መነአልወድም ነበረ እርግማን ጨርሶ፣
ግን ላንተ ወዳጄ ሆዴ በጣም ጢሶ ፣
ዛሬስ ተራገምኩኝ ይሁን ብዬ ጮህኩኝ ይኸው በገሃድ፣
የወሬው ፈጣሪ ሰብቀኛው አመድ ።
ዮሐንስ አድማሱ
ኀብርና ምርምር /1966/
“ . . . የ13 ወራት የፀሐይ ብርሃን (13 Months of Sunshine) በሚለው ፖስተር ላይ ቡና ስታፈላ የምናውቃት ቆንጆ ወ/ሮ ውቢት አመንሲሳ ከባሕል ምኒስቴር ወደ ቱሪዝም ኮምሽን በፍስሃ ገዳ ልዩ ትዕዛዝ ተዛወረች። . . . “
የደርግ ዘመን የአራዳ ሹክሹክታ !
በአሁኑ ወቅት ብዙ ጽሁፎች በመፅሐፍት አለያም በድረ ገጽ ለንባብ ሲቀርቡ ይታያሉ። ከነዚህም መሐከል ብዙዎቹ ታሪክ ቀመስ ናቸው። በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ፣ በኢሕአፓ፣ በደርግና ኢሠፓ ብሎም በቀድሞው ሠራዊት፣ በወያኔና ሻዕብያ ላይ የሚያተኩሩ ይበዙባቸዋል። እነዚህ የዘመኑ ጦማሮች የሰነቁት ታሪክ የሚያጠነጥነው በግለሰብ፣ በድርጅት ታሪኮች፣ በአንድ ወቅት የተፈጸሙ ክስተቶችና እንቅስቃሴዎች ላይ ነው። ጽሁፎቹ በተለይ አዲሱ ትውልድ ስለሃገሩ እንዲያውቅ “እንደሚረዱ“ አያጠራጥርም። እንደሚረዱ የሚለውን በትምህርተ ጥቅስ ያስቀመጥኩት አንዳንዶቹ ለማስተማር ሳይሆን ለማደናገር የተዘጋጁ እንደሆኑ ከሚያቀነቅኗቸው የተፋለሱ ጭብጦች በግልፅ መረዳት ስለሚቻል ነው።
ይህን ለማለት የደፈርኩት አንዳንዶቹን ጽሁፎችን በሃቅ ሚዛን እየሰፈርን ስንመለከታቸው በውስጣቸው እንደዋዛ ሊታለፉ የማይገቡ የገዘፉ ስህተቶችን ደጉሰው እናገኛለን። ማንኛውንም ታሪክ-ነክም ሆነ ፖለቲካዊ ይዘት ያለውን ጽሁፍ ለሕዝብ ንባብ የሚያቀርቡ ግለሰቦች ስለሚያነሷቸው ጭብጦች ትክክለኛ መረጃ የመስጠትና ለታሪኩ ዋቢ ሆኖ የመቅረብ ሃላፊነት ብቻ ሳይሆን የትረካ ሚዛናዊነቱንም ጭምር መጠበቅ እንዳለባቸው ሊያስተውሉ በተገባ ነበር። ነገር ግን ይህ ሳይሆን ቀርቶ በተቃራኒው ከእውነት ያፈነገጡ በርካታ ትረካዎች በሃገራችን ስነ-ጽሁፍ ዘርፍ እንዳሻቸው ሲናኙ እየተስተዋለ ነው።
በአንድ ጽሁፍ ውስጥ የሚተላለፈው መልዕክት ሃላፊነት የጎደለው ከሆነ ታሪክን በማዛባት ረገድ የሚያስከትለውን ጉዳት አስቀድሞ ማጤን አያዳግትም። የመረጃና ኢንፎርሜሽንን ደህንነት/ትክክለኝነት የመጠበቅ ሃላፊነት ደግሞ ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ የዜግነትና የሙያ ሃላፊነት ጭምር ነው የሚሆነው። ይህም አሳሳቢ የሚሆነው ጽሁፎቹ የማታ ማታ በታሪክነት እየተዘገቡ ነገ ህያው ምስክር ሆነው እንደሚቀጥሉ ስለምንረዳ ነው። ምናልባት ታሪክ ከዚህ በላይ የተሻለ የራሱ አጻጻፍ ዘዬ ሊኖረው ይቻላል። ቢሆንም ግን ዛሬ እነዚህ በየቦታው በመጻሐፍት