጡ ለውስጥነት መርኽ የተገዛ መንፈስ ለሁላችንንም ዬአብነቱ ተመስጦ – ትውፊትን ቀልቦናል። ለአርበኞች ግንቦት ሰባት ውህደትም በአካል ሥህነ ቤዛ ያልተገኘበት መሠረታዊ ምክንያት የመጓጓዣ ሰነዱ ጊዜ ያስፈልገው እንደ ነበር – ከኢሳት አምስተርዳም – አዳምጠናል። ሳያበራ ብዕር የጨበጠ፣ ዬማይክ ራህብተኛ፤ የአትራኖስ ጉጉተኛ መንፈስ ሁሉ ዱላ /ቆመጥ/ ባለማቋረጥ ይቆረጣል፤ ዱላው ወይንም ቆመጡን አስተካክሎ ዓይንህ ጥርስህ ብሎ ከርክሞ ይዘጋጃል፤ ያው መሰናዶው ተዘውትሮ ለፕሮፌስር ብርሃኑ ነጋና ለመንትያው ይሆናል። አቤት! – ትእግስቱ! እንዲህ ዓይነት ሆደ ሰፊነት ብቻ ነው ኢትዮጵያን ከእነህልቆ መከራዋና ችግሮቿ መሸከም – የሚችለው። ሰለጠነበት – በመከራው። ኖረበትም። ፍጹም ያልተገባ፤ ከፖለቲካዊ መንገዶች የወጡ ከኢትዮጵያዊነት ሥነ ተፈጥሮም ያፈነገጡ ዬተቸዎችን – ከሰብዕ ዝቅ የሚያደርግ ዘለፋ ሁሉንም አስመችቶ – ቻለ። ይህ ከብረት ቁርጥራጭ የተሠራው ጥንካሬውና ብርታቱ ደግሞ እልፎች አጥር ቅጥር እንዲሆኑለት ግድ አላቸው። የመንደር ሆነ የጎጥ ሪጋ ቤት ባልደረባ ያልሆነው – ጥልቅነቱን ለማዳመጥ እንፈቅዳለን! ተግባሩ ብቻ ነው የስምሪታችን መሃንዲስ! ሩቅ አሳቢነቱ ቅዱስ መንፈሳችን ነው! …. የመሪነት ጥራቱ ርትህ ሰጪ ትርጉማችን ነው! ዓይናችን የህሊናችን ሚዛን ነው! እሱ ራሱ ነፃነት ነው።
ጽናትን ለዋጠ ኢትዮጵያዊነት – እኔ ምን እላላሁ? ምንስ አቅም አለኝ? እግዚአብሄር ይስጥልን ከማለት በስተቀር። ይህ ሰው በጣም እጅግ ሩቅ ነው። ይህን በእውነቱ በመከራ ብዛት ከሃገሩ ለሚፈልሰው ወጣት የዜግነት ብቃት ት/ቤት ተቋም ነው። በህልሜም በውኔም የሚነስተኝ በሀገሬ በኢትዮጵያ ብሄራዊነትን አጀንዳው ያደረገ ትምህርተ – ዜግነት፤ ፍትህን ማዕከሉ የሆነ ትምህርተ ሥነ – እኩልነት፤ ሰማያዊ የተፈጥሮ ሥጦታዎችን በአስኳልነት የተንተራሰ ትምህርተ ሥነ – ፍቅራዊነት በመደበኛ ትምህርትነት ሥርዓት ተቀርፆላቸው በመደበኛ ት/ቤት የሚሰጥበት፤ ሙያም ሆነ ዬሥራ መስክም አንዲሆኑ ምንአልባትም ወደ ኮሌጆች ወይንም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መግቢያም መስፈርት እንዲሆኑ መስከረምን እጠብቅ ነበር። እንሆ የአሁኑ መንገዱ ድባባዊ ውበት አለው። ዬዋዜማው ጣፋጭ ጠረን እያወደን ነው። እኔስ እላለሁ እንዲህ ዓይነት ስንዱነት፤ ቀዳዳውን ሁሉ ቀድሞ የደፈነ አንበሳነት፤ ልዑቅ ብልህነት ለወለደችህ እናትህ፤ ለምትማራቸው የፖለቲካ ድርጅት አካላትና