Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ኢህአዴግ የሰራው ቤት! ግድግዳው ሰንበሌጥ!

$
0
0

ገለታው ዘለቀ

እንደ መግቢያ
ፌደራሊዝም የመንግስት ኣወቃቀር ሰፊ የቆዳ ስፋትና ብዙ ህዝብ ላላቸው ኣገሮች፣ በዛ ያሉ የተለያየ ቋንቋና ባህል ያላቸው ቡድኖች ላላቸው ሃገሮች፣ ተመራጭ ኣስተዳደራዊ መዋቅር እንደሆነ እጅግ ብዙ ሰው በዓለም ላይ ይስማማል። ፌደራሊዝም የተመረጠበት ዋናው ምክንያት ስልጣን እና ፍትህ ከህዝቡ እንዳይርቅ ነው። እንዳይርቅ ስንል ከመልክዓ ምድርም ከወረፋም ኣንጻር ነው። ትላልቅ የሆኑ ኣገሮች ስልጣንን ቢያማክሉ ዜጎች ለኣንዳንድ ጉዳዮች ስልጣን ወደተጠራቀመበት ለመሄድ ስለሚርቃቸው ብዙ ከሆኑ ደግሞ ሰልፉ ስለሚበዛ ወረፋው መጉላላትን ስለሚፈጥር ነው። ዜጎች ስልጣን ወርዶ ከፍተኛ የሆኑ ጉዳዮቻቸውን ሳይቀር በክልሎቻቸው እንዲታይላቸው መደረጉ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን ፍትህንና ኣገልግሎትን ለማደል በጣም ይረዳል። ስልጣን ተማክሎ የመካከለኛና ዝቅተኛ ደረጃ ባለስልጣናት እንደ ቧንቧ ማስተላለፍ ብቻ ከሆነ ስራቸው መንግስትና ህዝብ ልብ ለልብ ከመራራቃቸውም በላይ በውሳኔና በእቅድ ላይ ተሳትፎኣቸው ዝቅተኛ ይሆናል ኣገልግሎት ኣሰጣጡም ብዙ ችግር ይገጥመዋል።። ሌላው ደግሞ የተለያየ ባህልና ቋንቋ ያላቸው ቡድኖች በተለያየ መልክዓ ምድር ለብቻ ለብቻ ሰፍረው ነገር ግን ደግሞ ኣንድ ኣገር መስርተው እየኖሩ ከሆነ እንዲሁ ባንድ በኩል ባህላቸውንና ቋንቋቸውን ጠብቀው በኣንድ ሃገር ጥላ ስር እንዲኖሩ የሚረዳ መሆኑንም ሁሉም ይረዳል። ኢትዮጵያ ካላት የቆዳ ስፋትና ካላት የህዝብ ብዛት እንዲሁም ካላት የቡድኖች ብዛት ኣንጻር ፌደራሊዝም ተመራጭ ኣስተዳደር መሆኑን እጅግ ብዙ ሰው ያምናልና በዚህ ላይ ውይይት ኣስፈላጊ ኣይደለም።

eprdfበዚህች በዛሬዋ መጣጥፌ የማስተላልፈው መልእክት ፌደራሊዝም ጠቃሚነቱን ለመግለጽ ሳይሆን ኣቶ መለስ ዲዛይን ኣደረጉት ወይም በሳቸው ምህንድስና ተዋቀረ የተባለውን የዛሬይቱን ኢትዮጵያን የፌደራል ኣወቃቀር ትንሽ መተቸት እፈልጋለሁ። መተቸትም ብቻ ሳይሆን ምን ኣልባት ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሊጠቀሙበት ይችሉ ይሆናል በሚል ተስፋ ኣማራጭ የፌደራል ኣወቃቀር ኣሳብ ለማቀበል እሞክራለሁ።

የኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት

የኢትዮጵያ ፌደራል ሲስተም ተፈጥሮ በሚገባ ከሚገለጽባቸው ጉዳዮች መካከል ኣንዱ የክልሎች መንግስታት ኣወቃቀር ነው። እነዚህ መንግስታት ሲዋቀሩ መስፈርቱ ምን ምን እንደሆነ ማወቅ የኢትዮጵያን ፌዴራል ስርዓት ለመረዳትና ለመገምገም ይጠቅማል። ኣቶ መለስ ዲዛይን ያደረጉትን ይህንን የክልል ኣፈጻጸም ብዙ ሰው የሚገልጸው በብሄር ፌደራሊዝም(Ethnic federalism) ነው። በርግጥም የፖለቲካውን ኣወቃቀር ስናይ ማለትም የፖለቲካው እግሮች(radicals) በብሄር ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ፌደራሊዝም ካለ የብሄር ፌደራሊዝም ነው ያለው ለማለት ያስችለናል። ይሁን እንጂ የክልል መንግስታቱ ኣመሰራረት በምን ላይ እንደቆመ ማየት ደግሞ የመንግስትን ተፈጥሮና ፍላጎት ለማየት ይረዳናል። ስለዚህ የነዚህ የዘጠኝ ክልሎች መንግስታት ምስረታ ይህንን የብሄር ፌደራሊዝም የተባለውን መርህ ተከትሎ ነው ወይ የተፈጸመው ብለን ማየት ተገቢ ነው። የገዢው መንግስት ኣካላትና ደጋፊዎቻቸው እንደሚገልጹት የክልል መንግስታት ምስረታው ራስን በራስ ማስተዳደርን መሰረት ያደረገ፣ ማንነትን ያገናዘበ፣ የብሄር ብሄረሰቦችን መብት ያገናዘበ እንደሆነ በኣጠቃላይም በብሄር ፌደራሊዝም(Ethnic federalism) ሊገለጽ እንደሚችል ይስማማሉ።

