አቶ መለስ በመጨረሻ ሰሞናቸው ስለ ድርጅታቸው ኢህአዴግ አጥብቀው ሲያራምዱት የነበረው መተካካት! ወይም አንዳንዴ ሲሉት እንደነበረው ”ዱላ ቅብብል” ነበር። (እርግጥ ነው እኛ ዱላ የምትቀባበሉት ማንን ለመግረፍ ነው ስንል አሽሟጠን እንደነበር አይዘነጋንም) ነገር ግን አሁን አቶ መለስ ሞተዋል እና ዱላ ቅብብሉን ለተተኪዎች ሰጥተዋል ከንግዲህ በቃቸው የተባሉ አንጋፋ እና ገፋፋ ባለስልጣኖች ሁሉ ወደ ፊት ሊመጡ Delete ከተደረጉበት Recycle Bin ዳግም ተመልሰው Desktop ላይ ጉብ ብለዋል። ”ዱርዬ” እንዳልባል ፈርቼ እንጂ በበርጫ ቋንቋ ተገርበዋል ከተቃሙበት ተነስተዋል ብላቸውም በደንብ ይገልጸዋል።
እና በደፈናው፤ ህውሃትቲትም ሆነች ኢህአዴግዬ የአቶ መለስ ራዕይ እያለች ደጋግማ ብትቀውጠውም የሰውዬው ራዕይም ክቡርነትም ታላቅነትም ያለው በተወሰኑ ሰዎች ጭንቅላት እና በባለቤታቸው ወይዘሮ አዜብ ውስጥ ብቻ ነውን… እያለን እየጠረጠርን ያ. ሁ. ነ. ያ.
እና አቶ መለስ መተካካት ሲሉ የፈጠሯት ነገር (አሁንም በቅንፍ በርግጥ እርሳቸውም ተቀናቃኞቻቸውን እና ተፎካካሪዎቻቸውን ገሸሽ ለማድረግ የተጠቀሙባት መላ ናት እንደሚባለም እናውቃለን…. ግን አንናገርም።) ብቻ ግን እነዚህ ሪፖርተር የጠቀሳቸው ጉምቱዎች አቶ መለስ በሌሎች ሲተኳቸው፤ ራሳቸውን ደግሞ እግዜሩ በ አቶ ሃይሌ ተክቷቸው መተካታቸውን ጠብቀው ዳግም የተመለሱ ናቸው። ጉምቱዎቹ አቶ መለስ ተመልሰው እንደማይመጡ ሲያውቁ… ሹልክ ብለው ከየከረሙበት ወደ ስልጣናቸው መጥተዋል ብንልም ይሆናል!
ቀልዱ ቀልድ ነው… ጨዋታውም ጨዋታ ነው….ምሩ ግን ኢህአዴግ ራሷ ያወጣችውን ህግ ራሷ እንኳ ለማክበር ሞራል እና አቅም ሳይኖራት እኛን አክብሩ እያለች ቁም ስቅላችንን ስታወጣው ነውር አይደለም ወይ…. ብለን እየጠየቅን፤ እግረ መንገዳችንንም መለስ ዜናዊ በሌሉበት አጓጉል ተደፍረዋል እና እነሆ መለስ ዳግም ሞቱ!!! እንላለን… (ነፍሳቸውን እንዳሻው ያድርግልን!!!)