Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የፈራ ይመለስ! (ከተመስገን ደሳለኝ)

$
0
0

በ2004 ዓ.ም የካቲት 23 ቀን በታተመችው ‹‹ፍትሕ›› ጋዜጣ ላይ፣ ‹‹የፈራ ይመለስ!›› በሚል ተመሳሳይ ርዕስ፣ ከሰላማዊ አብዮት ውጪ አማራጭ ካለመኖሩም ባለፈ፣ ኢህአዴግ ቢያንስ ሕገ-መንግስታዊ ጥበቃ ላላቸው ሕዝባዊ ጥያቄዎች ምላሽ የመስጠት አቅምም ፍላጎትም እንደሌለውለመሞገት ሞክሬ ነበር፡፡ ግና፣ አገዛዙ ለእንዲህ ያሉ ግዴታዎች የተዘጋጀ ባለመሆኑ ከማድመጥ-መዳ–መጥን፤ ከመመከር-መከራን፤ ከማሰብ-ቃሊቲ መሰብሰብን፤ ከመሻሻል-ከሀገር ማሸሽን፤ ከማመን-መርገጥን… በመምረጡ፤ ዛሬም ድረስ ነፃነት ናፋቂው ዘመነኛ ትውልድ፣ በፀጥታ አርምሞ ወደተዋጡት አደባባዮች ከማማተር ያለፈ አማራጭ እንዳያገኝ ገፊ-ምክንያት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ያንን ጽሑፉም ከዓመት ከስድስት ወር በላይ ፍርድ ቤት ከምመላለስባቸው ክሶች የአንዱ መወንጀያ አድርጎ በተከበረችዋ ፍትሕ እየተሳለቀባት ነው፡፡ በርግጥ ጉዳዩ ገና እልባት ያላገኘ በመሆኑ፣ በዚህ ተጠየቅ አናነሳውም፡፡
ያ ጽሑፍ የታተመባት ‹‹ፍትሕ›› ጋዜጣ የስርዓቱ ቅጥ ያጣ አፈና ሰለባ የመሆኗን ጉዳይ ግን ሁሌም ስናወሳው እንኖራለን፤ ምክንያቱም የ‹‹ቅድመ-ምርመራ›› (ሳንሱር) ግብአተ-መሬት በግላጭ በሕገ-መንግስቱ ሳይቀር ከታወጀ ሃያ ዓመት ባስቆጠረበት ኢህአዴጋዊ ዘመን የተፈፀመ ታላቅ መብት ረገጣ ነውና፤ ያውም ተራ የወሮበሎች ረገጣ መሆኑን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ፡፡ በመንግስታዊው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ለዚሁ ሕገ-ወጥ ተግባር አድፍጠው እንዲጠብቁ የተመደቡ ‹ግልገል› ካድሬዎች ጋዜጣዋ የምትታተምበትን ሐሙስ ቀንን በዝምታ አሳልፈው ነገር ግን ድንገት በዕለተ አርብ ማለዳ ‹‹ይህንን ዜና ማውጣት አትችሉም! ቆርጣችሁ አውጡ›› ማለታቸው ነው፤ ምን ዋጋ አለው ትዕዛዛቸው ተቀባይነት ባለማግኘቱ፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ገንዘብ ውጪ የተደረገበትን፣ 30 ሺህ የጋዜጣዋ ህትመት እንዲቃጠል በፍርድ ቤቱ አማካኝነት በጭካኔ በየኑ፤ ‹‹ፍትሕ››ንም በሕገ-ወጥ መንገድ ዳግም እንዳትታተም አገዱ፤ ይህ ሁሉ ከሆነ እነሆ ሃያ ወራት ተቆጥሯል፡፡ ግና፣ የተከፈለው ሁሉ ስለነገ የተሻለች ኢትዮጵያ ሲባል ነውና ባለፈ ጉዳይ ማለቃቀሱን እዚሁ ገታ አድርገን፣ ኩነቱንም ከነጋዴነት ለተሻገሩ ታሪክ ጸሐፊዎች ትተን፣ በአዲስ መስመር ወደ አጀንዳችን እንለፍ፡፡

የፈራ ይመለስ!
