Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ኢትዮጵያዊነት የመንፈስ ንባብ ነው –ለእኔ! ከሥርጉተ ሥላሴ

$
0
0

ከሥርጉተ ሥላሴ 11.01.2014

sreateሰንበትን እንደ መክለፍት በእኛነት ዙሪያ ልል አሰብኩ። …  … አብሶ ሩሄን በትዝታ በሚያባክኑኝ ዬውስጥ – ለውስጥ የመንፈስ ሃዲዶች ዙሪያ ትንሽ ማለት ወደድኩ። የጹሑፉ ጥራት እስተዚህም ነው። ግን የሃሳቤ ፍሰት ማንነቴን ስለሚዳስስልኝ፤ ፍቅሬን – ትዝታዬን ይመግበኛል። ኢትዮጵያዊነት ንባብ ነው። ሲፈቀድልን ብቻ ማንበብ እንቻላለን። ኢትዮጵያዊነት ትርጉም ነው፤ ሲፈቀድልን ብቻ መተርጎም እንቻላለን። ኢትዮጵያዊነት ሚስጢር ነው ሲፈቀድልን ብቻ ነው፤ ቁልፉን መክፈት የሚችለው። ኢትዮጵያዊነት የመኖር ሕይወት ነው ሲፈቅድልን መታደስ ይቻላል፤ ለዛውም አምሮብን። ኢትዮጵያዊነት መንፈስ ነው፤ ሲሰጠን ብቻ ዓይናችን ይከፈታል …. በስተቀር ዲዳ ሃሳብ ማስተናገድ ዕጣችን ይሆናል። ይህ ደግሞ ቅርስ አልባ ባዶነት፤ እርሾ አልባ ዘርየለሽ መሆን ነው። አያድርስ!

 

ኢትዮጵያዊነት ፍጹም ተወዳዳሪነት የማይገኝለት ተናፋቂ ማንነት ነው። ናፍቆቱ ውስጥን እንደ አሻው ገዝቶ አፍርህን በህሊናህ ስትቃኘው ፍውሰትን ያድልኃል፤ው ደግሞ ውበቱ ይቆጣጠርኃል። ስትፈቅድለት ትድናለህ። እሺ ስትለው ትፈወሳለህ፤ በስተቀር ግን ጉጉ ማንጉግ የሆነ አንካሳ መንፈስ ይጨፍርብኃል …፤ እስኪበቃው ያጨቀይኃል። አሸንፈውና ውጣ! … አሸናፊነትን ዋጥ አድርገውና ውስጥህን አሳምርብት …. ጌጥ ይጣላልን?

 

እንጀራን ስትወደው፤ ሽሮ ሰፍ ሲያደርግህ፤ ቁርጡ ሲታይህ፤ ቆሎው ሰፍ ሲያደርግ፤ ምቸት አብሹ ውል ሲልህ፤ ክትፎው ሲመጣብህ ሚጥሚጣዋን ስትዳስሳት፤ ቆጮን ስታላምጠው፤ ጭኮውን ቀረብ አድርገህ ስታሸተው፤ ዳቦው በእንሰት ወይንም በኮባ ተደፍቶ ከነክብሩ በሞገስ  በቁንዶ በርበሪ ለምለም ዝንጣፊ ወይንም ጉዝጓዝ ተሽሞንሙኖ ሲታይህ፤ አንባሻው ሲሸትህ፤ ንፍሮው ሽው ሲልህ፤ ዝግኑ – ጥብሱ – ቅቅሉ – ጎረድ  ጎረዱ፤ ዝልቦው፤ ቦዘናው፤ ገንፎው ቅንጨው፤ ጨጨብሳው፤  ፍርፍሩ ሲያሰኝህ ዕወቀው ይህ ስሜት ውስጥህን ገዝቶ አንተነትህን የሰጠህ ስለመሆኑ። በጣም በእርግጠኝነት  ከዚህ ፈጽሞ አታመልጥምና ውበቱን አጊጥበት! ….

