ከሥርጉተ ሥላሴ 05.09.2014 (ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ)
„እንሆ፣ እንደ ምድጃ እሳት የሚነድ ቀን ይመጣል፤ ትዕቢተኞችና ኃጢአትን የሚሠሩ ሁሉ ገላባ ይሆናሉ፤ የሚመጣውም ቀን ያቃጥላቸዋል፣ ሥርናንና ቅርንጫፍንም አይተውላቸውም፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሄር። ነገር ግን ስሜን ለምትፈሩት ለእናንተ የጽድቅ ፀሐይ ትወጣለች፤ ፈውስም በክንፎቿ ውስጥ ይሆናል። እናንትም ትወጣላችሁ እንደ ሰባም እንቦሳ ትፈነጫላችሁ፤ በምሠራበት ቀን በደሎኞች ከእግራችሁ ጫማ በታች አመድ ይሆናሉና፤ እናንተ ትረግጡአቸዋላችሁ፡፤ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሄር“ (ትንቢተ ሚልክያስ ምዕራፍ 9 ከቁ. 1 እስከ 3)
የባንዳ አመድነት ጊዜው ቢረዝምም አይቀሬ ነው። የህዝብ ከመጠን ያለፈ ዕንባ ማዕትን ያወርዳል። ቀን የተዘጋባቸው የነፃነት ሰዎች ደግሞ አንገታቸውን ቀና አድርገው ጸሐይን ያያሉ – ይህ በኢትዮጵያ ምድር አይቀሬ ነው። ውስጣችን ጠርገን ዕንባችን እዬረጨን አቤት ካልን —- ግን የአዎንታዊነት አርበኝነትን ይጠይቃል። በፍላጎታችን ውስጥ በርግጠኝነት ስለመኖራችን ማንነት ፊረመኞች ከሆን። ግን እርግጠኞች ነን? ፍላጎታችን – እንፈልገዋለን? የማዬው ብስልና ጥሬ ስለሆነ። ዝንቅ ፍላጎት – የጎሽ መስመር – የተበረዘ ሥህነ – ስርክራኪ ጠረን ይሸተኛልና። የእኛ ጥንካሬ ምንጩ መከራ ሆኖ ግን አቅም እያለን ያንሰናል። ጠላትንም እጅግ አቃለን በማዬት ቀኑም አጭር እንደሆነ እናስባለን። ግነቱም ኩሰቱም ለነፃነት ትግሉ የሚበጅ አይመስለኝም። ቀኑን የሚያሳጥረው የተግባር ሥልጡንነት – የተባ ስልት፤ የማድረግ ፈቃደኝነትና የውስጥ ተቀባይነት፤ ዕድሎችን በመተርጎም ቅልጥፍና ጥራትን በሚገባ አደራጅቶ ስምሪቱ በፍላጎት ልክ መመጣጠን ሲቻል ብቻ ነው። ብዙ ምቹ ሁኔታዎች አሉ። ሁኔታዎችን አድምጦ ከተግባር ጋር ማጣመር ከተቻለ አቅምን መምራት ይቻል ይመስለኛል።
ወደ ርዕሰ ጉዳዬ ስዘልቅ – ነገ ለወያኔ ምኑ ነው? ብዬ መልሱን ደግሞ እኔው እራሴ ልመልሰው ደመኛው ነው አልኩኝ። ትክከለኛ መልስ ነው። ወያኔ ስለ ነገ የሀገር ቀጣይነት፤ የሀገር መኖር ሆነ የቀጣዩ ትውልድ ግንባታና ጥንቃቄ በሚመለከት ባዕዱ ነው። ነገ ስለሚባል ነገር ወያኔ አስታውሶት አያውቅም። እንዲያውም ነገ ለወያኔ የሚፈራው ጦሩ ዕዳውም ነው። ስለምን?
