Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የጠንቋይ ፖለቲካ  -ከከተማ ዋቅጅራ

$
0
0

ethiopia_detail_mapሰይጣን በባህሪው ፍቅር፣ መስማማት፣ መዋደድ፣ መከባበር፤ አይወድም። በተገላቢጦሽ ጥላቻን፣ መለያየትን፣ መጣላትን፣ በገዳደልን፤ ይወደዋል። ጠንቋይ የሰይጣን አገልጋይ ስለሆነ ወደሱ የሚመጡትን በሙሉ ዙሪያቸው በጠላት እንደተከበቡ አድርጎ ይነግራቸዋል። በግራ በኩል ያሉት ጎረቤትህ  አንተን ለማጥፋት የተነሱ ናቸውና ተጠንቀቃቸው ይለዋል። በቀኝ በኩል ያሉት ጎረቤቶችህ ያንተን እድል ጥርግ አድርገው ወስደውብህ እንዳታድግ  ያደረጉህ እነሱ ናቸውና ማርከሻው እኔ ጋር ስላለ እሰጥሃለው ሌላ ግዜ ግን ወደነሱ መንደር እንዳትሄድ እራቃቸው ይለዋል። በፊለፊት ያሉት ጎረቤቶችህ ደግሞ ሃብት እንዳይኖርህ ሰርተህ እንዳታድግ ተምረህ እንዳትራቀቅ በማድረግ አስረውህ የያዙህ እነሱ ናቸውና ሽሻቸው ይለዋል። በኋላ በኩል ያሉትን ጎረቤቶቹን ደግሞ በልጆችህ እንዳትደሰት ባለህ ባህል እንዳትኮራ በትዳርህ ደስተኛ እንዳትሆን ቤትህን የሚያተራምሱት እነሱ ናቸውና ሽሻቸው አሽሻቸው ይለዋል። ከፊት ከኋላ ከግራና ከቀኝ ከምስራቅ ከምዕራብ ከደቡብ ከሰሜን ያሉት በሙሉ ጠላት ናቸውና እራቃቸው፣ አርቃቸው፤ አትቅረባቸው፣ ተጠንቀቃቸው፣ አጥፋቸው፤እያለ ጠንቋዩ ደጋግሞ ስለሚነግረው ምንም የማያውቀው የጎረቤት ሰዉ በገቡ በወጡ ቁጥር ከጠንቋዩ በተነገረው የማጠፋፋት መልዕክት የመበታተን አጀንዳ ጥርስ እየተነከሰባቸው የጎሪጥ እየታዩ እንዲኖሩ ይደረጋሉ። ከባዱ ነገር እና ትልቅ ስህተት የሚሆነው በጠንቋይ ፖለቲካ አራማጆች የሚተላለፈው መልዕክት በመቀበል ወዳጅ የሆነውን ህዝብ ጣላት፣ አንድ የሆነውን ህዝብ ሁለት፣ የተቀራረቡትን ህዝብ ማራራቅ፣ የተዋደዱትን ህዝብ ማጣላት፣ አደጋው ለራስ ነው። ወዳጅ የሆነው ህዝብ በፍቅር የሚኖረውን ህዝብ በግድ ጠላት ነህ ጠላት ነህ እየተባለ ሲነገረው ዝም ያለውን ህዝብ በመነካካት የተነሳ እንደሆነ ጥቂት የጠንቋይ ፖለቲካ አራማጆች እና ተከታዮቹ ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል ነውና በጥልቀት ሊታሰብበት ይገባል።

ወያኔና ሻብያ በጠንቋይ ፖለቲካ አካሄዳቸው ለግዜው በሆነ ከሁለት አስር አመታት በላይ በስልጣን ቆይተውበታል። እዚህ ጋር ለኤርትራ ህዝብ ጥቂት ጥያቄዎችን ጣል አድርጌ ልለፍ። ሻብያ የኤርትራ ጠላት ኢትዮጵያ እንደሆነ ደጋግሞ ለትውልዱ ይነግራቸዋል ኢትዮጵያ ከኤርትራ የሚፈልጉት ወርቋንና ቀይ ባህርን ነው ህዝቧን ግን አይፈልጉም በማለት ህዝቡ ለኢትዮጵያ መጥፎ አመለካከት እንዲኖረው አድርጓል። በቅርብ ኢሳያስ አፍዎርቄ በኢሳት ጋዜጠኖች በቀረበለት ጥያቄ ግን የንስሃ ያህል ትንሽ ተናግሯል የኢትዮጵያ ህዝብ እና የኤርትራ ህዝብ የትኛውም ፖለቲከኛ ቢመጣ አይለያዩም የሚል ጣል በማድረግ አስምቶን የኤርትራ ጠላት ወያኔ ነው እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ አይደለም ብሏል። ይሄ ጥሩ ጅማሬ ነው የኢትዮጵያም የኤርትራም ጠላት ወያኔ ከሆነ አንድ የጋራ ጠላት አለን ማለት ነውና መደጋገፍ ይቻላል ማለት ነው። ጥላቻን በማስተማር የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚደረግ ሩጫ ጉዳት ለራስ ነው ይታሰብበት።

