Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

“የትግራይ ህዝብ የህወሓት ደጋፊ አይደለም”–አብርሃ ደስታ (ከአዲስ ጉዳይ መጽሔት ጋር ያደረገው ቃለ-ምልልስ)

$
0
0

abreha desta
አዲስ ጉዳይ መጽሄት ቅጽ 8 ቁ. 205/ የካቲት 2006

አዲስ ጉዳይ፡- የህወሓት የ39 ዓመታት ጉዞ በግልህ እንዴት ታየዋለህ?

አብርሃ ደስታ፡- በእኔ አመለካከት የህወሓት ጥረት ከመጀመሪያ አንስቶ ስልጣን ለመያዝ ነው፡፡ አሁንም በስልጣን ለመቆየት ሲሉ ኢኮኖሚውን እየተቆጣጠሩት ነው፡፡ የህዝቡን መረጃ የማግኘት መብት፤ የህዝቡን አስተሳሰብ ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ ነው ያሉት፡፡ ጉዞው ስልጣን የመያዝ እና በስልጣን የመቆየት ጉዳይ ነው።

አዲስ ጉዳይ፡- ፓርቲው ግን ‘‘ለመመስረቴ ምክንያቱ የህዝብ ብሶት ነው’’ ይላል፡፡

አብርሃ ደስታ፡- ይህ ፕሮፓጋንዳ ነው። መጀመሪያ ለትግል ሲነሱ ህዝቡ የስርዓት ለውጥ ፈልጎ ታግሏል። ነገር ግን የህወሓት መሪዎች ስልጣን የመያዝ ዓላማ እንጂ ህዝቡን የስልጣን ባለቤት ማድረግ አልነበረም። በመሆኑም የህዝቡን ብሶት ስልጣን ለመያዝ ተጠቅመውበታል። ከዚህ ውጪ ለእኔ የእነርሱ ደርግን አስወግደው ስልጣን መያዝ የደርግን ሚና ለመጣወት እንጂ ህዝቡን ለመጥቀም አልነበረም።

አዲስ ጉዳይ፡- አንዳንዶች ህወሓት ወደ ኋላ አካባቢ የትግል መስመሩን ስቷል ሲሉ ሌሎች ደግሞ ፓርቲው ከመመስረቱ አንስቶ ዓላማው ስህተት ነበር ይላሉ። የአንተ አስተያየት ምንድነው?

አብርሃ ደስታ፡- እዚህ ላይ እኔ ህወሓትን የማየው በሁለት ከፍዬ መሆኑ ይታወቅልኝ። ስልጣን ፈላጊው የህወሓት አመራር እና ነፃነት ፈላጊው የህወሓት ታጋይ፡፡ ደርግ ገና ስልጣኑን ከያዘ ከወራት በኋላ ወደ ጫካ ገቡ። ስለዚህ የህወሓት አመራሮች ጫካ የገቡት የደርግ መንግስትን ጭካኔ ስላዩ ወይም የደርግን አምባገነንነት ስለተገነዘቡ ነው ለማለት አልደፍርም። ምክንያቱም በጥቂት ወራት ውስጥ ብቻ የህወሓት አመራሮች የደርግን ጨቋኝነት የሚያውቁበት ሁኔታ አለ ማለት በጣም አስቸጋሪ ነው። ዓላማቸው ስልጣን ነበር። ሲነሱም እንደሚታወቀው ትግራይን ለማስገንጠል ነበር፡፡ ይሄም ሆኖ ህወሓቶች ሲንቀሳቀሱ የደርግ መንግስት የወሰደው የኋይል እርምጃ ነበር። ይሄ እርምጃ ግን በጣም በስህተት የተሞላ ሆነ፡፡ ደርግ ጫካ የገቡትን ሰዎች ለማንበርከክ ሲል ህዝቡን በማስፈራራት ብሎም የመግደል እና ሌሎችም እርምጃዎችን ይወስድ ነበር፡፡ ይሄን ተከትሎም ህዝቡ የደርግን ግፍ በመቃወም ተነሳስቷል። ህዝቡ ለትግል በተነሳበት ወቅት ህወሓትን ተቀላቅሏል፡፡ የአብዛኛው የህወሓት ታጋይም ሆነ የትግራይ ህዝብ ዓላማ ከጭቆናና ከግድያ ለመዳን እንጂ ስለ ትግራይም ሆነ ስለ ኤርትራ መገንጠል ምንም የሚያስቡበት ጊዜ አልነበራቸውም፡፡ ይሁን እንጂ ይሄን የኅብረተሰቡን ጭቆና የማስወገድ እንቅስቃሴ ለራሳቸው ፍላጎት አውለውታል፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- ኢህኣዴግ የአራት ፓርቲዎች ግንባር ቢሆንም ፍፁም የህወሓት የበላይነት በግንባሩ ነግሷል የሚሉ አሉ። ይህን ሀሳብ እንዴት ታየዋለህ?

addis guday magazine
አብርሃ ደስታ፡- አብዛኞቹ የኢህኣዴግ አባል ፓርቲዎች የህወሓት ውጤቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች ህወሓት እንዲመሰረቱና እንዲደራጁ ያደረጋቸው ናቸው፡፡ በዚህ አምናለሁ፡፡ ይህንን ሃሳብም እቀበለዋለሁ፡፡ ነገር ግን እዚህ ላይ አንድ ግልጽ መሆን ያለበት ጉዳይ ህወሓት ራሱ የጥቂት ግለሰቦች ስብስብ መሆኑ ነው።

አዲስ ጉዳይ፡- ይህንን ሃሳብ ዘርዘር አድርገህ ብታብራራው?

አብርሃ ደስታ፡- በትግሉ ወቅት በጊዜው በነበረው ጨቋኝ ስርዓት የተነሳ ህዝቡ ሌላ የተሻለ አማራጭ ስላልነበረው ህወሓትን ደግፏል፡፡ ይሁን እንጂ ህወሓት ስልጣን ከያዘ በኋላ በሺኅ የሚቆጠሩ ታጋዮችን ሆን ተብሎ እንዲባረሩ ተደርገዋል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ገና ፓርቲው ስልጣን እንደያዘ የአመራሩ ተነኮሎች ግልፅ እየሆኑ ሲመጡ የህወሓት ታጋዮች መቃወም በመጀመራቸው ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ነው ህወሓት የተወሰኑ ግለሰቦች ስብስብ መሆኑ መረሳት የለበትም የምለው፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- አንድ ወቅት ህወሓት በትግራይ የሚከተለው የፖለቲካ ስልት ‘‘እኔ ከሌለሁ ደርግ ይመጣባችኋል’’ ዓይነት መሆኑን ተናግረህ ነበር።

አብርሃ ደስታ፡- አዎ! ይሄ እውነት ነው፡፡ እንደውም ዋናው የህወሃት የትግራይ የፕሮፓጋንዳ መሳሪያው እኔ ከሌለሁ ሌሎች መጥተው ይበሉሃል የሚሉት ሃሳቦች ናቸው፡፡ በእርግጥ የደርግ ስርዓት እንዳይመለስ መፈራረሱ የታወቀ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይሄ ፕሮፖጋንዳ እየሰራ አይደለም። በትግራይ ውስጥ ብዙ ተቃውሞ አለ። በእርግጥ ይሄ ‘‘ደርግ መጣ’’ የሚለው ቃል የትግራይን ህዝብ ማስደንገጡ አይቀርም። በጊዜው ብዙ ስቃይና ግድያ ያየ ህዝብ ስለሆነ ማለቴ ነው፡፡ ስለዚህ ይደነግጥና ‘‘ከደርግማ ህወሓት ይሻለናል’’ ይላል፡፡ ይሁን እንጂ ደርግ ሊመለስ እንደማይችል ከዚህ በኋላ በጥቅሉ ወደ ወታደራዊ ስርዓት ልንመለስ እንደማንችል ለህዝቡ በማስረዳት ለውጥ የምናመጣበትን መንገድ እናመቻቻለን የሚል ዕምነት ነው ያለኝ፡፡ ይሄ ፕሮፖጋንዳም ካሁን በኋላ አይሰራም።

አዲስ ጉዳይ፡- ይህን የምትልበት ምክንያትህ ምንድነው?

አብርሃ ደስታ፡- ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ህዝቡ ደርግ ሊመለስ እንደማይችል በሚገባ እያመነ መምጣቱ ነው። እኛም በዚህ ላይ በስፋት እንሰራበታለን። ህዝቡም ዲሞክራሲያዊ አሰራር እና ዲሞክራሲያዊ መንግስት እንደሚያስፈልገው እየተረዳ ነው። ይሁን እንጂ የህዝቡ ግንዛቤ እያደገ በመጣ ቁጥር የህወሓት አፈናም በዚያው መጠን እያደገ መምጣቱ አይቀርም። በዚህ የተነሳም ህዝብ እየታፈነ ነው። የመሰብሰብ፤ የመደራጀትና የመናገር ዲሞክራሲያዊ መብቶቹን አሁን እየተነጠቀ ነው። በዚህ ላይ ተገቢውን መልካም አስተዳደር እያገኘ አይደለም። በዚህ የተነሳም ህወሓት ደርግ ይመጣል ብሎ ለሚነዛው ፕሮፖጋንዳ የትግራይ ህዝብም ‘‘እናንተም እኮ ሌላው ደርግ ናችሁ’’ እያለ ነው። ‘‘ደርግም የሚደበድበንና የሚገድለን ስንናገር መብታችንን ለማስከበር ስንሞክር እንጂ እናንተም ማፈኑንና መግደሉን ጀምራችኋል። እናንተ እራሳችሁ እያፈናችሁ በመሆኑ ደርግ መጣ አትበሉን፡፡ እናንተ እራሳችሁ እንደ ደርግ እየሆናችሁ ነው’’ በማለት ህዝቡ ግልፅ መልዕክት አስተላልፏል። በዚህ የተነሳ ይህ ደርግ ይመጣባችኋል የሚለው ፕሮፖጋንዳ የሚሰራ አልሆነም።

አዲስ ጉዳይ፡- ብዙዎች በትግራይ የህወሓት ደጋፊ እንጂ ተቃዋሚ አለ ብለው አያምኑም። አንተ ደግሞ ተቃውሞ አለ እያልክ ነው . . . .

አብርሃ ደስታ፡- አዎ! በትግራይ ተቃውሞ አለ ብዬ ለእነዚህ ሰዎች ላረጋግጥላቸው እፈልጋለሁ። እንደውም በሙሉ ነፃነት ህዝቡ ምርጫ ማድረግ ቢፈቀድለት ህወሓት በትግራይ ይመረጣል የሚል እምነት የለኝም። ለምን ብትል እኛ በተለያዩ ቦታዎች ተዟዙረን ህዝቡን በደንብ አናግረናል። በሄድንበት የትግራይ አካባቢ በሙሉ ግን ተቃዋሚ አለ። ህዝቡ እኛን እንደሚደግፍ እየገለፀልን ነው። ነገር ግን ህዝቡ የሚጠራጠረው ‘እኛ ሰው እንፈልጋለን ነገር ግን ህወሓት በምርጫ ቢሸነፍ ስልጣን ያስረክባል የሚል ግምት የለንም። እናንተን ሆነ ሌሎች ተቃዋሚዎችን ያፍናል። ከዚህ በባሰ መልኩም ሊያጠፋችሁ ይችላል። በተለይ ለዲሞክራሲያዊ አሰራር ዕድል መሆኑን ስለምናውቅ በዚህ መንገድ ለውጥ ለመምጣቱ እርግጠኞች አይደለንም’ እያሉ ነው ያሉት። ስለዚህ እኔ ከዚህ ሃሳብ የወሰድኩት ከሌሎች ግምት በተቃራኒው አፈናው በትግራይ የባሰ መሆኑን ለማሳየት ነው። ይብዛም ይነስ በሌሎች አካባቢዎች እኮ ሰላማዊ ሰልፍ እየተፈቀደ ነው። በትግራይ ግን ሰላማዊ ሰልፍም ሆነ መሰብሰብ እንኳን እየተከለከለ ነው።

አዲስ ጉዳይ፡- አፈናው ባይበዛ በትግራይ ተቃዋሚዎች በብዛት ይኖሩ ነበር ብለህ ታስባለህ?

