ከመሳይ መኮንን
እንኳን አደረሳችሁ:: የሞላ አስገዶም ወደ ህወሀት ካምፕ መግባት አዲሱን አመት በተለያዩ ስሜቶች እንድንቀበል አድርጎናል:: ይህን ያህል አጀንዳ ይሆናል ብዬ አልገመትኩም:: ስለሞላ እስከማውቀው ድረስ ጥሩ ኢትዮጵያዊ: እንደ ህወሀቶች ዘረኝነት የማይነካካው: በመግባባት ለመስራት ከልቡ የሚሻ ነበር:; መቼም ሰው እንደ እህል አይቀመስም:: መለኮታዊ ሃይል ኖሮ ልብ የቀበረውን ማወቅ አይቻል:: በሞላ ደም ውስጥ የሚንተከተከውና ዛሬ ላይ አደባባይ የወጣው ማንነት የሰው ልጅን ፈጽሞ አንብቦ እንደማይጨረስ አንዱ ማሳያ ሊሆን ይችላል:: ግን አንድ የማልደብቀው ሀቅ አለ:: ይህን የምናገረው ሞላ አሁን ወደ ህወሀት ጠቅልሎ በመግባቱ የተነሳ አይደለም:: ዕውነት ስለሆነ ነው:: ያኔ ያን ዕውነት ማፈንዳቱ ለትግሉ ጉዳት እንጂ ጥቅም አይኖረውም::
አዎን! ሞላ ባህላዊ መሪ ነው:: ለ5 ደቂቃዎች ከእሱ ጋር ፖለቲካ ለመጫወት አይቻልም:: ስለ ኢትዮጵያ ውስብስብ ፖለቲካ ያለው ግንዛቤ ያስደነግጣል:: ማለት ጥልቀት የለውም:: ቀናነቱና ገራገርነቱ ፖለቲካዊ ድክመቱን ባይሸፍኑለትም አብሮ ላለመስራት የሚጎረብጥ ሰው አልነበረም:: እርጋታውና ጨዋነቱም ሌላው ድክመቱን የሚጋርዱ ባህርያቱ ናቸው::
አሁን ሞላ የለም:: ደሚህት ግን ከነሙሉ ሰራዊቱ ትግሉን ተቀላቅሏል:: በደሚህት ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰራዊቱ አባል ከተለያዩ የኢትዮጵያ አከባቢዎች የመጡ ናቸው:: የትግራይ የሚለው ስያሜ ቀድሞ ስለያዘ እንጂ ሰራዊቱ ሙሉውን ኢትዮጵያ የሚወክል ነው:: እኛም በኤርትራ ቆይታችን ይህን ታዝበናል:: የሰራዊቱ ስሜት ከሞላ አመራር ጋር የሚመጣጠን አይደለም:: አንድ ቀን ሰራዊቱ ፈተና እንደሚሆንበት ሞላ የተገነዘበው ይመስለኛል:: በደሚሀት ካምፖች በነበረኝ ተከታታይ ጉብኝቶች የተረዳሁት የሞላ አመራርና የደሚሀት ሰራዊት ፍላጎት ለየቅል መሆናቸውን ነው:: ይህን ጉዳይም አንድ ምሽት ላይ ባሬንቱ ከተማ ቢራ እየተጎነጨን አንስቼበታለሁ::
” ሰራዊቱ ኢትዮጵያዊ: ስያሜው ግን የትግራይ:: ምን ማለት ነው?”
ሞላ በወቅቱ ጥሩ መልስ ሰጠኝ:: አሁን ላይ ስገምት የማያምንበትን ነው የነገረኝ
” ቀላል ነው:: ስያሜው አያስጨንቅም:: “ት” ን በ”ኢ” የመቀየር ያህል ቀላል ነው:: ዋናው ተግባብቶ መስራት ነው” አለኝ::
ሞላ መግባባት አቅቶት ወይም በሌላ ምክንያት ወደ ህወሀት ሄዷል:: ኢትዮጵያዊ መልክ የተላበሰው ደሚህት ግን ከትግሉ ጋር ነው:: ግለሰብ በራሱ ውሳኔ መንገዱን መርጧል:: ጨርቅ ያድርግለት:: የኢትዮጵያ ትግል ከባህላዊው አመራር ካልተላቀቀ ለውጥ አይኖርም:: የሚንጠባጠበውን እያራገፉ ከመጓዝ ውጭ አማራጭ የለም:: በግለሰቦች ላይ የተንጠለጠለ ትግል ወደ መቃብሩ ወርዷል:: ሞላ ለጊዜው ጭረት ሊፈጥር ይችላል:: ከዚያ ያለፈ ጉዳት የለውም:: ደሚሀት መግለጪያ ያወጣል ተብሎ ይጠበቃል:: አዲሱ ዓመት ዘመናዊውና በዕውቀት ላይ የተመሰረተው የምር የሆነው ትግል የሚጀምርበት ይሆን ዘንድ ሁሉም የሚችለውን ያድርግ:: መልካም በዓል!!!