Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

“በእኔ ስም አይሆነም!”ክፍል ሦስት (በልጅግ ዓሊ)

$
0
0

ብረሥላሴ ደስታ ( ካርሜሎ ክሪሼንቲ) የሚባል ጣላኒያዊ የሃገራችን ወዳጅ ወደ ደብረ ሊባኖስ ተጉዞ የጀግናውን የአበበ አረጋይን መቃብር ተመልክቶ የተሰማውን ሃዘን እንዲህ ብሎ አጫወተኝ።

 

gth“ስለ አበበ አረጋዊ ጀግንነት የሰማሁት ከአንድ በጦርነቱ ከነበረ ኢጣልያዊ  ሽማግሌ ነበር። ወደ ኢትዮጵያ ስጓዝ ለእኚህ ጀግና ለማስታወስ  የተሠሩ  ብዙ ሐውልቶች፣ ብዙ ሙዚየሞች እንደሚገጥመኝ ገምቼ ነበር።  ነገር ግን የገጠመኝ የእኚህ የጀግናችን መቃብር ደብረሊባኖስ ውስጥ ዳዋ በልቶት የሚንከባከበው አጥቶ ነው። በጣም አዘንኩ። በአካባቢው ያገኙትን በመጠቀም ለማጽዳት ሞከርኩ። ከተሳካልኝ በሕይወቴ ውስጥ የአበበ አረጋይን መቃብር በተሻለ ሁኔታና ከጎኑም ሰፋ ያለ ሙዚየም ባሠራ ደስ ይለኛል።”

 

ገብረሥላሴ(ካርሜሎ) እስከ አሁን ድረስ በልቡ ዕረፍት አላገኘም። ቀን ሲሞላለት ለእኚህ ጀግና ብዙ ማድረግ አስቧል። አዎ ዛሬ ብዙዎቻችን ላለፈ ታሪካችን አንጨነቅም። አዎ ብዙዎቻችን አዲስ በወያኔ በተፈጠረው የዘር ፓለቲካ አማካኝነት ሁሉን ነገር ከዘር አንጻር እንመለከተው ይሆናል። ዛሬ በፋሽሽት ኢጣሊያ ስለተጨፈጨፉት ዜጎቻችን መስማት ያዳግተን ይሆናል። ግን ደግሞ ቴዲ አፍሮ በዘፈኑ እንደገለጸው “የኋላው  ከሌለ የለም የፊቱ” ነውና፣ ወደድንም ጠላንም ለዛሬ ማንነታችን የፊቱ ታሪካችን ነጸብራቅ ነው። ብንክደውም ጥላችን ሆኖ ይከታተለናል።

 

ታሪካችን ለማጉደፍ፣ መስዋቱንም ለማዋረድ የሚደረገውን ጥረት ዛሬም በሰፊው እንደቀጠለ ነው። ይህንን ደባ ቆርጠን መታገል ይኖርብናል።  ዜጎቻችንን የጨፈጨፉ እነ ግራዚያኒ እንደ ጀግና ሲቆጠሩና ሃውልት ሲገነባላቸው ይህንን መቃወም ወደ ኋላ የማንልበት ተግባራችን መሆን አለበት።  ይህ በተለይ በፋሽሽት ኢጣሊያን የተሠራውን ግፍ ማጋለጥ  የዓለም አቀፍ ትብብር ለፍትህ(GLOBAL ALLIANCE FOR JUSTICE:  THE ETHIOPIAN CAUSE) http://www.globalallianceforethiopia.org  ብቻ የሚመስላቸው ትንሽ አይደሉም። አንዳንድ ድረ ገጾች ይህንን ከላይ የጠቀስኩትን ድርጅት የሚያወጣውን መግለጫ አልፈውም ስለ ፋሽሽት ኢጣሊያ፣ ስለ ቫቲካን ፋሽሽቶችን መተባበር የሚገልጽ ጽሁፍ በድረ ገጻቸው ልዩ ልዩ ምክንያት በመስጠት ላለማውጣት የወሰኑ አሉ። ይህ የሚያሳዝን ነው።  ቫቲካን ከፋሽሽት ወረራ ጊዜ ከሞሶሎኒ ማበርዋ የአደባባይ ምሥጢር ነው።  ስለ ቫቲካን ከፋሽስቶች ትብብር ለማወቅ ለምትፈልጉ ከላይ የጠቀስኩትን ድረ ገጽ ብትጎበኙ ጠቃሚ ነው።

 

