Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የአሰብ ጉዳይ:- “ጦርነት ፈርተን ግን ሀገራችንን አሳልፈን አንሰጥም”–ከአብርሃ ደስታ

$
0
0

 

ገና በጠዋቱ “ዓሰብን ማስመለስ አለብን የምትለው እንዴት ነው? ወደ አላስፈላጊ ጦርነትና ደም ማፋሰስ ልታስገቡን ፈለጋቹ?” የሚል አስተያየት አዘል ጥያቄ አገኘሁ።
asab port
መጀመርያ ወደ ጭንቅላታችን መምጣት ያለበት ጉዳይ ‘የዓሰብ ወደብ የማነው?’ የሚል ነው። ዓሰብ የኢትዮጵያ ልአላዊ ግዛት (ንብረት) ስለመሆኑ ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊና ሕጋዊ (በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት) ማረጋገጫዎች አሉን። ዓሰብ የኛ ስለመሆኑ የሚያጠራጥር ምንም ምክንያት የለም። ማስረጃዎቹ (ማረጋገጫዎቹ) እዚሁ ፌስቡክ ላይ ባልፅፋቸውም በወደቡ ባለቤትነታችን ጥርጣሬ አይግባቹ። ስለዚህ ጥያቂያችን ፍትሐብሄር ነው።

ሁለተኛ ጉዳይ ዓሰብ የኛ ቢሆንም አሁን ያለው ግን በኤርትራ ቁጥጥር ስር ነው። ንብረት ሃብታችን ተነጥቀናል ማለት ነው። ጥያቄው መሆን ያለበት ‘ዓሰብ ወደብ ለኢትዮጵያ ያስፈልጋል?’ የሚል ነው። መልሱ: ‘አዎ! ያስፈልጋታል’ ነው። የባህር በሯን የተነጠቀች ብቸኛዋ ትልቅ ሀገር ኢትዮጵያ ናት። በአሁኑ ግዜ የባህር በር የአንድ ሀገር የህልውና በር ነው። የህልውና በሩ መዘጋት የለበትም። ስለዚህ ኢትዮጵያ ንብረቷ (ወደቧ) የማስመለስ መብትም ታሪካዊ ግዴታም አለባት።

 

ሦስተኛ ‘እንዴት ነው ወደቡን ማስመለስ የምንችለው?’ የሚል ጥያቄ ማየት ተገቢ ነው። ምክንያቱም ዓሰብ የኢትዮጵያ ቢሆንም በመሪዎቻችን ሐላፊነት የጎደለው ዉሳኔ ምክንያት ለኤርትራ ተሰጥቶ ይገኛል። ‘ወደባችን አለ አግባብ ለኤርትራ በመሰጠቱ ምክንያት ዓሰብን የማስመለስ ጉዳይ ከባድ ሊያደርገው ይችላል’ የሚል ሐሳብ ቢነሳ አግባብነት አለው። ጦርነትም ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት ሊቀቅ ይችላል።

ግን ማትኮር ያለብን ስለ ጦርነት አይደለም፤ ስለ ዓሰብ ንብረትነት እንጂ። ዓሰብ የኛ መሆኑ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ማረጋገጥ (ማሳመን) ይኖርብናል። በዓሰብ ጉዳይ ፅኑ አቋም ይዘን የኢትዮጵያም የኤርትራም ህዝብ እንዲገነዘበው መጣር አለብን። የዓለም ህዝብ ይሁን መንግስትታት ይደግፉናል። ምክንያቱም የባለቤትነት መከራከርያ ነጥባችን ጠንካራ ነው። የዓለም አቀፍ ሕግም ይደግፈናል። ዓሰብ የኢትዮጵያ ስለ መሆኑ የሚመሰክግሩ የተለያዩ ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶችም አሉ።

አራተኛ ዓሰብ የኛ መሆኑ ቢናረጋግጥና ለዓለም መንግስታትና ማህበረሰብ ቢናሳውቅ እንኳ እንዴት ዓሰብን መመለስ እንችላለን? የኤርትራ መንግስትኮ ፍቃደኛ አይሆንም፣ ጦርነት ሊነሳ ይችላል … ወዘተ የሚሉ ጉዳዮች መነሳታቸው አይቀርም። ግን ችግር የለውም። ዓሰብ የኛ መሆኑ ካረጋገጥን ‘ንብረታችን መልስልን’ ብለን የመጠየቅ መብት አለን። የኤርትራ መንግስት ፍቃደኛ ላይሆን ይችላል። ጦርነትም ሊከፍት ይችላል።

