የቀጥታው መንገድ ቅጣቱ ማዬሉ ።
ከሥርጉተ ሥላሴ 10.12.2013
ፎለቄዋ ደማሟ እና ሳቢዋ እማማ ዊኒ የአፓርታይድ ሴራ ከነፃነት በፊትም ሆነ በኋላም ግቡን ያሳካባት ድንቅ የነፃነት አርበኛ ሴት ናት። ዕውቅናዋን ግን በስውር ያለው አፓርታይድም ሆነ የዓለም ሚዲያ እንደ ተጫነው ነው – ዛሬም። ድንቋ የነፃነት እናት ዊኒ ጥንካሬዋ ከብረት ቁርጥራጭ የተሰራ ነው። የፍቅርት ዊኒ የአርበኝነት የተጋድሎ ታሪክ ብሄራዊ ብቻ አልነበረም። የዓለምን ህዝብ ጥንካሬና ብርታት በፍጹም እናታዊ ሰማያዊ መክሊት በልግስና የመገበ ነበር፤
ወርቋ ዊኒ ለፓርቲዋ ተልዕኮ መሳካት ዘወትር ጥራላች – ባትላላች፤ ዊኒ ለአካሏ ለተከበሩ የሰላም መሪ ለኔልሰን ማንዴላ የጽናት ማህጸን ሆና ጽናትን በልዩ ሁኔታ ሸልማላች፤ እማማ እያሉ በንጹህ ልባቸው እናትነትነቷን ላፃደቁ የደቡብ እፍሪካ ግፉዓን ህዝቦችም በገፍ ሳትሰስት ፍቅሯን አጥብታለች- ዛሬም። ከማህጸኗ የፈለቁትን ልጇቿን በመከራዋ ዘመን ሁሉ እንደ አባትም እንደ እናትም ሆና በአንድ ክንዷ እንደ ወታደር ዘባኛም ሆና በታታሪነት አገልግላቸዋለች። ከጥቃትም ታድጋቸዋላች። በማናቸውም ዙሪያ ትንፋሿን ከትንፋሻቸው ጋር አጋባታ ጠረናቸውን አጣጥማ፤ ገረድና ሎሌ በመሆን በትጋት በፍቅር ተገዝታላቸዋለች። መንፈሳቸው ላይ ይፈታታናቸው የነበረውን ያን ጥቁር ጥላት የበታችንት ስሜት ታግላ አሸንፋለች። ዕንቋዋ ዊኒ የድል አንባ ናት። ከመከራ የፈለቀች የምትጥም ነፍስ ናት – የመንፈስም ቅዱስ ቋንቋ።
ክብርት ዊኒ ቤበተሰብ ኃላፊነቷ የጓዷውን ገመና ሁሉ ብቻዋን በጸጋ አስተናግዳለች። ሴቶች የማህበራዊ ኑሮ መስራቾች ናቸውና በዘርፉም መሪ ሁና አደረጃታለች። የማህበራዊ ኑሮ እውነተኛ እረኛም ሆናለች። በግፍ ይጨፈጨፉ፤ ወደ እስር ይጋዙ የነበሩ ወገኖቿን ከጎናቸው በመሆን ዕንባቸውን ተጋርታላች። አጽናንታቸዋላች። ትዳራቸው ለተፈታ፤ ለተበተነ እንቁዋ ዊኒ ቅርብም ነበረች – ሚስጢር! በእዬአንዳንዱ ቀንና ሰከንድ በፈተና በተከዘነው ህይወቷ ሁሉ የነፃነት ሰንደቅን ተሸክማ ተጋድላላች። ሁለቱ ከነትዳራቸው ቀጥለው ቢሆን … ትንግርትን ዓለም ያይ ነበር። በአዲስ ርዕዮት ዓለም ብዙኃን ይታዳም በነበረ … አዲስ ምዕራፍ ለዘመኑ በአናገረም ነበር ….
