Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

“የአሲምባ ፍቅር”–መጽሃፍ ቅኝት –በክንፉ አሰፋ

$
0
0

ye-asimba-fikir (2)ደራሲ           ካሕሳይ አብርሃ ብስራት

 

ብዛት 446 ገጾች

 

በተስፋዬ ወልደዮሃንስ አዲስ አበባ ታትሞ የተሰራጨ

 

* ከስር በስእሉ እንደሚታየው ኢሲምባ 3250 ሜትር ከፍታ ላይ በትግራይ ውስጥ ያለ ተራራ ነው አሲምባ በዚህ ከፍታው ሳቢያ ሌሊት ላይ በጉም ይሸፈናል። አሲምባ “ቀይ አንባ” ማለት ነው።

 

           እንደ መንደርደርያ

ይሀ መጽሃፍ በዋሽንግተን ዲሲ – ሳንኮፋ ቢሮ ውስጥ ሲመረቅ በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝቼ ነበር። መገኘት ብቻ ሳይሆን በዝግጅቱ ላይ ግራ ያጋቡኝን ጥያቄዎች ለመጽሃፉ ደራሲ አቅርቤለት ነበር። የኔ ግርታ ምናልባትም የብዙዎቻችሁ ጥያቄ ሊሆን ስለሚችል እዚህ ላይ እንደገና ማንሳቱን መረጥኩ። የመጀመርያው ጥያቄ “ይህ ታሪክ 30 አመታት አለፈው። ታዲያ አንድ ትውልድ ካለፈ በኋላ አሁን ይፋ መሆኑ ለምን አስፈለገ?” የሚልና ሁለተኛው ደግሞ “ስለዚያ ትውልድ ሌሎች ከጻፏቸው መጽሃፍትና መጣጥፎች ‘የአሲምባ ታሪክ’ ን ለየት የሚያደርገውስ ምንድነው? ስለቀደመው ትውልድ አሉታዊ ይዘት ይኖረው ይሆን? ‘ የሚሉ ነበሩ።

ለጥያቄዎቼ ያገኘሁት መልስ ሳይሆን የመልስ ምት ነበር። በዚያች ትንሽ አዳራሽ ውስጥ የነበሩት የኢህአፓ ሰዎች ጥያቄውን በበጎ ሳይሆን በክፉ ስለተመለከቱት፤ ምላሻችውም የበጎ አልነበረም።  የመጽሃፉ ደራሲ አቶ ካሕሳይ አብርሃም በመልሳችው አንድ አረፍተ-ነገር በተናገሩ ቁጥር ይጨበጨብላቸው ነበር። እናም ቤቱን የሞሉት የዚያ ትውልድ ወገኖች ምላሽ የማብራራትና የማስረዳት ሳይሆን ይልቁንም ራስን የመከላከል (ዲፌንሲቭ) አይነት ነው የነበረው። ውይይቱ እየገፋ ሲሄድ ትውልድን እያንጻጸሩ አንዱን ትውልድ ብቻ የማወደስ አዝማሚያ ላይም ተደረሰ። በመጽሃፉ ምረቃ ዋና ተናጋሪ የነበሩት ፕ/ር ሃይሌ ገሪማ ግን ሂደቱን ስላልወደዱት በመሃል ጣልቃ መግባት ነበረባቸው። ተናጋሪዎቹን በመውቀስ ለቀረቡት ጥያቄዎች በስርዓቱ መለስ መስጠት እንዳለባቸውና የዚህ ጥያቄ ምላሽም በጣም አስፈላጊ ስለመሆኑ ምክር ሰጡ።

ከዚያ በኋላም የውይይቱ አጀንዳ አልተቀየረም። ርዕሱም ከዚህ መስመር ሳይወጣ ዝግጅቱ ተገባደደ። ሁሉም በዚያ ዘመን ስለነበረው ትውልድ ጽናት፣ ፍቅር እና መተሳሰብ እያንሳ 30 አመት ወደኋላ ተመልሶ ነጎደ። እኔ ግን ለጥያቄዎቼ ተገቢውን መልስ ሳላገኝ፤ ይልቁንም የራሴውኑ ትውልድ እስኪበቃው አስወቅሼ ከሳንኮፋ ቢሮ ወጣሁ። መውጫው በር ላይ ግን አንዲት ጠና ያሉ የቀድሞ ኢህአፓ ታጋይ የነበሩ ወይዘሮ ያዙኝ።