አብርሃ ደስታ፡- በየትኛውም የትግራይ አካባቢ ከተወሰኑ ካድሬዎች በቀር ህወሓትን የሚደግፍ የለም። ጥቂት ደጋፊዎችን ፖሊስንና መከላከያውን ይዞ ነው ህዝቡን በዘዴ የሚያቀናው እንጂ እንደ ህዝብ የትግራይ ህዝብ የህወሓት ደጋፊ ነው የሚለው ለእኔ አሁን የማይሰራ ሃሳብ ነው።

አዲስ ጉዳይ፡- መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመደመር ህወሓት/ኢህኣዴግ እስከ 40 ዓመት በስልጣን መቆየት እንዳለበት እየተናገረ ነው።

አብርሃ ደስታ፡- ህወሓት ገና 50 ዓመት ይገዛል የሚለውን ነገር በትግራይ አዘውትረው በአደባባይ የሚናገሩት ነው። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን እንዲህ ያለው አቋም የተሳሳተ ነው። በእርግጥ የእነርሱ ኋይማኖት በስልጣን ላይ ለመቆየት የሚያስችላቸውን ነገር ብቻ ማድረግ ነው። ልማት ያለ ዲሞክራሲ አይመጣም። ልማትን የሚያመጣው መንግስት ብቻ ሳይሆን ህዝቡ ነው። ህዝቡ የልማቱ አምጪ እስከሆነ ድረስ በሙሉ ነፃነት ህዝቡ መስራት፤ በማንኛውም ቦታ በእኩልነት የመታየት መብቱ መከበርና ሰው በስራው እንጂ በሌላ አመለካከት መገምገሙ መቆም አለበት። ይሄ ነገር እስካልመጣ ድረስ ዘላቂ ልማት አይኖርም።አሁን ባለው ሁኔታ እንኳን ለውጥ ሊመጣ ቀርቶ ለውጡ እንዳለ እንኳን ለመቆየት የሚችል አይደለም፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- ህወሓትን ለረጅም ዓመታት ከመግዘት የሚያግደው ምንድን ነው?

አብርሃ ደስታ፡- ህወሓት በከፍተኛ ደረጃ በሙስና የበሰበሰ ነው። እንኳን በውጪው ህዝብ ይቅርና በራሱ ውስጥ እንኳን በጣም ብዙ ቅሬታዎች አሉ። በዚህ መሰረት ህወሓት ጊዜ ቢሰጠውም ለውጥ ሊያመጣ የሚችል አይደለም። ምክንያቱም ሙስናና አድልዎ በቡድኑ ውስጥ ተበራክቷል። በህዝቡም ያለው ተቀባይነት ዝቅ በማለቱ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ እየቀነሰ ነው።

