Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

በአዲስ ዓመት ፍቅር ብንመሰርት –ይገረም አለሙ

$
0
0

ፍቅር ያስታግሳል፣ፍቅር ያስተዛዝናል ፣ፍቅር አያቀናናም፣ፍቅር አያስመካም፣ፍቅር አያስታብይም፤ብቻየን ይድላኝ አየሰኝም፤አያበሳጭም፤ክፉ ነገርን አያሳስብም፤ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል አንጂ ስለ አመጻ ደስ አይለውም ሁሉን ይታገሳል፣ሁሉን ያምናል፣ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣በሁሉ ይጸናል፡፡
( ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1 ም13 ቁ.1-7)

ethiopian newyear 2008
ከቁጥር መለወጥ ውጪ አዲስ ዓመት የመባሉ አዲስነት ምንነት የማይታወቅበት የአዲስ አመት መባቻ ላይ አንገኛለን፡፡ በሀገራችን የተለመደ በሆነው ይህን…ልዩ የሚያደርገው በሚለው አነጋገር ካየነው ይህን የአዲስ አመት ጅማሮ ልዩ የሚያደርጉ ሁለት ጉዳዮች አሉ፡፡ አንደኛው ሀያ አራት አመታት ኢትዮጵያን የገዛው ወያኔ በመቶ ከመቶ አሸናፊነት ለቀጣይ አምስት አመታት አገዛዝ መንግስት የሚመስርትበት ዋዜማ መሆኑ ሲሆን ሁለተኛው የነጻነት ታጋዮች ወደ ተግባር የተሸጋገሩበት ማግስት መሆኑ ነው፡፡
እንዳንችል የሚያደርጉ ግለሰባዊ ባህሪያቶቻችን አላስችል እያሉን እንጂ ይህን አዲስ ዐመት ልዩ የሚያደርገው የሚያስብል ከላይ ከተጠቀሱት ከሁለቱም የሚልቅና የሚበጅ ነገር ማከናወን እንችል ነበር፡አለመታደላች ይሆን ወይንም እንደሚባለው ርግማ ኖሮብን ማድረግ እየቻልን ባለመቻላችን ብዙዎች በጥቂቶች ለመገዛታችን እኛው ምክንያት ሆነን እንገኛለን፡፡

አነርሱ የአገዛዝ ዘመናቸውን በመቶ ከመቶ ውጤት አድርሰው ለአምስት አመታት እየተዘጋጁ ለሀያና ሰላሳ አመትም ሊገዙን እያሰቡ ናቸው፡፡ እኛ ደግሞ አገዛዙን ለማውገዝ ለመርገም አንድ ሆነን ከምናወግዘው አገዛዝ ለመላቀቅ ለሚያስችለው ትግል ግን አንድ ሆነን መቆም ተስኖናል፡፡ ይህ ደግሞ ዛሬ የጀመረ ሳይሆን በየዘመናቱ የነበረ የማያረጅ የማይለወጥ የራሳችን ጠላት ራሳችን እንድንሆን ያደረገን መጥፎ በሽታ ነው፡፡
ታዲያ ከዚህ በሽታ የመዳኛችንን መድሀኒት ብናገኘው ይህን የአዲስ አመት መባቻ ከልዩም ልዩ አያደርገውም ነበር ትላላችሁ! ከራስ በላይ ለሀገር ማሰብ በመጥፋቱ፣ በቃል የሚናሩትን በተግባር ሆኖ መገኘት አለመቻሉ፣ ከህዝብ ነጻነት ይልቅ የራስን ጥቅም ማስቀደሙ ወዘተ ግድግዳ ሆኖ አላገናኝ ማለቱ እንጂ ጉዳዩ የማይቻል ከባድ ነገር ሆኖ አይደለም፡፡ የበርሊንም ግንብ ፈርሷል፡፡

እስቲ ይታያችሁ፣ደግሞም ይቆጭ ያንገብግባችሁ፣በኢትጵያዊነታችን አንድ ነን፣ ወያኔ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ መወገድ ያለበት ዘረኛና አንባገነን አገዛዝ በመሆኑ ላይ ልዩነት የለንም፡፡ ኢትዮጵያ የቀደምት ሥልጣኔ ባለቤት ነገር ግን የዴሞክራሲ ባይተዋር መሆኗ አብቅቶ የህግ ልዕልና የተረጋገጠባት፣ ሰብአዊ መብት የተከበረባት ልጆቿ በሰላም፣ በፍቅር፣ በእኩልነትና በነጻነት የሚኖሩባት ዴሞክራሲያዊት ሀገር እንድትሆን በመመኘትም ልዩነት ያለን አይመስለኝም፡፡ታዲያ እነርሱ ጥቂቶቹ ህውሀቶች ለጥፋት ሲተባበሩ፣ የአገዛዝ ዘመናቸውን ለማራዘም አንድ ሆነው በአንድ ተሰልፈው የበደል ናዳ ሲያወርዱብን እኛ ኢትዮጵያውያን ናዳውን ለመመከትና የአገዛዝ ዘመናችንን ለማሳጠር አንድ ሆነን የማንቆምበት፣ በአንድ ተሰልፈን የማንታገልበት ምክንያት ምን ይሆን፡፡ እንዳይቻል ያደረግነው እኛው ራሳችን ነን እንጂ ይቻላል፡፡ጥቂቶች በአንድነትና በጽናት ቆመው ሲገዙን እኛ ብዙ ሆነን በጽናት ጉድለትና አንድነት በማጣት ሀያ አራት አመታት መገዛታችን አያስቆጭም፡ውጤት አልባ የእድሜ ልክ ተቀዋሚነትስ አያሳፍርም፣አረ በቃ እንበል፡፡ ካልን ደግሞ ወንድም እህቶቻችን እየከፈሉት ካለው መስዋዕትነት አንጻር ይህ ብዙም የሚባል አይሆንምና አሁኑኑ በአዲስ አመት ዋዜማ ተግባራዊ እናድርገው፡፡