“.. ሰቆቃውን ማስታወስ እንኳን አንፈልግም። በፊታችን ሲደፉ የነበሩ ወገኖች፣ ይደርስብን የነበረው ግፍና በደል…. የጓዶች አሰቃቂ እልቂት… ይህንን ሁሉ ስናስታውስ ያመናል። በዚህም የተነሳ በተቻለ መጠን ሁሉንም ለመርሳት ነው ይምንሻው…።” አሉኝ።

እኔም ለዚሁ ነበር የጠየቅኩት። ደራሲው ከመድረክ ላይ ይህንን ምላሽ ቢሰጠኝ ኖሮ ባልተከፋሁ ነበር። በርግጥ ታሪኩ ዘግይቶ ለመውጣቱ ምክንያቱ ይህ ከሆነ ሁሉም ሊረዳው ይችላል። የኛ ትውልድ ግን ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)  በጎ የሆነ አመለካከት የለውም።  ከዚህ ቀደም ስለ ኢሕአፓ ያነበብናቸውም ሆኑ የሰማናቸው ታሪኮች ሁሉ አሉታዊ ይዘት ያላቸው ናቸው። የክፍሉ ታደሰ “ያ ትውልድ” እና በልጂግ አሊ በቅርብ ያሳተመው “ቀለበቴን ስጧት” መጽሃፎች ትንሽ ለየት ይላሉ። በተለይ “ቀለበቴን ስጧት” የሚለውን መድብል አንብቤ እንደጨረስኩ ስላዛ ትውልድ ያለኝ አመለካከት የተቀየረ ይመስለኛል። ምንም እንኳን ድርጅታዊ ችግሮች ቢታዩበትም፣ ያ ትውልድ ለተነሳለት አላማ የከፈለው መስዋዕትነት እና ያሳይ የነበረው የአላማ ጽናት በእጅጉ የሚደነቅ መሆኑን ከመጽሃፉ ታሪኮች መገንዘብ ይቻላል።

***

          “የአሲምባ ፍቅር” መጽሃፍ ደግሞ እንደወረደ የተተረከ የዚያ ትውልድ የጦር ሜዳ ውሎ ላይ ያጠነጥናል።

 

ከሰላሳ አመታት የስደት ኑሮ በኋላ ከሚኖርበት ዴንቨር ኮሎራዶ በመነሳት ይመር ንጉሴ የተባለን ገበሬ ለመጠየቅ ወደ ወልዲያ፣ ክዚያም ወደ አሲምባ ያመራል – ካሕሳይ አብርሃ ብስራት (አማኑኤል)። ካሕሳይ ስፍራው እስኪደርስ የነበረው ታሪክ ልብ እያንጠለጠለ ይሄድና በስፍራው ሲደርስ ያጋጠመውን አሳዛኝ ዜና ይተርካል። ካሕሳይ በ 1968 ከአሲምባ ወደ ወልዲያ ለወታደራዊ ተልዕኮ ሄዶ በሚሊሽያ ይመር ንጉሴ ነበር የተማረከው።

የመጽሃፉ ደራሲ ካሕሳይ አብርሃ በ1999 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ እሱን የሚመለከት ታሪክ በጋዜጣ ላይ መውጣቱን ያነብባል። በጋዜጣው የወጣው የእሱ እና የሦስት የትግል ጓደኞቹ ታሪክ በደራሲው ውስጥ ለዓመታት ታፍኖ የከረመውን ፥ ታሪኩን በመጽሃፍ የማውጣት ህልም ነፍስ  እንደዘራበት ይናገራል። ከአመታት ውጣ ውረድ በኋላም ህልሙ እውን ሆኖ መጽሃፉ ለንባብ በቃ።

 

ታሪኩ ከ1968 ዓ.ም. እስከ 1970 ዓ.ም. ድረስ የነበረውን የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ሠራዊት (ኢሕአሠ) የትግል ሂደት በስፋት ይቃኛል። በደራሲው የግል የትግል ውጣ-ውረድ ላይ የተሞረኮዘው ይህ ትረካ በመጀመሪያ በመቅረጸ-ድምጽ (ቴፕ) እንዲቀረጽ ተደርጎ ከዚያም የብዙዎች አስተያየት ከታከለበት በኋላ ወደ መጽሃፍ የተለወጠ ታሪክ ነው።