አባላት ብቻም ሳይሆን እርምጃህ – ውሳኔህ – በፈተና የመጽናት በርነትህ የትውልድ አዲስ የሰንደቅዓላማ ትምህርት ቤት ስለሆነ – ታኮራለህ! እኛ የስደቱን መከራ መቋቋም ተስኖን የሌላ ሀገር ዜግነት ለማግኘት እንጠቁራለን – እንከስላለን፤ አንተ ግን የአብነቶች ቀንዲል ብርኃነ – ሞገስ ሆንክለት – ለኢትዮጵያዊ ዜግነትህ። ….. እንዲህ ነው ተምሳሌነት፤ እንዲህ ነው የመሆን መቻል አርበኝነት። እኔስ ኮራሁብህ። እኔስ አምነቴን ጣልኩብህ። እልፎችም ይህን መሠረታዊ በኽረ ጉዳይ ልብ ይሉት ዘንድም በትህትና – አመለክታለሁ፤ አብሶ ለነገ ዕንቡጥ ወጣቶቻችን። ነገ ማደሪያው በውል – የመንፈስ ማረፊያ አግኝቷል። ልጆች ከሚስሙት ነገር ይልቅ ከሚያዩት ነገር ብዙ ይማራሉ። ከሚጨበጥ ሃቅ ዕውቀትን – ይገበያሉ። „ልብ ያለው ሸብ“ ይላል ጎንደሬ ሲተርት ….
ሰሞኑን ኢትዮ ሚዲያ ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባርና የግንቦት 7 ለፍትህ ለነፃነትና ለዴሞክራሲ ሲዋህዱ „ዬኢትዮጵያ ህዝብ“ የቀረበትን ተያያዥ ጉዳዮችን ያብራራ – ክፍል ሦስት ከክፍል ሁለት ቀድሞ ከወንድሜ ከጋዜጠኛ ደምስ በለጠ አንድ ጹሑፍ አንብቤያለሁ። በጹሑፉ ጭብጥ ዙሪያ እምለው – አይኖረኝም። ቀደም ባሉት ጹሑፎቼ በአግባቡ ከውኘዋለሁና። ለአለቀበት ለተሸናፊ አጀንዳም ጊዜ ማዋስም አስፈላጊ – አይደለም። ነገር ግን የህሊና ዓይን የሚሆን ቁምነገር ባለው ዕውነት ላይ የተቃጣውን ዘላላ ስንኝ ከእርእሴ ጋር የሚሄደውን ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት እሱን ልሂድበት ወደድኩኝ። ወሳኝ ጉዳይ ነውና። ማስተዋልን – „ታላቋ አሜሪካን ሆነ ዓለምን የፈጠረው ማንነቴ ኢትዮጵያዊነት ዜግነቴን ለሚዛን ሊያቀርብ አይችልም፤ ምርጫዬም ህይወቴም“ ያለው አንበሳ እኮ ነው የግንቦት 7 ሊቀመንበር በቃሊቲ እስር ቤት ሆኖ ሃሳቡን አፍላቂ፤ በኋላም መሥራችነቱ ደግሞ ከመንፈስ መንትያ ወንድሙ ጋር በሀገረ – አሜሪካ። ይህ ድንግልናው ያልተገሰሰ መንፈስ ነው ከኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር መንፈስ ጋር የተዋህደው። የሥህነ – ቤዛን ተቀናቃኞቹን መፈናፈኛ የሚያሳጣ አሸናፊው የቀደመ ዝግጁነት፤ ተመስጥሮ የከተመበት ረቂቅ እጅግ ጥልቅ መንፈስን አለማወቁ ነበር ፆምን – ያስገደፈው።