ስም የሚወጡት መደብሎች ነገ ለትናንትናውም ሆነ ለዛሬው ታሪካችን እንደ ትክክለኛ የመረጃ ምንጭ ተወስደው መጠቀሳቸው አይቀሬ ነው። ሃላፊነት የጎደላቸው ጻሐፊዎች እስካሉ ድረስ ዛሬም ሆነ ነገ ሚዛኑን ያጋደለ አለያም እውነትን ያደበዘዘ ጽሁፍ ማንበባችን አይቀሬ ነው። ለእያንዳንዱ ጽሁፍ ግድፈት አግባብ ያለው የማረሚያ ምላሽ በወቅቱ መስጠት ተገቢ ቢሆንም ቅሉ ዘወትር ይህን ማድረግ ግን አይቻልም።
ለአብነት አንዳንድ ጭብጦችን እናንሳ። በአንድ ወቅት ባንድ እንቅስቃሴ ላይ የተሳተፉ እንኳን ስለ ሁኔታው የተዘበራረቀ መረጃ ነው የሚያቀርቡት። እንቅስቃሴው የተደረገበት ቦታ፣ ሰዓት፣ የነበሩ ግለሰቦች በተተዘበራረቀ ሁኔታ ተጽፈው ይገኛሉ። ለምሳሌ ዘነበ ፈለቀ በጻፈው “ነበር“ በሚለው መጽሐፍ ላይ (ገጽ 17 – 26) የደርግ አባላት 109 መሆናቸውን ነው የዘረዘሩት። በሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ “እኛና አብዮቱ“ መጽሐፍ ላይ (ገጽ 68 – 74 ) የደርግ አባላት ቁጥር 108 ነው። በዚህ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ ባለው ኮሚቴ ውስጥ የተረሳ ወይም የተጨመረ ሰው አለ ማለት ነው። የአንድ ሰው መጨመር ወይም መቅረት ቀላል ሊመስል ይችላል። እውነታው ግን ከባድ ስህተት ነው። አለአግባብ የተጨመረ ካለ ቢያንስ ለ60ዎቹ የቀዳማዊ ሃይለሥላሴ መንግሥት ባለስልጣናት ግድያ በታሪክ ተጠያቂ ሊሆን ነው። በስህተት ካልተጨመረ ደግሞ በዚህ ግዙፍ ታሪክ ላይ ያደረገው አስተዋጽዖ ተረሳ ማለት ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ የቀድሞውን የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት አስመልክቶ አንዴ እየተጋነነ፣ ሌላ ጊዜ እየተኮነነ፣ ከከፍተኛና ዝቅተኛ መኮንኖች እስከ ባለሌላ ማዕረጎች ድረስ የሚጻፉትን የወቅቱን መድብሎች ካስተዋልን፣ እርስ በራሳቸው የሚቃረኑ አያሌ የአፃፃፍ ግድፈቶች ያሉባቸው ከመሆናቸውም ባሻገር የታሪክ መዛባት የሚታይባቸውም ጭምር እንደሆኑ እንገነዘባለን። የማዕረግ እድገት የከለከላቸውን አጋነው እየኮነኑ በአንፃሩ ደግሞ ለእነርሱ ቀረቤታ አለያም ጠቀሜታ ያለውን አላግባብ ሲክቡ ይስተዋላሉ። እንዲህ ያለው ሌጣና የተዛባ፣ ሚዛን የሌለው አፃፃፍ፣ የግል ጥላቻንና ቂምን ማወጃ፣ መድብል ከመሆን ባለፈ እውነት በማቋት ረገድ የሚፈይደው አንዳች ነገር አይኖረውም።