ጥያቄ፡- የኤርትራ አባት  እና  እንቶቼ ወንድም እና እህቶቼ ኤርትራ ነጻ ወታለችን? የጀብሃ እና የሻቢያ የ30 አመት የትግል ውጤት ሊያመጣ የተፈለገው ነጻነት እንደዚ አይነቱን ነውን? ኤርትራ  ውስጥ ደርግ ስልጣን ላይ በነበረበት ግዜ ከሚሞተው ህዝብ ቁጥር አሁን በዘመነ ሻብያ ግዜ መቶ እጥፍ ለምን ጨመረ? በደርግ ዘመን ተቸግሮ አገሩን ጥሎ ከሚሰደደው ኤርትራዊ በዘመነ ሻብያ ግዜ በመቶ እጥፍ ለምን ጨመረ? በደርግ ግዜ በዩኒቨርስቲ ደረጃ ተምረው ከሚመረቁ የኤርትራ ተማሪዎች በዘመነ ሻብያ ግዜ ለምን በመቶ እጥፍ ቀነሰ? ተተኪው ትውልድ ካልተማረ  ነገ አገሪቷን የሚረከባት ዜጋ ምን አይነት ሊሆን ይችል ይሆን? በኤርትራ አገር ላይ ወደፊት ሊመጣ የሚችለውን ቀውስ ቆም ብሎ ያስተዋለ  ኢርትራዊ ይኖር ይሆን? ካለስ ዝምታን የተመረጠው እስከመቼ ነው?  እዚህ ጋር ደርግ ይሻላል እያልኩኝ ሳይሆን በሁለቱ መንግስት ዘመን ያለውም በህዝቡ ላይ የነበረውን ሁኔታ ማነጻጸሬ እንደሆነ ይታወቅልኝ። ብቻ ብዙ አልገባበትም ምናልባትም በሌላ ግዜ አስፈላጊ ሆኖ ከታየኝ በሰፊው ልመለስበት እችላለው አሁን ግን የኛ ችግር ገዝፎ እና ጎልቶ ስላለ ወደዛ እሄዳለው።  ልናገር የምፈልገው ኢትዮጵያኑ ስለ ኤርትራ መናገር የምንፈልገው የኤርትራን የማእድን ሃብቷን ፈልገን አይደለም የራሳችንንም ሃብት በአግባቡ አልሰበሰብን እንኳን የሰው ልንመኝ ነገር ግን የወንድም እና የእህትነት ፍቅር ግድ ብሎን እንጂ ሃብትና ንብረቷን የሚመኝ ማንም ኢትዮጵያዊ የለም።

የጠንቁይ ፖለቲካ በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ውስጥ ለማስረጽ ሃያ አራት አመት ሙሉ እየተሰራበት ጉዳይ ነው። ወያኔም ስልጣኑ ላይ እስካለ ድረስም ይገፋበታል። የትግሬ ጠላት አማራ፣ ኦሮሞ፣ ደቡቡ፣ ሱማሌው፣ አፋሩ፣ ጋንቤላው፣ ነው። የኦሮሞ ጠላት አማራ፣ ሱማሌው፣ ደቡቡ፣ ጋንቤላው፣ አፋሩ፣ ነው። የአማራው ጠላት ኦሮሞው ፣ ሱማለው፣ ደቡቡ፣ አፋሩ፣ ጋንቤላው ነው። የደቡቡ ጠላት ኦሮሞ፣ አማራ፣ ሱማለው፣ ጋንቤላው፣ አፋሩ ነው ……. ይሉናል።  በሰላምና በፍቅር ይኖር የነበረውን ህዝብ በጠላትነት እየሰየሙ ባሰመሩት የሞት መስመር ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ ወዳጅ የነበሩት ህዝቦች እና አንድ የነበረውን ህዝብ እንደ ጠላት እንዲተያዩ  የሚያደርግ  የጠንቋይ ፖለቲካ አካሄድ ነው።