ካሕሳይ ኢሕአሠን በ15 አመቱ ሲቀላቀል በትምህርቱ ብዙም ያልግፋ የአርሶ አደር ልጅ ነበር። አሲምባ እንደደረሰ እውነተኛ ስሙን ረስቶ “አማኑኤል” የሚል መጠርያ ተሰጠው።  ብዙም ሳይቆይ ከጥቂት ወታደራዊና ፖለቲካዊ ስልጠና በኋላ ለወታደራዊ ግዳጅ ተላከ። አሲምባን ለቅቆ እስኪኮበልል ድረስም በበርካታ የፍልሚያ መስኮችም ተሰማርቶ እንደነበር በአሲምባ ፍቅር ይተርካል።

የመጽሃፉ ደራሲ በዚያ በለጋ እድሜው ወደ ትጥቅ ትግሉ እንዲገባ ያነሳሱት ምክንያቶች ላይ በጽሁፉ ብዙም ትኩረት አላደረገም። ከምክንያቶቹ ይልቅ በተግባራቱ ላይ በስፋት ሄዶባቸዋል። ይሁንና የብሄር መብት እና የመሬት ጥያቄ ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን ከመጽሃፉ መገንዘብ ይቻላል። ስለ ብሄር ጥያቄ ያነሳው ነጥብ “ዩኒቨርሲቲ ለማለፍ ከፈለጋችሁ አማርኛ በደንብ ማወቅ አለባችሁ። አማርኛ ካላለፋችሁ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት አትችሉም።”  (የአሲምባ ፍቅር ገጽ 33) የሚለውን የስምንተኛ ክፍል መምህሩን ማብራሪያ ይጠቅሳል። እናም ከሌሎች ትምህርቶች በተለየ አማርኛን ብዙ ግዜ ሰጥቶ ማጥናቱን ካሕሳይ አምርሮ ይተቻል።

ይህ ከብሄር ጥያቄ ጋር ለምን እንደተያያዘ ግራ ያጋባል። ዩኒቨርሲቲ ለመግባት አማርኛ ብቻ ሳይሆን እንግሊዝኛም መስፈርት ነበር። የሂሳብ ትምህርትም እንዲሁ። እነዚህ እንደመስፈርት መቅረባቸው ስህተት ነው የምንል ከሆነ፡ ሁሉንም መጥቀስ ይገባናል። ካሕሳይ የእንግሊዝኛ ቋንቋ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ መስፈርት ስለመሆኑ ምንም የጠቀሰው ነገር የለም።  ለካሕሳይ ከእንግሊዝኛ ይልቅ  አማርኛ ነው የሚቀርበው። አማርኛን ጠንቅቆ ማውቁ ነው “የአሲምባ ፍቅር”ን በአማርኛ ለንባብ ያበቃልን። የአንድ ሃገር ህዝብ ለመግባባት አንድ የጋራ ቋንቋ መኖሩ ጉዳቱ ምኑ ላይ ነው?  የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ አማርኛ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቋንቋ ሆነ። ይህ ከብሄር ጭቆና ጋር ምን አገናኘው? አማርኛ ከአረብኛ ቀጥሎ በአለም ላይ ሁለተኛው የሴም ቋንቋ አይደላም እንዴ? ኢህአፓ በወቅቱ የብሄር ጥያቄን በዚህ አይን የሚያየው ከሆነ በጣም ያሳዝናል።

የመሬት ጥያቄን በተመለከተ ደግሞ ደራሲው በአባቱ ላይ ይደርስ የነበረው በደል እንዳስቆጨው በገጽ 31-32 ላይ አስፍሯል። ከመሬት ጋር በተያያዘ አባቱ ለዳኛ ጉቦ እየሰጡ እንደሚኖሩ ጽፏል (የአሲምባ ፍቅር ገጽ 32)።  እንዚህ ጉዳዮች እና ከዩኒቨርሲቲ በክረምቱ ወራት የሚመጡ ወጣቶች “መሬት ላራሹ” እያሉ ወደ ትግሉ እንዲገባ እንደገፋፉት ይናገራል። ፍትህን ለማምጣትም ቆርጦ ወደ አሲምባ ተራራ አመራ።

ፍትሕ ላጡ ወገኖቹ ተቆርቁሮና የህዝብ ብሶት ገፍቶት ወደ አሲምባ በረሃ የገባው ካህሳይ በገጽ 52 ላይ እንዲህ ይለናል።

“ኪንኪታ የሚባል ቦታ በሌሊት ገባን። ሊነጋጋ ሲል የደርግ ሰላይ መሆኑ የተነገረንን ሃይሉ ካህሳይ የሚባለውን ሰው ቤት ከበብነው። … ሃይሉ ካህሳይ ሰንገዴ ከደረስን በኋላ ውሳኔ ተሰጥቶበት በሰራዊቱ የተገደለ የመጀመሪያው ሰው ሆነ።” (የአሲምባ ፍቅር ገጽ 52)

