አባቴ ሁሌ የሚነግረኝ ነገር ነበር አራዳ ማለት ይለኛል አራዳ ማለት፡- ለነብሱ ያደረ፣ እውነተኛ፣ ፈሪ ያልሆነ፣ አላማውን በእውነት የሚገልጽ፣ ታዛዥ፣ ህብረተሰቡን በቅን የሚያገለግል፣ የሚያውቀውን በቅንነት የሚያሳውቅ፣ የፍቅር ሰባኪ፣ የሰላም መዝሙረኛ፣ የጥበብ ቅኝት ተቀኚ፣ የፍልስፍና አባት፣ የተበላሹ መንገዶችን ጠራጊ፣ ማስተዋልና ጥበብን በልቡ አስቀማጭ፣ በእውነት የዘነጠ፣ ለውሸት ቦታ የሌለው፣ ስጋን አደላዳይ፣ ነፍሱን አዳኝ፣ ከፍ ባለ ማማ ተቀምጦ ከአትሮኑሱ ስር የሚገኝ፣ የእውቀት ጫፍ ላይ ደረሶ ከፊደል ቆጣሪወች ጋር ፊደል የሚቆጥር፣ ከራሱ ከፍታ የህዝቡ ከፍታን የሚወድ፣ ከራሱ ድምቀት የአገርን መድመቅን የሚናፍቅ፣ ለታናሹ ታዛዥ፣ ለታላቁ አገልጋይ፣ አባቶቹን አክባሪ፣ እናቶቹን አፍቃሪ፣ ሲጠሩት አቤት ሲልኩት ወዴት የሚል፣ ቢዘምር ላገሩ፣ ቅኔ ቢቀኝ ለህዝቡ፣ ለነብሱም ለስጋውም ያደረ ማለት ነው። ይለኝ ነበር
ሁሉም ሰው እኩል ተሰጥኦ አይሰጠውም ለአንዱ ድምጽ፣ ለሌላው ደራሲነት፣ ለአንዱ መካሪ፣ ለሌላው አስተማሪ፣ ለአንዱ ቀዳሽ፣ ሌሌላው አራሽ፣ ብቻ ሁሉም የራሱ ተሰጥኦ አለው ዋናው ነገር ተሰጥኦህን በአግባቡ እና በእውነተኛ መንገድ መጠቀሙ ነው። እናም ርዕዮት ንጽ አእምሮ፣ ቆራጥ ልቦና፣ እውነት የሚናገር ብዕር፣ ተሰጥቷታል። ለዚህም ምስክር የምትጽፋቸው ጽሁፍ ይናገራል። እስር ሳይበግራት ጥንካሬዋን ያሳየች ከስር ከወጣችም በኃላ የብዕሯ ቀለም ሳይነጥብባት ስራዋን የቀጠለች ንጹህ ህሊና ያላት ያወቀችውን የምታሳውቅ የአገር አለኝታ የህዝብ መከታ የሆነች በኢትዮጵያዊያኑ ልቦና ውስጥ የሴት ጀግና ሆና የተቀመጠች አራዳ ነች።
እንዲህም ሆኗል ሁለት ጓደኛሞች ቡና እና ጊዮርጊስ ሲጫወቱ አንድ የጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ደጋፊ ሌላኛው ደግሞ የቡና ስፖርት ክለብ ደጋፊ ናቸው። ዘንድሮማ የደጋፊ ነገር ችግር የለብንም ንብ ደግፉ፣ ቢራቢሮን ደግፉ፣ ዝንብን ደግፉ፣ ጢንዝዛን ደግፉ፣ በግድም በእጅም ግንቦት20 ደግፉ፣ የሚባልበት ጊዜ ላይ ስለደረስን ድጋፌን በደንብ ትረዱታላቹሁ ብዬ እገምታለው። እናም የቡናው ደጋፊ ቡና ያሸንፋል የጊዮርጊስ ደጋፊ ጊዮርጊስ ያሸንፋል በማለት በ 1000 ብር ያሲዛሉ። ለማንኛው እንድንተማመን ውል ተጻጽፈን እንፈራረም ይላሉ። በውሉ መሰረት እንደሚተገበር ይስማማሉ። እንዲህ ይል ነበር ውሉ፡-
እከሌ የተባለው እና እከሌ የተባለው ዛሬ በዚህ ቀን ቡና እና ጊዮርጊስ በሚያደርጉት የእግር ኳስ ጨዋታ ቡና ካሸነፈም፣ ቡና ከተሸነፈ፣ እንዲሁም አቻ ከወጣ የቡና ደጋፊ የሆነው 2000 ብር የእከሌ መሆኑን በፊርማችን እናረጋግጣለን ብሎው ተፈራርመው ወደ እስታዲዮሙ ይገባሉ። በጨዋታውም ጊዮርጊስ ያሸንፍና በል ብሬን ብሬን እኛ እንደዚህ ነን ይለዋል የጊዮርጊስ ደጋፊ። የጎርጊሱ ደጋፊ መጻፍና ማንበብ አይችልም ነበር። ውሉን ምን እንደሚል ስላልተረዳው ክርክር ተጀመረ። በኋላ ላይ ክርክሩ ሲያይል ወደ ጋደኞቻቸው ወሰዱት ዳኝነትን ጠየቁ ጋደኞቻቸው ውሉን ሲያዩት በጣም ሳቁ። ቡና ቢያሸንፍም ቢሸነፍም አቻ ቢወጣም እሱ ይውሰደው ብለህ ነው እኮ ነው የፈረምከው አሉት። የዚህን ጊዜ በጣም ተናደደ። ብር ከመቁጠርህ በፊት ፊደል ቁጠር አሉት። እስከአሁንም እንዲህ እየተባለ ይቀለድበታል።
