ከዘኢትዮጵያ ጋዜጣ የተገኘ
አቶ በረከት ለትልቁ የኢህአዴግ ጉባኤ እንኳ ወደ መቀሌ አልሄዱም። የድርጅቱ አካሄድ የተያዘው አቅጣጫ አልተስማማኝም ብለው መቅረታቸው ተሰምቷል። ወዳጆቻቸው እነ አቶ አባይ ፀሐዬ በመተካካቱ የወጡ ሲሆን በረከት ግን በገዛ ፍቃዳቸው መልቀቃቸው ተነግሯል። በብአዴን (ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት እንኳ ቢመረጡ ጨርሰው እንደማይቀበሉትና ከድርጅቱ ማናቸውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ተቆጥበው መቀመጥን መምረጣቸው ተገልጿል። አቶ መለስ ከሞቱ ወዲህ እንደነገሩ ሆነው ቢቆዩም፣ ራዕይ አስፈጻሚ፣ ወራሽ አውራሽ ሆነው ለመቀጠል ፍላጎቱ እንደነበራቸው አጀማመራቸው ያስታውቅ ነበር። አቶ መለስ ሲሞቱ እንዲህ ብለው ነበር፦
መለስን ሕይወቱ ከማለፉ ከአምስት ቀናት በፊት በስልክ አግኝቼ ስለ ጤንነቱ ጠይቄው ነበር፡፡ አስከፊውን ዜና የሰማሁት ሕይወቱ ባለፈ ጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ነው፡፡ በአጋጣሚ አጠገቡ አልነበርኩም፡፡ ተደወለልን፡፡ ከእንቅልፋችን ተቀስቅሰን ተሽሎታል የሚለውን ወሬ ሰምተን ስለነበር ተዝናንተን መተኛት ጀምረን ነበር፡፡ እና የመጨረሻዎቹ ቀናት ላይ ነው ችግር ያጋጠመው፡ ፡ ሲቀሰቅሱኝ ባልተለመደ ሰዓት ነበር፡፡ 5፡40 ላይ ሕይወቱ አልፎ 6፡10 ላይ ተቀሰቀስኩ፡፡ በዚህ ሰዓት ላይ የሚቀሰቅሰኝ ሰው ስላልነበረ “አቶ መለስ አርፏል” ማለት ነው የሚል ነገር ተሰማኝ፡፡ ያኔ በአንድ በኩል ባዶነት ተሰማኝ፤ በአንድ በኩል ደግሞ ትልቅ ኃይል ተሰማኝ፡፡ የዚህን ሰውዬ ራዕይ እንደ ኢሕአዴግ በቡድን ማሳካት አለብን የሚል ብርታት ሰጠኝ፡፡ እኔ አቶ መለስን እስከመጨረሻዋ ሰዓት ድረስ እየሠራ ነው የማውቀው፤ እየታገለ እየደከመ ራዕዩን እውን ለማድረግ ሲሠራ ነው የማውቀው፡፡ ሳጣው ባዶነት ብቻ አይደለም የተሰማኝ፤ ከፊቴ ሆኖ ሁሌም ወደፊት የሚጎትተኝ እንድሠራ የሚገፋፋኝ አሁንም ከጎኔ እንዳለ ነው የተሰማኝ፡፡
አሁን ያ ስሜት ምን ሆነ? ምናልባት ለመለስብቻ ሲታዘዙ የኖሩት አቶ በረከት አሁን ከቀሩት የሕወሓት ኢህኢሃዴግ “ትርክምርኪዎች” ውስጥ ከፊት ሆኖ ወደፊት የሚጎትታቸው፣ ለሥራ የሚገፋፋቸው አንድም ሰው አላገኙ ይሆናል። እንኳን ብአዴን ወያኔ መባል ያኮራቸው የነበረው የኢህአዴጉ አቶ በረከት አሁን ዛሬ ላይ ደርሰው ሁሉ ነገር የደበራቸው መስልዋል። በፊትማ ለምሳሌ ሕወሃት 40ኛ ዓመቱን ሲያከብር፦