„አያውቁንም እኛን አያውቁንም“ ይላሉ በህብረ ዜማ – ሁለመናው። በምንም ብሄራዊ አምክንዮ ግድፈት የሚታማባት ነገር የለም። ስንዱ ነው። …. እርግጥ ነው ያላወቅነው፣ ውስጡን ዘልቀን ለመመርምር ያልፈቀድን ወይንም የተሰወረብን ግን ተከድኖ የኖረ የራሳችን የእኛ ሲሳያችነን ዕውቅና ለመስጠት ድፍረት ስለሚያንሰን ብቻ ነው። ስለምን? ኢጎና የበታችነት ስሜት ቤተ ዘመዶቻችን – ስላደረግናቸው። እኔ እንደማዬው ፓለቲካ ሳይንስ መሆኑ ቀርቶ ግላዊ ጥላችን ጥግ ነው ብለን ስለምናምን። ፓለቲካ በተጨባጭ እውነት ላይ ስምምነት፤ ትብብር፤ መወያዬት፤ መግባባት፤ ለብዙሃኑ ፍላጎት ራስን ለማስገዛት መፍቀድ፤ ሰጥቶ መቀበል ወዘተ … መሆንም ረሳነው። በእውነቱ በብሄራዊ ሐገራዊ ጉዳይ ሙሉ ተሳታፊ ለመሆን እኔን ጨምሮ የውስጥ ለውጥ – ያስፈልገናል። ቀናዎች አይደለንም። ኃይል ፈጣሪነታችን ለአሉታዊ ነገሮች ብቻ ነው። ህወሓትማ – ተራሳ። በጎዊ ለሆኑ ለውጦች ጥቂቶች አልተዘጋጀነም – አንፈቅድም። ጎጥን መሻገር ነው የሰውነት መለኪያው። ኢጎን መደርመስ ነው ጀግንነት፤ መንደርተኝነትን ማሸነፍ ነው ለቀጣዩ ብሄራዊ ቀልም – ስምረት። አቅምን መለካት ነው ሥልጡንነት። በ እጅ በአለ ሃብት ብቻ መተንበይ ነው ብልህነት።
ወገኖቼ ኢትዮጵያዊነት የሚንጠለጠል፤ የሚለጠፍ፤ በጎን የሚታደርበት፤ ወይንም የሚለበጥ አይደለም፤ በውስጡ የሚኖርበት ሚስጢር እንጂ። አፈፃጸሙ፤ አተረጓጎሙ፤ አካሄዱ እንደ ተፈጠረበት መክሊት ይሆናል። ውድ የሐገሬ ልጆች ሥህነ – ቤዛ ዬአሜሪካ ዜግነት ባለመውሰዱ ወይንም አሜሪካዊ ባለመሆኑ እንደ አሻው መንቀሳቀስ – አይችልም። ሌላም በፖለቲካ አቋሙ የሚደርስበትን ማናቸውም ቅጣቱን መቋቋም የሚችልበት መጠለያ ተደራቢ ዜግነት – የለውም። ከኢትዮጵያዊነቱ ውጩ ጥበቃ የሚያደርግለት ምንም ምድራዊ ነገር የለም። በጣም የሚገርም የራስ መተማመን ጣዝማ ባለሃብት ነው። ብልህ ሆናችሁ ውስጡን አዳምጡት – በትህትና። ለዛውም እንዲህ በዬአቅጣጫው ጦር በተመዘዘበት ሁኔታ። … ህሊና የሚባለው ነገር እኮ ሚዛን ሊኖረው ይገባል። ለትችቱም – ለወቀሳውም። አሁን አሁን ሳስበው የበታችንት ስሜት አብዝቶ የሚንጣቸው የራሳችን ናቸው የሚባሉት ሳይቀሩ ፊት ለፊት ቢያገኙት ምን ያደርጉት ይሆን እንዲህ በደም ፍላት ሲወራጩ – እላለሁ። አርበኛ አንዳርጋቸው ጽጌ ሲታሠር ድምጽ ያላሰሙትም ዛሬ በተቆርቋሪነት ስለ አስተሳሰሩ ሂደት በፖለቲካ ተንታኝነት ይሁን በልብ ወለድ ጸሐፊነት ተስልፈው እያዬሁ ነው። ይህ ለእኔ ቆዳ መልስ ንሰኃ እንደ መግባት ነው። ያን ሰቅጣጭ ጥቃት – ጥቃቴ ነው ብሎ ለመቀበል ጊዜ ሊቀለበው ባልተጋባ ነበር። እስኪ ልሰብበት የሚያሰኝ አልነበረም። ዬብሄራዊ ውርዴት ብስጩነት አደብ ወይንም ታዛቢነት ሊሸለመው ባልተጋበ ነበር። የጥቃት ትኩስ እሬሳን አስቀምጦ ሠርግና መልስን – አዳምጠናል – ዛሬም እንዲሁ ተዛነፍ ነገር እናዳምጣለን ዘመኑን የምንታዘብ ሰዎች። ቢያንስ ፈጣሪ አምላክ „ሰው“ ብሎ ሲፈጥር የሠራለትን ሰማያዊ ህግ የእኛ – እንበለው።
መከራን መጋራት ኢትዮጵያዊ መለያችን ነበር። ችግርን መካፈል ፍጹማዊ ዓርማችን ነበር። ጥቃትን አለማስመችት የአደራ ሥጦታችን ነበር። እራቅነው ልበል ወይንስ አራቆትነው?! የሆነ ሆኖ የኔዎቹ – የኢትዮጵያዊነት ንባቡን ትርጓሜውና ሚስጥሩን እናመሳጥር፤ በተደሞና በአርምሞ ቢባል „ከአሜሪካው ዜግነት ኢትዮጵያዊነት ይበልጥብኛል። እንዲያውም አይመጣጠኑም“ ላለ የቀደመ መንፈስ ከዚህ በላይ ስለ ኢትዮጵያዊነቱ ከቶ ምን ሊገልጸው ይችላል? ምን አምክንዮ አለ ይህን ዕውንት (fact) ታግሎ ሞግቶ የሚረታ? የአውነት ጭብጥ ብቻ ነው የሰውን ልብ ቀልብ – የሚገዛው እንጂ የተገለበ ስሜት አይደለም። በስሜት ፌስታ አንጂ ውስጥን ማንበብ ሆነ መተርጎም – አይቻልም። በጥላቻም አምላክን ማስከፋት፤ የሆኖ ሆኖ ከተወረወረ ቀስት የሚጠብቀው አምላክ ጠበቀው እንጂ …. እንደሚቃጣው ጦርማ ….
የብልጹጉ ቅብዕ በብሄራዊ ፍቅር – ህትምተ።
አውነት ለመናገር እንዛ ቀኑን በሐሩር ጨለማውን ደግሞ በግርማ ሌሊት የሚተጉት ቅዱሳን ደናግል ዬአቨው እና ዬእናቶቻችን ጸሎት የሰጠን ሙሴ ነው ፕሮፌስር ዶር. ብርሃኑ ነጋ። ባለቤት ያልነበረው ዬብሄራዊ አመክንዮ መንፈሱ ጥግ አገኘ። ስለዚህም ሥጦታውን አናቅለው! ይህን የእውነት ውቅያኖስ እንቀበለው ዘንድም አቅም እንዲኖረን ፈጣሪያችን በፀሎት – እንጠይቅ። በፍቅር አሸናፊነቱ በእሱ ክህሎት ብቻ የተከወነ – አይደለም። የቀደመ „ቅብዕ“ አለበት። እደግመዋለሁ ይህን ቃል ህቅ የሚላቸው ደሞቼ ስላላችሁ የቀደመ „ቅብዕ“ አለበት። „ቅብዕው“ የጸሎት አጥር ከምንም ነገር በላይ ያስፈልገዋልና ሱባኤ በግል አቅም ያላችሁ፤ ህይወቱ ያላችሁ ትተጉበት ዘንድ እኔ ሎሌያችሁ ሥርጉተ ሥላሴ በአጋጣሚው በትህትና አሳስባለሁ። ትውልዱ ትውልድ እንዲሆን የምትሹ ቅን ወገኖቼ – መሆን ብቻ አንዲመራችሁ እባካችሁን – ፍቀዱ። የህልም ስኬት የሚገኘው በመሆን አውራ መንገድ ብቻ ነው እንጂ ገብያው በተፈታ በትነት ንድፈ ሃሳብ አይደለም።