የብዕር አርበኛዋ ርዕዮት አለሙ በአንድ ብእር 17 አመት ጫካ ነበርን፣ ጀግና ነበርን፣ የሚሉትን ያርበደበደ ታንክ አለን፣ አዳፍኔ አለን፣ የሚሉትን ያዳፈነች። እውነት በመጻፏ ሽብር የመሰላቸው፣ ብዕሯን ከወረቀትጋር በማዋሃዷ ጀግና ነን ብለው የተኮፈሱትን ያራደች፣ የድንጋይ መሰረት ሳይሆኑ የእንቧይ ካብ መሆናቸውን ያሳየች፣ ብዕርተኛ ነች። የእርዮት ብእር ሰለ ሕዝብ ነጻነት የሚናገር፣ ሰለ አገሯ ክብር ቀለምን የሚተፋ፣ አስተማሪ ብእር ነው። መለስ ዜናዊ |<<ከሺ ጦር ባተሌ አንድ ብዕር የያዘ ሰው ለኛ ከባድ ነው>> ብለው እንደተናገሩት በአንዲት ብዕር ማንም አይደፈረንም ብለው የውሸት ፕሮፖጋንዳ ሲናገር የነበረውን የወያኔን ምሽግ ሚግ አብራሪ ወይም ታንከኛ ሆና ሳይሆን ያራደችው፣ ብዕሯ አሁን ስልጣን ላይ ያለውን ገዥ ፓርቲ ምን እንደሚል ያልገባቸው አልያም እውነት ውስጣቸው ስለሌ በብዕሯ ቀለም የተሸበሩት። እርሷ ግን እውነትን በመግለጽ፣ አገርን በመውደድ፣ ህዝብን በማክበር ብዕራን ያነሳች አራዳ ነች። እናም ብር ከመቁጠር ፊደል መቁጠር ይሻላል የሚለውን አባባል ጋብዥያቸዋለው። በእውቀት የበለጸገ እና በእውነተኛ መንገድ ላይ የቆመ ብዕር ያስተምረዋል እንጂ አያስፈራውምና ነው በብዕር የሚሸበር ያልተማረ ወይም በእውነተኛ መንገድ ያልቆመ ብቻ ነው።
እርዮት ስጋዋ የታሰረ ህሊናዋ ያልታሰረ ብዕርተና ነች። ገራፊን ገርፈሃል፣ አሳሪን አስረሃል፣ ገዳይን ገድለሃል፣ የምትል የእውነት ብዕር ያነሳች በዕረኛ ነች። ስጋችን ሲያገኝ የሚወፍር፣ ሲያጣ ደግሞ የሚከሳ ነው። አእምሮአችን ግን እውነትን ስንሰጠው ብቻ ነጻ አድርጎ የሚያኖረን የራሳችን ፍርድ ቤት ነው። ለአእምሮዋ እውነትን ያስገባች፣ እውነትንም ያወጣች፣ ከዘላለም ጸጸት የጸዳች፣ ከራሳ ጋር የተስማማች ብዕርተኛ ነች። ሕዝብ ማለት እሷ፣ እሷ ማለት ሕዝብ፣ መሆኑን ያስመሰከረች የዘመኑ የሴት ተምሳሌት የሆነች አራዳ ነች።
እንጂ አራዳ የሚለው ትርጉም እንደኛ ዘመን ትርጉም እንደተሰጠው የቃመና ያስቃመ፣ ያጨሰና ያስጨሰ፣ የጠጣና ያስጠጣ፣ ከፍ ብሎ የዘለለ እና የወደቀ፣ የሰረቀና ያሰረቀ፣ ያመሸና ያስመሸ፣ የጨፈረ እና ያስጨፈረ፣ እስታ በል፣ ላሽ በል፣ ተቄ በል፣ ጩባ፣ ፍሉስ፣ ሼባው፣ ጌጃው፣ ማኛው ,… የሚለው የሚጠቀም እና የሚያደርግ አራዳ አይደለም። እንደዚ አይነቱ ከራስ መጣላት፣ ከቤተሰብ መጣላት፣ ከጎረቤት መጣላት፣ ከህብረተሰብ መጣላት፣ ከአገር መጣላት፣ ብሎም ከእግዛቤሔር ጋርም መጣላት ነው። ስጋውንም ነብሱንም የሚጎዳ አራዳ የሚለው ትርጉምን አይስማማውም።
ሁላችንም አራዳ ለመሆን የአባቶቻችንን ምክር እንስማ እላለው። አራዳ በኢትዮጵያ ምድር በዝቶ ይብቀልባት፣ ይውጣባት፣ ይታይባት፣ ያብብባት። አራዳ ዶክተር ወላ እንጅነር፣ አራዳ ወታደር ወላ መምህር፣ አራዳ አርሶ አደር ወላ ኢንቨስተር፣ አራዳ ደራሲ ወላ ሃያሲ፣, አራዳ ሳይንቲስት ወላ ጂኦሎጂስት፣ አራዳ ፖለቲከኛ ወላ ዳኛ፣ አራዳ መሪ ..ሆኖ ታታሪ.. በህግ አዳሪ.. ህዝቡን አስከባሪ.. ያብዛልን ፈጣሪ።
ከተማ ዋቅጅራ
21.08.2015
Email- waqjirak@yahoo.com