“እኛ ብአዴኖችም ሁሌም ቢሆን ራሳችንን ከህወሓት ነጥለን ያየንበት ጊዜ የለም። ሁላችንም “ወየንቲ ኢና” (ወያኔዎች ነን) ነው የምንለው።” ብለው የነበሩት አቶ በረከት ሰምዖን ወ/ገሪማ ዛሬ ማንንም መሆን አልፈለጉም።
ሰውየው በትውልድ ጎንደር በውልደት ከኤርትራ፣ በምልምል ከኢህአፓ፣ በድርጅት ከብአዴን በተጋድሎ ከወያኔ ሆነው እዚህም እዚያም እንደ ጆከር ሲሳቡ የኖሩ ሰው ናቸው።
ባንድ ወቅት፣ ህወሓቶች ጫካ በነበሩ ጊዜ፣ አቶ መለስ በሚገኙበት የፖለቲካ ጽ/ቤት ውስጥ፣ ከሳቸው ጋር የፖለቲካና በተለይም የፕሮፖጋንዳ ሥራውን በኃላፊነት የሚሠሩ ጥቂት ሰዎች ነበሩ። አቶ መለስ ዜናዊ፣ አቶ ዓለምሰገድ ገ/አምላክ (በክፍፍሉ ጊዜ የወጡት) አቶ አማረ አረጋዊና አቶ በረከት ሰምዖን ይገኙበታል። እንደሚባለው በአቶ መለስ ዜናዊና በአቶ በረከት ሰምዖን መካከል መቀራረቡ የተጀመረው ከዚያን ጊዜ አንስቶ ነው። ይበልጥ የተቀራረቡት ደግሞ በክፍፍሉ የፓርቲው የርዕዮተ ዓለም ሰው አቶ ዓለምሰገድ ከወጡ በኋላ ይመስላል።
ከዚያን ጊዜ አንስቶ አቶ መለስ የሚናገሩት አቶ በረከትን፣ አቶ በረከትም የሚያስፈጽሙት አቶ መለስን እየሆነ አንበደትና ጆሮ ሆነው ቀጥለዋል። ኢህአዴግ ውስጥ አቶ በረከትን ያለ አቶ መለስ ማሰብ አለመቻሉ እርግጥ እንደሆነ ሁሉ፣ አቶ መለስንም በረከት ማሰብ ቀላል አይደለም። መለስን በመሸጥ፣ በእያንዳንዱ ካድሬ ውስጥ በማስረጽ፣ አፈ ጮሌ ካድሬዎችን በመመልመል፣ የሕግ ባለሙያዎችን በተለይ ዳኞችን በመዘወር፣ የሚዲያ ተቋማትን በማሽከርከር፣ ባንኮችን በቦርድ በማስተዳደር፣ የኢህአዴግና የአቶ መለስ ትልቁ ባለውለታ ናቸው። አዳዲስ የሚበቅሉ የተቃዋሚ ድርጅቶችን ከስር ከስር እየተከታተሉ በመንቀል፣ በተለይም የግል ሚዲያዎችን በማዘጋትና ጋዜጠኞቻቸውን በማሰር ከአገር እንዲሰደዱ በማድረግ ነቃፊውን እየነቀሉ ደጋፊዎቻቸውን እየተከሉ የህወሓት ኢህአዴግን እድሜ ያሰነበቱ ሰው ናቸው። ያውቁታልና ግን አይሆኑ የሆኑለት ድርጅታቸው ካሁን በኋላ ብዙ ርቆ የሚሄድ አልመሰላቸውም።
በረከት ትግርኛ ተናጋሪነታቸው ተጨምሮበት ብአዴንና ሕወሓት ውስጥ እየዘለሉ፣ መለስን ተደግፈው የሁለት ቤት ቤተኛ ነበሩ። አዛዥ ናዛዥ ሆነውም ኖረዋል። ወያኔዎቹ እኛ “ብአዴን” ነን አይበሉ እንጂ፣ እነ አቶ በረከት “ወያኔ ነን” ማለታቸው አይገርምም። በረከት ወያኔ ብቻ ሳይሆኑ ከተወሰነ ጊዜ በኋላም ወያኔዎችን ሳይቀር ሲያሾሩ የነበሩ ሰው ናቸው። በተለይ አቶ መለስ እንደቃታ ሲስቧቸው እንደ ጥይት እየተወነጨፉ ተቃዋሚዎቻቸውን ሲነድሉ ኖረዋል። ከበረሃ ጀምሮ የህወሃቶቹን አማርኛ ባማቅናት፣ የኢህአዴግ መግለጫዎችን በማዋዛት ቃል እያመነጩ ሲረጩ ሲያስረጩ የኖሩ ሰው ናቸው። “ኢሕአዴግ አስተዋይ እና አገሪቷን ከእንቅልፏ የቀሰቀሰ ድርጅት ነው” በማለትም ድርጅታቸውን የሚያሽሞነሙኑትን የአቶ በረከትን ውለታ ህወሓት/ ኢህዴጎቹ መቸም የሚረሱት አይሆንም። የኢህአዴጎቹ ክህደት እንደተጠበቀ ሆኖ በአገልግሎት ዘመናቸው አቶ በረከት ብዙ ጠላቶችን ያፈሩ በመሆናቸው ባላንጣዎቻቸው ብዙ ናቸው።
