ከሥርጉተ ሥላሴ 04.07.2014 (ሲውዘርላንድ – ዙሪክ)
የምልዕቱ ሙቀቱ የፈላ፣ የማያቋርጥ ጠላትን የሚያርገበግብ፣ የጠላትን መጋኛ የሚያናውጥ ከሆነ ድንበር አልቦሽ የነፃነት እንቅስቃሴ እልህን አመንጭቶ ቁርጠኝነትን መንበር ላይ ያወጣል። ቁርጠኝነቱም በፈንታው ደግሞ እራሱን ወልዶ ተግባራትን በቅድመ ተከተል በስክንት አልምቶ ግንባርን ባለማጠፍ ፍሬ – ዘር የሚያመርትብት አዲስ ምዕርፍን በተደሞ ያውጃል።
ማፈርና አንገቱን ዘቅዝቆ መሄድ ያለበት ታሪክን የገደለ፤ የቀደምት አርበኛ አባቶቻችነን አጽማቸውን ከመቃብር እያወጣ መስዋዕትነታቸውን ዋጋ አልቦሽ ያደረገው፤ ያፈሰሱትን የድል ደም ነጋሪት ለባዕድ ውጭ ወራሪ የሚቸረችረው የማንነት ነጋዴው ሙጃው ወያኔ እንጂ የአባቶቹን አደራ ተረክቦ ለአንዲት ቀደምት ሉዕላዊት ሀገር የሚታገል የነፃነት መንፈስ ሊሆን አይገባም – ፈጽሞ።
በዬትኛውም መስፈርት ቢሆን በቀደሙት ኢትዮጵውያን ደምና አጥንት የቆዬውን የማንነታችን ተቋማት በስልትን በቋሳ መዶሻ የተረተረ፤ በፋስ የፈለጠ፤ በረግረግ አስውጦ የደረመሰ ጃርት የ90 ሚሊዮን የ80 ህብረ ብሄር ቀላማትን ያበበን ማንነት ያቀላ፤ የጥቁር ህዝብ አብነታዊነትን ትርጉምን ያበለዘ – ያፈለሰ ይህን መንፈስ የመምራት አቅምም ተፈጥሮውም ፈጽሞ የለውም። ይህንን ነው በላዩ ላይ እዬተናደ እዬፈረሰ ያለውን ማንነትን ተገንዝቦ በጽናት በህብረትና በአንድነት የቆሰለንውን ዜግነት እንታደገው ዘንድ ዘመኑ በአጽህኖት የሚያስተምረው። በዬትኛውም ሁኔታ ኃላፊነቱን የዘለለ ትውልድ ከተጠያቂነት አይድንም። ሳቢያ ማስታገሻ ቢሆን እንጂ እርግማንን አይፈውስም። ስለሆነም አትኩሮቱ ምክንያታዊ በሆነው እራስን ሆኖ በሁለት እግር የመቆም ጉዳይ ነው።
ለአንድ ጎሳ እጅግ ለወረደ የዘር ትርምስና የጥላቻ ጫጩትን ፍልፍሎ ለሞሸረ ሀገር በቀል ባንዳ ጥቃት እጅ መስጠት እውነትም ደማችን ተበርዟል፤ ተስልበናል ማለት ነው። ስለዚህም ከበፊቱ በበለጠ በጠነከረ – በተሰበበሰ – በሰከነ መንገድ አቅምን ያዳመጠ፤ አቅምን በአግባቡ ሊመራ የሚችል ዘርፍ ብዙ ዘላቂ በመርህ ላይ የተመሰረተ፤ መርህ የሚመራው ጽኑ አለታማ አንድነት ፈጥሮ በመንቀሳቀስ የልብን ማደረስ ይቻላል።
አኃታዊ እራይ የሁለመና ብቁ ወታደር እንዲሆን የምንፈቅድበት አራት ዓይናማው መንገዳችን ደግሞ ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረው አለምን የፈጠረው ሚስጥር ኢትዮጵያዊነት ጄኒራላችን ሊሆን ይገባል። በዚህ ማቀፍ ውስጥ መደማመጥ ከተቻለ የምንፈልገውን ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ነገን ማግኘት እንችላለን።