የብሄር ፌደራሊዝም በምሁራንና በኣብዛኛው ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ነቀፌታ ያለበት ቢሆንም መንግስት ግን በተለይ የብሄር ብሄረሰቦችን “ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን” እንዳጎናጸፈለት ደጋግሞ ይገልጻል። ኣጥብቀው ለሚቃወሙት ወገኖች ደግሞ የብሄር ፌደራሊዝም እኛ ጋር ብቻ ኣይደለም ያለው ስዊዘርላንድን፣ ህንድን፣ ቤልጂየምን ተመልከቱ እነሱም በብሄር ላይ የተመሰረተ ፌደራሊዝም ነው ያላቸው ይላል። በመሰረቱ ግን የነዚህን ኣገሮች ኣወቃቀር በሚገባ ማየት ያስፈልግ ይመስለኛል። ርግጥ ነው ስዊዘርላንድ ምንም እንኳን የህዝብ ብዛቱዋ ትንሽ ቢሆንም ጀርመንኛ ተናጋሪዎችን፣ ጣሊያንኛ ተናጋሪዎችን፣ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎችንና ሪሂቶ ሮማንስን በሃያ ስድስት ካንቶኖች ከፋፍላ በባህላዊ ኣስተዳደር እያስተዳደረች ያለች ኣገር ናት። ። ስዊዘርላንድ ውስጥ ያለው ይህ ቋንቋን የተከተለ ኣከላለል ባንድ በኩል ባህልን እየጠበቁ በሌላ በኩል ለኣስተዳደር ኣመቺነቱን በማየት ነው። የስዊዘርላንድ ኣከላለል ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ሳይሆን ኣስተዳደራዊ ኣመቺነትን በማየት ነው። በብሄር በፖለቲካ መደራጀትን የስዊዘርላንድ ህግ ይከለክላል። ከኢትዮጵያ የሚለየው በዚህ ነው። የኢትዮጵያ የክልሎች ኣወቃቀር በብሄር ፖለቲካ ላይ የተመሰረተ ፌደራሊዝሙም የሚመነጨው ከዚህ ኣስተሳሰብ ነው።ዋናው ፍልስፍናቸውም “ብሄሮች ራሳቸውን በራሳቸው ያስተዳድሩ” የሚል ፖለቲካዊ ኣስተዳደርን የሚመለከት በመሆኑ ነው ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ነው የሚያሰኘን። የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም ከዚሁ ከብሄር ፖለቲካ ኣስተሳሰብ የመነጨ ሲሆን የስዊዝ ደግሞ በኣንድ ብሄራዊ ፖለቲካዊ ማንነት ጥላ ስር ያደረ ባህላዊ ኣስተዳደር ተደርጎ ነው ሊወሰድ የሚችለው። ስዊዘርላንድ ከላይ እንደ ጥላ የረበበ ኣንድያ ጠንካራ ማንነት ያላት ሲሆን ኢትዮጵያ በኣሁኑ ጊዜ ብሄራዊ ማንነቷ የት እንዳለ የት እንደተጠለለ በሚገባ ኣይታይም። ለዚህም ነው ብዙ ኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያዊነታችንስ? የት ጣላችሁት? ….ወዘተ. እያሉ የሚያጉረመርሙትና ፍለጋ የገቡት:: በኢሕ ኣዴግ ዘመን ኢትዮጵያዊነት የት ኣደረ? የት ነው ያለው? ብለን ኣጥብቀን ከጠየቅን ኢትዮጵያዊነትን ኣድሮ የምናገኘውና ብሄራዊ ማንነት የሚገለጸው በብሄር ፓርቲዎች ግንባር ደረጃ ነው። ኢሕ ኣዴግ ኣይዲዮሎጂ በሌላቸው የብሄር ፓርቲዎች የተገነባ ግንባር ሲሆን የግንባር ተፈጥሮ ደግሞ ለኣንድ ለተወሰነ ዓላማ የሚሰባሰቡበት ድርጅት ነው። በርግጥ ኢሕዓዴግ የሚባለው ራሱ በዓለም ላይ ኣለ ወይ? የሚለውን ፍልስፍናዊ ጥያቄ ለጊዜው ቁጭ ኣርገነው ግንባር የሚመሰረተው ለኣንድ ለተወሰነ ዓላማ ነው። ግንባር የመሰረቱ ድርጅቶች መንግስት የመጣል ተፈጥሮ ካላቸው እስኪጥሉ ኣብረው ይታገሉና ከዚያ በሁዋላ ወይ ይዋሃዳሉ ወይ በየፊናቸው ይቀጥላሉ። ግንባር በተፈጥሮው ኣድራሽ ነው። ዘላለማዊ ኣይደለም። ትልቁ ችግር ግንባር መሆኑ ብቻ ሳይሆን በብሄር ድርጅቶች የተፈጠረ ግንባር መሆኑ ነው። ኢሕ ኣዴግ ስልጣን ሲይዝ ወይም መንግስት ሲመሰርት ይሄው የግንባር ተፈጥሮው ይንጸባረቃል። ኣንቅጽ ሰላሳ ዘጠኝም የዚህ ተፈጥሮ ውጤት ይመስላል። እስከ ተወሰነ ኣብረን ግንባር ፈጥረን እንሄዳለን ካልሆነ እንለያያለን ኣይነት ነው ነገሩ። ብዙ ጊዜ የመንግስት ተወካዮች ኢህዓዴግ ስልጣን ከለቀቀ ኣገሪቱ ትበታተናለች ብለው የሚናገሩትና የሚያምኑት እነሱ የፈጠሩዋት ኢትዮጵያ ብሄራዊ ማንነት በግንባር ደረጃ ተውሸልሽሎ ያለ በመሆኑ ይሄው እየታያቸው ሊሆን ይችላል። ስዊዘርላንድ ምንም እንኳን ክልል የሰራችው በቋንቋና በባህል ላይ ቢሆንም ፖለቲካዊ ጨዋታዋ ግን በኣንድ ጠንካራ የፖለቲካ ማንነት ጥላ ስር ነው። ይህን ብሄራዊ ማንነት ትቶ በብሄር ማንነት ላይ የፖለቲካ ቤት መስራትና የጀርመንኛ ተናጋሪዎች የፖለቲካ ድርጅት የፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች ድርጅት የሚባል ነገር በህግ ክልክል ነው።ግንባር ነኝ የሚለው ኢህዓዴግ ኢትዮጵያን በግንባር የፖለቲካ ኣስተሳሰብ የሚያስተዳደር ሲሆን እስከ መቼ ለሚለው ጥያቄ መልሱ ኣይታወቅም።ይህ ኣንቀጽ ሰላሳ ዘጠኝ ለማስፈራሪያ ተቀምጦም ከሆነ ማንን ለማስፈራራት እንደተቀመጠም ኣይታወቅም። ጉዳዩ በማስፈራራት ወይም ካልሆነ እንለያያለን ብለን ሰለጻፍን ዋስትና ኣይሆነንም።
EPRDF
የዚህ ዘመን ኣስተዳደራዊ ችግር የሚመነጨው ከፖለቲካው የመጀመሪያ የእምነት ምንጭ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ የብሄር ፖለቲካ እምነት ዋናው መነሻ ስነ -ህይወታዊ (DNA and genealogy)ጉዳይን ኣጥብቆ የያዘ መሆኑ ነው። በዚህ ኣሳብ ልብ ውስጥ ያለው ጉዳይ ኣንድ ሰው ኣገር ለሚለው ጽንሰ ሃሳብ ማሰብ ሲጀምር ከታች እንዲጀምር ነው የሚበረታታው። ቤተሰብ፣ ዘመድ ኣዝማድ፣ ጎሳ፣ ብሄር ከዚያ ኣገር እያለ ከታች ወደ ላይ የሚሄድ እምነት ነው። የህወሃት ሰዎች የደም ጉዳይ ነው…… ተፈጥሮ ነው…… ምን እናድርገው? ይላሉ።እርግጥ ነው ስነ-ተፈጥሮኣዊ እውነት ኣለ። ኣንድ ሰው ለቤተሰቡ ማለትም ለወንድሙ፣ ለእህቱ፣ ለናቱ፣ ላባቱ ወዘተ. የሚራራና የሚታመን ቅርብ ልብ ኣለው። ከዚያም ከፍ ሲል ለዘመዶቹ ከዚያም ባህል ኣቋራጭ (cross cultural) ጉዳይ ሲመጣ ለባህላዊ ቡድኑ ተቆርቋሪ መሆኑ ተፈጥሮኣዊና ስነ-ተፈጥሮኣዊ ሊሆን ይችላል።ይሄ ኣይካድም። የብሄር ፖለቲካ ይህንን ስነ ህይወታዊ ትንታኔ ይዞ ነው ፖለቲካዊ ይዘት ያለበሰው። ከዚህ ጽኑ የጄነቲክ እምነቱ የተነሳም ብሄሮች በራሳቸው ባህላዊ ቡድን ኣባል ኣስተዳደራዊ መዋቅር ቢዘረጉ ኣስተዳደሩ ርህራሄ ይሞላዋል፣ ችግርን መረዳት ይኖራል፣ ከፍተኛ ተግባቦት ይኖራል፣ ስለዚህ በተወላጁ መተዳደሩ ተፈጥሮኣዊ መሰረት ያለው ነው የሚል እምነት ያለ ይመስላል።ይሄ መሰረታዊ የብሄር ፖለቲካ ፍልስፍና በርግጥ ገዢውን መንግስት ኣብከንክኖታል ወይ? የሚለውን እንተወውና በኣጠቃላይ የብሄር ፖለቲካ እምነት ምንጩ እንደዚያ ነው። የዚህ የብሄር ፖለቲካ መሰረታዊ እምነት ግን ትልቅ ችግር ያለበት ነው። ችግሩ ምንድነው? ካልን የዴሞክራሲና የፍትህ ተፈጥሮ ከዚህ መሰረታዊ እምነት ጋር ኣብሮ ኣለመሄዱ ነው። ዴሞክራሲና ፍትህ ከላይ ሆነው ነው የምናያቸው። ፍትህና ዴሞክራሲ መርህ ነው ወገናቸው። ጀነቲክ ወይም የደም ሃረግ ጉዳይ ዓይደለም። ዴሞክራሲ ኣስተዳደሩን ሲዘረጋ በብዙሃን ድምጽ ከላይ ይነሳና ወደ ታች እስከ ግለሰብ ድረስ ወርዶ፣ የልዩነት የመጨረሻው ቅንጣት እስከ ሆነው የግለሰቦች የተለያየ ተሰጥዖ፣ችሎታና ምርጫ ድረስ ወርዶ እንክብካቤ የሚያደርግ ስርዓት ነው። እነዚህ ሁለት የሃገር ዋልታና ማገሮች ማለትም ፍትህና ዴሞክራሲ ከዚያ ከብሄር ፖለቲካ ጋር የሚጻረሩት በዚህ ነው። ኣንዳንዴ ወንድምህና ኣንድ የማታውቀው ሰው በፍትህ ፊት በዴሞክራሲ ፊት ቆመው ሳለ ወንድምህ ካጠፋ በወንድምህ ላይ ትፈርድ ዘንድ ያስገድድህና የባዮሎጂውን የርህራሄ የምናምኑን ጉዳይ ይሰብረዋል። የጀነቲኩን ጉዳይ ኣደባባይ ላይ ሳያወጣ ግለሰባዊ ኣድርጎት ቁጭ ይላል። በመሆኑም ዴሞክራት መሪዎች በኣስተዳደር ጊዜ ከላይ ይሆኑና የተፈጥሮ ሃላፊነታቸውን ከዘመዶቻቸው ጋር የሚወጡት በጓዳ ነው። ንስር በተፈጥሮው ከፍ ብሎ ይበራል። ከፍ ብሎ እየበረረ ወደ መሬት ጥቃቅን የሆኑ ነገሮችን ነጥሎ የማየት ችሎታ ኣለው። ዴሞክራት መሪዎች የዴሞክራሲንና የፍትህን መርሆዎች ከላይ ይዘው ታች የግለሰቦችን ህይወት የሚነካ ስራ ይሰራሉ። የብሄር ፖለቲካ መሪዎች ደግሞ ጄነቲክ የሆነውን ተፈጥሮኣዊ የጓዳ ግንኙነት የፖለቲካ ቤት ሰርተው ኣደባባይ ኣውጥተው ደግሞ በሌላ በኩል ዴሞክራሲን በሌላ እጃቸው ለመጎተት ሲሞክሩ ይታያል። በኢትዮጵያ ውስጥ ኣሁን ያለው ግጭት ይሄ ነው። የዚህ የብሄር ፖለቲካ ኤነርጂ ለዴሞክራሲ ያልተመቸውም በዚህ ነው። በእንዲህ ዓይነት መሬት ላይ ዴሞክራሲ ቢዘራ ኣይበቅልም። የዴሞክራሲና የብሄር ፖለቲካ ተፈጥሮ ኣብሮ ባለመሄዱ ነው ዛሬ ዴሞክራሲ በሃገራችን የጠፋው። ከፍ ሲል እንዳልኩት የህወሓትና የሌሎች ብሄር ተኮር ድርጅቶች ችግር የእምነት ችግር ነው። ይህ እምነት ደግሞ ባዮሎጂካዊ እውነት ቢኖረውም ኣስተዳደራዊና ፖለቲካዊ መልክ ሲይዝ ጥሩ ኣይደለም። የብሄር ፖለቲካ በዓለም ታሪክ ውስጥ ብዙ ኪሳራ ኣምጥቱዋል።የብሄር ፖለቲካ ኣራማጆች ካደጉበት መንደር ወጥተው ኢትዮጵያን በሙሉ ዓይን ማየት መጀመር ካልቻሉ የኢትዮጵያን ኣንድነት መረዳት ያዳግታቸዋል። ታላቋ የሰብአዊ መብት ተሟጋች የተባበሩት ህዝቦች የስደተኞች ድርጅት (UNHCR) መልካም ፈቃድ ኣምባሳደርና የፊልም ተዋናይ ኣንጀሊና ጆሊ በኣንድ ወቅት የተናገረችውን ቁምነገር እዚህ ጋር መጥቀስ ኣስፈላጊ ይመስለኛል።