ዛሬ አመርትኩ ያለውን የዞግ ኩረት ነገ ፍርከስክስ ብሎ ስለሚያገኘው ወያኔ ነገን ሲያስብ ወባ ይይዘዋል። እንዳሰበው እንዳለመው አልሄደለትም። ማለት መንፈስን በማማረት ብሄራዊነትን ማክሰል የነገ መሰረተ አስትምኽሮቶ ነበር። ግን አልሆነለትም። አመድ ለብሶ አኮፋዳውን ተሸክሞ አሸዋ እያመረተ ስለመሆኑ፤ አበቀልኩ ያለው የአረም ችግኝ ሁሉ አፈር ለብሶ ትቢያ ተንተርሶ ፍግ ሲሆን እያዬ እንዴት አይንዘፍዘፍ።
ተግቶ ታጥቆ የተናሳበት „ብሄርተኝነት“ እያለ እያደነ „በአሸባሪነት“ የሚፈርጃቸው ወጣቶች „ዬሽብርተኝነት“ ወንጀላቸው ሀገራዊነትን ኢትዮጵያዊነትን መርሃቸው ስላደረጉ ብቻ ነው። ሳልጠግበው እንደወደድኩት መዳራሻውን ለማዬት እጅግ እጓጓለት የነበረውን የአንድነቱ አቶ ሃብታሙ አሸባሪው ወያኔ ካሰናዳለት የወየኔ ቁሮ ዬወጣት ሊግ ዬመሪነት እድገት ደረጃ መስፈርቱ አለማሟላቱን የነገሩን አቶ ኤርምያስ ለገሰ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ „ብሄርተኛ“ በሚል ስለመሆኑ ነበር።
አሁን ይህ አመክንዮ እጅግ በጽሞና ላስተዋለው፤ በጥልቀት በነገረ ጉዳዩ ሥረዎ ግንድ ውስጥ እራስን አስቀምጦ ማለትም ይህችን ነጥብ ብቻ ይዞ እያንዳንዱ ዜጋ ቢፈትሽ የወያኔ ሃርነት ትግራይን የነገን ህልም ቁልጭ አድርጎ ያሳዬናል። አንድ ኢትዮጵያዊ ወጣት፤ በላቀ ብቃት እጅግ ሊታመን በማይችል የህሊና ጥሪት ሁሉንም አሟልቶ „አጥባቂ ብሄርተኝነት“ በሚል መሥፈርት ለብቃቱ ሌላ ተለጣፊ መመዘኛ ተሰርቶ – ተገለለ።
አክብሮተ – ኢትዮጵያዊነት ሊያስከብርና ሊያስመርጥ ሲገባ እንዲህ ከደረጃ የሚያስገልል – የሚያስገፋ ከሆነ የነገይቱ ኢትዮጵያ ለወያኔ በትክክልም ደመኛው ናት ማለት ነው። ወያኔን ብዙ ምላጭ አለው። ምላጩ ወይንም ቅርፊቱ የቁጥር ድንበር የለውም። አስኪደክማችሁና እስኪያሰለቻችሁ ድረስ ብትልጡት – ብትልጡት – ብትልጡት ተደጋግሞ የምታገኙት የአምክንዮ እንብርት ኢትዮጵያን በጠላትነት በጥርሱ መያዙን ነው።
ኢትዮጵያ ሀገራችን ቅጽል ወይንም ተወላጠ ሥም ሳይሆን ልዩ የሆነ ገናና ሥም መጠሪያ አላት። ይህ ሥሟ በሚመራት – በሚያስተዳድራት – በሚገዛት ቡድን ተደፍሮ አይጠራም። „ሀገሪቱ – በሀገሪቱ፤ በእሷ፤“ በቃ በተወላጠ ሥም ነው የምትጠራው። ሄሮድስ መለስ አፋቸውን ከፍተው „እናት ሀገሬ ኢትዮጵያ“ ዜግነቴ፤ የእኔነቴ መገለጫ ኢትዮጵያዊነት የነፃነቴ ዓርማ ሰንድቅዓላማዬ ሳይሉ“ ቀን እንጦርጦስ ላካቸው። ባዶ ሳጥናቸው ነው የተቀበረው። እሬሳው እራሱ አልተመለሰም እንደ እኔ። ከሰመጠበት ጉድጓድ እንደተከረቸመ – ተከረቸመ።