ይህ ፎቶው ላይ ያለው ዬሥህነ – ቤዛ ህይወቱን ለመስጠት ቃል ያሰረባት የተግባሩ ቀለበት ነው፤ ለእርቃንነት አባት ለነበሩት ለሟቹ ሄሮድስ መለስ ዜናዊ የህቅታ ቋት፤ የኮሶ ተክል – ነበር። ሲዮት ያንገፈግፋቸው ነበር። በሽታቸውም ይነሳ ነበር። ሰንደቅአላማችን አይደለም በእጃቸው ለአንድም ደቂቃ በጎናቸው ተቀምጦ – አያውቅም። በመጤ እንደራሴ የተናጡ ስለነበሩ። „ሐገሬ“ ማለት „ኢትዮጵያ“ „ሰንደቅአለማዬ“ ማለት ዛራቸውን ያስነሳ ነበር። የሌለህን ነገር ከአንተ ሥር ያሉ ወይንም በቅርብህ የሚገኙ ሰዎች ሲያደርጉት ወይንም ሲኖራቸው የህሊና ስውር ቅጣቱ ስለሚነስትህ ያን የማዬት አቅም ምሶ መቅበር ቀዳሚ ተግባርህ ይሆናል። ለዚህም ነበር ለሰንደቅዓላማችን የማሰሪያ ህግ ተረቆ – የጸደቀበት። አርበኛ ያልሆነ የሐገር መሪ ባንዳን ይሾማል – ይሸልማል። ስለምን? አርበኛው ደረቱን ነፍቶ ቀና ብሎ የመሄድ አቅም ስለሚኖረው አርበኝነት አልቦሹ መሪ መንፈሱ እያዬ እንዳይቀጣ መሰሎቹን – ይመርጣል። ጀግኖችንና አቅም ያላቸውን ያባራቸዋል ወይንም ያገላቸዋል። ጎባጣው የሚፈልገው እንደ እሱ የጎበጠውን ወይንም ተጎንብሶ የሚሄደውን ነው። ቀና ብሎ የሚሄደውን የመቋቋም አቅሙ ሙት መሬትን የሙጥኝ ስለሚል። በነፃነት ትግሉም በዬነጥብ ጣቢያው አቅምን የሚበላው የዚህ በሽታ ውርስነት ነው። በአጋጣሚው አቅም ያላችሁም – አንድ በሉት። ለነገም ነቀርሳ ስለሆነ። የነፃነት ትግሉ ሰብል ትርጉሙ ከትንሹ ዛሬ መጀመርም አለበት።
ለዚህም ነበር ሄሮድስ መለስ ዜናው ከአርበኝነት ጋር የነበሩ የቦታ ሥሞች ሳይቀር እያደኑ፤ ኢትዮጵዊ ተቋሞቿን – እያሳደዱ፤ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ክብር እዬረገጡና እዬገፈፉም፤ ማናቸውንም የክብር መግለጫዎቻችን በሙሉ በጥርሳቸው እንዳያዟቸው ማለፍ አይቀርምና – ያለፉት፤ ለእርሳቸው ባንዳዊ መንፈስ ፍሰኃ ሲሉ፤ ያ የክብር – የሞገስ ተክሊል ባላውለታችን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅዓላማችን በሽታቸው ነበር። ለነገሩ – አይመጣጠኑም፤ ከወላጃቸው የወረሱት ባንዳነትን ነበርና። ለመሰሎቻቸውም ቢሆን ዛሬም – ይበጠብጣቸዋል። እንደ ጎደለ እንስራ ውሃ – ያንቦጫቡጫቸዋል። ለአርበኛው ደም ግን ዘውዱ ነው! ነገም ከኢትዮጵያ ህዝብና ከመሬቷ ከደረሰው የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማኒፌስቶ በደል ባላነሰ ብሄራዊ ቋሚ ሰንድቅዓላማችን ያሳለፈውን የ24 ዓመት የአፓርታይድ ዬተገላይነት ዘመን አሳር ሊክስለት የሚችለው ፍሬ ነገር ዬአንድ ዬአምክንዮ ዕሴት ብቻ ነው። ይህ ትውልድ ያሸነፈ ፓርቲ ቢያሸንፍ፤ ከንጹህ ተፈጥሮ ላይ ምንም ዓይነት የፍላጎት ነቁጥ እንዲኖርበት መፍቀድ – የለበትም። ከነተፈጥሮው እንዲዘልቅ እሱን ማስቀደም የመንፈሳችን ዓይን ሊሆን ይገባል። ይህ እንደ አንድ ተራ ዜጋ የአደራ ቃሌ ነው። ሰንደቅዓላማችን ይበቃዋል – ተቃጥሏል – ተቃሏል – ታስሯል – ተቀዷል፤ ከረጢት ሆኗል፤ በፍዳ ተቀቅሏል፤ „ቀብረነዋልም“ ብለውናል። የቻሉትን ያህል የቂምና የቋሳ መገበሪያ – አድርገውታል። „በቃን!“ የሰንደቅአላማችን መከራ የነፃነት ትግላችን መሪ መርህም ሊሆን ይገባል። የብሄራዊ ዜግነታችን መለያ የጋራ ጋሻ አሻራ ዓርማችን፤ የሁለንትናችን ቀላማም ውበት – ማራኪነት – ተወዳጅነት – አድማቂነት፤ ሳቢነት፤ ተፈቃሪነት ብቁ ገላጫችን ነውና። ሰንደቅዓላማችን ምራቁን የዋጣ የተረጋጋ ምሩቅ የድል ዋዜማችን – ዝልቅ ቅርሳችን ነው።
እርግጥ ነው። ሥህነ – ቤዛ ከድንኳኑ ሲደርስ ዓርማውን ፎቶው ላይ እንደምታዩት በእጁ ይዞ ትልሙንም አደራ ሰጥቶ ነው። አሁን ተመስገን ነው። ጊዜና ዘመን የማይሽረው ሰንደቅዓላማችን በእጁ ብቻ ሳይሆን በመንፈሱ የታታመ ሥህነ – ሙሴ ፈጣሪ በሥነ ጥበቡ – ፈጠረ። በቅጡ 17 ዓመት ሳይሞላው ነበር ገና በታዳጊ ወጣትነቱ ሐገሬ ውስጤ፤ ፍላጎትሽ – ፍላጎቴ፤ መንፈስሽ – መንፈሴ፤ ራዕይሽ – ራዕዬ፤ ችግርሽ – ችግሬ በማለት ልዕልቱን በልቡ አስቀምጦ አጋጣሚዎችን ሳያሾልክ ወይንም በአጋጣሚዎች ሳይሾልክ፤ ሁሉንም እንደፈቀደለት በተድሞና በበዛ ታጋሽነት – የታደመበት። መቻልን – በመቻቻል አስጊጦ ኖረበት። በርሃም ቤቱ ነበር። ዱር ገደሉም በአርበኝነት ቤቱ ነበር። ስደትም ጊዜያዊ መጠለያው ነበር። ወደ ሀገሩ ተመልሶ በስብዕዊነት ዙሪያ፤ በነፃነት አኩልነት የዲሞክራሲያዊ ፈለግ ዙሪያ የበኩልን ሙሉ ድርሻ በቅንነት አበርክቷል፤ ችግርን በዬአይነቱ አስተናግዷል። እግር ብረቱንም ቢሆን በስደት በኢህአፓ ሱዳን መሬት ላይ፤ በሀገሩም በህወሓት በማዕከላዊና በቃሊቲ አዲስ አባባ ሁለም እንዳይቀርበት አይቶታል። አብሶ እስር ቤት ሌላ የህይወት ምዕራፍ ነው። ጣፍጭነቱ የህዝብን ፍላጎት ፈቅደህ ለመስዋዕትነት ቤተኝነት ስለሆነ በቁም የመጽደቅ ያህል ነው – ለእኔ። ሥህነ ቤዛ ሁሉንም የመኖር ዓይነቶች ረሃብን ሳይቀር ኑሮ እንሆ የፋፋ ተግባር አኖረ። ዛሬም ቀን በጠፋን፣ ኢትዮጵያዊው ቀን በዘረኝነትና በጭቆና በተጠፈረበት ጭንቅ ወቅት፣ ለእስርኛው ኢትዮጵያዊነት ለአዲስ ቀን ተስፋ ጥብቅና ቆሞ ዱር ቤቴ አለ። ዋቢ!
