አማኑኤል ዘሰላም
amanuelzeselam@gmail.com
በምርጫ ዘጠና ሰባት ወቅት የነበረዉን ሁላችንም የምናስታወሰው ነዉ። ያኔ የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምጹን ለቅንጅት ቢሰጥም፣ ሕወሃት/ኢሕአዴግ የሕዝቡን ድምጽ ነጥቆ እስከአሁን ድረስ በኃይልና በጡንቻ እየገዛ ነዉ። በስልጣን ላይ ለመቆየት በቀዳሚነት አገዛዙ የወሰዳቸው አምስት እርምጃዎች ነበሩ። እነርሱም የቅንጅት አመራሮችን ማስወገድ(እንዲታሰሩ፣ እንዲሰደዱ በማድረግ)፤ ቅንጅትን መከፋፈል፣ ሕዝቡን ተስፋ ማስቆረጥ፣ ሌላ ጠንካራ ተቃዋሚ እንዳያንሰራራ ማፈን እና እኮኖሚዉን እንደመቆጣጠራቸዉ በጥቅም በጉያቸው የሚያስገቧቸዉን ማብዛት።
አገዛዙ እነዚህን የክፋት ስትራቴጂዎች ይዞ ሲንቀሳቀስ፣ በተቃዋሚ ወገን ያሉት ግን ፣ የአገዛዙን ተንኮል ለማምከን ፣ ተመጣጣኝ ሥራ ሰርተዋል ማለት አይቻልም።
«ተባበሩ ወይንም ተሰባበሩ» የሚባል አባባል አለ። ትብብር መልካምና ወሳኝ ነዉ። «መተባበር ያስፈልጋል» ተብሎ ግን የማይሆንና የማይሰራ ትብብር ዉስጥ መግባት ግን ችግር አለዉ። ገዢውን ፓርቲ በተለያዩ ምክንያቶች ስለሚቃወሙ ብቻ፣ ደርጅቶች አንድ ላይ መሰባሰብና መቀናጀት የለባቸውም። የቅንጅቱ ወይም ትብብሩ መስፈርት «ኢሕአዴግን መቃወም» ከሆነ ትልቅ ስህተት ነዉ የሚሰራዉ። ነገር ግን ትብብር/ቅንጅት የሚፈጥሩ ድርጅቶች፣ በፖለቲካ አቋሞቻቸውና ፕሮግራሞቻቸው የተቀራረቡ፣ አብረዉ ሊሰሩ የሚችሉ መሆን አለባቸው።በፖለቲካ ፕሮግራሞቻቸው መሰረታዊ ልዩነቶች እያሉ፣ የሚደረግ ትብብር፣ በሂደት መፍረሱ አይቀርም።
ኢትዮጵያ ዉስጥ በርካታ ደርጅቶች አሉ። አብዛኞቹ አገር አቀፍ ሲሆኑ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ አንድን ጎሳ ብቻ ያቀፉ ናቸው። በጎሳ ድርጅቶችና በአገር አቀፍ ደርጅቶች መካከል በጋራ ሊሰሩ የሚችሉ ስራዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን እነዚህ ድርጅቶች ሊቀናጁ አይችሉም። ለምን መሰረታዊ የፖለቲካ ፕሮግራም ልዩነቶች አሏቸዉና። (የጎሳ ድርጅቶች በአገር አቀፍ ደረጃ መደራጅት ጥቅሙ ገብቷቸው፣ የአቋም መሸጋሸግ እስካላደረጉ ድረስ)
ከጎስ ድርጅቶች ዉጭ፣ በርካታ ተመሳሳይነት ያላቸው አገር አቀፍ ደርጅቶች እንዳሉ ይታወቃል። ለምሳሌ መኢአድ፣ አንድነት፣ ሰማያዊ እና ኢዴፓ ፣ አራቱም ቅንጅት የነበሩ፣ ተመሳሳይ የፖለቲካ ፕሮግራም ያላቸው ድርጅቶች ናቸው። አራቱም አሁን ያለዉ በዘር ላይ የተመሰረተ ከፋፋይና ዘረኛ ፌዴራል አወቃቀር መቀየር አለበት ብለው ያምናሉ። አራቱም ለሁሉም ዜጎቿና ብሄረሰቦቿ እኩል የሆነች አንዲት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትመሰረት ይፈልጋሉ። አራቱም ኢትዮጵያ የባህር በር ሊኖራት እንደሚገባ በማስረገጥ፣ የአልጀርሱን ስምምነት ይቃወማሉ። አራቱም አሁን ባለዉ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችና የመሬት ጥያቄ ዙሪያም ተመሳሳይ አቋም አላቸው። በአጭሩ አራቱም ቀድሞ በሕዝብ ትልቅ ድጋፍ አግኝቶ የነበረዉን የቅንጅት ማኒፌስቶን ይቀበላሉ።
