Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ሥህነ –ቤዛ! ቅኝተ –ፕሮፌስር ብርሃኑ ነጋ! –ሥርጉተ ሥላሴ

$
0
0

28.08.2015 /ሲወዘርላንድ –  ዙሪክ/

ምዕርፍ አራት –  ዕርገት!

 

ሳይሽ እውላለሁ ከልቤ አስቀምጬ

ሳይሽም አድራለሁ እቅፍ አንተርሼ

አወሳሳሻለሁ አድርሽኝ ለብሼ፤

አነሳሳሻለሁ ፍቅር አንተርሼ፤

እመጣልሻለሁ ግንነት ደግሼ

እንደ ወጣሁ አልቀር አይቀር እንደ መሼ!

Birhanuእንዴት ናችሁ የሐገሬ ልጆች። የዚህች የሥንኝ – ቋጠሮ ዕርእስ „አድርሽኝ“ የሚለው መሆኑን በትህትና አሳስቤ ወደ ባለፈው ምዕራፍ ሦስትን የከውንኩብትን ትንሽ ከፍ ብዬ ላውሳ  „…. እናት ሐገሩን ኢትዮጵያን ጽላቱ እንደ አደረገ – ኖረበት። መታደል ነው። ዘመን የማይሽረው፤ ድንበር ያለወሰነው የእናትና የልጅ ንጡሕ ጡታዊ ሃዲድ፤ እትብታዊ ትስስር በፍቅራዊነት ክህሎት ሲመነዘር እናት ሆዱ ያሰኘዋል። የእትብት ጥሪኝ አንዲህ ረቂቅ ግን ብቁና ብልህ አስተዳዳሪነት ነው። እራሱን በዜግነት ፕሮግራም ወይንም ማኒፌስቶ ለመምራት የቻለ ዘላቂ ተስፋችን መምራት ስለመቻሉ ምስክሩ ተግባሩ ብቻ ነው። ያዬነው ከመሆን ተነስቶ ወደ መሆን ሲሄድ ነው።“ ለጥቄ ሳጠቃልለው ደግሞ እንዲህ ብዬ ነበር „እንደ ዘመኑ ታዳሚነታችን ያዬነው ወይንም የሰማነውን ወይንም ካነበብነው ያገናዘብነው፤ እሱን የተረጎምንበትን ሆነ ወደ ውስጡ ዘልቀን መክሊቱን ያደመጥነው ነገር ምን ሌላስ ይኖረው ይሆን? ወጣቱ መማር ያለበትን፤ መከተል ያለበትን ትክክለኛ መንገድ የማሳዬትን“ አስፈላጊነት በዚህ ልፋማ ዕይታዬ ነበር  የቋጨሁት።

ዛሬ ምዕራፍ አራትን እንደ ዕርገት ወይንም የወስጥ መሰብሰቢያ ዕልፍኝ ለማድረግ ሃሳቡ አለኝ።

ምዕታት ገድላቸውን – ሲዘክሩ፤ ታሪክ ሂደቱን – ሲመሰክር፤ ትናንት አደራን አቆይቶ በጥንቃቄ – ሲያስርክብ፤ ትውፊት ትውልዱን በውርርስ ቅብብል – ሲመረምር፤ ሐገር ዕንባውን ለዘመኑ ጥቁር አንበሳ – ስትልክ፤ የልዕልታችን የምጥ ጥሪኝ ምሬት ድረሱልኝ ስያሰማ፤ የጀግንነት ቀለማም አደራ ዝክረውን – ሲቀምር፤ ሰማይም ቅዕብዕውን ሲልክ – በስምምነት ረጋ ብሎ በአንድምታ – ሰከነ።

የኔታነት፤

የኔታነት የከበረ ጸጋ ነው። የኔታነት ፈጣሪ አምላካችንም የመረጠውና በምድር በነበረበት ጊዜም የተገበረው፣ የቅዱስ መንፈስ ምርቃት የተቸረው የዕውቀቶች ሁሉ መሰላል ነው። መምህርነት ከመንፈሳዊው ዓለም ወጥተን በገሃዱ ዓለምም ቢሆን ተግባር ቀለብ የሆነ የትውልድ ቀዳሚ ብቸኛ ተጠሪ፤ የከበረ – የደመቀ – ዕድሜ ጠገብ – ልምድ ዘለቅ – ምስጉን የንጋት አጥቢያ ኮከብ ሙያ ነው። መምህርነት የወላጃዊነት ፍጹማዊ መንፈስ – የረበበት፤ የኃላፊነትን ስሜት በቅንነት ፈቅዶ የሚቀበሉበት የሙያዎች ሁሉ እጬጌ ነው። መምህርነት ጥሩ አስተዳዳሪነት፤ ጥንግ የሥነ – ልቦና መክሊት ያለው የአንድ ሐገር የብቁ ዜጋ መሠረተ – ሟተት ነው።

መምህርነት ማሕበራዊነትን በተግባር የሚያነጋግር የግንኙነት መሥመርም ነው። መምህርነት የሀገርን ችግር ከሁሉ ቀድሞ የመጋራት ብቻ ሳይሆን መፍትሄ በማመንጨት በኩልም አንቱ የሆነ ሙያ ነው። መምህርነት የመመዘን – ውጤትን በዕውነት ላይ የመገምግም – ርትህን በሁለገብ መልኩ ዓይቶ እንደ ተፈጥሮው የመተርጎም፤ዳኘት አቅም ያለው የሙያዎች ሁሉ ዓፄ ነው። አንድ ለሙያው ኃላፊነት የሚሰማው ብቁ መምህር ትውልዱን በተገባው መልኩ ለመቅረጽ መነሻው እውነትና የዕውነት ጭብጦች ብቻ ናቸው ውስጥን የሚመሩት። ተግባሩን በጊዜ ሰሌዳ የሚመራ የትልም መሃንዲስ ነው። ብልህ መምህር ሊያስተምር ብቻ ሳይሆን ከተማሪዎቹም ሊማር እንደሚችል የተሰጠው መሆኑ ተፈጥሮን ቅጥ ባለው ሁኔታ መተርጎም ከመቻሉ ሚስጢር – ይቀዳል። ስለ መምህርነት ኃላፊነት ብቃት ጠቅላላ ገጽታ ስገልጽ ሟቹን ወላጅ አባቴን መምህሩንና የቤተመጻህፍት ባለሙያ የሆነውን አበይን፤ መካር መምህርት ታላቅ አህቴን – እትዬን በመንፈሴ ውስጥ ተጠዬቁ እያልኩ ነው። በእነሱ መዋለ ህይወት ያዬኋቸው ብርቅ ብልሃቶች፤ ጥልቅ የራስ መተማመን ጥሪቶቼ ሆነው እኔን ቀጥ አድርገው ያነጹኝ በመሆናቸው ዬተጠቃሚነቴን ጭማቂ ሰብላማነትም ጭምር ነው። ስለዚህ ምስክርነቴ ከህይወት እውነተኝነት ይመነጫል። ከዚህ ጋር አንድ ትልቅ አምክንዮ ሊነሳ ይችላል። ታዲያ ጠ/ሚር ኃይለማርያም ደሳለኝስ መምህር አይደሉም ወይ ልትሉኝ ትቻላለችሁ። እውነት ለመናገር ሳይፈቀድላቸው ነው ወደ ሙያው ዘው ያሉት ብዬ አስባለሁ። ከዚህ ጸጋ ጋር መሆን አይደለም ንክኪው የላቸውም። ስለሆነም እሳቸው ህይወታቸውን የሚመሩት በጀርባቸው ነው። ምን አልባትም በጀርባ መኖርን የመረጡ የመጀመሪያው ጠ/ሚር መምህር ሳይሆኑ አይቀሩም። በጀርባው የሚኖር ሰው ሲያነብም የወረቀቱን ጀርባ ነው። ሲናገርም የፍሬ ነገሩን ቅርፊት ነው። በጀርባ ነው ኑሮን ሲያነጋግርም ያው ጀርበኛ ነው። ጀርባና ጀርባ ደግሞ ገደል ይሆናል ዕጣቸው። ስለዚህ ያን ክቡር ሙያ አንዲህ ቀንጣ ከሆኑ ተማላ ግድፈቶች ጋር ማስታመም አይገባም ባይ ነኝ። የሆነ ሆኖ ዛሬ እናት ሐገሬ ኢትዮጵያ ብቁ መምህር ብቻ ሳይሆን ከእሷ ዝቀሽ ጸጋም የበለጠ ለመማር የፈቀደ የኔታ አግኝታለች። እልልታ …..