አዎ፣ ይመለስ!! ፍርሃቱን ‹‹አሜን›› ብሎ ተቀብሎ ለመመለስ ከወሰነ በመረጠው የጭቆና ቀንበር እየተቀጠቀጠ ማደር መብቱ ነው፤ ግና፣ አንዳንድ ፈሪዎች፣ አንዳንድ መሀል ሰፋሪዎች በስመ ‹‹ጸሐፊነት›› ጥያቄውን በማጣጣል ለውጡን ለማራዘም (ለማደናቀፍ) የሚያደርጉት ሙከራ ከንቱ እንደሆነ በቅድሚያ ላስገነዝብ እወዳለሁ፡፡ ደግሞም እነኚህ የጭቆና ዘመን አራዛሚዎች እያገለገሉት ያለው ስርዓት የሚያከፋፍለው ብሔራዊ ዳቦ እየተመናመነ መምጣቱን፣ ገዥዎቹ ራሳቸው የፓርቲያቸው ችግር (7 ሚሊዮን የሚደርሱ ካድሬዎችን ከማግበስበሱ አኳያ) ‹‹የጥቅመኞች መብዛት›› እንደሆነ በይፋ አምነው ከተቀበሉት ጋር ስንገምደው የነገ ቀናቸው ‹‹ከኢህአዴግ ጋር ብሩህ›› እንዳልሆነ እግረ መንገዴንም ልጠቁማቸው እፈልጋለሁ፡፡ በአንፃሩ እነዚያ ሀገሪቷን እያሰመጠ ያለውን የመከራ ረግረግ ተረድተው አብዮቱን ተስፋ ያደረጉ ጎበዛዝት እና ወይዛዝርት ደግሞ ይበልጥ እንዲነቁ፣ ይበልጥ እንዲበረቱ… የጊዜውን መቃረብ ላስታውሳቸው እወዳለሁ፡፡ ምክንያቱም በቁጣ አደባባይ ለመውጣት እንቅፋት የሆነው ብሔራዊ ፍርሃት ይሰበር ዘንድ ለመስበክ፣ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ በነፃነቷ ትበጽህ ዘንድ ካስረገጠው ከዚህ መቶ አስራ ስምንተኛው የዐድዋ ድል ዋዜማ የበለጠ ምቹ ጊዜ የለምና (ይህ ድል በነፃነት የሚያምን የሰው ልጅ ሁሉ፣ ያለቀለም ልዩነት ሊዘክረው የሚገባ ስለመሆኑ ለእነርሱም ጭምር መመስክር ግዴታ ይመስለኛል)
እንዲህ በጽሑፍ ሲገለፅ በእጅጉ የሚቀለው የዐድዋ ገድል፣ እልፍ አእላፍ የሀገሬ ሰዎች መተኪያ አልባ ህይወታቸውን የገበሩበት በመሆኑ፣ በየዓመቱ ደግመን ደጋግመን የመዘከርና አደራውን የመቀበል ታሪካዊ ግዴታ ውስጥ ጥሎን ማለፉ እውነት ነው፡፡ ‹‹የተሰጠኝ ህይወት ዛሬ በነፃነት፣ ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት›› እንድትል እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ)፤ እኒያ ሰማዕታት ከዳር እስከዳር ነቅለው ‹‹…ሀገር የሞተ እንደሁ ወዴት ይደረሳል?›› በሚል መታመን ተቀስቅሰው፣ ባሕር አቋርጦ፣ አድማስ ተሻግሮ የመጣውን ወራሪ ሀፍረት አልብሰው፣ ሀፍረት አስታጥቀው፣ ሀፍረት አጉርሰው… የመመለሳቸው ብርታት ባለዕዳዎች መሆናችንን ዘመን ሊሽረው አይችልም፡፡ ያ ጣፋጭ ድል ኢትዮጵያችንን በዓለም ፊት ‹ነፃ ሀገር› የተሰኘ የታሪክ ሜዳሊያ አጥልቃ ትኮራ ዘንድ ካባ ማጎናፀፉም ዓመታዊ ዝክሩ መቼም ቢሆን በቸልታ እንዳይታለፍ አድርጎታል፡፡ እናም እነዛን ባለውለታዎች ከታላቅ የክብር ሰላምታ ጋር እንዲህ ስል ላወድሳቸው እገደዳለሁ፡-

ዘላለማዊ ክብር ለዐድዋ ጀግኖች!!!
የፈራ ይመለስ!
