ከሥርጉተ ሥላሴ 12.09.2015 /ሲወዘርላንድ – ዙሪክ/
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱሳን አሃዱ አምላክ አሜን! ሳይገባኝና ሳልመቸው፤ አሮጌውን ዓመት ሸኝተን የመንገድ ጠራጊውን የሰማዕቱን ቅዱስ ዮኋንስን ስንቀበል፤ በ2007 ዓ.ም ከተከወኑት ድንቅ ተግባራት – ለእኔ፤ አውራ የሆነው የኢትዮዽያ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖታችን ደማቅነት በሚመለከት፤ የውስጤን መንፈስ ለመግለጽ መፍቀድ ግድ አለኝ። በውነቱ ቁንጮ የሆነ ብሄራዊነትን ያበራ፤ ለልዕልቴ ለኢትዮጵያ አለንልሽ ያለ፤ ዕንባዋን የተጋራ ጉልላት ተግባር ስለሆነ።
እንዲህም ሆነ – የተግባር ቀጠሮ ሳይኖረን የሙያ አባቴና የሥራም አለቃዬ – ደወለልኝ። ቃል ስጠብቅ ዘለግ አድርጎ በድምቀት „ዎህ“ አለ። ትንፋሼን ሰብሰብ አድርጌ „ምነው በደህና?“ ስል በድንጋጤ ግን በልስሉስ ለዛ ጠዬቅኩት „ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ መርቀርዮዎስ ፓትርያርከ ዘኢትዮጵያ ፈጣሪ አምላካችን ጠብቆ በሰላም አሜሪካ መግባታቸውን – አበሰረኝ። ሐሤታችነን ሳናባክን ስልኩ በሠናዩ ዜና ደወል ተጠናቀ። ከሁለት ቀናት በኋላ አብሮ አደጌ ከካናዳ – ከአንኮቨር ደወለልኝ። ታላቁ በዓለም ዓቀፋ ሰብዕዊ መብት አስከባሪ ድርጅት ቁልፍ ነበረችና ሂደቱን – አጫወተኝ። ሰንበት ላይ የቤቱ ሳተና – ሁለገብ አግልጋዩ፤ ረጋ ብሎ ታናሽ ወንድሜ ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን የሚገኙበትን ሁኔታ – ነገረኝ። እግዜብሄርንም – አመሰገን። ከዛ በኋላም የሱባኤ አባትነት አብነትነታቸውን እማርበት፤ ነፍስ እገዛበት ዘንድ፤ አዝዬ ያሳደጉት ታናሽ ወንድሜ ሁለገቡን ሸክሜን እችልበት ዘንድ፤ እንደ ታላቅ ወንድም ታናሼ – ያስተምረኛል። ምሳሌነታቸው የብፁዕነታቸው ሊቅ ጉልትም ነውና።
ምስላቸው አድህኖዬ ነው። ህይወታቸው ታምራቴ ነው። ታናሼ ወንድሜ በዚህ የመከራ ዘመን ለቤቱ መመረጡ፤ በጎንደር በገላእድ ተራራ ሥር፤ የአዳም ሰገድ እያሱ ቅርስ – ታቦቱን ንጉሠ ነገስቱ የተሸከሙለት፤ የሃይማኖት – የታሪክ እልፍኝ በሆነው በደብረ -ብርሃን ሥላሴ በሊቀ ሊቃውንትነት ጥንግ አገልጋይ የነበሩት አቨው አያቶቻችን ነዳያን፤ ሊለምኑ ላፈሩ ወገኖቻቸው ድንኳን ጥለው፤ አደግድገው እስከ 4 ፍሪዳ አርደው የልደተ ክርስቶስን ፆም መፍቻን በረከት ያፍሱ የነበሩት፤ የመላዕከብርሃናት ልሳነወርቅ ኃይለሥላሴ የትውፊት ወራሻቸው የመላዕከ ብርሃናት ገብረአጋይስት ልሳነወርቅ – ጸጋ ትንፋሽ በእርሱ በታናሽ ወንድሜ ላይ አርፎ፤ የተገፋው የሊቀ ሊቃውንታት ቅዱስ ዓውደ ምህረት ቤተኛ በስደት ሀገር ሥሉስ ቅዱስ አደረጉልን። ተመስገን።