የኢትዮጵያን አንድነት የሚቃወሙ ሁሉ የዳግማዊ ምንሊክን ሃውልት ለማፈረስ የሚያደርጉት ጥረት ጥንትም ይሁን አሁን እንደቀጠለ ነው። በፋሽሽት ወረራ ወቅት የቅኝ ግዛት ሚኒስተር የነበረው ሌሶና(Lessona) በሌሊት የዳግማዊ ምንሊክን ሐውልት ከቦታው አንስቶት እንደነበር የሚታወስ ነው። ይህ ግለሰብ ወደ አዲስ አበባ በባቡር ሲጓዝ በደጃዝማች ፍቅረ ማርያም ሥር የነበሩ አርበኞች አደጋ ጥለውበት ነበር። ይህ በጎን የምታዩት ፎቶ ይህንን የሚሳይ ሲሆን ኢያን ካምፕቤል(IAN CAMPBELL) የሚባል ጸሐፊ (The plot to kill Graziani – ገጽ 100) ከሚለው መጽሐፉ ላይ በሰፊው አትቶታል።

 

ዛሬም ቢሆን ይህንን የፋሽስቶች ዓላማ ተቀብለው ምንሊክን የሚቃወሙ ከሃውልቱ ጋር የሚጣሉ በየቦታው እናገኛለን። በእውን በምንሊክ ዘመን በደረሰባቸው ግፍ ከሆነ ሁኔታው በዛ ዘመን ካለው የዓለም ሥልጣኔ አንጻር ልንመለከተውና እውነተኛውን ሁኔታ ለታሪክ ማስቀመጥ ይኖርብን ይሆናል። ነገር ግን ብዙዎቹ በምንሊክ ዘመን ለደረሰባቸው ጭቆና ሳይሆን የኢትዮጵያን አንድነት ለማፍረስ ካላቸው ፍላጎት ወይም ለወቅታዊ ሥልጣን ቃረማ ምንሊክን ሲያወግዙ ይታያሉ። ጣሊያኖች በአደዋ ጦርነት ወቅት በደረሰባቸው ውርደት ምከንያት  ምንሊክን ቢጠሉ የሚገርም አይሆንም። የዘንድሮ የሃገራችን ዘረኞችም የምንሊክን የአደዋ ድል ያነሳ ሁሉ ጠላታችን ነው በማለት የሚያደርጉት ቅስቀሳ ለምን እንደሆነ የረባ ትንታኔ ሲሰጡ አይሰሙም።

በክፍል አንድና ሁለት እንደገለጽኩት በሃገራችን ያን ሁሉ ጭፍጨፋ ያካሄደው ፋሽሽቱ ግራዚያኒን ለማስታወስ በአሁኑ ወቅት አፊሌ ከተማ ውስጥ የተጀመረው ሃውልት የማነፅ እንቅስቃሴ መቃወም የሁላችንንም ትብብር ይጠይቃል። በክፍል አንድና ሁለት በአፊሌ የተሠራውን ሃውልት በሚመለከት የተነሳው ተቃውሞ ጁላይ 28 ላይ አፊሌ ከተማ ውስጥ የተሳካ ሰልፍ ተደርጓል። በአካባቢው የሚገኙ አምስት ከንቲባዎች የኢጣሊያንን ባንዲራ በማሸረጥ በቦታው ተገኝተው ተቃውሟቸውን አሰምተው ነበር። የፋሽሽቱ ግራዚያኒ ደጋፊ የሆነው የአፊሌ ከተማ ከንቲባ ይህ በግራዚያኒ ላይ የተነሳውን ተቃዉሞ በመቃወም “እዚህ የምትገኙት በሙሉ የአፊሌ ከተማ ነዋሪዎች አይደላችሁም“ በማለት ላቀረበው ተቃውሞ በሰልፉ ላይ የነበረ የአፊሌ ነዋሪ የሆነ ግለሰብ “የአፊሌ ሕዝብ ከንቲባውን ፈርቶ እንደቀረ አስረድቷል“። በሰልፉ ላይ የዜጎቻችን ተሳትፎ የጎላ አልነበረም።

 

በዚህ የግራዚያኒን ሐውልት በመቃወም ተግባር ላይ በተለይ በኢጣሊያን የሚገኙ ዜጎቻችን ተሳትፏቸው የጎላ መሆን ቢገባውም በጣሊያን የዜጎቻችንን ኑሮ በኢጣሊያን የሚያፈናፍን ሆኖ አላገኘሁትም። ከኑሮ ትግል አልፈው ይህንን ዓይነት ትግል ለማካሄድ በጣም አስቸጋሪ ነው። እስቲ ስለኑሯቸው በጥቂቱ።

 

 

ክፍል አራት

የዜጎቻችን ኑሮ በሮማ

 

ጣሊያን ዋና ከተማ ሮማ  የዜጎቻችን ቁጥር ከመቼውም ባለይ  በዚህ ዓመት ከፍ ብሏል ። በሊቢያ የመንግሥት አለመኖር በፈጠረው ሁኔታ ምክንያት ከሰሃራ በርሃ የሚፈልሰው ወጣት ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል። የሰሃራ በረሃ ጉዞም ከዛም በሊቢያም ባህሩን አቋርጠው አውሮፓ እስኪደርሱ ያለው ጉዞ ከበፊቱ የበለጠ አደገኛ ሆኗል። በሶርያ የተፈጠረው የእርስ በእርስ ጦርነትም የልዩ ልዩ ዐረብ ሃገር ዜጎች ወደ አውሮፓ በሶርያውያን ስም ለመፍለስ ምክንያት ሆኗል። ይህ ጉዞ በሁለት ግንባር የሚካሔድ ነው። አንዱ ግንባር ከቱኒዚያ ሲሆን ፣ ሌላው ደግሞ ከሊቢያ ነው።