ዛሬ የሚታሠሩት – ለመረጃ ሳይበቁ ሳንሰማው የሚሰወሩት – የሚገለሉት – የሚገደሉት – የሚታፈኑት ሃጢያታቸው ነገን ሊያሳድር የሚችለውን ሀገራዊ ፍቅር በውስጣቸው ጽላታቸው ስላደረጉ ብቻ ነው። ለሰንድቅዓላማ ክብር ምላሹ እስር ነው። ብሄራዊነት አርበኝነት መታፈን መገረፍ ነው። ስለምን የኢትዮጵያ ሰንድቅ ዓላማ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ለወያኔ የደም ግፊቱን ያስነሳበታል። ነገ መቆዬት የሚችለው ደግሞ በዚህ የደም ዋጋ በተከፈለበት አርማ ሥር ብቻ ነው።
ወያኔ በባላንጣነት እንደ ቀረመት ሥጋ የሸነሸነው አካል ድልዝ አርማ ሳይሆን የልባችን ጌታ በህብረ ቀለማት አንድነት ያፀና፤ ግርማ ሞገስ ያለው ብሄራዊነት ከምንጩ ከሰንደቅአላማችን ነው። ይህ ደግሞ ለወያኔ ሃርነት ትግራይ ውጋቱ ነው። ወያኔ ሲገባ እኮ እኔ በዓይኔ ያዬሁት የእግሩ ገንቤላ አድርጎት ነበር የገባው ሰንድቅዓላማችን፤ በወያኔ ሃርነት ትግራይ መሪ „የተራከሰው“ ስለ ቃሉ ሎቱ ስብሃት ጉልላታችን፣ አፍሪካን ከደሟ ጋር ያገናኘው አብነታዊ ምልክታችን፣ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ዜግነታችን እንደ ማንነት መግለጫነት ጠብቆ ያቆዬ ልዩ ሰማያዊ ባለውለታችን ስለመሆኑ በሚገባ ስለሚረዳ ወያኔ ትውልዱ በዚህ ሥር እንዲሰባሰብ አይሻም። የአረሙ ወያኔ ፍላጎት – ትውልዱ ከስንት ሞቶ ሺህ ዓመት ወደ ኋላ ተመልሶ ጎጥ ላይ እንዲቸክል ነው የሚሻው። በዚህ ስሌት ነገን አርመጥምጦ የዶግ አመድ ማደረግ ነው የወያኔ ሠርጉ። የወያኔ አንጡራ ፍላጎት ይሄ ነው። ትውልዱ ደግሞ እስርን – ስደትን – መገለልን – ረሃብን ፈቅዶ ከደሙ ጋር ሙጭጭ ብሎ ሞትም ድህነትም ከአንተ ጋር ብሏል። ….. ያረሙ ወያኔ እንብርት ገልብጦ ከበሮውን የሚያስደልቀው የወያኔ ሃርነት ትግራይ ዓርማ ለመላ ኢትዮጵያ ህዝብ ምኑም አይደለም።
ከዚህ ሰንድቅዓላማ ጋር የሚጣላ ማናቸውም ድርጅት በሉት ንቅናቄ ወይንም ግንባር በሉት የተቀባይነት መንፈሳዊ ሃብቱ እሳተ ጎመራ ይበለዋል። ሰንደቅአላማችን መንፈስ አለው የሚያስጠጋ – የሚያጽናና – ተስፋ የሚሆን – አፍቅሮትም። የተለዬ መክሊትና ጸጋ ያለው የተመረቀ ዓርማ ነው። ምህረትም ነው። እንዲህ በሰው ሰራሽ እሳቤ መሰረዝ ቀርቶ መነቅነቅ አይቻልም። ልብ ውስጥ ልብ ሆኖ መኖር ዬቻለ ትንግርተኛ ነው። ቅዱስ መጸሐፋችን ነው – ሰንደቅአለማችን። ፍቅር ሰጥቶ ፍቅርን በገፍ የተቀለበ የፍቅር እጬጌ ነው ሰንድቅአላማችን።
ሌላም ነገር ማንሳት ይቻላል በርካሽ እዬቸበቸበ ያለው የደም ዋጋ መሬታችን ነገ ምርት ስለማብቀሉ ደንታ የለውም ወያኔ፤ ገዢዎች ቢፈልጉ በመርዝ ቢፈልጉ በኬሚካል ቢያነዱት ጉዳዩ አይደለም ወያኔ። ዬነገ የኢትዮጵያዊ ትውልድ ፍልሰት ምኞቱ ስለሆነ ዛሬ በሥልጣኑ በመጠቀም የነገን ውድመት ሌትና ቀን በርትቶ እዬሠራበት ነው ያለው። በእዳም ማግሥት እንዲቧጥጥ አብዝቶ እዬባተለ ነው።
በትምህርቱ ዘርፍም ስንመጣ የዛቀጠ ደረጃ ላይ ይገኝበታል። እርግጥ የተለዬ እንክብካቤና ትኩረት ያልተነፋጋቸው አሉ። እድገቱ ሆነ የሚያስገኘው ዕሴት እርግጥ አሁን አይታይም፤ የዕውቀት ዕድገትና የግንባታ ፍሬ የሚታዬው በተደራረቡ ዓመታት ነው። በሂደት ልክ የደቡብ አፍሪካን ስልት የተከተለ ግንባት ከሥር ተስተካክሎ በፈለገው ቦታ ላይ እንደ ተጀመረ ይታያል። ይህ ያልተመጣጠነ የአትኩሮት ዝንባሌ በሰፊው ህዝብ ልጆች የበቀል ቂም ልኩን ወይንም መጠኑን ያሳያል። ስለምን? የተሻለ ኢትዮጵያዊ ትውልድ – የበለጠ ትውልድ – የቀደመ ትውልድ ለወያኔ የህልሙ መቃብር ቆፋሪ ስለሚያደርገው በዚህ መልክ እያላሰላሰ ትውልዱን አስተኝቶ መገደሉን ተያይዞታል።
የእነሱማ ልጆች አይደለም የምርጥ ዘር ቤተሰቦች ማናቸውም የቀረቤታ ግንኙነት ያለው ሁሉ በሚሊዮን ዶላር ውጪ ሀገር ይማራሉ። በዓመት በተደጋጋሚ እረፍት ጊዜያቸውን እዬተመላለሱ ያሳልፋሉ። ልጆቹም የሚወለዱት አሜሪካ ሲሆን የቀጥታ ዜግነታቸውን እንዲያገኙ …. ይደረጋል። ሌላም ሌላም —- ይህን አድላዊ ጭቆና ሰፊው ህዝብ ከነገን ጋር አስልቶ ከልቡ ሆኖ ሊመረምረው ይገባል።
ይህ የድብብቆሽ ጨዋታ መፈታት አለበት። ሰንድቅአላማችን የኢትዮጵያን ነፃነት ያቆዬ፤ ያዋጋ፤ ያደራጀ፤ በመከራችን ቀን ሁሉ ያልተለዬን፣ አንባሳደራችን ሲሆን፤ በዚህ ማዕቀፍ ሥር የሚመሩ አምክንዮዎች ብቻ ናቸው የእኛ ሊሆን የሚችሉት እንጂ „ለታላቋ ትግራይ“ ህልም አልሞ ተነሰቶ – ተሳክቶለትም በጠላትነት በሚከተክታት አርማ ሥር ማደገደግ ውርዴትም ውርዴም ነው። ለነገሩ ጭቆናው ሆነ መጋፋቱ ብሄራዊነታችን ሆነ ሰንደቀችንም ይጨምራል።