…. አንተን አሳምሮ የሚገልጸህ ተራጓሚህ መሆንህን አትዝለለው፤ እርቀህ የማትርቀው ወስጥህ ነውና – አድምጠው።

ቄጤማው ለሽ ብሎ … ረከቦቱ ተኮፍሶ፤ ጭሱ ትጉልል – ትጉልል እያለ ሀገር ምድሩን ሲያካልለው፤ ማዕዛው የእጣኑ ዝንቅንቁ ጨስጨስ ሲል፤ ፍንጃሉ ወይንም ስኒው ላይ የፈረስ ጭራ መስሎ ቆረር ሲል፤ ጤናዳሙ ጣል ብሎ ወይ በወተት ወይ እንዲሁ፤ ጨው ሆነ ማጣፈጫ ታክሎበት ፉት ፉት – ትኩስ ትኩሱን፤ ዳበስ አድርገው – ሁንለት።  የቡና ቁርሱ በቀለምሽሽ ተሽሞንሙኖ ቀረብ ሲል ቸርፈስ፤  ዘንጣፌ ሚጢሚጣዋ በተን ብላበት፤ ወይ ዳቦዋ … በህብረት  በአብሮነት  ሰምሮ ከልብህ ከት ብለህ ስትስቅ – ስትተራራብ … ያ ነው ፎሎቄው አንተነትህን የሰጠህ ኢትዮጵያዊነት። ይህን ዘለህ ወይንም ጨፍልቀህ ልትሄድ ብትል አይሆንም —  አትችልም በፍጹም፤ እባክህን አትግደርደር። አንተ ማለት የዚህ ውጤት ጭማቂ ነህ።  ማንነትህ የተቀዳው ከዚህ ማርን ከሚያዘንብ ባህል ነው። እዚህ ላይ ያለው ንባብ ልዩ ነው … ይጣፍጣል፤ መንፈስን በሽብሸባ ዘና ያደርጋል፤ በዜማ ይቃኛል። ግን ትጉህ አንባቢ ይሻል – ስትታደል ይገለጽላኃል በስተቀር …. አንተን እራስህን ተላልፈኸዋል …. ተመለስ! የተፈጥሮ መስተውትህን ድጠህ አትስበረው። ይህ ቅልቅል ግን ውህድ ውብ ቅመም ቁንጅናህ እንዲሆን …. አብስለው።

 

ዋው! ስንቱ ይዘርዘር …. የንብ አውራ በመሰለ ሽንጣም ሞሰብ፤ ሌማት፤ ጥራር፤ ሰብሰብ ብለህ ስተታድም፤ ስትጎራራስ፤ በሞቴ አፈር ስሆን፣ ይህችን ይሀችን ብቻ!ች በእኔ ሞት ወይንም በእከሌ ወይንም በእከሊት ሞት እየተባልክ በአፍ በእፍህ ፍቅርን ተጥቅልሎ ስትጎርስ ዬት እንደተቀዳህ ሹክ ይልኃል፤ ጣዕሙን ኑርበት – ለራስህ ብትል። አድምጠው አንተን እራስህን አግኝተህ አንገትህን ቀና አድርገህ እዬው፤ የነፃነት ቅኔ ዘጉባኤ በራስ መተማማን ስሜት እንዲፈነድቅ የረዳህ አንትን በአንተነትህ የፈጠረህ ቅዱስ መንፈስ ነው። የራስህም ጌታ እንድትሆን …. ያደርግኃል። አስተውል እባክህን? … ምንጩ ይህ ነው የማንነትህ ፈርጥ። ስታከበረው ማን እንደ አንተ ጌታ! ውስጥህ የባዕድ ሽፍትንት እንደይጨፍርበት ካልፈቀድክ፤ አንተ ዬዛ የጥቁር አንበሳ ደም ትውፊት ስለመሆንህ አሳምሮ ይነገርኃል – ያስተምርኃል። የዚህ ልዑቅ ንጥር አካል ቤተኛ – ተጋሪ መሆንህ ተሰጥቶኃልና እንኳን ደስ አለህ። …. እንዳይሾልክብህ ግን ጠብቀው!

 

… ያደክበት፣ ያ … ሜዳማ መስክ? ወይንም ያ … ጋራ ሸንተረሩ – ጅረቱ – ፋፏፈቴው የእነ-ባሮ፤ ፤ ዬእነ -አንገረብ የእነ-ጣና የእነ-አባይ፤ የእነ-መረብ፤ የእነ-ቀኃ፤ የቢሸፍቱ ሐይቅ ወዘተ የሌሎችንም ዋናና ገባር ወንዞች፤ ሐይቆች፤ጠረን – ስበት ከልብ ሆነህ መርምረው፤ እዬተራጨህ ትጫወትበት የነበረው ንፁህ አዬር በቅንነት ቅዘፈው፣ ሂድበትበት፤ ዋኝበት፤ ተፈጥሮህ የተቀመረበት የአንት ጸጋ ነው፤ ወስጥህን አሳምርበት፤ የአንተ ልዩ መለያ የተቀረጸበት መንፈስ ነው። በልጅነት ጊዜ ሰኞ ማክሰኞው፤ ቅልሞሹ፤ ገበጣው፤ ድብብቆሹ፤  በማዕድ ጥያቄ ተጠይቆ ላልመለሰ መሸነፉን እድምተኛው ሲወስንበት ፍርዱን ተቀብሎ ተሸናፊው የማይበላውን እንዲባላ በድምጽ ብልጫ ሲወሰንበት፤ ወርርዱ፤ ያ ውድና ደግ የልጅነት ዘመንህ የሰጠህ – የለገሰህ – የሸለመህ ረቂቅ ፍቅርን ካሰብከው በመንፈስህ እንዲሸራሸር ከፈቀድክለት እሱ ነው ተነስቶ የማይጠገብ ኢትዮጵያዊነት ማለት … አትረሳውም አይደል? ወደ ዛ … አዎንታዊ ዕውነት የህሊና ዓይን ላከው … ትበራለህ!

