ከሥርጉተ ሥላሴ 17.08.2014 (ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ)
ዛሬ ዕለተ ሰንበት እ.ኤ.አ 17.08.2014 ጀግና አበራ ሃይለመድህን ሲዊዘርላንድ ጄኔባ የገባበት 7ኛ ወሩ ነው። ቤቴ ውስጥም ሰባት ሻማዎች እዬበሩ ነው። ይገባል አይደል?! ፎቶው ደግሞ ፊት ለፊቴ አለ -አይቼም አልጠግበውም!
ወገኖቼ የኔዎቹ ልክ የስድስተኛ ወሩ ስናከበር እኛ ማለትም በ17.07.2014 ከሰዓት በኋላ ዘንድሮ ወፉ ያላወጣቸው የማልዥያ አዬር መንገድ ዩክሬን ላይ ዳግም ሃዘን አደጋ የገጠማቸው ዜና ተደመጠ። አንድም የሰው ዘር ቁራጭ ምልክት ሳይገኝ አመድ ዶቄት ሆኖ መላ ዓለም በሃዘን ሰቆቃ የተደመመበት የጨለመው ዕለት ነበር። እንደ ሰው ለተፈጠረ፤ ብቁ ህሊና ላለው ፍጡር ይህ ድንገተኛ አደጋ ቀለምም፣ ወሰንም፣ ደንበርም ሳይኖረው የሰው ልጅ በሙሉ ሃዘኑን በተለያዬ መልኩ ተጋርቶታል።
የዚህ መከራ ቀን ፊርማ ሳይደርቅ ነበር በዕንባ ተሰቅዛ አሳሯን በምታዬው እናት ሀገራችን ኢትዮጵያ የዘረኛው የወያኔ አስተዳደር የጀግና ካፒቴን አበራ ሃይለመድህን ክስ በአምሳሉ በፈጠረው ፍትህ አልቦሽ ተቋም ምስክር አዳመጥን ብሎ የባዶነት ሙጣጭ ሂደቱን የገለጠልን።
ህሊና ቢኖር 202 ፍጡራንና ነፍስ የታደገውን ወጣት ተግባር ዩክሬን ከደረሰው ሰቅጣጭ አደጋ፤ አስደንጋጭ ዜና ጋር አነጻጽሮ – በማስተዋልም ፈትሾ፤ ቆም ብሎ ማሰብ በቻለ ነበር። አቅልም ህሊናም መግዛት ወይንም መሸመት አይቻል ነገር ሆኖ ነው እንጂ፤ „ተፈጥሮን ተመክሮ አያድነውም“ ይላሉ ቀደምቶቹ … ባልተራራቀ ቀንም እንደ ማልዢያውም ባይሆን የአውሮፕላን አደጋ ተከስቷል። ሰው ማለት ታላቅ የፍጡርና የፍጥረታት አውራ ነው። ፍጥረቱም – ጽንሰቱም – ውልደቱም ሆነ ዕድገቱ ረቂቅ ነው። የሰው ልጅን የነገረ ፍጥረት ረቂቅነት በሰው ልጅ ህሊናዊ ቀመር ወይንም ፍለስፍና ሳይንስ ሊደፍረው ከቶውንም አይችልም። ለወያኔ ደግሞ ሰው ማለት ሸቀጥ ነው። እሚገዛ – እሚለወጥ – እሚሸቀጥ እንዳወጣ በጉልት ገብያ የሚቸበቸብ። ባለፈም እንደ አውዳመት ዶሮ ባገኘበት አርዶ ባሰኘው ቦታ የሚጥለው የበቀል ማስከኛው፣ የደም ጥማቱ እርካታ ማወራራጃ – መፈተኛ – መሞከሪያ ….
ስለሆነም አረሙ ወያኔ የበለጠበት ሰው ሰራሹ ቆርቆሮ በሰላም አርፎ እስከ ዓይን ጥርሱ ተረከቦ ግን በጥቃቅን ወጪዎች ስሌት እንዲህ ይዳክራል። ይህ ነው የወያኔ የስብዕዊነት፤ የዕንባ ተቆርቋሪ ድርጅት በሚር/ ማዕረግ አደራጀሁ እያለ የሚያላግጠው። ሰው ለወያኔ ከእንሰሳትም፤ ከማሽን መሳሪያም እጅግ ያነሰ ፍጡር …..