በቀበሮ ጉድጓድ ታፍኖና ለዓመታት ደሙንና ሕይወቱን እየገበረ ለሃገር ሉዓላዊነት አብሮ ሲወድቅ ሲዋደቅ የኖረን ሠራዊት ታሪክ ከግል ጥቅም አንፃር እየመነዘሩ ዋጋ ማሳጣት የሠራዊቱን ገድል ማዛባት ነው የሚሆነው። የዚህ ዓይነቱ ቅኝት ዞሮ ዞሮ በስተመጨረሻው እውነቱ ሲጋለጥ ራስን የሚያስገምትና ዋጋ የሚያሳጣ ሊሆን ስለሚችል አስቀድሞ ሊጤንበት ይገባል። ሥራ ሠራተኛውን አክባሪ እንደመሆኑ መጠን፣ የሰው ልጅ እሱ ስለራሱ ከሚደረድረው ስንክሳር ይልቅ ሥራው ራሱ ሲናገርለት በሁሉም ዘንድ ይበልጥ ይከበራል። ከዚህ ውጭ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘትና ራስን ለማስከበር ሲባል የግል ገድል ክበው እየፃፉ በማስነበብ የአንድን ታሪክን ፍሰት ለማዛባት መሞከር ጸያፍ ተግባር ይመስለኛል።
የቀድሞውን የኢትዮጵያን ተማሪዎች እንቅስቃሴንም በሚመለከት ደግሞ ሁኔታው የከፋ ሆኖ እናየዋለን። የራስን ወንጀል ለመሸፈን ሲባል የኋሊት ተጉዞ ያንን በቆራጦች የተገነባን ትግል ጥላሸት መቀባት ሃላፊነት የጎደለው ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ ስህተትም ጭምር ነው የሚሆነው። የኢሕአፓን ታሪክ በሚመለከት ሁኔታው ከዚህ የተሻለ ሆኖ አይታይም። አንዳንድ የቀድሞ አባላት በዘንድሮ መነጽር የጥንቱን ታሪክ ለመተንተን የሚያደርጉት ጥረት ውሃ የማይቋጥር ነው። ችግሩ ግን እውነተኛውን የድርጅቱን ታሪክ ለማግኘት በሕቡዕ የሚንቀሳቀስ ስለነበር አስቸጋሪ ነው። ቢሆንም ግን በአንኳር ጥያቄዎች ላይ አሁን በሕይወት የሚገኙ የቀድሞ አመራር አባላት መልስ የሚሆን በመተባበር መጻፍ ይችሉ ነበር። ግን ለዛ አልታደልንም።
በአሁኑ ወቅት በሕይወት የሚገኙ ኢሕአፓ አመራር አባላትም ቢሆኑ እውነተኛውን ታሪክ ጽፎ ለሕዝብ ንባብ፣ ለታሪክ ማጣቀሻ እንደማብቃት ይባስ ብለው የግል መቆራቆሻ መድረክ ማድረጋቸው ሌላው አሳፋሪ ተግባር ነው። ይልቁንም ለሚቀጥለው ትውልድ ትምህርት ይሆን ዘንድ እውነትን በእውነትነቱ፣ ድክመትን በማስተማሪያነቱ፣ ጥንካሬን ደግሞ በአብነቱ ወስዶ በሃቅ ለሕዝብማሳየትና ለቀጣዩ ትውልድ የትግል ማመላከቻ በማድረግ ሌላ ታሪካዊ ስህተት እንዳይደገምና ቀጣዩ ትውልድ የማይገባ የመከራ አዙሪት ውስጥ እንዳይዘፈቅ ታሪካዊና ሕዝባዊ ሃላፊነትን መወጣት ነው የሚበጀዉ። ከዚህ ውጭ “ከእኛ ወዲያ ፉጨት . . . “ በሚል፣ ሌሎችም እንዳይጽፉ ዝም ለማሰኘት የሚደረገው ግትር አስተሳሰብና ጭፍን ትችት በድርጅቱና በቀደምት ታጋዮቹ ፅኑ የመስዋዕትነት ትግል ታሪክ ላይ ሸፍጥ የመስራት ያህል ነው።
እስቲ ለእማኝ ያህል ይህ ከላይ የጠቀስኩትን በሚመለከት አንዳንድ ሁኔታዎችን አብረን እንመልከት።