 

የምንጩን ውኃ ገለጥ – ገለጥ አድርገህ ፎልፎል የሚለውን ጎንበስ ብለህ ጠጥተህ ስትራካ እሱ ነው የአንተነትህ ቅኝት – እሺ! ተከታይህም ተራው ሲደርስ ትራፊ ነው ሳይል ተጎንብሶ ጥሙን ሲያረካ አንተ የተቀዳህበት ማንነት እሱ ነው ወርቅ ጸጋ ተመቸው! በቆሬ – በግሬራ – ወተቱ ከዛው ታልቦ ትኩሱን በርከክ ብለህ ስትጎነጭ አቤት ፍሰኃው! ይህ ለውስጥህ በገፍ ማንነትህ ያበቀለ መክሊትህ ነውና አጣጥመው! እርጎውን በፋጋ ጎንበስ ብለህ ውስጥህ ራስ ስታደርግበት፤ እርጎው በጉርና ተገፍቶ ቅቤው ሲወጣ፤ ትኩሷና አናትህን ረጠብ ስታደርግህ ነጮቹ ያልደረሱበት ሳውና ይሉኃል ይህ ነው።

 

ይህ ማንነት ተቀድቶ ያማያልቅ የኤዶም ገንት ነው … ግን ሚስጢር የመተርጎም ብቃቱ ካለህ፤ ከላይ … ከላይ የማታነበንብ ከሆንክ ብቻ …. ይህ መንፈስ ነው ማንነትህ የጸደቀበት – የበቀለበት – ያፈራበት። አትለፈው —-  ነገ ውስጡን አታገኘውማና ጠንቀቅ ነዋ!  አንተ ከሸፍትክበት እሱም ጀርባውን መስጠቱ አይቀሬ ነው – በጊዜ! …. በአንኮላው – በዋንጫው – በብርሌው ጥሩው ገፈታውን እፍ እፍ ብለህ ለቀቅ ስታደርገው፤ በተኃዋን በብርሌ ቆረር እያደረክ ወደ ሰራዊቶችህ ስትልከው፤ ቡቡኙምንም ጥምህን ሲያባርር ረጠብ የሚያደርግህ ያ ውስጥነት ህይውት እስበው፤ ፍቀድና ….  ዘና አድርገህ አጣጥመው … አስላው …. ቁጠረው ….  ሥፍር ቁጥር የሌለው ሐሤት ታገኝበታለህ። ያ ሐሤትህ የተጸነሰበት ጀግናው ማንነትህ፤ የነጠረው የአንተነትህ ጮማ ነው ….

 

ቁምጣዋን፤ ቦላሌዋን፤ ሽርጡን፤ ሳንጃውን – ኮልቱን – አልቢኑን – ግልቢያውን – ዋናውን ጉዞውን – ሁሉንም ከልብህ ሆነህ እሰባቸው፤ በምልሰት ጊዜ ሰጥተህ አጫውታቸው፤ ይሰጥህ የነበረውን ደስታ ምልሰት አድርገልት፤ ያ ነው ውዱ ዕሴትህ፤  ሙሉ ወርዱ፤ ሽብሽብዎ በመቀነት ሸብ ሲል፤ ጃኖው ቀለማሙ ህይወት፤ ጥልፋማ ማንነትህ የተወለደበት ውስጥህ ነው …. ከመንፈሰህ ጋር ስለመሆንህም አረጋግጥ …. ጤናማነትን ይሸልምኃል።

 

እርገት። ኢትዮጵያዊነት ጥሪኝ አለው። ኢትዮጵያዊነት ሥራዓትን ፈጥሮ ጨዋነትን ያበቀለ፤ መቻቻልን ውጦ በውስጡ ያጸደቀ፤ ትእግስትን ተቀበሎ ውስጥን የሚዳኝ የፍቅር ቤት ነው። እያንዳንዱ የአመጋገብ፤ የአኗኗር፤ የዕምነት፤ የወግና የልምድ ሞራሉ ልራቅህ ቢባል የማይቻል፤ መስጥረን፤ ተሸሽገን፤ ተቆራኝተን እዬኖርን ግን ቅብ ሽፍትነት ብታቆለባባስ ትርፉ ትዝብት ብቻ ነው ውጤቱም ባዶነት።

 

ምስጋናዬ ከልብ ነው። ኑሩልኝ የኔዎቼ።

 

ወስጤን ከሽኖ ጌጠኛ ያደረገው፤ የውበቴ ማርዳ፤ የመንፈሴ ዘውድ፤ ኢትዮጵያዊነት ይኑር ለዘለዓለም!

ፈተናን ከመፈጠሩ በፊት አሸንፎ የተፈጠረ ማንነት – ኢትዮጵያዊነት!

 

 

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles