Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ :: ህወሃት ጎጠኝነትን ብትኮንን የመለስ ዜናዊ አጽም ይወቅሳታል።

$
0
0

ቢላል አበጋዝ

ዋሽግቶን ዲ ሲ

ዓርብ ፣ ኦገስት 28 ቀን 2015

tplf-rotten-apple-245x300ማን የብሄር ብሄረሰብ፤ መገንጠል ፤መገነጣጠልን አሾረው፤ ደነገገው  ? እቅድ ሀ ሲቻል ኢትዮጵያን ግጦ ለመብላት እቅድ ለ ደግሞ ትግራይ መገንጠል።ኢትዮጵያን ማፈራረስ የማንና አሁንም የሚሰራበት ዕቅድ ነው ? አንባቢን ማሰልቸት አልሻም::ዛሬ አትወጡት መቀራቅር ገባችሁ።ጀምበር እየጠለቀችባችሁ ሲሆን ዘረኝነትን “የምትኮንኑ” ሆናችሁ::ይህን ስትሉ መስማት እኮ ለኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ትልቅ ድል ነው። እያጥወለወላችሁ ካፋችሁ ወጣ። ሌሎችን ግን ለዚህ ክፋት፤ውድቀት፤ብልሽት አትውቀሱ።

የህወሃት ዋና ቃል አቀባይ ሀይለ ማርያም ደሳለኝ በቪኦአ(አሜሪካ ድምጽ) ጎጠኝነትን የሚያወግዝ መግለጫ ሰጥቷል።”ብሄራዊ መግባባት” “ዲሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት” የተለመደው “ኪራይ ሰብሳቢ” ሁሉንም የህወሃት ንግድ ምልክቶች እየጠቀሰ የጎጠኝነት መዘዝን፤አስከፊው ህወሃት: ያመጣውን፤ የዘራውን መርዝ ኮነነ። አጃኢብ! ይላል ያገሬ ሰው።ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ። አይሰማ የለም ህወሃት ጎጠኝነትን ስታወግዝ ሰማን።ደስ የሚለው ከቱባ ዘረኞቹ ብንሰማው ነበር።በድርቅና “አማራ” ከሆኑት በሰማነው። እነሱ ግን ተላላኪ መረጡ። እንደሚቀፋቸው አልጠራጠርም።መጋረጃ ኋላ ሆኖ መዘወር ነው ዘዴአቸው።ሟቹ መለስን የሚወዳደር አፈጮሌ አላፈራችሁም። ልውጣ ቢልም አታስወጡት።እርስ በርስ የተጠላለፋችሁ መንጋ መሃይሞች።ሸር ብቻ።ኪራይ ሰብስባችሁ ወደውጭ አገር በፊት ለፊት የሞሸለቃችሁትን ስታሸሹ፤ማነው  ኪራይ ሰብሳቢው ?

ክልል፤ ዘረኝነት አደጋ ነው።ይህን መንገድ አትሂዱበት ስትባሉ “በህግ” ደንግጋችሁ እስከ መገንጠል ብላችሁ አምሳችሁ አተራምሳችሁ ዛሬ ዘረኝነትን ለመኮነን ደረሳችሁ!ግን ማነው ዘረኛው? ትምክህተኛ ያላችሁት አማራ ?ያጥላላችሁ እስር ቤት ያጎራችሁት ኦሮሞ? የጨፈጨፋችሁት አኝዋክ የገደላችሁት አፋርና የኦዴን ሶማሊ ? ያተራመሳችሁ የደቡብ ህዝብ? ማነው ዘረኛው? ትልቁንና አስገራሚው ውሸት ዋሻችሁ ዛሬ ! የተለመደው ማጭበርበር ስለሆነ ተከታዩን እንጠብቃለን።ወደ ትግራይ ያካለላችሁትን ልንመልስ ነው ልትሉን ነው? ለሱዳን የለገሳችሁትን መሬት አስመለስን ልትሉን? “ጎጠኝነትን ኮንኑ” ተብሎ የተኩላ ባህሪያችሁ ሊረሳ? አካሄዳችሁ የደፋር ነው። ህዝብ ታዝቧችሁ አብቅቷል። ጽዋው ሞልቶ ፈሷል። ያበቃ ነገር ነው። አውቃችሁ ባትሰራም ይችን ትሪክ እንስራት ብላችሁ ነው። ይህ ድርጊታችሁ ፍርሃታችሁን፤ህዝቡ ሊያስወግዳችሁ፤ከጫንቃው ሊያወርዳችሁ መነሳቱን፤ መቁረጡን አመናችሁ ማለት ነው።እብሪቱ የታል? “ልክ ማስገባት ነው” የታል? እንዴ ህወሃቶች ምን ነካችሁ?

የድሮ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች ህወሃቶችን ትተን ጉዳያቸው ያገር ጉዳይ እንጂ የጎጥ አልነበረም። የዘር አልነበረም።ጭቆና ይቅር።መብት ይከበር::አርሶ አደር ላባደር አይበዝበዝ።የባእድ ተልካሻ ባህል አንፈልግም።ደቡብ አፍሪካ የነገሰው አፓርቴድ ይጥፋ።ቅርብ እሩቅም ያሉ የዴሞክራሲ ትግሎችን የመደገፍ ነበር።ዓለምን ሁሉ ያካለለ እይታ ነበር።ጎጥ አልነበረም ወጉ። ምሁርነት ባገራችን ክቡር የነበረ ጊዜ። ደጉ ዘመን:: ምሁራን ጀግኖችም ነበሩ።ህወሃቶችን ትተን።ድሮ ዩንቨርስቲ አንድ ከክፍለ አገር የመጣ ተማሪ በአራት ዓመታት ከራሱ ክፍለ አገሩ የመጡትን ብቻ ሳይሆን ከመላ ኢትዮጵያ የመጡት ጋር ተምሮ የእድሜ ልክ ጓደኛም አፍርቶ ህይወቱ የተቃና ዜጋ እንዲሆን እድል የሚያገኝበት ነበር።ዩንቨርስቲ በክልል።ስራ በክልል።ንግድ በክልል።ሁሉን አጥራችሁት ዛሬ ሰብል አማረላችሁ።እጨዱ እንጂ ! መምህራኑ ብቻ አይወቀሱም። እናንተ በመንግስት ደረጃ ላደረጋችሁት።በክልል አጥራችሁ ያደገውን ትውልድ ነው የሚያስተምሩት።መምህራኑም በእድሜ ያልጠኑ ከሆነ የስርዓታችሁ ውጤቶች ናቸው።አትላኩባቸው።ዛሩም አውልያውም እናንተው ህወሃቶች ናችሁ!