እኛ ጦርነት አንፈልግም። ሕጋዊ ንብረታችን (ወደባችን) በሰለማዊ መንገድ እንዲሰጠን ነው የምንጠይቀው። አዎ! ጦርነት አንፈልግም። ጦርነት አንፈልግም ማለት ግን ጦርነት ከፍተን በሃይል የሌላ ሀገርና ህዝብ ንብረት አንወርም ማለት እንጂ ጦርነት ፈርተን ልአላዊ ግዛታችን (ሃብታችን) ለሌሎች ሃይሎች አሳልፈን እንሰጣለን ማለት አይደለም። ጦርነት አንፈልግም ማለት ጦርነት እንፈራለን ማለት አይደለም። አዎ! ጦርነት ስለማንፈልግ ሌሎች ህዝቦችን አንወርም። ጦርነት ፈርተን ግን እናት ሀገራችን አናስደፍርም።

ጦርነት ስለማንፈልግ ዓሰብን በሰለማዊ መንገድ የምንረከብበት መንገድ እናመቻቻለን። የኤርትራ መንግስት ጦርነት ሊከፍትብን ይችላል ብለን ግን ሃብት ንብረታችን ከመጠየቅ ወደኋላ አንልም። ጦርነት ተፈርቶኮ የሀገር ግዛት አሳልፎ አይሰጥም። ጦርነት ተፈርቶኮ ልአላዊ ግዛትን ከማስከበር ወደኋላ አይባልም። በባድመ ጉዳይ ጦርነት ዉስጥ የገባነው ጦርነት ስለምንፈልግ ሳይሆን ልአላዊ ግዛታችን የማስከበር፣ ሀገራችን ከወራሪዎች የመከላከል ሀገራዊ ግዴታ ስላለብን ነው። ጦርነት ፈርተን እጃችንና እግራችን አጣጥፈን የባድመን መሬት ለሻዕቢያ ወራሪዎች አሳልፈን አልሰጠንም።

(በኋላ በፖለቲካዊ ዉሳኔ፣ በመሪዎቻችን ግድየለሽነት ምክንያት ባድመን መስዋእት ከፍለን በደም አስመልሰን ሲናበቃ በእስክርቢቶ ለወራሪዎች ተላልፎ ተሰጠ እንጂ። በጦርነት የተመለሰ ንብረት በድርድር ሲከሽፍ በታሪክ ለመጀመርያ ግዜ ነው። የባድመ ጉዳይ …!)

ምንም እንኳ ጦርነት ባንፈልግም ሃብት ንብረታችን ግን አሳልፈን አንሰጥም። ጦርነት መስዋእት ይጠይቃል። ግን ለሀገራችን መስዋእት ብንከፍል ችግሩ ምንድነው? ለሀገራችንኮ መሞት አለብን። በምንክያት መስዋእት መሆን እንቻላለን። ደግሞኮ ኢህአዴጎች የዓሰብን ጉዳይ ስናነሳባቸው ‘ጦርነት ናፋቂዎች’ ይሉናል። እኔ ግን ለሀገር መስዋእት ብንከፍል ጉዳት የለውም ባይ ነኝ። እንኳንም ለሀገራችን ኢትዮጵያ ለሶማሊያም እየሞትን ነው። ይቅርታ ለሶማሊያም እየሞትን አይደለንም። ምክንያቱ ላልታወቀ ጉዳይ ነው በሶማሊያ እየሞትን ያለነው። ወታደሮቻችን በሀገረ ሶማሊያ እየሞቱ ያሉ ለምን ዓላማ ነው? ዜጎቻችን ዓላማው ለማይታወቅ ጉዳይ በሶማሊያ ከሚሞቱ ለሀገራችን ቢሞቱ አይሻልም ነበር? ኢህአዴጎች ‘ጦርነት ጥሩ አይደለም’ ይሉናል። ጦርነት ጥሩ አለመሆኑ ቢያውቁ ኑሮ ለምን በሶማሊያ ያሉ ወገኖቻችን ወደ ሀገራቸው አያስገቡም?

አዎ! ጦርነት ጥሩ አይደለም። በተቻለ መጠን ጦርነትን ማስወገድ አለብን። ጦርነት ፈርተን ግን ሀገራችንን አሳልፈን አንሰጥም።

አሜን!


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles