ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት እሑድ ሰኔ ፳፪ ቀን ፪ሺህ፮ ዓ.ም. ቅፅ ፪ ፣ ቁጥር ፳፭
- የዘመኑ «የትግሬ-ወያኔ ተቃዋሚዎች» ተብዬ ዘዬ፦ የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች እንጂ የዐማራ ነገድ ተወላጆች አልተፈናቀሉም፣ አልተገደሉም፤
ባለፉት ፷(ስድሣ) እና ፸(ሰባ) ዓመታት ውስጥ፥ በኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ታሪክ ውስጥ «ተፈጠሩ» ለሚባሉ ሁለንተናዊ ችግሮች ሁሉ ተጠያቂ ተደርጎ የሚቀርበው እና በተገኘበት ቦታ ሁሉ የግፍ እና የሥቃይ ዓይነቶችን እንዲቀበል የሚደረገው የዐማራው ነገድ መሆኑን እያዬን እና እየሰማን ነው። ከሁሉም በላይ በትግሬ-ወያኔ ዘረኛ የአገዛዝ ዘመን፣ የዐማራው ነገድ ተወላጆች በጅምላ የአገሪቱ ነገዶች እና ጎሣዎች አውራ ጠላት እንደሆኑ ተቆጥረው በተገኙበት ሁሉ፥ እንዲገደሉ፣ እንዲታሠሩ፣ እንዲሰቃዩ፣ እንዲሣደዱ፣ እንደ ሙክት ተዘቅዝቀው ተሰቅለው ቆዳቸው እንዲገፈፍ፣ በቤት ውስጥ ተዘግተው በእሣት እንዲቃጠሉ፣ ከነሕይዎታቸው ታስረው ገደል እንዲወርወሩ፣ ነፍሰጡር የዐማራ እናቶች ሆዳቸው በሣንጃ ተተልትሎ ሽል እንዲሰለብ፣ ኃብት ንብረታቸውን ተነጥቀው ከአያት ከቅድመ-አያቶቻቸው ጀምሮ ከኖሩባቸው ቀዬዎች እንዲባረሩ ወይም ደግሞ በሥነልቡና ጫና ለዘመናት ከኖሩባቸው አካባቢዎች ተሸማቅቀው እንዲለቁ፣ በዐማራነታቸው እና በኢትዮጵያዊ ማንነታቸው እንዲያፍሩ፣ እየተደረገ መሆኑን ዓለም ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ሃቅ ነው። በዐማራው ነገድ ላይ ለሚደርሰው አሣዛኝ እና አሣፋሪ ክስተት፣ ከድርጊቱ ተላሚዎች እና ፈፃሚዎች ባልተናነሰ ሁኔታ፣ ከራሱ ከዐማራው አብራክ የወጡ ልሂቃን፣ በተለይም «የኢትዮጵያን ፖለቲካ እንዘውራለን» የሚሉቱ፣ የሚፈፅሙት የክህደት እና የባንዳነት ተግባር፣ ለታሪክ እና ለትውልድ ትልቅ ጠባሣ ትቶ እንደሚያልፍ ማንም አመዛዛኝ ኅሊና ያለው ሰብዓዊ ፍጡር የሚገነዘበው ጉዳይ ነው። ለአብነት ያህል በዐማራው ነገድ ተወላጆች ላይ የዘር ማጥፋት እና የዘር ማጽዳት ዘመቻ ከተፈተባቸው የኢትዮጵያ ክፍሎች መካከል በተለይ ከአምቦ እስከ ደምቢ-ዶሎ ባሉት አካባቢዎች ከ፲፱፻፹ ዓ.ም. ጀምሮ የሚፈፀሙትን ግፎች አለፍ አለፍ እያልን እንመልከት።
- በ፲፱፻፹ ዓ.ም. በወቅቱ አጠራር በወለጋ ክፍለሀገር፣ አሶሳ አውራጃ፣ ባምቤሲ ወረዳ፣ ልዩ ስሙ ሸርቆሌ በሚባለው ቀበሌ ይኖሩ በነበሩት ዐማሮች ላይ በሻቢያ አመራር ሠጪነት፣ የኦነግ ሠራዊት ፬፻(አራት መቶ) ዐማራዎችን ሰብስቦ፣ የስዊድን ተራድዖ ድርጅት ባሠራው የ፩ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመማሪያ ክፍሎች ውስጥ በማጎር፣ በሙሉ ከእነሕይዎታቸው በእሣት አጋይቷቸዋል።