እንደዚያም ሆኖ ግን እነዚህ ድርጅቶች፣ አብረዉ እንደገና መቀናጀት እስከአሁን አልቻሉም። ይሄ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ዴሞክራሲን ለተጠማው ወገናችን በጣም አሳዛኝ ሲሆን፣ ለአገዛዙና ለአምባገነኖች ደግሞ በጣም ያስደሰተ ዜና። ይሄ በአስቸኳይ መቀየር ያለበት ይመስለኛል።
በአቶ ልደቱ አያሌው ይመራ የነበረው ኢዴፓ፣ ምን አይነት ሁኔታ ላይ እንዳለ ብዙም አላውቅም። በምርጫ 2002 ኤዴፓዎች፣ በአንዳንድ ጉዳዮች ከኢሕአዴግ ጎን በመሰለፍ ፣ ከሌሎች ተቃዋሚዎች የተለዩ እንደሆኑ ለማሳየት ሞክረው ነበር። ነገር ግን ያ አካሄዳቸው ብዙ ዉጤት ያመጣላቸው አይመስለኝም። ይሄን በሚገባ እነርሱ እራሳቸው የተረዱ ይመስለኛል።
አንዳንዶቻችን ደግሞ መረጃ ሳንይዝ፣ በኢዴፓ አመራሮች ላይ ስንዘነዝራቸው የነበሩ በርካታ ክሶችም ጠቃሚ አልነበሩም። ይህ፣ ከኢሕአዴግ ጋር ደምሮ ፣ ኤዴፓዎችን የማጥቃት ዘመቻ፣ ኤዴፓ ወደ ኢሕአዴግ እንዲጠጋ በማድረጉ አንጻር አስተዋጾ ያደረገ ይመስለኛል። እኛ ነን ወደዚያ የገፋናቸው። ሕወሃት/ኢሕአዴጎች ብልጥ ናቸዉና ፣ ሆን ብለው ለ ኤዴፓ ነገሮችን በማመቻቸት፣ በደስታ አስተናገዷቸው። በዚህም መልክ ኤዴፓን ኒዉትራላይዝድ የማድረግ አላማቸው ከሞላ ጎደል ተሳካ።
እንግዲህ ኤዴፓዎችና እኛ ብዙ ተባብለናል። ብዙ ስህተቶች ሰርተናል። ነገር ግን ወቅቱ ትብብርን ይጠይቃል። «ያለፉትን ቁርሾዎች ወደ ጎን በመተዉ፣ በፖለቲካ ፕሮግራም ከሚመሳሰሏቸው ጋር ኤዴፓ አብሮ መስራት መጀመር ይገባዋል» እያልኩ ሌሎቻችን ደግሞ ኤዴፓን ለመቀበል እንድንዘጋጅ እጠይቃለሁ። ለምን ሕወሃት/ኢሕአዴግ ያሸንፋል ?
ወደ ሰማያዊ ፓርቲ ስንመጣ ይሄን እላለሁ። የሰማያዊ ፓርቲ፣ አዲስ ፓርቲ ቢሆንም በአጭር ጊዜ ውስጥ የገነነ ፓርቲ ለመሆን ችሏል። በተለይም የአመራር አባላቱ ድፍረትና ቆራጥነት በዉጭ አገር ብዙ ደጋፊዎችን አፍርቶላቸዋል። ለዚህ በወጣቶች ለሚመራ ድርጅት፣ እኔም በግለሰብ ደረጃ ትልቅ አድናቆት አለኝ።
ነገር ግን ሰማያዊዎች አንድ ማስተካከል ያላባቸው ጉዳይ አለ። ከሌሎች ድርጅቶ ጋር የመስራት ፍላጎት ብዙም ያላቸው አይመስልም። በትብብርና በአንድነት ማመን ይኖርባቸዋል። ለጊዜው ትልቅ የሆኑ ቢመስላቸው፣ አይሳሳቱ፣ ለብቻቸው ብዙ ርቀዉ እንደማይሄዱ ላረጋግጥላቸው እወዳለሁ። ይህ የ«ብቻህን ተጓዝ» አቋማቸዉን ትተው፣ ከሌሎች፣ በፖለቲካ ፕሮግራም ከሚመሳሰሏቸው ጋር አብሮ መስራት መጀመር ይጠበቅባቸዋል። በተለይም ደግሞ በዉጭ ካሉ ጽንፈኛ ፖለቲከኞች መጠበቅ አለባቸው። በአገር ቤት ካሉ ወንድሞቻቸው ጋር በበጋራ በመሆን ትግሉን ከአገር ቤት መምራት አለባቸው እንጂ ዉጭ ባሉ መመራት የለባቸዉም።
ወደ መኢአድና የአንድነት ፓርቲ ስመጣ ደግሞ፣ ተስፋ ሰጪ ምልክቶችን እያየው መሆኔን መግለጽ እወዳለሁ። ለዚህም አንድ ምሳሌ ልጥቀስ። አቶ አበባዉ መሃሪ ጌታነህ ይባላሉ። የአንጋፋዉ የመኢአድ ሊቀመንበር ናቸው። በቅርቡ ኤስ.ቢ.ሲ ከተባለ ራዲዮ ጣቢያ ጋር አጭር ቃለ መጠይቅ አድርገው ነበር። «ከአንድነት ፓርቲ ጋር ለመዋሃድ በንግግር ላይ መሆናችሁ ይነገራል። ይህ ምን ያህል እዉነት ነዉ። ከሆነስ ከዉህደቱ ምን ፋይዳ ይገኛል ይላሉ ?» ተብለው ሲጠየቁ፣ አቶ መሃሪ የሚከተለዉን ነበር የመለሱት።