 

በሊቢያ ጋዳፊን በመቃወም የተነሳው የእርስ በእርስ ብጥብጥ ሊቢያ ውስጥ ሆነው ይጠብቁ የነበሩ ስደተኞችን ስቃይ ውስጥ ከቶ ነበር። እነዚህ ስደተኞች ጦርነቱን በመፍራት ወደ ቱኒዚያ ሸሽተው በሊቢያና በቱኒዚያ ድንበር አጠገብ በሚገኝ ራስ አጂዲር( Ras Ajdir) በሚባል ቦታ  ሾሴ መጠለያ ጣቢያ የነበሩ ብዙ ወገኖቻችንን ነበሩ። ቱኒዚያ ውስጥ በዜጎቻችን ላይ የሚደርሰውና በዓይኔ የተመለከትኩትን ስቃይ ለመግለጽ አዳጋች ነው። ሌሎች ሃገሮች  ዜጎቻችውን ሲወስዱ አፍሪካውያን እዛ በርሃ ውስጥ ነበር የቀሩት። ከእነዚህ ስደተኞች ውስጥ አንዳንዶቹ ተሳክቶላቸው ወደ ምዕራብ ሃገሮች ጥገኝነት ቢያገኙም ብዙዎቹ ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ክፍል ካለ አንዳች እርዳት በርሃ ውስጥ በትኗቸዋል። እነዚህ ዜጎቻችን ከቱኒዝ እንደገና ወደ ሊቢያ ተመልሰው አሳቃቂውን ጉዞ ለማድረግ ተገደዋል። በዚህ ጉዞ ብዙዎቹ ሕይወታቸው አልፎል።

 

 

አሁን ደግሞ እነዚሁን ወገኖቻችንን ከቱኒዚያ ወጥተው ወደ ሊቢያ ተመልሰው፣ አሰቃቂውን የባሕር ጉዞ አድርገው ሮም ደርሰው አግኝቻቸዋለሁ። ምንም እንኳን አውሮፓ መድረሳቸው የሚያስደስት ቢሆንም ኢጣሊያ ሮም የተሻለ ኑሮ ገጥሟቸዋል ማለት አይቻልም።  ከላምፓዱዛና ከሌሎቹ ደሴቶች ሕይወታቸው ተርፎ ጉዞአቸውን ወደ ሮም ያደረጉት ስደተኞች የሚገኙበት ሁኔታ ስመለከት የዜጎቻችን ስቃይ አውሮፓ ስለደረሱ ብቻ እንደማይቀረፍ ጎልቶ ይታያል። (ፎቶው አዲስ የመጡት ስደተኞች መተኛ አጥተው በየቦታው ተኝተው የሚያሳይ ነው።)

 

ከሊቢያ የመጡትን ስደተኞችና ስለሮማ  ስደተኞች ለመነጋገር ከተፈለገ ሦስት ቃላቶችን አንባቢያን ከአማርኛ መዘገበ ቃላት ውስጥ እንድትከቱልኝ እጠይቃለሁ።

1ኛ ፊሽ – - – ፊሽ ማለት በስደተኛው የአማርኛ አጠቃቀም ውስጥ ዐሻራ ማለት ነው።(ፊሽ አለብህ ወይ? ፣ ፊሽ ተደርግሃል ወይ ? ማለት ዐሻራ ተወስዶብሃል ወይ ? ዐሻራህን አንስተውታል ወይ ማለት ነው ። ቃሉ ከየት እንደመጣ ጠይቄ መረዳት አልቻልኩም። ዐሻራ የሚለው ቃል በማርጀት ፊሽ የሚለው በወጣቱ አካባቢ ተጠቃሚነቱ በዝቷል።

2ኛ ቤት ሰበራ – - -  ማለት የግል ወይም የመንግሥትን ቤት በጉልበት ፤ በሕዝብ ብዛት መውረር ማለት ነው። ( የቤት ችግር እዚህ ሮም ውስጥ ስላለ መክፈል የማይችሉ የብዙ ሃገር ዜጎች (ጣሊያኖችም ጭምር ) ባዶ ሆኖ የተዘጋ የመንግሥት ወይም የግል ቤትን በመውረር በሩን ሰብረው ገብቶ መውረርን የችግር መፍቻ ካደርጉ ሰንብተዋል።

3ኛ መጠረዝ – - -  ታስሮ ወደ መጡበት ቦታ መመለስ ( ለምሳሌ ወደ ጣሊያን ተጠረዘ – - – ወደ ጣሊያን እንዲመለስ ተደረገ።)