- በ፲፱፻፹፪ ዓ.ም. በወቅቱ አጠራር በወለጋ ክፍለሀገር፣ አሶሳ አውራጃ፣ በአሶሳ ከተማ ይኖሩ በነበሩት ዐማሮች ላይ በሻቢያ አመራር ሠጪነት፣ የኦነግ ሠራዊት ፭፻(አምሥት መቶ) ያህሉን ሰብስቦ፣ በጥይት ረሽኗቸዋል፣ ከፊሉን ደግሞ ከእነሕይዎታቸው በእሣት አጋይቷቸዋል።
- ከ፲፱፻፺፪ – ፲፱፻፺፫ ዓ.ም. በነበረው ጊዜ በምሥራቅ ወለጋ የወያኔ/ኦሕዴድ ካድሬዎች እና ታጣቂ ነፍሰ ገዳዮች የአካባቢውን የኦሮሞ ተወላጆች በማነሣሣት በሺህዎች የሚቆጠሩ ዐማሮችን በጥይት ቆልተዋል፣ በገጀራ ጨፍጭፈዋል፤ ከ፳ሺህ የማያንሱትን አፈናቅለው ወደ ቡሬ(ጎጃም) አባርረዋቸዋል። የ«ዐማራ ክልል» የሚባለውን የሚገዛው ሌላው የትግሬ-ወያኔ ሎሌ የሆነው ብአዴን፣ እኒያን በኦሕዴድ ግፍ የተፈናቀሉትን ዐማሮች በወባ ወረርሽኝ በሚያልቁበት በጃዊ (አገው ምድር) ቆላማ ሥፍራ በተናቸው። ዛሬ ከእኒያ መከረኞች መካከል በሕይወት የሚኖሩ ካሉ በተዓምር የተረፉት ብቻ ናቸው።
- በመጋቢት ወር ፪ሺህ፮ ዓ.ም. ከምዕራብ ሸዋ (አምቦ ዳኖ ወረዳ) በመቶዎች የሚቆጠሩ የዐማራ ተወላጆችን የትግሬ-ወያኔ ተላላኪ በሆነው የኦሕዴድ ካድሬዎች እና ታጣቂዎች አማካይነት «አገራችሁ አይደለምና ውጡ» ተብለው ተባርረዋል፣፳፮ (ሃያ ስድስት) የሚሆኑት በአሠቃቂ ሁኔታ ተደብድበዋል፣ አቶ ጌጡ ክብረት የተባሉት ዐማራ በአሠቃቂ ሁኔታ በገጀራ ተቆራርጠው ተገድለዋል።
- በግንቦት ወር ፪ሺህ፮ ዓ.ም. በወለጋ ክፍለሀገር በጊምቢ እና በቄለም አውራጃዎች ይኖሩ በነበሩ፣ በቁጥር ከ፫ ሺህ እስከ ፰ሺህበሚደርሱ ዐማሮች ላይ፣ የትግሬ-ወያኔ/ኦሕዴድ ካድሬዎች እና ታጣቂ ነፍሰገዳዮች አሠቃቂ እና ዘግናኝ የሆኑ ግፎችን በመፈጸም፣ ኃብት ንብረታቸውን ነጥቀው አባርረዋቸዋል፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዐማሮችን ጨፍጭፈዋቸዋል። በተለይ አርብ ግንቦት ፲፭ ቀን ፪ሺህ፮ ዓ.ም. በቅፅ ፪፣ ቁጥር ፳፩ባወጣነው መግለጫችን በዝርዝር እንዳብራራነው በጊምቢ ከተማ እና በአካባቢው ይኖሩ በነበሩት ዐማሮች ላይ የደረሰው ግፍ እና በደል ዘግናኝ ነው።
