ከኤርሚያስ ለገሰ
በዛሬው እለት የአዲሳአባ ኢሕአዴግ ወደ 221 የሚጠጉ አመራሮችንና 4100 በላይ ሠራተኞችን ተጠያቂ ሊያደርግ እንደሆነ ተሰምቷል ። እነዚህ ሰዎች በህግ እንደሚጠየቁም ተነግሮአል።
የሕውሐት ሰዎች እንደለመዱት አዲሳአባ እንደ ኡደት የሚሽከረከረው የብልሽት አረንቋ ውስጥ የተዘፈቀችው በእነዚህ ሰዎች ምክንያት እንደሆነ ሊነግሩን ተዘጋጅተዋል። ህውሀት አይኑን ጨፍኖ፣ ልቡን አደንድኖ አገዛዙን በአዲሳአባ ላይ ጭኖ ሲያበቃ ተጠያቂነትን በንጱሀን አሊያም በጥቂት ፍርፋሪ ለቃሚዎች ላይ ለማላከክ መፈለጉ ” ለማያውቅሽ ታጠኝ!” የሚለውን ብሂል ያስታውሰናል። ህውሀት ከተማይቱን በሕገመንግሥት ፣ በአዋጅ፣ በመመሪያ እና ደንቦች ጠፍንጐ በማሰር መላወሻ ማሳጣቱ እየታወቀ የማንኪያ ማእበል መፍጠር የማይችሉ የከተማይቱን ነዋሪዎች ሜዳ ላይ ለመበተን መዘጋጀቱ የጥላቻውን ጫፍ የሚያመላክት ነው።
አዲሳአባ ብሶት የሚሰማባት ከተማ ናት። ይሄ እውነት ነው!! …በአዲሳአባ ምሬቱና ብሶቱ በፈጠረው ተቃውሞ ቢያንስ ከ250 በላይ ዜጐቿ በጥይት ተደብድበው የሚገደሉባት ከተማ ናት( በ1993 ከ42 በላይ፣ በ1997 ከ200 በላይ ንፁሐን መገደላቸውን ልብ ይሏል!)
ይህ ሁሉ መከራ በአዲሳአባ ህዝብ ላይ እየዘነበ ያለው ህውሀት ከመጀመሪያው ጀምሮ አዲሳአባን ስለሚጠላት መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ሐቅ ነው። ይህ በመረጃ ላይ የተደገፈ ነው። የትላንቶቹ በረኸኞች የዛሬዎቹ ፈላጭ ቆራጮች አዲሳአባን ለማጥፋት አሊያም የእነሱ አገዛዝ ማእከል እንድትሆን የነበራቸውን ህልም እየፈፀሙ ነው።
ያጋጣሚ ነገር ሆኖ የዛሬ 14 አመት በፊት በህውሀት አዘጋጅነት የኢትየጵያ ጥናት አለም አቀፍ ጉባኤ ላይ የመሳተፍ እድል አጋጥሞኝ ነበር። በጉባኤው ጥናታዊ ፅሁፍ ካቀረቡት ግለሰቦች አንዱ የአቶ ስብሐት የቅርብ ሰው የሆኑት ዶክተር ተከስተ ነጋሽ ነበሩ። ዶክተሩ ለጥናቱ መነሻ ካደረጉበት ዘዴዎች አንዱ የሕውሐት ባለስልጣንን ቃለ መጠይቅ ማድረግ ነበር። እናም እኝህ ግለሰብ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ የህውሀትን የጫካ ሚስጥር በኮንፍረንሱ (አቦይ ስብሐት በተገኘበት) ዘርግፈውታል። የስርአቱ ደጋፊ የሆነው ሪፓርተር በህዳር 1993 ባወጣው መፅሔት የዶክተሩን ሪፖርተር እንደወረደ አቅርቦታል። ለአብነት ያህል በገጵ 13 ያለው በከፊል እንዲህ ይነበባል፣
“… የፌደራሉ አካል የሆነችው ትግራይ መፈታት ያለባቸው በርካታ ታሪካዊ ጥያቄዎች አሉባት። ለምሣሌ ጣሊያን ኤርትራን ከመያዙ በፊት ትግራይ ከአገሪቱ ታላላቅ ክፍሎች አንዷና ከፍተኛ ሚና ያላት ነበረች። በጣልያን ቅኝ ግዛት የተነሳ ዋና ከተማዋ ወደ አዲስ አበባ በመዘዋወሩም ምክንያት ትግራይ እየተገለለችና ሚናዋ እየቀነሰ ሄደ። ከ1890 እስከ 1991(እኤአ) ትግራይ ተገልለዋል የቆየችበት ምእተ አመት ነው። ሕውሀት ይህን በመረዳት ትግራይን ወደቀድሞው ቦታዋ ለመመለስ ፣ የአጠቃላይ እንቅስቃሴው እንብርት ለማድረግ ታግሏል” በማለት ነበር በጵሁፋቸው ያሰፈሩት።