አይደለም ሰው ከነህይወቱ ተርፎ። አውሮፕላኑ ብቻውን አደጋ ቢድርስበት እንኳን ሰው ተረፈ ተመስገን ይባላል። በሌላ በኩልም ዬትልቁ የሰው ልጅ ተፈጥሮ ሞተሩ መንፈሱ ነው። በዚህም ዘርፍ እጅግ በጥንቃቄ ነበር ትክክል የከወነው። አደጋ ሲደርስ ለዛውም ሰማይ ላይ ያቺ የግቢ ውጪ ነፍስ ቆይታ እራሱ በምንም ምንዛሬ ሊሰላ ከቶውንም አይችለም። ግን ለአድናቆት ቀርቶ እንደ ሰው ለማሰብ ለተሳነው የዘረኛው አፓርታይድ የወያኔ ከፋፋይ ሥርዓት ለፍጡራን ደንታ ቢስ በመሆኑ ስሌቱን በጎጥና በሂሳብ እንዲሁም በጭካኔ መንፈስ እንዲህ ያወራርደዋል። እንጠብቃለን …. አዬር አልባው ፉኛ ችሎት የሚሰጠውን ብይን ….
ካፒቴን አበራ ሃይለመድህን ከመጠን የዘለለውን ረገጣና ግፍን መክቶ – ጥቃትን ለማውጣት ትክክል ሆኖ የተፈጠረ ብቁ ዜጋ ነው። „አሻምን“ የገለጠበት መንገዱ በስክነት ከእጁ በገባ ዕድል ለትክክለኛው ጊዜ ትክክለኛውን ሁኔታ፤ ለትክክለኛው አቅም ትክክለኛውን የኃላፊነት ደረጃ፤ ለትክለኛው ውሳኔ ትክክለኛውን ችሎታ መግቦ ትክክልን አቅም መግቦ፤ በትክክል ንጹህ አዬርን አስማምቶ ሰጥቶ ካለ ብክነት ንጥርነትን በስኬት አወራርዶ ዕውነት – ትክክል ሆነ ከደባባዩ ላይም ዋለ። ፍትህ – ርትህ – ፍርድ ይሏችኋል ይህ ነው። የተገፋ -የተገለለ መንፈስ በዚህ መልክ የጠላቱን ዕላቂ መንፈስ ያወላልቃል።
ሲፈጠር ተስተካክሎ ስለነበረ በዝምታ የከወነው ድንቅ ተግባር አቋሙን፤ ውሳኔውን፤ ድርጊቱን፤ ችሎታውን፤ ለትክክል ውስጥ ሸልሞ ለዘመኑ ትክክሉን የጀግንነት ጥሪት ባለቤት ለመሆን እንሆ ቻለ። አረሙ ወያኔ እንዲህ ተቆፍሮ ተቀብሮ እንደ ኖረ አውሬ ያዬውን ሁሉ በሽብር ሴራ ፈርጆ መቆሚያ መቀመጫ ላሳጣው ግዑፋን ትውልድ የደም መላሹ ወጣት አንዳዊነትን በአሃታዊ ፍላጎት ቀምሮ ድልን ያበለገ እራስ እግሩ ፍሬ ዘር እርምጃ ነበር የወሰደው።
ጀግናዬ አበራ ሃይለመድህን ይህን ዬታሪክ ዕለት እዚህ ሲዊዘርላንድ ካስመዘገበ ጀምሮ እኔ በግሌ አድርጌ የማላውቃቸውን ነገሮች እፈጽማለሁ። እንዴት ቢሉ …. ሁልጊዜ ጉግል ገብቼ ምን የአውሮፕላን ክስተት እንደተፈጠረ አያለሁ። በሰማይ ላይ አውሮፕላን ሲበርም ቀና ብዬ አይና በሰላም ያግባችሁ እላለሁ። ከአደጋዎች ሁሉ የከፋው ሰማይ ላይ አመድ – ዱቄት ሆኖ ለወሬ ነጋሪ እንኳን ሳይበቁ መቅረት ነውና ለህይወቴ በዚህ ዙሪያ አዲስ ምዕራፍ ነው ማለት እችላለሁ። ማለት ልክ ከቤተሰቤ አንድ ሰው በዚህ ሙያ እንደተሰማራ ያህል ነው ውስጤ እያዳመጠ ያለው።
ዓይን ያለው ህሊና፤ መንፈስ ያለው ፍላጎት፤ ተስፋ ያለው ችሎታ እንዲህ ካለምንም ግድፈት ሲከውን መምህርነቱ፤ አብነቱ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ዓለምአቀፋዊ ነው። ያኮራል ወንድም ጋሼ – ተባረክልኝ!