1ኛ . በአንድ ርዕስ ላይ አንዱ የካበውን ሊላው ሲንደው መታየት የተለመደ ሆኗል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው በአለፉት ሳምንታት አቶ አሰፋ ጫቦ በተለያዩ ድረ ገፆች ላይ “ኦ አዳም አንተ !!“ በሚል ርዕስ ስለ ደርግ ባለስልጣኑ ሻለቃ ፍስሃ ገዳ ያስነበቡንን ጽሁፍና በወቅቱ የኢሠፓ አባል የነበሩት ዶክተር አያሌው መርጊያው ጎበና “እናት ሀገር ! የኢሕአፓ እንቆቅልሽ“ በሚል መድብላቸው ያሰፈሩትን ጽሁፍ እንመለክት።
አቶ አሰፋ ጫቦ በጽሑፋቸዉ ጓደኛቸው የነበሩትን የደርግ ባለስልጣን ሻለቃ ፍሰሃ ገዳን “ምርጥ ተተኪ የማይገኝላቸው ዜጋ“ አድርገዉ ሲስሏቸው፣ በተቃራኒ ገጽታው በወቅቱ አብረው ይሠሩ የነበሩት ዶክተር አያሌው መርጊያ ደግሞ የመጥፎ ባህል አቀንቃኝ እንደነበሩ ይገልጻሉ። ስለሆነም ሻለቃ ፍስሃ ገዳ በዶክተሩ ድርሰት የአሸሼ ገዳሜ አቀነባባሪ ፣ የዝሙትና የዋልጌነት፣ የስርቆትና የብኩንነት፣ እንዲሁም የዝርፊያና የጦፈ የጥቁር ገበያ ንግድ አስተባባሪ አድርገው አቅርበዋቸዋል።
አቶ አሰፋ ጫቦ ፡ –
“አንድ አራት አመት ያክል ደርግ ጽሕፈት ቤት ቢሮ ነበርንና ፍስሐ ገዳን በየቀኑም ባይሆን ብዙ ጊዜ የማግኘት እድል ነበረኝ። ብዙም የምንነጋገረው አልነበረም። አስፈላጊ በሆኑ ነጥቦች ብቻ ካልሆነ በስተቀረ። የቀረውን ሳንነጋር የምንግባባ (Given) ይመስለኛል። የታውቀ ነው በሚሉት መልክ። ከማስታውቂያ ኮምቲ በኋላ የፕሬዚዳንቱ፤የመንግስቱ ኃይለ ማርያም፣ የፕሮቶኮል ሹም ሆነ። ይህ የሚሰማማው ስራ መሆኑን የነገርኩት ይመስለኛል። የፕሮቶኮል ሹም ስራ አሻማ ነው ብዬ ስለማምን።ከዚያ እኔ ማእከላዊ ከወርድኩ በኋላ የሆቴልና ቱሪዝም ኮሚሽነር ሆኖ መሾሙን ሰማሁ። ዋናውን የአሻም ስራ አገኘ አልኩኝ በልቤ። በሆቴሊና ቱሪዝም ዘርፍ ከመስራቹ አቶ ኃብተ ስላሴ ታፈሰ ጋር የሚነጻጸር ምናልባትም ሊበልጥ የሚችል ለውጥ ያመጣ ፍስሽ ገዳ መሆኑን ዛሬ ወዳጅም ጠላትም አምኖ ተቀብሎ በዚያ ላይ ተንተርሶ ወደሚቀጡለት ደርጃ ያደረሱት ይመስለኛል። ወዳጅም ጠላትም ከማለት ሁሉም ተቀብሎ ብል የሚሻል ይመስለናኛል። ፍስሀ ጠላት ያለው ሊኖረውም የሚችል ስለማይመስለኝ ነው።
http://www.zehabesha.com/amharic/archives/46038
የዶክተር አያሌውን ደግሞ ምንም ሳልቀንስ ሳልጨምር ከመጽሀፉ ገጽ 33 ላይ የሰፈረውን አንድ አንቀፅ እነሆ፡
“በደርግ ጊዜ በተለይም በአስረሽ ምችው ሻምበል ፍስሐ ገዳ ዘመን ቱሪዝምና ሆቴሎች ኮሚሽን የስካር የዝሙት፣ የዋልጌነት፣ ስርቆት፣ የብኩንነት ፣ የዝርፊያ ፣ የጦፈ የጥቁር ዶላር ንግድ ማካሄጃ ዋሻና ግቢ ነበር። ወጣት ሴቶቻችንን ለአረቦች ዶላር ማግኛ እንደሸቀጥ ለመጠቀም ማስተባበርና ማስተናገድ ሙያው የሚጠይቀው ከፍተኛ የችሎታ መመዘኛ ነበር። ሻምበል ፍሰሐ ገዳ ወይም የደርግ ባለስልጣናትንና ወዳጆቻቸውን ላንጋኖ ሶደሬና ወንዶ ገነት ለመዝናናት ሲሄዱ በተቀናጀ በተደራጀ መልክ ወጣትና ውብ የሴት
አስተናጋጆችን ለአዝናኝነት እያስተባበሩ በመላክ ሽር ጉድ ማለት ሌላው ከፍተኛ የብቃትና የችሎታ መመዘኛ ነበር ። ይህን ተግባራት የሚያከናውኑና የሚያስተባብሩ ነበር ታማኝ ትጉ ታታሪ አዋቂ ባለሙያ የሚያስቆጥረው።“
እዚህ ላይ ማንን እንመን ? አቶ አሰፋ ጫቦን ወይስ ዶክተር አያሌውን ? ተስማምታችሁ ተርኩልን ማለት እንግዲህ ይህ ነው። ሻለቃ ፍሰሃ ገዳን በጥፋታቸዉ መኮነን፣ በልማታቸዉ መመስግን ይገባቸዋል። በሁለቱም ጽሁፍ የምናጣው ይህንኑ ነው። አቶ አሰፋ ጫቦ ጓደኛቸውን ለማመስገን የተጓዙበትን መንገድ በትዝብት አልፈን የደርግን አሠራርና ባህርይ ስናስብ ለሥርዓቱ ታማኝነት እንዲሁ በቀላሉ የሚገኝ ሳይሆን በሌሎች ላይ በሚፈፀም ግፍ የሚገኝ እንደነበር መረዳት አያዳግትም። ታማኝነት ከሌለ ደግሞ በሥልጣን ላይ መቆየት ከቶ የሚቻል አልነበረም። የመንግስቱ ኃይለ ማርያም፣ የፕሮቶኮል ሹም ለመሆን መቼም ምን እንደሚያስፈልግ ማንም መገመት ይችላል። ታማኝ ለመሆን ታማኝ ያልሆኑትን ማጋለጥ ወይም ማግለል አስፈላጊ ነበር። በሥልጣን ላይ እስከ ደርግ መጨረሻ ለመቆየት ደግሞ ቢያንስ በሌሎች ላይ ግፍ ሲፈጸም ዝም ማለት ወይም መደገፍን ይጠይቃል። በተለይ በደርግ አባልነት በመጀመሪያው ረድፍ ተሰልፈው የነበሩ ግለሰቦች ገና ከጅምሩ በ60ዎቹ የንጹሃን ደም እጃቸው የተነከረ ለመሆኑ አያሌ ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል። ንፁሃን ዜጎችን ይገደሉ ብሎ እጅ መቀሰር ለግድያው ተባባሪነት ትልቅ ማረጋገጫ ነው የሚል እምነት አለኝ። ይህንና ይህንን በመሳሰሉ ሌሎች በርካታ ምክንያቶች ናቸው በደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ዘመን አቶ አሰፋ ጫቦ ሊስሏቸው እንደፈለጉት ገፀ-ባህሪይ ዓይነት ፍሰሃ ገዳን ፈልገን የምናጣቸው።
ከግል ወዳጅነትና ትስስር ይሁን ወይም ከጥቅም ተጋሪነት ስሌት በውል ባይታወቅም፣ ከደርግ ባህሪይ አንፃር ዛሬ ሻለቃ ፍሰሃ ገዳ “ጀግና” ተብለው ቢሰየሙ ከቶ ሊያስደንቀን አይገባም። የትልልቆቹን ወንጀል በብዕር ጸበል ለማፅዳት ከተቻለ የትንንሾቹም በዚያው ፀበል ፈውስ ሊያገኝ እንደሚችል ታሳቢ አድርጎ ከሆነ ቆንጆ ስህተት ነው። ነገር ግን መደከም ያለበት አዲሱ ትውልድ ካለፈው ስህተት እንዲማር እስከተፈለገ ድረስ እውነቱን እንዲያውቅና የታሪክ ሚዛን እንዳይዛባ ከማድረግ ባለፈ ሌላ የተሻለና አማራጭ መንገድ አይኖርም።