ድምጻቸውን ለጾም፤ ሩሃቸውን ለሰጊድ፤ ጠረናቸውን ለዓለም ስምምነት – ለሰላም፤ ነፍሳቸዉን ለወንጌል ቀኖና እና ዶግማ ተገዢነት፤ ዘመናቸውን ለሱባኤ አባትነት – በቅንነት፤ የሰጡ ቅዱስ ሐዋርያ አባት ናቸው። ቅዱስ አባታችን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቀርዮዎስ ፓትርያርከ ርዕሰ ሊቃነ ዻዻሳት ዘኢትዮጵያ ቅዱስ አባታችን ከምድረ አራዊት ሴራ ልዑል አምላካችን አውጥቶ፤ እንደ የበዛ ጭምትነታቸዉ፤ ቀሪ መዋለ እድሜያቸውን ያላዩትን የስደት መከራ እንደ ወዳጃቸው ውጽፍተ ወርቅ እንዲዩት ሲመርጥላቸው ለግዑፋን የወንጌል አርበኞች፤ ለሃይማኖታቸው ቀናዕይ ለሆኑት የኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ማህበረ ምዕመናን እንዲሁም በስደት ሐገር ለሚወለዱ የፍቅር ተስፋዎችና ለማግሥት ተረካቢዎች ሁነኛ የአብነት ሰብሳቢ ፊደል እንዲሆኑ መርቆ ነው። የአብነት ሊቀ – ትጉኃን ቅዱስ አባታችን በቀስታ እየተራመ፤ዱ በፈርኃ እግዚአብሄር ልቅና እራሳቸውን እጅግ ዝቅ በማድረግ፤ ተዕቅቦን በተግባር በማበልጸግ፤ ዘመነ ሱባኤቸውን ለሐዋርያነትን የፈቀዱ መሆናቸው እኔ በግሌ ቅዱስነታቸውን የማየት ህልሜ ልክ የልጅነት ህልሜን እየሩሳሌም የማየት ያህል ነው ላያቸው እጅግ እምናፍቀው። ምክንያቱም የተመሰጠረው ፍጹም ልዩ ሥነ – ምግባር በራሱ የመዳኛ ጸበልና እምነት ነው። ገዳማዊ ህይወታቸው ሥርዬት ድህነት ነው። ብፁዕነታቸው የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታ ናቸው ሚስጥርም ናቸው ኦርቶዶክስ ተዋህዶን አስከበሩት በረቂቁ ሰማያዊ ጸጋቸው።
ከዛ ከበላህሰቦች እጅ የወጡበት ማዕልትም ለእኔ ቅዱስ እለቴ ነው። በሰለጠነው ዓለም እየኖሩ፤ በህግ እግዚአብሄር እንዲህ ከሁሉ ነገር እርቆ እዩኝ እዩኝን ተጸይፎ ሌትና ቀን ዘግቶ በምነና መኖር – ለትውልዱ የድርሳን መጸሐፍ ነው። ሰው የላትም እናት ሀገር ኢትዮዽያ ለሚሉት ይህ አመክንዮ የማዕዘን ድንጋይ ነው።
ብጽዖ ወቅዱስ አባታችን አቡነ መርቀርዮስ የህጋዊ ቅዱስ ሲኖዶስ ፓትርያርከ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ የሥም ክብርና ዝናን ለቅድስናቸው እንዳይመጥን ያደረጉት በድርጊት ነው። አስተዳደራዊ የኃላፊነት ቦታውን ለፈቀዱት በመመረቅ፤ ቅዱስነታቸው የሱባኤውን ትጋት ወደዱት፤ ይህ ሰማያዊ ጸጋ ትውልድን በኤዶም መንፈስ ያበቅላል፤ መመካት አይገባም እንጂ እውነት የጥንት የጥዋቱ የዘመነ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ብርሃን ገድልና ታምራት ትውፊትን እንሆ በዘመናችን እያዬን ነው፤ የድምጻቸው ዜማ እጅግ ተናፋቂ የሆነውም የሃዲዱ ክህሎት ሚስጢር – ዓዕማድ ስለሆነ ነው። ብፁዑነታቸው ማንንም አይጋፉም – ተመስገን።