ህውሀት አዲሳአባን የጨከነባት መሰረታዊ ምክንያት ከላይ የተጠቀሰው ነው። ዛሬ አዲስአባ ለሕውሐት የመበዝበዣ ማእከላዊ እንብርት ሆናለች።ህህውሀት አዲሳአባን የመሰለች ውስብስብ ከተማን ለመምራት እውቀትም ሆነ ግንዛቤ የሌላቸው ምስለኔዎች በመመደብ ህዝቡን የመበቀል ስራ አጠናክሮ ቀጥሎበታል። እንደ ዱብ እዳ ከየቦታው እየተለቃቀሙ የሚመጡት ካድሬዎች በነዋሪው ህዝብ ላይ በመፈናጠጥ አድራጊ ፈጣሪ ሆነዋል። ካድሬዎቹ የገቡበት ዘረኝነትና ንቅዘት ስሩን እስከ ታች ተክሎ ህዝቡን ደም እምባ እያስለቀሰ ነው።
ይሁን እንጂ ጉዳዩ ” የጢስ ዶሮ ” የሚባለው ሆነና ዘመቻው ወደ መንግስት ሰራተኛው ሆነ። ቢሮክራሲው የሚፈጥረው ችግር የስርአቱ አደጋ ሆኖ ብቅ አለ።እርግጥ አሁን ባለው የሕውሐት አገዛዝ ቢሮክራሲው እንደማይለወጥ እምነቴ መሆኑን በተደጋጋሚ ገልጫለሁ። ስራ ማጓተት ፣ ባለጉዳይ ማንገላታት፣ የተቀነባበረ ሳቦታጅ መፈፀም፣ የባለሥልጣናትን ገመና ማጋለጥ፣ ሚስጥራዊ መረጃዎች አፈትልከው እንዲወጡ ማድረግ በነጳነት ትግል ውስጥ ካለ የቢሮክራሲ አባል የሚጠበቅ ነው። ይህን ማድረግ እስከቻለ ድረስ ብቻ ነው የነፃነት ትግሉ አካል መሆን የሚችለው።
እዚህ ጋር ለአዲሳአባ ህዝብ አንድ መልእክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ። ህውሀት “በመልካም አስተዳደር ዙሪያ የሞት ሽረት ትግል እያደረግን ነው” በማለት ሊነግራችሁ መፈለጉ የማይቀር ሐቅ ነው። በየወረዳው እና ሌሎች አዳራሾች እየሰበሰበ እንድታሞግሱት መጠየቁ አይቀርም። ከዚህም በተጨማሪ በሬዲዮ እና ቴሌቪዥን እየቀረባችሁ እንድታንቆለጳጵሱት ያደርጋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ በፍራቻ ተወጥሮ ተባባሪ መሆን በታሪክ ተጠያቂ ያደርጋል። የህሊና እረፍትም አይሰጥም። ህውሀት በወሰደው በዚህ እርምጃ ብቻ ከ20ሺህ በላይ የአዲስአባ ነዋሪ ጉረሮ ይዘጋል። በአስርሺህ የሚጠጉ ህጳናት እና ታዳጊዎች ከትምህርት ገበታ ይፈናቀላሉ። ሆድ ባዶ ሆኖ ወደ ትምህርት ቤት የሚኬድበት አንዳችም ሰዋዊ ምክንያት ስለሌለ።
በመሆኑም የአዲሳአባ ነዋሪ ህውሀት ካባረራቸው ወንድም እና እህቶቹ ጐን መሰለፍ አለበት። ቢሮክራሲው ስራ የሚበድለው ስርአቱን አንገታግቶ ለመጣል በትግል ላይ ስለሆነ በመረዳት መደገፍ መቻል አለበት። ወደ እምነት ተቋማት ከወትሮው ባልተለመደ ሁኔታ በመሄድ ፀሎት ማድረስ ያስፈልጋል( የአንዳንዶቹ ግምገማ አክራሪነት የሚል ታፔላ እንደተለጠፈ ሰምቻለሁ!)። በመጨረሻም ከስራ ለተባረሩ ቤተሰቦች የማቴሪያልና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል። መጪው ጊዜ አዲስ አመት እና ወደ ትምህርት ቤት መመለሻ እንደመሆኑ መጠን የህብረተሰቡ ርብርብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተፈላጊ ነው።
አንቺ! የእትብቴ መቀበሪያ አዲሳአባ ሆይ! ኢትየጵያ ነፃ ስትወጣ አንቺም ትወጫለሽ!! የነዋሪዎችሽም ትሆኛለሽ!!