የናፍቆት እፍታ።
ሥህነ – ቤዛ እናት ሐገሩን ከምንምና ከማንም በላይ – ይወዳል። ጠረኗ አዘውትሮ – ይናፍቀዋል። ገፆዋ በፍቅር – ይጠራዋል። ውስጧ አሳምሮ – ይመራዋል። መንፈሷ በትህትና – ይገዛዋል። ወዟ – ይስበዋል። እናቱን — ይናፍቃታል ሽው — ትዝ ትለዋለች። አልሆንለት ብሎ እንጂ ከእሷ ተለይቶ መኖሩ ባዕዱ ነው። ለዚህም ነው በነበረው ቀዳዳ ወደ እናት ሀገሩ ሁለመናውን ይዞ በቅንነት ለማገልገል – የተመለሰው። ከፍቅሩ ጥልቅነት የተነሳ የተወሰደ፤ ከናፍቆቱ ርህርና የተቀዳ ውሳኔ ነበር። በሙያው ሀገሩን ለመጥቀም አስልቶ ነበር። በዛን ጊዜም ዬእናቱን ውለታ ለመወጣት ናፍቆቱን ያወራረደው በመሃያ አልነበረም። ፍቅሩን የገለጠበት መንገዱ ከማንኛችም እጅግ በረቀቀ መልኩ በነፃ እልፍኝ ነበር። በሂሳባዊ ስሌት ከእናቴ ጋር እንዴት ተብሎ ብሎ ነበር ትጋቱን – ያስመሰከረው። ይህም ሌላ ወግ ያለው ዘለግ አድርገን ለማዬት ያልፈቀድንለት ንጡር አንጡራ ሚስጢር ነው፤ ለነገ መገኘት፤ ለነገ መዋል፤ ለነገ – ማደር ብቻ ሳይሆን – ለነገ መሰንበት፤ አልፎ ተርፎ ለነገ – ተወዲያም ደልደል ያለ ድልድል ለመሆን – በመፍቀድ፤ የሚገርመው እስከ ዛሬ በአበረከተው መልካም ነገር ሳይዝናና፤ ሳይኩራራ፤ ሳይዝልም አለ እንደአለ። አንዲት ብጣቂ ሽልማት ሳናዘጋጅለት፤ የምስጋና ቀን ሳናዘጋጅለት። እናት ሐገሩን ኢትዮጵያን ጽላቱ እንደ አደረገ – ኖረበት። መታደል ነው። ዘመን የማይሽረው፤ ድንበር ያለወሰነው የእናትና የልጅ ንጡሕ ጡታዊ ሃዲድ፤ እትብታዊ ትስስር በፍቅራዊነት ክህሎት ሲመነዘር እናት ሆዱ ያሰኘዋል። የእትብት ጥሪኝ አንዲህ ረቂቅ ግን ብቁና ብልህ አስተዳዳሪነት ነው። እራሱን በዜግነት ፕሮግራም ወይንም ማኒፌስቶ ለመምራት የቻለ ዘላቂ ተስፋችን መምራት ስለመቻሉ ምስክሩ ተግባሩ ብቻ ነው። ያዬነው ከመሆን ተነስቶ ነው ወደ መሆን ሲሄድ ነው።
ክወና።
አዎን! ሥህነ ቤዛ ከግብዝነት ጋርም የተፋታ ነው፤ በተለያዬ ጊዜ ከሰጣቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች፤ ቃለ ምልልሶች እንዲሁም የስብሰባ ሂደቶች፣ የተረዳሁት ቁም ነገር … እጅግም አሳንሶ የነፃነት ጎህ ሲቀድ መጸሐፉን “ ይህቺው የኔው