2ኛ. አንዳንድ ታሪኮች ከመቸኮልም ይሁን ጥናት ባለማድረግ ትልልቅ ስህተቶች፣ ዝርክርክነት ይነበብባቸዋል። ለዚህ እንደ መረጃ የሚሆነን አስደናቂው ታሪክ የጥላሁን ገሠሠ ታሪክ ነው። ጥላሁንን በተመለከተ በሁለት መድብሎች ውስጥ የተለያየ የታሪክ ገፅታ ይዞ እናነባለን። አንደኛው በዘካሪያ መሐመድ “የሕይወት ታሪኩና ምሥጢር“ ሲሆን ሌላኛው “የኢትዮጵያ የሙዚቃ ንጉስ“ በሚል በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር የተዘጋጀው ነው። ይህንን ትልቅ ውዝግብ ያስነሳ የተዛባ የታሪክ ቅኝት አስመልክቶ ራሱን ለእውነት በማንበርከክ በአደባባይ ወጥቶ አንዱ የሌላኛው ጭብጥ በመቀበል መረጃዬ የተሳሳተ ነው፣ ከይቅርታ ጋር በዚህ አርሙት ለማለት የደፈረ እሰከአሁን አላነበብኩም። ካለ ግን እታረማለሁ።
በሁለቱ መጽሐፍት ውስጥ ያለው ልዩነት ጥልቀት ያለው ጥናት ሳይደረግ ከሚሰራ ስህተት የመነጨ ይመስለኛል። በደራሲያኑ ማሕበር መጽሐፍ (ገጽ 4 -5) ጥላሁን የተወለደው ጠበንጃ ያዝ ሰፈር ነው በሚል ይነበባል። በዘካሪያ ማህመድ መጽሐፍ (ገጽ 29 – 30) ጥላሁን ገሠሠ የተወለደው ጎሮ/ሶየማ የገጠር ቀበሌ ነው። ሁለቱን መጽሐፍት ስናነብ ግራ ሊገባን ይችላል። ጥላሁን የተወለደው ወሊሶ ወይስ አዲስ አበባ ጠበንጃ ያዥ ሰፈር? ተራ ጥያቄዎች እንኳን መልስ አላገኙም። ይህ ዓይነቱ ስህተት በአሁኑ ጊዜ በተደጋጋሚ መጽሐፍት ውስጥ ጎልቶ የሚታይ ችግር ነው። እነዚህ እንኳን ከጊዜ ቅርበታቸውና ከመረጃ አቅርቦት አንፃር ስህተት ሊፈጠርባቸው ባልተገባ ነበር።
3ኛ. በጥላቻና ሕዝብን ለማሳሳት የተጻፉ መጽሐፍት በአሁኑ ወቅት በብዛት ይገኛሉ። ይህ ደግሞ ሆነ ተብሎ የሚደረግ በመሆኑ እንደ ወንጀልም ይቆጠራል። በተለይ በወያኔ የሚተዳደሩ ግለሰቦች ታሪክን ለማበላሸት በሰፊው የተያያዙት ነው። በጥላቻና የሌሎችን ታሪክን ለማበላሸት ከተጻፉት ውስጥ በሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ ተደርሶ በጸሐይ አሳታሚ ድርጅት የታተመው “እኛና አብዮቱ“ ከፍተኛውን ቦታ ይይዛል። በውስጡ ሳይሰልቅ ገርድፎ ያቋታቸው ውሸቶች በመብዛታቸው አያሌ ትችቶች በድረ ገፆች ሲያስተናግድ ከርሟል። ለእማኝ ያህል በገጽ 230 ላይ ያለውን እነሆ፡ –
“. . . ዝግጅቱ ከሞላ ጎደል በዚህ ሁኔታ ከተጠናቀቀ በኋላ የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት ጉባኤ አባላት ሁነው የተመረጡት ሰዎች ተጠርተው በ1968 ታህሣሥ ወር መጨረሻ አካባቢ ጽ/ቤቱን እንዲያቋቁሙ ተደረገ። መሥራች የጉባኤ አባላትም ፦
አቶ የወንድወስን ኃይሉ
አቶ መሥፍን ካሡ
ደ/ር ሰናይ ልኬ
ዶ/ር ነገደ ጎበዜ
አቶ ኃይሌ ፊዳ
ዶ/ር ፍቅሬ መርዕድ
አቶ አሰፋ መድህኔ
አቶ እሸቱ ጮሌ
ዶ/ር መለስ አያሌው
አቶ ተስፋዬ ሸዋዬ
አቶ ባሮ ቱምሳ