መቻቻል ችሎቱ
እንደተረገዘ ህይወቱ።
ይህቺ ግጥም በአንድ ወቅት የቋጠርኳት ነበረች። አሁን ከእኛ የሚጠበቀው ደግሞ፤
የመቻቻል ችሎቱ
በኢጎ ላይ መዝምቱ። ይህ ከሆነ – እልህ እራሱ፤ እራሱን አፍርቶ መንገዳችን ይጠርጋል። ከግባችንም ያደርሳል። የጠላትህን ብልት ለመርታት የአንተን ብልት ስታሰናደው ብቻ ይሆናል። ለማሸነፍ ሆድ ዕቃውን ማወቅ አለብህ። ስታውቀው ታሸንፈዋለህ። ለማሸነፍ ግን መጀመሪያ ህሊናህን አሸንፈው። ጠላትህን በስሱ ብልቱ ገብተህ ማረድ የምትችለው የታላቁን ራዕይ የጥሪ ድምጽ ለማድመጥ ሥልጡን መንፈስ ሲኖርህ ብቻ ነው። ቅን ልቦናህን ገቢር ላይ ማዋል ስትችል ብቻ ጠላትህን ታራግፋዋለህ እስከነ ጉቶው። የቆረጥክ ዕለት በተፈለገው ግዳጅህ ላይ ከነፍስህ ያለህ ወይንም ያልተዛበህ ወይንም ያልሾለክ መሆንህ ታውቀዋለህ። ያን ጊዜ ከቀደምት አደራ በይነት ፍውሰት እንደ ዋጋህ ይከፈለሃል። ይህ ደግሞ ቢመቱም ቢኖሩም ህይወት ነው። ጧፍ።
ይህ ያሰፈራው ያርበተበተው ወገቡን ሲያልፈሰፍሰው የነበረው ወያኔ የሚወስዳቸው ግልጽ ወይንም ስውር ጥቃቶች የታላቁን ሀገራዊ የአደራ ራዕይ የሚያፍታታ – የሚመክት እያንዳንዱ ስለመፈጠሩ ምክንያታዊነት መተርጎም እንዲያስችለው ይረዳዋል። ይመራዋል። ከጎን ሊቀመጥ የሚገባው መንፈስ ከፈቀደልክለትህ የጀግናህ ሊሆን ይገባል።
የተከበሩ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የእኛ ናቸው። የነፃነት ትግሉ አካል ናቸው። የኢትዮጵያዊነት ረቂቅ መንፈስ ወስጣቸውን አብዝቶ የጎበኘው ነው። የተከበሩ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የሠራ አካላት ሴሌ ናቸው። እንጎልም። ስለሆነም ጥቃታቸው ከጎረበጠን ወለም ዘለም ቆሞ፤ ወጣ ገብ ትግል ቆሞ፤ ኢጎ ተገፍትሮ ተቀብሮ – ግልጽ የጠራ መስመርን እንድንከትል አስተምሯል። ቆሞም ይሰብከናል። አባትም ሆኖ ይመክረናል። ይህን ስንተላለፍ ዘመነ – ህግጋትን፤ መርኃ ነፃነትን፤ ጊዜ ጠገብ አደራን ተላልፈናልና እርግማን ይሆንብናል። እርግማኑ ውስጥን ማጣት ነው። ይህ ደግሞ ከንቱነት ነው።
የተከበሩ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ማናቸውም እንግልትና መከራቸው ለእኛ ከብረት የተሰራ ቁርጥራጭ ጽናትን ለእሳቸው ደግሞ ክስተታዊ (phenomenal) ሰብዕናቸውን የበለጠ ያነጠረዋል። ከመከራ በሰተጀርባ ታላቅ ክብር አለና። ለ እናት ሐገራችን ለኢትዮጵያ ክስተት (phenomenal) ናቸው።