ይህ በዐማራው ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍ እና ስቃይ ሰሚ እና ሃግ ባይ ያጣው፦ አንድም ዐማራው የሚፈጸምበትን በደል አለመረዳቱ፣ አልያም በአብዛኛው የዐማራው ነገድ ልሂቃን ዕምነት «የትግሬ-ወያኔ እና ተከታዮቹ በደሉን የሚፈጽሙት ከዘር ጥላቻ ተነስተው ሣይሆን፣ ከማንኞቹም አምባገነን ገዥዎች ድርጊት ባልተለዬ ሁኔታ ነው፤» ከሚል የተሣሣተ መነሻ፤ ወይም ደግሞ በሁለቱም ምክንያቶች ነው። በሌላው ወገን ደግሞ «አሸናፊዎች ነን፣ ገዥዎች ነን» የሚሉት የትግሬ-ወያኔ እና በሥሩ የተደራጁት ዓላማ አስፈጻሚዎች የ«ላም አሸናፊዎች» በመሆናቸው ነው። የዐማራው ጠላቶች ዐማራው በዘር ተደራጅቶ የማያውቅ እና ዘረኛም እንዳልሆነ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ስለዚህ ዐማራው እነርሱ በከፈቱት መንገድ ከተጓዘ «ልንቋቋመው አንችልም» ብለው ስለሚያምኑ፣ ገና ሳይደራጅ ዘሩን ማጥፋት አለብን ብለው፣ እንደላም አሸናፊ ዐማራውን በተናጠል እየተከታተሉ ይመነጥራሉ። የሚያሣዝነው ግን የዐማራው ነገድ ችግር፣ በራሱ ነገድ አባሎች በተለይም በልሂቃኑ ጭምር በችግርነቱ አለመታየቱ፣ ለችግሩ መባባስና ከዚህ ደረጃ ላይ መድረስ የራሱን አስተዋፅዖ አድርጓል። ባለፉት ፳፫(ሃያ ሦሥት) ዓመታት በዐማራው ነገድ ተወላጆች ላይ የሚፈጸመው ግፍ ከመብዛቱ የተነሣ ኢትዮጵያን በጠቅላላ እና መላውን ምሥራቅ አፍሪቃ በተመሠቃቀለ የእርስ በእርስ ፍጅት የሚከት የብሶት ማዕበል እየተንተከተከ መሆኑን መገንዘብ ብልህነት ነው። ስለሆነም የዐማራ ልጅ የሆንክ ይህን ግፍ ማስቆም የሚቻለው በመሸሽ፣ በመፍራት፣ ለሌላ አካል «አቤት» በማለት ብቻ አይደለም። ግፉ፣ እንግልቱ፣ መሣደዱ፣ ንብረት መቀማቱ፣ በኢትዮጵያዊ ዐማራ ማንነት መሸማቀቁ የሚቆመው እያንዳንዱ ዐማራ ኅሊናው ሲሸፍት፣ ከዚያም «እምቢ ለነፃነቴ! እምቢ ለኃይማኖቴ! እምቢ ለንብረቴ! እምቢ ለአገሬ! በቃ!» ብሎ የራሱን ዕርምጃ ሲወስድ ብቻ ነው። በመሆኑም በየትኛውም አኅጉር፣ በየትኛውም ሥፍራ የምትኖሩ የዐማራ ነገድ አባሎች በዘራችን ምክንያት እየተፈጸመብን ያለውን የዘር ማፅዳት እና የዘር ማጥፋት ወንጀል ለመቋቋም የምንችለው፣ የችግሩ መፍቻ ቁልፍ በእጃችን መሆኑን ስናምን ብቻ ነው። ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ለመመሥረት የበቃውም በዐማራው ላይ በተከታታይ ጊዜያት የሚደረጉት ግፎች ባስከተሉት ጉዳት በተቆጩ የዐማራ ልጆች ነው። ስለሆነም ሞረሽ ወገኔ ትላንትም ሆነ ዛሬ በዐማራው ላይ የሚደርሰው ግፍ እና ሠቆቃ እንዲቆም በዓለም ዙሪያ ያሉት የነገዱ አባሎች እንዲቀላቀሉን፣ ኃይላችንንም አስተባብረን ለተገፉት እና ለሚበደሉት ወገኖቻችን አለኝታ እንድንሆን ጥሪውን ያቀርባል። ዐማራን ከፈጽሞ ጥፋት እንታደጋለን! የዐማራው ደም የውሻ ደም ሆኖ አይቀርም! ፈለገ-አሥራት የትውልዳችን ቃልኪዳን ነው! ኢትዮጵያ በጀግና እና ቆራጥ ልጆቿ መስዋዕትነት ታፍራ እና ተከብራ ለዘለዓለም ትኖራለች