ውሸት ሲበዛ ተደጋግሞም ሲነገር እውነት ይሆናል ብለው የሚያምኑ ሰዎች የጠንቋይ ፖለቲካቸውን ሲነግሩት ምንም በማያውቀውን ህብረተሰብ ላይ ብዝታን መፍጠሩ አይቀሬ ነው። በአሁኑ ሰዓት እውነት ዝምታን መምረጥ የለበትም። ዝምታ መልስ በማይሆንበት ቦታ ላይ የግድ መናገር ያስፈልጋል። እውነትን እየሻሩ በምትኩ ውሸትን የሆነውን የጠንቋይን ፖለቲካ በአንድም በሌላም ሁኔታ ለህብረተሰቡ እየተሰበከለት ባለበት  ሁኔታ እውነተኞች ዝምታ ከቶውኑ መልስ ሊሆን አይችልም። እውነትን እና እውነተኞችን እያጠፉ ሃሰት  እና ሃሰተኞችን በተለያየ መድረክ አግዝፎ መናገር ምን ያህል ከባድ ግዜ ላይ እንደደረስን የሚያሳይ ነውና ያልነቃህ ንቃ የተኛህም ተነሳ እውነትን ይዘህ ዝምታ ይብቃ። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አንድ ህብረተሰብ በሌላው ህብረተሰብ ላይ ጠላት ሆኖ የተነሳበት ወይንም ለመጠፋፋት የሞከሩበት ግዜ የለም። የጠንቋይ ፖለቲካ አራማጆች እንደሚሉት አንዱ ህብረተሰብ ሌላውን ህብረተሰብ የማጥፋት ፍላጎት ኖሮት ቢሆን ኖሮ ዛሬ ኢትዮጵያ  ውስጥ ከሰማኒያ በላይ ቋንቋ ተናጋሪ ሊገኝ ባልቻለ  ነበረ መላው ኢትዮጵያዊ አንድ ቁንቋ አንድ እምነት አንድ ዘር ሆኖ በቀረ ነበረ። ነገር ግን የሚታየው እውነት ግን የጠንቋይ ፖለቲከኞች አራማጆች እንደሚሉት ስላልሆነ እውነቱ ሊገለጽ በሰፊውም ሊነገር ይገባል። የጠንቋይ ፖለቲካ አራማጆች በሙሉ ላደረሱት ጉዳትም  በህግ ሊጠየቁ ይገባል።

ግዜው ወሳኝ የትግል ሰዓት ላይ አድርሶናል። ስንዴው ከገለባው እውነተኛው ከሃሰተኛው የሚለይበት ግዜ ላይ ነን። ጣልያን ኢትዮጵያን መውረር በምትፈልግበት ግዜ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ስትደርስ ዋና ዋና የተባሉትን ሰዎች በአደባባይ በመግደል ህዝቡ ፈርቶ ይገዛልኛል በሚል ህሳቤ አረመኔአዊ ድርጊት በንጹሃን እና በጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ላይ በአደባባይ በመፈጸም እንዳሰቡት ሳይሆን ጭራሽ በመላው ህዝብ መሃል ቁጣና እልህ ተቀጣጠለ። በኢትዮጵያን መሃል ባንዳዎችን መልምለው የክብር ሊሻን በመሸለም የኢትዮጵያን ህዝብ ለማሸማቀቅ ቢሞክሩም ጣልያንም ድረስ ወስደው የስልጣን ካባ በመደረብ አሞግሰው ህዝባችንን እንዲሰልሉላቸው በመላክ መረጃዎችን ቢያገኝም የኢትዮጵያኑን ጀግንነት ግን ሊቋቋሙት ባለመቻላቸው ከሽንፈት አላዳናቸውም።