ብሄራዊ ነፃነቱ ርቦት ቀደም ብሎ ዱር ቤቴ ያለው የኢትዮጵያ ብሄራዊ የነፃነት ተስፋ አርበኛ መምህሩን ብቻ ሳይሆን ተማሪውንም ሥህነ – ቤዛን አግኝቷል። ተማሪውን ብቻ ሳይሆን አባቱንም አግኝቷል። አባቱንም ብቻ ሳይሆን ለተሳትፎው ትክክለኛ ሚዛኑን አግኝቷል። የታደለው ሠራዊት በዬደቂቃው ከምምህሩ ከሥህነ – ቤዛ በግድፈት ያልባለቀውን ውባታም ጸጋዎችን እዬተመገበ፤ እሱ ያለውን የነፃነት ፍቅርና ዬተመክሮ ዕምቅ ሃብት እያጎራረሰው እንደ አባት አደሩ እቀና ፍቅርን – በአብሮነትን መኖርን – መማር – ማስተማርን በጋራ ለመጋራት ለድል ስምረት ደስ ብሎት፤ ዘና ብሎ – ተረጋግቶ – በሰከነ አመራር ለራዕዩ እንዲተጋ አምላኩ ስለፈቀደለት ድካሙ – ጥረቱ – መስዋዕትነቱ – ህልሙ ፍሬ ዘለቅ እንደሚሆን ባለተስፋው የአርበኝነት መንፈስ ተጋሪው ዬሚሊዮኖች ፈቃድ እንዲሆን ግድ ይላል።

ዬዕውነት መሪነት።

ጊዜን አድመጦ የተነሳው ብሄራዊ ፍላጎት፣ በተረጋጋ አያያዝ ከጅምሩ እስከ ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ድረስ ልብ ሞልቶ ሊያናግር የሚችለው መሰረታዊ ቁም ነገር ከአርበኛው ጋር የተዋህደው መንፈስ ዕብለትን የሚጸዬፍ ሰብዕና ካለው ጋር መሆኑ ሌላው የድል ዋዜማ ነው። ድል ሲታሰብ በሃሰት ዲሪቶ ተጠቅልሎ ከሆነ ነገ ቢከፍቱት ተልባ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። በሀገራችን ብሄራዊ ታሪክ ውስጥ የውሸትን – የግነትን ግንብ የናዳው የመጀመሪያው ሚዲያ የቀድሞው የግንቦት ሰባት ራዲዮ ነበር። ራዲዮው በምሥረታ ዘመኑ ተግቼ ሳደምጠው ነበር፤ መረጃ ሲሰጥ አንድ ሰው ከሆነ „አንድ ሰው፣ ጥቂት ሰው ከሆነ ጥቂት ሰው፣ ሁለት ሰው ከሆነ ሁለት ሰው“ በማለት ለእውነት ጥብቅና ሚዲያ ሲቆም በታሪካችን የመጀመሪያው ነው ማለት እችላለሁ። ይህ ለምን ሆነ? ሚዲያው ዕውነትን ከተቀበለ፣ ስለ ዕውነት ክብር ካለው፤ ስለ ዕውነት አሸናፊነት – ስለ ውሸት ተሸናፊነት የቀደመ ህሊና ይመራው ስለ ነበር ነው። ስለዚህ ነፃነት ራህቡ የሆነው የኢትዮጵያ ብሄራዊ አርበኛ እውነት አንደ ተፍጥሮው ዘመን ሸልሞታልና ፈጣሪውን ያመስግን። ዕውነት ዋስ፣ ጠበቃ፣ ጥግ፣ ነገም ሰለሆነ በዝንፈት መረጃ ከእንግዲህ የኢትዮጵያ ነፃነት የአርበኝነት ውሎ – አይታወክም። የእውነት ሁነኛ የሆነው አርበኛ ቅንጣት ታክል ዕብለትን የሞሸረ መሸማቀቅ አንደማይገጥመው በጣም በእርግጠኝነት መግለጽ እችላለሁ – ይህ ለዚህ ዘመን ልዩ ሥጦታ ነው። ነገም ሃሰትን የጀርባ አጥንት ያደረጉ ቦንዳዎች ሁሉ ሞሽሸው – ይሞታሉ፤ ከእንግዲህ በተዛባ – በዘበጠ መረጃ መታመስ ተቀበረ። ውህደቱ የኢትዮዽያ ውስጥነት ነው።

ርትህ – ፈላጊነት፤

ፍትህን የሚወዷት የእውነት አርበኞች ብቻ ናቸው። የፍትህ እጦት የህግ የበላይነት መጠለያ ማጣት ነው፤ ዛሬ የሚሊዮኖች ዕንባ ሁሉንም የመከራ ዓይነት መፈተኛ የሆነው ሃሰት ቀን ስለ ሰጠው ነው። ለነገሩ እራሱ ህወሓት ውሸት እኮ ነው። ነገር ግን በተለያዬ ሁኔታ ሥህነ – ቤዛ በተሳተፈባቸው መስኮች ሁሉ ፍትህ ፈላጊነቱ ከውስጡ ስለመሆኑ ተመልከቻለሁ። ስለዚህ ዛሬ አደራን በተቀበለው የታሪካችን ልዩ ምዕራፍ ህግን መሠረት ያደረገ ፍትሃዊ አመራርና አስተዳደር አርበኛው ወገኔ በቅርበት ስለሚያገኝ ሁለመናውን ለውስጡ ፍላጎት ለመስገዛት የሚጎትተው አንዳችም ኢ – ህጋዊ የሆነ ነገር አለመኖሩ፤ ማግስትን ጨምሮ የሚያሳምር የውበት ማክዳ ይሆናል የሚል ሙሉ ዕምነት አለኝ። ስለዚህም ተሳፋችን መሠረቱ ጥብቅ ማገር ያለው ነው – የማይነቃነቅ።

