ግርማ ካሳ
በአንቀጽ 19፣ ንኡስ አንቀጽ 3፣ የአገሪቷ ሕገ መንግስት፣ ዜጎች ሲታሰሩ በ48 ሰዓት ዉስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለባቸው በግልጽ ይደነግጋል። ክሱ በግልጽ ችሎት መሰማቱን ተከሳሾች የማይፈልጉ ከሆነ፣ ወይንም በአገር ደህንነት ላይ ችግር ያመጣል ተብሎ ካልታሰበ በቀር፣ በአንቀጽ 20 ፣ ንኡስ አንቀጽ 1 እንደተቀመጠው፣ ዜጎች በግልጽ ችሎት የመሰማት መብት አላቸው።
አንቀጽ 21 ንኡስ አንቀጽ 2፣ በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ዜጎች ከትዳር ጓደኞቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው፣ ከሃይማኖት አማካሪዎቻቸው፣ ከሐኪሞቻቸው እና ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር የመገናኘትና በነርሱም የመጎብኘት መብት እንዳላቸው በግልጽ አስፍሯል።
እነ ሃብታሙ አያሌው ፣ ሐምሌ አንድ ቀን ነው የታሰሩት። ማእካላዊ እንደታሰሩ እንደታወቀ፣ ጠበቃዎቻቸው ሊጎበኗቸው ይሄዳሉ። «የፀረ ሽብር ኃላፊውን አናግሩ» የሚል ምላሽ ይሰጣቸዋል። እስረኞችን ማናገር ስላልቻሉ፣ ጠበቆቹን ፍርድ ቤት ይከሳሉ። የፌደራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት የአራዳ ምድብ ፍ/ብሔር ችሎት የጸረ-ሽብር ግብረ ኃይል ባለስልጣናት እስረኞቹን ይዘው እንዲቀርቡ፣ ሐምሌ 6 ቀን ትእዛዝ ይሰጣል። ኮማንደር ተክላይ መብራቱ በታዘዘው መሰረት ይቀርባሉ። ታሳሪዎቹን ግን ይዘው አልመጡም። ተከሳሾቹ በሰኔ 30 ቀን 2006 ዓ.ም በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በወጣ የመያዣ ትዕዛዝ፣ ሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም እንደተያዙና ሐምሌ 2 ቀን 2006 ዓ.ም ፍ/ቤት ቀርበው ቀጠሮ እንደጠየቁባቸውና በህጉ መሰረት መብታቸው ተጠብቆ እንዳለ ይናገራሉ። ማስረጃ አምጡ ተብለው በተጠየቁት መሰረት፣ በነጋታው የጽሁፍ ማስረጃ ያቀርባሉ። ፍርድ ቤቱም የእስረኞች ጠበቆችን ክስ ፋይል ይዘጋል። ኮማንደር ተክላይ፣ እስረኞቹ በ48 ሰዓት ዉስጥ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ያሳይል ያሉትን የወረቀት ማስረጃ ቢያቀርቡም፣ እስረኞችን ያያቸው ማንም ሰው የለም። ይኸው ሐምሌ 15 ደርሰናል። ጠበቆች፣ ቤተሰብ፣ መንፈሳዊ አባቶች …አንዳቸውም እስረኞችን እስከ አሁን ማየት አልቻሉም። እስረኞቹ ምንም አይነት ሁኔታ ላይ እንዳሉ አይታወቀም።