ይህ የመጀመሪያ እርምጃ ኢፍታዊነትን በኢፍታዊ መንገድ ለመታገል መነሳትን ያሳየናል።  ድርጊቱ ያ ትውልድ የተነሳለት መብትን የማስጠበቅ አላማ መስመሩን እንዲለቅ ማድረጉን ይጠቁማል። ወጣቱ ወደ አሲምባ ሲነጉድ ለነጻነት ትግል እንጂ ለግድያና ለዝርፊያ እንዳልነበር ከጅምሩ ተናግሯልና።

ካህሳይ ኪዚያም ቀጠለ። በገጽ 65-66 ላይ በመጀመሪያዎቹ ወራት በዳሎል ለዘረፋ በተሰማሩበት ወቅት በየነ አብረሃ የሚባል “ነጭ ለባሽ” መኖሪያ ቤት በመሄድ፣

“… ንብረቱን ዘረፍነው፤ ከነበሩት ከብቶች እና ከእህሉ ግማሹን ከፍለን ለሚስቱ በመተው እኩሌታውን ወሰድን።… አንዱን በሬ ለማረድ ፈለግንና ለመያዝ ሞከርን፤ በሬው ሃይለኛ ስለነበር በመሳሪያ ተመትቶ ወደቀና አርደን ስጋውን ይዘን ሄድን።” (የአሲምባ ፍቅር ገጽ 65)

ካህሳይ ግን ይህ ኢፍትሃዊ ውሳኔ ስሜቱን እንደነካው በመጽሃፉ አስፍሯል።

ከመጽሃፉ እንደምንረዳው የኢህአፓ ወታደራዊ ክንፍ ነው የተባለው ኢህአሠ የፖለቲካ አመራሩን ከየትኛው አንጃ እንደሚያገኝ ግልጽ አልነበረም።  ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ እና ጸጋዬ ደብተራው አሲምባ ግንቦት ወር 1968 ዓ.ም. ሲገናኙ የተወያዩበት አንደኛው አጀንዳ ይኸው ጉዳይ ነበር። በገጽ 100 ላይ እንደሰፈረው ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዳታደርጉ የሚል ትዕዛዝ የያዘ የጽሁፍ ማስረጃ  ጸጋዬ ደብተራው ከእጅ ቦርሳው አውጥቶ ለዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ አሳየው። “ዶ/ር ተስፋዬ ወረቀቱን ተቀብሎ ተመለከተና፡ ያሳየው መረጃ የፓርቲው ትዕዛዝ እንዳልሆን ለደብተራው ነገረው።” (የአሲምባ ፍቅር ገጽ 100) ኢህአፓ አመራሩም ሆነ አሰራሩ ምስጢራዊ በመሆኑ፡ ማን ምን እንደሚሰራ፡ መመርያና ትዕዛዞች ከየት እንደሚመጡ በግልጽ የሚታወቅ ነገር አልነበረም።

በገጽ 107 ላይ ደግሞ የጆርጅ ኦርዌልን “አኒማል ፋርም” የሚያስታውሰን አንድ አስገራሚ ክስተት ሰፍሯል። የኢህአሠ ሰራዊት ከአሲምባ ወጥቶ ወደ ወሎና ጎንደር እንደርታ ሲጓዝ የጸጋዬ ደብተራው ሽጉጥ ጠፍቶ በከተማው ሁሉ ተፈልጎ ሳይገኝ ቀረ። በሰራዊቱ ደንብ ጸጋዬ መቀጣት ነበረበት። ሌሎቻችን ስናጠፋ እና እቃ ስንጥል እንደምንቀጣው ጸጋዬም መቀጣት አለበት እያለ ሰራዊቱ ማጉረምረም ጀመረ። ደራሲውም ከአርጎምጓሚዎቹ አንዱ እንደነበር አምኗል። ጸጋዬ ደብተራው ካህሳይን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤

“አንዳንድ ጊዜ ሃቅ መናገር ያስወነጅላል። … ስታስበው ማነው ቀጪ፤ ማነው ተቀጪ? አንዳንድ ጊዜ አይቶ እንዳላየ ማለፍ አለብህ። … ሲል ጸጋዬ ደብተራው ካህሳይን መክሮ ሸኘው… (የአሲምባ ፍቅር ገጽ 107)።  ጆርጅ ኦርዌል “እንሣት ሁሉ እኩል ናቸው። አንዳንድ እንስሳ ግን ከሌሎቹ እንስሳት የበለጠ እኩል ናቸው።” ይለናል።