“If you don’t get out of the box you’ve been raised in, you won’t understand how much bigger the world is” Angelina Jolie

eprdf_meetingሌላው የዚህ የፌደራሊዝም ምህንድስና ጉዳይ ሲነሳ የኢትዮጵያን ኢሜጅ የማስተካከልም ስራ ነው። የኢትዮጵያን ብዙነትና ኣንድነት ማሳየት የሚችል የፌደራል ስርዓት ያስፈልጋል። የኣሁኑን ስርዓት ስናይ ኢትዮጵያን የሚገዛት የብሄር ፖለቲካ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የሚያሳዝነው የብሄር ፖለቲካው ኣምባገነን መሆኑ ነው። በዚያው በብሄር ከተደራጁት መካከል ኣንዱ ሲበዛ ሃይለኛ ሆኖ በኣምባገነንነት ይኖራል። ለስሙ የብሄር ጉዳይ ይግነን እንጂ ኣንድ ሃይለኛ ፓርቲ በየቡድኑ የተወከሉትን ኣስተዳዳሪዎች የሚቆጣጠርበት እንደፈለገ የሚያደርግበት ሁኔታ በመሆኑ ስልጣን በተግባር ያለ ልክ ተማክሎ ነው የሚታየው። ይሄ ችግርም የዚሁ የብሄር ፖለቲካ ተጽእኖ መገለጫ ነው። እንደዚህ ዓይነቱ ፖለቲካ ባለበት ምድር ዳይቨርስ የሆኑ ከተሞች እንደ ኣዲስ ኣበባና ሌሎች ከተሞች ችግር ውስጥ ይገባሉ። ኣጠቃላይ የሆነው ኣስተሳሰብ ቢያንስ ወደ ማንነት ድምጽ(Identity Voting) ሊመራቸው ይችላልና በምርጫዎች ላይ ጥላ መጣሉ ኣይቀርም።ኣንድ ሰው ኣዲስ ኣበባ እየኖረ በመታወቂያው ላይ ኣማራ… ትግሬ…. እየተባለ መጻፉ የዚህ ኣስተሳሰብ ውጤት ነው። ፓለቲካው ኣስተዳደራዊ ጉዳይን ከማንነት ጋር ስለጨፈለቀው የፖለቲካ ሰዎች ለምርጫ ሲቀርቡ የብሄር ዳራቸውን የማወቅ ፍላጎት በዜጎች ዘንድ ከማደሩም በላይ ከተመራጩ ታለንትና ፖለቲካዊ ብቃት ይልቅ ለጄነቲክ ጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ ስለሚገፋ ዜጎች ለማንነት ድምጽ(identity voting) መጋለጣቸው ኣይቀርም ከዚያም ጋር ተያይዞ ለሚመጣ ሃሜትና ጉምጉምታ መጋለጣቸውም ኣይቀርም በውጤቱም ኣጠቃላይ የዴሞክራሲን ባህል እያጠፋ ይሄዳል።የህዝቡን ስነ ልቦናም ያበላሻል።ኣክቲቪስቶች ሳናውቀው የዚህ ፖለቲካ ሰለባ እንዳንሆን መጠንቀቅ ኣለብን። ሳናውቀው ሰለባ ከሆንን ኣዲስ ኣበባ ኣካባቢ ሁለት ሰው ሲሞት የምንጮኸውን ያህል ኦጋዴን ወይም ጋምቤላ በጅምላ ሲጨፈጨፉ ኣዘናችን ያን ያህል ላይሆን ይችላል።
የብሄር ፖለቲካ ችግሩ የመነሻው እምነት ነው ብለናል።ዴሞክራሲስ እምነት ኣይደለም ወይ? የሚል ጥያቄ ይነሳል።በርግጥ ዴሞክራሲ ይልቃል ስንልም በእምነት ነው። በዴሞክራሲ ላይ ስንቆምም በዴሞክራሲ ላይ ታምነን ነው። ልዩነቱ ዴሞክራሲ በተፈጥሮው የቆመበት መሰረት ከጄነቲክ፣ ከባህልና ቋንቋ መሰረት በላይ በሰው ግለሰባዊ ስብእናና ታለንት ላይ በመታመን ፍትህን ማደል ሲሆን በጋራ ምርጫ ጊዜ ደግሞ ኣንድ ሰው ለኣንድ ድምጽን መሰረት ያደረገ ነጻ ምርጫ ኣድርጎ በድምሩ ኣብላጫ ያለውን ድምጽ ኣሸናፊ በማድረግ ተሸናፊው የኣሸናፊውን ድምጽ ኣክብሮ በጋራ እስከ ቀጣዩ ምርጫ መስራት ነው። ዴሞክራሲ ከላይ ሆኖ የሚያይ በመሆኑ በዚህ ጥላ ስር ዜጎች ቢያርፉ እረፍትና መተማመን ሊያመጣላቸው ይችላል የሚል እምነት ነው ያለው። ይህ እምነት ደግሞ በተግባር ተፈትኖ የወጣለት በመሆኑ ነው የምንመርጠው። ከሁሉም በላይ ከዘመኑ የሰው ልጆች ኣስተሳሰብ ደረጃ ጋር ኣብሮ መጓዝ የቻለ የኣስተዳደር ጥበብ ሆኖ በመገኘቱ ነው ይህን እምነት የበለጠ እንድናምነው የሚያደርገን። ሌላው ከፍ ሲል እንዳልነው የዚህ የብሄር ፖለቲካ እምነት የፍትህ ኣሳላፊዎቹን ብሄራዊ ማንነት ለማወቅ በፍትህና ኣገልግሎት ፈላጊዎች ዘንድ ፍላጎት እንዲሰርጽ ማድረጉ ነው። በዴሞክራሲ ጊዜ ይህ ስሜት ጨርሶ ይጠፋል ማለት ኣይደለም። ይሁን እንጂ ከላይ ያለው የዴሞክራሲ መርህ ለዜጎች መተማመኛ ስለሆነ በኣንዳንድ ሰዎች ስሜት ላይ ሊጎላ የሚችለውን ችግር ተጠያቂነት የሚባለው ነገር ስላለ ይህንን ስሜት ያደበዝዘዋል፣ ቀስ እያለ ዴሞክራሲ ባህል እየሆነ ሲመጣ ደግሞ ይህ ስሜት እየከሰመ ይሄዳል።የኢትዮጵያን ኢሜጅ ስናስብ የኣንድ ብሄር የበላይነት የነበረባት ኣገር ከነበረች ኣሁን ደግሞ የበለጠ ስም ኣውጥቶ የሌላ ኣንድ ብሄር የበላይነት ካለ ለውጥ የለም። የኢትዮጵያ ኢሜጅ የሚስተካከለው በዴሞክራሲና በፍትህ ነው። ዜጎች እንደ ዜጋ ቡድኖች እንደ ቡድን እኩል ሲሆኑ የቡድኖች ትንሽና ትልቅነት ሲጠፋ ፍትህ ሲበየን የሃገሪቱ ኢሜጅ ይስተካከላል። መቶ የፖለቲካ ፓርቲ በየስማችን ማቋቋሙ የኢትዮጵያን ኢሜጅ ኣያሳይም። ካሳየም የተበታተነች ኣገር መሆኑዋን ነው። ባህላዊ ማንነትንና ፖለቲካዊ ማንነትን መለየት ያስፈልጋል ። ብዙ ኣገሮች እምነትንና ኣስተዳደርን ለይተው ይታያል። በኢትዮጵያ ህገ መንግስትም ኣንቀጽ ኣስራ ኣንድ ላይ ሃይማኖትና መንግስት መለያየታቸውን ይገልጻል። ልክ እንደዚህ ኢትዮጵያ ባህላዊ ማንነትንና ፖለቲካዊ ማንነትን መለየት ኣለባት ለዚህም ኣንቀጽ ኣስራ ሁለት ብላ እነዚህ ጉዳዮች መለያየታቸውን ማስመር ኣለባት።