ውይይትን መድፈር፤

ቀደም ባለው ጊዜም ከፊውዳል ሥርዓት በፊት በነበሩት ሆነ ዛሬ የዐለም አስተዳዳሪ ውይይት ነው። ንግግር በፊውዳሉ ዘመን የህዝብ ንብረትነቱን ተነጥቆ የጥቂት የመሬት ከበርቴዎች ስለነበር  „ፊውዳሊዝም የንግግር የጨላማ ዘመን“ ይባል ነበር።ለማንኛውም ውይይት ዘመናችንም የፈቀደው ሰፊ የማህበረሰብ ሙሉዑ የተሳትፎ ማሳ ነው። ማናቸውም ችግሮችን በመፍቻነት መሳሪያ የሆነው ውይይት ነው። ውይይት የሥነ – ንግግር ዘርፍ ነው። ሥነ – ንግግር ሁለት አውራ ቤተሰቦች አሉት። አንዱ ተናገሪ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አድማጭ ነው። የሁለቱ አጋፋሪ ሃዲድ ደግሞ ውይይት ነው። በዚህ ዘርፍ እኔ እንዳስተዋልኩት ከአንድ ብቁ መሪ የሚጠበቀውን ተናጋሪነት፤ አድማጭነት፤ ውይይትን የመድፈር አቅም ያለው መሪ ብሄራዊ ሠራዊታችን አግኝቷል ባይ ነኝ። አንድ ጥሩ ተናጋሪ ሠራዊቱን ለግዳጅ ለማሰማራት ብቻ ሳይሆን የሰራዊቱን አቅለግዳጅ ለማሰማራት በሰው ሃይል በተከታታይነት በማደራት እረገድም አዲስ ሃሳብን ለመቀበል አለመሸሸት ወሳኝ ስለሆነ፤ ይህ ጸጋ ያለው ሥነ – ቤዛና እና ሠራዊቱ በመደማመጥ ላይ የሰከነ የድል ባለቤትነቱ አይቀሬ ይሆናል። ህይወቱ በበሰለ ውይይት ተቀምሮ ያዪሁት ስለሆነም አርበኞቻችን ጥሩ አድማጭነት ጥሩ ተዋጊነት ብቻ ሳይሆን ጥሩ አሸናፊነትም ነውና ከልባቸው ሆነው ሙሴያቸውን ያደምጡት ዘንድ በታላቅ አክብሮት – አሳስባቸዋለሁ።

ችግርን መጋራት፤

መቼም ጦር ግንባር ላይ ትልቁ መስፈርት ይመስለኛል አንድ ሙሴ የአካሎቹን ችግር፤ መካራን በመጋራት አብይ ድርሻ አለው ፤ ለዚህ ደግሞ ሥህነ – ቤዛ ተፈጥሮባታል። ይህን የምለው ያለምክንያት – አይደለም። አዲስ አባባ በማዕካላዊ ታሥሮ በነበረበት ጊዜ የቤተ – ኦሮሞ ወንድሞቻችን ምሬታቸውን ጮክ ብለው ሲገልጹ አዳምጦ፣ ከልቦናው አስተውሎ አሳሪዎቹን እባካችሁ እንዳወያያቸው ፍቀዱልኝ በማለት ጠይቆ ነበር። የሚገርመው እሱም እስረኛ ነበር። ግን አልተፈቀደለትም። የእስረኛ ወገኖቹን ብሶት በቅርበት ለማደማጥ ችግር ላይ ሆኖ እንኳን መፍቀዱ በማናቸውም ሁኔታ ችግር ለሚገጥም ወገን ቅርብ ስለመሆኑ፣ አጽህኖታዊ መምህርነቱን ጉልበታም አንዲሆን ስለሚያደርግ በፈተናችሁ፣ በችግራችሁ፤ በውስጥ ብሶታችሁ ሁሉ አብሮ ሊሆን የሚችል መሪ ማግኝት የሰው ሥጦታ አይደለም፤ ግልጽ ሆናችሁ በመቅረብ ውስጣችሁ የሚላችሁን – ንገሩት። በመከራ ዕንባ፣ በአሳር ራህብ ሲቀልድ ዬኖረው የህወሓት ዘመን ማክተሙን የምታዩበት ብሩህ ዋዜማ ላይ እንዳለን ይሰማኛል ለእኔ፣ የአምላካችን  የሥነ ስኬት መሳሪያውን እንዲህ ረቂቅ ጸጋዎችን ለማዬት የመንፈስ ጥንካሬ አዎንታዊ ጉልበት ሲኖረው ብቻ ነው።

ዬእናት ሆዱነት – ፊርማ።

እናት ሆድነት የሚመነጨው ኢትዮጵያን ጽላት ከማድረግ ይመነጫል። ሥጦታም ነው ሰማያዊ። ሁላችንንም የእኔ ብሎ መቀበል።ይህን ብሄራዊ ስሜት ያልተቀማ፤ ሁለመናውን የእናቱን ጠረን ያጣጠመ ብቁ ዜጋ የወገኖቹን መከፋት የእኔ ብሎ የመቀበል አቅም እንዲኖረው ያደርገዋል። ለዚህም የሃቅ (fact) መጸሐፍ ጸሐፊው ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና „የቃሊቲው መንግሥት“ መጸሐፉ ላይ ሥህነ – ቤዛ  ጠያቂ ለሌላቸው አዛውንታት እዛው እስር ቤት አብሮ በቃልቲ ታሥሮ ጉዳያቸውን በባለቤትነት ተረክቦ በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ ዋስ በመሆን፤ ስንቅ ሊያቅብላቸው የሚችል ቤተሰብ የሌላቸውን ወገኖች ዬራሱን ስንቅ በማከፈል ብቻ ሳይወሰን መጸሐፉን „የነፃነት ጎህ ሲቀድ“ ሥጦታ ከባርከተላቸው አንዱ እኒያ አዛውንት አባታችን አንዱ እንደሆኑ ነው እኔ የተረዳሁት።

በዚህ የሰብዕዊነቱን ትልቅነት ዘመነ አራዊታዊ አስተዳደር ሲያከትም „ሰብዕዊነት“ ህጋችን – መተዳደሪያችን – ኑሯችን ሊሆን እንደሚችል ምልክቱ በብሄራዊ የነፃነት ሠራዊታችን ግንባታ መሰረቱን የሚጠለው በጭካኔ ላይ ሳይሆን „ሰውን“ አልቆ በተረጎመው ልዑቅ የዓለም ህዝብ ሁለመና ቋንቋ በሆነው „ሰው“ ከሚለው አምክንዮ ስለሚነሳ ነገ ብረሃን ነው። …. ውትድርና „ዬሰው“ ዘርን የሚያጠፋ ሳይሆን „ውትድርና „ለሰው ልጆች“ ተቆርቋሪ፣ ጠባቂ ተቋም እንዲሆን መንገዱ እዬተጠረገ ነው። … ይህ ለቀጣዩ ትውልድ ቋሳ – ገደል፤ ቂም – ገደል፤ ምህረት – አምንጪ፤ ፍቅርን – ከብካቢ፤ አብሮነትን – አንጋሺ አስከዛሬ ያልተጀመረ ወፍ ያወጣው አዲሱ መንገድ ነው። ….. ልናዬው የሚናፍቀን። ….. ልንኖርበት – የምንፈቅደው። ሰውኛ ጠርን ያለው። አዲስ ህይወት። ……. አንዳችን – ለሁላችን፤ ሁላችን – ለአንዳችን፤ እንደ ተፈጥሯችን ለመኖር የሚፈቀድልን፤ ፍንድቅድቅ ያለ ያልኖርንበት ግን አስኳሉ በሚያምር ሁኔታ የተጀመረ። ከዚህ ጋር በኢትዮጵያ መሬት በአካልም በመንፈስም በቀድሞው የኢትዮጵያ ሰብዕዊነት ጉባኤ /ኢሰመጉ/ የነበረው በኽረ የተባ ተሳትፎም ውስጡ ምን ያህል ለስብዕዊነት ክፍትና ግልጥ ፣ ቀና፣ ቅን እንደሆነ የሚያሳይ ንጡር ፊርማችን ነው።