ይህ ፍጽምና በሸኘነው ዐመት ጉልሁን ትውልዳዊ ድርሻ በላቀ ጸጋ – ከወነ። በሀገራቸው በኢትዮጵያ በሦስተኛ ዜግነት እንኳን መኖር ያልተፈቀደላቸው ምንዱባን በሊቢያ መሬት ደማቸው የአፈራቸውን መሬት በራሮት ሲጣራ። ሰማእትነታቸው ኢትዮጵያዊ ዜግነትን ከወያኔ ሃርነት እግር ሥር ሲለምን። ኢትዮጵያ ላይ ያለው የፓትርያርኩ ጽ/ቤት በመሪው በሰማዕትነት ላይ ዘና ያለ ስላቅን -አስደምጦናል። ሎቱ ስብኃት። ለበላህሰብ ጥላነቱንም ዕንባ እየተራጨን – በአርምሞና በተደሞ አድምጠናል። የዘጠኙ ቅዱሳን የትናንት ቤተ ማዕዶት እንዴት ለማህጸኗ ነፍሶች ከዕንባቸው ጋራ ይጠቅጠቁ። እግዚዖ፨
የቅዱስ አባታችን የአቡነ ተክለሃይማኖት ጥርኝ፤ የእናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ የገድል ባዕት፤ የነብዩ መሃመድ የልጆቻቸው የመካራ ማሳለፊያ ጥግ – የሆነች፤ የሁሉም ማዕድ፤ ማዕድነቷ ተደፍጥጦ ስሌቱ በዘውጋዊነት ተወራርዶ፤ ለሃይማኖታቸው ክብር ሲሉ እንደ ተሰውት ታላላቆች ከነመስቀላቸው ሲታረዱ፤ የእስልምና ዕምነት ተከታይ ወንድማቸው ሳይቀር እኔም ከእነሱ ጋር ብሎ አንገቱን ለቢላዋ ሲሰጥ፤ ዘመናትን በፍቅር በቃል ኪዳን ቀለበት ቃሉን ሲሰጥ፤ ኢትዮዽያዊነት ደምቆ – መራ። ለምድራዊ ኑሮ የተጋ ኢትዮዽያ የሚገኘው የፓትርያርኩ ቢሮ ሃዘንተኞቹ በጭካኔ በሰለጠኑ የዞግ አንጋቾች ሲደበደቡ – ሲሳደዱ – ሲታሰሩ ለበደሉ ማካካሻ ልዩ ሥጦታ የአበጃችሁ ፊርማውን – ድል ባለ ድግስ በዕለ ሢመቱ ደም ደም እየሸተ አፈር እያነባች – አከበሩ። በቀደምቶቹ ሆነ በዛሬዎች ሰማዕታት ተዘመነ፤ ግራጫማ ክር የተላጠበት የፍቀት ዘመን ይህ ነው። እንግዲህ የመሃል – የዳር – እየተባለ ማህበረ ምእመኑ በውጪ ሀገር በዘውገ ክታብ ተጠቅልሎ ሽፍን ዬህወሃት ተባባሪዎች ሲያምሱት የኖሩበት ዘመን – ንጹሁ ቅዱስ አምላክ ወርቅን ያነጠረበት፤ ሰማያዊ ታምራት እንዲህ – ተገለጠ። ንጽህና የት ላይ እንደሆነ ጆሮ ላለው አወጄ።
ፈጣሪ አምላካችን ተከታዮችን የሚያስተምረው በምሳሌ ነው። ከእንቅልፉችን እንድንነቃ ከወደድን ታምር በማያቋርጥ ሁኔታ አሳይቶናል። ለእርቅ ጉባኤ የተላኩት አራት ዐይና በትልልፍ ረግጠው የሄዱትን ጉባኤ ዜና ሳያቀርቡ፤ ቤታቸውም ሳይገቡ ነበር የቀሩት። የአንድ የተመረጠ ብላቴና ታምራዊ ድምጽ ፍቅር እሰከ መቃብር – አድርጓል።
ልዑል እግዚአብሄር ፍቅሩን ሰጥቶናል። ይህ ፍቅር ጥጋችን ነው። ስለሆነም ቀን በአማጠች ቁጥር እረኛ አባት ይሰጠናል። የኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ታብብ – ትለመልም ዘንድ አብነቷን ሸልሟታል። ለገሃዱ ዓለምም መሪ ሰጥቶናል። ይህ ዐመት ለእኔ ልዩ ነው። ለገሃዱም – ለመንፈሳዊ ህይወቴ ቅኔ በዜማ ተቀኝቶልኛል።
ቸርነቱ የማያልቅበት አምላካችን ወደ እኛ እንሆ ተመለከተ። ሰምዕታት በሊቢያ ሥያሜው በህገ ቤተክርስቲያናችን ከብሮ ጸድቆ ታወጀ። ፆመ ፍልሰቲት የወልዮሽ የሱባኤ ሰሞናት ሆና መከራውን ተጋራች። ለልጆቻቻው አባት የሆኑት ቅዱስ አባታን „ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ መርቀርዮዎስ የህጋዊ ቅዱስ ሲኖደስ ፓትርያርከ – ዘኢትዮጵያ ሰፊ ዝግጅት የተደረገበትን የበዐለ ሢመት መሰናዶ የሰማእታቱ ክብር ብቻ እንዲበለጽግበት ፈቀዱ። ለዚህ ላጠናቀቅነው ዐመት „የድንቅነት መብራት መሪ ኮከብ „ እኔ የሥላሴ ባርያ ሥርጉተ ሥላሴ – ብዬዋለሁ። የሰማዕቱ ቅዱስ ሐዋርያ የዼጥሮስ ሃውልት ለባንዳነት ባደረ ዘረኛ ህወሃትና ተባባሪ የቅናት ተቋማት ቢነሳም፤ „የዼጥሮስ ያችን ሰዐት“ ቅኔ፤ የንጽህት ቅድስት እናታችን „ምነው እመብርሃን“ ተማህጽኖ ቢጠቀጠቅም፤ የእናታችን የተማህጽዕኖ ዘለዐለማዊ ክብር በመታበይ በህወሃት ቢነፈግም፤ የብላቴ ጌታ ጸጋየ ገብረመድህን ድምጽ ቢረገጥም፤ የእዮሩ አደባባይ ግን የተስፋ አባት አልነሳንም። አሉን ንግሥተ ኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን እንደ ትናቱም ዛሬም ቅዱሳን አሏት። ይደልወን ውስጣቸው ያደረጉ ሰማዕትነትንም የዘከሩ የቅንነት እጬጌዎች።
ሌላው በአጋጣሚው ማንሳት የምሻው ቁም-ነገርበስደት ሀገር የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ በግራም በቀኝም በበታችነት ዲያቢሎሳዊ መንፈስ ላይ ታች ለምትሉ ወገኖቼ እናንተ እንደምታስቡት ማዕከላዊ አውደ ምህረታችን ቅጽር ግቪው – ደጀሰላሙ – አቃቤቱ ቤተ – መቅደሱ ሁለመናው በእንቁላል ውሃ የተገነባ፤ እጅግ በአጠረ ዕድሜ በልቅና እንደ ፈቃዱ የተራጀ፤ ቅዱስ መንፈሱን ለባንዳ ፍርፋሪ ያላስገዛ፤ የማንነቱ ጌታ መሆኑን በልበ ሙሉነት – እናገረዋለሁ። እውነት ሁልጊዜም አሸናፊ ናት።
ቀሪዉ የአባቶቻችን ተግባራት ማህበረ ምእመኑን በዕንባ ዙሪያ የማሰባሰቡን ባሊህ ቢሉት መልካም ይሆናል። ብትን አፈር ያሳጣቸው ይሄው ነውና። ቢያንስ ለኢሳት ቤተ ክርስቲያናችን ኃላፊነቱን በሥሯ የተደራጅ የኢሳት ቤተሰቦች እንዲኖሩ እሷም ከምታገኘው በኲራት እራሷን ችላ እንደ አንድ ቤተሰብ የበረከቱ ተሳታፊ የምትሆንበት መርህ ነድፋ መንቀሳቀስ ይኖርባታል – በትህትና እና በአክብሮት። በነፃነት የመኖር ትሩፋት ከቤተክርስትያናችን በላይ መምህር የለም። እዛው ከጎረቤት እየኖሩ የኢሳት ብሄራዊ ተልዕኮ አይደለም መፈጠሩን ብዙወች አያውቁም። ለዛውም የሚችሉ። ስለዚህም በዚህ ዙሪያ ጠንካራ ማዕከላዊ የተግባር ዘመቻ ያስፈልጋል። ጊዜ ሊሰጠውም አይገባም። እንዲያውም ተዘግይቷል። የኢትዮጵያ ሳትላይት ቴሌቪዥን ከሥሙ ጀምሮ ህብራችን – ክብራችንም ነው። ኢሳት ለቅድስት ቤተክርስትያናችን ልሣነወርቅ ሽልማቷ ነው።
