ነጻነት ዘለቀ – ከአዲስ አበባ
የግርማ ካሣን ጽሑፎች አልፎ አልፎ አነባቸዋለሁ፡፡ ሀገር ወዳድ መሆኑን ይጠቁማሉ – ጽሑፎቹ፡፡ ታታሪ ሰው ይመስለኛል፤ በጥረቱና በሀገር ፍቅር ስሜቱ እወደዋለሁ፡፡ ሁልጊዜ ሳይታክት ይጽፋል፡፡ ሳይታክቱ የሚጽፉ ብፁዓንነት የሚበዛባቸው ቢሆን ዕድለኞች ግን ናቸው፡፡ ብዙዎቻችን እየደከመን መጻፍ ቀርቶ ማንበባችንንም እያቆምን በምንገኝበት ሰዓት አዘውትሮ መጻፍ መታደል ነው፡፡
አያ ግርማ ሰሞኑን የጻፋቸውን ሁለት ያህል መጣጥፎች አንብቤያለሁ፡፡ ሁለቱም ግንቦት ሰባትን ለመንቀፍ ብዕራዊ አንደበታቸውን ያሾሉ ናቸው፡፡ መነቃቀፍ በራሱ መጥፎ አይደለም፡፡ አግባብነትና እውነት ያለው መነቃቀፍ ወይም መወቃቀስ የዕድገት መሠረት በመሆኑ ሊጠላ አይገባውም፡፡ ነቀፌታንና ትችትን መፍራት ብልህነት አይደለም፡፡ ብሂሉ “ያልተቀጣ ሕጻን ሲቆጡት ያለቅሳል” እንደሚል አንድ በግለሰብም ይሁን በቡድን ደረጃ የሚገኝ አካል ጥፋት ካለው ያን ጥፋት በተጨባጭ መረጃና ከተገኘም ማስረጃ ነቅሰው ቢመክሩት መካሪውን “አንተን ብሎ መካሪ፤ ለራስህ ምን ታውቅና” በማለት ምክሩን ላለመቀበል መሞከር አስተዋይነት የሚጎድለው ጠያፍ ነገር ነው፡፡ አንድ ሰው ሌላው ቀርቶ ዕብድና ማይም ቢሆን እንኳን፣ ለሰው የሚያስላልፈው ገምቢ ሃሳብ አያጣም፡፡ ችግሩ መናናቅ ካልሆነ በስተቀር ወይም ጭፍን ጥላቻ ካላወረን አንዳችን ለአንዳችን ጥሩ መስተዋት ነን፡፡ ስንተቻች ግን የተደበቀ ሌላ አጀንዳ የምናራምድ ለመሆናችን ፍንጭ የሚሰጡ በቀጥታ ወይም በዐይነ ውሃችን የሚታወቁ ስስ ስሜቶች ከታዩብን ሚዛናዊነታችን ጥያቄ ውስጥ ይገባና ትዝብት ላይ ልንወድቅ እንችላለን፡፡ ጭፍን ፍቅርና ጭፍን ጥላቻ ሁለቱም በእኩል መንገድ ጎጂዎችና ጥቁር ጥላ የሚጥሉ ናቸው፡፡ መግባባት ሳይሆን መናቆርና ከንቱ መተቻቸት እንዲስፋፋ ያደርጋሉና ከነዚህ መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ ለገምቢ ምክርና አስተያየት ልቦቻችንን ቀና አድርገን ብንሳሳብ ተጠቃሚዎች እንሆናለን፡፡ አለበለዚያ የዱሮው ጥፋት በአዲስ መንፈስ ወደአዲስ ሰውነት ውስጥ እየተዛነቀ መስማማት ሳይኖር እንደስከዛሬው እየተቋሰልንና እየተዳማን እንኖራለን፡፡ ለማንኛውም በዚህ ረገድ ልቦናችንን ክፍት ብናደርግ ጥሩ ነው፡፡ መገፈታተር ይብቃንና ስሜት ለስሜት ለመናበብ እንጣር፤ አንጎዳበትም፡፡