የአሁኑ ጎጠኝነትን መኮነን ለፖለቲካ ፍጆታ መሆኑን ማንም ያውቀዋል።አንዴም በህወሃቶች መሀል ክልል ዘረኝነት አከራክሮ አለያይቶ አያውቅም።እርስ በርስ “እኔ ብልጫ ያለኝ ዘረኛ ነኝ” መባባል ምባልባት አጋጭቶ ይሆናል። “እንኳ ተፈጠርናን” ማን ሊረሳ።ሰቆቃውን፤ድብደባውን እስሩን እያባሳችሁት አሁን ጎጠኝነት አሳስቧችሁ? በፍርድ ስም እያላገጣችሁ ? እረ እንዴት ? እንደሚመስለኝ ከዚህ የበለጠ የምትሸፍጡት ሸፍጥ ይህ የዛሬው አንደኛ ትእይንት ይመስለኛል። ሌሎች ውጥረት ማርገቢያዎች “ክልል ይቅር” “ተነሱ እንነሳ አሰብን እናስመልስ” “ኤርትራ እንዝመት” ሎሎች አኬል ዳማ መሰለ ድራማዎች ተጨምረው።ቱባ ወያኔዎች ባደባባይ “ኢትዮጵያ ማሪን በድለንሻል” ሊሉም ይችላሉ።ህዝብ ግን ህወሃቶች ተራ ሌብነታቸውን ለመቀጠል የሚያካሂዱት መሆኑ ያውቃል።የኦሮሞ ህዝብ ዛሬ እያየን እየሰማን::  የሀረር አማሮች  ስልጣን እደያዛችሁ፤ ከቀዬው ያፈናቀላችሁት።የአፋር፡ የኦጋዴን የአኝዋኮች ስቃይ የት ያድርስ ? በመምህራን እና ተማሪዎች ላይ ሊላከክ ? ዩንቨርስቲን ያህል የውቀት የምርምር ቀዬ እጅግ ኋላ ቀር የሆነው የዘረኝነት ኩሬ መሆኑን ታዝበው የቆጫታቸው ምሁራኑ በብሶት ቢናገሩም፤ያውም ታፍነው ስራ አልባ ሆነው ያገር ፍቅር ቢናግራቸው፤”እዲህ ያለ ዘመን ደረስን” ብለው ቢናገሩ እውነቱን አፈረጡት።ሌላ ምንም።

ህዝብ አሁን ምን ያድርግ ? የእስታሁን ትዕግስቱ፤እስበስ መቻቻሉ አምበርክኳችኋል።እንደ ውጭ ጠላት አገርን መተራችሁ፤ህዝቡን ፈተናችሁት። በአንጻሩ ህዝቡ መርዛችሁን እንዳከሸፈ ነው።የዘረኝነት መጥፋት እናንተ ሳትወገዱ የሚታሰብ አይደለም።የኔ መሰሎች ይህን ማለት ማክረር፤ጥላቻ፤ አይደለም። ሬኮርዳችሁ እንዲህ የሚፋቅ አይደለም። የከሰረ መንገድ ይዛችኋል ለተረፈች አጭር እድሜአችሁ መፍጨርጨር ነው።

ከእባብ እንቁላል እርግብ አይገኝም።ህወሃት ተጣሞ ያደገ ያረጀ ያፈጀ የተንኮል ድርጅት ነው።የተቀነባበረው የስለላ ክፍላችሁ ተግባር አንድም እንዲህ ህዝብ ያረረበትን ጉዳይ አንስታችሁ የአዞ እንባ ማፍሰስ ነው።ሌላው በአይጋ ፎረምና በሌሎች አንዳንድ ድረ ገጾች ቀስበቀስ የምታናፍሱት ብኩን ፕሮፓጋንዳ ነው።ያፈናቀላችሁትን፤መሬቱን ለውጭ ከበርቴ የሸጣችሁበትን፤ዘሩን ጠቅሳችሁ ጢቅ ብላችሁ የተፋችሁበትን ህዝብ መልሳችሁ በዘረኝነት መውቀስ እብደታችሁን አመልካች ነው።የዘረኝነት ሰንኮፉ እናንተ ስትነቀሉ ተመነገለ ማለት ነው።የለውጥ ሱናሚ ድምጹ ከሰሜን ኢትዮጵያ ተነስቷል።እንደወትሮው።አገር ወዳዱ በዓለም የተሰራጨው ኢትዮጵያዊ ለወገኑ መቆሙን ተግባራዊ እያደረገ ነው።ህወሃቶች የሽኝት ግብዣችሁ ድግሱ አልቋል።ለበስ ለበስ፤ ወጣ ወጣ ነው ሻንጣችሁን ይዛችሁ።

ኢትዮጵያ በሰላም ተከብራ በዜጎቿ ሁሉ አንድነት ለዘለዓለም ትኑር!

 

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>