መጀመሪያ ወደ ኣነሳነው ጉዳይ እንመለስና ለዛሬው የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም ሌላዋ የኢህዓዴግ ምሳሌ ደግሞ ህንድ ናት:: እውነት ነው በርግጥ ህንድ ውስጥ የክልል ፓርቲዎች ኣሉ:: ኢትዮጵያ ውስጥ ህወሃት ብዓዴን ወዘተ. እንደሚባለው ህንድም ውስጥ የክልል ወይም(state or local parties) የሚሉዋቸው ፓርቲዎች ኣሉ።። ይሁን እንጂ ስልጣኑን የያዘውና እጅግ ኣብዛኛውን መቀመጫ የተቆጣጠረው ብሄራዊ ኣጀንዳ ያለው በዚህ ኣመት ለጠቅላይ ሚንስትርነት በተመረጡት ናረንድራ ሞዲ የሚመራው BJP የተሰኘው ብሄራዊ ፓርቲ ሲሆን የክልል ፓርቲዎች ተሰሚነታቸው በጣም ዝቅተኛ ነው።በያዝነው ኣመት ህንድ ውስጥ በነበረው ምርጫ ቀደም ባሉት ጊዚያት ከተለያዩ ፓርቲዎች ጋር ውህደት ፈጽሞ ተጠናክሮ የወጣው BJP ፓርቲ ኣምሳ ኣንድ ነጥብ ዘጥኝ በመቶ የሚሆነውን ኣጠቃላይ ምርጫ ያሸነፈ ሲሆን ሌሎች ከፍተኛ መቀመጫ የያዙትም ብሄራዊ ፓርቲዎች ናቸው። የክልል ፓርቲዎች እዚህ ግባ የማይባል ውጤት ነው ያላቸው። በኣጠቃላይ ህንድ በብሄራዊ ፓርቲዎች የመንፈስ ልእልና የምትመራ ኣገር ስትሆን ብሄራዊ ፓርቲ ቢዳከምና የክልል ፓርቲ ቢያብብ በርግጥ ህንድም ኣደጋ ላይ መውደቋ ኣይቀርም። ነገር ግን የሚመስለው ህንዶች የክልል ፓርቲዎችን ለጊዜው ዝም ያሉዋቸው ሲሆን በምርጫ እየቀለሉ ቀስ እያሉ ይጠፋሉ ከሚል ዘዴም ሊሆን ይችላል እንጂ ህንድም ብትሆን የማንነት ፖለቲካን የምታበረታታ ኣገር ኣይደለችም።ማሌዢያን ብናይ በርግጥም በዘር ላይ የተመሰረቱ ወይም ስያሜያቸው ከዘር ጋር የተያያዘ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኣሉ። ጠንካራ የሆነ ፓርቲ ቢኖራቸውም በብሄር ላይ የቆሙት ፓርቲዎች የኣድቫንቴጅ ጥያቄዎችን በየጊዜው እንዲያነሱ ያደርጋቸዋል። በህንድና በማሌዢያ የዚህ የብሄር ፖለቲካ ክፉ ውጤት ጎልቶ ካልታየባቸው ጉዳዮች መካከል ኣንዱ የኢኮኖሚው እድገትም ይመስላል። ዜጎች የኢኮኖሚ ሁኔታቸው ሻል ሲል ዘንጋ ቢሉም የኢኮኖሚው ሁኔታ መናጋት ሲጀምር እንደ እምቅ ችግር ሆኖ መነሳቱ ዓይቀርም። በቅርቡ የእስያ ሪቪው እንደዘገበው የማሌዢያ ኢኮኖሚ መውደቅ ሲጀምር ዘረኝነት ብድግ ማለቱን ገልጹዋል። በዘር ላይ የቆመ ፖለቲካ ሲኖርና የሪሶርስ ማነስ ሲሰማን ያ በዘር ላይ የቆመው ፖለቲካ ድርጅት ስልጣኑን ተጠቅሞ ወገኑን ይረዳል ብለን መጠርጠር የመጀመሪያ የዓመጽ መነሻችን እንዲሆን ሊያደርግ ይችላል። የትም ሃገር በብሄር ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ የሚያራምዱ ሁሉ መውጫ ፍለጋ እየጣሩ እንጂ ተደስተው ኣይኖሩም። ብሄራዊ ማንነታቸው ተናግቶ፣ ፍትህ ቀጭጮ ተቸግረው ነው ያሉት።

ቤልጂየምም ብትሆን ከኢትዮጵያ የተለየች ናት። በዘውዳዊ ህገመንግስት (constitutional monarchy) ስር ያሉ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢኖሩም ኣንድ ከላይ የረበበ ብሄራዊ ኣንድነት ይዙዋቸው ይታያል። ስለ ህገመንግስታዊ ሞናርኪ ሳስብ ለእኔ የሚመስለኝ፣ ያልተጻፈ ቢሆንም፣ ምንም እንኳን ከዘውዳዊ ኣገዛዝ ወደ ዘመናዊነት መሸጋገር ያማራቸው ኣገሮች ኣዲሱ ትውልድ በኣንድ ወቅት ዘውዳዊ ኣባቱን ኣሁን እኔ ኣዲስ ኣስተዳደር ተገልጦልኛል፣ ዴሞክራሲ በተባለ ጥበብ ኣገሪቱን ላስተዳድር ነው ብሎ ለውጥ ሲጀምር ዘውዳዊ ኣገዛዙን በስምምነት ኣስተዳደራዊ ጉዳዮችን እንዲሰጠው ጠየቀ ማለት ኣዲስ የሚመጣው ኣስተዳደራዊ ስርዓት፣ ዳይናሚክ የሆነው ጥበብ ፣ ሉዓላዊነትን ከዘውዱ ይነጥቃል ማለት ኣይመስለኝም። ዘውዱ ኣሁንም የኣገሪቱን ሰማይና የብስ የሚገዛ ይመስለኛል። ኣልገባኝ እንደሆን ኣላውቅም። ለማናቸውም ግን ዘውዳዊ ኣገዛዙን ያልገደሉ ዘመናዊነት ሲመጣ ወደ ህገ መንግስታዊ ዘውዳዊ ኣገዛዝ ሲመጡ በህገ መንግስት ብዙውን ኣስተዳደራዊ ስልጣን ኣዲስ ነገር ተገልጦልኛል ላለው ትውልድ ቢሰጠውም ልእልናው ግን ኣለና ያ ልእልና የኣንድ ሃገር ብሄራዊ ማንነትን ሊገልጽ የሚችል ከላይ የረበበ ጥላ ሊሆንላቸው ይችላል:: የዳር ድንበርን (territorial integrity) ጉዳይ በህይወት ሆኖ ታሪክን የሚያስታውስ ይመስለኛል። የቤልጂየም ንጉስ ፊሊፕ ኣንድነትን ሲያበረታቱ ነው የምናየው። ይህም የቤልጂየም ዘውድ ለኣንድነታቸው መገለጫ መሆኑን ያሳያል። ኢትዮጵያ በ1960ዎቹ ጊዜ የሆነ ኣዲስ ነገር በራልኝ ያለው ትውልድ ዘውዱን በድንጋይ ስቶ ሲያበቃ ወታደር ሲመጣ በጥይት ብሎ ስለገደለ ብሄራዊ ኣንድነታችንን የምንገልጽበት ምልክት (symbol) በብሄር ፖለቲካ ጊዜ የለንም።

ኔፓል እንደሚታወቀው እንደ ኢትዮጵያ ብዙ የተለያየ ቋንቋና ባህል ያላቸው ቡድኖች የሚኖሩባት ኣገር ናት። ይህቺ ኣገር በ 2008 ዓ.ም ከፍጹም ዘውዳዊ ኣገዛዝ ከተላቀቀች በሁዋላ ኣዲሲቱዋን ኔፓልን በምን መንገድ ኣዋቅረን እንቀጥል የሚለው ጉዳይ እስካሁን ያልተቋጨ የኔፓሊስ ሌሂቃን የቤት ስራ ሆኖ ይታያል። የማኦይስቶች እምነትና ግፊት ኔፓል በብሄር ፌደራሊዝም እንድትተዳደር ሲሆን የኔፓል ኮንግረስ ፓርቲ መሪና የኣሁኑ ጠቅላይ ሚንስትር ሶሺል ኮይራላ ግን ይህን ኣሳብ በጥብቅ እየተቃወሙ ነው። የኔፓል ኮንግረስ ፓርቲ በሃገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የፖለቲካ መሰረት(constituency) ያለው ሲሆን ይህ ፓርቲ የብሄር ፌደራሊዝም በዓለም ላይ ግጭትን ያመጣ በመሆኑ ኣዲስ ሊፈጥሩት ባሰቡት ህገ መንግስት እንዳይካተት እየወተወቱ ነው።

