Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

እንደራሴ ስሚዝ እ ኬረን ባስ አዲስ አበባ ሊሄዱ ነው

$
0
0

በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Chris-Smithአሜሪካና ሌሎች ለሰብአዊ መብት መከበር ዋጋ የሚሰጡ አገሮች በሙሉ በ”አዲስ አበባው” አገዛዝ ላይ ጠንካራ አቋም መያዛቸውን ያለ አንዳች ማወላወል ማሳየት እንደሚገባቸው አሳስበው የነበሩት ኮንግረንስ ማን ክሪስ ስሚዝና ባልደረባቸው እንደራሴ ኬረን ባስ አዲስ አበባ እንደሚገቡ ተጠቆመ። በሰኔ (ጁን) ወር “… የአሜሪካ መንግስትም ሆነ ሌሎች የምዕራብ አገራት፣ ኢህአዴግ ኢትዮጵያዊያን ላይ እየፈጸመ ያለውን ተግባር በመረዳት አቋማቸውን በግልጽ ማስቀመጥ ይገባቸዋል” የሚል ጥሪ ያስተላለፉት ክሪስ ስሚዝ አዲስ አበባ መምጣት ኢህአዴግን እንዳሳሰበው ለማወቅ ተችሏል።

ኢትዮጵያ ከመለስ በኋላ” በሚል አጀንዳ ተዘጋጅቶ የነበረውን የምክክር ስብሰባ የመሩት የአሜሪካን ምክር ቤት እንደራሴ /ኮንግረንስማን/ ክሪስ ስሚዝና ሌላዋ ባልደረባቸው እንደራሴ ኬረን ባስ ኢህአዴግ እስር ቤቶችን እንዲያሳይ፣ የታሰሩትን የፖለቲካ እስረኞችንም ይሁን ከሙስሊሙ ኅብረተሰብ በግፍ ለእስር የተዳረጉትን እንዲያስጎበኝ ለሚቀርብለት ጥያቄና በጸረ ሽብርና ህጉ ዙሪያ የሚሰጠው ምላሽ በጉጉት ይጠበቃል።

ምክክሩን ሲከፍቱ አቶ መለስን “አሮጋንት /እብሪተኛ/፣ የፈለገውን ነገር በፈለገው ጊዜ የሚያደርግ ሰው እንደነበር አዲስ አበባ ሄጄ ባነጋገርኩበት ወቅት አረጋግጫለሁ” በማለት የገለጹት ክሪስ ስሚዝ፣ ከባልደረባቸው ጋር ወደ አዲስ አበባ የሚያመሩት አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታራምደውን አቋም ለመመርመር የሚያስችላትን ስራ ለመስራት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

ከምክክሩ በፊትና በኋላ ክሪስ ስሚዝ በሰጡት ጠንካራ አስተያየት የተደናገጠው ኢህአዴግ አዲስ ዘመን በሚባለው ልሳኑ “አሜሪካ የኢትዮጵያ አጋርና ወዳጅ መሆንዋን አረጋገጠች” በማለት የሌሎች ተናጋሪዎችን  ወደጎን በመተው የአምባሳደር ዶናልድ ያማሞቶን ብቻ አንድ ሃረግ ንግግር ቀንጭቦ ዘግቦ ነበር። በአሜሪካ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣን ባልተለመደ ሁኔታ የተብጠለጠለው ኢህአዴግ ወዳጆቹን ለማረጋጋት ያማሞቶን ጠቅሶ ያሰራጨው ዜና በወቅቱ በደጋፊዎቹ የፌስቡክ ገጽ ላይ በስፋት ተበትኖ ነበር።

እንደራሴ ኬረን ባስ

bahnሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አሜሪካ አቋሟን የምትፈትሽበት ወቅት ላይ መሆኗን ያመላክታል የተባለው የአዲስ አበባ ጉብኝት አስመልክቶ የጎልጉል ምንጮች እንዳሉት ኢህአዴግ የፖለተካውን ምህዳር በማጥበብ፣ በጸረ ሽብር ህጉ እያሳበበ የመናገርና የመሰብሰብ መብትን ማፈኑ፣ የነጻ ሚዲያና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ማነቁ፣ በተለይም በእስር ቤት የሚሰቃዩ ወገኖችን በአካል በመገኘት በማነጋገር አቋም ለመውሰድ መታቀዱን አመልክተዋል። ይህም ከፖለቲካ እስረኞች ጀምሮ፣ ጋዜጠኞችን፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን፣ የሙስሊሙን ኅብረተሰብ ጥያቄ ከፍ አድገው በማንሳታቸው ለእስር የተዳረጉትን ወዘተ የሚያጠቃልል ይሆናል፡፡