የበለጸገ የተመክሮ ክህሎት አውድማ።

ተመክሮ በልምድም በሙያያም በዕድሜም የሚገኝ የብስለት ዕሴት ነው። የሰው ልጅ በትምህርት ተቋማት ብቻ አይደለም ልምድን የሚቀስመው። ይልቁንም የሰው ልጅ ለመማር ፈቃዱን ለመንፈሱ ከሰጠ ከሁሉም መልካም ነገሮች መማር ይችላል። በተለይ አንድ ሰው በተፈጥሮ የአስተዳደግ ብድለት ወይንም የማንነት ችግር ከሌለበት ከሚያሳድገው ታናሽ የአብርክና የማህጸን ልጅም እንኳን በዬሰዓቱ ት/ቤት ከቤቱ ጀምሮ አለው። የመጀመሪያዋ የህይወት ት/ቤት እናት ናት። ከዚህ ላይ ነው ሚስጢሩ ያለው። ሥህነ – ቤዛ  በአደገበት ቤተሰብ ገና ከውጥኑ በእውቀት መጎልመሱን የምታዩት ገና ት/ቤት እያለ ነበር የተማሪዎችን ውክልና ያስገኘው። ያ „ሀ“ ብሎ የቅብዕ ተመክሮው የተጠነሰሰበት ዓውደ – ማሳ ነበር። ከዚያ በኋላ በሀገር ውስጥ ሆነ በውጪ ሐገር የተሰማራባቸው የሥራ መስኮች፤ ውይይቶችን በመምራት፤ በሽምግልና ንቁ ተሳትፍ በማድረግ፤ አስታራቂነት-  በአስማሚነት ነጠላና ድርብርብ፤  ወላዊና ግላዊ የፖለቲካን ችግሮችን ሳይገፋ ልክ እንደ ወለደች እንደ እናት እጅግ አስጠግቶ ያዪባቸው ፈሊጦቹ ማግኔቶች ናቸው። ኃላፊነትን ሳይሸሽ – አጋጣሚዎችን ሁሉ ለተሳትፎ መፈቀዱ፤ የደረጀ ተመክሮውን ሁለገብና ሰብላማ እንዲሆን አድርጎታል። ይህ „ሁለገብ“ የትግል ስልት ሚስጢሩ ዝልቅ ነው። ይህ የዳበረ ልምድና በከፍተኛ ዩንቨርስቲዎች፤ በብሄራዊ ሐገራዊ የፓርቲ ምስረታ አዲስ ሃሳብ አስገኝነቱና የክንው ሂደቱ ጥሩ አዳማጭ ከሆን ምን አንዳለው፤ ምን እንደሚፈልግ፤ ምን እንደሚችል በተጨባጭ – አሳይቶናል። ዕውቅት ላይ የተመሠረ ብቃቱ፤ በተመክሮ የዳበረ ክህሎት፤ ተግባር ጠገብ በመሆኑ ለብሄራዊ የነፃነት አርበኛችን የቀና መንገድ ይሆነዋል። በአግባቡ በታነጸ፣ በተደራጀ መንፈስ ውስጥ ነገንም አሳምሮ መተመን ያስችላል። እውነት ለመናገር ውጤቱን ለመተንበይ ነብይነትን አይጠይቅም።

የሠራዊት ሥነምግባር

ሥነ – ምግባር በብዙ መልኮች የተለያዩ ገጽታዎች አሉት። እራሱን ያሸነፈ በዬትኛውም የሥነ – ምግባር ዓይነቶች ለመተዳዳር በህግጋቱ ወይንም በደንቦች ለመተዳደር ዝግጁ ነው። የውትድርና ሥነ – ምግባር ደግሞ ጠብቅ ያለ በመሆኑ በዚህ ሙያ ላልነበሩ ወገኖች ሲጀመር ከበድ ሊላቸው ይችላል። ነገር ግን ለሥነ – ቤዛ ወጣትነቱን በርሃ ላይ በኢህአፓ ጋንታ ውስጥ ተሰልፎ የሠራ በመሆኑ፤ የነበረውን ልምዱ ዘመኑ ከሚፈቅደው ከሙሉ ዕድሜ ጋር ይታደስለት እንደሆነ እንጂ አዲሱ ስላልሆነ፤ በሥነ ምግባሩ ውስጥ የኖረ ስለሆነ የልምድ ልውውጥ የሽግግር ጊዜ ሳያስፈልገው በቀጥታ ተግባር መስመር ላይ ለመግባት ይቀለዋል። ከዚህ ጋር ላስውሰው እምሻው ትልቁ ቁም ነገር ወጣት ሳለ ኤርትራመሬት ላይ  ከተሰጠው ምርጫ አንዱን መርጦ የዕውቀት ባለጸጋ እንዲሆን፤ ሌሎች ልምዶችን እንዲያካብት ወደ ሱዳን መሻገሪያ የነበረችው መሬት ስትሆን ዛሬ በጉልምስናው ደግሞ ብሄራዊ ሃላፊነቱን ይወጣ ዘንድ እጇን ዘርጋታ የተቀበለችው የተከደነ ሚስጢር የሚቀናባት መሬት መሆኗ ነው። ለሥህን – ቤዛ የኤርትራ መሬት አዲሱ አይደለም። ትናንት ነበረበት። ወደ ሱዳን ከመሄዱ በፊት ኖሮባታል። በርሃ ቀመስ አዬሯን ቀድሞ – አጣጥሞታል። ወዙም ናት። ከዛ በኋላ ነው ወደ ሱዳን ያቀናው፤ ዛሬ ደግሞ ከአሜሪካ ወደ ኤርትራ እንዲህ መንገድ ሲዘረጋ ፈጣሪ አምካላችን ምን ይሆን ያሰበው? ይንፍቀኛል ይህ ሚስጢር ተትርጉሞ ተመሳጥሮ በሥነ – ጥበቡ የማይበት።

የቤተሰብ ሃላፊነት በመቀበል መብቀል።

ቤተሰብ የማህበረሰቡ መሰረት ነው። የአንድ ማህበረሰብ መነሻ የሆነው ቤተሰባዊ አስተዳደር በሀገር ግንባታ ላይ እጅግ መሠረታዊ ጉዳይ ነው። አንድ ብቁ የቤተሰብ መሪ ሌላውንም ለመምራት መሳሪያው በማዳፉ ነው። ሥህን – ቤዛ ባለትዳርና የልጆች አባት መሆኑ፤ በሠራዊቱ ውስጥ ያሉትን ከቤተሰብ ጋር የተያያዙ ማናቸውንም ጉዳዮች በፈቃደኝነት ለማስተናገድ በሩ ክፍት ነው። ሠራዊቱን እንደ ቤተሰቡ የማዬት አቅሙም እዮር ነው። ሠራዊቱ በቤተሰቡ ጉዳይ ለሚያቀርበው ጥያቄም ብቁ አድማጫቸው ይሆናል። ሁሉንም ለመጋራት ስንዱነቱ ወግ ያለው መስመር ነው። ከዚህ ጋር በምንም ሁኔታ ኑሮው ጥገኛ አይሆንም። በዘመናይ ኑሮው በኃላፊነት ቤት ውስጥ ተግባር ላይ የተገኘበት ልምዱ ሠራዊቱ በድንቅነት የሚማርባቸው ት/ቤቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ሙሉ ዕምነት አለኝ።

ናፍቆትን መጋራት – በተመሰጦ።

ናፍቆት ብትፈልጉትም ባትፈልጉትም የማይለቅ የመንፈስ ሞጋች፤ አዛዥም ናዛዥም ሥነ – አምክንዮ ነው። የሚፍቅ ሰው ጠረኑ „ሰውኛ“ ነው። የሚናፍቅ ሰው ፍቅር ነው። የሚናፍቅ ሰው የእኛ ነው። ናፍቆት የውስጥ ነው። ስለሆነም ረቂቅ ነው። ረቂቅነቱን አብራርቶ ለመግለጥ ቢቸግርም ናፍቆት ፍቅር የያዘው ሰው እንደሚያብተከትከው መላ ቅጥ – ያሳጣል። አንዳንድ ጊዜም የህመም ስሜትን ያስከትላል ግን ህመሙ ሥም የለሽ ነው። ናፍቆት ልትሸሸው የማትችል የምትወደው ሆኖ የማታገኘው ስትሆን ግን ብስጩ የሚያድርግ ነው። ሀገሩን የሚወድ ህዝቡንም ከልቡ ውስጥ – ይወዳል። ሀገሩን የሚናፍቅ ህዝቡንም ከህሊናው – ይናፍቃል። ናፍቆቱን ለማወራረድ አጋጣሚውን ሲያገኝ ደግሞ ለእሱ የሰማይ ገነት ነው።