አንድ ሰው ብዙ ነው። ሰው መኖርን አስቦ መኖር ሳያማክረው ወይንም መኖርን ሳይወስንበት በእንዲህ ዓይነት አጋጣሚ ማለፍ ዘላለማዊ ጸጸት ነው። ጀግና አበራ ሃይለመድህን በዞግ የከረፋ አስተዳደር መከራውን – መከፋቱን – ቅሬታውን – መሸከም አለመቻሉን የገለጸበት መንገዱ ሆነ ከማናቸውም ጉዳት ያዳነውን የሰው ልጅ ሆነ ንብረት ስሌቱን በሂሳብ መተመን ዕብንነት ይመስለኛል።
ጀግናዬ – ለተፈጠረበት መክሊቱ – የልጅነት ምኞቱ፤ የወጣትነቱ ተስፋው አፈጻጸሙና ሂደቱ እንከን የማይወጣለት ትክክሉ ልኩ ነው። የኔው ጀግና አበራ ሃይለመድህን እንኳንም ተፈጠረ። ደመ ከልብ ሆኖ ለቀረ ወገን ፊት ላይ ሆኖ እንዲህ መከተ።
ዛሬ እንዲህ በአንድ የመንደር አስተዳደር ሀገር ተከትፋ እየታመሰች ባለችበት ወቅት፤ ልጆቿ በዬሄዱበት እዬታደኑ በመርዝ ጋዝ መሞከሪያ በሆኑበት ወቅት፤ አልፎ ተርፎ ውጪ ያለነውን ብዕርና አንደበት ለመዝጋት፤ አብሶ የነገ ተረካቢ ወጣቶቻን ግንባር ቀደም፣ ትንታግ፣ ሀገር ወዳድ የነፃነት ትግሉን ቤተኞችን ከእንቅስቃሴያቸው ለመገደብ ከፍተኛ የሥነ – ልቦና ጦርነት በታወጀበት ዘመን እንዲህ ሞግድ ግጣሙን ሲያገኝ የሰማይ ታምር ነው። ጀግንነትና አደራ ተጋቡ። ቃላቶች ሁሉ ሰልፍ ቢወጡ መተርጎም የማይችሉት ብሄራዊ የሀገር ፍቅር እንዲህ ፈክቶ በተባ ድፍረት በትክክል ተከውኖ አዬን።
የኔዎቹ ታስታውሱ እንደሆን ቱቦው የዘር አስተዳደር ቀለብ ተሰፋሪዎች ልዑክ ሆነው እዚህ ሲዊዘርላንድ መጥተው በነበረቡት ጊዜ „ታሟል“ ይሰጠን ነበር ጥያቄያቸው። አሁን ደግሞ „ጤነኛ ነው“ በወንጀል ይጠዬቃል። አያችሁት የበቀል ብቅሉ ወያኔ ጥልቅ ሴራና የቋሳ ጉድጓድ። ፍርዱም ባለጉዳዩ በሌለበት ይታያል። የሥነ -ልቦናውም ጦርነት ይቀጥላል። ግን በማያውቁት ተፈጥሮ ላይ ስለሆነ ይሄን አጅሬ ሃይልዬ መንፈሱን ከቀለሙ ጋር አስተጋብቶ የሀገሬውን ቋንቋ ጥናቱን አስከንድቶት ይሆናል – ትክክል ነዋ! ጠፈፍ ብሎ የተፈጠረ የህሊና ዓይንና ጆሮ።