“የሚሆነው እስከሚሆን መጠበቅ ነው” በማለት ለጎልጉል አስተያየት የሰጡ አንድ ዲፕሎማት እንዳሉት ነሐሴ 10 ወይም 11 ቀን 2005 (ኦገስት 16 ወይም 17፤ 2013) ወደ ኢትዮጵያ የሚያመሩት ሁለቱ እንደራሴዎች፤ ለኢህአዴግ የሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች እጅግ መሰረታዊ እንደሆኑ ይናገራሉ።

“ጉብኝቱ የሽርሽርና እንደተለመደው አይነት የሁለትዮሽ ስብሰባና ስምምነት ለማድረግ አይደለም” የሚሉት አስተያየት ሰጪ “ኢህአዴግ በቅርቡ የአውሮፓ ህብረት ተወካዮች እስር ቤቶችን እንዳይጎበኙ እንደከለከለው ማድረግ አይችልም” ብለዋል። ሲያስረዱም “በደቡብ ሱዳን ያለው የፖለቲካ ኡደት፣ በሶማሊያ ጭብጡ ያለየለት ሁከት፣ በኤርትራ ያለው የዛለ መንግስት እጣፈንታና የኢትዮጵያን ህዝብ በዘር ከፋፍሎ ጥቂቶች እንዲበለጽጉ ያደረገው ኢህአዴግ መጨረሻው አሜሪካንን በእጅጉ ሃሳብ ላይ ጥሏታል። በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ ውስጥ እየሰፋ የሄደው ቁርሾና የጥላቻ ፖለቲካ ሳይፈነዳ ኢህአዴግን ማረቅ የአሜሪካ ቀዳሚ አጀንዳ ሆኗል። ይህንን አጀንዳ አሜሪካ በቀላሉ ተጭበርብራ የምትቆልፈው አይሆንም።”

“የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ህገደንብ” የሚል ስያሜ ያለው ህግ ኢትዮጵያን የሚመራው ኢህአዴግ ከአሜሪካ መንግስት ለሚፈልገው ማናቸውም ድጋፍ መሟላት የሚገባቸውን የሰብአዊና የዴሞክራሲ መብት ግብአቶችን በቅድመ ሁኔታ የሚያስቀምጥ ነበር። ይህ ህግ ኢህአዴግ በከፍተኛ ደረጃ ገንዘብ አፍስሶ በአሜሪካን ጎትጓቾች (ሎቢዪስቶች) ዘመቻ ያካሄደበትና የወቅቱ የቡሽ አስተዳደር “እንዝላልነት” ታክሎበት ሊመክን ችሏል። ይህን ህግ እንደገና ለማጸደቅ እንደሚሰሩ በግልጽ የተናገሩት ስሚዝ፣ “አሁን ፖሊሲያችንን ዳግም የመፈተሽያ ጊዜ ላይ ነን። ቁም ነገሩ ከተጨቆኑት ወገኖች ጋር መቆሙ ላይ ነው። ከተጨቆኑት ወገኖች ጋር እንቆማለን” በማለት አቋማቸውን ግልጽ አድርገው ነበር።

በዚህ ይሁን በሌላ ምክንያት የመለስ ምትክ የሆኑት አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝና የስኳር ሚኒስትሩ አቶ አባይ ጸሐዬ ሰሞኑንን “የዲሞክራሲ ማበብ የህልውና ጉዳይ ነው” በማለት ለተለያዩ መገናኛዎች በየፊናቸው የተናገሩትን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በስፋት ዘግቦታል። እነሱ ይህን ይበሉ እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው እውነታው ከመለስ እጅ በተካሄደው ርክክብ መሰረት አፈናውን አጠናክሮ የቀጠለ ስለመሆኑ ከየአቅጣጫው የሚጎርፈው መረጃ ከወትሮው በተለየ ይፋ እየሆነ ነው።

ኢትዮጵያን በነጻ አውጪ ስም እየመራ ያለው ህወሃት በራሳቸው በአሜሪካኖቹ ቋንቋ ‘አሸባሪን መዋጋት’ በሚል ሰበብ ምዕራባውያንን ሲያልባቸው ቢቆይም “ሽብርንና ሽብርተኛነትን የመታገል ትብብር ግን የዜጎችን ሰብአዊ መብት ለመርገጥ ፍቃድ ማግኛ አይደለም። የመብት ረገጣ ሽፋን ሊሆን አይገባም” ሲሉ በጀርመን ሬዲዮ የመረረ ንግግር ንግግር የተናገሩት እንደራሴ ስሚዝ “ዛሬ አሜሪካ አቋሟን የምትፈትሽበት ጊዜ ላይ ነች” በማለት ከሁለት ወር በፊት የተናገሩትን ከዳር ያደርሱት ይሆን የሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚያገኝበት ወቅት ተደርሷል፡፡

 

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>