«አበው ሲተርቱ ላም ባልዋለበት ኩመት ለቀማ ይላሉ። ሰላም ጠላቱ ከሆነ የአገዛዝ ቡድን ጋራ በሰላማዊ ትግል ገጠሞ ሰለማዊ ድል አስመዘግባለሁ ብሎ ማሰብ ከሰላማዊ ጭንቅላት የሚፈልቅ ሰላማዊ አስተሳሰብ ነዉ ብዬ አላምንም። …ትግል ሱስ አይደለም። እንደ አቦል ቡና ሱስ አይደለም። አሁን የምናየዉ የሰላማዊ ታጋዮች፣ የትግል ሱስ ያለባቸው አይነት ነዉ እንጂ ከዉጤት አኳያ የፖለቲካ ምህዳሩ በጠበበት አገር ዉስጥ ምንም አይነት ለዉጥ ሊያመጡ የሚችሉበት ሁኔታ አይታየኝም። እስካሁን የአገዛዙን እድሜ በማራዘም ረገድ አስተዋጾ እያደረጉ ነዉ ። ምናልባትም የታሪክ ተወቃሽነት ሊያደርጋቸዉም ይችላል። ከልምዳቸውም ተነስተዉ ዉጤት ይመጣክል ብለው ይጠብቃሉ ?»
አንድ አድምጫ ለወጣት የአንድነት ፓርቲ አመራር አባላት፣ ም/ፕሬዘዳንቱ አቶ በላይ በፈቃዱና የሕዝብ ግንኙነት ክፍላ ሃላፊዉ አቶ ሃብታሙ አያሌዉ፣ በኢሳት ያቀረቡት አስተያየት በዛሽ ጥያቄ ነበር።
አሁን በስልጣን ላይ ያለዉ መንግስት፣ የሰብአዊ መብትን የሚረገጥ፣ ፍርድን የሚያዛባ ፍጹም አምባገነን እንደሆነ ሁላችንም የምናወቀው ነዉ። ታዲያ ምንድን ነዉ መፍትሄዉ ?
አራት አማራጮ ነው ያሉት።
1) በግብጽ እና በቱኒዚያ እንደታየው፣ ሕዝብን አደራጅቱ ፣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የእምቢተኝነት ዘመቻ በማካሄድ መንግስት ለሕዝብ ጥያቄ እንዲገዛ ማስገደድ፣
2) በደቡብ አፍሪካ የነጮች ፓርቲ የነበረዉ፣ ብሄራዊው ፓርቲ፣ ፒተር ቦታን አስወገዶ በምትካቸዉ ፍሬደሪክ ደክለርክን በማስመረጥ፣ ከጨቋኙ ፓርቲ ዉስጥ ለዉጦች እንዲመጣ እንደተደረገዉ፣ በኢሕአዴግ ዉስጥ ያሉ ፣ ጥሩ ልብ ያላቸዉ መልካም ሰዎች አይለው እንዲወጡና የሚፈለገዉ ለዉጥ በኢሕአዴግ በራሱ እንዲመጣ ማድረግ፣
3) ሕወሃት/ኢሕአዴግ ደርግን እንዳደረገው መሳሪያ አንስቶ በኃይል የመንግስት ለዉጥ ማምጣት፣
4) አርፎ፣ ባርነትን ተቀበሎ፣ አንገት ደፍቶ፣ እንደ እንስሳ መኖር፣
አብዛኞቹ ኢትዮጵያዊያን አራተኛዉን አማራጭ የመረጡ መሰለኝ። በተለያዩ ምክንያቶች። አንደኛው ፍርሃት ነዉ። ገዢው ፓርቲ ከስራቸው እንዳያባርራቸው፣ ከቤታቸው እንዳያፈናቅላቸው፣ ማዳበሪያ እንዳይከለከላቸው፣ እንዳያስራቸው ……ሁለተኛው ምክንያት ተስፋ መቆረጥ ነዉ። በኢሕአፓ ጊዜ፣ በቅርቡ ደግሞ በቅንጅት የነበረዉን በማስታወስ «አይ ዝም ብለን ነዉ የምንደክመው ለዉጥ እንደው አይመጣም። ተቃዋሚዎቹ ደካማ ናቸው» የሚል አስተሳሰብን በመያዝ፣ አገዛዙን አጉዝፎ የራስን ኃይል ግን አሳንሶ ማየት። ሶስተኛው ምክንያት፣ ዳያስፖራዉ ወይንም ደግሞ «እንዋጋለን» የሚሉ ሽምቅ ተዋጊዎች፣ «ነጻ ያወጡኛል» ብሎ በመጠበቅ ቁጭ ማለትን መምረጥ ነዉ።
እንግዲህ እዚህ ላይ ኢትዮጵያዉያን ማሰብ ያለብን ይመስለኛል። ይሄ አማራጭ ስብእናችንን እና ክብራችንን የሚያወርድ አማራጭ ነዉ። በአጭሩ «ባርነት» ነዉ። ከዚህ አማራጭ ፈቀቅ ብለን መሄድ ያለብን ይመስለኛል። ዘጠና ሚሊዮኖች ሆነን ጥቂቶች በአንገታችን ላይ ቀንበር አስረው፣ ተናገሩ የሚሉንን ብቻ እየተናገርን፣ ቁጭ በሉ ሲሉን እየተቀመጥን እንደ እንሥሳ መኖር የለብንም።