ስለሆነም በንጹሁ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንድቅዓላማ ሥር ማናቸውም መስዋዕትነት ጥሞ ሊከወን ይቻላል። „በታላቋ ትግራይ“ ህልም ግን ከንቱነት ነው። ሞቱም ሆነ መሰዋዕትነቱ ዋጋ ቢስ ነው። በጠላትነት የተፈረጀ ሰንድቅዓላማ ባለቤቶች ሆነን ሥጋና ደማችን ተረግጦ፤ የአደራ መክሊታችን ተጠቅጥቆ ይህን ተላልፎ በዬትኛውም መስፈርት አንዲት ጋት ለወያኔ ደጋፍ የሚያሰጥ አቅም ቢኖር ብክነት ነው። ሊሆንም አይገባም።
የናቀው – ያንቋሸሸው – የተጸዬፈው – የረገጠው፤ ማሰሪያ ህግ የሰራለት እኮ ሚሊዮኖች ለብሰነው ስንወጣ ስለሚያርመጠምጠው ነው እኮ። አይኑ እኮ የወያኔ ጉርሽጥ ነው የሚሆነው መግለጫችን – ኩራታችን – ፍቅራችንን ሰንድቅአላማችን ስናጌጥበት። እንዴት የዚህ ሚስጢር ድንቡልቡል ይሆንብናል። በምንም ነገር ሊጠቀለል የማይችል ሃቅ እኮ ነው፤ እኛ ስንዋበት ዓይነት የወጣላቸው ደጋፊዎቹ ሳይቀሩ ነው ከእሳት እንደ ገባ ፕላስቲክ ኩምትርትር – ኩፍትርትር የሚሉት። ይህን አምክንዮ ለማዘከር አቅምን በአግባቡ አደራጅቶ የጠሉትን፤ የፈሩትን ነገር ማስጎንጨት ደግሞ መስፈርቱ ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው።
እንቆቅልሹን የወያኔ ሃርነት ትግራይን የለበጣ ንድፍ በሆድ አደርንት የተሰለፈው ሃይል ቢሆን ሊያሰተውለው የሚገባው ቁም ነገር —- የሚሠራው፣ የሚደክመው፣ የሚጥረው፣ የሚረገርገው ለራሱ መጥፊያ – ለራሱ ሰብዕና መደርመሻ መሆኑን በሚገባ ክልቡ ሆኖ ሊመረምረው ይገባል። እንደገና አዎን እንደገና ይመርምረው። ይህንን ነው ኢትዮጵያዊው ሁሉ ዓይኑ ተገልጦ ሊያስተውለው የሚገባ ፍሬ ነገር። አንጡራ የነገ ጠላት ጋር በምን ሂሳብ ቅንጣት መንፈስ ይቸርለታል? ዕብንነት ነው። እያሉ መሳት እራስን።
እርግጥ ነው አንድ እውነት አለ። ገዢ በሆነው የወያኔ ሃርነት ትግራይ ሥር ምልዕቱ ሥራ መሥራቱ ላም ጣም ያጣውን ኑሮውን መግፋቱ ግድ ነው። 90 ሚሊዮን ህዝብ ልሰደድም ወይንም ልሸፍትም ቢል የማይሆን ነው። ነገር ግን እኛ የአንተ ነን የሚለውን የሙጃውን ቧልት ግን አፈረጥርጦ ሊያውቀው – ሊገነዘበው ይገባል። ስንዴ እንክርዳድ አይሆንም እንክርዳድም ስንዴ አይሆንም። ወያኔ ከበቀለበበት ዓላማው አንዲት ስንዝር ፈቅ አይልም። ማሳው ዘርኝነት ነው። ድልዝ የለው ስንጥር የለው። የወያኔ ሃርነት ትግራይ መላያ ፍጥረቱ በዞግ ፍልስፍና አፈናና ረጋጣ ማካሄድ።