የጥቁር አልማዝዋ ዊኒ ቀጥታ ናት። ቀጠታ – ቀጥታ ነው። በቀጥታው መንገድ ተጉዛላች። ይህ የቀጥታ መንገድ ያሰጋው አፓርታይድ የሴራ መረብ አዘጋጅቶ ብዙ ተፈታትኗታል። በግድያ ሙከራ እጇ አለበት ብሎ ጥላሸት ከመቀባት ባሻጋር የትዳር፤ የመንፈስ፤ የትንፋሽ፤ የራዕይ አጋሯን የመጀመሪያ የጥምር ንዑድ ፍቅር ቀምቷታል። ይህ አሳንጋላ እንቆቆ ነው። በእያንዳንዱ የዊኒ ህይወት ውስጥ የአፓርታይድ የስላላ ድርጅት የሸርና የተንኮል መርዝ አለበት – በረቂቅ።
ዓለም – ዓቀፉ የሴቶች ድርጅትም ዝምታ በመምርጡ የዊኒ የጥንካሬ፤ ሕይወት የዘራ ሙሉዑና እኩል ተሳትፎ ታፍኖ መቅረቱ፤ ተቆርቋሪ አጥቶ ነጥፎ መቅረቱ ለእኔ እሳት ነው ረመጥ። ይህም በመሆኑ ውቧ ዊኒ ከዓለም ዓቀፉ የነፃነት ተጋድሎ ታሪክ ውስጥ ምዕራፍ ከፋች ሆና ግን ተዘላ ዕውቅናዋ … ባክኖና ከስቶ ቀረ። ነገር ግን እናቴ ዊኒ እንኳንስ በደቡብ አፍሪካውያን የነፃነት ቤተሰቦች በእኛ ውስጥ ያለውን የፍቅር ፏፏቴና ማንም ሰው ሊወስደው ወይንም ሊቀማው ወይንም ሊፍቀው አይችልም። እኛ ምሳሌያችነን ዊኒን የማይነጥፍ ፍቅር ሸልመናታል። የክብርትነቷ የተጋድሎ ሞገድ ከሰላሙ መሪ፤ ከጽናቱ አውሯ፤ ከማሃሪው ከኔልሰን እረፍት በኋላ አቅጣጫው ወደ ዬት የሚለው ሁላችንም የምናዬው ይሆናል …. የታፈና፤ የታመቀ ነገር ባንቧ መተንፈሻ ካላተሰራላት በማናቸውም ጊዜና ሁኔታ ሊፈነዳ ይችላል። አቅጣጫውን ከሳተ ደግሞ አደጋው ከአደጋ ባላይ ነው – እሳተ ጎመራ … ኢትዮጵያዊነት የሚመሩ ሁሉ ልብ ሊሉት የሚገባ ቁምነገር ነው … ሁሉ ነገር የመተንፈሻ ጥግ አብዝቶ ይናፍቀዋልና ….
ከዚህ አንፃር በዊኒ እና በማንዴላ የተፈጸመው ሴራ በልዑል ቻርልስና በልዕልት ዲያናም ተፍጽሟል ብዬ እኔ አስባለሁ። የልዕልት ዲያና ዕውቅና መሬትን ማነቃነቅ ሲጀመር የልዕሉ የቻርልስ ልብ ከትዳር አጋሩ እንዲሸፍት ተደረገ። ለልዕልት ዲያናም ሌላ ድራማ ተዘጋጀ …. ክብሯን ዝቅ አድርጎ ለህልፈት የሚያበቃ የበቀል ፍቅራዊ መንገድ … ሁሉም ሆነ። ነገር ግን ዛሬም ነገም የልዕልት ዲያና ታሪክና ፍቅር ማንም ፈልቅቆ ሊሸጠው ሊለውጠው የማይችል በጽኑ አግናባት በደማችን ውስጥ የተገናባ ሆነ። ለዚህ ማካካሻ የእንግሊዙ ቤተመንግሥት ዛሬ በልዑል ዊሊያም ጋብቻ ላይ ያለው የቅነንት ዕይታ ያን … የጠቆረ ታሪክ እንዲያጥብ የታለመ ነው። በአጭር ጊዜ የከሰመውን የልዕልት ደያና ራዕይና የሰብዕዊነት …. ጉዞ መጫናገፍ …. የሚሰውር አዲስ ትዕይንት ነው …. ለእኔ። ልዕልት ዲያና ዕድሉን አግኝተው ቀጥለው ቢሆን የተተበተበውን ሴራና ሸር፤ በሌሎች ሀገሮች ጣልቃ በመግባት ማማስና ማተራመስ …. መሰል ጎምዛዛ ገጠመኞች ተግ ይሉ በነበረ …..