እንዲህ ዓይነት በማንነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ብዙህ በሆኑ ሃገሮች ቀርቶ ሆሞ ጂኒየስ በሆኑ ኣገሮችም እንኳን ጥሩ ኣይደለም። በዓለማችን ላይ እንደምናየው በሃይማኖት ማንነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ በሚያራምዱ ኣገሮች ውስጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በሰፊው ከመስተዋላቸውም በላይ በኣንዳንድ ኣካባቢዎች ጽንፈኞችን እያፈራ እንደነ ኣልቃይዳ፣ ኣይ ኤስ ኣይ ኤስ (ISIS)፣ ኣልሽባብ፣ህዝቦላ፣ሃማስ የመሳሰሉትን ለዓለም ህዝብ ስጋት የሆኑ ድርጅቶችን ፈጥሮኣል። በዚህ በሃይማኖት ማንነት ላይ የሚመሰረትን ፖለቲካና በሃይማኖት ማንነት ላይ የሚገነባ ብሄራዊነትን በተመለከተ በዓለም ላይ ትኩረት ያገኘ ሲሆን በባህላዊ ማንነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ኣደገኛነቱ ብዙም ትኩረት ያገኘ ኣይመስልም። የማንነት ፖለቲካ ሃይማኖታዊም ይሁን በብሄር ላይ የተመሰረተ በዓለማችን የሁዋላ ታሪክ ውስጥ ጥሩ ምስክርነት የለው። የዓለምን የዘር ማጥፋት ታሪክ ብንመረምር በዓለም ላይ ከተፈጸሙት የዘር ማጥፋት ወንጀሎች መካከል ኣብዛኛዎቹ በኣንድም በሌላም መንገድ ወይ ሃይማኖታዊ ወይ ደግሞ ከብሄር ፖለቲካ ጋር በተያያዘ የመጣ ጥፋት ነው። በኣርመን፣ በሩዋንዳ፣ በናይጄሪያ፣ በቦስኒያ፣የተፈጸሙትን ወንጀሎች መጥቀስ ይቻላል። በጣም የታወቀው የሆልኮስት የዘር ማጥፋት ወንጀል መነሻም እነ ሂትለር ያመጡት ዘረኝነትን ሳይንሳዊ ለማድረግ በመሞከር (Scientific racism) ፖለቲካዊ ይዘት እንዲኖረው ስላደረጉ ነው። እነ ሂትለር ብሄራዊ ስሜትን ሊገነቡበት የፈለጉበት ፍልስፍና ኣደገኘ ነበር። የማንነት ፖለቲካ ብዙህ ለሆኑ ኣገሮች ቀርቶ ሆሞ ጂኒየስ ለሆኑ ኣገሮችም የሚጠቅም ኣይደለም። ሆሞ ጂኒየስ የሆኑ ኣገሮች ብሄራዊነትን ለመገንባት ብለው ባህላዊ ማንነታቸውን በጣም ካራገቡት ውጪያዊ ሶሺያል ካፒታላቸውን(External social capital) ይጎዳል።ብዙህነትን (Multiculturalism) ወይም ዓለማቀፋዊነት ላይ የሚኖራቸው ተሳትፎ ዝቅተኛ ከመሆኑም በላይ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት እድገታቸውን ይገታዋል። ብሄራዊ ኩራትን(national pride) ኣገራቸው ለሰባዊና ለዴሞክራሲ እድገት በምታደርገው ጥረት፣ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገት ባላቸው ኣስተዋጾ፣ ዓለማቀፋዊ ተቋማትን ለማገዝ በሚያደርጉት ጥረት ዜጎች እንዲኮሩ ማድረግ በጣም ጥሩ ይመስላል። በቅርቡ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ስዊድን ፍርድ ቤት ሊከሰሱ እንደሆነ ስሰማ ሁለት ነገር ኣሰብኩ። ኣንደኛው ለውጥ ፈላጊው ኢትዮጵያዊ ምን ይሰማዋል? የሚል ነው። ይህንን ሳስብ ኣንደኛ ደስታ ሁለተኛ ሃዘን ነው። ደስታው የሚመነጨው የሚያዝንባቸውን መሪዎች ሊጠይቅ የሚችልበት ፍርድ ቤት ከባህር ማዶ መኖሩን ሲሰማ ሲሆን የሚያሳዝነው ደግሞ በሃገሩ ሰማይ ስር የራሱ ፍርድ ቤት ጉዳቱን ሳይፈርድለት በመቅረቱ ፍትህ ፍለጋ ባህር ማዶ በማለሙ ነው። በሌላ በኩል ያሰብኩት ኣሁን እኔ ስዊድናዊ ብሆን ይህን ዜና ስሰማ ምን ይሰማኛል? ብየ ነው። ስዊድናዊ ብሆን ኖሮ ደስ ይለኝ ነበር፣ በሃገሬ እኮራ ነበር። የምኮራውም በሃገራቸው ፍትህ ያጡ ህዝቦች እኔ በገነባሁት ነጻ ፍርድ ቤት ፍትህ በመፈለጋቸው ነው። ጥላ በመሆኔ የሌሎች ህዝቦች ፍትህ ማጣት ለእኔም እንደሚሰማኝ በማሳየቴ ደስታ ይሰማኛል እኮራለሁ ብየ ኣሰብኩ። ዜጎች በነጻ ተቋማት ላይ የተመሰረተ ብሄራዊ ኩራት እንዲያዳብሩ ማድረግ ጥሩ ይመስለኛል ለማለት ነው ይህን ያመጣሁት።

ኣገሮች ባህላዊ ማንነትን በኣንድ በኩል እየተንከባከቡ በሌላ በኩል ለመልቲ ካልቸራሊዝም ክፍት መሆን ካልቻሉ እየመጣች ያለችዋ ኣለም ታስቸግራቸዋለች። ብዙህ የሆኑ ኣገሮች ደግሞ ለየብቻ ሆሞ ጂኒየስ መሆን ፍትህ ሊያመጣ ይችላል የሚል እምነታቸው መሰረቱ ከዴሞክራሲ ጋር የማይሄድ መሆኑን መገንዘብ ካልቻሉ የብዙ ሰውን ህይወት እየጎዱ ሊኖሩ ይችላሉ።ስለ መልቲ ካልቸራሊዝም ሳስብ የሚሰማኝ ነገር ኣለ። ብዙ ጊዜ የምእራቡ ዓለም ባህል ተጫነን ሲባል እሰማለሁ። የምእራብ ዓለም ባህል ምን እንደሆነ በሚገባ ኣልገባኝም። የምእራብ ኣገራት ብዙ ናቸው። ስለ ባህል ካወራን እነዚህ ሃጋራት በጣም የተለያየ የየራሳቸው ባህል ያላቸው ናቸው። የምእራቡ ባህል ሲባል ምን ኣልባት የምእራብ ስልጣኔ ከሆነ ስልጣኔን መከላከል ኣስፈላጊ ዓይደለም።ስልጣኔ በራሱ መጥፎ ባህልን ኣይፈጥርም ነገር ግን ስልጣኔ ስናስገባ ወይም ስንፈጥር ማህበራዊ ለውጥ ውስጥ እንገባለንና በዚህ ለውጥ ጊዜ ለህብረተሰብ እድገት የማይጠቅሙ ክስተቶች ብቅ ብቅ ማለታቸው ኣይቀርም።ይሄ የማህበራዊ ለውጥ ኣንዱ ክስተት ነው። በዚህ ጊዜ እነዚህን ኣላስፈላጊ ክስተቶች ዳብረው ባህል ከመሆናቸው በፊት የመቅጨት ስራ በመንግስትና በህዝቡ በኩል መሰራት ኣለበት። ከዚህ ውጭ ስለ ምእራባዊያን መረዳት ያለብን ኣሁን ለምናያት የሰለጠነች ኣለም ያደረጉት ኣስተዋጾ እጅግ ከፍተኛ ነው። ለእኔ ከክርስቶስ በታች የዚህ ዓለም ብርሃን ናቸው። የምእራቡ ዓለም የስልጣኔ ባህል ዓለማችንን ከጎጂ ባህሎችና ልምዶች በማላቀቅ ላይ ይገኛል። ዓለም ስለ ሰብዓዊ መብት ያላትን ግንዛቤ እንድታሰፋ፣ ዴሞክራሲን እንድትለማመድ፣መልካም ኣስተዳደር እንዲሰፍን፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እዚህ እንዲደርስ የደከሙት ድካም ኣይዘነጋም። የዓለም ህዝቦች በሰብዓዊ መብት ዙሪያ እንዲነቁ፣ ገዢዎቻቸውን ስለ መብታቸው እንዲጠይቁ፣ ሰብዓዊ መብት የዓለም ህዝቦች ባህል እንዲሆን ከፍተኛ ኣስተዋጽዖ ኣድርገዋል። ታላላቅ የሰብዓዊ መብት ተሙዋጋች ድርጅቶችን በማቋቋም ታላቅ ኣስተዋጾ ኣድርገዋል። በኣፍሪካ በላቲን ኣሜሪካና በእስያ ኣገሮች የሚታዩትን ብዙ ጎጂ ልማዶች ለማስቀረት የወሰዱት እርምጃ ብዙ ለውጥን ኣምጥቱዋል። የምእራብ ኣገሮችና ኣሜሪካ ሌላው በዓለም ህዝቦች ዘንድ ሊረሳ የማይችለው ኣስተዋጾ ሴቶች መብታቸው እንዲከበር ማድረጋቸው ነው። ከባህል ጋር እየተያያዘ ሴቶች በብዙ ኣገራት ከፍተኛ በደል የሚፈጸምባቸው ሲሆን ይህንን ለማስቀረት የተጫወቱት ሚና በዓለም ሴቶች ዘንድ ተደናቂ ያደርጋቸዋል። ኣንድ ጊዜ ኣንድ ህንዳዊ ኣገኝቼ ስለ ህንድ ባህል ጠየኩት። የሰማሁት ነገር ስለነበረ ነው የጠየኩት። እንዴት ነው ሴቶችን በእሳት የማቃጠሉ ባህል እየጠፋ ነው ወይ? ብየ ጠየኩት። ኣዎ የሰባዊ መብት ተሙዋጋች ድርጅቶች እየለፉ ነው እየቀነሰ የመጣ ይመስለኛል ኣለኝ። ህንድ፣ ባንግላዴሽ፣ ፓኪስታን ኣካባቢ ሙሽራን ማቃጠል(bride burning) የሚባል ባህል ኣለ። በዚህ ባህል መሰረት ሴቲቱ ኣግብታ ባሉዋን ካላረካችና የምትሰጠው ጥሎሽ ህይወቱን ካልለወጠው በሚነድ እሳት ያቃጥላት ዘንድ የሚፈቅድ ባህል ኣለ። ይህንን የመሳሰሉ ጎጂና ኣስደንጋጭ ባህሎች ለማስቀረት የዓለምን ግማሽ የሚሆነውን ህዝብ ማለትም ሴቶችን ነጻ ለማውጣት ከፍተኛ ሚና ሲጫወቱ የሚታዩት የምእራብ ኣገሮች ህዝቦችና መንግስታት ናቸውና ሊመሰገኑ ይገባቸዋል።ከነሱ የምንማረው እጅግ ብዙ ነው። በኣፍሪካ ኣህጉራችን ውስጥ ብዙ ብሄሮች ሰውነታቸውን በስለት ሲዘለዝሉ ይታያል፣ ጠለፋ፣ ኣስገድዶ መድፈር፣ የሴት ልጅ ግርዛት፣ ስንቱ ተቆጥሮ። ደቡብ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ ስለ ሴት ልጅ የሰማሁት ኣስደንግጦኝ ነበር። በዚያ ብሄረሰብ ባህል መሰረት ሴት ልጅ የወር ኣበባዋ ሲመጣ ከቤት ትወጣና ጫካ ውስጥ ትደበቃለች። ለተውሰኑ ቀናት ብቻዋን ተገልላ ከቆየች በሁዋላ እንደገና ወደ ቤቱዋ ትመለሳለች።እንዲህ የመሳሰሉ ጎጂ ልማዶችን ለማስቀረት ህዝብን ማስተማር ስልጣኔን ማስረጽ ብቻ ሳይሆን የሚያስቀጣ መሆን ኣለበት። ከምስራቁ ዓለምም የምንማረው ኣለ። ሰራተኛነትን ከቻይናዊያንና ከኮርያዊያን እንማራለን። ማቴሪያል ካልቸራችንን ለማሻሻል ከኮርያና ከጃፓን የምናደርገው ግንኙነት በጣም ጠቃሚ ነው። በሌላ በኩል እኛ ኢትዮጵያዊያን በባህልም፣በታሪክም ብዙ የምናካፍለው ኣለንና ክፍት በመሆን ከዓለም ህዝቦች ጋር እውቀትን መከፋፈል ያስፈልጋል። በዓሁኑ ሰዓት ቴክኖሎጂ፣ ትራንስፖርት የሰው ልጅ እውቀት ዓለምን በጣም እያቀራረባት ስለሆነ የዓለም ህዝቦች እያዋጡ የጋራ ባህልን ሲመሰርቱ ነው እያየን ያለነው። ይሄ ደግሞ መልካም ነው። ዋናው ጉዳይ ኣንዳንድ ኣደገኛ የሆኑ ባህሎች ጎልተው ሲታዩ እነዚህን ባህሎች የራሳችንም ይሁኑ ማህበራዊ ለውጥን ተከትለው የመጡ ይሁኑ ቶሎ ብሎ የመቅጨት ስራ መስራት ነው።