እንግዲህ ጀግኖች አባቶቻችን በዚህ መልኩ ላለፉት ሶስት ሺህ ዘመናት ለነፃነታችን ሲዋደቁ ኖረዋል፡፡ በውጤቱም ነፃ ሀገር አስረክበውናል፡፡ ይሁንና ዛሬም እኛ ዘመነኛ ትውልድ ‹‹ነፃነት›› እያለን የምንጮኽለት ይህ ክቡር ጉዳይ ገና ምላሽ ላገኘም፡፡ በርግጥ ጥያቄው ከባዕድ ወረራና ተወራሪ ጋር የሚጋመድ አይደለም፤ ከሀገር ልጆች ጭቆና እንጂ፡፡ እንዲህ ‹ነፃነታችንን!› እያልን የምንጮኽለት መንፈስም፣ ወራሪውን ጣሊያን ያሸነፉ ቀዳሚ አባቶች ያላቆዩልን፣ ግን ደግሞ በጥያቄው ስም ጥተው፣ መልሰው መንፈሱን የጨፈለቁት ገዥዎቻችን የነጠቁንን መብት የሚወክል ነው፡፡ በአናቱም የትግሉ መንገድ በቅኝ ግዛት ለማሳደር በቀቢፀ-ተስፋ ተሞልቶ ወሰን የተጋፋው ጣሊያን ተሸንፎ ከተባረረበት ጋር ዝምድና የሌለው መሆኑን መረዳት ያሻል፡፡ ምክንያቱም ዘመነኛው የነፃነት ጥያቄ፣ እንደ ዐድዋው መድፍ አጓርቶ፤ መትረየስ የሳት-ላንቃውን ከፍቶ ሞት እየረጨ ሊፈታው አይችልምና ነው፡፡ ይህ አይነቱ የፋኖ መንገድ አንድም ጊዜው ያለፈበት ሲሆን፤ ሁለትም ህወሓት-ኢህአዴግን ለአራት ኪሎው ቤተ-መንግስት ቢያበቃውም፣ የታየው ለውጥ መለዮ ለባሽ ወታደርን፣ ገና ዝላዩን ባልጨረሰ የተማሪ አምባገነን ከመተካት አለመዝለሉ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
ስለሆነም ዛሬ ጭቆናን የማሸነፊያ ብቸኛ መንገድ የፍርሃት ሰንሰለትን ሰባብሮ፣ በጨቋኞች ፍቃድ ለቆመው ስርዓትም ሆነ በድምፀ-አልባ ተወካዮቹ አጃቢነት ለፀደቁት ሕግጋት አለመታዘዝ ላይ የተመሰረተ ብቻ ነው፡፡ በእምቢተኝነት ደም-አልባ ሰላማዊ አመፅ የገዥዎችን ሰፈር ማራድ፤ እኩይ አላማዎቻቸውን የሚያስፈፅሙ ተቋማትን ጥርስ አልባ ማድረግ፤ አደባባዮችን በሰው ጎርፍ ማጥለቅለቅ፤ የትኛውንም አይነት ተቋማዊ ትብብርን መንፈግ፤ ኤፈርትና መሰሎቹን የንግድ ድርጅቶቻቸውን ማግለል፤ ሁሉም ፖለቲካዊ ፍላጎቶቻችን በኢትዮጵያዊ ዜግነት ስር እንደሚፈቱ ከልብ በማመን-ነገን ማለም፤ ለጥያቄው እስኪንበረከኩ ድረስ በሰላማዊው ተቃውሞ ፀንቶ መቆምንና መሰል ስልቶችን መተግበር ብቸኛ አማራጭ ነው፡፡ ይህ ይፈፀም ዘንድም በራስ ጉያ ፀለምት ለብሶ የተሸሸገ ፍርሃትን የተሻገሩ ጎበዛዝትና ወይዛዝርት ሊፈተኑበት፤ ከሽፈው የቀሩት ደግሞ ጥያቄውን በማጥላላትም ሆነ የተራራ ያህል በማግዘፍ ፍርሃትን አንብረው የአገዛዙን ዕድሜ ለማራዘም ደፋ-ቀና ከማለት ይታቀቡ ዘንድ የሚገደዱበት ዕለት ከደጅ መድረሱን ለመተንበይ ነብይ መሆንን አይጠይቅም፤ አይኖች-ያያሉ፤ ጆሮዎችም- ይሰማሉና፡፡
ግና፣ ይቺም ኑሮ ሆና እንዲህ የትውልድ ተጋሪዬ ጭሮ ግሮ ለማደር (አነስተኛና ጥቃቅንን ልብ ይሏል) በፖለቲካ አቋም እና በዘውግ ማንነት ተፈትኖ ማለፍ ግድ በሆነበት የሀገሬ ምድር፣ እውነት መመስከርን ስለምን በጀብደኝነት አንድምታ ታቃልለዋለህ? የተጠናወተህን ገደብ አልባ ፍርሃት፣ ለውጥ የሚጠይቁ ድምፆችን በማጣጣል ለመሸፋፈን መዳከር የት ያደርስሀል? የወላዋይ ብዕርህን ‹‹የለሁበትም!!›› ቅኔ ለበስ አቤቱታ እና ‹እውነት ለመናገር ጊዜና ቦታ አለው› የሚል ፍርሃታዊ ማምለጫህንስ ስለምን ለታናናሾችህ ለመጋት ትደክማለህ? በአገዛዙ መዝገበ-ቃላት ‹‹ፅንፈኛ፣ ጀብደኛ…›› ብለህ ማምታታትስ ባለፈ ዘመን ላይ መከተር አይደለምን? እውነት እውነት እልሀለሁም፡- በሰላማዊ መንገድ የስርዓት ለውጥን መጠየቅ፣ በ‹አትነሳም ወይ!› የሀገር ባለቤትነት ከፍታ ለአደባባይ ተቃውሞ ዘመነኞችን በእሪታ መጣራት፣ በየትኛውም የታሪክ ስፍር ጀብደኝነት ሆኖ አያውቅም፤ ለሕሊና መታመን እንጂ፡፡
በግልባጩ ነፃነትን ያህል ውድ ነገር የሚጠይቀውን ክቡድ መንፈስ ለማራከስ መሽቀዳደም፣ በንፁሀን ደም ከተጨማለቀው ጨቋኝ ገዥ የታማኝ ባለሟልነትን ማዕረግ ለማግኘት መባተል፣ ከዘመን መንፈስ ቀልባሽነት፣ በሞቀበት ከሚዘፍን ሆድ- አዳሪነት… ከቶስ ቢሆን በምን ይለያል? እመነኝ ‹ከአንድ እጅ ጣት በላይ የሚቆጠሩ ሀገራዊ የለውጥ ዕድሎች ስለምን ባከኑ ?› ብለህ ብታንሰላስል፤ ተጠያቂው የአገዛዙ አፈ-ሙዝ ብቻ አለመሆኑ ይገባሀል፤ ይልቁንም ሕዝብን በ‹ጎልያድ›፣ መንግስትን በ‹ዳዊት› መስለው የሚሰብኩ ሃሳዊያን ጻሐፍት ያነበሩት ታላቅ ፍርሃትም ድርሻ እንዳለው ትረዳለህና፡፡ ግና፣ ይህ ሁሉ ሆኖም አንድ ነገር እውነት ነው፤ ከገዘፈ የአመድ ተራራ ስር ፍንጥርጣሪ የጋሉ ፍሞችን የሚያገላብጥ ትውልድ እየመጣ ነው፡፡ ያን ጊዜም አንተን ዘንግቶ የትውልዱ መንፈስ ወካዮችን ብራና ላይ በክብር ይከትባል፡፡ ለነገሩ ቢዘገይም ታሪክ ከእውነት እንጂ ከፍርሃት ውል ኖሯት አያውቅም፡፡
የፈራ ይመለስ!
temesgen
ጥቂት ጉልበታሞች ለሚንደላቀ ጥቂት ጉልበታሞች ለሚንደላቀቁበት፣ ዘጠና ሚሊዮን ሕዝብ ለምን ይሰቃያል? ጭቆናን በዚህ ደረጃ ታግሶ መሸከምስ ከግዑዝነት በምን ይለያል? የወፍን ያህል የራስ ጎጆ መመኘት እንኳ እንደ ህብስተ መና በራቀበት ምድር፣ ግብር-ነጠቃን ባስከነዳበት ሀገር፣ ዜጎች በምርኮኛ ሕግ ተቀፍድደው ውለው በሚያድሩበት ክልል፣ መማር ድንጋይ ከመፍለጥ በማያሻግርበት ዘመን፣ የመኖርና ያለመኖር ግድግዳ ተደርምሶ ሁሉም ነገር ትርጉም የለሽ በሆነባት፣ ፍዘት፣ ቁዘማ ባረበበባት ኢትዮጵያ… ዝምታ ስንት ዘመን ይፈጃል? ኢህአዴግ እንዲህ በክፋት ጎዳና እየተመላለሰ፣ በጭካኔ በትር እያስገበረ፣ ፍትሕን የ‹አመፃ ድምፅ ማፈኛ›› አርጩሜ አድርጎ እያሴሰናት… ከሁለት አስርት በላይ ተደላድሎ እንዲቀመጥ ያደረገው የቀደሙት ትውልዶች ርግማን አይምሰልህ፤ አገር-ለበስ ፍርሃት እና ቸልተኝነት እንጂ፡፡ በአናቱም ስደት የስርዓቱ ማስተንፈሻ እንጂ የለውጥ ኃይል ሆኖ አያውቅምና ሲገፉህ- አትንደርደር፤ ሲያስሩህ-አትሸበር፤ ሲከሱህ-አትደንብር፤ ሲወነጅሉህ-አትሸማቀቅ፤ ሲያስፈራሩህ-አትደንግጥ፣ ሲያባራሩህ- አትሩጥ… ምክንያቱም ፍርሃትን የመስበሪያ ፅኑ አለት ይህ ብቻ ነውና፡፡ በተቀረ እነርሱ የሚለፍፉለት ‹‹ምርጫ›› ከአንድም አራቴ ሲያፋፍሩበት በመታየቱ ካለፈው ለውጥ ይኖረዋል ብለህ አትሞኝ፤ ከዚህ በኋላ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው ሰላማዊ እምቢተኝነት አንጂ፣ አባዱላ ገመዳን ተሸክሞት እስከመሮጥ ያደረሰው ያ የይስሙላ ኮሮጆ አይደለም፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገትም ብቻውን የፖለቲካ ለውጥ አያመጣም፡፡ ዳሩ፣ ሲጀመርስ ዕድገቱ የት አለና?! ኢህአዴግ በነቢብ ‹መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ አፋፍ ደርሻለሁ› በሚል ፕሮፓጋንዳ ቢያሰለቸንም፤ በገቢር አዳዲስ ምሬቶችን እያቆረ ስለመሆኑ በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ‹‹አደህይቶ ማዳከም!›› እንዲሉ ፕሮፌሰር መስፍን፣ ድህነትን የሚፈለፍሉ ኩሬዎችን በየመንደሩ ከመቆፈር ቸል ብሎ አያውቅም፡፡ ይሁንና የፍትህ መዛባት፣ ስራ-አጥነት፣ የመኖሪያ ቤት ችግር፣ መቆጣጠር የተሳነው የዋጋ ግሽበት፣ ማቆሚያ ያጣው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ፣ ባልተጠና እቅድ ተቆፋፍረው ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ መንገዶች፣ አመቺ የስራ ቦታን በድርጅት የድጋፍና ተቃውሞ ሚዛን ማከፋፈል፣ አድሎአዊ አሰራር…
ብሶት የሚወልዳቸውን ነፃነት አብሳሪ አናብስት ጋላቢ ጀግኖችን ማበራከቱ አይቀሬ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ዶ/ር መረራ ጉዲና ‹‹የራበው ሕዝብ መሪዎቹን ይበላል›› የሚል ቅድመ-ትንቢያ ቢነግረንም፣ ሰሞኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላንን ጠልፎ ከመድረሻው ውጪ ያሳረፈው የኃይለመድህን አበራ ክስተት ደግሞ በአንፃሩ ርሃብን ያሸነፈው የማህበረሰብ ክፍልም ሰዋዊ ነፃነቱን ለማስረገጥ ሲል መሪዎችን ሊባላ እንደሚችል የሚያመላክት ነው፡፡ ይህ ሰው ማህበራዊ አክብሮትን በሚያጎናፅፍ ሙያ የተሰማራ ከመሆኑም በላይ፣ በኢትዮጵያ የሲቪል ሰርቪስ እርከን እጅግ ከፍተኛ ሊባል የሚችል ደሞዝ ተከፋይ ነው፡፡ ከዚህ አኳያም በአስከፊ ደረጃ የተንሰራፋውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም ብዙም እንደማይቸገር በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ ሀገር ቤት መኖር ካልፈለገም፣ ወደበለፀጉት ሀገራት ተሻግሮ ስራ ማግኘት እንደማይሳነው ያውቃል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ግና፣ ይህ ሁሉ እውነት ቢሆንም የመረጠው መንገድ በራስ ላይ ቀድሞ ሊገመት