የወያኔው ሄሮድስ መልስ ሴራ – ተንኮል – በቀል – ጥላቻ – የማግለል ፓሊሲ ጠብተው ያደጉት ከአፓርታይድ ምንጭ ነው። ልዩነቱ የአፓርታይዱ አመራር እንደ ማርክሲስቶቹ ሳይንሳዊ ትንተና በማህረሰብ እድገት ከፒታሊዚም ላይ ሲተገበር የሄሮድሱ መለስ ዘረኛነት ደግሞ ከቤተሰብ ቀጥሎ ካላው ጎሳ ላይ መተከዙ ነው፤ ወይንም በሌላ አገላላጽ በሰለጠናና ባልሰለጠነ፤ በአደገ ህሊናና ባላደገ መንፈስ የሚታዳደር ወይንም የሚመራ ከመሆኑ ላይ ነው እንጂ …. ወያኔ ሃውዚን ሲያሰደበደብ ቅንጣትም ስለነዛ ንፁኃን ዜጎች አላሳበም – ፈጽሞ። የእሱ የቋሳ ተልዕኮ በኮሶ ተጥቅልሎ መሳካቱ ብቻ ነበር ያደናበረው። የደቡብ አፍሪካውያኑን የክብርት ዊኒ እጅ አለበት ተብሎ በሚጠረጠረው የብዙ ሰዎች ህልፈትም እኔ የማዬው ከዚህ አንጻር ነው። የዊኒና የኔልሰን ትዳር፤ የቻርልስና የዲያናንም ትዳር መፍረስንም የማዬው ከዚህ ዕይታ ነው። ጭራ ሳይሆን ሥር መፈለግ የመፍትሄ መዳረሻ ነውና። ልንገመግመው የሚገባ …. ከዚህ አንፃር ነው የሚል እድምታ ነው ያለኝ። በእውነቱ ቁጭ ብሎ ማሰብ ነገሮችን በትኖ በማጥናት ዘሩን መፈለግ የትውልዱ ታሪክ ጸሐፊዎች ወሳኝ ተግባር ይመስለኛል።
ስለዚህ ለተከበሩ የጽናት አርበኛው ድል፤ ክብር፤ ዓለምዓቀፋዊ ተወዳጅነት ዊኒ እንብርትና አንጎል ናት። ኔልሰን እስር ቤት በነበሩ ጊዜ የዊኒ ደብዳቤዎች ጨላማውን ተዳፈረው ሌትና ቀን ጽናትን ተግተው የሚያጠቡ ብርኃናት ነበሩ። ወደ ቀዝቃዛው ክፍል ተጉዘው ሳይታክቱ በታታሪነት ትእግስትን የሰነቁ ሙቀቶች ነበሩ። በዛች ጠበቃ ክፍል ዘምተው የማይደክሙ የተስፋ ሰፊ እልፍኞች ነበሩ። በራህብና በጥማት ኩርምት ላላው አንጀት ሙሉዑ ተበልቶ የማይልቅ የሰማይ መና ነበሩ፤ ተጥጥተው የማይነጥፉ የኤዶም ፏፋቴዎች ነበሩ። በእሾህ የታጠረው አካባቢ የነፃነት ጎህ የሚዘንብበት የማግሥት ራዕይ ርችት ነበረው። ማንም በሌለበት የጣሪያና ግድግድጋ ጋብቻ ኑሮ ብቸኝነትን ያለ ይግባኝ የረታ ዳኛነት ነበረው። የልጅ እቅፍ ስስት ሲመጠምጥ፤ የደህንነተቻውና የዕድገታቸው ብሥራት በእርግጠኝነት ያበስሩ ዕለታዊ ሰበር ዜናዎች ነበሩ ለኔልሰን። ዊኒ ለማንዴላ ሁሉንም ነበረች። በዛ ጠቀራማ ጉዘው ባለዬው የነፃነት ጥብቆ እስር ቤት ዊኒ ለማንዴላ የመንፈስ ሀገሩ ነበረች።