የተነሳንበትን መሰረታዊ ጉዳይ እንዳንስት ወደ ፌደራሊዝሙ ጉዳይ እንመለስና የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም ወይም የክልሎች መንግስታት ኣመሰራረት ብዙዎቻችን በብሄር ፌደራሊዝም እንግለጸው እንጂ እውነቱን ለመናገር ስም የለውም። የሶሲዮሎጂና የፖለቲካ ምሁራን ያልመከሩበት በነሲብ የተደረገ የክልልሎች መንግስታት ምስረታ የተካሄደ ነው የሚመስለው። ከሁሉም በላይ ትግራይን ለመከለል የተጨነቀውን ያህል ራሱ ፓለቲካው በሚያምነው “ራስን በራስ የማስተዳደር” መርህ ሌሎቹ ተከልለው ኣይታይም። ትግራይ ክልል ከተመሰረተ በሁዋላ ውሎ ኣድሮ እንዴውም ራያ ውስጥ ብዙ ትግርኛ ተናጋሪ ኣገኘን ብለው ወደ ትግራይ ከልለዋል ወልቃይትንም እንደዚሁ።ይህ ዓይነቱ ድርጊት የትግራይን ህዝብ ጠቅሞታል ለማለት ሳይሆን የመንግስትን ኣሰራር ለማሳየት ነው። በተለይ …በተለይ ….የደቡብ ህዝቦች ኣንድ ክልል የመሆኑ ነገር መነሻው ምን እንደሆነ ኣይታወቅም። እንደሚታወቀው ደቡብ ውስጥ ወደ 56 የሚጠጉ ብሄሮች ያሉ ሲሖን እነዚህን ብሄሮች በሙሉ ሰብስቦ ኣንድ ክልል ሊያደርጋቸው የሚችል ምን መመዘኛ ነበር ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። ለምን የደቡብ ክልል ኣንድ ክልል ተባለ ኣይደለም ጥያቄው። ጥያቄው የደቡብ ክልል የሚባል ክልል ከተፈጠረ ለምን የሰሜን ክልል፣ የምስራቅ ክልል፣ የምእራብ ክልል እያለ ኣልቀጠለም የሚል ነው።ጥያቄው የህወሃትን መርህ ኣልባነት ለማሳየት ነው። በደቡብ ውስጥ ያሉ እነዚህ ብዙ ብሄሮች ኣንድ መንግስት ብቻ እንዲመሰርቱ የተደረጉበት ምክንያት ኣንዳንድ የወያኔ ሰዎች ሲናገሩ የደቡብ ብሄሮች በስነ ልቡና የተቀራረቡ እንደሆኑ ይገልጻሉ። ይሄ ምን ማለት እንደሆነ ኣይታወቅም። ለምሳሌ ያህል ጉራጌንና ኮንሶን ብንወስድ ሁለቱም ብሄሮች በቋንቋም ሆነ በባህል በጣም የተራራቁ ናቸው። ጉራጌ የሴም ቋንቋ ተናጋሪ ኮንሶ ደግሞ የኩሽ ቋንቋ ተናጋሪ ነው። በጉራጌና በኮንሶ መካከል ካለው የባህልና የቋንቋ ዝምድና ይልቅ የኣማራና የትግራይ የባህልና የቋንቋ ዝምድና ይቀራረባል። ይህንን የምለው ምን ያህል መርህ ኣልባ የሆነ ኣንድን ክልል ብቻ ለመጥቀም የተደረገ የክልል ኣመሰራረት እንደሆነ ለማሳየት እንጂ የኢትዮጵያዊያን ጥያቄ ይሄ ኣይደለም እንዴውም ባህልና ቋንቋ ኣንድ መንግስት መስርተን ለመኖር እንቅፋቶቻችን ኣይደሉም ከዚህ በፊት ለዘመናት ኖረናል እያሉ ነው።