ከዚያ ባሻገር በኢሕአፓ አመራር አባላት መካከል የተፈጠረው የአካሄድ ልዩነት፥  ያልተማሩ አባላትን የመናቅ እና የማግለል ሂደት፣  የትጥቅ ትግሉ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ  እንዳሳደረ ደራሲው ፈራ ተባ እያለ አስፍሯል። የአካሄድ ልዩነት የሚያሳዩ አባላት በ”አንጃ”ነት  የተፈረጁትን መገደል፣ ማሰር እና ሽሽት፣  የአመራር ብቃት መጉደል፥ ሰራዊቱን እያስመታው መጥቶ፣ በመጨረሻ አሲምባ ከኢሕአሠ ምሽግነቱ ለማክተሙ ምክንያት ሆኗል።

ታሪኩ በጥቅል ሲታይ ከሞት ፍርድ አስመልጦ ለዛሬ መኖሩ ያበቃው የወሎው ገበሬ ይመር ንጉሤና  በትግል ወቅት ስላገኛት የመጀመርያ የፍቅር ጓደኛኛው በታጋይ ድላይ ዙርያ ያጠነጥናል።

በአሲምባ ለመጀመሪያ ጊዜ በድላይ ፍቅር ቢለከፍም በፍቅሩ ምክንያት ከአላማው ላለመውጣት ሲታገል እንደነበር ትረካው ጉልህ አድርጎ ያሳየናል። ካህሳይ ፍቅርን ያጣጣመው በድላይ ነው። ከሷ ጋር በበረሃ የማይረሳ ትውስታዎችምም አሉት።  ካህሳይ ከድላይ ይልቅ ለአሲምባ ተራራ ያለው ፍቅር ግን ይበረታል።

ካህሳይ በትምህርቱ ብዙም ያልገፋ ወጣት ቢሆንም የዚያን ወቅት ውስብሰብ ክስተቶች የማስታወስ ችሎታው ይሚደነቅ ነው። በሦስት ዓመት የትግል ጊዜያት በኢሕአሠ ውስጥ ያሳለፋቸውን ውጣ ውረዶች በስፋት ይተረካል።   የከተማውን፣ የቀበሌውን፣ የመንደሮችን ስሞች፣ ከዚህ አልፎም የቀየዎችንና ተራሮች፣ ወንዞችና  የኮረብታዎችን ስሞች ሁሉ በመጽሃፉ ቁልጭ አድርጎ ስሏቸዋል። የታጋይ ጓዶቹን እርከን፣  እውነተኛ ስሞች፣  ቅጽልና ምስጢራዊ ስሞችም ሁሉ ከሰላሳ አመታት በኋላ አልረሳቸውም። ማን መች እንደተሰዋ፣ የት እና እንዴት እንደተሰዋ ሁሉ ያስታውሳል።

ደራሲው ከአሜሪካ የስደት  ቆይታቸው በኋላ አሲምባ ተብሎ የሚጠራውን ይህንን  ”ቀይ አንባ” ተራራ ጐብኝቷል። ወደ አሲምባ የሄደበትም ምክንያት ከዛሬ ሰላሳ አመት በፊት የማረከውንና ከሞት ያተረፈውን የገበሬ ሚሊሽያ ለማመስገን ነበር። በዚህ ጉብኝቱ ታዲያ የአሲምባ አካባቢ መልማቱን መንገድ መግባቱን፣ ውኃ መገደቡን፣ ትምህርት ቤት መሠራቱን ይመሰክራል። እሱ ራሱ ከ 30 ዓመታት በፊት ታግሎለት ስለነበረው የመብትና የፍትህ ጥያቄ መሟላት ላይ ግን ምንም አላለም።

መጽሃፉ በዚያ ዘመን በትግሉ ውስጥ ለነበረ፡  በትዝታ ማዕበል ሰላሳ አመት ወደኋላ ይወስደዋል። ለአዲሱ ትውልድ ደግሞ ስለዚያ ውስብስብና አስቸጋሪ የትግል ዘመን ውጣ ውረድ ያስቃኘዋል።  ይህንን በይዘቱ ለየት ያለ መጽሃፍ ገዝቶ ማንበቡ ስላለፈው ትውልድ በርካታ ግንዛቤዎች ይሰጠናል። (ስዕል – የአሲምባ ተራራ)


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>