ጅሎች ብዬ ልጀምር። የተከበሩ ኔልሰን ማንዴላ ሰው ናቸው። አንዳንድ ሰዎች ኔልሰንና የኛዋቹን አርበኞች አታመሳስሉ ይላሉ። ምን ያንሳቸዋል። „ በእጅ የያዙት ወርቅ“ እንዲሉት ካልሆነ በሰተቀር መስዋዕትነትን በጸጋ ተቀብሎ በማስተናገድ እረግድ እኩል ነው። በጠላት ወረዳ የተነሰረዘው ጥላቻ ጥቃት እኩል ነው – በቀሉም በቀል ነው። በፈተና መፈተሉም እኩል። የሞቋቋም ትክሻ ጽናቱም ጽናት ነው። ተጋድሎውም ዓለምን ያስደመመ ተጋድሎ ነው። መከራን ፈቅዶ የመቀበል አቅሙም መሳ ለመሳ ነው።
ዘረኛው ወያኔ „ሀ“ ብሎ የነፃ ፕሬሱን ሲያውጅ ለመበቀያ ነበር። ከተጠቂዎች በኽሩ የኛው ማንዴላ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ነው። ሁሉ እያለው ሁሉም እዬተቻለው ግን ለነፃነት ራህቡ ሁሉንም የመከራ ዓይነት ፈቅዶና ወዶ ሰጠ። ሁልጊዜ ፎቶግራፎችን ሳያቸው ጸሐይ ናቸው ለእኔ ይሞቁኛል። የሚያስተላልፋቸው መልዕክቶች ሁሉ ነገን የሚያበሩ ዛሬን የሚያጽናኑ ናቸው። እስክንድር ፍቅር ነው። እስክንድር እስር ቤት ሆኖ ሳቂተኛ – ማህሪ ነው። በጮርቃው በእናቱ ማህጸን የቃሊቲ ታዳሚ የነበረው ታምሩ ናፍቆት እስክንድር ከበቀል የጸዳ አዕምሮ እንዲኖረው መልእክቱን ሁልጊዜ በአፅኽኖት ይልካል። አደራውን ለእኛዋ ዊኒ ለጋዜጠኛ ሰርካለም ሰጥቷል። እኛም ብንታደምበት ምንኛ ዕድለኞች በሆን ነበር። ሥጋውን ተውት፤ ለረቂቁ ዓለም … የጻድቃን ጉዞ በሆነ — በነበረ።
የጣይቱ ልዩ ዓርማ ሰርኪ እንደ ዊኒ በዛ ድቅድቅ ጨላማ አይዞህ ትላላች። በርታ ጠንክር ትላላች። ታውጃላች የኛ ጌጥ ሆናለች። መራራውን የመጨረሻ መለያዬት የባሰ ቢመጣ እንኳን ቆርጣላች። ጨክና ወስናላች። ፈቀቅ ሳትል ሁሉንም ተቀበል ብላ ቃሏን ለኪዳኗ፤ ብርታትን ከጽናት አጋባታ ልካላች። የሰርክዬ ዱካ ጽናት ለነፃነት ግብር መሆን አለበት ብላ አስተምራናለች። የሰርክዬ ብርታት ምንጩ ከትናቶቹ አርበኞቻችን ከእነ – ንግሥት ጣይቱ - ከዊኒ ጋር ያበረ ነው።