 

እነዚህ ሦስት ትርጉሞች ማወቅ ለዜጎቻችንን የሮማ ኑሮ አስፈላጊ ነው።  ሦስቱም ከስደተኞች በተለይ በቅርብ ከመጡት ጋር የተዋሃዱ ናቸው።

 

ባሕሩን አቋርጠው ወደ አውሮፓ የደረሱ ስደተኞች ፊሽ (ዐሻራ) ይነሳሉ። ይህ ፊሽ ሌላ የአውሮፓ ሃገር ቢሄዱ ከየት እንደመጡ ለማወቅ ይረዳል። የሌላ ሃገር ፊሽ የተገኘበት ሰው ፊሽ ወደሰጠበት ሀገር ይጠረዛል።  በአውሮፓውያን ሕግ ስደተኞቹ መጀመሪያ የደረሱበት የአውሮፓ ሃገር ነው ስደተኛነት መጠየቅ የሚቻለው። አንድ የአውሮፓ ሃገር ስደተኝነት የጠየቀ ግለሰብ ሌላ ሃገር ቢጠይቅ እንኳን ተቀባይነት ለማግኘት አይችልም። ሌሎች ምክንያቶች እስከሌሉ ድረስ።

 

ፊሽ የሌለበት ስደተኛ በጣም እድለኛ ነው። ሌላ አውሮፓ ሃገር ጥገኝነት መጠየቅ ይችላል። ይህ ግን ደግሞ ቀላል አይደለም ። መጀመሪያ ከጣሊያን ወጥቶ ሌላው ሃገር መድረስ አለበት። የሌላው ሃገር ጉዞ እስከሚሳካ እስከዚያ ጣሊያን ውስጥ መቆየት አለበት። ጥያቄው የት ነው የሚቆየው? ነው። ዘመድ ያለው ከዘመድ ተጠግቶ ይኖራል። የሌለው ግን መወደቂያ የለውም። ሮማ ውስጥ ግን የተሰበሩ ቤቶች ስላሉ እዚያ አካባቢ ሄዶ ጊዜያዊ መጠለያ ያገኛል።

 

 

በአሁን ጊዜ በጣሊያን ውስጥ በተለይ በሮማ ቤት መስበር በሰፊው በመካሄድ ላይ ነው። እንቅስቃሴውን የሚካሄደው በዓላማቸው ሕዝብ መኖሪያ አጥቶ ሕንጻዎች ክፍት ሆነው መቀመጣቸውን የሚቃወሙ ቡድኖች ናቸው። የቡድኑ አባሎች የግድ የቤት ችግር ላይኖርባቸው ይችላል። ግን ይህንን እንቅስቃሴ ይመራሉ። ይህ የሚደረገው በሚስጥር ነው። አንድ ቤት ባዶ መሆኑ ከታወቀ ይህንን የሚያቀነባብሩት የኮሚቴ አባላት ይወስኑና ችግር ያለባቸውንም ይሁን በተወረረው ቤት የሚኖሩትን በድብቅ ምስጢራዊ በሆነ መንገድ አዲስ በሚወረረው ሕንጻ አካባቢ እንዲሰበሰቡ ይጠራሉ። ከዛም አዲሱን ሕንጻ ሰብረው ቤቱን ገብተው ይወራሉ። በዚህ ሰዓት ቁጥሩ ብዙ የሆነ ሰው በመሰብስቡ ምክንያት ጠባቂዎችም ሆነ ፖሊስ ኃይል አይኖረውም። ሕጻን፣ ወጣት፣ አሮጊት ወይም ሽማግሌ ልዩነት ሳይኖረው በዚህ ወረራ ላይ ይሳተፋሉ። ከዚያም ያንን ቤት ተከፋፍለው ይይዛሉ። ነገሩ ረጋ ሲል ከሌሎች ከተወረሩ ቤቶች ለእርዳታ የመጡት ይመለሱና አዲሶቹ ተከፋፍለው ቤቱን ይይዛሉ። መንግሥት ዓመጹን በመፍራት ችግሩን ያበርዳል።

 

ሮም ውስጥ የተሰበሩ ቤቶች በብዛት ቢገኙም፣ ሙሉ በሙሉ በዜጎቻችንን ቁጥጥር ሥር ያሉ  ሁለት ሕንጻዎች አሉ። አንደኛው ኮለንቲና ሲባል ሁለተኛው አነኒና ይባላል። ሁለቱም ሕንጻዎች የአውሮፓም ሆነ የኢጣሊያን ሕግ አያስተዳድራቸውም። በተቋቋመ ኮሚቴ ነው የሚተዳደሩት። ሕንጻዎቹ ከውጭ ሲመለከቷቸው ውብ ናቸው። ውስጥ ግብቶ ማየት የሚያሰቅቅ ነው።

 

 

