የቀድሞው ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ይህቺን ዓለም ከተሰናበቱ ሦስት ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም፣ ሀገሪቱን በሙት መንፈስ የሚያምሱት ገዢዎችና ተከታዮቻቸው ደጋግመው እያነሷቸው ይገኛሉ። ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ የተረፈ ራዕይ የነበራቸውና ዓለምንም ያጎደሉ ስለመሆናቸው አብዝተው እየተናገሩላቸው ቢሆንም፣ ጥላቻ ያመቀና ዘረኝነትን በልቡ የሰነቀ እንዴት ሀገራዊ እንደምንስ አህጉራዊ ራዕይ ይኖረዋል? በመንደሩ ፍቅር የወደቀና ጽልመትን አውርሶን፣ በተግባር የዓለም ግርጌ አድርጎን የሄደ፣ እንደምንስ ሃገራዊ ሕልም ይኖረዋል ብሎ መጠየቁ፣ ከሙት ጋር ሙግት መግጠም ሳይሆን፣ በሙት መንፈስ ሀገሪቱን ለሚያምሱ መልዕክት ይሆናል።
ከግንቦት ሃያ 1983 ዓ/ም ጀምሮ፣ አንዴ በጊዜያዊነት፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በሽግግር ጊዜ ፕሬዚዳንትነት፣ በመቀጠልም በጠቅላይ ሚንስትርነት እስከ ዕለተ-ሞታቸው የኢትዮጵያን የመሪነት መንበር የጨበጡትና በቁጥር አንድነት ለሃያ አንድ ዓመታት ከሁለት ወራት የቆዩት፤ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንደገለጸልን ደግሞ ለተጨማሪ አንድ ወር በመንፈስ ከቤልጂየሙ ሴንት ሉክ ሆስፒታል መንበራቸው ላይ የቆዩት መለስ ዜናዊ፣ የኢትዮጵያ ሲባሉ ኖረው፣ በተግባር ግን የኢትዮጵያ መሪ ሳይሆኑ፣ የትግራይ ክልል ተጠሪ ሆነው ማለፋቸው ለሚያይ የተገለጠ፤ ለሚያስተውል ያልተሰወረ የመሆኑን ያህል፣ አቶ መለሰም በድርጊት ብቻ ሳይሆን፣ በቃላትም ይህንኑ ሲያራጋግጡልን ኖረው አልፈዋል።
የካቲት 11 ቀን 1984 ዓ/ም፣ እንዲሁም በመስከረም ወር 1999 ዓ/ም፣ በትግራይ-መቀሌ በአደባባይ እና በስብሰባ አዳራሽ የተናገሩትን ማስታወሱ፣ በምርጫ 2002 ዓ/ም ለትግራይ ሕዝብ ያስተላለፉትን መልዕክት መጥቀሱ፣ እንዲሁም ሕወሃትን በአስተሳሰብና በትግርኛ ተናጋሪነት ብቻ ሳይሆን፣ የትግራይ ተወላጅነትን ደም የግድ ወደሚል ደረጃ ያወረዱበትን ፍፁም ጫፍ የረገጠ ዘረኝነት ማንሳቱ፣ ለአንዳንዶች የአዋጁን በጆሮ ያህል ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ በሃብት ግንባር-ቀደም ሆናለች የሚባለውን የድንቁርና ተረት ሳያላምጡ የሚውጡና ግራ-ቀኝ ለማየት ያልታደሉ፣በጉድጓድ ውስጥ ተጥለው በጠባቧ ቀዳዳ ልክ ዓለምን የሚመለከቱ የዋሆች መኖራቸውንም ታሳቢ ማድረጉ ተገቢ ነው።
ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ፣ የኢሕአዲግነትን ካባ አጥልቆ፣ በሻዕቢያ ሜካናይዝድ ኃይል ድጋፍ፣ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ/ም አዲስ አበባን ሲቆጣጠር፣ የግዜያዊ መንግስት ፕሬዚዳንት መሆናቸው የተነገረን ባለ ራዕዩ መሪያቸው መለስ ዜናዊ፣ ስለባንዲራ ጨርቅነት አውርተው፣ የአክሱም ሐውልት ባለመብትነት የትግራይ ሕዝብ ብቻ ስለመሆኑ ተናግረው፣ ወላይታው ስለአክሱም ሐውልት ምን አገባው የሚል ምሳሌ ሲሰጡ ታዲያ የአደዋ ሰው አዲስ አበባ ቤተ-መንግስት ምን ይሰራል? የሚል ሃይ ባይ የለምና፣ ከወር በኋላ የኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት ፕሬዚዳንት መሆናቸው ተገልፆ በመንበራቸው ቀጠሉ። የሽግግሩ መንግስት ፕሬዚዳንትም ለሕወሃት 17ኛ ዓመት በዓል ወደ መቀሌ ተጓዙ። የኢትዮጵያው ፕሬዚዳንት መለስ ዜናዊ፣ የካቲት 11 ቀን 1984 ዓ/ም በሕወሃት 17ኛ ዓመት በዓል ላይ ለትግራይ ሕዝብ ፣ “እንኳን ከናንተ ተወለድኩኝ! እንኳንም የሌላ አልሆንኩኝ..” ሲሉ ከፍተኛ ጭብጨባ ተከተለ።
የፖለቲካው ስንክሳር የማይገባውና አቶ መለስ የሁሉም ነኝ የሚሉበት ወንበር ላይ መሆናቸውን ያልተረዳው ሕዝብ ማጨብጨቡ ተፈጥሯዊ ቢሆንም፣ የሕወሃት መሪዎችም እጃቸውን ማውለብለባቸው ህመም ካልሆነ፣ ዘረኝነት መሆኑ ግን ግልጽ ነው። ንግግሩን ያልሰሙ እንዲሰሙም በአማርኛ ቋንቋ ተተርጉሞ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጋዜጣ ላይ ታተመ፤ የኢትዮጵያው ፕሬዚዳንት እንኳን ከትግራይ ተወለድኩኝ ያሉበት በሌላ እነጋገር፣ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ሲዳማ፣ ወላይታ፣ ወዘተ ባለመሆናቸው መደሰታቸውን የገለጹበት “ታሪካዊ” ንግግር፣ ሞራልና የሕግ የበላይነት ባለበት ከሥልጣን የሚያሽር፣ የሚያሳፍርና የሚያስወቅስ ቢሆንም፣ አቶ መለስ ግን ከነ ሙሉ ስልጣናቸው ስያሜ ቀይረው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መመረጣቸውን፣ ነሐሴ 17 ቀን 1987 ዓ/ም ፓርላማው ነገረን። በፓርላማው 178 ወንበር የያዙት ኦሕዴዶች፣ 136 ወንበር የታደላቸው ብአዴኖች፣ እንዲሁም 123ቱ የተለቀቀላቸው ደኢሕዴኖች – እንኳን ከትግሬ ተወለድኩ ያሉትን መለስ ዜናዊን በሙሉ ድምጽ ሲመርጡ ራሳቸውን እየሰደቡ መሆናቸው ግልጽ ቢሆንም፣ ጠመንጃውን የያዘውና ቀለብ የሚሰፍርላቸው ሕወሃት በመሆኑ፣ እጅ አውጥቶ ራስን ከመዝለፍ ባሻገር፣ እየተከፈላቸው በመልዕክተኝነት ሲገድሉና ሲያስገድሉ መኖራቸውም እውነት ነው።የቀድሞው ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም እየተሸነፉ ሲሄዱና ሥልጣን እየከዳቸው፣ ሁሉ ነገር ከእጃቸው እየወጣ በነበረበት የ1983 ዓ/ም መጀመሪያ ፣ በደብረብርሃን ከተማ ተገኝተው፣ የሰሜን ሸዋ ሕዝብ ሲዘምት እንጂ ሲዘመትበት አላየንም በማለት የተናገሩትን ሲተቹና ሲያብጠለጥሉ የሰማናቸው የሕወሃት ሰዎችና ደጋፊዎቻቸው፣ የሌላውን ኃላፊነት የጎደለው ንግግር ለማውገዝ ደጋግመው ሲጽፉና ሲሰብኩ እንዳልሰማናቸው፣ ኃላፊነት የጎደለው ብቻ ሳይሆን ከመሪ የማይጠበቅ ዘረኛ ንግግር ከነርሱ ሰው ሲመጣ ባለራዕይ እያሉ ያለሃፍረት እያንቆለጳጵሱ ቀጥለዋል።
አቶ መለስ ዜናዊ ሥልጣን በያዙ በወራት ጊዜ ውስጥ መቀሌ ተገኝተው የተናገሩትን ኃላፊነት የጎደለው ንግግር፣ አንዳንዶች የሥልጣን ሙቀት የፈጠረው ስካር ስለሚሆን፣ ሲውል-ሲያድር ይሰክናሉ በሚል ዕድል እንስጣቸው በማለት ነገሩን በረጋ ሁኔታ ለማየት የሞከሩ ቢሆንም፣ አቶ መለስ በሥልጣን ሙቀት ሳይሆን፣ የሚያምኑበትን አስበው እንደተናገሩ ለአሥመራው መፅሔት ሕውየት ማረጋገጫ የሰጡት በጥቂት ዓመታት ልዩነት ነበር። በኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ስር የሚታተመው ሕውየት የትግርኛ መፅሔት፣ስበኢትዮጵያ አቆጣጠር 1989 ዓ/ም በምዕራባዊያኑ በ1997 ከአቶ መለስ ጋር ባደረገው ቃለ-ምልልስ “አንተ የኢትዮጵያ መሪ ሆነህ እንዴት እንኳን ከትግራይ ተወለድኩ ትላለህ፤ ይህ አባባል ሌሎችን አያስከፋም ወይ?” በሚል ላነሳባቸው ጥያቄ፣ በአባባላቸው እንደማይፀፀቱ፣ የተናገሩትም ተገቢ መሆኑን ማረጋጋጫ ሰጡ። በእሳት ተፈትኖ ወርቅነትን ካስመሰከረ ሕዝብ መወለዴ ያኮራኛል ብል ምን ነውር አለው? ሲሉም መልሰው ጠየቁ። “በእሳት ተፈትኖ፣ ጨርቅ ሳይሆን ወርቅ የሆነ” በማለትም፣ በርሳቸው አባባልና አስተሳሰብ በእሳት ያልተፈተኑትን ወይም ተፈትነው ጨርቅ የሆኑትን እየቀጠቀጡ፣ እያሰሩና እየገደሉ፣ እያሰደዱና እየዘረፉ ቀጠሉ።
በየካቲት ወር 1984 ዓ/ም መቀሌ ላይ የተናገሩት ሥልጣን በፈጠረው ስካር ነው በማለት ሰለርሳቸው ሆነው የተጨነቁት፣ ከአምስት ዓመታት በኋላ አቶ መለስ የኢትዮጵያን ሕዝብ በወርቅና በጨርቅ ፈርጀው ራሳቸውን የወርቁ አካል መሆናቸውን ሲያውጁ፣ የሥልጣን ስካር “ሃንጎቨር” ወይም ያደረ ስካር ከእርሳቸው ጋር አብሮ አምስት ዓመታት ስለዘለቀ ነው በማለት ይሉኝታ-አልባ ሙግት ሲያነሱ ባናይም፣ ሲቆዩ ጥላቻቸው እየረከሰ፣ ባይተዋርነቱ እየቀነሰ ሁሉንም የራሴ የሚል ስሜት የድርባቸው ይሆናል በሚል ተስፋ ያደረጉ መኖራቸው ግን እውነት ነው። ሆኖም ተስፋቸው በአቶ መለስ ዘረኛ አመራር እየሟሸሸ፣ የይሉኝታን ገደብ ባለፈው የሥልጣን፣ የዘረፋና የስግብግብነት ጉዞ እየተሟጠጠ ቢሄድም፣ በኢትዮጵያ ምድር፣ በኢትዮጵያውያን የጋራ ሃብትና ሲሣይ ዓለሙን እየቀጨ፣ ሁለት አሥርተ-ዓመታት በሥልጣን ላይ የቆየ መሪ፣ በ2000 ዓ/ም የትግራይ ወጣቶችን ለብቻ ሰብስቦ የትግሬነት የአደራ ቃል ኪዳን ይጭንባቸዋል ብሎ የሚጠብቅ፣ እርሱ እንደነርሱ ዘረኝነቱ ወደ ሕመም የተቀየረበት፣ እልያም ጥልቅ የፖለቲካ ልሂቅ መሆን ይኖርበታል።
የኢትዮጵያን ማዕከላዊ ሥልጣን በተቆጣጠሩ በ10ኛው ወር መቀሌ ከተማ ላይ እንኳን ከናንተ ተወለድኩኝ በማለት ብዙዎችን ያሳዘነና ያሳቀቀ ንግግር ያደረጉት መለስ ዜናዊ፣ በሥልጣናቸው ላይ 15 ዓመታት ያህል ተደላድለው ቆይተውም፣ ሕመሙ አብሯቸው እንደቀጠለ መስከረም 9 ቀን 1999 ዓ/ም መቀሌ ላይ ከድርጊት ባሻገር በቃላትም አረጋገጡት፤ የተግራይ ወጣቶችን ሰብስበው የሚከተለውን መልዕክት አስተላለፉ። “ወደዳችሁም ጠላችሁም የአያቶቻችሁን ዓላማ ትረከባላችሁ፤ ጥያቄው ከአያቶቻችሁ ይበልጥ ትሰራላችሁ ወይ? የሚለው ነው፤ የትግራይ ተስፋ ባለፉት ላይ ሳይሆን በእናንተ እጅ ነው።” በማለትም አሳሰቡ።
በቮይስ ኦፍ አሜሪካ የአማርኛው አገልግሎት በወቅቱ የተዘገበው ይህ የአቶ መለስ ዜናዊ ንግግር፣ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያዊ መሪ የግድ እንደሚላትና የዘረኝነት ልክፍት በፍቅር፣ በሃብትና በሥልጣን እንደማይረክስ ከማመልከቱ ባሻገር፣ የጥላቻ ቫይረስ የተሸከሙ ብዙ ሺህዎች እየተቀፈቀፉ ለመሆናቸው ፣ ማኀበራዊ መድረኮችን ዛሬ በጥላቻ የወረሩት የርሳቸው ደቀ-መዛምርት በቂ ማሳያ ናቸው።እነዚህ ከአጥማቂው በላይ ጥላቻ ደማቸው ውስጥ የሚንተከተከው ወጣቶች፣ ባለራዕይ የሚሏቸው መሪያቸው፣ የጥላቻ እና የዘረኝነት ማጣቀሻ ወይንም ሪፈረንስ ሆነው በኢትዮጵያ የትምህርት ካሪኩለም ውስጥ በምሳሌነት ሲጠቀሱ፣ እነርሱ የድርጊት ምሳሌ ሆነው ጭለማ ውስጥ የነበሩበትን የጥላቻ ዘመን በፍቅር ሲናዘዙም እናያለን፤ እንሰማለን!አቶ መለስ ይህችን ምድር ሊሰናበቱ ሁሉት ዓመት በቀራቸው ወቅት በተደረገው የ2002 ዓ/ም ምርጫ “ትግራይ ውስጥ ምንም አይነት ልዩነት እንዳይኖር ወይንም ስንጥቅ እንዳይታይ ጥሪ ማድረጋቸውን የአንድ ወቅት የርሳቸው የትግል አጋር አቶ ገብሩ አሥራት በመስከረም 2005 ዓ/ም በታተመው ሎሚ መፅሔት ላይ የተናገሩትንም ማስታወሱ፣ ጥላቻው ወይንም ሕመሙ እስከ መቃብር አብሮ እንደዘለቀ ማሳያ ነው።
የሕወሃቶች ባለ ራዕይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን በክፋት፣ በዘረኝነትና በአድላዊነት የሚያስታውሳቸው፣ በርግጥም በንግግር ችሎታቸውም የማይረሳቸው፣ በአደባባይ ዘለፋቸውና ፀያፍ ቃላታቸውም የሚታሰቡት መለስ ዜናዊ፣ ሥልጣንና ሃብት፣ ወደ አንድ አካባቢ ሲገፉ መኖራቸውም የአደባባይ ምስጢር ሆኖ ቀጥሏል።በሥልጣንና በሃብት ጋራ ላይ በሰፊው የተዘረጉት የአንድ አካባቢ ሰዎች የመሆናቸውን ያህል፣ በስማቸው የሚነገድባቸው፣ከነጉስቁልናቸው የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች መኖራቸውም የማይካድ እውነት ነው። የሀገሪቱን ወታደራዊና የጸጥታ መዋቅር፣ እንዲሁም የኢኮኖሚ አውታር፣ መወሰኛውን የፖለቲካ ጡንቻ በአንድ ሰፈር ሰዎች እጅ አስገብተው፣ ከየጎጡ የተመረጡ የሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ለምልክት አስቀምጠው ኢትዮጵያን ሲቀጠቅጡ፣ ሲዘርፉና ሲያስዘርፉ ያለፉት መለስ ዜናዊ፣ ትግራይን የኢንዱስትሪ ማዕከል የማድረግ ህልማቸውን መልክ- መልክ አስይዘው ማለፋቸውን ባለቤታቸው በአደባባይ በድምጽና በምስል መስክረዋል።
ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለምንም መያዣ አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር አስወስደውና ከነወለዱ የተበለሸ ብድር በሚል አንዲሠረዝ አርገው፣ የሃገሪቱ የልማት ባንክም የሕወሃት ካዝና እንዲሆን መንገዱን በውጉ ጠርገው፣ የሕወሃቱን ኢሣይያስ ባሕረን በቁንጮ አስቀምጠው ሄደዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክንም በነ አቶ ስየ ቤተሰብ ሥር አቆይተው፣ ወደነ አቶ ዓባይ ፀሐዬ ቤተሰብ አሸጋግረው፣ ባለራዕዩ መሪያቸው ተሰናብተዋል። በሕወሃቱ ኤፈርት እንዲሁም በግለሰቦች ስም የሚደረገው ዘረፋ ሳይበቃ፣ የሃገሪቱን የመከላከያ ተቋም በንግድና ኮንስትራክሽን ዘርፍ እንዲሰማራ መንገዱን ጠርገው የሕወሃት ሰዎችን አደላድለዋል። የመከላከያ ሚኒስቴር ንግድ ውስጥ መግባቱ በዐይን የሚታይና በግልጽ የተነገረ ቢሆንም፣ ኦዲት እንዳይደረግም መንገዶች ተጠርገዋል፡፡ ይህ የመከላከያ ተቋም አማራ ወይንም ኦሮምያ ወይንም ሶማሊያ ወይንም ደቡብ ውስጥ አንድ የመርፌ ሱቅ ሳይከፍት፣ ትግራይ ውስጥ በርካታ ፋብሪካዎች ተክሏል። የፓወር ኢንጂን ኤሌክትሪክ ዎርክሾፕ፣ የኧርዝ ሙቪንግ ማሽን መገጣጠሚያ እንዲሁም የፀረ-ተባይ ኬሚካል ፋብሪካ ጨምሮበ አጠቃላይ ወደ ሰባት ፋብሪካዎችን በመቀሌ የገነባ ሲሆን፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች ፋብሪካ በማይጨው፣ ውቅሮ፣ አዲግራት፣ አክሱም፣ ሽሬ ወዘተ.. የገነባ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ከአንድ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ አስራ ሰባት ፕሮጀክቶችን በትግራይ ክልል በመከናወን ላይ መሆኑንም ከክልሉ ኢንቬስትመንት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያስረዳል። ይህም የውጭ ባለሃብቶች በክልሉ የመለዋወጫ ችግር እንዳይገጥማቸው መሆኑ ተመልክቷል። ቬሎሲቲ የተባለ የተባበሩት አረብ ኢምሬት አንዲሁም ቢ. ዲ. ኤል. የተባለ የባንግላዴሽ ኩባንያዎች ወዘተ.. በጨርቃ-ጨርቅ ዘርፍ እንዲሰማሩ ዕድሉ በመመቻቸቱ፣ ትግራይን የኢንዱስትሪ ማዕከል የማድረጉ ተግባራዊ ጉዞ ቀጥሏል።
አቶ መለስ ዜናዊ በቃልም ፣ በድርጊትም ለተነሱበት ዓላማ ቆመው፣ በታገተው ሕዝብና ክልሎች ኪሣራ ዘረኛ ፖሊሲ ሲቀርጹ፣ ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ የነበሩ፣ በጥቅሉ ኢትዮጵያዊ አጀንዳ ሳይኖራቸው፣ በተግባርም ኢትዮጵያዊ መሪ ሳይሆኑ ያለፉ በመሆናቸው በጥቅል ለኢትዮጵያውያን እንኳን ባለራዕይ፣ በመሪነት መዝገብ ውስጥ በወጉ ያልተጻፉ መሆናቸውም ሊሰመርበት ይገባል።
አቶ መለስ ዜናዊ ከሰላሣ ቢሊዮን ዶላር በለይ የውጭ ብድር ጭነውብን፣ ከአርባ ቢሊዮን ዶላር በላይ ዕርዳታ እየጎረፈ፣ በዓለም ላይ ከኒጀር ቀጥሎ ሁለተኛ ደሃ አድርግወን የሄዱ፣ ከቴክኖሎጂ ነጥለውን፣ከመንግስት አልባዋ ሶማሊያ ጋር አስተካክለውን ያለፉ፣ በቃላት እያፋፉን፣ በተግባር አቀጭጨው፣ በድርጊት አድቅቀው፣ በብልጭልጭ ቅብ ጉስቁልናችንን ሸፍነው፣ ደሃ አበራክተው፣ ድህነትን አስታቅፈውን የሄዱ የጭለማ ዘመን ተምሳሌት ናቸው። የሃገሪቱን የትምህርት ሥርዓት የገደሉ፣ የሥልጣንን ክብርና ዋጋ ለሞራል አልባዎችና ዕውቀት ላይ ለሸፈቱ መንገደኞች ስጥተው ልጆቻችንን ተምሳሌት የነሱ፣ ከዛሬ አልፈው ለነገ ዕዳ የተዉብን፣ የኢትዮጵያን ሃያ አምስት ዓመታት በከንቱ ያባከኑና ከነገም ተጨማሪ ዓመታትን ያበላሹ፣ ታሪክ በዕኩይ ድርጊታቸው ሲያስታውሳቸው የሚኖር፣ ለስደትና ለጥቃት ያጋለጡን ፣ የገደሉንና ያስራቡን ፣ የሰው ልጅን የክፋት መጠን ያየንባቸው ፣ የዘረኝነት አክሊል የደፉና ክፋትን የሰነቁ በታሪካችን በዕኩይ ድርጊታቸው ሲታወሱ የሚኖሩ ናቸው።
አቶ መለስ ዜናዊ ላይመለሱ ከሄዱ ከሦስት ዓመታት በኋላ የማነሳቸው፣ በሙት ወቃሽነት መንፈስ ሳይሆን፣ በሙት መንፈስ የሚመሩት ተከታዮቻቸው ካረፉም ከሦስት ዓመታት በኋላም ሥጋ ለባሽነታቸውን እንድንጠራጠር አብዝተው ሲለፉ፣ እውነቱን በመፈንጠቅ በዘረኝነት የተለወሱ፣ በአካባቢ ልጅነት የተበከሉ በድን ሃሳቦች፣ ከጠባቧ ኩሬ ከዘረኞቹ ማኀበር ባሻገር ቦታ እንደሌለው ለማስገንዘብ ጭምር ነው። እነዚህ የርሳቸው አምላኪዎች ህሊናቸው የለበሰው የዘረኝነት ሞራ የሚገፈፈው በሃሳብ ልዕልና ሳይሆን፣ በኃይል ልዕልና ወይንም በጉልበት ብቻ መሆኑም ሊሰመርበት ይገባል። ይህንን በተገቢው ተገንዝበው፣ ግራና ቀኙን አንብበው፣ ግላዊና ቤተሰባዊ ምቾታቸውን ጥለው በረሃ የወረዱት የነፃነት አርበኞች፣ በለጋ ዕድሜያቸው ፍትህና ነፃነትን ሽተው መሳሪያ ያነሱ ጉብሎች፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን አክብሮታቸውን የማይነፍጓቸው፣ በዘረኝነት፣ በአፈናና በድንቁርና ላይ የተነሱ፣ ፍትህ፣ ነፃነት፣ እኩልነትና ዴሞክራሲን ያነገቡ፣ በጨለማው ላይ ብርሃን የሚረጩ ተስፋዎቻችን ናቸው።፡ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያዊ መሪ የምታገኝበት፣ በቀለም ላይ የሸፈቱ፣ በገንዘብ የድንቁርና ቆብ የጫኑ በድንቁርና ሃገር የሚያምሱበት፣ ዘረኞች ኢትዮጵያን የሚያተረማምሱበት ሁኔታም ያበቃል። ኢትዮጵያችን ትነሳለች፤ ከሀገራት ግርጌም ትወጣለች።
ከኢሳት የሃሳብ መንገድ ወደ ጽሁፍ የተመለሰ