ጋዜጠኛ ሰርካላም ፋሲል የጫጉላ ጊዜዋን በእብሪተኛች የተነጠቀች፤ ቅብጥብ የሚያደርገውን የበኽር ልጅ የእርግዝና ወራቶቿን ከቤተሰብ ቁልምጥ ተለይታ በሳጥናኤላዊ መለስ አስተዳደር በግፍ የተቀማች፤ የአራስነት ወጓን ደግሞ ለአረመኔዎች ቋሳ ሰላባ የሆነ ነው። ከድንቅ በላይ የተግባር ጻድቅ ናት – ሰርኬ። ዊኒና ኔልሰን ሰርኬና እስክንድር ራዕያቸው አንድ ነው። ነፃነት በቃ …. ለዚህ ደግሞ ዋጋውን እኩል ከፍለዋል። አሁንም እዬከፈሉ ነው። ሰርኬ ለእኔ ሚስጥር ናት። ሰርኬ ለእኔ አብነቴ ናት። ሰርኬ ለእኔ ትምህርት ቤቴ ናት። ሰርኬ ለእኔ የጽናቴ ድሪ ናት። ሰርኬ ለእኔ የነገ የተስፋ ሃዲዲ ናት … ሰርኬ ለሁላችን ተቋማችን ናት። የጽናቱ አርበኛ የእስክንድር የጽናት ውበት ጋዜጠኛ ሰርካለም ናት። ጋዜጠና ሰርኬ ኪዳንም ናት – የመንፈስ ውል። የአደራ የዓይን ማረፊያ – ብርቅ።
አዳራ! እላለሁ እኔ ሥርጉተ ሥላሴ የዓለም የሚዲያ ተቋማት የኔልሰን ክብር ከዊኒ እንደነጠለው ሳይሆን ከነፃነት በኋላም ሆነ በፊት ሰርኬንና እስክድርን እኩል በክብር ፍቅርን አጎልምሰን እንሸልማቸው። ዓይነታ ናቸውና። ዛሬም እስክንድርን ስናስታውስ ሰርኬን „ባልና ሚስት ከአንድ ወንዝ“ እንዲሉ መታደላችን እባካችሁ የሀገሬ ልጆች እናክበረው ትርጉምንም እንወቅበት። ትውልዱ ዓርማውም ማህተሙም ይህ እንዲሆን እሻለሁ። ኔልሰን ይህን ሁሉ ጸጋ የተጎናጸፉት፤ የተማሩት፤ ዝቀሹን ተመክሮ የተካኑበት ብቃትን ለዓለም የመሩበት፤ እንደ እናታቸው ጡት የጠቡት እኮ የክብሮቻችን የጄ/ ታደሰ ብሩ፤ የሻንበል ጉታ ዲንቃ፤ የኮ/ ፈቃዱ ወንድሙ ፤ የመቶ አለቃ ፈቃዱና የ50 አለቃ ደበበ ተማሪ ከማሆን የተገኘ ሚስጢር ነው። ዛሬም፤ ነገም የኢትዮጵያዊነት ሚስጢር ገቢራዊ ማድረጉን ካለመታከት ተግተን ልንፈጽመው ይጋባል። ከዚህ ሚስጢር ጋር እዬተላላፍን እኮ ነው የምናጠፈውም … ለድልም የማንበቃው። እኛ መሪ ነን። መሪነታችን ግን እንግራው በተፈጥሮችን ሚስጢራዊ ዲስፕሊን …
በጋዜጠኛ እስክንድር የብቃት፤ የብርታት ጥናካሬ፤ የጽናትም አቅም ደም ውስጥ ቅሙሙ ከፈርጣችን ከጋዜጠኛ ሰርካለም ነው የሚቀዳው። ይህን ማማሳጠር፤ መተርጎም ለዓለምም ማስተማር አለብን። ይህ ትውልዳዊ ድርሻችን ነው … ይህን የነጻነት ድርሳን ፈልፍሉና ረቂቁን የጽናት ጎለጎታ ድረሱበት … /የቤት ሥራ/ ጽላትም እናድርገው።
http://www.ethiotube.net/video/28543/A-must-watch-The-deception-exposedEskendirs-wife-speak እስኪ እዩት። አዳምጡትም …
http://www.zehabesha.com/2013/10/serkalem-fasil-send-a-voice-message-to-her-husband-eskinder-nega/
