ራዕይ ለበጎ ነገርና ራዕይ ለመጥፎ ነገር ብለን እንመልከት። የሀገር መሪዎች ለሀገራቸው በጎ ነገር ለመከወን መልካሙን ራዕይ ሰንቀው በመነሳት በኣካባቢያቸው ለተቀየሰው በጎ ነገር የመልካም ተግባር ራዕይ ያላቸውን ኣሽከሮቻቸውን ሳይሆን የሥራ ባልደረቦቻቸውን መርጠው በመያዝ ክንውኖቻቸውን ይቀጥላሉ። በተቃራኒው የቆሙ መሪዎች ደግሞ መጥፎውን ተግባሮቻቸውን ከሚመርጧቸው የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ይያያዙታል።
የትግራይ ሕዝብ ነፃ ኣውጪ ግንባር ቀንደኛ መሪ መለስ ዜናዊ ኣስረስ ኢትዮጵያን ለመበታተን፣ ለማፈራረስ፣ ለመቆራረስ፣ ኣሳልፎ ለመስጠት፣ ለማስማማትና ለመሸጥ ራዕይ ነበረው። ሲተገብር ነበር፣ ጀሌዎቹም እየተገበሩት ነው። መለስ ዜናዊ ኣስረስ ኢትዮጵያውያንን ለመግደል፣ ለማፈናቀል፣ እንደ ሸቀጥ ለመሸጥ ራዕይ ነበረው፣ በተግባር ኣሳይቷል። ያሰለጠናቸው ካድሬዎቹም በተተለመው መሠረት እንደሚተገብሩ ቃል ገብተው ትግበራውን ተያይዘውታል። መለስ ዜናዊ ኣስረስ ለኃያላን መንግሥታት ተላላኪ ለመሆን፣ ሀገሪቷን ከሳሎን እስከ ማዕድ ቤት ድረስ እንዲዝናኑበትና በዋናው በር ሰተት ብለው ግብተው በጓሮ በር እንዲወጡና ኣዛዥና ኣናዛዥ እንዲሆኑ ኣድርጓል፣ እያደረገም ነበር። ጀሌዎቹም ቀጥለውበታል። መለስ ዜናዊ ኣስረስ የሀገርን ሀብት መዝረፍ፣ መሸጥና ማስወሰድ ራዕዩ ስለነበር በተግባር ኣሳይቷል፣ በጀሌዎቹም ተቀጥሎበታል። መለስ ዜናዊ ኣስረስ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ኣዋርዷል፡ ኣታሏል። መለስ ዜናዊ ኣስረስ ዘርን ለይቶ በማጥፋት ላይ በማተኮር በማምከን፣ በመግደል፣ በማፈናቀል፣ በበሽታ እንዲለከፉ በማድረግ፣ በማስራብ፣ በመሸጥ፣ በማባረርና እንዲሰደዱ በመገፋፋት ራዕዩን ተወጥቷል፣ ኣሁንም የርሱ ሥልጡኖች በመተግበር ላይ ናቸው።
መለስ ዜናዊ ኣስረስ የትግራይ ሕዝብ ነፃ ኣውጪ ግንባር ቁንጮ መሪ በመሆን ድርጅቱን ለኣሥራ ሰባት ዓመታት እየጋለበ መጥቶ ሥልጣን ላይ ወጣ። ሥልጣን ለማግኘት ይደረግ በነበረው ፍልሚያ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ወጣቶችን፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ኣንወጋም ያሉ የትግራይ ኣዛውንቶችን፣ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ሠራዊትን ገድሏል፣ ኣስገድሏል። የሥልጣን ወንበሩ ላይ ፊጥ ካለ በኋላም ኢትዮጵያውንን ለሃያ ኣንድ ዓመታት ኣረመኔያዊ የኣገዛዝ ዱላውን እያሳፈረባቸው ገዛ። በዚህ በሠላሳ ስምንት የሥልጣን ዓመታት ኣንድም ቀን ለሀገርና ለወገን በጎ ነገር ሳይሠራ መላ ሰውነቱ በኢትዮጵያውያን ደም እንደተነከረ ድንገተኛ ሞት ወሰደው።