በእስረኞች ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ከመድረሱ የተነሳ፣ ሰው እንዳያያቸው ሆን ተብሎ በሚስጥርና በጨለማ ፍርድ ቤት ቀርበው፣ እንደ ተለመደው የ28 ቀን ቀጠሮ ተሰጥቶ ሊሆን ይችላል። አሊያም ኮማንደር ተክላይ አንዱን ካድሬ ዳኛ ፣ እስረኞቹ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ፣ ፎርጅድ ወረቀት እንዲጽፍ አስደርገዉትም ይሆናል የሚል ግምትም አለኝ።
በዚህም ሆነ በዚያ፣ አንድ ነገር በጣም ግልጽ የሆነ ነገር አለ። እርሱም ኢሕአዴግ ሕገ መንግስቱን በአፍጢሙ እንደደፋው ነው። ፍርድ ቤት መቀለጃ ሆኗል። «የሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ በመሞከር» እያሉ ሌሎችን ይከሳሉ። ግን ሕግ መንግስቱን እየናዱ ያሉት እነርሱ እራሳቸው ሆነዋል። ሌላዉን ሽብርተኛ እያሉ ይከሳሉ። ሕዝቡን እያሸበሩ ያሉት ግን እነርሱ ናቸው።
ይህ በአገዛዙ የምናየው፣ አይን ያወጣለት የሕግ ጥሰትና መንግስታዊ ዉንብድና ፣ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ኢሰብአዊ ግፍና ንቀት የኢሕአዴግ ስርዓት ፍጻሜ መጀመሪያ ነው።
አንድ መርሳት የሌለብን ነገር አለ። ይሄን ሁሉ የሚያደርጉት ፈርተን፣ ባርነትን አሜን ብለን ተቀብለን፣ ተስፋ ቆርጠን እንድንቀመጥ ነው። «እነ ሃብታሙን ያየህ ፣ ተማር። አርፈህ ቁጭ በል» የሚል መልእክትን ለማስተላለፍ ነው። ነገር ግን አይሰራም። የአሁኑ ትዉልድ በሌሎች አገሮች ስላለው ነጻነት ያነባል፤ ያዳምጣል፤ ያውቃል። በምንም መልኩ ነጻነቱንና መብቱን ተገፎ መኖር የሚፈልግ ትዉልድ አይደለም። ለዚህም ነው፣ ትላንት እነ እስክንደር ነጋ ቢታሰሩም ከሁሉም አቅጣጫ እሳት የላሱ ደፋር ጋዜጠኞችና ብሎገሮች ብቅ፣ ብቅ ያሉት። እንደገና ደግሞ አሁንም ጋዜጠኞችና ብሎገሮችን አሰሩ። ነገ ደግሞ ሌሎች ሁለት እጥፍ ወጥተው የነ እስክንደርን ፣ የዞን ዘጠኞችን ድምጽ ማስተጋባት ይቀጥላሉ።
ትላንት እነ አንዱዋለም አራጌ ቢታሰሩም፣ እሳት የለበሱ፣ እንደ አብርሃ ደስታ፣ ሃብታሙ አያሌው ያሉ ሰላማዊ ወጣት ፖለቲከኞች ብቅ ብለዋል። የማይፈሩ፣ ብስለት ያላቸው፣ የሰላማዊ ትግል አርበኞች !!! እንደገና አገዛዙ እነ ሃብታሙን አሰረ። ሰው ግን አይደናገጥም። ብዙዎች ሰላማዊ ትግሉን ይቀላቀላሉ። እነ ሃብታሙ ዳግማዊ አንዱዋለም ነበሩ። አሁን ደግሞ ዳግማዊ አብርሃዎች፣ ዳግማዊ የሺዋሶች፣ ዳግማዊ ሃብታሙዎች ፣ ዳግማዊ ዳንኤሎች፣ ዳግማዊ ወይንሸቶች ይወጣሉ። በምንም መልኩ አገዛዙ ለዲሞክራሲና ለነጻነት የሚሰማዉን ጩኸት ዝም ማሰኘት አይችልም። በምንም መልኩ ጥቂቶች የሚሊዮኖች ድምጽ ማፈን አይችሉም።
ጨዉ ለራስህ ስትል ጣፍጥ እንደሚባለው፣ ኢሕአዴጎች ለራሳቸው ሲሉ የሚበጀዉን በቶሎ ያደርጉ ዘንድ አስጠነቅቃለሁ። አለበለዚያ ግን አወዳደቃቸው እጅግ በጣም የከፋ ነው የሚሆነው። ከሚሊዮኖች ጋር ተጣልተው የትም አይደርሱምና።