እነዚህ ሁለት ሕንጻዎች ሌሎች ከተሰበሩ ቤቶች ለየት የሚያደርጋቸው ከአስተባባሪው ኮሚቴ ነጻ ወጥተው ራሳቸውን በማስተዳደራቸው ነው። ይህ ማለት አስተባባሪው ኮሚቴ ለሌሎች ቤቶች ሰበራም ሆነ ለተቃውሞ ሰልፍ የእነዚህ የሁለቱን ነዋሪዎችን አይጠራቸውም፣ አያስገድዳቸውም። ይህ ማለት በቤት ሰበራ ኮሚቴ የሚተዳደሩት ሕንጻዎች ውስጥ የሚኖሩ ስደተኞች እልክ አስጨራሽ የሆነ ትግል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። እነዚህ የኮሚቴ አባላት የሰዎችን መብት መከበር ዋና አላማቸው ስለሆነ በሚያደርጉት ትግል ላይ መሳተፍ ግዴታ ነው ። የእኔ ችግር ተፈትቷል ብሎ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ አይፈቀድም። የተደጋገመ ሰልፍ ላይ መገኘት ግዴታ ነው። ይህ ለዜጎቻችን ደግሞ የማይዋጥ ነው ። የእራስ ችግር ከተፈታ በኋላ ለሌሎች ችግር መታገል ደግሞ አለመደብንም። ስለዚህ ከዚህ የጋራ ትግል ወጥተው ብቻቸውን መኖር አማራጭ በመሆኑ ኮሚቴዎችን በማባረር ራሳቸውን ማስተዳደርን መርጠዋል። ከዚያም በተረፈ የሕንጻውን ሁኔታ በሚመለከት ራሳቸው ነዋሪዎቹ የመደራደር መብት አላቸው።

ኮለቲናና አነኒና በአሁኑ ወቅት በሰሃራ አድርገው፣ ያንን  ስቃይ የበዛበትን፣ ሞት የረከሰበት ጉዞ አጠናቀው ጣሊያን የደረሱትን ዜጎቻችንን በመቀበልና ማረፊያ በመሆን ይህ ነው የማይባል ትልቅ እርዳታ እያደረጉ ነው። እነዚህ ሕንጻዎች በአውሮፓ ደረጃ መፍረስ የሚገባቸው ቢሆኑንም በውስጡ ግን ብዙ ተዓምሮችን ለማየት ይቻላል። መጀመሪያ ሕንጻዎቹን የወረሩት ዛሬ በብዛት በዚህ ሕንጻ ውስጥ አይኖሩም። የያዙትን ክፍል ‚ ሸጠው ሄደዋል። የተሸጠለትም ደግሞ ከፋፍሎ አከራይቶታል። ክፍል ለመግዘት እስከ አስር ሽህ ኢሮ ሲደርስ፣ ለመከራየት ደግሞ በወር እስከ 200 ኢሮ  ይሆናል። ይህ መክፈል የማይችል አዲስ መጤ ደግሞ ከፎቁ ሥር ካለው የመኪና ማቆሚያ ፍራሽና ብርድልብስ ለምኖ ይተኛል። ይህንን ማመን ያዳግት ይሆናል። ግን ሐቅ ነው። መንገዱ ተሳክቶለት ወደ ሌላ የአውሮፓ ሃገር እስከሚሄድ በብርድ እየተጠበሰ ይቀመጣል። ምግብ ደግሞ እየተለመነ ይኖራል። በዚህ ቦታ የምንታዘበው ብዙ አሳፋሪ ተግባሮች አሉ። ቁማር፣ ስካር፣ ድብድብ የየዕለቱ ተግባሮች ናቸው።

 

ከኢጣሊያን ወደ ሌሎች ሃገሮችም ሆነ ፣ ከኢጣሊያን ሌሎች ቦታዎች ወደ ሮማ መሻጋጋሪያው በባቡር ነው የሚሆነው። ይህንን ጉዞ የሚቀነባብሩም ደላላዎች ባቡር ጣቢያ  አይጠፉም። ባቡር ጣቢያው ተርሚኒ ይባላል። እስቲ ትንሽ ስለ ተርሚኒ።

 

 

 

ክፍል አምስት

 

ተርሚኒ

 

ጣሊያ- ሮማ  ለመጎብኘትም ሆነ ጥገኝነት ለመጠየቅ የመጣ ዜጋችን ወደ ባቡር ጣቢው ጎራ ማለቱ አይቀርም። ባቡር ጣቢያው ተርሚኒ ይባላል። ቦታው ለሚዝናና ወይም ሰው ለሚጠብቅ በሚስማማ ሁኔታ የተሠራ ነው። ከትልቁ አዳራሽ ውስጥ አንድ ፎቅ ነገር አለ። እዛ ላይ ደግሞ አንድ ቡና ቤት ። ይህ ቡና ቤት ቻዎ ይባላል። ቀጠሮም ያለው ይሁን የሌለው እዛ ቡና ቤት ተቀምጦ ወደ ታች ገቢው እና ወጭውን ያነጣጥራል። ቻዎ ቡና ቤት ሁሉንም ለመቆጣጠር የሚያመች ገዢ ምድር ነው። ቡናውም ጥሩ ነው። አካባቢውም ያመቻል። የጠፋብዎትን ዜጋችንን ሁለት ቀን ከተመላለሱ ሊያገኙት  ይችላሉ። ቻዎ እንገናኝ የሮም የቀጠሮ ቦታ ነው።