አይደለም እነሱ እነ – የዘር ብልቂያጦች፤ የዘር በሽተኞች ቀርቶ የወለዱት አጅግ በሚደንቅ እንክብካቤና ሥነ – ምግባር ኮትኩተው ያሳደጉት ክብርት እናቱ ወ/ሮ የህዝብአለም ሥዩምና የተከበሩ አባቱ አቶ አበራ ተገኜ አያውቁትም – በፍጹም። የማያውቁትን ልጅ ነው ወልደው ያሳደጉት። እርምጃውና ዕቅዱ፤ ዕቅዱና ውጤቱ፤ ብልህነቱና ላቂያነቱ በዚህ ዘመን ከቶ የማይተሰብ ነው። ደሙን ሲመልስ ኮሽ ሳያደርግ በእጥፍ ድርብ፤ እራሱንም ጠብቆ – ክብሩንም ጠብቆ – የሙያውን ክህሎት ጠብቆ – የሙያውን ሥነ ምግባር ሳያጓድል እንግዶቹን እንዳከበረ፤ የኢትዮጵያዊነትን ጠንቃቃነት በናሙናነት ጠብቆ ታሪክንም አልምቶ ነው። ቀበቶውንስ እሱ ይታጠቀው …. ትክክሉ ነውና። ወንድነቱን እሱ ይነገር ትክክሉ ነውና። ተግባርም ይናገር ትክክሉን አግኝቷልና። ተመስገን – ተስፋዬ!
ካፒቴን አበራ ሃይለመድህን መሰደድን ሲተረጉመው በጠላቱ ጦር ሰፈር ላይ የመንፈስ ትቅማጥ አውጆ፤ ጥቃቱን አስገድዶ ግቶ -፤ ለጎጠኛው ወያኔ – ቁርስ – ምሳ እራቱን ሽንፈትን – አስጎንጭቶ። የሴራ – የሸር – ዬኢጎ – የምቀኝነትን ትብትቦችን በተከደነ መንገድ አፈር አስግጦ። መገለልን – በተግባሩ አሸንፎ፤ እንደ ወያኔ ላለ ሙጃ አስተዳደር ትክክሉ እንዲህ ዓይነት የዝምታ ገድል ነው። ጠላት ባለሰበው – ባለወጠነው – ባላተኮረበት መንገድ ሆድ ዕቃውን እንዳልነበር አድርጎ ማስማጥ – ማስመጥ። ማጥቃት እኮ መልኩም ዘርፉም ረቂቅ ነው። ረቂቅነቱን እንዲህ በትክክል ኢትዮጵያዊነት መሸነፍ አለመሆኑ ይተረጎማል። ለመክሊቱ ያደረ ፍጥረት ትክክልነቱን በድርጊት እንዲህ ያበሥራል። የኔ ጌታ – የእኔ አባት – የእኔ ውድ – ዬእኔ ብርቅ እግዚአብሄር አምላክ የልቦናህን አሟልቶ ያሳዬኝ። እግዚአብሄር ይስጥልኝ። ውድድድድ ….
ክብረቶቼ የምትችሉ በፌስ ቡካችሁ – በቲዩተር አካውንታችሁ ጀግናችሁን ከፍ አድርጋችሁ ሰንደቃችሁ አድርጋችሁ ብተውሉ ቤታችን አውዳችን ጠረኑ ጀግና – ጀግና ….. ይመቻችሁ። መሸቢያ – ጊዜ።
ጀግኖቻችን የመንገዳችን መብራቶች ናቸው!
ደሜን ሳዳምጠው ውስጤን አገኘዋለሁ!
ለእኔስ ሰው ሆኜ መፈጠሬ ብቻ ይበቃኛል!
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።