ሥህነ – ቤዛ የኤርትራን መሬት ሲረግጥ አቀባባል ያደረጉለትን ወገኖቹን ሲያገኝ እንዲት እቅፍ አድርጎ እንደያዛቸው ፎቶውን ደጋግማችሁ – መርምሩት። እዩት – አስተውሉት። አዳምጡት – ማህበራዊ ሚደያ ላይ ስላለ – በትህትና ። እንደዛ ጥብቅ አድርጎ፣ እንደዛ ጥግት ብሎ የሀገሩን ወዝ ሲጣጣ ተመልክተናል። ስለዚህ ራህብን የሚያውቀው የተራበው ስለሆነ፤ ናፍቆትን የሚያውቀውም የናፍቆት ጉጉተኛ ስለሆነ፤ የሠራዊታችን አባላትና አካላት ላለባቸው ብሄራዊ፣ ቤተሰባዊ፣ ወገናዊ፤ ነፃነታዊ የናፍቆት ረሃብ ቅርባቸው አንደሚሆን ያ ፎቶ አሳምሮ ለሥርጉተ – ነግሯታል። እግዚአብሄርንም አምስግናበታለች። በሁኔታው ሁሉ ተሸብሬ ቢያስለቅሰኝም ግን ሻማዬን አብርቼ እናት ሀገሬን ከነሁለመናዋ በምልሰት – ቃኝቼበታለሁ። እኔም የሀገሬን የኢትዮጵያ ትዝታ ተሳለሜበታለሁ። አብሶ የገጠሩን አርሶ አደር ናፍቆት ለእኔ ልዩ ጌጤ ነውና፤ የሐገሬን የኢትዮጵያ ገበሬዎችንም ከምንም ከማንም በላይ እወዳቸዋለሁ።

የገበሬው ኑሮ ሥነ – ደንብ የእኔነቴ ሰነድ ነውና – ዕንባዬ በተፈጥሯዊ ሁለቱ መስኮቶች እዬለቀኩኝ ናፍቆቴን አወራርጄበታለሁ። ስለዚህም የምትፈልጉትን፤ በውስጣችሁ የምታልሙትን፤ በዕውን መሬት ላይ ሆኖ ስታዩት ሐሤት ነው። ዕንባን አምላክ – ያዳምጣል። ሰጠን! እኔ በሂደቱ ሁሉ እጅግ – ተማርኬያለሁ፤ ተመስጫለሁ፤ መንፈሴ ሁሉ – ረግቶልኛል። የብሄራዊ ነፃነት ናፍቆት ምርኮኛ ነኝና። ፈተናን እረቶ የወጣ ንጥር ቀለም በቦታው ተገኜ።

ዬሃሳብ ነፃነትን – መፍቀድ።

ነፃ ማሕበረሰብ ህልማችን ነው። አዲስ ሃሳብ ለማፍለቅ የሚችሉ ወገኖች በባዕታቸው ምን ያህል እስረኛ አንደሆኑ ከልቡ ሆኖ ያዳማጠው ሙሴ በሀገሩ በኢትዮጵያ በተገኘ ጊዜ የሃሳብ ነፃነት መታሰርን በተለያዩ አንግላት ውስጥ ሆኖ ከልቡ መርምሮታል። ዬነፃነት አስፈላጊነት በሚገባ ውስጡን ዘልቆ መጎብኘት ብቻ ሳይሆን፤  ባገኘው አጋጣሚ፤ በጹሑፎቹ፤ በመመጣጥፉ በቃለምልልሱ፤ በኢህአፓም በነበረበት ጊዜ ለእስር የዳረገው ይሄው መሆኑን – ተርድቻለሁ። በተሳተፋባቸው የውይይት መድረኮች፤ ፓናል ዴስከሽኖች፤ የአወያይነት – ዕድሎች፤ ፓለቲካዊ ክርክሮች (ሙግቶች) ሁሉ ተጠዬቅን የመፍቀድ አቅሙ ውስጡን በግልጥ ማዬት አስችሎኛል። ስለሆነም ለነፃነት ሁለገብ ተፈጥሮ ሐዋርያ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ስለዚህ ለሃሳብ ነፃነት ራሱን ያሰናዳ ብቻ ሳይሆን፤ ቀዳሚ ተሟጋችነቱን ሥራ ላይ ለማዋል በቅርበት በአርበኛው ውስጥ መገኘቱ፤ ካለምንም እንቅፋት በሠራዊቱ ውስጥ ሃሳብን ያለ ተዕቅቦ ማንሸራሸር – ያስችላል። ስለዚህም የሠራዊቱ አባላት የሚሰማቸውን፤ ይጠቅማል የሚሉትን፤ ያወጣል የሚሉትን ሳይሸማቀቁ፤ ሳይሰጉ ያለምንም ገደብ የሚገልፁበት አጋጣሚው ሰፊ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ ይህ የመጀመሪያው ዬሃሳብ ነፃነት ት/ቤት የመሆኑ ዕድሉም ሰፊ ይሆናል ብዬ አስባለሁ። ሰው እራሱን መግለጽ ሲችል ውስጡን ማዬት ይቻላል። ውስጡን ማዬት ሲቻል ደግሞ ለመምራት ሆነ ለማስተዳደር ቀና መስመር ተገኘ ማለት ነውና፤ መክሊትና ምኞት አኃታዊ ጋብቻ ይፈጽማሉ ብዬ አስባለሁ። ይህ በራሱ የበላይነት እዬሞሸሸ፤ የበታችነትም በአዲስ መንፈስ እያቆጠቆጠ መሃል ላይ የመደማመጥ ባህል መባቻ ዕውጃ ክ/ጊዜ ይሆናል። ነገም ሳይታፈን እንደ እድገቱ እንዲበቅል ይለፍ – ይኖረዋል።

አጽህኖት

ተፈጥሮ ብዙ የምትልገሰው ነገር አላት። የሰው ልጅ ማህበራዊ አንሰሳ ነው የሚበላው ኑሮውን የሚመራው በማህበራዊ ሁነቶች ስለመሆኑ ለማገናዘብ ነው። ማህበራዊነት የወልዮሽ ገብታ ነው። የወልዮሹ ሌማት በፖለቲካ ዕሳቤ ሲዘምን በግል ኃላፊንትና በጋራ አመራር ላይ የተመሠረተ ይሆናል። በዚህ የአደረጃጃት ሂደታዊ መዋለ ጉዞ ቀደም ባለው ጊዜ ግንቦት 7ን ሳስተዋለው አጽህኖት ያለው ስልጡን አመራር አንደ ነበረው ነው። እኔ በንቅናቄው መሪ አካላት የብቃት ድልድል፤ የምርጫ ስምሪት ልዩ የሆነ የጸደቀ መንፈስ አይቸበታለሁ። ኮሽ የሚል ነገር አይደመጥም። አፈንግጦ የሚወጣ የሥነ – ምግባር ግድፈት – አይታይም። አልፎ ተርፎም የሌላውን ደንበር የጣሰ የሥነ – ምግባራ ጉዱፍ ቅንጣት የነቁጥ ያህል – አልታዬበትም። ፍጹም የተረጋጋ፤ በውስጡ ሰላም ተጠቃሚ፤ በተሰጠው ጸጋ አቅሙን የገነባ ንቅናቄ ሆነ ነበር የማዬው። እንዲያውም ከውስጤ ሆኜ ስለምከታተለው የቤተሳባዊ አቀራረብ አያያዙ አመዝኖ አይቼዋለሁ።