የግርማን መጣጥፎች የምመለከተው እንግዲህ ከዚህ በላይ ከጠቆምኳቸው ሃሳቦች በመነሳት ነው፡፡ ግርማ ግንቦት ሰባትን ለመንቀፍ የተጠቀመባቸውን አንዳንድ ቃላት አልወደድኳቸውም፡፡ በቀዳሚው ጽሑፉ ላይ የኢሕአዴግን ግንቦት ሰባትን አለመፍራት ለመግለጽ የተጠቀመባቸው ቃላትና ድምፀቱ ራሱ (ቶን) ለትችት የሚዳርገው ነው፡፡ በመጀመሪያ “ኢሕአዴግ ግንቦት ሰባትን አይፈራም” የሚለው ነገር ከግርማ ሣይሆን ከራሱ ከኢሕአዴግ ቢወጣ የተሻለ ነው – ግርማ የኢሕአዴግ ቃል አቀባይ እስካልሆነ ድረስ ማት ነው፤ በርግጥም በማግሥቱ ኢሕአዴግ ከምልክት ቋንቋና ከተግባራዊ እንቅስቃሴው ባለፈ በግልጽ “ግንቦት ሰባት ያሰጋኛል” ቢል ግርማን ማጣፊያው ያጥረዋል፡፡ ግርማ ቢያንስ በለዘበ አማርኛ “ግንቦት ሰባት አሁን ባለው (ወታደራዊ) አቋሙ ኢሕአዴግን የሚያስፈራው አይመስለኝም፡፡ ጊዜው ገና ነውና ኢሕአዴግ በጦር ማንንም የሚፈራበት ሁኔታ በግልጽ አይታየኝም፡፡…” ቢል የእኔንም ብዕር ባላናገረ ነበር፡፡ ግና አንዳች ነገር በሚያስጠረጥር ሁኔታ ግርማ የኢሕአዲግን የሕዝብ ግንኙነት ሥፍራ መውሰዱን መገመት ችያለሁ – ባለማወቅ ሊሆን እንደሚችልም አስባለሁ፡፡ ይህንን ስል ደግሞ ከጽሑፎቹ አጠቃላይ ይዘት በመነሣት ግርማን በወያኔነት ለመክሰስ ወይም ከነጭራሹም ለመጠርጠር በቂ ምክንያት አለኝ ለማለት እንዳልሆነ መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡
በበኩሌ ኢሕአዴግ እንደግንቦት ሰባት የሚፈራው ነገር እንደሌለ በሙሉ ልብ እመሰክራለሁ፡፡ ይህን ስል ግንቦት ሰባት አንዳንድ “ወዳጆቹ” እንደሚሉት ከ30 የማይበልጡ ተዋዎች ኖሩትም ዜሮ የተዋጊ ኃይል ኑረውም ያ ከጉዳይ ሳይጣፍ ነው፡፡ ግንቦት ሰባት መጠሪያው ብቻ ወያኔን የሚገባት እንደሚያሳጣው በስድስተኛው ሕዋሴ እረዳዋለሁ – ስሙ ብቻውን ያምጰረጵረዋል፡፡ ጠላት በሁለት ይከፈላል – ተጨባጭና እምቅ ተብሎ፡፡ እንደማንኛውም ጠላትና ወዳጅ አፍሪ አካል የወያኔ ጠላቶች ሁለቱም ናቸው፡፡ ይበልጥ ወያኔን የሚያሰጋው ጠላት ግን ከተጨባጩ ይልቅ እምቁ ነው፡፡ እምቁ ወደተጨባጭነት የሚለወጥበትን ሰዓት ደግሞ ወያኔ ቀርቶ ሰይጣንም ላያውቀው ይችላል፤ ግርማም እኔም አናውቀውም – ግን ያስፈራል፡፡ መፍራ ደግሞ ተፈጥሯዊ ነው፤ በአለመፍራት ጮቤ አይረገጥም፡፡ አልፈራም የሚል ጀብደኛና ጉረኛ ብቻ ነው፡፡ ግንቦት ሰባት ያነገበው ዓላማ በመላው ጭቁን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚደገፍ ዓላማ ነው፡፡ ግንቦት ሰባት ሲጠራ ወያኔ የሚርበተበተውና ይይዘውንና