የማይችል አደጋ የሚጋብዝን ነው፡፡ እንግዲህ ከእነዚህ ተጨባጭ እውነቶች ተነስተን (እርሱ ራሱ ድርጊቱን የፈፀመበት ምክንያት ለስዊዘርላንድ ፍርድ ቤት እስኪናገር መጠበቁን ታሳቢ አድርገን) መላ-ምቶችን ማስቀመጥ እንችላለን ብዬ አስባለሁ፡፡ ለድርጊቱ በዋናነት መግፍኤ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው አየር መንገዱ የገባበት ችግር ነው፤ ምክንያቱም ድርጅቱ በሂደት ህልፈቱን ወደሚያውጅበት መስቀል (ችንካር) እንዲያዘግም ገፊ ከሆኑ ጉዳዮች አስተዳደራዊ በደል የአንበሳውን ድርሻ ይይዛልና፡፡ አገዛዙ አንዳንድ የድርጅቱን ሰራተኞች በመዓት አይኑ ወደሚመመለከትበት ጠርዝ ያደረሰው ከዚህ ቀደም ‹በአውሮፕላኖቹ ላይ ባለኮከቡን ባንዲራ አትማለሁ› በሚል የፈጠረው አንጃ-ግራንጃ፣ በተወሰኑ ነባርና በጣም ወሳኝ ሰራተኞች ፊት-አውራሪነት በተቀሰቀሰ ተቃውሞ የተስተጓጎለበት ደረቅ እውነታ አንዱ ተደርጎ ይጠቀሳል፤ ሌላው ደግሞ ጠንካራና በሚገባ የተደራጃ የነበረውን የሰራተኛ ማህበር ለመቆጣጠር ያደረገውን ሙከራ ተከትሎ የገጠመው ተግዳሮት ነው (ዛሬ ማህበሩን ማስገበር መቻሉ ሳይዘነጋ)፡፡ እንዲህ አይነት ሕገ-መንግስታዊ ድፍረቶችን የስርዓቱ ኤጲስ-ቆጶሳት በቸልታ የሚያልፏቸው ባለመሆኑ፣ የተወሰዱት የማባረርና ከቦታ ዝቅ የማድረግ ፖለቲካዊ እርምጃዎች አየር መንገዱ ዛሬ ለደረሰበት ውድቀት መንገድ ከመጥረጉም በላይ፣ ተማራሪ ሰራተኞች እንዲበዙ አድርጓል፡፡ በአመክንዮ ድርጅቱ ከባለሙያ እጥረት (አቅም ማነስ) ጋር ብቻ ተያይዞ እየደረሰበት ያለውን ችግር ለመረዳት በስምንት ወር ውስጥ ብቻ ያጋጠመውን አራት ትላልቅ አደጋዎች ልጥቀስ፡- ካርጎ (Cargo MD-11F) አውሮፕላን ልምድ ያላቸው ኦፕሬተሮች በመባረራቸው፣ አዳዲሶቹ አበባ ለመጫን ሲሞክሩ በቆመበት ቦታ በቂጡ ወድቆ ጉዳት ደርሶበታል፤ ቦይንግ 767 (Boing 767) ከሞተር ጋር በተያያዘ ችግር ሮም ላይ ተገዶ አርፏል (በኋላ በተደረገለት ምርመራም ጥቂት ደቂቃዎች በአየር ላይ ቢቆይ ኖሮ ሊጋይ ይችል እንደነበረ ታውቋል)፤ ፎከር (Foker) አውሮፕላን ሞተሩ ተቃጥሎ ካርቱም ላይ አርፏል (ይህም ጥቂት ደቂቃ ቢዘገይ ኖሮ ተመሳሳይ አደጋ ይደርስበት እንደነበር ተነግሯል)፤ ቦይንግ 767-383 ኢ.አር (Boing 767-383 ER) ታንዛኒያ ውስጥ ማረፍ የነበረበትን ቦታ ስቶ፣ ትናንሽ አውሮፕላኖች የሚያርፉበት አሩሻ አየር ማረፊያ ለማረፍ ባደረገው ሙከራ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዞ ትልቅ የእርሻ ማሳ ውስጥ ሊቀረቀር ችሏል፡፡ እነዚህና መሰል ችግሮች ከኃይለመድህን አበራ እርምጃ ጋር ሲደማመሩ አየር መንገዱ ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ ለመረዳት ያስችላሉ፡፡
በአናቱም የጄኔቫው ክስተት የመሪዎቻችንን ውሸታምነት ከመቼውም በላይ የከፋ ደረጃ መድረሱን አሳይቶ አልፏል፡፡ ይኸውም የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤትን በሚኒስትር ማዕረግ የሚመራው አቶ ሬድዋን ሁሴን፣ ጠለፋው በተሰማበት ሰዓታት ውስጥ ለሮይተር በሰጠው ቃለ-መጠይቅ ‹‹ድርጊቱን የፈፀሙት ካርቱም ላይ የተሳፈሩ አሸባሪዎች ናቸው›› ከማለቱ ጋር ይያዛል፡፡ ይህ ንግግር እንደቀላል ስህተት መታየት ያለበት አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም መንግስት በሀሰት ንፁሀንን ለማሰር ሲያሴር የሚሰጠው ሰበብ እንዲህ አይነት ፈጠራ መሆኑን ያስረግጥልናልና (ይህንን ጽሑፍ እያዘጋጀሁ ሳለሁ እንኳ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የሰማሁት ዜና ሀገር ውስጥ ያሉ የተወሰኑ የግል ሚዲያዎችን ሁለት ኢምባሲዎች እንደሚያሽከረክሯቸው የሚወነጅል መሆኑ ተጨማሪ ማሳያ ይመስለኛል)፡፡ በርግጥ ስርዓቱ በከረባት ታንቀው የሀሰት ወሬዎችን ሚዲያ ፊት ቀርበው የሚያወሩ ደፋር ሚኒስትሮችን በብዛት መሰብሰቡ እውነት ቢሆንም፣ ከሬደዋን ሁሴን በፊት አቶ በረከት ስምኦን እንዲህ አይነት እጅና እግር የሌላቸውን ነጭ ውሸቶች ራሱ ከመጋፈጥ ይልቅ ብዙ ጊዜ በምክትሉ አቶ ሽመልስ ከማል በኩል ያስነግር እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይሁንና በረከት ቦታውን ለሬድዋን ካስተላለፈ በኋላ በሬድዋንና ሽመልስ መካከል ያለው የፖለቲካ ጉልበት ያን ያህል የሚበላለጥ ባለመሆኑ፣ እንደቀድሞ ሁሉ ሬድዋን፣ በምክትሉ ለመጠቀም አስቸጋሪ እንደሆነበት ሰምቻለሁ (በነገራችን ላይ የአቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝም ‹አለቃ እኔ ነኝ› የሚለው የሰሞኑ መከራከሪያ፣ እነበረከት-ደብረፅዮንን ከጣራ በላይ ሳያስቃቸው የሚቀር አይመስለኝም)
የሆነው ሆኖ ከላይ የተጠቀሱት ክስተቶች ከፍተኛ ደሞዝ የሚከፍል ድርጅት ሰራተኞችንም ያሳተፈ መሆኑን፤ በአምስት መቶ ብር አምስት ቤተሰብ ለማስተዳደር ከሚባትለው ኢትዮጵያዊ ጋር ካጋመድነው ሀገሪቱ ያለችበትን የፖለቲካ ክስረት፣ የኑሮ ውድነት ያነበረው ምሬት፣. አድሎአዊ አስተዳደር፣ መንግስታዊ ሙስና የደረሰበት አስከፊ ገፅታ፣ ተጠያቂነት ያሌለባቸው የፀጥታ ሰራተኞች የሚፈፅሙት ሕገ-ወጥ ተግባር፣ የአጠቃላይ መብት ጭፍለቃ… ተደማምረው መነሻና መድረሻው የታወቀውን የለውጥ ንቅናቄ መቀላቀልን ብቸኛ አማራጭ ያደርገዋል ብዬ አስባለሁ፡፡
የፈራ ይመለስ!