«ሂደቱ እዉነት ነዉ። ተጀምሯል። የሁለቱ ፓርቲዎች ፍላጎት ያሳዩበት ሁኔታ ነዉ ያለው። በእዉነት ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሚያመች ሁኔታ ይሄ ድርድር ይጠናቀቃል። የኢትዮጵያን ሕዝብ የድል ባለቤት ወይንም የመብቱ ባለቤት ያደርጋል ብለን እናስባለን። ይሄ ዉህደት የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ ነዉ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ “ወይ ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ” የሚል ነዉ። ሕዝቡ የትብብርን ግፊት እያደረገ ነዉ። “አንድ ላይ ሆናችሁ ይሄን ክፉ መንግስት መገርሰስ አለባችሁ። አንድ ላይ ካልሆናችሁ ለዉጥ ማምጣት ያስቸግራል” እያለ ሕዝቡ ግፊት እያደረገ ነዉ ያለዉ። ይሄንን የሕዝቡን ፍላጎት ምክንያት በማድረግ እየተደራደርን ነዉ» [1]
መኢአድ በአገሪቷ ክልሎች ሁሉ መረብ ያለዉ ፣ ከአንጋፋዉና ተወዳጁ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ጊዜ ጀመሮ፣ ለኢትዮጵያ አንድነትና ለዜጎቿ መብት የታገለ አንጋፋ ድርጅት ነዉ። እልም ያለ የአገራችን ገጠሪቷ ክፍል ብትሄዱ በዚያ መኢአድ አለ።
የአንድነት ፓርቲ በበኩሉ፣ በቅርቡ በደሴ፣ ጎንደር፣ መቀሌ፣ አርባ ምንጭ ፣ ባህር ዳር፣ ፍቼ፣ ባሌ ሮቢ፣ ጂንካ፣ አዳማ፣ ወላይታ ሶዳ ..በመሳሰሉ የአገሪቷ ክፍሎች፣ ባደረገዉ የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት እንቅስቃሴ በግልጽ እንዳሳየው፣ በጣም ጠንካራ ድርጅታዊ መዋቅር ያለው፣ አገር ዉስጥ ሆነ በዉጭ አገር በስፋትና በብዛት ደጋፊዎችን ያፈራ፣ በሳል ደርጅት ነዉ።
የመኢአድና አንድነት መቀራረብ ወቅታዊ፣ ትግሉን አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያስኬድ፣ በማያሻማ መልኩ የኢትዮጵያን ፖለቲካ የሚቀየር መልካም ዜና ነዉ። ይሄ፣ ሕዝቡ እነርሱ የሚሉትን ብቻ በፍርሃት አሜን ብሎ እንዲቀበልና አማራጭ እንዳይኖረዉ የሚፈልጉ ሕወሃት/ኢሕአዴጎችን የሚያስከፋ ነዉ። እንግዲህ የስርዓት ለዉጥ እንዲመጣ ከተፈለገ፣ ይህ አይነቱ፣ አገዛዙን ከመስደብና ከመርገም ያለፈ፣ ነገር ድርጅታዊ ጥንካሬን በሕዝቡ ዘንድ የሚያጎለብት፣ የሕዝቡን አመኔታና ድፍረት የሚያሳድግ፣ በሳል የፖለቲካ ሥራ መሰራት አለበት።
መኢአድ ከጥቂት ወራት በፊት አዲስ አመራር አባላትን መርጧል። የአንድነት ፓርቲም፣ በቅርቡ በሚያደርገዉ ጠቅላላ ጉባኤ፣ አዳዲስ ወጣቶችን በብዛት ያካተተ አመርሮችን ይመርጣል ተብሎ ይጠበቃል። ከአዳዲስ አመራሮች ጋር፣ የመኢአድና የአንድነት መቀናጀት እዉን ይሆናል የሚል ትልቅ ተስፋ አለኝ። እድነ አንድ ኢትዮጵያዊም የመኢአድ እና የአንድነት አመራር አባላትን እያደረጉት ባለው ዉይይት «በርቱበት፣ ቀጥሉበት፤ ለሕዝቡም መልካም ዜና አሰሙት» እላለሁ።
እግዚአብሄር ያክብርልኝ !
[1] http://www.sbs.com.au/yourlanguage/amharic/highlight/page/id/303599/t/Interview-with-Abebaw-Mehari/