ይጨብጠውን የሚያጣው እንግዲህ ንቅናቄው በኒኩሌር መሣሪያ ትጥቅ ታምቶ ሳይሆን በዚህ ንቅናቄ የትግል መቅደስ ውስጥ በክብር ታቅፋ የተቀመጠችው የወይዘሪት ነጻነት ፅላት ባልታሰበ ቅጽበት አፈትልካ ወደሕዝቡ መሀል የገባች እንደሆነ በወያኔና ጭፍሮቹ ላይ ሊደርስ የሚችለው አደጋ ከወዲሁ ቁልጭ ብሎ እየታየው ነው፤ ሌላ አይደለም፡፡ ለአቶ ግርማ ግልጽ ሆኜ ከሆነ ወያኔ ግንቦት ሰባትን አሳምሮ ይፈራዋል፡፡ ይህን ተጨባጭ የሚመስል ነገር በመናገሬ በግንቦት ሰባትነት ልፈረጅ አይገባም፡፡ ግርማን በወያኔነት መፈረጅ እንደማይገባን መከራከሬ እኔንም ነጻ ለማውጣት ነውና እኔንም ባለመፈረጅ እባካችሁን ተባበሩኝ፡፡
በዛሬው መጣጥፉ አቶ ግርማ ለዚሁ ንቅናቄ አንድ ግልጽ ደብዳቤ ጽፎ በዘሃበሻ ላይ አስነብቦናል፡፡ ብዙዎች የመንጫጫት ያህል ብዙ ነገር ጽፈዋል፡፡ ለወደፊቱ እንደዚህ መሆን የለበትም – “የአህያ ‹ጓዝ› በሆድ ይያዛል ነው”ና ለአንዳንድ ንግግሮችና ትችቶች ብዙ ክብደት መስጠት ቢያንስ ጊዜን ይሻማል፤ የትኩረት አቅጣጫንም ያዛባል፡፡ አንድ ሰው የመሰለውን ሲጽፍ በመጣበት መንገድ ተጉዞ በጽሑፍ ተገቢውን መልስ መስጠት እንጂ መሳደብና ሌላ ሌላ ታሪክ መቸክቸክ አስፈላጊም ተገቢም አይመስለኝም፡፡ ሥራ ፈት ወያኔዎች እንደዚያ ቢያደርጉ ሥራቸው ነውና ምንዳም ያገኙበታልና ምንም አይደል ሊባል ይችላል፡፡ በትግል ላይ ከሚገኙ ወገኖች ውስጥ በዚህ ዓይነት የአንድን ታዋቂ ጸሐፊ ስም ለማጉደፍ በመሞከር ሙያ ላይ የተሠማራ ሰው ካለ ግን ስህተት ነውና ለወደስተፊት ይታረም፡፡ እውነት እንደሆነች በብዕር ቱማታ ይቅርና በመትረየስና በታንክም ቢሆን ከላችበት ቦታ ንቅንቅ አትልም፡፡ ግንቦት ሰባት ከሻዕቢያ ሥር መወተፉ በርግጥም ሀገርን የሚጎዳ ነገር ካለውና ድርጅቱ ከዚህ ተግባሩ እንዲታቀብ ሃሳብ መሰንዘር የዜግነት ግዴታ እንጂ እንደባይተዋር ሊያስወቅስና ምን አገባህ ሊያስብል አይገባም፡፡ ቅስምን ለመስበር የሚደረገው ጥረት በብልህነትና በአስተዋይነት ቢቀየር መልካም ነው፡፡ ስለጋራ ሀገራችን መጨነቅ የሁላችንም ኃላፊነትና ግዴታም ነው፡፡
በበኩሌ ግንቦት ሰባት ከሻዕቢያ ጋር ብቻ ሳይሆን በዓለም አሉ ከሚባሉ አምባገነኖች ጋር ተባብሮና ዕርዳታም አግኝቶ ኢትዮጵያን ነጻ ቢያወጣ ደስተኛ ነኝ፡፡ ዝንጀሮዋ “ቀድሞ የመቀመጫየን” ነው ያለችው፡፡ ተደጋግሞ በብዙዎች እንደተነገረውም የአንድን ድርጅት የመታገያ መስመር የሚመርጥለት ራሱ ድርጅቱ እንጂ ሌላ ሊሆን አይገባውም፡፡ ይህን ስል ኤርትራ ለኢትዮጵያ ነጻነት የምትቆም ሀገር ስለመሆንዋ መጣጥፋዊ ዋስትና ዋስትና እየሰጠሁ እንዳልሆነ መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ነገር ግን ወያኔ በምንም መንገድ ከሻዕቢያ የተሻለ እንዳልሆነ በመሃላ ማረጋገጥ እፈልጋለሁ፡፡ ትልቁ ዕንቆቅልሽ…