የተከበሩ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ፍቅራቸውን ፍላጎታቸውን መውረስ ይቻላል። የሳቸውን የተከደነ ሲሳይ፤ አዳዲስ የሠላጡኑ ጸጋዎችንና ጸሐይ ያልነካቸውን ግኝቶችን፤ የተመክሮ ዝቀሽ ትጋታቸውን መተካት ግን አይቻልም። አንድ ሰው መሰሉ ምንጩ ያልተደባለቀ – ዋና (original) ብቻ ነው ያለው። ለዚህም ነው አሻራችን የተለያዬ የሚሆነው። የውስጥ ቅመማቸው ከነተፈጥሮው ከባለቤቱ ዘንድ ብቻ ነው የሚገኘው። ይህ ስምዬለሽ ህመም የሚሰማን ከሆነ ቢያንስ በእጃችን ላሉት የተገባውን ክብር ለመስጠት፤ ለመንፈሳቸው ጥበቃ ልናደርግላቸው ይገባል። ትውልዱ ሲያጣው ሳይሆን ሃብቱን በእጁ የሚገኘውን ብቃቱን በዝብዞ ለፍላጎት ተጠቃሚ መሆን ብልህንትን ማዘከር ይመስለናል። ለዚህ ደግሞ እኛ አልታደልንም። እስኪ ልብን ይስጠን። አሜን! አብሶ ለዬት ብለው የሚፈጠሩትን ለማግኘት የአንድ ትውልድ ዘመንን ይጠይቃል። ማን የቅኔው ልዑልን ሎሬት ጸጋዬ ገብረምድህንን ተከ? ማን የተከበሩ ፕሮፌስር አስራት ወልደዬስን ተካ? ማን የንጉሦች ንጉሥን ዐጼ ሚኒሊክን ተካ? በጠራ ቋንቋ ትውልድ ሊተካቸው የማይችሉ ብልህ አምድ ወይንም ምሰሶ (pillar) መሪ አጥተናል። መምራት ሥነ – ጥበብ ነው። ተሰጥዖ። እርግጥ ጥበቡ በክህሎት ሊበለጽግ ይችላል። ይህም ቢሆን በቋንቋ ዶክትሬቱን የወሰደ ሁሉ አይጽፍም። ዬሚናገር ሁሉ የሚዲያ አንባቢ ሊሆን አይችልም፤ የሚጽፍም እንዲሁ። አርቀው አስበው ሥልትን በሥልት አዋቅረው መወደድን ያህል ዲታነትን ማግኘታቸው ግን ለትውልዱ ቅምጥ ሃብት ነው። አብነት – በግንባር ሥጋነት።
ሌላው እውነት ለመናገር ጠላታችን ማን ነው? ዬጠላታችን ፍላጎታችን ለማወቅ የጠላታችን በደል ሥር አለማግኘት ነበር ማለት እችላላሁ። ዛሬስ?! የኔዎቹ የጥንካሬ ምንጩ እኛው ነን። ዓለምን የፈጠረውን ዶግማ በአግባቡ ማድመጥ ከቻልን። ምን ቀረኝ? „ስለምን እንዲህ ሆነ? ስለምን ዜናው ዘገዬ? የምንል እንኖራለንለን።“ ከእግዚአብሄር ፈቃድ ውጪ አንዲት ስንዝር መራመድ አይቻልም። ይህን የሚያውቀው ቀኑን የወሰነው ባለቤቱ ብቻ ነው። „ነገር ሁሉ ለበጎ ይሆን ዘንድ ግድ ነው“ የነፃነት ትግሉ ከእሬት በላይ መራራ ነው። መራራ የሚያደርገው ደግሞ ጦርነቱ የእርስ በርስ መሆኑ ነው። ቀለብ የሚሰፈርልት ሆድ አደረሙ በከብትንት እዬተነዳ ነው። ውስጥን የሚያነብ ዘመን አመጣሽ መሳሪያ እስኪገኝ ድረስ ከመቼውም በበለጠ ጠንቃቃነት በብልህነት፤ ሚዛናዊነት በማስተዋል ይምራን፤ ግብታዊነትን አለመረጋጋትን ሆነ አፍ እላፊን እንግታ። „ሙያ በልብ ይላል“ ጎንደሬ …. አንድ ልከል „ልብ ያለው ሸብ።“ የመከራ እንቅብ ሲሞላ ይፈሳል – ሲከርም ይበጠሳል። ቀጣዩ የወያኔ ጥቃት በዚህ መልክ አይመጣም። ዌኢ ምግብን በመበከል። ወይ የቤተሰብን ሰላም በማወክ። ወይ መኪና ኪስ ውስጥ ፈንጂ በመቅበር ሊሆን ይችላል። ግንባር ላይ የወጣችሁ ወገኖቼ „ሃበሻ ቤት ግብይታችሁን በልክ ታደርጉት ዘንድ በአጽህኖት አሳስባለሁ።