በሀገራችን ባህል/ልማድ በተለይ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በከተማም ከጥንቱ ባህል ጨርሶ ባልተለያዩት ዘንድ በአዲስ አመት መግቢያ የቅዱስ ዮሐንስ እለት ችቦ ተለኩሶ ከቤት ሲወጣ ከቤቱ በር ግራና ቀኝ እየተተረኮሰ የጎመን ምንቸት ውጣ የገንፎ ምንቸት ግባ ይባላል፡፡ ይህ መልእክቱ ግልጽ ነውና ዝርዝር ውስጥ መግባት አያስፈልግም፡፡

እኛስ አገዛዝ በቃ የምንል ኢትዮጵያውያን በያለንበት ችቦ ለኩሰን አንደ ባህል ወጉ እየተረኮስን ባይሆንም በዚህ የዘመን መለወጫ እለት የድምጻዊት አስቴር አወቀን አንድ አድርገን ጌታ የሚለውን ዘፈን እያንጎራጎርን የጥል ምንቸት ውጣ የፍቅር ምንቸት ግባ፣ የበቀል ምንቸት ውጣ የይቅርታ ምንቸት ግባ፣ የጥርጣሬ የሸፍጥና የሴራ ምንቸት ውጣ፣ የመተማመን የቀናነትና የግልጽነት ምንቸት ግባ የማቃር ምንቸት ውጣ የመግባባት ምንቸት ግባ ወዘተ ማለት ብንችል ምንኛ መታደል ነበር፡፡

ለሀገር ይበጃሉ የተባሉ ያልተነገሩ ያልተጻፉ ነሮች የሉም ተግባራዊነት የለም እንጂ፡፡ ሌላው ቀርቶ በተቃውሞው ጎራ የነበሩና ያሉ ከተናገሩትና ከጻፉት ከፊሉን እንኳን ተግባራዊ ማድረግ ችለው ቢሆን ሀገራችን ዛሬ ካለችበት በብዙ መልኩ የተለወጠች ለመሆን በቻለች ነበር፡፡ እናም ከላይ የገለጽኩትን ለማለት መድፈሩ የመጀመሪያ ርምጃ ሆኖ ያሉትን ለመፈጸም መቻል ደግሞ ዋናውና ወሳኙ ጉዳይ ይሆናል፡፡ የምንለውን ተፈጻሚ ለማድረግ ለቃል የመታምን፣ ለህሊና የመገዛትና ከራስ በላይ የማሰብ ቁርጠኝነቱ ካለ 2008ን ለአስተማማኝ ለውጥ የሚያበቃንን ጠንካራ መሰረት የምንጥልበት አመት ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህን ማድረግ ቻልን ማለት ደግሞ ለለውጥ ምቹ ሁኔታ መፍጠርና ትውልድ ተሻጋሪ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት የሚያበቃንን ጥርጊያ ጎዳና ተያያዝነው ማለት ነበር፡፡ ለሀገርና ለትውልድ ማሰብ ካለ ይህ የማይቻልም የሚገድም አይደለም፡፡ ይቻላል!
ዛሬም እንደ ትናንቱ ወያኔን በማውገዝ አንድ ሆነን ከወያኔ አገዛዝ ለመላቀቅ ግን በየሰበብ ምክንያቱ አንድ ሆነን መቆም ካልቻልን የነጻነቱን ቀን እናራዝመዋልን፡፡ ነገር ግን ዘላለማዊ ምድራዊ ሥልጣን የለምና አንድ ቀን ወያኔና የምንይልክ ቤተ መንግሥት መለያየታቸው አይቀርም፡፡ የሚቻለው እንዳይቻል እንቅፋት ሆነን መስዋእትነቱ እንዲከብድና የወያኔ አገዛዝ ዘመን እንዲራዘም ያደረግን ወገኖች ያኔ ታሪክ ይመሰክርብናል ትውልድም ይፈርድብናል፡፡

በአንድ ሀገር ልጅነት መንፈስ ለጋራ ሀገራችን እንዳንቆም የሚያደርጉንን ሳንካዎች ከውስጣችን አስወጥተን የሀሳብ ልዩነት ያለ፣የሚኖር፣ሊጠፋም የማይችል መሆኑን ተገንዝበን አንድነታችንን አጠንክረን በልዩነቶቻችን ተከባብረን መተማመን፣ ፍቅርና አንድነት በመፍጠር ከወያኔ አገዛዝ ለመላቀቅ የሚያስችለንን መንገድ ለመያዝ ዋናው ቁልፍ መነጋገር መቻል ነው፡፡መቀራረብ መደማመጥ፤

የቱንም ያህል ስንቆፍር ውለን ስንቆፍር ብናድር የሚያለያዩን ጉዳዮች አንድ ከሚያደርጉን በዝተውም ልቀውም ሊገኙ አይችሉም፡፡ እንደውም በሀቅና በንጹህ ህሊና በንጽጽር ከተፈተሸ የሚያለያዩን ሚዛን የማይደፉ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ገነውና ጎልተው ማዶና ማዶ እንድንቆም ለማድረግ የሚያስችል አቅም ያገኙት ከእኔ በላይ የሚል አጋንንት ሰፍሮብን የመነጋገር ፈቃደኝነት፣ የመወያየት ባህል፤ የመደማመጥ ትእግሰት ያሳጣን በመሆናችን ነው፡፡ እናም በዚህ አዲስ አመት ዋዜማ ይህን አጋንንት እናስወጣና የፍቅርን አምላክ ወደ ውስጣችን እናስገባ፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>