ማምሻዬን እጅግ በጣም ከማክበረው ወዳጄ ጋር ሁሌም ስለሚያስጨንቀን ነገር ስናወጋ እረጅም ሰዓት ቆየን፡፡አንዴ ስንስማማ ሣይመስለን ሲቀር በአሳብ ስንለያይ ከቆየን በኋላ ወዳጄ በጃፓን አገር አብዝቶ ስለሚነገር ተረት እንዲህ ሲል ተረከልኝ፡፡ ተረቱ እጅግ በጣም ድንቅ ከመሆኑ ባለፈ የቡዙ ነገር አመላካች ነው፡፡
=====
መንገዱ እንዲሁ ቀላል አልነበረም፡፡ እጅግ አያሌ ቀናትን የሚፈጅ፣ ተጨማሪ ስንቅ የማይሸመትበት እና እጅግ አድካሚ ነበር፡፡ ከዚሁ ሁሉ በላይ ደግሞ በመካከል እጅግ አስቸጋር እና ረጅም የሆነ ተራራ መገኘቱ ነው፡፡ ነገር ግን ሁለቱም ተስፋ ባለመቁረጥ ተጓዙ፡፡ እያረፉ እና እየተነሱ ያንን ተራራ ከሁለት አቅጣጫ ተያያዙት፡፡ በድንገት ጫፉ ላይ ሲደርሱ አንደኛው ሌላኛውን ተመለከተ፡፡ አንዱ የሌላኛውን መኖር ፈፅሞ አያውቁም ነበርና ሁለቱም ተገረሙ፤ ደነገጡም፡፡
ወዲያው ተቃቅፈው ከተሳሳሙ በኋላ አንዱ ኦሳካን ሌላኛው ደግሞ ኪዮቶን ለማየት በመጓዝ ላይ መሆናቸውን ተጨዋወቱ፡፡ ከተረፋቸውም ስንቅ አውጥተው አብረው በሉ፡፡ ሳር ላይ ጋደም ብለው ትንሽ እረፍት አደረጉ፡፡
በመካከል የኦሳካው እንቁራሪት ‹‹እንዲህ ትናንሾች መሆናችን ምንኛ መጥፎ እድል ነው›› አለ፡፡ የኪዮቶው እንቁራሪት ደንግጦ ‹‹ምን ተጎዳህ?›› አለው፡፡ የኦሳካውም ‹‹ትልልቆች ብንሆን ኖሮ እዚህ ተራራ ጫፍ ላይ ቁመን የምንሄድባቸውን ከተሞች በሩቅ ማየት እንችል ነበር፡፡ ከዚያም በእውነት እዚያ ድረስ መሄዳችን ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም የሚለውን ሳንለፋ እንወስን ነበር›› አለው፡፡ ያን ጊዜ የኪዮቶው እንቁራሪት ራሱን ከነቀነቀ በኋላ ‹‹ቀላል ነው እኮ፤ ትልልቅ መሆን አይጠበቅብንም፡፡ ምን መሰለህ ሁለታችንም በኋለኛው እግራችን ብቻ እንቆማለን፡፡ በፊት እግራችን ደግሞ እንያያዛለን፡፡ ከዚያም ፊታችንን ወደ ምንሄድበት ከተማ አዙረን ማየት እንችላለን›› አለ፡፡ በሃሳቡም ሁለቱም ተደሰቱ፡፡
ከዚያም ሁለቱም በኋላ እግራቸው ቆመው አንገታቸውን ቀና አደረጉና በፊት እግራቸው ተያያዙ፡፡ አፍንጫቸውን ወደ ሚሔዱበት አቅጣጫ አዞሩት፡፡ እናም ከተማው ታያቸው፡፡ ‹‹ይገርምሃል፤ አሳካ ከኪዮቶ በምንም አትለይም፡፡ ፎቆቿ፣ መንገዶቿ፣ መብራቶቿ፣ መኪኖቿ ሁሉም ያው ናቸው፡፡ ተመሳሳይ ነገር ለማየትማ እዚያ ድረስ ምን አለፋኝ? ለውጥ ላይመጣ ድካሙ ምንድነው?›› አለ የኪዮቶው እንቁራሪት፡፡ ‹‹ልክ ነህ፡፡ ኪዮቶም እንደ ኦሳካ ናት፡፡ ምንም ለውጥ የላትም፡፡ ለካስ የትም ቦታ ቢሔዱ ተመሳሳይ ነው፡፡ መንገደኞች ዝም ብለው ነው ለካ የሚደክሙት፡፡ ትርፉ ድካም መሆኑን ባውቅ ኖሮ ይህንን ያክል አልደክምም ነበር›› በማለት የኦሳካውም እንቁራሪትም ተመሳሳይ ሃሳብ ነበር የሰነዘረው፡፡
የሁለቱን እንቁራሪቶች ሁኔታ እያየች ትስቅ የነበረች ጉንዳን ‹‹እናንተ እንቁራሪቶች ሞኞች ናችሁ ልበል፤ ወደፊት ብትቆሙም እኮ የምታዩት ወደ ኋላ ነው፡፡ ስለቆማችሁ ብቻ ይታያችኋል ማለትኮ አይደለም፡፡ ዋናው መቆማችሁ ሳይሆን አቋቋማችሁ እንዲሁም ማየታችሁ ሳይሆን አስተያየታችሁ ነው›› አለቻቸው፡፡
እንቁራሪቶቹም ተናደው ‹‹ዞር በይ አንቺ ጉንዳን፤ አንቺ ከኛ በምን በልጠሸ ነው፡፡ ድሮም እናንተ ጉንዳኖች የእንቁራሪቶችን በጎ አትመኙም፡፡ እኛ ያየነውን ለማየት እንቁራሪት መሆን ያስፈልጋል›› አሉና አባረሯት፡፡ ከዚያም ከተያያዙበት ተላቀቁ እና ሳሩ ላይ አረፍ አሉ፡፡
ሁለቱም ያልገባቸው ነገር ቢኖር የኋላ እግራቸውን ዘርግተው የፊት እግራቸውን ወደ ላይ አድርገው ሲቆሙ አፍንጫቸው ወደ ፊት አይናቸው ግን ወደ ኋላ እንደሚያይ ነው፡፡ ሁለቱም ወደ ፊት ያዩ መሰላቸው እንጂ ያዩት የመጡበትን ከተማ ነው፡፡ ሁለቱም የተስማሙት ተመሳሳይ ነገር አይተው አይደለም፡፡ የሚያውቁትን ነገር ስላዩ ብቻ ነው፡፡ ከስንት ትግል በኋላ ተራራው ላይ መድረስ ብቻውን አዲስ ነገር ለማየት አያበቃም፡፡ አዲስ ነገር የማየት ፍላጎት ብቻውንም አዲስ ነገር አያሳይም፡፡ ተደጋግፎ ቀጥ ብሎ መቆም ብቻውን አዲስ ራእይ አያመጣም፡፡ እንዴት እና ወዴት ነው የምናየው? የሚለው ወሳኝ ነው፡፡