የደቡብ ህዝብ በኣንድ መንግስት ስር ሲተዳደር “ራስን በራስ የማስተዳደር መብት” የሚባለው የኢህዓዴግ መርህ ትግራይ ላይ የሰራውን ያህል ኣይሰራም ማለት ነው። ክልል ኣመሰራረቱ በህዝብ ብዛት ነው እንዳይባል የትግራይ ክልል ከሲዳማ ህዝብ ጋር ተመጣጣኝ ነበር። ለዚህ ነው የሲዳማ ህዝብ እኛስ ለምንድነው በዞን ደረጃ የምንታየው ለምን መንግስት ኣንሆንም ብለው እየጠየቁ ያሉት። መንግስት ራሱ ባወጣው መስፈርት መሰረት ነው እየጠየቁ ያሉት። ያም ሆኖ ግን ትግራይ ላይ የሰራው “ራስን በራስ የማስተዳደር” መብት ሲዳማ ላይ ኣይሰራም። በመሰረቱ የብሄርን ፖለቲካ ተከትሎ የመጣው የፌደራል ኣወቃቀሩ ዝም ብሎ የተዋገረ ስለሆነ ጥርት ያለ ምላሽ ኣይገኝበትም። የደቡብ ህዝብ ደስ የሚለው ወያኔ ያንን ኣለ ያንን ብዙም ከቁብ ሳይቆጥር ኣንድነቱን ጠብቆ ይኖራል። ጥያቄው ግን የመርህ ጥያቄ ነው። የደቡብ ህዝብ ኢህዓዴግ ከገባ በሁዋላ የፖለቲካ ተሳትፎው ጥያቄ ለማኝ ነበር። እንደሚታወቀው ይህንን የብሄር ፖለቲካ ተከትሎ ኢህዓዴግ እንደገባ ሁሉም የደቡብ ብሄሮች የፖለቲካ ድርጅት ኣቋቁመው ነበር። እነዚህ የየብሄሩ የፖለቲካ ድርጅቶጅ ቁጥራችሁ ትንሽ ስለሆነ ለመንግስትነት ኣትበቁም ኣይነት ተባሉና የደቡብ ህዝቦች የሚባል መንግስት ሲመሰርቱ ደህዴግ የሚባል የክልል ፓርቲ ተጠናክሮ ወጣ ተባለ። ይህ ድርጅት በነዚያ ከየብሄሩ በመጡ ፓርቲዎች የተዋቀረ ግንባር ነው። የሚገርመው ይህ ግንባር ወደ ፌደራል ሲመጣ እንደገና ኢህዓዴግ ከተባለው ኣስገራሚ ድርጅት ጋር ሌላ ግንባር ይፈጥራል ይህ ማለት እነዚያ በየብሄሩ የተመሰረቱት ድርጅቶች የኢህዓዴግ የልጅ ልጆች ይሆናሉ ማለት ነው። ወይም ኢህዓዴግ ኣያት ነው ማለት ነው። ኢህዓዴግ ለህወሃት ኣባት እንደሆነው ሁሉ ለነዚያ ለደቡብ ብሄሮች ድርጅቶች ኣባት መሆን ኣልቻለም ማለት ነው። በቁጥራቸው ምክንያት የልጅ ልጅ ሆነው ሲኖሩ ሲኖሩ ቆዩና ከብዙ ኣመታት በሁዋላ በኣስራ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ኣምስት የየብሄሩን ፓርቲ እያፈረሱ ያን ደህዴግ የተሰኘውን ኣንድ ክልላዊ ፓርቲ ኣድርገው እነሱ ከሰሙ። ይህ የሚሻል ቢሆንም ኣሁንም ግን ከመንግስት ኣጠቃላይ የፖለቲካ ኣወቃቀር ጋር ሲታይ የደቡብ የፖለቲካ ተሳትፎ ጉዳይ ጥያቄ ያለበት ነው። የሎጂክ ጥያቄዎችን የሚለምን ሁኔታ የከበበው ነው። የኣሁኑን ጠቅላይ ሚንስትር ኣቶ ሃይለማርያምን ከብሄራቸው ኣንጻር ራሳቸውን የሚገልጹበት የፖለቲካ ድርጅት የላቸውም ማለት ነው። እንደ ህወሃት፣ ብዓዴን፣ ኦህዴድ ጓዶቻቸው ራሳቸውን ፖለቲካዊ በሆነ መንገድ የሚገልጹበት ድርጅት ሳይሆን ያላቸው ከመልክዓ ምድር ኣንጻር የሚገልጹበትን ድርጅት ነው የሚመሩት። ደቡብ ቢሄዱ ደግሞ የመጡበት ብሄር የፖለቲካ ድርጅት ባይኖራቸውም ኣጠቃላይ የፖለቲካው ስሜት የሚገፋቸው ሰዎች የወላይታ ተወካይ ነው የሚያደርጓቸው። ጨዋታው በየቤትህ እደር ከሆነ እንዲህ ዓይነት ብዙ መልስ የሌላቸው ጥያቄዎችን የሚያስነሳ ፌደራሊዝም ነው ያለው ኣገራችን ውስጥ።

የኢትዮጵያ የፌደራሊዝም ጉዳይ ሰሜኑን በቋንቋ ደቡቡን በጂኦግራፊ የሸነሸነ ሲሆን የክልል መንግስት ኣመሰራረቱ የኢህዓዴግን መርህ ኣልባነት ምህንድስናው ኣንድ ኣካባቢን ብቻ እንዳሰቡት ለማድረግ የተሰራ እንጂ ወጥነት የሌለው ነው። ዋናው የኢትዮጵያ መንግስት መገለጫ በብሄር ፖለቲካ ሲሆን ቡድኖች በባህላዊ ማንነታቸው ራሳቸውን ፖለቲካዊ በሆነ መንገድ እንዲገልጹ የሚያደርግ ሲሆን የደቡብ ብሄሮች ግን ራሳቸውን ከፖለቲካ ኣንጻር የሚገልጹት በብሄር ማንነታቸው ሳይሆን በጂኦግራፊ በመገናኘታቸው ነው። ከፍ ሲል እንዳልኩት ኮንሶ ከጉራጌ ይልቅ በባህልም በሃይማኖትም ለኦሮሞ ነው የሚቀርበው። የኮንሶ ህዝብ ዋቃ የተሰኘ ኣምላክ የሚያመልክ ሲሆን ከኦሮሞ ጋር የተወራረሰ ነው። በቡርጂና በሱርና ብሄረሰብ መካከል ካለው የባህልና የቋንቋ ግንኙንነት ይልቅ ቡርጂዎች ለጉጂ ኦሮሞዎች የቀረበ ነገር ኣላቸው። ብዙዎቹ የቡርጂ ማህበረሰብ ኣባላት ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ናቸው። ደቡብ ውስጥ የሴም፣ የኩሽ፣ የኦሞና የናይሎ ሳሃራ ቋንቋ ተናጋሪዎች ያሉበት የኢትዮጵያ ተምሳሊት የሆነ ክልል ነው።

እንግዲህ ደቡብ ኢትዮጵያዊያን ከዚህ ከሃገሪቱ የምንነት ፖለቲካ (Identity politics) ኣንጻር ራሳቸውን የሚገልጹት ከደቡብ ኣንጻር ነው ማለት ነው። እንዴው ወያኔ ራሱ የሚለውን ተከትለን በራሱ ሎጂክ እንጠይቀው ብለን እንጂ የብሄር ፖለቲካው ምን ሊጠቅማቸው።
ለስራ ጉዳይ ለተወሰነ ጊዜ ደቡብ ኣካባቢ ነበርኩና የታዘብኩት ነገር የመገንጠል ጥያቄ ሲነሳ ለደቡብ ህዝቦች የሚመች ጥያቄ ኣይደልም። ሌሎች ብሄሮች ሰሜን ምስራቅ ምእራብ ሳይባሉ እነሱን በጂኦግራፊ ብቻ ደቡብ ብሎ መሰየሙ ግራ እንደሚያጋባቸው ተረድቻለሁ። ያም ሆኖ ግን የኢትዮጵያን ኣንድነት ስለሚናፍቁ ኣንድ ቀን የዚህ የብሄር ፖለቲካ ሲቀር ጥያቄያቸው እንደሚፈታ ያስባሉ።

በኣጠቃላይ በብሄር ላይ የቆመ ፖለቲካ የምታራምድ ኣገር፣ ራስን በራስ ማስተዳደር ከዳቦና ከእንጀራ በላይ ሆኖ ኣግኝቸዋለሁ ለሚለው መንግስት ኣንዳንዶቹን ብሄሮች መስፈርቱ ባልታወቀ መልኩ ለመንግስትነት ማእረግ ኣትበቁም ወይ በልዩ ወረዳ ወይ በዞን ደረጃ ተሰየሙ መባሉ ኢፍትሃዊ እኮ ነው። ቡድንን ቡድን የሚያሰኘው የህዝቡ ብዛት ሳይሆን ቋንቋውና ባህሉ ሲሆን የማንም ቋንቋ ከማንም ኣይበልጥም ኣያንስምና እነዚህ ቡድኖች ሁሉ የክልል መንግስትነት ጥያቄ ቢያነሱ ምን ጥፋት ኣላቸው?

ሰማኒያ የሚሆኑ ቡድኖች ባሉበት ኣገር ቁጥራቸው ኣነስ ያለውን “ኣናሳ” እያሉ ወደ ኣንዱ ለጠፍ እያደረጉ ዘጠኝ ክልል መስራት ምን ይባላል? ፍትህ የጎደለው እንዲሆን ያደረገው ራሱ መንግስት ይዞት የተነሳው እምነት ነው። ኣድካሚ የሆነ እምነት:: የኢትዮጵያን የቡድንም ሆነ የግለሰብ ጥያቄ የማይመልስ እምነት። በጣም ያሳዝናል።

በኣጠቃላይ የኢትዮጵያ ክልል ኣመሰራረት ከራሱ ከኢህኣዴግ ፖለቲካ ጋር የተጋጨ፣ ከሁሉም በላይ ከኢትዩጵያ ተፈጥሮ ጋር የተጋጨ፣ ሳይንሳዊ ያልሆነና መርህ የጎደለው በመሆኑ ይህ ነገር የሚመጣ መንግስት ሲመጣ በተሻለ ክልል ማሰዳደር ይቻል ዘንድ ኢትዮጵያዊያን ከወዲሁ ልናስብበት ይገባል።
በኣጠቃላይ ይህን ሁሉ የማወራው የኣቶ መለስ ምህንድስና ምን ያህል እንዳሻው የተዋቀረ እንደሆነ ለመግለጽ ነው። ከዚህ በላይ የኢትዮጵያን የኣርባ ኣመት የማንነት ጥያቄ በተሻለ የሚመልስና ወጥነት ያለውና በመርህ ላይ የተመሰረት ፌደራሊዝም ስርዓት ለመመስረት ጥቂት ኣሳብ ለማቀበል እፈልጋለሁ።
የኣዲሲቱ ኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት እንዲህ ቢሆንስ?