በተለይም በሕወሓት ካድሬዎችና ደጋፊዎች ዘንድ፣ በኤርትራ ተወላጅነታቸው ስለሚታወቁ፣ በሳቸው ላይ የሚሰነዘረውን ጭፍን ጥላቻ ለማንበብ የትኛውንም የህወሃት ካድሬ ጎተት አድርጎ ስለ አቶ በረከት መጠየቅ በቂ ነው።
በረከት ግን ለህወሓቶቹ እንደሱ አይደሉም። የማለዳው የትግል አጋራቸው አቶ ያሬድ ጥበቡ፣ ጥር 11/2004 ፍትህ ጋዜጣ ላይ እንዳስነበቡንና አቶ በረከትም በሁለት ምርጫዎች ወግ መጽሐፋቸው ቀዳሚ ገጽ ላይ እንደገለጸሉን፣ ካህሳሁን ገብረ ሕይወት የሚባል ታላቅ ወንድም ነበራቸው። በወያኔዎቹ ስለተገደለው ካሣሁን አቶ ያሬድ እንዲህ ብለዋል፦
ካሳሁንን በኢህአፓ ሰራዊት ውስጥ አውቀው ነበር ፡፡ እጅግ ተወዳጅ ሰው እንደነበር ትዝ ይለኛል ፡፡ ታዲያ ተሓህት ‹‹ትግሬ ለትግሬዎች ፣ የትልቋ ኢትዮጵያ (በትግርኛ ዓባይ ኢትዮጵያ ይሉታል) ህልመኞች ከሃገራችን ውጡ›› ብሎ ድንገት በከፈተብን ጥቃት ካሳሁን ውጊያ ላይ ተማረከ ፡፡ ከጠባቂዎቹ አምልጦ በአካባቢው ወደነበረችው የጀብሓ አሃዱ አስጥሉኝ ብሎ ሲሮጥ የወያኔ ዘቦች በጀርባው ባወረዱበት የመትረየስ ጥይት ተመትቶ እንደተሰዋ አሳዛኙ ዜና ደረሰን ፡፡ አዎን ካሳሁን ‹‹ትግራይ የኢትዮጵያ አይደለችም፣ የአማራና የትግሬ ለማኞች አብረው መለመን እንኳ አይችሉም›› ብለው የትግራይን ህዝብ ይቀሰቅሱ በነበሩ ጠባብ ብሄርተኞች እጅ ነበር የወደቀው ፡፡ ታዲያ በ1992 ህወሃት አመራር ውስጥ ክፍፍል ሲፈጠር፣ በረከት የመለስ አዳኝ ሆኖ የቆመ በመምሰል የወንድሙን ገዳዮች በከፊል የተበቀላቸው ነበር የመሰለኝ ፡፡ ሆኖም እዚህ የመጀመሪያ ገፅ ላይ ወንድሙን ካሳሁንን ‹‹እነሆ በተለምክልኝ መንገድ እጉዋዛለሁ›› ሲል፣ በረከት ከጠባብ ብሄርተኞች ጋር የሚያደርገው ትግል አሁንም የቀጠለ መሆኑን ነው ሹክ የሚለን ፡፡
ተስፋዬ ገ/አብ በሌላ ጽሑፍ እንደገለጸው ደግሞ የአቶ በከረት ስምዖን እውነተኛ ስም መብራህቱ ገ/ሕይወት ሲሆን አቶ በረከት ለራሳቸው ያወጡት ስም በኢህአፓ አባልነቱ ተገድሏል ብለው ካሉት ከእውነተኛው አቶ በረከት ሰምዖን የወሰዱት ስም ነው። እንደ አጻጻፉ ከሆነ ሞቷል የተባለው ሌላኛው በረከት ሰምዖን አሁንም አውሮፓ ውስጥ በህይወት ያለ ሲሆን ወንድምና እህቶቹም የኤርትራ ባለሥልጣናት ሆነው ይሠራሉ።
