• የቴዲ ወላጅ አባት ካሳሁን_ግርማሞ እና እናቱ ጥላዬ_አራጌ ( ራዬ ) ለጥበብ የተሰጡ ናቸው። እናቱ ጥላዬ አራጌ የመድረክ ተወዛዋዥ ስትሆን አባቱ ካሳሁን ግርማሞ መድረክ እያዝናና በማስተዋወቅ ተወዳጅ እና ተደናቂ ነበር። በተጨማሪም በሬድዮ ጋዜጠኝነት በሚያገለግልበት ወቅት በሚያቀርባቸው ወንጀል ነክ የፖሊስ ተከታታይ የምርመራ ታሪኮች ብዙ አድማጭ እና አድናቂ አፍርቷል።
እንዲሁም የመድረክ ተወዛዋዧ ጥላዬ አራጌ ቴዲን ስትጸንሰው 16 የአስራ ስድስት አመት ወጣት ነበረች። ቴዲን እርጉዝ እያለች ደብረ ዘይት(ቢሾፍቱ) ጎራ ብላ በነበረበት ወቅት ታላቁ ሰአሊ ለማ ጉያ በልዩ ሁኔታ የሳለውን የአፄ ቴዎድሮስን ስዕል ያበረከተላት። ስዕሉን አተኩራ እየተመለከተች ባለቤቷን “ካሳሁን…ካሳ” ብላ ጠርታው የምትወልደውን ልጅ ስሙን ቴዎድሮስ … ቴዎድሮስ_ካሳሁን እንደምትለው የነገረችው።
ሀምሌ 7/1968 ዓ.ም ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ ዱብ አለ።…የኢትዮጵያ ሙዚቃም አዲስ ንጉስ አገኘች። ቴዎድሮስ የስድስት አመት ልደቱን ሲያከብር እናቱ ራዬ አልተገኘችም። የወላጆቹ ትዳር ሊዘልቅ የቻለው እስከ አምስት አመቱ ነበር። ቴዲም ከአባቱ ጋር አደገ።
ታዳጊው ቴዲ የሙዚቃ ፍቅር በውስጡ ተንሰራፍቶ ልቡን አሸፈተው…ጥበብ ገዛው!! ከወላጆቹ ግን ተቃውሞ ነበር የጠበቀው። ለሙዚቃ ያለውን ፍቅር ለአባቱ ለማሳየት በተደጋጋሚ ቢሞክርም ከአባቱ አበረታች ምላሽ አላገኘም።
ወላጆቹ ከጥበብ የልፋታቸውን ያላገኙ ሰዎች ስለሆኑ ወይም ከጥበብ ያተረፉት የሰውን አድናቆት እና ፍቅር ብቻ ስለሆነ የነሱ ጉዳት በልጃቸው እንዲደገም አልፈቀዱም። የወላጆቹ ተቃውሞ ቀጠለ። ነገር ግን ቴዲ ለራሱ ፍቃድ ሰጥቶ ወደ ጥበብ ባህር ጭልጥ ብሎ ገባ።
በአንድ አስገራሚ እለት እናቱ ራዬ በህመም አልጋ የያዘችውን እህቷን እያስታመመች ሳለ ፊቷን ወደ ተከፈተው ቴሌቪዥን ዞር ስታደርግ አይኖቿ የሚያዩትን ልታምን አልቻለችም። ልጇ ቴዲ “ትዝታ” የሚለውን ሙዚቃ እየተጫወተ ነበር። ተደነቀች!
ዘፈኑ ሲያበቃ እራስዋን ቴሌቭዥኑ ስር ተንበርክካ ነበር ያገኘችው። አባቱ ደግሞ ለስራ ጉዳይ ከአዲስ አበባ ውጪ ቆይቶ እንደመጣ የሜነጃይተስ ህመም አጋጥሞት የህክምና ክትትል አድርጎ ሻል ብሎት እንዳገገመ ነበር የአንድ ብቸኛ ልጁን ሙዚቃ ለመጀመሪያ ጊዜ ያዳመጠው።
በእርጋታ ደስታውን ገለፀ። በወዳጆቹ ልጁ ሲደነቅ ሲያይ ኩራት ተሰማው። ይሁን እንጂ አባቱ ካሳሁን ግርማሞ ቴዎድሮስ ካሳሁን በዘፈኖቹ ሀገር ሲነቀንቅ ለማየት አልታደለም።