በዓለም ላይ የነበሩና ያሉም ኣምባገነን መሪዎች ለሥልጣናቸው ሲሉ ብዙ ወንጀሎችን ቢሠሩም ለሀገራቸው ግን በጎ ነገር ከመሥራት ኣይቆጠቡም። ሕዝባቸውንም ይወዳሉ። መለስ ዜናዊ ግን ኢትዮጵያንም ኢትዮጵያውያንንም ኣይወድም ነበር። ስለሆነም የመጥፎ ተግባር ራዕይ እንደ ነበረው በግልፅ ኣስመስክሮ ኣልፏል። በመሆኑም የርሱ ራዕይ የመጥፎ ድርጊት ተምሳሌት ሲሆን ጀሌ ተከታዮቹም የርሱን መጥፎ ራዕይ እንተገብራለን እያሉ በመፎከር ላይ ናቸው።
ግብፃውያን ንጉሦቻቸውን ከሰው በላይ ከእግዚኣብሔር በታች እየቆጠሩ መለስተኛ እግዚኣብሔሮች (mini gods) እያሉ ያመልኩባቸው ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ግን የሰው ልጅ ንቃት እየዳበረ ሲመጣና ንጉሦችም እንደኛው ሰዎች መሆናቸውን እያወቁ ስለመጡ የኣምልኮት ተግባሩ ቀረ። እንደ ኣምላክ ይመንናሉ እንጂ እንደ የሰው ልጅ ኣይሞቱም ሲባል የነበረውም ሐሰት ሆኖ ሲሞቱ እኛው ባይናችን ለማየትና ለመመስከር በቅተናል።
የሰው ልጅ በራሱ ኣምሳል በተፈጠረ የሰው ልጅ ማምለክ በቀረበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ሆነን የትግራይ ሕዝብ ነፃ ኣውጪ ግንባር ኣባላት ግን በሺህ ዓመታት ወደ ኋላ ተመልሰው በመለስ ዜናዊ እያመለኩ ናቸው። ጧት ጧት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን እየሔዱ መቃብሩን (እውነት ተቀብሮ ከሆነ) ሳይሳለሙም የሚቀሩ ኣይመስለኝም። እንኳን በመጥፎ ድርጊቱ በታወቀው መለስ ዜናዊ ቀርቶ በጎ ነገርም ሠርቶ ቢሆን ኖሮ በኣንድ ግለሰብ ማምለኩ ኣስፈላጊ ኣይደለም ማለቱ ብቻ ሳይሆን ኋላቀርነትና በራስ ኣለመተማመንም ነው። ለሀገርና ለወገን የሚበጅ ጥሩ ሥራ ሠርቶ ከሆነ በጎ ሥራው ይመሰክርለታል። ሥራው ያስወድሰዋል። ሥራው ያስከብረዋል። በሞተ ጊዜም በግዳጅ ከማስለቀስ ተጠቃሚ ሕዝብ ካለ ለማልቀስ ትዕዛዝ ባላስፈለገ ነበር። ኣለበለዚያ ግን ሀገር እያጠፋና ሕዝብ እየጨረሰ እንደ ጣዖት የሚሰገድለት ምክንያት የለም። እንዲያውም እንደዚህ ያሉ ኣምባገነን ኣረመኔ መሪዎች ለሌሎችም የመጥፎ ኣርኣያ ተምሳሌት እንዳይሆኑ መወገዝና መወገድ ኣለባቸው። ፀረ ሀገርና ፀረ ሕዝብ የሚወደስበት ምክንያት ካለ ኣወዳሾቹም ከዚያው ከፀርነት ሥርዓቱ ጋር የሚደመሩ ናቸው። “ግም ለግም ኣብረህ ኣዝግም” ይባል የለ።
የትግራይ ሕዝብ ነፃ ኣውጪ ግንባር ባለሥልጣናት ዛሬ መለስን ቢያወድሱና ቢያመልኩበትም ወደፊት ተግባሩና ተግባራቸው ፈጦ ስለሚታይና ስለሚያጋልጣቸው እነርሱም ነገ ያፍሩበታል፣ ኣሁንም ማፈር የጀመሩ እንዳሉ ከእንቅስቃሴኣቸው እያየንና እየተመለከትን ነው። “እኛስ ብለን ነበር የወለጋን ወርቅ ተቋጥራ ተገኘች በምናምን ጨርቅ” እንደሚባለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኣካሔዳቸው የመልካም ጅምር ስለኣልነበረ እንዲያስተካክሉ ነግሮኣቸው ነበር። የሕዝብን ሃሳብ መቀበልን እንደ ነውር የሚቆጥሩት የወያኔ ኣባላት ግን እነርሱ ካሉት ውጭ መቀበል ስለኣልፈለጉ ለውርደት ተዳረጉ። ገናም መቀመቅ ይወርዳሉ።