የችሎታው ትኩረት ብቁነት ዓላማን ለማሰካት ባለ ልዩ ብቁነት፤ አቅል ያለው – ብልህነት፤ የቁርጠኛ ሃሳብ – ቤተኝነት፤ የአውንታዊነት ጣዕምና ለዛ፤ ጊዜን የመተመን – ስልታዊነት፤ ጠንካራ – ሰራተኝነት፤ የወራት ቅደም ተከተልና ለቀድመው ልዩ አጽህኖት መስጠትን፤ ሌሎችን ለመሳብ ሆነ ለማነሳሳት እንዲሁም ለማንቀሳቀስ ያስቻለው ልዩ ተስጦዕው ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ከሁሉ በላይ ወደፊት ለማዬት ያለው አጽህኖት ዘመን አሻጋሪ  – አድርጎታል። ራሱን ሳይሸሽ ፈተናን እዬረታ ወደ ፊት መገስገሱ የድፍረቱ ልክ በእጁ ካለው ሙሉ አቅሙ የሚቀዳ ስለመሆኑ ምስክሩ ተግባሩ ነው። ራዕዩን በማካፈል ወይንም በማጋራት ረገድም ቆጥቋጣ – አይደለም። ስለሆነም ነው በፖለቲካ አመራሩ አጽህኖታዊ ብቃት ተፏካካሪነቱ ሆነ ተደማጭነቶ ነጥሮ በመውጣት ጉልበታም መሆኑ ለጠላትም ለወዳጅም የማይነቃነቅ ብረት መዝጊያ መሆኑን ያስመሰከረው። ለዚህም ነበር እኔ በግሌ በዬአጋጣሚ የሚነሱ ወጀቦችን ጥሼ በመግባት የውትድርና ወይንም የዘበኝነት ተግባር ስከውን የኖርኩት። ለእኔ የተግባሩ ሂደት ምላሽ የሚሰጠኝ የዲሞክራሲ ባህሉ በማዕካላዊ አመራሩ አድጎ የጎለመሰ ስለመሆኑ ከመነሻው ነበር የተገነዘብኩት። „የሚያድግ ጥጃ ከገመዱ። በአያያዝ ይቀደዳል በአነጋገር ይፈረዳል“ እንዲሉ። ዓላማውን በአውሮፓ ሲያስተዋውቅ የጻፍኩት መጣጥፍ  „ሽልማታችን“ ይል ነበር። ሁለተኛ ሂደቱንም „ወርቅ ያነጠረ ብረት ያቀለጠ“ የሚል እርግጠኛ የሚያደርግ እርምጃ ነበር የወሰድኩት ዛሬ ላይ ሁኜ መጣጥፎቹን ሳነብ – ይገርመኛል። ምክንያቱም ጥርት ያለው የአደረጃጃት መሰረቱ ገና ከውጥኑ ብልሃቱ ያናግር ነበር። ትርምሳዊ ወጀቦችን ኬላ የሠራላቸው በማንፌስቶ ላይ ነበር። ሁለቱንም የፁሑፎቼን ሊንኮች መጨረሻ ላይ እለጥፋቸዋለሁ። ዛሬም አጽህኖት መገብ ሂደቱ ለተስፋ እውነተኛ ጽኑ አርበኛ እንዲሆን አድርጎታል። አጽህኖታዊ ጉዞው ለራዕያችን የትውልድ ያህል አስተማማኝ ነው ማለት እችላለሁ። መሪ ያለው ፍላጎት ዛሬን ያኖራል። ነገን – ያስገኛል። ከነገ ወዲያንም ይገራል – በአጽህኖት!

እንቅልፍ አልቦሽ – ገድነት

ገድ ለመንገድ ልዩ ዕድል ነው። የነቃ መንፈስ ሲፈጠር እንቅልፍን – ይጸዬፈዋል። ተኝቶ መኖር ክፍሉ – አይደለም። የነቃ መንፈስ ተስፋ ቆራጭነት ተዋሽም አይደለም። የነቃ መንፈስ ሽንፈት መንገዱ – አይደለም። መዳፍ የሚስቀድመው መንፈስ ሁልጊዜም ትጉህ  – ታታሪና ባተሌ ነው። ተግባር ባለበት ሁሉ የተግባር ገበሬ ሰብላማ ነው። ሳተናው – ዓላማ ያለው ስለሆነ ታክቶ የሚተወው አንዳችም ነገር አይኖረውም። መጀመሪያ በበር ይጀምራል። በሩ ሲዘጋ በመስኮት። መስኮቱ ሲዘጋ በጣሪያ፤ ጣሪያው ሲዘጋ ደግሞ በምድር በታች። ሁሉንም ዓይነት ነገር በሁለገብ ይሞክራል – ራዕዩን በድል ያሰክናል። ከሥህነ – ቤዛ ያዬነው ይህን ነው። በተፈቀደለትም – ባልተፈቀደለትም፤ በተወደደለትም ባልተወደደበትም፤ ይለፍ በተሰጣውም ይለፍ በተከለከለበትም መንገድ ሳይተኛ ይልቁንም በጠንካራ መንፈስ ቀጠለ — ቀጠለ —- ቀጠለ ዕድለኛ ነው የልብ አድራሽ አጋርም አላጣም። አይዞሕ ባይም አልተነፈገም፤ ይሔው በዚህ ቀጪ የህወሓት ፋሽስታዊ ዘመን የሚሊዮኖች ድምጽ ለመሆን የሰጠው እንቅልፍ አልቦሽነቱ ነው እላለሁ – እኔው። ይቻላል እንደ ገና አንደ ገና – ከተመኮረ። ከዚህ ብዙ የምንማርበት የተምሳሌት፤ የአብነት ሰብሎች አሉ። በተለይም ወጣቱ እኔም እንደሱ …. ማለትን፤ ሞዴላችሁ – ተምሳሌችሁ ገድም ነውና። መንፈሳችሁን ሳትሰስቱ ቀልቡት ለእናንተው ነው የሚታክተው ነገን ለመውለድ። ድምጹን ሩሃችሁ አድርጉት።

ዕድልን አለማሽሎክ

ብዙ ሰው ለዚህ ተጠቃሚ አይደለም። እንዲያውም ዕድሉ ካለፈ በኋላ እንኳን ዕድሉ ስለመኖሩ ማስተወስ እንኳን የማይቻልበት ብዙ ገጠመኞች አሉ። በዚህ ዘርፍ ሥህነ – ቤዛ በጣም በሠለጠነ አኳኋን ዕድሉን ሁሉ – ተጥቅሞበታል። ሁልአቀፍ ችሎታው – ሃይሉ ሆነ ብርታታቱ የተቀዳውም ከዚኽው ነው። ዝልቅ ፍላጎቱን – ዘለግ ያለ ራዕዩን ለማሳካት ታላቁ መሳሪያው የሚያገኛቸውን ዕድሎች ጥቃቅኖች ናቸው ብሎ ሳይንቅ በሚገባ ተጥቅሞባቸዋል። ግዙፎችንም ከነፈተናቸው የመሸከም አቅሙም አንቱ ነው። ይህ ፍጹም ረቂቅ የሆነ ጸጋ ለሁላችንም ተቋም ሊሆኑ የሚችል – ይመስለኛል። ስዋሰው።