 

አዲስ አባባል  – - -  ጣሊያን ውስጥ አንድ የአማርኛ አጠቃቀም አለ። በኋላ እንሰማማ የሚል ነው። ይህ ማለት በኋላ እንድዋወል፣እስከ በኋላ  ማለት ነው። ብዙ ጊዜ በስልክም ሆነ በአካል ሰዎች ሲሰነባበቱ ይህንን አባባል ይጠቀማሉ። በኋላ እንሰማማ ። በሌሎች የአውሮፓ ሃገሮች ያልሰማሁት አጠቃቀም ነው። ይህ አባባል ከኢጣልኛው (ci sentiamo dopo) ከሚለው አነጋገር የመጣ ነው እንደሆነ ተረድቻለሁ።

 

ሮምን የጎበኘ ዜጋችን ተርሚኒ ባቡር ጣቢያ ከሚገኘው ቻዎ ቡና ቤት ፎቁ ላይ ቁጭ ብሎ ጣፋጭ የጣሊያን ቡናውን እየጠጣ ወደ ታች ቁልቁል የሚተራመሰውን ሕዝብ እየተመለከተ ከጎን፣ ከጀርባ፣ ካጠገብ የሚሰማውን የተለያየ  ቋንቋ እየሰማ መደሰት የተለመደ ነው። ተርሚኒ ቻዎ ቡና ቤት ሮምን ለቀው ከወጡ በኋላም ቢሆን የማይለቅ ትዝታ አለው።

 

አዎ ቻዎ ልዩ ትዝታ አላት። የቆየ ዘናጭ፣ አዲስ የመጣ እንግዳ፣ የሲኞራ ቤት ሥራ ያደከማት ዜጋችን፣ ኪሱ ሳንቲም የሌለው ቀፋይ፣ ፓለቲከኛው፣ ጸረ ፓለቲካው፣ የቸኮለ ሠራተኛ፣ ሥራ አጥ፣ ሥራ ፈላጊ፣ ከሥራ እረፍት አግኝቶ መዝናናት የፈለገ፣ የተቀጣጠረ፣ ያልተቀጣጠረ፣ ሚስቱ ሠርታ የምታስተዳድረው ጎረምሳ፣ ሥራ ያደከመው፣ ከዛም አልፎ ተርፎ ከኤርትራ ማሰልጠኛ ጣቢያ ከሰዋ አምልጦ የመጣ አዲስ ባለሸበጥ ጫማ ጎረምሳ  . . .  ወዘተ ይሰበሰቡባታል።  ሁላችንም ከፎቁ ተደርድረን ከስር የምታልፈውን ዜጋችን ከዓይናችን እስከምትጠፋ የምንገላምጥበት ምርጥ ቦታ ነው። ቻዎ ቆይቶ የተገናኘ የሞቀ ሰላምታ፣ የደረት ለደረት ድለቃ የጎላበት፣ እንስት መተዋወቅ የፈለገም ሆነ ብቸኝነት ያጠቃትም ዜጋችንም ዘንጣ የምትታይበት ምርጥ ቦታ ነው። ቻዎ ከባዱ ቡና እስፕሬሶ የከበደን፣ ካፌ ሉንጎ አሜሩካኖ የምናዝበት፣ ጣፈጭ ኬክ (ኮርኔንቶ) በቡና ይዘን የምንዝናናበት ነው። ቻዎ ቡና ቤት የማይረሳ ትዝታ አለው።

 