ከጥቁሯ አልማዝ ከዊኒ ይልቅ አሜሪካዊቷ የተከበሩ ሄነሪ ክሊንትን ዕድለኛ ናቸው እላለሁ። የቀድሞው ክቡር ፕሬዚዳንት ቪል ክሊንተን በጥንካሬያቸው ሁሉ አካላቸው ወ/ሮ ሄነሪ ክሊንትን ነበሩ። መደማመጣቸው፤ መከባባራቸው፤ መተሳሰባቸው ሁለቱም በአገኙት የከፍተኛ ሥልጣን አጋጣሚ ዓለምን አስተምረውበታል። በአንድ ወቅት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሄነሪ ክሊንትን ባለቤታቸው በፆታዊ ግድፈት ተከሰው በነበረ ጊዜ ከአካላቸው ወገን ምንም ዓይነት ለግድፈቱ እውቅና በመስጠት ሆነም የአጋፋሪነት እርምጃ አለመወሰዱ የገረመው አንድ ጋዜጠኛ እንዲህ ሲል ክብርት ሄነሪ ክሊንትን ጠይቋቸው ነበር „ አለሰማሽም ስለ ፕሬዚዳን ክሊንተን የሚወራውን ሆነ ያዬሽውስ የለምን?“ ሲል … መልሳቸው እንዲህ ነበር“ እናቴ ስታሳደገኝ ሰው የሚለውን ከሰማሁ የምሰራው የሰዎችን እንደምሰራ፤ ካልሰማሁ ግን የራሴን ሥር ለመስራት እንደምችል አስተምራኛለችና፤ የሰማውትም ዬያዬሁትም የለም“ በማለት እጹብ የሆነውን የተግባር ሰውነት ነበር ያሳዩት። ይህ የበሰለና የሰለጠነ ግንዛቤ … እስከ መሪነት አሳጫቸው። …. ትዳራቸውንም ከፍርሰት ታደጉት … ታሪካቸውንም ሙሉዑ አደረጉት። ክቡር ኔልሰን ፈተናውን አሸንፈው ቢሆን … ደስታዬ ሐሴት በሆነ …
„ልብ ያለው ሸብ“ ይላል ጎንደሬ … የአሜሪካን ህዝብ መስጥሮ የሰነቀውን ተግባር ለፕሬዚዳንትት ተፎካካሪነት አበቃቸው። የተከበሩ ብልኋ ሄነሪ ክሊንትን ከ2008 አስከ 20012 የታላቋ አሜራካ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር በመሆን ዕውቅና ክብር ማግኘታቸው ብቻ ሳይሆን የሴቶችን የእኩልነት ብቃትና አቅምን በድርጊት ሰብከዋል። ዕድለኝነታቸው ከዚህ አንጻር ነው …. እውነት ለመናገር ተመሳሳይ ፍላጎት፤ ሙያ ዓላማና ራዕይ ያላቸው ጋብቻዎች የሎተሪያ ያህል ዕጣታቸው ጠባብ ነው … ከተሳካላቸው ግን ሀገርን ከምንም በላይ ሊጠቅም የሚችል ልዩ ሥጦታ ነው …. ። ከዚህ ጋር በተያያዘ መልኩ ቀዳማይ እመቤት ወ/ሮ ሚሻዬል ኦባም ጥንካሪያቸው ነገን የሚያሰውብ ይመስለኛል። ልዕልት ካትሪንም መንገዱን ትከተላላች ብዬ አስባለሁ ….
