Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የመሐል ሀገር ሰው መልዕክት ለትግራይ ሰው! (በፍቃዱ ኃይሉ)

$
0
0

በፍቃዱ ኃይሉ
ትግራይ የኢትዮጵያ ገናና ታሪክ መሬቷ ላይ የተጻፈባት ክልል ናት፡፡ ብዙዎች ‹‹የኢትዮጵያ ራስ ናት›› የሚሉት ለዚህ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ ወደኋላ 3000 ዓመት የሚያደርሰው የአክሱም ስልጣኔ አሻራውን ትቶ የሄደው በትግራይ ክልል፣ አክሱም ከተማ ነው፡፡ ከአረቦች ተቀድቷል የሚባለውን የንግስተ ሳባ ታሪክ ‹‹ክብረ ነገስት›› በሚባለው መጽሐፍ ተርጉመው ለዚህ ትውልድ ያኖሩልን የትግራይ ሊቃውንት ናቸው፡፡
ሌላው ቀርቶ ህብረ-ብሄራዊ ቅርስ የሆነንን የሳባ ፊደል ለመላው ኢትዮጵያዊ ያወረሱት የትግራይ ሊቃውንት ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያዊነት ቀለሞች አንዱ የሆነው ያሬዳዊው ዜማ የተቀዳው ከትግራይ ምድር ነው፡፡ እነዚህና ሌሎች ያልጠቀስኳቸው እውነታዎች ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚኮራባቸው ናቸው፡፡
ኢትዮጵያዊነት በትግራይና በሌሎችም ህዝቦች አኩሪ ታሪክ፣ ባህልና ስርዓት ተገምዶ የተፈጠረ ማንነት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ነገሥታት በመጡና በሄዱ ቁጥር ለራሳቸው ጥቅም አንዱን ወገን ከጎናቸው በማሰለፍ ሌላውን ወገን ያጠቁ ነበር፡፡ የአሁኑ የሀገራችን ገዢዎችም፣ ይህንን ስልት እየተጠቀሙ በስጋና መንፈስ የተገነባውን ህብረታችንን ሊያፈርሱብን ከጫፍ ደርሰዋል፡፡ የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ለዚህ እኩይ ተግባር ትግራዋዮች ተባባሪ እንዳይሆኑ መጠየቅ ነው፡፡
እንደሚታወቀው አምባገነኑን ደርግ ለመጣል በተደረገው ትግል የትግራይ ህዝብ የከፈለው መስዋዕትነት ቀላል አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ደርግን ተክቶ ስልጣን የያዘው ሕወሓት ቃል የገባውን ዴሞክራሲ እና ነጻነት ማምጣት ከብዶታል፡፡ እንዲያውም መልሶ ከደርግ ያልተናነሰ አምባገነን ሊሆን ተቃርቧል፡፡ ይህ አልበቃ ብሎት በትግራይ ህዝብ ስም የጥቂት ግለሰቦችን ጥቅም እያካበተ ነው፡፡ በዚህም የከፋፍለህ ግዛ ስልቱ በትግራይ ህዝብ እና በሌሎቻችን መካከል የቅራኔ ግንብ እየገነባ ነው፡፡
እኔ የመሐል ሀገር ሰው ነኝ፡፡ የመሐል ሀገር ሰው በሕወሓት ከፋፍለህ ግዛ ስልት ምን ያክል እንደተሸወደ አይቻለሁ፡፡ እኔም የችግሩ ሰለባ ነኝ፡፡ የመሐል ሀገር ሰው ትግራዋይ ሁሉ የሕወሓት አባል ይመስለዋል ቢባል የተጋነነ ውሸት አይደለም፡፡ የፖለቲካ ቅሬታ ያለው የመሐል ሀገር ሰው ትግራዋዮች ፊት ችግሩን አያወራም፡፡ ሁሉም አንድ ናቸው ብሎ ይፈራል፡፡ ታዲያ በዚህ የመሐል ሀገር ሰው ሊወቀስ አይገባም፡፡ ምክንያቱም የሕወሓት ፖሮፖጋንዳ ሰለባ አድርጎታል፡፡ ሕወሓት ራሱን የትግራይ ሕዝብ ወኪል አስመስሎ ያቀርባል፡፡ በደል እና ጭቆና የበዛበት የመሐል ሀገር ሕዝብ፣ ሕወሓት የጨቆነው የትግራይ ህዝብ የጨቆነው ይመስለዋል፡፡
በዚህ ጉዳይ ከብዙ የትግራይ ልጆች ጋር ካወራሁ በኋላ ሌላ ነገር ተገለጸልኝ፡፡ ለካስ ትንሽ የማይባሉ የትግራይ ልጆቹ የመሐል ሀገር ሰው ይጠላናል ብለው ያስባሉ፡፡ የመሐል ሀገር ሰው በሕወሓት እና በትግራይ ሕዝብ መሐል ያለውን ልዩነት መረዳት ባለመቻሉ፣ የትግራይ ሰው በፍራቻ ከሕወሓት ሌላ አማራጭ እንዳይዝ አድርጎታል፡፡ ሕወሓት የጨቋኞች ቡድን ነው፡፡ አንድ ጨቋኝ ቡድን ደግሞ እየመረጠ አይበድልም፡፡ ለስልጣኑ እና ለጥቅሙ ያልተመቸውን ሁሉ ይበድላል፡፡ ስለዚህ የህወሓት ጨቋኝነት ለትግራይ ሕዝብም የሚቀር አይደለም፡፡ እኔ (የመሐል ሀገር ሰው) የትግራይ ህዝብ ከህወሓት የተባበረ የሚመስለኝ በስርዓቱ ተጠቃሚ ስለሆነ ይመስለኝ ነበር፡፡ ተሳስቻለሁ፡፡ ለካስ የእኛ ጥርጣሬ የፈጠረው ፍራቻ ነው፡፡
ከትግራይ ልጆች ጋር በግልጽ ስንነጋገር የተረዳሁት ይህንን ነው፡፡ የትግራይ ሰዎች ሕወሓትን የሚመርጡ የሚመስሉት ሌላ የሚያምኑት ባለማግኘታቸው ነው፡፡ እርግጥ ነው፣ ጭቆናም ሆነ ነጻነት ለአንዱ ተሰጥቶ ለሌላው የሚነፈግ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ሁላችንም በህብረት የምንኖርባት ሀገር እስከሆነች ድረስ፣ የትግራይ ህዝብ ነጻ ወጥቶ ሌላው ሳይወጣ አይቀርም፡፡ ሌላው እየተጨቆነ ከሆነ ደግሞ የትግራይም ህዝብ እየተጨቆነ ነው ማለት ነው፡፡ እንደተረዳሁት ግን፣ ይህንን ሐቅ የሕወሓት ፕሮፖጋንዳ ሸፍኖታል፡፡
ልክ የመሐል ሀገር ሰዎች የትግራይ ሰዎችን ሁሉ በሕወሓት አባልነትና ደጋፊነት እንደሚጠረጥሯቸውና እንደሚፈሯቸው ሁሉ፣ የትግራይ ሰዎችም የመሐል ሀገር ሰዎች ከህወሓት ጋር ቀይጠው ያጠቁናል ብለው ይጠረጥራሉ፤ ወይም ይፈራሉ፡፡ ይህ በመካከላችን ትልቅ የፍርሃት ግድግዳ ፈጥሯል፡፡ ግድግዳውን በመተማመን ማፍረስ ደግሞ የእኔና የእናንተ ኃላፊነት ነው፡፡
ጋዜጠኛ ዮናስ በላይ ሽፍቶቹ፣ ወያኔዎች እና የትግራይ ህዝብ የተለያዩ ናቸው ይላል፡፡ ወያኔዎቹ የነጻነት ታጋዮች ናቸው፡፡ ሽፍቶቹ ደግሞ በነጻነት ታጋዮቹ ስም የሚነግዱት የአሁኖቹ ጨቋኞች (ሕወሓቶች) ናቸው፡፡ ዮናስ በላይ የትግራይ ህዝብ የሽፍቶቹ ተባባሪ እንዳልሆነ የጻፈውን ከልቤ ተቀብየዋለሁ፡፡ የትግራይ ህዝብ የሽፍቶቹ ተባባሪ ካልሆነ አሁን ብዙዎቻችን እያደረግን ያለነውን የነጻነትና የዴሞክራሲ ጥረት (ትግል) ይቀላቀላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በእርግጥም ብዙ ትግራዋይ የነጻነት ታጋዮች ዛሬም አሉ፡፡ ነገር ግን ትግላቸው ከመሐል፣ ከምዕራብ፣ ከምስራቅና ደቡብ ሀገር ሰዎች ጋር መቀናጀት አልቻለም፡፡
እዚህ ጋር ከብዙ በእስር ከሚሰቃዩ የትግራይ ልጆች መሀከል አብርሃ ደስታን መጥቀስ ይኖርብኛል፡፡ አብርሃ የትም ቦታ የሚደረግ ጭቆና ይሰማኛል ብሎ የሚታገል ታጋይ፣ ምሁርና ምክንያታዊ የሐውዜን ልጅ ነው፡፡ አብርሃ ከማንም በላይ በትግራይ እና በመሐል ሀገር ሰው መካከል ያለውን አለመተማመን የሰበረ ሰው ነው፡፡ አብርሃ በኃይለኛ ብዕሩ ሕወሓትን ሲተች የተመለከቱ የመሐል ሀገር ሰዎች ‹‹ለካስ ትግራዋዮችም ህወሓትን ይቃወማሉ›› አስብሏቸዋል፡፡ ይህንን ሰው ግን ለነጻነት ታግያለሁ የሚለው ሕወሓት በመቃወሙ አስሮታል፡፡ አሁን በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ጠያቂ ተከልክሎ፣ በጥብቅ ክትትል እንደወንጀለኛ ታስሯል፡፡ በትግራይ ልጆች መስዋዕትነት ስልጣን ላይ የወጣው ሕወሓት በስልጣኑ ከመጡበት ለትግራይ ልጆችም እንደማይመለስ አብርሃ ደስታ ማሳያ ነው፡፡
ሕወሓት በትግራይ ስም እየነገደ ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብ በህወሓት ስም መልካም ገጽታው እየጎደፈ ነው፡፡ ይህ ግን መቀጠል የሌለበት ታሪክ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ፣ በተለይ የትግራይ ወጣቶች ይህንን ታሪክ ከሌላው ሕዝብ ጎን ቆመው ማስቆም አለባቸው፡፡ የትግራይ ህዝብ ለጭቆና እምቢ ባይነት ሕወሓት በሚል ስም ራሳቸውን ለሚጠሩት ሽፍቶችም መዋል አለበት፡፡ ኑ! እምቢ አልጨቆንም እንበል፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>