ሃቁ ይህ ነው። አሁን በቅንነት ያሉ ወገኖች ኢትዮጵያ አደገች እያሉ የሚላግጡትን የወያኔን ጭንብሉን ገለጥ ቢያደርጉት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ „ለታላቋ ትግራይ“ ሴራ እዬሰራ እዬተባበረ መሆኑን መገንዘብ ያስችለዋል። ማለት ትውልድና ሀገርን ከሚገድል ዶክተሪን ጋር ፈቅዶ ግን ሳይገባው ወይንም በግድዬለሽነት ተጋብቷል ማለት ነው። ይሄ ነው እውነቱ። ውጪ ያለውም ቢሆን የወያኔ ደጋፊነቱ ቁልጭ ባለ መልኩ ነገ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት እንዳይኖር አብሮ ከትሟል ማለት ነው። ለማን ሲባል? „ለታላቋ ትግራይ ልዕልና“ ሲባል።
ይህ ነገን ያበረክታልን? ፈጽሞ! ታላቅነታችን፤ ኃይላችን ሆነ ተፈሪነታችን ያለው ከኢትዮጵያዊነታችን ብቻ ነው። „የታላቋ ትግራይ ምሥረታ“ ህልም ሆኖ የሚቀር ብናኝ ነው። የልተባረከ የረከሰ መንገድ። ቀንና ብቃት፤ ፈቃድና መሆን ሲጋቡ ተኖ ሚቀር ግልብ ጭድ ህልም ነው።
አያችሁ ልብ ቢኖር አሁን ፍዳውን የሚያው ውዴ ልበለው እንዴት ብዕሩ እንደ ናፈቀኝ እኮ፤ ጋዜጠኛ አብርሃም ደስታ እንኳን ይሄን ስቃይ የመቀበሉ አመክንዮ ይሄ ነው። ታናሼ አብርሽ ነገ እንዲኖር ይፈልጋል። ዬሀገሩ ዬኢትዮጵያ ሉዕላዊነቷ ተከብሮ እንዲቀጥል ይፈልጋል። እናት ሀገሩ ኢትዮጵያ ወደብ እንዲኖራት ይሻል። ጦርነትን ባይፈቅደውም ግን ግድ ከሆነ ማደረግ እንደሚገባ አበክሮ ገልፆል። ወጣቱ መምህሩ ጸሐፊው ጋዜጠኛ አብርሃም ደስታ የለበጣ ሳይሆን „ግድ ከሆነ“ ብሏል። የእውነት መርህና የሃቅ ፍላጎት እርገትን በጽኑ ይሻል። የሚሰማውን ከውስጡ ሆኖ ፍርፋሪ ሳያስቀር እራሱን ውስጡን እንደ ህፃን ልጅ አሳይቶናል። ታዲያ ሰው እንዴት ከእሱ መማር አይችልም?!
„የታላቋ ትግራይ ራዕይ“ እኮ ለዚህ ጀግና ይቀርበው ነበር። ያ የሁላችንም ታናሽ ከዛ ረግረጋማ የጎሳ ዝልቦ እራሱን አውጥቶ እንሆ ለታላቋ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ቀለጠ። …. አብርሽ እንዲህ ሲያደርግ እኛ እንዴት በጥፋትና በምክነት ከበከተ የጎጥ ዶክተሪን ጋር እንሰለፍ?! …. ያሳፍራል ….
እያንዳንዱን የወያኔ ሃርነት ትግራይን ትልምና ጉዞ ስትበትኗት መርዝ አለው። እኛነትን፣ ማንነትን፣ ውስጥነትን፣ ወጥነትን አብሮነትን፤ ቤተሰባዊነትን፤ አርበኝነትን፤ ብሄራዊነትን፤ የኢትዮጵያዊነት፣ ፍቅራዊነት፣ ህይወታዊነትን የሚያጠፋ ማላታይን። ወያኔ እኮ ዲዲቲ ነው …..