የስርዓቱ ልዝብ ተቃዋሚዎች ቀጣይ የሀገሪቱ ዕድል አብዮት ስለመሆኑ በተነሳ ቁጥር በግርድፍ ትንታኔ ሊነግሩን የሚሞክሩት ‹ኢትዮጵያ በ40 ዓመት ውስጥ ሶስት አብዮት ማስተናገድ አትችልም› የሚል ነው፡፡ ይሁንና ሙግታቸው ሁለት ግድፈቶችን ያዘለ ይመስለኛል፡፡ የመጀመሪያው የብሉይ አብዮትን መሰረታዊ ባህሪ ካለመረዳት ይነሳል፤ ዛሬም ድረስ የ66ቱን አብዮት አስመልክቶ የሚነሳው ተዋስኦ፣ ክስተቱ ብሉይ ማህበራዊ አብዮቶች ከሚባሉት መካከል እንደሚያስመድበው የሚያስረግጥ ነው፡፡ ይህ ስሌትም ብሉይ አብዮቶች ራሳቸውን በተለያዩ የዘመን ወቅቶች የመደጋገም ተጨባጭ ባህሪ እንዳላቸው ያመላክታል፡፡ እናም የሙግቱ ጥራዝ ነጠቅ አቀንቃኞች በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ከሚመደቡት መካከል ሩሲያና ፈረንሳይ በሁለትና ሶስት አብዮቶች ከመናጣቸው አኳያ ‹ኢትዮጵያንስ ምን ያህል የተለየች ሊያደርጋት ይችላል?› ለሚለው ጥያቄ በቂ መልስ የሚኖራቸው አይመስለኝም፡፡ በ66ቱ ከተነሱት ሁለት ዋነኛ (የመሬትና የብሔር) ጥያቄዎች፣ በ83ቱ ማህበረ- ፖለቲካዊ ሽግግርም ተነስተው አለመመለሳቸውን፣ ያሳለፍናቸው ሃያ ሁለት ዓመታት በበቂ ሁኔታ አስረጅ ናቸው፡፡ ይህ እውነታም ነው ሀገሬ ሶስተኛውን አብዮት ከማስተናገድ ውጪ የተሻለ ምርጫ እንዳይኖራት ያስገደደው፡፡
ሁለተኛው ጭብጥ በኢህአዴግ ስር ያዘገመችው ኢትዮጵያ ለአብዮት መነቃቃት የሚያበቁ ስርዓታዊ ክሽፈቶች መኖራቸውን ክዶ ከማለፍ ጋር የሚያያዝ ይሆናል፡፡ ለከተማ አብዮት መፈንዳት ወሳኝ ሆነው ከሚጠቀሱ ጭብጦች ብዙዎቹን የእኛይቷም ምድር እንደምታሟላ ከዚህ በፊትም ለማስታወስ ሞክሬያለሁ፡፡ በተለይም ሥራ-አጥ የተማሩ ከተሜ ወጣቶች አለቅጥ መብዛት እና ወጣቶች ከአጠቃላዩ ሕዝብ ወደ 37% የሚጠጉ መሆናቸውን ከአረቡ ፀደይ መንፈስ አኳያ ስንቃኘው አብዮቱን አይቀሬ ያደርገዋል፡፡ በአናቱም የሁለቱ ኃይማኖት ተከታዮች በመንግስት ላይ የያዙት የቅራኔ ልክ፣ የተቋጠረ የምሬት ፅንስ ስለመኖሩ በድፍረት ለመናገር ያስችላል፡፡ ለሁለት ዓመታት የዘለቀው የሙስሊሙ ጥያቄም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የለዘበ ቢመስልም በሂደት እንደገና መቀስቀሱ አይቀሬ ነው፡፡ ምክንያቱም የእምነቱ ተከታዮች መሰረታዊ ጥያቄ የኃይማኖቱን ሙሉ ነፃነት መከወን ከመሆኑ ላይ ተነስተን፣ የተሰጠው መልስ መዋቅራዊ እንደነበረ ካስተዋልን ‹‹እንቅስቃሴው መለዘብ አለበት›› ያሉ ልሂቃንም ሳይቀሩ የነፃነቱ ጥያቄ በድጋሚ ተነስቶ መጅሊሱን እንዲነቀንቅ መፈለጋቸውን አምነን እንድንቀበል ያስገድደናል፡፡
ሌላው ጉዳይ የኦርቶዶክስ ኃይማኖት ተከታዮች ጉርምርምታ እና ማህበረ ቅዱሳን ላይ በሲኖዶሱ በኩል የሚካሄደው መንግስታዊ ጉንተላ፣ ምን ይዞ እንደሚመጣ ለመገመት የግድ ነገ ላይ መቆምን የማይጠይቅ መሆኑ ነው፡፡ በተጨማሪ ዛሬም5 እየተነሱ ካሉት የማንነት ጥያቄዎች አልፎ፣ በቅርምቱ ከአያቶቻቸው መሬት ከተፈናቀሉ ወጣቶች ምሬት ጋር የኢኮኖሚውን ድቀት አዛምደን ስንመለከት፣ ፍርሃትን አቸንፈው ወደኋላ ላለመመለስ የደፈሩ ወጣቶች ስርዓቱን እንደሚንዱት ለመመልከት ጥቂት ወራትን ብቻ መታገስ ይበቃል፡፡ ‹‹አብዮት የወይን ዘለላ ነው፤ እስኪበስል እንጂ መሬት እስኪወድቅ አትታገሰውም›› እንዲል ቼ ጉቬራ፤ ያረገዘውን አብዮት ከማዋለድ ያለፈ ምርጫ የለም፡፡
በድጋሚ ክብር ለዐድዋ ጀግኖች!!!


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>