ትልምና ግብ

ትልም ህልም ስለሆነ ሁሉ ሰው ሊኖረው ይችላል። ቁምነገሩ ለትልሙ ስኬት መንገድ መምረጥ፤ ሂደቱን አስቀድሞ በርቀት መተንበይ ከመቻሉ ላይ ነው። ይህን ሥህነ – ቤዛ በሚወጥናቸው አዳዲስ ትልሞች፤ በሚሳተፍባቸው አዳዲስ የተግባር ማሳዎች በጋራ የመሥራት መርህን ዕውን ለማድረግ ከማን ጋር ነው የምሥራው? የሚለውን ቀድሞ ጊዜ ወስዶ እልባት የሚሰጥ ብልህ ሰው መሆኑን እኔ በግሌ – ተገንዝቤያለሁ። ዝም ብሎ አቅሙን አያባክንም። የሁለመና የስሌት ቀመሩ ዝንጥ ያለች ሌሊኛ – ሥልጡን -ሞድኛ ናት። ማማከር ይወዳል – በጥንቁቁነት። በግል ህይወቱም ቢሆን ፈተና ያለባቸውን አቅጣጫዎች ሁሉ ደፍሮ የመጀመር አቅሙ ድጋፍ የሚያገኘው ከቤቱ ከትዳር አካሉ ጀምሮ ነው። ይህ የምርጫውን ጥራትና ብቃት አሳምሮ – ይተረጉምልናል። እሱ አብዝቶ ጊዜ በሚሰጥባቸው ማናቸውም ጉዳዮች የቤተሰቡን ጊዜ በእጅጉ ይቀናንሳል፤ ያጎሳቆላል፤ ባለፈም ጥቃትም ያደርሳል። ነገር ግን ስሌቱ የነብይነት ያህል ስለሆነ ዬስኬቱ ፍሬው ዝቀሽ ነው። ያካክሳል። ድፍረቱ አቅምን የለካ ብቻ ሳይሆን የወቅት ሥጦታዎችንም – ያብራራ ነው። ስለዚህ አሁንም ይህን የመሰለ እርምጃ ሲወስድ በግልብ አስቦ በጥድፊያ ተልሞ የከወነው አይደለም። ምክንያቱም ካለፈበት የህይወት ተመክሮው ሁሉ እራሱን የማድመጥ አቅሙ የፀሐይ ብርሃን ያህል ጉልበት አለው። እርምጃው ሳቢ፣ ሌሎችንም በቀጥታ ወደ መንገዱ – የሚያስገባ፤ ሌሎችን በፍቅር የሚነሳሳና የሚያሳትፍ ግልጽነት – ቀጥተኝነት በተጠያቂነት ያጌጠ መንገድ ተከታይ ነው። ……

መርኽ

የጋራ ሥራ ሁነኛነት መለኪያው የመርኽ ሰውነት ነው። መርኽ የሚነሳው እራስን ከመግዛት፤ እራስን ከማስተዳደር፤ እራሰን ከማቅ ነው። በሂደቱ ጉስቁል የሚያድርጉ ገጠመኞች ሊኖሩ ቢችሉም የመርኽ ሰው የመርህ ተፈጻሚት በራሱ ላይ ሲሆን አደላድሎና አስመችቶ የመቀበል አቅሙ ነው የመርኸው ሰው የሚያሰኘው። የሰው ልጅ በግል ህይወቱ ህይወቱን የሚመራበት ደንበር ሊኖረው ይገባል። ያን ደንበር ጥሶ እንዳይሄድ የሚያደርገው መርኽ አክባሪነቱ ነው። በማናቸውም ሃይማኖታዊ፤ ባህላዊ፤ ሙያዊው፤ ፖለቲካዊ ተሳትፏዊ፤ ሃላፊነታዊ፤ ወላዊ ጉዳዮች ሁሉ በአባልነት እራሱን ሲያስመዘግብ ማዕቀፉ አስተዳደሪው ውል ያሠረበት መርኽ ይሆናል። በዚህ መሥፈርት እንደ ሌሎቹ የቁም ነገር መስኮች ሁሉ መርኽ ይከበር የመጀመሪያው ቀዳሚው የሥህነ – ቤዛ የፊደል ገበታው መሆኑን በሚገባ – ተገንዝቤያለሁ። ለዚህም ነው እላፊ ሄዶ የሌላውን ድንበር ሲጥስ የማይታዬው። ይህ ሥህነ – ምግባር በኃላፊነት የሚመራቸውን ድርጀቶችም ከተመልካች ጠረባ አድኖታል።

ሌላው በመርኽ አልተገዛም ብሎ የመወቅስ አንድ ሰው እሱ በዛ መርኽ ውስጥ መሆኑን ማረጋጋጥ አለበት። አንድ ሰው መብቱ በአደባባይ ተረገጠ ብሎ የሚጮኽ ሰው ለዛውም ለረጋጮች ተራጋጭ ጥብቅና የቆመ ሰው፤ ለሌላው የሚሰጠው የሰውነት ክብርም በማዋረድ፣ በማንቋሸሽ፤ በሳቅና በስላቅ መሞሽር፤ በማጣጣል ማንቆጥቆጥ – አይኖርበትም። ለዛውም ቁጥር ሥፍር የሌላቸው አንቱ አቅም ያላቸው ደጋፊዎች ላሉት፤ የጋራ ጠላት ወያኔ ያሰረው – በሌለበት ሞት የፈረደበት፤  ያ ሰው ልኩም ደረጃውም አቅሙም ከፍ ያለ ሆኖ ፤ የበዛ ተቀባይነትና ተደማጭነት ያለው፤ ህወሓት ጠላቴ ነው ባዩ ወገኑን አውርዶ ሲጠቀጥቅ ለመርኽ ተገዥነቱን ታዛቢዎች ውስጡን እንዲለኩ፤ ስዕላቸውን እንዲያስተካክሉ ገልጦ አስርክቧል ማለት ነው። አብሶ ተምሬያለሁ በሚለው ወገን ከሆነ ግድፈቱ የሚፈጸመው የእኔ ማህይምነት በስንት ጣዕሙ ትላለች – ሥርጉትሻ። እድገት ወደ ላይ እንጂ ቁልቁል ሲሆን፣ አጋጣሚዎች ሁሉ መክነው ሲታዩ፣ ለትውልድ የውርዴት ት/ቤት ናሙና ለመሆን እራስ መፍቀድ ስለሆነ፣ ጸሎት ያስፈልገዋል። የሆነ ሆኖ የመርኽ ሰውነቱ ፍሬ አዘል ሰብል ገብ የሆነው ሥህን – ቤዛ በመርኽ ምሰሶነት የነገ የድህነት አብይ መንገድ ነው። የመርኽ ሰውነት የሚያስከብረው እራስን ብቻ ሳይሆን ሐገርንም ጭምር ነው። በግድፈቶች ልክ ሀገር ትወቃሳለች፤ በመልካም ነገሮች ልክም ሀገር ትከብራለች። ቀደም ባላው ጊዜ ሐገራችን ኢትዮጵያ ጎልታ የምትታይ ተፈሪ – ተከባሪ ሐገር ነበረች። የመርኽ ልጇቿ አንቱ አሰኝተዋታል። ዛሬም ጥሪያዋ ይኸው ነው። የሐገር ፍቅር የሚባለው መጀመሪያ ራስን በመርኽ ማስገዛት ነው። አብሶ ያልተጻፈው ህጋችን ከዩንቨርስቲ ምርቁነት በላይ – በላይ ነው። ልብ ይስጠን።