ቀን ሞልቶ እስኪጻፍ ይደር እንጂ ቻዎና ደላላዎቻም ብዙ ታሪክ አላቸው። ለታዘበ ማን ምን እንደሆነ ቻዎ ለሳምንት ከተመላለሰ ይገለጽለታል። ቻዎና ደላሎቿ ብዙ ታዕምሮችን የሚፈጽሙበት ቦታ ነው። እዚሁ ተርሚኒ ቻዎ ቡና ቤት ተቀምጠው አዲስ የመጡትና የቆዩትን ዜጎቻችንን መለየት ይቻላል። በአለባበስ ፣ በአካሄድ ፣ ባነጋገር . . . ። በተለይ በሴቶች እህቶቻችንና በወንድሞቻችን መካከል ልዩነቱ የጎላ ነው። ብዙዎቹ እህቶቻችን ሰው ቤት ተቀጥረው የሚሠሩ በመሆናቸው ምክንያት ያችን በሳምንት አንድ ቀን የሆነች ዕረፍታቸውን በጸጉር ቤት፣ በሱቅ መዞር፣ ወዳጅን ማግኘት፣ ለዘመድ አዝማድ መደወል . . .  ለማብቃቃት ሲራወጡ ይታያሉ። ወንዶችም እንደ እህቶቸችን ባይሆንም ትንሽ ጥድፊያ አለባቸው። ግን በዛው ደግሞ ለብሶ፣ አማምሮ ቻዎ ቡና ቤት ውስጥ ቡናውን ሲጠጣ፣ አላፊ አግዳሚውን በዓይኑ ሲሸኝ የሚውል ደግሞ ትንሽ አይደለም። ይህንን ሽሙንሙን ጠጋ ብለው ቢጠይቁት ሚስቱ ሲኞራ ጋ የምትሰራ ሆና በሳምንት አንድ ቀን ወይም በየቀኑ ማታ ማታ የምትመጣ እንደሆነች ይነግርዎታል። የሚኖሩት በተሰበረ ቤት ውስጥ እንደሆነም አይደብቅዎትም። ዋናው የእሱ ስራ ቤቱ ለመስበር የተባበሩት ኮሚቴዎች በሚያዙትን ሰልፍ ላይ ቤተሰቡን ወክሎ መገኘት ብቻ እንደሆነ ይነግሮታል።

 

አዲስ መጤዎችንና የቆዩትን ለማወቅ በንግግር ለማወቅ ከፈለጉ ደግሞ ከባድ አይደለም። የቆዩት እንደ ጣሊያኖቹ እጃቸውን ሲወናጭፉ ያገኙቸዋል። አዳዲሶቹ ግን በዚህ ግርግር በባዛበት ትልቅ ከተማ ውስጥ፣ ነገ ምን እንደሚጠብቃቸው፣ ስለማያውቁ በጭንቀት ያዩት ሰው ሁሉ የሚያውቃቸው እየመሰላቸው ዓይናቸው ሲቅበዠበዥ ያገኙአቸዋል።

 

ሮማ በነበርኩበት ወቅት ተርሚኒ ቻዎ ጎራ ሳልል አላልፍም። ብዙ ጊዜ እዛ ቡና ቤት የሚደበሩ ዜጎቻችንን ተመሳሳይነት አላቸው። በተለይ አንድ ሁል ጊዜ የማላጣት አስቂኝ ዜጋችን ምን ጊዜም የማልረሳት ነች። ቻዎና ደላላዎቻ ጋር ትጠቃለላለች።

 

ይህቺ አስቂኝ ፍጡር ራሷ ላይ ያደረገችው ሰው ሰራሽ ጸጉር (ዊግ) እድሜዋን ከሚያሳብቀው ፊቷ ጋር ቅራኔ ውስጥ ገብቶ ጦርነት የገጠመ ይመስላል። የምታደርጋቸው ልብሶች  አሁንም ለእሷነቷ ማንነት የማይመጠን ነው። ከንፈሯ ላይ ያለው የከንፈር ቀለም ጀማሪ ቀለም ቀቢ የተማረበት ይመስላል። ጣትዎ ላይ የሳካችው ሰው ሰራሽ ጥፍር ከማማር አልፎ የቡቱ ቡቱቱን ጥፍር መስሏል። አብራቸው የምትቀመጠው ልጆችም ቢሆኑ ጫጩቷን ታቅፋ የተቀመጠች እናት ዶሮ ያስመስሏታል። የቆየች መሆኗን ግልጽ ነው። አዲስ በመጡትና ጣሊያንኛ በማይችሉ ዜጎቻቸን ላይ የጣሊያን ቃላት በመጠቀም ግራ ስታጋባቸው መታዘብ በቀላሉ ይቻላል።

 

አጠገብዋ የሚኮለኮሉት ወጣቶች ሁልጊዜ ይቀያየራሉ። ዛሬ ያሉት ከትንሽ ቀናት የሉም። እነርሱ ሲሄዱ ሌሎች ይመጣሉ። ወጣት ሴቶች ወጣት ወንዶች ይከቧታል። በጣም ቁልፍ አስፈላጊ ሰው እንደሆነች ሁኔታው የተከታተለ አያጣውም። ምኞቴ ምን እንደምታወራቸው መስማት ነበር። አንድ ሁለቴ ጠጋ ብል ንግግሯን አቋመች። የጋሜ( የደላላ) ጠባይ ስላየሁባት ፍላጎቴ ጨመረ። አንድ ቀን ብቻዎን አገኘኋት ጠጋ ብዬ በአማርኛ ሰላም አልኳት። በትግርኛ መለሰችልኝ። ትግርኛ እንደማልችል ነገርኳት። እዋይ ብላ በጣሊያንኛ ቀጠለች። መግባባት ጠፋ። ምንም ማድረግ አልተቻለም። ቻዎ ብላኝ ሄደች። ተስፋ አልቆረጥኩም። መከታተል ቀጠልኩ። ብዙም አልወሰደብኝም ምሥጢሩ ተገኘ። አዲስ የሚመጡት ልጆች ጉዳይ አስፈጻሚና ወደ ሌሎች ሃገሮች አሳፋሪ፣ ዘመድ ወዳጅ ገንዘብ ቢልክ ተቀብላ የምትሰጥ ጠንከር ያለ ሥራ እንዳላት ተረዳሁ። ሌላም ብዙ ብዙ ነገር ሥራዋ ያካትታል . . .  በእሷ የሚያለቅሱም፣ የሚደሰቱም አግኝቻለሁ። ደግነቷን የሚናገረው ከማዘር ቴሬዛ ሲያወዳድራት ፣ የጠላት ደግሞ መምህር ግርማ ሰሞኑን ሮማ ውስጥ አስወጡ ከሚባለው ሰይጣን ያመሳስላታል። የሥራ ጸባዩ ከሁለቱ መሃል አስቀምጧታል።