ዶ/ር በዛብህ ማሩ
አቶ ዮሐንስ አድማሱ ናቸው።
የተመረጡት የጉባኤ አባላት የመጀመሪያ ስብሰባ ባካሄዱበት ቀን ዮሐንስ አድማሱ በኢሕአፓ ራሱን እንዲያገል በተሰጠው መመሪያ ምክንያት በስብሰባው ሳይገኝ ቀረ ። . . .“
በቁጥር 13 የሚገኘውን ዮሐንስ አድማሱን ለአብነት እንመልከት። ይህ ሆነ የተባለው በ1968 ታህሣሥ ወር መጨረሻ ገደማ ነበር።
የአዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ ፕረስ 2004 ዓ. ም. ባሳተመው “ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ አጭር የሕይወትና የጽሑፍ ታሪክ“ በዮሐንስ አድማሱ ተጽፎ በወንድሙ ዶ/ር ዮናስ አድማሱ የተሰናኘው መጽሐፍ መቅድም ላይ ስለ ዮሐንስ አድማሱ እንዲህ ይላል፡ –
“ በ1967 ዓ. ም. በወታደራዊ መንግሥት የታወጀውን የ1967ቱ የዕድገት በሕብረት ዘመቻ በሂርና ተመድቦ ሲሰራ በነበረበት ጊዜ ነው ሕይወቱ ያለፈው። ሰኔ 7 ቀን ፣ 1967 ከዕድገት በሕብረት መምሪያ በተጻፈ ባለ ሦስት ገጽ ዘገባ መሠረት ዮሐንስ ነፍሱ ከስጋው የተለየችው በሰኔ 3 ቀን 1967 ዓ. ም. ከአንድ ቀን በፊት የጀመረው ሕመም ስለጠናበት ወደ አሰበ ተፈሪ ሆስፒታል ሲወስዱት በመንገድ ላይ፣ መጣቀሻ በምታባል መንደር ነው። . . .“
ሰኔ 3 ቀን 1967 ዓም ያረፈው ዮሐንስ አድማሱ በታህሳስ 1968 ዓ.ም. በኢሕአፓ ስብሰባው ላይ እንዳይገኝ ተደረገ ብሎ መጻፍ የሚያስከፋ ነውረኛ ተግባርና የጥላቻ እርሾ ውጤት ነው የሚመስለው። ታላቁን ደራሲ ዮሐንስ አድማሱን በተደጋጋሚ በአብዮቱ ወቅት በተሰለፉ የተለያዩ ቡድኖች ውስጥ ለመመደብ የሚደረገው ጥረት ብዙ ነው። ሻምበል ፍቅረሥላሴ በኢሕአፓነት ሲከሱት ሌሎች ወጣት ፀሐፊዎች በመኢሶንነት ሲመድቡት ተነበዋል። እነዚህ ሁሉ ሃሜቶች የተፈጠሩት ዮሐንስ አድማሱ ላይ በጠቀስኩት ግጥም የወሬ ፈጣሪ ፣ ሰብቀኛ ብሎ በሰማቸው ወሬ ፈጣሪዎች ነው።
እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው ከብዙዎቹ በጣም ጥቂቶቹ ነጥቦች ሲሆን ሌሎች በየመጽሐፉ በብዛት ይገኛሉ። እነዚህን የመሳሰሉ የተሳሳቱ መረጃዎች በማንበብ የነጻው ፕረስ ወጣት ጋዜጠኞች ሳይቀሩ ከፍተኛ የሆነ ስህተት እየጻፉ ይነበባሉ። ችግሩ የተጻፈ ሁሉ እውነት እየመሰለን የምንቀበል ብዙ መሆናችንም ጭምር ነው።