አሁን የኢትዮጵያ ሁኔታ መጨረሻው ምዕራፍ ላይ እየተቃረብን ስለመጣ የጠንቋይ ፖለቲካ በኢትዮጵያ  ውስጥ መቀበሪያው አፋፍ ላይ መድረሱን ምልክቶች እየታዩ  ነው። እውነት በአደባባይ የሚነገርበት ሃሰትም በአደባባይ የሚገለጽበት ግዜ ተቃርቧል። ከአሁን በኋላ የተጀመረው ትግል ወደፊት እንጂ ወደኋላ የሚል የለም። የኢትዮጵያ እውነተኛ ታጋዮች እና የጠንቋይ ፖለቲካ አራማጆች ሁለት የትግል አምድ ተተክለዋል። አንዱ ሊወድቅ የተቃረበው ሌላው  በጽናት ሊቆም የተቃረበው። ግዜው የምርጫ ነውና  በተግባር ተገልጾ የሚታይ ምርጫ። ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን በሰላም፣ በደስታ፣ በፍቅር ማኖር አልያም ኢትዮጵያን እያዘረፉ፣ እያበጣበጡ፣ እንዲኖሩ የመፍቀድ ምርጫ። ከዘላለም ባርነት ታግሎ ለራስ እና ለአገር ነጻነት የምናመጣበት ግዜው አሁን ነው።

ሞላ አስግዶም ከተወሰኑ ሰራዊቶች ጋር ከጠንቋይ ፖለቲካ አራማጆች ዘንድ ተቀላቀለ ተብሎ መነገሩ ምንም አይነት መረበሽን አይፈጥርም። ምክንያቱም ሰዓቱ የምርጫ ነውና ወይ ኢትዮጵያዊ መሆን አልያም የጠንቋይ ፖለቲካ ተከታይ መሆን ምርጫው ይሄ ነው። ምነዋ ጀነራል ከማል ገልቹ ሰራዊቶችን አስከትሎ  ወያኔን አልከዳም እንዴ። የአየር ኃይል አባላቶች ከተዋጊ ሄልኮፕተር ጋር ክደው አልሄዱም እንዴ ዛሬስ ወያኔ ውስጥ ያለው መከላከያ ሰራዊት አጋጣሚውን እየጠበቀ የጠንቋይ ፖለቲካ ጥለው በመውጣት ከኢትዮጵያ ታጋዮች ጋር በመሆን ትግሉን በአጭር ግዜ  ውስጥ የኢትዮጵያ የነጻነት ብስራት መንገሪያ የጠንቋይ ፖለቲካ መጥፊያ በጋራ እንደሚያደርሱት የማያውቅ ማንም ኢትዮጵያዊ የለም። ያኔ የጠንቋይ ፖለቲካ  አራማጆችን ማየት ነው  እውነት በነገሰበት ሃሰት ለመቆም ሃይል የለውምና ሁሌም ኢትዮጵያ እና ህዝቧ አሸናፊዎች ናቸው።

ከእንግዲህ ጥቂት ጥቅመኞች ለመጥቀም ተብሎ በሱማሌ አገር  የሚገደል ንጽህ የኢትዮጵያ ወታደር እንዳይኖር፣ ከእንግዲህ አገር ጥሎ  በመሰደድ በየበረሃው የሚሞት ወገን እንዳይኖር፣ በአረብ አገር በስቃይ እና በግፍ የሚገደሉ ወገኖች እንዳይኖሩ፣ ጥቂቶች ጠግበው ብዝኋኑ ተርበው የሚኖርበት አገር እንዳይኖረን፣ ታናሽ ታላቁን ታላቅ ታናሹን፣ ባለስልጣን ተራውን ተራውም ባለስልጣኑን በማክበር በህግ በመተዳደር የህግ የበላይነት ተከብሮ ማየት ከፈለግን…..ወታደር፣ አስተማሪ፣ ተማሪ፣ ገበሬ ፣ ሰራተኛ፣ ነጋዴ፣ ሴት፣ ወንድ፤ ሳንል ትግሉን በመቀላቀል በገጠር በከተማ፣ ከመሃል እስከ ዳር ተነስተን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ግዜ የጠንቋይ ፖለቲካን በኢትዮጵያ ምድር ማጥፋት ያለብን ግዜ አሁን ነው። የተጀመረው ትግል  ማንም ቢከዳ ታላላቅ ታጋዮችን ይዘው የፖለቲካ ስራ ቢሰሩባቸው የጠንቋይ ፖለቲካ የጣር ጩኽት ነውና ከእንግዲ በኋላ ወደ ኋላ ሳይሆን ወደ ፊት … ወደ ፊት… ወደ  ፊት… ነው።

ፍቅር እና እውነት የሰው ልጅን  ሁል ግዜ በነጻነት የሚያኖሩት ናቸው። ትግሉን በመደገፍ መሰናክሎችን በማስወገድ ህዝባችንን ከጠንቋይ ፖለቲካ ነጻ እናውጣ።

 

ከተማ ዋቅጅራ

19.09.2015

Email- waqjirak@yahoo.com

 

 

 

 

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>