 

አዎ ሮምና ተርሚኒ ብዙ ትዝታዎች አላቸው። ሮም ተርሚኒ ፣ ተርሚኒ ሮም . . . .

 

እዚሁ ተርሚኒ ውስጥ በምመላለስበት ወቅት አንድ ከስዊድን የመጣ አንድ ግለስብ አገኘሁ። ይህ ግለሰብ ብቻዬን ስለተቀመጥኩ ቦታው እንዳልተያዘ ጠይቆኝ ተቀመጠ። በዚህ ጥያቄው ግለሰቡ ከውጭ እንደመጣ ጠረጠርኩ። ቻዎ ቡና ቤት ውስጥ ከታዘብኩት ጉዳይ አንዱ ሁሉም ባይሆኑም ብዙዎቹ ሰላም ብለው አጠገብህ ሲቀመጡ ስለቦታው መያዝ አይጠይቁም።  ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ

 

- የዚህ ነዋሪ ነህ? ብሎ ጥያቄውን አቀረበልኝ።

- አይደለሁም ብዬ መለስኩ።

- በቀጥታ ከየት መምጣቴን ሳይጠይቅ የመምህር ግርማን ተዐምር ለማየት ነው የመጣኸው? ብሎ የሰሞኑን ጣሊያንን ብቻ ሳይሆን አውሮፓን ያመሰውን ጉዳይ ጠየቀኝ።

- አይደለም አንተስ ? አልኩት ።

- ቆዳው የተላላጠውን እጁን(Psoriasis)እያሳየ ለዚህ ነው የመጣሁት። መምህር ግርማ ይህንን ያድናሉ የሚል ሰምቼ አለኝ።

-ታዲያ ያድኑኛል ብለህ ታምናለህ? ነበር ጥያቄዬ። በእውነቱ ባደረግነው ጭውውት ከበሽታው ለመዳን በመምህሩ ላይ  ያሳደረውን እምነት ተመልክቻለው። ለትንሽ ደቂቃ ቢሆን እግዜር እረድቶት ቢድን እንዴት የሚያስደስት ነበር።

 

ይህንን እውነተኛ ችግር ያለበትን ከተመለከትኩ በኋላ ከጀርመን ለዚሁ ጉዳይ የመጡ ብዙ አግኝቼ አነጋግሬ ነበር። ብዙዎቹ እውነተኛ በሽታ ሳይሆን የወሬ በሽታ ይዟቸው ነበር። ያንን ሁሉ ገንዘብ አጥፍተው ወሬ ለመቃረም መምጣታቸው ሳያስደንቀኝ አልቀረም። አዎ ለእነዚህ የወሬ በሸተኞች መምህር ግርማ መድሐኒት ቢያገኙ ኖሮ ስለ መምህር ግርማ ችሎታ የምስማው ታዕምር ግማሹም አይኖርም ነበር። በእውነት ከታመሙትና መፍትሄ ከሚፈልጉት ጋር የተጣላቻትን ጓደኛዋን በቡዳነት ለማሰደብ የሰፍር ሰው ሰብስባ፣ ቪዲዮ አስቀድታ ወደ መጣችበት ተፈውሳ የተመለሰች ሰው አጋጣሞኛል።

 

ጣሊያን በዜጎቻችን ችግር ተወጥራለች። ይህ ሳምንት ግን የታዕምር ነበር። በዚህም ሳምንት ሆነ በሌሎች በጣሊያን የግራዚያኒን ጉዳይ አንስቶ መወያየት ቢሞከር እንኳን አድማጭ አይገኝም። ተመልሶ ተመላልሶ ወደ መምህር ግርማ ታዕምር ይቀየራል።

 

ምን አልባት የአፊሌ ከተማ ከንቲባ ኢትዮጵያውያን ስለ ታሪካቸው ደንታ የላቸውም ያለው እውነት ይሆን?

 

 

ስለ ታሪካችን መከበር የሚታገሉ በሰላም ይክረሙ!

 

 

በልጅግ ዓሊ

beljig.ali@gmail.com

 

ሐምሌ – 2014 ሮማ


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>