ማህበረ ምዕመኑ ውርዴት እንዲገባቸው ማድረግ ያስፈልጋል። ከመንፈሱ ጋር ለሚኖር ኢትዮዽያዊ የበታችነት ውርዴ ነው። የተዋህዶ ልጆች የህጋዊ ሲኖዶስ ቤተኞች ከመረጃ ፍሰት እጥረት የተነሳ የህወሓት ዜና ማሰራጫ ሰለባ ሆነዋልና ቅዱሱ ማዕዳችን ከጥፋት ውሃ ያድናቸው ዘንድ እኔ የሥላሴ ባርያ ትቪያዋና ታናሿ ዝቅ ብዬ – አሳስባችሁአለሁ። እለምናችሁ – እማጸናችኋለሁ።
በተጨማሪም አካል የሌለው የመዳህኒትዓለም አገልጋይ የቃለ ወንጌል ታሪክ የነፃነት ተጋድሎ ታሪክ መሆኑን የሳተ የተላለፈ ግድፈትም አዳምጣለሁ። ይህም መንገዱ ልክ አይደለም እና ሃግ ልትሉት ይገባል – በትህትና እና በአክብሮት። ህይወት ለሚገብረውም የአገር አድኑ ብሄራዊ ሠራዊታችን አስኳል የደጀንነት ተግባር ቀጠሮ ሊሰጠው አዬገባም ባይ ነኝ። ማህበረ ምእመኑ በመረጠው ዘርፍ ተሳትፎውን በቋሚነት ይጀምር ዘንድ ቤተ ክርስቲያናችን ባለድርሻነቷን በግብር ማስጌጥ ይኖርባታል። እንደ ትውፊቷ እንደ ጥንቱ እንደ ጥዋቱ።
የራስ ባለአደራ፨
ድጓ ፆመ ድጓ፤ መጸሐፍ ከቅኔ – ርትህ ዝማሬ፤
ለወንጌል ገበሬ – ለሰማዕታት ህብሬ፤
ሊቀ – ሊቃውንቱ በኃቲ ሲያዜሙ
ትውፊት ትሩፋቱ ዳዊትን ሲደግሙ፤
ህዋስ ሆነው ኖሩ ቃሉን ሲመግቡ
የኪዳን አዝመራ የእኛ ደመ ግቡ።
ማህሌት ተጠርታ ሃሌን አስቀድማ
ምስባክን አፍቅራ ቅዳሴን ቀምማ፤
ሰዕታት ባቋቋም – መርጌታው በንግሡ
ክብካብ በጽላቱ – ሙሴውም በአሃዱ፤
ደወሉ ተጣርቶ ጽናጽል ደጉሦ
ዕርግብ በር ይሆናል ሐሤትም መንኩሦ።
ስዋሰው ተራብቶ ግዕዝ ደጅ ተጠንቶ፤
ቅኝቱ ይወርዳል ብዕር ተባራይቶ፤
መንሹ ይርጋ ይላል ምርጥ ዘር አዝርቶ
ቃና ባይኑ ፈክቶ።
ፆም ጸሎት ተዋዶ ስግደት በተደሞ፤
መታቀብ ተፈቅዶ ሱባኤ ባርዕምሞ፤
ሩህ ትሰክናለች ዉህድ በአንክሮ፤
ቅድስና ቤቷ የኦርቶዶክስ ኑሮ።
የሰማእታት ቁንጮ የሐዋርያት ዕርገት፤
የነበያት ንባብ ያንድምታ ሊቃውንት
የሠለስቱ ረቂቅ የአይነታ እትብት፤
አብነት።
ሽብሸባው ሙሉወርድ ዜማውም በጃኖ
እልልታው ጅረት ነው የህሊና መቅኖ።
ሁልግዜም አሽታ አስብላ መግባ
በሰላማዊነት ጥናትን አዝምራ
አብራርታ ገምግማ ውስጡን ተመራምራ፤
ቀለሙን ጠጥታ፤ ሚስጢር አመሳጥራ፤
ዘመናት ቀናቱን በቅምረት አስምራ
የእኛ የንብ አውራ የትውፊት ጎመራ።
ብራናን አምርታ ሊቅነት በዕድምታ
ፈልቃ ትኖራለች ድንቅነት ገንብታ።
ችግርን ተጋርታ እመቤቴን ጠርታ