አዲስ ጉዳይ፡- የተለያዩ ሰዎች በህወሓት የተነሳ የትግራይ ህዝብ በሃብት ክፍፍሉ የተለየ ተጠቃሚ እንደሆነ ያምናሉ።

አብርሃ ደስታ፡- ምን አለ መሰለህ። በእርግጥ በህወሓት የስልጣን ዘመን እየበለፀጉ ያሉ ግለሰቦች አሉ። ነገር ግን እነዚህ የበለፀጉ ግለሰቦች ለባለስልጣነቱ የቅርብ የስጋ ዝምድና ያላቸው ናቸው። ወይም ራሳቸው ባለስልጣናቱ ናቸው። በመሆኑም በሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች እነዚህ ትግርኛ ተናጋሪዎች ፎቅ ሲገነቡ ወይም የተለያዩ ቢዝነሶችን ሲሰሩ እያዩ የትግራይ ተወላጆች ሃብታም እየሆኑ ነው ብለው ቢናገሩ አይፈረድባቸውም። ምክንያቱም እነማን መሆናቸውን አያውቁም። ከዚህ ውጪ አብዛኛው የትግራይ ህዝብ በድህነት ውስጥ ስለመኖሩም መረጃ ላይኖራቸው ይችላል። ስለዚህ አብዛኛው የትግራይ ህዝብ በድኅነት እየኖረ የባለስልጣናት ዘመዶች ሃብት እየሰበሰቡ መሆናቸውን በደንብ የምናውቀው እኛ የትግራይ ሰዎች ነን። በሌላ ቦታ በአማራ፣ በኦሮሚያም ሆነ በሌላው ክልል ሃብት የሚሰበሰብ ትግርኛ ተናጋሪ ብታይ አንተም የትግራይ ሰው ሃብት እያካበተ ነው የሚል ሃሳብ ልታዳብር ትችላለህ። በመሆኑም የሌላው ክልል ነዋሪ እንዲህ በማለቱ ሊፈረድበት አይገባም። ጉዳዩን በሚገባ ማስረዳት የሚኖርብንም እኛው የትግራይ ህዝቦች ነን። ባለስልጣናቱና ዘመዶቻቸው ከህዝብ የተሰጣቸውን ሃላፊነት አላግባብ በመጠቀም ሃብት እየሰበሰቡ መሆናቸውን ማጋለጥ ያለብን እኛው የትግራይ ሰዎች ነን።

አዲስ ጉዳይ፡- ህወሓት በኢኮኖሚው ላይ በበርካታ ድርጅቶች መሳተፉ፣ የደህንነት ኃይሉን መጠቀሙና ነፃ ሚዲያውንም ማዳከሙ ለሰላማዊ ትግሉ ተስፋ አስቆራጭ ነው የሚል ሃሳብ ይነሳል . . .

አብርሃ ደስታ፡- እውነት ነው። እንደተባለው ህወሓት ኢኮኖሚውን በስፋት መቆጣጠሩ ሚዲያውንም መቆጣጠሩ ወይም የግል ሚዲያውን አለመፈለጉ፤ በሰላማዊ ትግሉ ላይ እንቅፋት ይፈጥራል። ነገር ግን እንቅፋት ስለሚፈጥር፤ መንግስት አፋኝ በመሆኑ እና ለሰላማዊ ትግሉ በሩን በመዝጋቱ የተነሳ ተቃውሞ እንዳስፈለገ መታወቅ አለበት። እኛም እየተቃወምን ያለነው ይህንኑ አካሄድ ነው። እኛ እንደምናምነው ሚዲያውን ስለተቆጣጠረ፣ ህዝቡን ስላፈነ የሰላማዊ ትግል መንገድ ችግር ሊያደርስበት ይችላል እንጂ ሊያስቆመው አይችልም። ህዝቡ ለውጥ እስከፈለገ ድረስ መንግስት የፈለገውን አፈና ቢያካሂድ አስፈላጊን መስዋዕትነት በመክፈል ህዝቡን እያደራጀንና እያስተማርን ለውጥ ማምጣት ይቻለናል የሚል እምነት ነው ያለኝ።

አዲስ ጉዳይ፡- የህወሓት ምስረታ ሲታሰብ የተለያዩ መስዋዕትነት የከፈሉ ታጋዮች ስማቸው አብሮ ይነሳል። አንተ በግልህ መስዋዕት የሆኑት ታጋዮች ዓላማ ዳር ደርሷል ትላለህ?