ትልቁ ዕንቆቅልሽ አቶ ግርማ ግንቦት ሰባትን ከኤርትራ አውጥቶ ወደሀገር በማስገባት ከነሸንጎና ከነአንድነት ጋር በመተባር ወያኔን በ“ሰላማዊ ትግል ድባቅ እንዲመታ” ያደረገው ፌዘኛ ጥሪ እጅግ አስገርሞኛል፡፡ አቶ ግርማ አንዳንድ ነገሮችን ለማሰብ ሲፈልግ እንቅልፍ ይይዘዋል፡፡ አንዳንድ ነገሮችን ለማሰብ ሲፈልግ ደግሞ ይነቃል፡፡ ግንቦት ሰባት ምርጫ አጥቶ ወይም ካሉት ምርጫዎች ውስጥ የመረጠውን መርጦ ወደ ትግል ሜዳ እንደገባ ነግሮናል፡፡ እሱ በዚያው ይቅናው ብለን ከመጸለይ ይልቅ ሳቢውን ግረፈው እንዲሉ ወደማይሠራ የትግል ሥልት በመጋበዝ ቃሊቲ እንዲወረወሩ ወይም ቀድሞ በተፈረደባቸው ፍርድ እንደነመንግሥቱ ንዋይ ተክለ ሃይማኖት አካባቢ እንዲንጠለጠሉ ለማድረግ የተሸረበ ሤራ ያለ ይመስለኛል፤ ለምን? ትግሉ ቢኮላሽ ማን ይጠቀማል? እነብርሃኑ እኛን ምን አምጡ አሉና አስቸገሩን? ለምንድነው አንድ መሆን ካተቻለ፣ መስማማት ካልተፈለገ ሁሉም በመሰለው መንገድ ታግሎ ሁላችን የምንፈልጋት ነጻነት እንድትገኝ ዕድል የማንሰጠው? ማደፍረስ የሚቀናን ለምንድነው?
ትግሉን ለማወክ ካልሆነ ከብት ባልዋለበት ኩበት ለቀማ – ሰላምን በማያውቅ የወያኔ መንደር ውስጥ ሰላማዊ ትግል ፍለጋ እንዴት ኑና እጃችሁን ስጡ ተብሎ ይጻፋል? ችግሩ መጻፉ አይደለም – የተጻፈው ነገር ተግባራዊነት ግን አልተጤነበትም ነው እያልኩ ያለሁት፡፡ ግርማ ዐይቹን ጨፍኖ የጻፈውን ነገር እንደገና እንደሚያጤን እገምታለሁ፡፡ በአሁኒቷ ቅጽበት ማን ነው ለኢትዮጵያ አደገኛ? ግንቦት ሰባት ወይንስ ወያኔ ወይንስ ሻዕቢያ? ልብ ይደረግልኝ – ወደ “ጥንት” ታሪክ አልገባሁም፡፡
አቶ ግርማ ካሣ፡፡ እንዴት ነው ነገሩ? እውን ወያኔ ለሰላማዊ ትግል በሩን ከፍቷል? በዓለም ዙሪያ ያሉ ወገኖቻችን ስለሳዑዲዎች አረመኔነት ለመግለጽ ለወገናቸው ሲሉ በየሚኖሩባቸው ሀገራት ዋና ዋና ከተሞች ሲሰለፉ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ በሰማያዊ ፓርቲ ሰልፎኞች ላይ የተደረገውን ሰምተሃል ወይንስ ያኔ በሀገር ውስጥ አልነበርክም? ከዚህ የነሰ ትንሽ መብት የት አለ? ለዚህች