ህይወት ትሆናለች ነባቢት አብርታ።
የእሽት ባለብራ ትጉህ ባለ’ዝምራ
ገድፋ የማታውቀው የእኛ ባለ ቅኔ ከታምር ተምራ፤
መክሊት ተሰቷታል ከቅንነት ጎራ ሰንደቅ ልታበራ
መሆን ናት ነፃነት የመሆን ጎመራ የራስ ባለአደራ።
ሥጦታ – ለማተቤ ለቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ (ነሃሴ 23 . 2007 ሲዊዘርላንድ)
ለላይኛው ዕይታዬ የማጠናከሪያ ማጠቃለያ – በትህትና
፩ የኢሳት ቤተሰቦች ቅድስት ቤተክርስትያናችን በማዕዷ በቋሚነት ቢኖራት የታሪክ ታዳሚነት በሚዲያ ዙሪያ ይኖራታል። ብልህነትም – ይመስለኛል።
፪ ለነፃነት አርበኞቻችን የሰብዕዊነቱን ድርሻ ብትወስድ – ይህም ማለት የቀይ መስቀል የደም ባንክን ኃላፊነት ድርሻ ቢኖራት፤ በሃይማኖታችን ጥቃት ሆነ፤ የቀደምቱን አዳራ በተግባርን ማብራት ሲሆን፤ ይህም ደም ለመስጠት የተዘጋጁ ቅዱሳን የደሙን ዋጋ በሽልንጓ እንዲያደርጉ ሁኔታውን ማመቻቸት፤ ለነፍስም ለስጋም ጸጋ ነው፤ በዚህም ቅድስት ቤተክርስቲያናችንም ለድል ዋዜማ ባይተዋር አትሆንም። ታተርፋለች።
፫ ተዋህዶ በሁለገብ ብቃት ሃብታም ናት። ስለሆነም በዲፕሎማሲዉ መስክ ጉልህ ሚና ለመጫወት መሁራን ልጇቿን በአግባቡ የምታሰማራበት በር ቢኖራት ህልሜ ነው። ይህን የከፋ ዘመን ዕንባ ለመጋራት የሃብት ሃብት የሆነውን የሰው ኃይሏን ለማንቀሳቀስ አለን የሚባልለት ስምሪት ቢኖራት መልካም – ይመስለኛል። በልቶ ማደር ብቻውን ወይንም አማኝነት ብቻውን የሀገርን ክብር አይወክልም። ውርዴትን ደማችን ሊጸየፈው ይገባል – እላለሁ። ጠንከር ያለ፤ ቋት የሚገፋ ተግባር ከቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ጉልበታምና ሳቢ ተግባር ማዬትን – እናፍቃለሁ። ነፃነት „ሰውን“ ማዕከሉ ያደረገ የኔነት የማንነት ሃይማኖት ነውና።
ዬእኔ ክብረቶች – ከስንብት በፊት የሰማዕቱ ቅዱስ አባታችን የአደራ ዓይን መስከረም 5. 2015 በሲዊዘርላንድ ዙሪክ ከተማ ቃናቸውን – ቃላቸውን ማድመጥ ለምትፈቅዱ Tsegay Radio or www.tsegaye.ethio.info Aktueall Sendung የ10.09.2015 የጸጋዬ ራዲዮ ዝግጅት አርኬብ ላይ ማዳመጥ ትችላላችሁ። እርግጥ አዳራሽ ውስጥ የተቀዳ ስለሆነ ትእግስታችሁን – እጠይቃለሁ። ተከታዩን በሚቀጥለው ዝግጅቴ – ይቀርባል። ጉባኤው የመንፈስ ሃዲድ – ነበረው። እንዲህ ዓይነት ሁለቱንም ፅኑ ፍላጎቶቼን ኪዳኑን የፈቀደልኝ ጉባኤ ገጥሞኝ – አያውቅም። እኔ ብሄራዊ ብቻ ሳይሆን ዓለምዓቀፋዊዎችንም – ጉባኤዎችን አይቻቸዋለሁ። የ05.09.2015 ፍጹም ልዩ ነበር – ለበጎ ነገሮች ራህብተኛዋ – ለእኔ።
ለእኔስ ሰው መሆኔ ብቻ ይበቃኛል።
ወስብሃት ለእግዚአብሄር።