……………..
እዚያ ቀዬ
እዚያ መንደር
እነዚያ እልፍኝ
እዚያ ሰፈር
ያሉ ሰወች
ምን ነክቷቸው ሰው መሆንን የሚንቁ
ከራሳቸው የሚጣሉ
ከራሳቸው የሚርቁ
ምን ተውሳክ ነው የምን ደዌ
የምን ዛር ነው የምን ጋኔን
መለያቸው ሀገር መካድ
ጥረታቸው ታሪክ መናድ
ስብከታቸው ማንነትን ማደባየት
ስኬታቸው ሀገር ወዳድ ማሰቃየት
እዚያ ቤት ምንድነው ያለው
መስተፃልእ ከህዝብ ልብ
ለባርነት የሚያሰልፍ
ፍቅር ክብር የሚያጸይፍ
ለውርደት ሞት የሚያሰይፍ
ድንበር እንደጉድ የሚያስንቅ
ቅጥፈት እንደ እናት የሚያስወድድ
ምን ቅጠል ነው ምን ስራስር
ምኑን ዕፅ ነው የሚውጡ
በጠላ ድፍድፍ የሚጋቱ
ለሀገርና ወገን ሳይሆን
ለ’አለቃ የሚሞቱ
ለሀቅ እና ለእምነት ሳይሆን
ለክህደት የሚሟገቱ
የምን ደም ነው በስራቸው
በአካላቸው የሚዛወር
ምን መርዝ ነው በአንጎላቸው
በአእምሮአቸው የሚንፏለል
ከህብረት ይልቅ መነጠል
ከማዳን ይልቅ ማቃጠል
ከእምነት ይልቅ ክህደትን
ወገን ከድቶ ባንዳነትን
የሚያስወድድ
የሚያስመልክ
እጸ ቅጥፈት
እጸ ክፋት
እጸ ሴራ
እጸ ጥፋት
ምን መድሀኒት ነው የሚውጡ?
ምን ሀሺሽ ነው የሚያጤሱ?
ከአናት ወጥቶ የሚያቀውስ
መልካም ሲያይ የሚያንዘፈዝፍ
የህዝብ ውለታ
የሀገር መዝገብ የሚያጎድፍ
ለአድር ባይነት አደቁኖ
በሃሰት ለመፍረድ የሚያቀስስ
መሰረት ለመናድ ተክህኖ
ትውልድ ለማበስበስ የሚያጰጵስ
ከእባብ ምላስ ወተት አይፈልቅ
የባንዳ ደም በውሀ አይለቅ
ተኩላም እርግብ አትወልድ
የሌሊት ወፍ መዓልት አትለምድ
አመላቸው ካልሞቱ በቀር
በአርባም በሀምሳ አመት የማይለቅ
በእርጅና በሽበታቸው
በህይወት ሳሉ የማይደርቅ
አገር አፍርስ በሽታቸው
ተዋህዶ ከመቅኔያቸው
እነሱን አጥምቆ ላይተው
ለሃገር ተረፈ መርዛቸው፡፡
↧
የባንዳ ደም
↧