አብርሃ ደስታ፡- ይሄ ነገር ሲነሳ ጉዳዩን በጥንቃቄ በሁለት ከፍለን ማየት ይኖርብናል። የመሪዎቹ ዓላማ ስልጣን መያዝ ነበረ ብዬ ነው የማምነው። የእኛ ወላጆች ዓላማ ግን ነፃነት ነበር። ስለዚህ ለእኔ የትግሉ ዓላማ አልተሳካም ባይ ነኝ። ምክንያቱ ደግሞ የታጋዮቹ ዓላማ ለሰው ነፃነትን ማምጣት ነበር። አሁን ግን ነፃነት የለም። አፈና ነው ያለው። ስለዚህ የታጋይ ወላጆቻችን ዓላማ ህዝቡን ለማፈን እስካልነበረ ድረስ ዓላማው አልተሳካም የሚል እምነት ነው ያለኝ።

አዲስ ጉዳይ፡- የትግራይ ህዝብ እና የህወሓት መሪዎች በኤርትራ መገንጠልም ሆነ በኢትዮጵያዊ ህብረብሄራዊ ስሜት የተለያየ አቋም ያላቸው መሆኑ ይነገራል። እውነት ነው?

አብርሃ ደስታ፡- አዎ! የህወሓት መሪዎች ዓላማ ኤርትራን ማስገንጠልን የሚጨምር ነበር። ይሄን አቋማቸውን ደግሞ የተለያዩ ዶክመንቶች ጭምር ይመሰክሩታል። ህዝቡም ሆነ ታጋዮቹ ግን የኤርትራን መገንጠል የሚደግፉ አልነበሩም። ይሄን የህወሓት ኤርትራን ማስገንጠል ዓላማ የማይደግፉ ታጋዮች ሲገኙ ይቀጡ እና ይባረሩ ነበር። በተለይ ለኤርትራ ህዝብ ባርነት ወይስ ነፃነት የሚል ሪፈረንደም ሲቀርብ ብዙ ታጋዮች ተቃውመውታል። ይህ የህወሓት አመራር ድጋፍ ያለውን ሃሳብ በመቃወማቸው፤ የአሰብ ወደብ ጉዳይንና የዲሞክራሲ ጥያቄን በማንሳታቸው ባንድ ጊዜ ወደ 32 ሺኅ የሚጠጉ ታጋዮች ከህወሓት ተባረዋል። ከእነዚህ ውስጥ የታሰሩም የተገደሉም አሉ።

አዲስ ጉዳይ፡- ህወሓት የኢትዮጵያን የባህር በር አስነጥቋል ብለህ ታምናለህ?

አብርሃ ደስታ፡- አዎ! በትክክል አስነጥቋል ነው የምለው። ህወሓት ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታጣ ምክንያት ሆኗል።

አዲስ ጉዳይ፡- የህወሓት አመራሮች የአማራ ህዝብን ከገዢው መደብ ጋር ደብሎ በመሳል የብሄር ጥላቻ እንዲከሰት አድርገዋል ተብለው ይተቻሉ። አንተ ምን ትላለህ?

አብርሃ ደስታ፡- የህወሓት አመራሮች የአማራ ህዝብን ከገዢው መደብ ጋር አንድ አለመሆኑን ያውቃሉ። ነገር ግን ሆን ብለው ህዝቡንና ገዢ መደብን አንድ አድርገው የሚያቀርቡት ደግሞ ህዝቡ ተባብሮ በአንድ ላይ መቆም ከቻለ ለስልጣናቸው ስለሚያሰጋቸው ጭምር ነው። ይህ ዓይነቱ አቋም ደግሞ ከድሮም ጀምሮ የሚያራምዱት ነው። እኛ ልጆች ሆነን የሚነገረን ደርግ ማለት አማራ ማለት ነው ተብሎ ነበር። አማራ ማለት ደግሞ ደርግ ነው። በመሆኑም አማራ ገዢና ጨቋኝ ነው የሚሉ ነገሮች ናቸው። እስካሁን ድረስ ፀረ አማራ የሆኑ ዘፈኖች አሉ። ምክንያቱም ፀረ አማራ ማለት ፀረ ደርግ እንደማለት ስለነበር ነው። ይህ አስተሳሰብ የከፋፍለህ ግዛ ስትራቴጂ እንጂ የትግራይ ህዝብ በሙሉ ህወሓት አለመሆኑ እንደሚታወቅ ሁሉ የደርግ ስርዓት እና የአማራው ህዝብ አንድ አለመሆናቸው ይታወቃል። እነርሱ ግን ይሄን ይጠቀሙበታል፣ ከስልጣን በላይ የሚያስቡት ነገር ስለሌለ ማለቴ ነው።

አዲስ ጉዳይ፡- ያለህበት አረና ፓርቲ በትግራይ ውጤታማ የሚሆን ይመስልሃል?