ሌላው አማራጭ ሶስተኛው አማራጭ ነዉ። ነፍጥ የሚያስነሳ ሰላማዊ ያልሆነዉ አማራጭ። ይመስለኛል ከላይ የጠቀሷቸው ኢትዮጵያዊ የሰላማዊ ትግል አማራጮችን አጣጥለው ሲናገሩ፣ ይሄንኑ የጠመንጃ ትግል አስበው ሳይሆን እንዳልቀረ ነዉ። ዜጎች ግፍን ለመቃወም መሸፈት እና ነፍጥ ማንሳት ሙሉ መብታቸው እንደሆነ አያከራክርም። የትጥቅ ትግል አንስተናል የሚሉትን «ለምን አነሳችሁ» የማለት የሞራል ብቃትም የለኝም። ነገር ግን በትጥቅ ትግል አኳያ አንዳንድ መሰረታዊ ሃቆችን ለማንሳት እወዳለሁ፡
የትጥቅ ትግል ሲደረግ ወታደሮች ያሰፈልጋሉ። ወታደሮች ደግሞ ዉሃ አይደለም የሚተኩስት። መሳሪያ፣ ጥይት ያስፈልጋል። ወደ ጦርነት ሲኬድ መቁሰል መጎዳት አለ። በመሆኑም መድሃኒቶች፣ የሕክምና ባለሞያዎች መኖር አለባቸዉ። በትጥቅ ትግሉ የተሰማሩ መልበስ፣ መብላት አላባቸው። ወታደሮችን ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ ለማሰማራት ከባባድ የጭነት መኪናዎች፣ ናፋጣና ነዳጅ የግድ ነዉ። እዚህ ላይ አላበቃም። ወታደሮች የሚሰለጥኑበት ቦታ ያስፈልጋል።
ያኔ ሕወሃት እና ሻእቢያ፣ ድፍን ሱዳን ከጎናቸው ነበር። አሜሪካ፣ አረቦች የሚፈልጉትን ያስታጥቋቸዉ ነበር። አሁን ሽምቅ ተዋጊዎችን ሊረዱ የሚችሉት፣ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ እንደ ጠላት የሚታዩ ሻእቢያ እና ግብጽ ብቻ ናቸው። የግብጽ እና የሻእቢያ አጋር መሆን ደግሞ በቀጥታ ከሕዝብ ጋር የሚያላትም ነዉ። በመሆኑም አስተማማኝ ፣ ደጀን የሚሆን ፣ የሚረዳ አለ ማለት አይቻልም። ይህ የዉጭ ረዳት ኃይል በሌለበት ሁኔታ ፣ የትጥቅ ትግልን እንደ አማራጭ መዉሰድ አያስኬድም።
እርግጥ ነዉ፣ ከላይ እንደጠቀስኩት፣ ኮንቬሽናል በሆነ መንገድ የትጥቅ ትግል ማድረጉ ባያስኬድም፣ ግፍ ሲበዛበት፣ ሕዝቡ ግን በየቀበሌዉና በየወረዳው ጠመንጃ ሊያነሳ ይችላል። ጠመንጃም ከሌለው ቆመጥ። ይህ አይነቱ አመጽ ደግሞ አንዴ ከተለኮሰ፣ ማቆም የማይችልበት ሁኔታም ሊፈጠር ይችላል። ሶሪያን ተመለከቱ። ለስንት አመት ሊባኖስ የሆነቸዉን አስታወሱ። ሶማሊያን አስቡ። ይሄ ከእያንዳንዳችን ቁጥጥር ዉጭ የሆነ፣ እንደ አማራጭ ሊወሰድ የማይችል፣ ገዢዉ ፓርቲ ከወዲሁ ሊስይቆመው የሚችል ጉዳይ ነዉ። ይሄ እንዳይሆን ጸሎቴና ሞኞቴ ነዉ።
እንግዲህ የተሻሉት የምላቸው አማራጭች፣ አማራጭ አንድ እና ሁለት ናቸው። ሕዝቡ ወደ ጠመንጃ ሳይዞር፣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እምቢተኝነቱን እንዲገልጽ ማደራጀቱ ፣ ለዉጥ ከገዢዉ ፓርቲ ዉስጥም እንዲታይ መገፋፈቱ ብቸኞቹ ጠቃሚ አማራጮች ናቸው። እነዚህ አማራጮች እንደ ተጠበቀዉ ዉጤት ላያመጡ ይችላሉ። ጊዜ ለኢፈጁ ይችላሉ። ሶስተኛዉ የጦርነት አማራጭ፣ አማራጭ እንደማይሆን እየታወቀ፣ የሰላም አማራጮቹ አይሰሩም ብሎ መቀመጡ፣ አራተኛዉን የባርነት አማራጭ መምረጥ ነዉ። ከላይ የጠቀስኳቸው ኢትዮጵያዊ ወንድሜም በአገር ቤት የሚደረገዉን ሰላማዊ ትግል በሚያጣጥሉበት ጊዜ፣ አላወቁትም እንጂ፣ «ከቻላችሁ እንደ እኔ ተሰደዱ ፤ አለበለዚያ አርፋችሁ፣ ባርያ ሆናችሁ ተገዙ» እያሉን ነዉ።
አንደኛዉና ሁለተኛዉ አማራጮች ፣ በተለይም በአንደኛው (ሕዝብን አደራጅቶ አገዛዙን ማስጨነቅ) እንዴት ሊሰራ እንደሚችል የሚያመላክቱ አንዳንድ ሃሳቦችን በሚቀጥለው ጊዜ ይዤ እቀርባለሁ።
(በነገራችን ላይ አይሰራም ፣ አያዋጣም የምለው የትጥቅ ትግል አማራጭ ያዋጣል የሚሉ ካሉ፣ ለመማር ዝግጁ ነኝ፡፤ ታዲያ ወሬና ፉከራ ሳይሆን አሳማኝ ነጥቦች ያስቀምጡልኝ። ስለጠመንጃ ማዉራት ቀላል ነዉ። ባሩዱን ማሽተት ግን ሌላ ነገር ነዉ)