ጊዜና ጉልበት ይጠይቃል እንጂ ብዙ ብዙ እንደዚህ ዓይነት የታሪክ ግድፈቶችን እየነቀሱ ለሕዝብ ማቅረብ ይቻላል። ይህን ያነሳሁት ስህተቶች ለምን ተሰሩ ለማለት ሳይሆን ዓላማው ለምን? የሚለው ጥያቄ ሊጤን ይገባል ብየ ስለማምን ነው። ፍቅረሥላሴም ሆኑ ሌሎች መሰል ጓዶቻቸዉ በማርክሲዝም – ሌኒንዝም ካባ ሽፋን በጥላቻና ግፍ በዜጎች ላይ ጣት እየቀሰሩ በደቦ የከፋ ወንጀል ሲሰሩና ሲያስጨፈጭፉ እንዳልኖሩ ሁሉ ዛሬም ቢሆን እንደልማዳቸው ጣት የመቀሰር ውንጀላቸውን እንዳልተዉ ያረጋግጥልናል። ድሮ ጣት ቀስረዉ በአፈሙዝ ንፁሃን ወገኖችንን ሲያስጨፈጭፉ የኖሩ የደርግ ባለስልጣናት፣ ዛሬ ደግሞ ብዕር ቀስረው ዳግም ታሪኩን ለመጨፍለቅ ሲማስኑ እየተመለከትን ነው። ቀደም ሲል በሃገርና በወገን ላይ በሰሯቸው ግፎች በአዕምሯቸው ውስጥ የተፈጠረውን ጭንቀት ለማለዘብ ግፉ የተፈጸመባቸውን ወገኖች ዳግም በመክሰስ የወንጀል ሸክማቸውን ለመቀነስ እንደ ዓይነተኛ መሳሪያ ለመጠቀም ቆርጠው የተነሱ ይመስላል። ደርጎች ዛሬም በቀብራቸው አፋፍ ላይ ቆመው ሃቁን ተናግረው ንስሃ ለመግባት ዝግጁ አይደሉም። ከነወንጀላቸው ወደ ግብአተ መሬት መግባት ደግሞ የሞት ሞት ነው። ኢትዮጵያዊ እምነትም ባህልም አይደለም። እግዚአብሔር ለንስሃ ሞት ያብቃቸሁ ብለን እንመርቃቸው ?
አንድን ሀገራዊ ክስተት በሰከነ አይምሮ እውነትን ቃኝቶ፣ ጭብጡን በህሊና መዝኖ በመጻፍ ለሕዝብ ንባብ ማቅረብ እየተቻለ፣ ያለምንም አስገዳጅ ሁኔታ፣ ሃላፊነት በጎደለው መልኩ፣ በታሪክ መስክ ላይ እንዳሻቸው ሽምጥ በሌጣ ብዕር መጋለብ ምን ያህል ዳግም ሕዝብን መናቅና ሃገርን መበደል እንደሆነ፡ ፀሃፊዎች ሁሉ በውል ሊረዱት ይገባል። ሜዲያው ስለተመቸ ብቻ ውል እንደጠፋዉ ልቃቂት መያዣ መጨበጫ ያጣ ድርሰት መቸክቸክ ስምን በፃህፍት ተርታ ለማስመዝገብ ይፈይድ እንደሁ እንጅ ከታሪክ ተወቃሽነት ከቶ አያስመልጥም። አንዳንዶች ትላንት አብረው የሠሩትን ጥፋት በሌሎች ሲያሳብቡ የሚታዩ ሲሆኑ፣ ሌሎቹ ደግሞ የበሉበት ሌማት የአለላው ቀለም ገና ስላልረገፈ ባዲስ ቆዳ ለጉመው ታሪኩን ቀጥለው ለማስኬድ ይፍገመገማሉ። ከዚህ ውጭ የሆኑት እዝያም እዚህም እየዘለሉ የታሪክ ቃርሚያዎችና ያሉባልታ ስብስቦች የሚያቀርቡ ናቸው።
አንድን ታሪካዊ ክንውን ለመፃፍ መድፈር በራሱ የሚያስመሰግን ነገር ቢሆንም፣ እውነትን መግለጥ ደግሞ እጅጉን የላቀ፣ የሚያስከብርና የሚያስመሰግን ተግባር ነው። ለመጭውም ትውልድ ልናስተላልፈው የሚገባ ጭብጥና መልዕክት ዘላቂነት ከእኛ ሃቀኝነትና ሃገራዊና ህዝባዊ እይታ ይመነጫል። እኛ ሃላፊዎች ነን፣ ነገር ግን ሥራችን በመልካምም ይሁን በበጎ ጎኑ ተዘግቦና ህያው ሆኖ ይኖራል። ወደድንም ጠላንም፣ አለማንም አጠፋንም ታሪክ እየሠራን ነው። ስለዚህም ነው ለሃገርና ለሕዝብ ብሎም ለትውልድ ትክክለኛውንና እውነትን በማሳወቅ ረገድ ፃህፍት ታላቅ የሙያና ሃላፊነት ሚና የሚጠበቅባቸዉ።
ስለ ሃገራችን የሚያስቡ ሁሉ በሰላም ይክረሙ!
beljig.ali@gmail.com
ፍራንክፈርት 09.09.2015
\