በተረፈ ሽልማቴን ግን በዬትኛውም ሁኔታ በዬትኛውም ቦታ የፈጠራቸው አምላክ ለሰጣቸው መክሊት ጥበቃ ያደርጋል ብዬ አስባለሁ። የተፈቀደ መከራ የተማሰነለት ነውና ይመቻል። አባቶቻችን ፈተና ሲጠፋ ሁለት ሦስት ሱባኤ ይዘው ፈተና ዘገይብን ብለው አምላካቸውን ይጠይቁበታል። ከምድራዊ በረከት የሰማዩ ዝልቅ መሆኑን የማመሳጠር አቅሙም ህይወቱም ስላላቸው። ለአቶ አንዳርጋቸውም ከዚህ በላይ ትርጉም የሚያስፈልገው አይመስለኝም።
አዎን! ነገ ሌላ ቀን ነው። የእኛ ሆኖ ሊመጣ ይችላል። ከዚህ ሌላ የፖለቲካ ድርጅት ሆነ ንቅናቄ የቁብ ማህበር አይደለም። ሥርዓት አለው፤ ደንብ አለው። ከደንቡና ከፕሮግራሙ የመነጨ ደግሞ የውስጥ መመሪያ አለው፤ ከሁሉም የፈለቁ የአፈጻጻም ዝርዝር መመሪያዎች አሉት። በስሜትና በግባታዊነት አንድ ሰው ብቻውን ተነስቶ የሚወስነው ምንም ነገር የለም። አንድን ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅት አጋጣሚዎች ሊመሩት አይችሉም። ለዚህም የአደረጃጃት መርሁ ዴሚክራሲያዊ ማዕከላዊነት ዶግማው ነው። የተደራጀ – ድርጅት ባልተደራጀ ሁኔታ ለምን አልተንቀሳቀሰም ተብሎ ሊኮነን ግንቦት 7 በፍጹም አይገባም። የሆኖ ሆኖ አቅም ያላቸው ወገኖች በዬትም አቅጣጫ የሚነሳውን በትእግስትና በችሎት የተገባውን ግንዛቤ በማስጨበጥ አቅምን ማሰባሰብ፤ እቅምን በእጅ ለማቆዬት መባተል ያለባቸው ይመሰለኛል። ሰው ለሰው መዳህኒቱም መፍትሄውም ነው። ሰው ሲጨምር ኃይል ይኖራል። መክሊቱም በመጠንም በአይነትም ይጨምራል። ወቅታዊው ጉዳይ የገጠመን ፈተና ባለቤትነት ሁለንትና ሁላዊነት እንዲሆን ግን የእያንዳንዱ በግል ሁሉም በጋራ መሆን እንዲችል – ማድመጥ – ማስረዳት – መንገድ ማሳዬት ይገባል።
ጌጦቼ — እልህን አርግዞ ድልን ባሰላ እናታዊ ፍቅር ልሰናበት ፈለግሁ። ነገር ግን ቀድም ብዬ በ2013 በመስከረም ጽፌ አዲስ ቦይስ አውጥቶልኝ ከነበረው ውስጥ አንዱን ላላነበባችሁት ወገኖቼ እንሆ በታላቅ ትህትና። የቃላት እርማት ጭማሬ የለበትም። ሊንኩ ከሌላ ድህረ ገጽ አግኝቸዋለሁ ማመሳከር ትችሉ ዘንድ – እሺ ውዶቼ!
ማሰብ ከመፈለግ በፊት ይቀድማል!
ማንነትን ማን ያክበረው? የሰከነ – ድርጊት!
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።