አብርሃ ደስታ፡- በእርግጥ ብዙ አፈናዎች እየተካሄዱ ነው። ህዝቡን ለማወያየት ስንሞክር ስብሰባ እየተሰረዘብን፤ ከዚያም አልፎ ድብደባ እየደረሰብን ነው። ይሁን እንጂ የትግራይ ህዝብ ለውጥ እንደሚፈልግ ለእኛ ተስፋ ስጥቶናል። በመሆኑም እኛ ውጤታማ እንሆናለን ብዬ ነው የማስበው።

አዲስ ጉዳይ፡- አቶ ስብሃት ነጋ ‘‘አረናዎች የተቆጡ ህወሓቶች ናቸው’’ የሚል ሃሳብ ሰንዝረዋል። በእርግጥ አረና ህወሓት ነው?

አብርሃ ደስታ፡- አረናን እንደ ፓርቲ ከህወሓት ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም። ነገር ግን ጥቂት የቀድሞ የህወሓት ሰዎች ወደ አረና ስለገቡ በቂም ተበሳጭተው ነው በሚል ነገር ያነሳሉ። እነዚህ ሰዎች በእርግጥ ህወሓት ነበሩ። ነገር ግን ህወሓት ችግር እንዳለበት ሲረዱ ከፓርቲው በመውጣት አረና የተሻለ አካሄድ እንዳለው ሲረዱ የእኛን ፓርቲ ተቀላቀሉ። ከዚህ ውጪ ከፖለቲካ ርዕዮተ ዓለምም ሆነ ከአሰራር አንፃር በዓረናና ህወሓት መካከል ብዙ ልዩነቶች አሉ።

አዲስ ጉዳይ፡- ልዩነታችሁን በምሳሌ ልታስደግፍ ትችላለህ?

አብርሃ ደስታ፡- ለምሳሌ በእኛ ፓርቲ ውስጥ ማዕከላዊ ዲሞክራሲያዊነት ብሎ ነገር የለም። ሌሎች አካሄዶቻችንም በስፋት ከህወሓት የሚለዩ ናቸው። እነርሱ ወደ ኃይል እርምጃ የገቡት እኮ ለህዝቡ የእኛን አቅጣጫ በዝርዝር ስናስቀምጥ ጎልቶ በወጣው ልዩነት የተነሳ ነው። ስለዚህ ህወሓት ለስልጣን የሚቀናቀነውን ማንኛውንም ፓርቲ ማጥላላት ልማዱ ነው። ይህንን እኛም ስለምናውቀው ከህወሓቶች ለሚሰነዘር አስተያየት እኛ ያን ያህልም የምንጨነቅበት ጉዳይ አይሆንም።

አዲስ ጉዳይ፡- ህወሃት በትግራይ ወይም ኢህአዴግ በኢትዮጵያ በምርጫ ስልጣን የሚለቅ ይመስልሃል?

አብርሃ ደስታ፡- ህዝቡን መቀየር ከቻልንና ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብለን ህዝቡን ካስተባበርን በምርጫ ፓርቲው ስልጣን ሊለቅ ይችላል። በእርግጥ ፓርቲው በምርጫ ስልጣን ለመልቀቅ ፍቃደኛ አይደለም። የፈለገውን ያህል ኀይል ተጠቅሞ ህወሓት በስልጣን ላይ ለመቆየት እንደሚፈልግ ይታወቃል። ነገር ግን በምርጫ ተቀጥቶ ስልጣን እንዲለቅ ማስገደድ ይቻላል። ምርጫውን የሚሰርቅበት መዋቅሩን በማሳጣት ለህዝብ ድምፅ የሚንበረከክበት ዕድል አሁንም አለ።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>