ህሊና ቢኖር በማናቸውም ዘርፍ ጠላትን አውቆ ቆርጦ መለዬት የተገባ በሆነ ነበር። ነገ እንዳይመጣ አጥበቆ በሚሠራ የትውልድ መንጣሪ የፊት ለፊት ጠላት ቅርጥምጣሚ – ቅንጥብጣቢ ዬሆነ የመንፈስ እርሾ መለገስ ሰንድቅዓላማን መርገጥ ነው – ለእኔ። ይህ ጥቁር ዘመን ያልፋል። የማያልፈው ግን ለአደራ ሁነኛ መሆን ብቻ ነው። እንደ አርበኞቻችን የነፃነት ማገዶዎች። ሃቅን ፈልጎ፣ እውነትን ታጥቆ ነገን ከሚያጠፋ ጉያ ተለይቶ ለህሊና ማደር የቁም ጽድቅ ነው። ፓለቲከኛው ወጣት አቶ ሃብታሙ አያሌው ከዚህ የረድኤት እርከን ላይ ያለ ድንቅ ፍጡር ነው። ማዬት አይከፋም። አይቶ ግን ከረፋህኝ ብሎ በጊዜ መለዬት የሰውን ደረጃነት ያሰጣል። አብነትም ነው።
እኔ እንደማስበው ኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነት የለም ማለት አይቻልም። በሚገባ አለ ጦርነት። ጦርነቱ ዬሥነ -ልቦና ጦርነት ነው። ኢትዮጵያን እንደ ሀገር የማስቀጠልና ኢትዮጵያን ከዓለም ካርታ ዬማሰወገድ። ብሄራዊነትን የመደርመስና ጎሰኝነትን የማንገሥ። ይህ እንግዲህ 40 ዓመት ሁሉ የተሠራበት፣ የተደከመበት ደቂቃ ያልባከነበት የአጥፊው ወያኔ ሃርነት ትግራይ ማኒፌስቶ ቁልጭ ያለው አስፓልቱ ነው። ይህ መንገድ የጎረበጣቸው - ዕፀጹ ከተፈጠረበት ጀምሮ ይታገሉታል። ገዢ ሆኖም አልቀረለትም ጦርነቱ ቀጥሏል። ወራሪውም ባዶ እንስራውን አሸኮኮ አድርጎ አለ። ነገን እንዳይመጣ የሠራው ዳጥ እሱን ላጥ አድርጎ ያሰምጠውና ዘር አልባ አድርጎ አምክኖት ይቀራል። ምክንያቱም ፍልሚያው ከደም ጋር ነው። ደም – ቀለሙም ተግባሩም ተልዕኮውም ደም ነው። የደሙ መልክ ደግሞ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ነው።
ደምን ከእያንዳንዱ ዜጋ አውጥቶ የረከሰ ደም ማስገባት ፈጽሞ አይቻልም። እራሱ ሙከራው የማይቻል ከንቱነት ነው። በዚህ መንገድ መቀጠል አይቻልም።
እኔ አንድ ነገር አስባለሁኝ። ምንአልባትም ቀኑ እያለቀበት ሲመጣ፤ ወያኔ ማጣፊያው ሲያጥረው ከመሸ ከውስጥ እዬተጸዬፈ ግን እንደለመደበት ለማባጨል ንጹሑን ቅዱስ ሰንደቅዓላማችን ለብሶ ይመጣል እያለች ወፊቱ ሽክ እያለችኝ ነው። ሞላጫ ነው ስላችሁ። ግን ቢመጣ እንኳን በጽናት ፍላጎትን በውስጥ ጽላት አድርጎ፤ እናት ሀገር ኢትዮጵያ የአሳር መሞከሪያ የሆነውን የመፈተኛ ዘመኗ እንዲከትም ተግቶ ጠላትን ከነሥሩ ለመንቀል መሥራት አቅጣጫችን ሊሆን ይገባል – እላለሁ እኔው። ጎሳዊ አስተዳደር ታዬ አኮ – ከተከተን።
ዛሬ አንዲት ሳር ለኪስ አውላቂው ዬወያኔ ሃርነት ትግራይ ያቀበለ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁሉ የራሱን ውስጡን መፍረሱን ፈርሞቦታል። ሰው እንዴት ቤቱን – ቤተ መቅደሱን እንዴት ያፈርሳል – ፈቅዶ?! ለዛውም ከባንዳ ጋር ዶልቶ። የዚህ ሰላባ የሆነ ፍጡር የማንነቱም ጠላት ወያኔ ሳይሆን እራሱ ነው። ይህ ደግሞ ጭንጋፍነት ነው። በድኑን ቆሟል ማለት ነው። ውስጡ ሾልኮበታል። ስለምን? የሚሠራው አንድም ኢትዮጵያዊ ዜጋ አባል ለማይሆንበት ለወያኔ ሃርነት ትግራይ ድርጅት ነውና። ይህ ደግሞ ነገን አምካኝ ነው። ሰብዕናንም ያፋድሳል – ያሳድፋል። የነገ ማህጸን በወያኔ ሃርነት ትግራይ ዶክተሪን እንዲቃጠል ነው ዬሚፈለገው። ዘሃ ግራው ጠፍቶብን ከሆነ ንጥር ያለው ዕውነት ይሄ ነው …. ስለዚህ ቢያንስ መንፈስን ማሸፈት …. የወቅቱ መስመር ….. ሊሆን ይገባል። ለማን? ለምን? ግን እንዴት? – ውስጥን በመፈተሽ ከወርቅ እንክብሉ አመክንዮ ጋር መኖርን መምረጥ። ምርጫ ለራስ ነው ….
ክውና – የኔዎቹ እንሥራ – ለነገሩ በተለያዬ ጥፍጥፍ የወያኔ አፍራሽ ተግባር የሰለጠኑ የኛው ጉዶች እያሉ እንዴት መሥራት ይቻላል? ሁለት ሆኖ መሥራት አይደለም መታዬት እንኳን ችግር ነው እዬነው ነው ያለው ጉድ። ተያይዞ በመተኛት ያርፋሉ የእኛ ጉዶች ትንሽ ተግባር ሊያፈራ መነቃነቅ ሲጀመር ይባንኑና የወያኔውን ግልባጭ መርህ ተከትለው የተርትር ዘመቻቸውን በስልት ያሰነኩታል። ችግር ሆነ የማንነት መንፈስ እዬተገፋ – እዬተገፈተረ። ታማኝት እራሱ እዬተቃጠለ። የሆነ ሆኖ ከህሊና ጋር ኖሮ ማለፍ መኖር ነው። ከፊቱ ላይ ሆነው እኮ ነው የሰላም ትግል አርበኞች በድፍረት እዬታገሉ – እዬተቀቀሉ ያሉት …. ግን እኛ …. እምምምም …..////……
አብሶ ድርጅቶች ወኪሎቻቸውን የሚቆነጥጡበት ሥርኣት ያላቸውአይመስለኝም። ለእኔ ከአቅም ጋር የሚታገል የነፃነት ትግሉ ተወካይ የአረም ሾርባ ነው። ፈጠራ – ማደግ – መሻል ቀርቶ ሌላው ዬሚያንገበግበውን የተቃጠለበትን ዕንቡጥ ፍሬ ዘር በጋለ ማረሻ …. አዝናለሁ። የሚቻለውና ለውጤት የሚበቃው ለፍርሻም የማይደፈረው ብቻ ተሁኖ የሚሠራ ነገር ብቻ — በቃ! ሰዎ እኮ ተሰርቋል ልበል ይሆን? በነፃነት ሀገር እንደ ቃል ለመኖር እንኳን ፈተናውን መውደቅ – አዚም ይሆን? ወይንስ ምትኃት … እምታውቀውን አውሬ ስንት ቀን ሥጋ ታቀርበለታለህ – ሥጋውን ነጥቀህ ከባህር የወጣ አሳ ማደረግ እያለ። …. በሠለጠነ ዕሳቤ – በሰከነ ማስተዋል እንጂ በፉክክር ቤት አይሠራም። ደም ነፍስ ነውና!
ግን ጥቁር ለባሿ ኢትዮጵያ እሰከነ ምጧና እንባዋ በውስጥ አለችን? ወይንስ ዘብ ጠባቂ አደረግናት ይሆን? ይህ ማተብ የሚባለውስ የወያኔ መጋዝ በሞፈር ዘመት አቅም ኖሮት በጠሰውን? አይገባኝም? ያ የስቃይ መኖርን የሚያፋጥጥ የመከራ የወገን የቶርች ድምጽ ማህተሙ ተፋቀን? ከመቼው? እም!
ጨርስኩ – ኑሩልኝ የኔዎቹ። መሸቢያ ሰንበት!
ኢትዮጵያዊነት እዬነጠረ የሚሄድ ዬማንነት ዕንቁ ነው።
ደሜን ሳዳምጠው ውስጤን አገኘዋለሁ።
ለእኔ ስለፈቀድኩለት የባንዳ ቲወሪ አልጨፈረብኝም!
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።