እጅግ የምትናፍቁኝ የሀገሬ ልጆች … በዘለቄታ ሃብታችን ማድነቅ፤ ሃብታችን ማክበር፤ ሃብታችን ታሪካችን ማደረግ፤ ለሃብታችን እኛን መስጠት እግዚአብሄርን ከመፍራት ጋር አቡነ ዘሰማያታችን ወይንም ሰላዳችን ሊሆን ይገባል። ድንቆችን ማፍቅር፤ ምቀኝትን ገድለን ቅንነትን ካነገስን ታሪካችን በዘመኑ ማድመቅ ማስዋብ ይቻላል። አይከፈልበት። ዳጋት አያስወጣ ቁልቁላት አያሰውርድ። በእጅ ያለ እኮ ነው … ለድንቆቻችን ውስጣችን መሰጠት።
እርገት
እማማ … ዊኒ አንቺ እልኳት እንደ እናቴ ስለማያት … ዓለምዓቀፍ የሴቶች የእኩልነት፤ የአርነት መሪ ብትሆንልኝ ፈቃዴ ነው አቅም የለኝም እንጂ። ለሴቶች ታዳያለሽ ተብዬ እታማለሁ። እስከ አሻችሁ ድረስ እሙኝ ውቁኝ … ውስጤን በቀጣዩ ጹሑፌ አሳያችኋለሁ። የሰማዕቷ ሺብሬ ደስአለኝ ወጣትነቷ አፈር መሆኑ ይቆጠቁጠኛል፤ የክብርት ዳኛ ብርቱካን ፍቅርና ችሎታ ይንፍቀኛል – የሀገሬን ያህል። ያንሰፈስፈኛል። የእስረኛዋ የአበራሽ ሰቆቃም ያርመጠምጠኛል። የወጣቷ እስረኛ የጋዜጠኛ ርዕዮት ናፍቆት ሰቀቀን ስጋትን ሰንቆ ይነስተኛል። ሻማችን ርዕዮት በጡት ህምም እዬተሰቃዬች ነው። በእስር ቤቱ እንኳን ይህም ተቀንቶባት በወንበዴ ትራፊ ሴቶች ግልምጫ የዕለት ጉርሷ መሆኑ ያቃጥለኛል። የአብዛኞቹ ብቃታቸው የእህቶቼ ተዝቆ አያልቅም። የአብዛኞቹ ብልህነታቸው ተመርቶ አያልቅም። አብዛኞቹ ጥበባብ ናቸው …. መሆን ናቸው። ቆራጥ ናቸው – ሴቶች። የእማማ ዊኒ ቆራጣነት ነፃነትን የፈጠረ ቅምጥ ሀብት ነው። ጽናት መልኩን እምታውቁት ከሆነ ሴቶችን ይመስላል። የብርኃን ብሥራትን የገለጸቸው ቅድስት መግዳላዊት ነበረች። የዓለም የድህነት ድርሳንም ድንግል – ለተዋህዶ አማንያን … አምላካችን ከዲያብሎስ ጋር ተደራድሮ ሃጢያት ከምድር እንዲደረቅ በድፍረት የጠየቀችም ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ ናት። … ዋ! እመለሰላሁ በዚህ ዙሪያ ክብሮቼ በጥቂት ቀናት ውስጥ እሰከዛው ግን ለሰጣችሁኝ የማይጠገብ ትእግስት … ዝቅ ብዬ ኢትዮጵያዊ ጀርጋዳ ምስጋዬን እነሆ …. መልካም ጊዜ።
ሴቶች የመሆን ሸማ ሰሪዎች ናቸው!
ሰርኬ ለእስክንድር የመንፍስ ልዩ ሀገሩ ናት!
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ናፍቆት።