የትግራይ ሕዝብ ነፃ ኣውጪ ግንባር ቱባ ባለሥልጣናት መለስ ዜናዊን “ባለራዕዩ መሪያችን” ብለው የሚያሞካሹ፣ የሚያወድሱና የሚያመልኩ ከሆኑ ማንም ሳይነግራቸው ራሳቸው ራሳቸውን ኣዋርደዋል። ምክንያቱም ካለርሱ ምንም መስራት ኣንችልም ካሉ እርሱ የጋሪው ፈረስ ሲሆን እነርሱ ደግሞ የጋሪው ፈረስ መቀመጫ ሆነው ከኋላው እየተጎተቱ የሚከተሉት እንጂ ኣነርሱ ሃሳብ የማፍለቅና ተወያይተው ውሳኔ የመስጠት ችሎታውና ኣቅሙም ኣልነርበራቸውም ነበር ማለት ነው። ስለሆኑም እርሱን ተክተው መሥራት ስለኣልቻሉ የጣዖቱ ኣምላክ እየመራቸው ነው የሚሠሩት ማለት ነው።
እውነት የፖለቲካ ፓርቲ መሥርተው ይሠሩ ከነበሩ፣ በፓርቲ ኣወቃቀር መሪውን ተክቶ የሚሠራ ሁልጊዜ ዝግጁ ሆኖ ነው የሚቀመጠው። ይኸ ሆኖ ቢሆን ኖሮ መለስ ዜናዊ ሲሞት ወዲያ ተተኪው ሥልጣኑን መረከብ ይችል ነበር። ግን የውሸትና የማወናበጃ ማፊያ ድርጅት ስለሆነ ያፈራቸውም ጀሌዎቹ ማፊያዎች እንጂ ለሀገርና ለወገን የሚበጁ ኣይደሉም። እኔም ራሴ ይኸንን ዐረፍተ ነገር ስጽፍ እያፈርኩ ነው። ምክንያቱም ከራሳቸው ማፊያነትም ኣልፈው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ያስወቀሱ፣ሀገሪቷን ምሁር ኣልባ ያደረጉና የመሃይማን መፈንጪያ ያደረጉ፣ ሀገሪቷን በየመድረኩ የመጥፎ ተግባራት ተምሳሌት እንድትሆን ያደረጉ፣ የፖለቲካ ፓርቲ የሚባሉ ድርጅቶችንም ጭምር ያሰደቡ፣ ያሳፈሩና ያስወቀሱ ከመሆናቸውም ኣልፈው በኢትዮጵያ ምድር መፈጠራቸውና ኣሳፋሪና ወንጀለኛ ድርጅት ፈጥረው ሀገርንና ሕዝብን ማሳፈራቸው ነው።
ኢትዮጵያ ሀገር ወዳድ ምሁራን እያሏት በኃያላን መንግሥታትና ባካባቢ ጠላቶቿ እየተመራ ኢትዮጵያን ማስተዳደር ሳይሆን በጭቆናና በግፍ ኣገዛዝ ኢትዮጵያን ሲያፈራርስና ኢትዮጵያውያንን ሲጨፈጭፍ የኖረው ኣረመኔው መለስ ዜናዊ የኣሳፋሪ ድርጊት ፈጻሚ ሆኖ በመሞቱ በርሱ መስመር ላይ ያሉ መሪዎችና የበላይ ኣለቆቹም ኣፍረውበታል። በሌላ ጎኑ ደግሞ ራሳቸውን ማሻሻል ለሚሹ መሪዎች ጀርባቸውን እንዲመረምሩ ትምህርት ሰጥቶኣቸው ማለፉን ልብ ያለው ልብ ይለዋል። የሰው ልጅ መስተዋቱ ሰው ነው ተብሏልና ራሳቸውን የሚያዩበት ትምህርት ሳያገኙ ኣልቀሩም።
ኢትዮጵያን ከመፈራረስ ለመታደግና ኢትዮጵያውያንን ከገፍና ከግፍ ዕልቂት ለማዳን ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን እጅ ለእጅ ተያይዘን ዘብ እንቁም።
ቸር ይግጠመን። abatemsas@gmail.com.