ከተወሳሰበው ህይወታቸው ሌላ፣ የተወሳሰበው የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑት አቶ በረከት፣ አቶ ያሬድ እንደሚጠቅሱላቸው በሙስና አይታሙም። “በረከትን ቀረብ ብለው ያዩት ሁሉ የሚመሰክሩለት አንድ ነገር ቢኖር ‹‹ከምቀበርባት ስድስት ክንድ መሬት በቀር ሌላ ሃብት አልፈልግም’ ማለቱን ነው” ካሉ በኋላ “የነዚህን ሁሉ አንድምታ ወደፊት የምናየው ይሆናል ፡፡” ብለዋል። አቶ ያሬድ እንዳሉትም የአቶ በረከት ሃብት ወደፊት የሚታይ ይሆናል። የጤና እክል እንዳለባቸው የሚነገረው አቶ በረከት ግን “እኔን የሚያሳስበኝ የጤናቸው ጉዳይ ነው፡ ፡” እያሉ ባለሥልጣናትን በኃላፊነት መንከባከባቸውን የሚገልጹት ሼኽ መሀመድ ሁሴን አል አሙዲ፣ በአቶ በረከት መጽሐፍ ምረቃ ላይ እንዲህ ብለው ነበር፦
“አቶ በረከት እንዳለው ደቡብ አፍሪካ ሄጄ ጠይቄዋለሁ፤ የጠየኩት ግን አመፀኛ እና ልውጣ
ብሎ ስለሚያስቸግር ነው፡፡ ታከም፣ እረፍ ሲባል እሺ አይልም፡፡ እኔ ደቡብ አፍሪካ ሄጄ መጀመሪያ ያደረኩት ክፍሉን በሴኪዩሪቲ ማስከበብ ነበር፡፡ እሱ ግን በኋላ የብአዴን 25ኛ ዓመት በዓል ላይ ካልተገኘሁ ብሎ አስቸገረ ቃል አስገብቼ ይዤው መጣሁ፡፡ በ48 ሰዓት ውስጥ አንጠልጥዬ መለስኩት፤ እኔን የሚያሳስበኝ የጤናቸው ጉዳይ ነው፡፡”
በሙስና የማይታሙት አቶ በረከት ያሻቸውን በፈለጉ ጊዜ ግን የሚያዙት ቢሊየነር አላቸው። “አላሙዲን ጠይቄው አሳፍሮኝ አያውቅም” በማለት በመጽሐፋቸው ምረቃ ቀን እንዲህ ብለው ነበር ፦
“የእኔ ሥራ መጽሐፉን መጻፍ ብቻ ነበር፡፡ አልአሙዲ እንዲያሳትመው መመሪያ ብቻ ነው የሰጠሁት፡
፡ ደወልኩ እና እነዚህን መጽሐፎች ታሳትማቸዋለህ አልኩት” በማለት መጽሐፉን ከኢትዮጵያ ውጪ ከማሳተም ጀምሮ እንዲያ ባለ በደመቀ ሥነ ሥርዐት እንዲመረቅ የማድረግ ወጪውን ሼኹ እንደሸፈኑ መግለጻቸው በወቅቱ በአዲስ አድማስ ተመዘግቧል፡፡ ህመም ገጥሞኝ ደቡብ አፍሪካ ለሕክምና በሄድኩ ጊዜ እዛ ድረስ መጥቶ ጠይቆኝ ነበር፡፡ የልብ ወዳጆች ነን፡፡ አሊ አልአሙዲ ወሬኛ ነው፡፡ ጨዋታ ይወዳል ውጭ አገርም ሄዶ ቢሆን ሦስት ቀን አያድርም፤ ይደውላል፤ ደውሎም ቀልድ አዋቂ ነው ተሳስቀን ነው የምንለያየው፡፡ አሊ አልአሙዲ ሣቅ እና ዕድሜህን ያብዛልህ” በማለት ምርቃቱን አውርደውት ነበር፡፡
እንግዲህ አሁን አቶ በረከት ፖለቲካውም በቃኝ ወደማለቱ መምጣታቸው ተሰምቷል። ወይም ፖለቲካውም እንደ እሳቸው ያሉትን በቃኝ ብሏቸው ሊሆን ይችላል። ለማንኛውም በዓይን ጥቀሻ ብቻ ይጠሯቸው የነበሩ ግልገል ካድሬዎቻቸው አገር ሲመሩ ወይም ሲያደናብሩ እያዩ የሥራ ፍሬያቸውን በትዝታ ይቃኙት ይሆናል። እስከማኩረፍ ያደረሳቸው የሁኔታዎች መበለሻሸት ግን፣ በቃ ከእንግዲህ ኢህአዴግ በረከት የለውም ሳያሰኛቸው አይቀርም።