ጹሑፍ መውጣቷ … ልክ እንደ ተራ መጣጥፍ ፤ ክቡር አትበሉኝ – በቁጣ፤ ዶር. የሚለው ይበቃኛል – በትህትና ፤ የተለዬ ጸጋ እኔ የለኝም – ዝቅ ባለ ሙሁራዊ ሥነ ምግባር። እኔ በግሌ ይህን አደርኩት የምለው የለም – ከግል ኢጎ ጋር ፍቺ በመፈጸም፤ ከእኔም የተሻሉ ወገኖቼ አሉ – በልዩ ውስጣዊ አክብሮት“ ይለናል። ስለሆነም እንደ ዘመኑ ታዳሚነታችን ያዬነው ወይንም የሰማነውን ወይንም ካነበብነው ያገናዘብነው፤ እሱን የተረጎምንበትን ሆነ ወደ ውስጡ ዘልቀን መክሊቱን ያደመጥነው ነገር ምን ሌላስ ይኖረው ይሆን? ወጣቱ መማር ያለበትን፤ መከተል ያለበትን ትክክለኛ መንገድ ማሳያት ድርሻዬ ነውና በምዕራፍ አራት እንገናኝ ዘንድ – በቀጠሮ። ከስንብት በፊት ግን ትንሽ ቋጠሮ …
በቃኝ! ቤቱን ሠርቶ፤ ጉልቻ – ጎልቶ
ኪዳን – አሰማርቶ፤ መሆንን – አስልቶ፤
ከሥሩ – ተብራርቶ፤ ይሁን – አጎልብቶ
እሺታን – ጠጥቶ፤ አለልኝ – መጥቶ
ድምጽ ለቃል ሰጥቶ፤ መቻልን ገንብቶ
ሰንደቁን አስልቶ፤ ኢትዮጵያዊነትን ከሁሉ – አጉልቶ
ጀግና መንገድ ያዘ አደራን አንግቶ!
ሥጦታ – ለአርበኞቼ። እርእሱ በጉልህ የተጻፈው መጨረሻ ላይ ያለው ነው። ይህ የእኔ መንገድ ነው። 18.08.2015
ዛሬን ባርኮ እንዲህ በማዕዳችን በሃበሻ ቤት ያገናኘን አምላክ ልዑል እግዚአብሄርን አመስግኜ ልሰናበት – ወደድኩኝ። መሸቢያ ሰንበት – የኔዎቹ። ጌጤን ዘሃበሻን – ከውስጤ አመሰገንኩኝ – ኑሩልኝ።
ማሳሰቢያ – አባቱ የእኔ ጀግና ናትናኤልሻ እሺ – እኔ ሎሌህ ነኝ። በጹሑፎቼ መልእክትህን – እለጥፋለሁ። በራዲዮ ፕሮግራሜም ከበጋ እረፍት በኋላ በድምጽ መልእክትህን ሙሉውን – አስተላልፋለሁ። http://www.zehabesha.com/amharic/archives/45527
የብሄራዊ ነፃነት ትግላችን ለህወሓት ብጣቄ መላሾ አያጎበድድም!
ዬነፃነት ትግላችን የብሄራዊ ማንታችን ክብር ጉልህ መግለጫ ቁልፋችን ነው!
የነፃነት ትግሉ መሠረታዊ ዓላማ 90 ሚሊዮን ህዝብ ከህወሓት የባርነት እስር ቤት ማስለቀቅ ነው!
ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር!
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።