ድምዳሜ

ለእኔ ፎቶ ብዙ ነገር – ይነግረኛል። ለእኔ ጹሑፍ ብዙ – ያስተምረኛል። ለእኔ ንግግር ብዙ  – ያሳዬኛል። ሰውንም ሳገኝ ገበርዲኑን አካላዊ ቁመናውን ወይንም ቁመቱን ወይንም የዕውቀት ደረጃውን አይደለም የማዬው – ውስጡን ነው። ውስጥን ፈቅጄ ፈልጌ  ማዬቴ እራሴም የሚጎድልብኝን ነገር ለማስተካክል ነው። አለኝ የምለው ነገር ልፈትሽበት ነው። ከሁሉ በላይ ሐገራዊ በሆኑ አጋጣሚዎች እጅግ የለማ ሂደቶችን ዕድሌ ስላስተናገደ – ማነፃጸርም  – ማወዳደርም የምችልበት ውበታም የሆኑ ወቅታትን በህይወቴ አሳልፌያለሁ። አጋጣሚዎቹ ከዕድሜዬ በላይ እጥፍ ናቸው። እርግጥ ዬፈተና አጥር የበዛበት ቢሆንም ፈተናዎቼ በራሳቸው የይበቃኛል ተቋሞቼ ናቸው። ከሁሉ በላይ ተመክሮወቼ ሆነ ተፈጥሮዬ የማምንበትን ውስጤን ገልጬ የመድፈር አቅሙ አኑሮልኛል

ስለሆነም በሥህነ – ቤዛ ዙሪያ ምስጋናው ቀርቶ ድንበር ዘለል ዘለፋዎቹና አቅምን የሚፈታተኑ የጥላቻ ወጆቦች፤ የቅናት ቅንቅን „ሰው“ የሚለውን ታላቅ ፍጡር – የተዳፈሩ፤ የነፃነት ናፍቆት ቃናን – የተጋፉ፤ የተስፋዬ ተጻራሪ አቋሞች ስለነበሩ፤ ውስጤን ገልጬ ማሳዬት ግድ አለኝና እንዲህ በተከታታይ ልጽፍ – ፈልግሁኝ። እርግጥ አልፎ አልፎም የነበሩትን አውሎዎች በአጽህኖት ስገልጽ ብቆይም ራሱን አስችዬ በርዕስ መጻፉ ግን ወቅታዊ መሆኑ ብቻ ሳይሆን – እኔም አንዲት ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነኝና የእኔ ለሆኑ ሁነኛወች ነፃነቴን መጠቀም ግድ አለኝ ።

ላለው በኽረ አምክንዮ ነገ ኢትዮጵያ ሀገራችን በነበረችበት የታመሰ ረግረጋዊ ቂም ተከል መንገድ መቀጠል የለባትም። ለዚህም ጥራትና ብቃት ያለው፤ ሌሎች ከህይወቱ ሊማሩበት የሚችሉ፤ ተተኪዎች ተምሳሌነቱን ሊጠጡት የሚችሉት፤ ሞዴል ሊሆን የቻለ ራሱን በሁለገብ በብቃት ያሰናዳ መንፈስ ልዕልት ኢትዮጵያ – ያስፈልጋታል። ስለሆነም ተግባሩ ከዛሬ ጀምሮ መሬት ይዞ መሰራት ስላለበት አምኘበት ነው የጀመርኩት። ስለሆነም የምዕራፋት እርገት በጊዜያዊነት እንጂ እንደ አስፈላጊነቱ በዚህ ወሳኝና ዓይን ጉዳይ ላይ እምመላለስበት ቀጥተኛ ሀዲዴ ስለመሆኑ መግለጽ – አውዳለሁ። የዜግነት እኩልነት መንፈስ ቡቃያ ድርድር የለም።

በዓይን ቀልድ የለም። በሰንደቅዓላማችን ዳግሚያ ተንሳኤ ድርድር – ቧልት የለም። በአብሮነታችን የእኩልነት አዲስ የዴሚክራሲ ፍላጎታችን የላሜ ቦራ ጨዋታ ሆነ አፍራሽ ትዕይንት መከርቸም ይኖርበታል። ከሁሉ በላይ ድነት የማያጣው የሰፈርተኝነት፤ የቤተ – ነገድ ነቀርሳዊ ትርትር ዕሳቤ ቀብሩ መከወን አለበት። እኛ ሁሉን አሳታፊ፤ አዲስ ብሩህ የእኩልነት ሥርዓት ናፍቆት አለብን። አሸናፊና ተሸናፊ የሌለበት የመደማመጥ ስስት አለብን። አሸናፊው ሃሳብ ተሸናፊውንም በጥሩ አያያዝ ሳያገል እኩል ተጠቃሚ የሚሆንበትን ያደገ የዴሞክራሲ ሂደት ቀልባችን ነው። ስለሆነም ሥህነ – ቤዛ አርበኛ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ሆነ የከፍተኛ አርበኞች ግንቦት 7 አመራሮቹን ዓላማ የራሴ ጉዳይ ነውና ሥነ – ልቦናዊ ጥበቃውን በሚመለከት ሁልጊዜም ዘብ – እቆማለሁ። አርበኞቼ ከህይወቴ በላይ ናቸው። ናሙናነት እሳትን በመድፈር አርበኛ ነአምን ዘለቀ እና አርበኛ ኤፍሬም ማዲቦ በመሆን ጌጥ ሆኑ። ታሪክም ከበረ። ትውልድም ለሰንደቅዓላማው ባንድ ቅኔ ዜማ ዘመረ። ኑሩልን እግዚአብሄር ይስጥልን።

በመጨረሻ – መሆንን ላከበረ፣ መሆንን ለፈቀደ የኤርትራው ከፍተኛ የፖለቲካ አመራርም ከልብ በአክብሮት ምስጋናዬን አቀርባለሁ። እግዚአብሄር ይስጥልኝ። ብሌናችን የእኛ ብቻ ሳይሆን የናንተም ሃብት ነው። አንዲሁም የአፍሪካ ቀንድም፤ ባለፈም የአኽጉራችን የሰላም፣ የመረጋጋት የፍቅር ሃዲድ ሐዋርያ ነውና በጋራ በመከባበር ከድህነት፤ ከጥላቻ፤ ከፉክክር፤ ከቁርሾ የምንላቀቅበት፤ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ እትብታዊ ጉርብትና አውራ መንገድ ነውና ጥበቃውና ጥንቃቄውን አክሎ በኃላፊነት የኤርትራ ፕሬዚዳንታዊ ቢሮ እንዲወስድም በትሁት መንፈስ  – አሳስባለሁ። ዬኤርትራ ጉርብትና ለእኛ እንደ ኬንያ ወይንም እንደ ሱዳን አይደለም። እእ። ኤርትራ እኛ ናት። እስኪ ወግ ደርሶን መኖርን በፍቅር እንደ ገና አዎን! እንደ ገና በድርጊት አስጊጠን – እንሞሽር ….. ወህም እንበል። ተምሳሌነታዊ ጉርብትና እስኪ ጊዜ ይፈቅድለት። ለዚያ ያብቃን አዶናይ! አሜን!

ለነበረን ሽክ ያለ ዘንካታ የመደማመጥ ጊዜ አመሰግንኳችሁ። አከብርኳችሁ። ከልብ መንፈሴን ሸልምኳችሁ – ለእኔዎቹ ታዳሚዎቼ።

ዘሐበሻ ትእግስታችሁ አስተማረኝ  -ኑሩልኝ።  የልብ አድራሿ ነፃነት እንዲህ – ትጥማለች።

http://ethio.info/tsegaye/April2009/Edemta-Shelematachen.pdf

http://ethio.info/tsegaye/June2009/Tesfa-Ginbot-7-Sebesba.pdf

ለእኔስ ሰው መሆኔ ብቻ ይበቃኛል

እግዚአብሄር ይስጥልኝ

 

 

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>