ሚጢጢዬ መብት – በሌሎች ሀገራት የተፈቀደ – በኛዎቹ ናቡከደነፆሮች ግን በኃይል እርምጃ የተደፈጠጠ ሰልፍ ምን ያመለክታል? እርግጠኛ ነኝ ግርማ እዚህ ቦታ ስትደርስ በጻፍከው ነገር ልትፀፀት ትችላለህ፡፡ እነእስክንድር ነጋ ለምን ዘብጥያ ወረዱ? … ወያኔን በሰላማዊ ትግል ፈቃጅነት መፈረጅ ራሱ እንደኔ ከሆነ ወንጀል ነው – በኢትዮጵያውያን ደም መቀለድም ነው፡፡ ስዚህ አንተ ግንቦት ሰባትን እንደፈለግህ ጥላው ነገር ግን በነሱ ሰበብ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሰላማዊ ትግል ሁሉም ነገር የተመቻቸ ነው በሚል ቃና የምታስተላልፍላቸውን የኑ ታረዱ ጥሪ በፍጹም አልተቀበልኩትም፤ እነሱን መጉዳት ከተፈለገ ሌላ መንገድ መፈለግ ይቀላል፤ ለወያ ግን አይስጣቸው፤ የወያኔን ቅጣትና የበቀል እርምጃ “ለጠላትም አይስጥ”፡፡ “የደላው ሙቅ ያኝካል” አሉ፡፡ ለኔ አደገኛ ሆኖ ያገኘሁት ግንቦቶች ለወደፊቱ ሊያስከትሉ ይችላሉ ተብሎ ከሚሰጋ አደጋ ይልቅ አሁን በመጣጥፍህ ውስጥ የሚገኘው ኢትዮጵያ ውስጥ በሰላማዊ ትግል መንግሥትን እንታገለው የሚለው የደናቁርት አስተሳሰብና የወያኔ ጭራቅነት ናቸው፡፡ ወያኔ ከጦጣና ዝንጅሮ የሰውነትና የአእምሮ የዕድገት ደረጃ ባልወጣበት ሁኔታ፣ ዘረኝነት ከአጥናፍ አጥናፍ ሀገሪቱን ሰቅዞ ይዞ መግቢያ መውጫ ባሳጣን ሁኔታ፣ የኑሮ ውድነቱ ገድሎ ሊጨርሰን ባሰፈሰፈበት ሁኔታ፣ የትግሬዎች የበላይነት ነግሦ ሁሉም ነገር በነሱ ቁጥጥር ሥር ሆኖ እኛ የበይ ተመልካች በሆንበት ሁኔታ፣ … ምን ዓይነት ጥሪ ነው ለግንቦት ሰባት የምታስተላልፍላቸው? አሁን እነዚህ ሰዎች ከወያኔ ይበልጥ ለኢትዮጵያና ሕዝቧ አደጋ ሆነው ነውን? ለምን አንዳንዴ፣ እንዲያው ሲያመቸን አንዳንዴ እንደጤናማ ኢትዮጵያዊ ሆነን አናስብም? እስኪ እነዚህ ሰዎች የት ይሂዱና ትግላቸውን ይጀምሩ? አይ፣ እያሰብን እንጻፍ፤ እንናገርም፡፡ ለኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ከሰይጣንም በባሰ ሁኔታ ታላቁ ጠላት ወያኔና እርሱ የዘረጋው የዘረኞች የቢዝነስ ኢምፓየር ነው፡፡ ከአፓርታይድ የሚበልጥ የጭራቆች ንጉሠ ነገሥት ወያኔን አራት ኪሎ አስቀምጦ ስለሻዕቢያ ማውራት፣ ታላቁን የመለስ ሙት መንፈስ ቤተ መንግሥት አስቀምጦ ስለግንቦት ሰባት “አደገኛነት” ማውራት የበቅሎዋን ተረት መተረት ነው፤ “በቅሎ አባትሽ ማን ነው?” መልስ፡- “እናቴ ፈረስ ነች!” አስፈላጊ ከሆነ ሌላ ጊዜ እመለሳለሁ፡፡