በዚህ በወያኔ ብሄርተኛ ኣስተዳደር የተቆጣን ሰዎች ለለውጥ ስንታገል የምንፈልጋት ኢትዮጵያ ምን ዓይነት እንደሆነች በሚገባ ስለን ማሳየት ኣለብን።ምን ዓይነት የፌደራል ስርዓት ነው የምንፈልገው። ያለፈውን የኣርባ ኣመት ጥያቄ እንዴት ነው የምንፈታው ብለን ቀድመን ጥንቅቅ ኣድርገን ልናስብበት ይገባል።የወደፊቱዋን የፈለግናትን ኢትዮጵያን በጸዳ ሁኔታ ኣሰተዳደራዊ ቅርጹዋን ማሳየት ይጠበቃል። ኣንዳንድ ሰዎች የኣሁነ ዘመን ትግላችን ከፍትህና ከዴሞክራሲ ጥያቄም በላይ ሃገርን የማዳን ስራ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባዋል ይላሉ። ይህን ጉዳይ የምጋራው ሆኖ ኣገርን የሚያድን ጥርት ያለ ኣማራጭ የፖለቲካ ስርዓት ለኢትዮጵያ ህዝብ ማሳየት ይጠበቃል። በዚህ ረገድ ባለፈው ጊዜ ደጋግሜ በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ ውህደት ካልኩት ኣሳብ የሚቀዳ ኣንድ የመንግስት ኣወቃቀር ጠቆም ለማድረግ ነው ፍላጎቴ።
የክልል ኣመሰራረቱ የሚመነጨው ኢትዮጵያን ከምናይበት እይታ ነው። በዚህ ኣገባብ ኢትዮጵያን የምናየው በስምምነት ላይ ከተመሰረተ ባህላዊ ውህደት ኣሳብ ኣንጻር ነው።ከሁሉ የሚቀድመው በብሄራዊ እርቅ መንገድም ይሁን በሽግግር መንግስት ስም ቡድኖችን የሚያወያይ ከፍተኛ ኣገራዊ ኣጀንዳ ይዞ ወደ ስምምነት መምጣት ነው። ለውይይት ከምናቀርበው ኣሳብ ውስጥ ኢትዮጵያን በተሻለ ሊያስተዳድር የሚችል ጥበብ ማሳየት ከቻልን ቡድኖች የማይስማሙበት ጉዳይ የለም። ይህ ወይይትና ስምምነት የፓርቲዎች ጉዳይ ኣይደለም። ባለፉት ኣርባ ኣመታት ህዝባዊ ውክልና የሌላቸው ፓርቲዎች ልክ ህዝብ የመረጣቸው ይመስል ኣንዴ የማንነት ፖለቲካ ይሻላል፣ ኣንዴ ሶሻሊዝም ኣንዴ ምን እያሉ ቆይተዋል። ይህ ጉዳይ ተለውጦ ኣሁን ኣንድ ኢትዮጵያን ኣጠናክሮ ሊገነባ የሚችል የስምምነት ኣሳብ ይዞ ቡድኖችን በቀጥታ ማነጋገር ያስፈልጋል። ህዝቡ በቀጥታ ተሳታፊ የሆነበት ከፍተኛ ውይይት ተደርጎ ኣንድ ኪዳን ሊፈርም ያስፈልጋል። ከዚያ በሁዋላ ፓርቲዎች እየተነሱ ህገ መንግስት ኣርቅቀው እያስጸደቁ መንግስት እየተቀያየረ መኖር ይቻላል። ኢትዮጵያዊያን ልንወያይበት ከሚገባው ጉዳይ መካከል ኣንዱ የዚህ የፌደራሊዝም ጉዳይ በመሆኑ ፌደራሊዝሙ ብዙ የሆነችውን ኢትዮጵያን ባህላዊና ፖለቲካዊ ማንነቱዋን ለይቶ የሚያስተዳደር ቅርጽ ሊይዝ ይገባዋል። በዚህ መሰረት በሁለት ፌደሬሽን የምትመራ ሁለት መንግስታት ያሉዋት ኣገር ኣድርገን ብንሰራት የተሻ ይሆናል። ይህ ሁለት መንግስት ማለት ኣንደኛው ባህላዊ መንግስት ሲሆን ይህ መንግስት በህገ መንግስት ሃላፊነት የተሰጠው ባህላዊ ጉዳዮችን ለይቶ የሚንከባከብ ሲሆን ሌላው መንግስት ደግሞ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን የሚመራ ነው። እነዚህ ሁለት መንግስታት ቢመሰረቱ ኣንደኛ የማንነት ፖለቲካ ጥያቄያችንን ያቃልላል። ሁለተኛ ብዙህነታችንን ኣደባባይ ኣውጥቶ መልካችንን ያሳያል። ከዚህም በላይ ሰላምና ልማትን ለማፋጠን የማትከፋፈል ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማሳለፍ ይረዳናል።

ኢትዮጵያ ኣንድ ናት ስንልም ከነዚህ ከሁለት ዋልታና ማገር የተሰራች መሆኑዋን እያሰብን ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያ ሁለቱንም ማንነቶቹዋን ሳያደባልቅ የሚያስተዳድር ፌደራሊዝም ልትመሰርትና በሁለት መንግስታት ልትተዳደር ትችላለች። እነዚህ ሁለት መንግስታት ኣንዱ የባህል መንግስት ሲሆን ሁለተኛው ፓለቲካዊና ዴሞክራሲያዊ የሆነ መንግስት ነው። ሁለቱም መንግስታት በመሰረታዊ ህግ በሚገባ የተለየ ስልጣንና ተግባር ኖሩዋቸው ይኖራሉ። ፖለቲካዊው መንግስት ዳይናሚክ ሲሆን በየጊዜው ዴሞክራሲን እያሳደገ ዘመናዊ ኣሰራርን እያዳበረ ኣገሪቱን ወደተሻለ ህይወት ይመራል። ባህላዊው መንግስትም ባህሎቻችንን እየጠበቀ በመሰረታዊ ህጉ ላይ ያለውን ሃላፊነት እየተወጣ ይኖራል። ባህላዊ መንግስትን ስንመሰርት ዘመናዊነት መጣ ብለን ጥለን የነበርነውን ጠቃሚ ባህል ሁሉ እንድናነሳ ያደርገናል። የየቡድኖች ነገስታት ወደ ኣደባባይ በማውጣት በምንመሰርተው ህብረ ብሄር ቤተ መንግስት ይመጡና ከፍ ብለው ይታያሉ። ኮሚንዝም ያስጣለንን ባህል ሪስቶር እያደረግን ታሪካዊ ሃገራችንን የቀድሞ የፈጠራ ውጤቶቹዋን ኣክብረን ካዲሱ ትውልድ ፈጠራ ጋር ጎን ሎጎን ማስኬድ እንችላለን። ለኣርባ ኣመት የቆየውን የማንነት ጥያቄ በማቃለል ፣ ማንነትን ሳናወዳዽር የምንፈጥረው ስርዓት የረጋና ሰላም የሰፈነበት ይሆናል። በተለይ እኛ ኢትዮጵያዊያን ከኛ ሁኔታና የህይወት ልምድ፣ ካለፍንበት ረጅም ጎዳና ኣንጻር ፖለቲካዊና ባህላዊ ማንነቶችን ማደባለቅም ሆነ ኣንዱን ከኣንዱ የማበላለጡ ስሜት ጎድቶን ኣጨቃጭቆን ይታያልና ውድ ድር ውስጥ ሳናስገባ ባለንበት ቡድን ስም ራሳችንን ብንገልጽ ክፋት የለውም። ኣንድ ዜጋ ክርስቲያን ነኝ ብሎ ራሱን በዚህ ሃይማኖታዊ ማንነት ሲገልጽ ከኢትዮጵያዊነትህና ከክርስትናህ የቱን ታስቀድማለህ ወይም የቱ ይበልጣል እያሉ መፈተን ጠቀሜታ የለውም። ባህላዊ ማንነቶቻንንም እንደዚያ ማየት ነው። ኣንድ ዜጋ በባህላዊ ማንነትም ሆነ በፖለቲካዊ ማንነቱ ራሱን የሚገልጽበት ሁኔታ መኖር ኣለበት። በዚህ ጉዳይ ላይ ከዚህ በፊት ብዙ ብያለሁና ይብቃ። ይህንን ማንነቶቻችንን መለያየታችንን የሚያሳየው የሁለቱ መንግስታት ምስረታችን ነው። የምንመሰርታቸው መንግስታት ሌሎች ኣካባቢዎች ባህላዊ ኣስተዳደር ኣለ እንደሚባለው ሳይሆን በሚገባ በመሰረታዊ ህጉ የስልጣን ክፍፍል ያደረገ ቤተመንግስት የመሰረቱ መንግስታት ናቸው የሚኖሩን። ከህገ መንግስት ወይም መሰረታዊ ህጉ በላይ በሚውለው ኣዲስ ኪዳን ስር የሚመሩን ሁለት መንግስታት ማበጀታችን ኣንድ የመጀመሪያ ርምጃ ይሆንና ከዚህ በሁዋላ የክልሎችን ኣመሰራረት ወይም የፌደራሉን ኣወቃቀር በተመለከተም ሁለቱም መንግስታት የየራሳቸው ኣስተዳደራዊ ክልል ይኖራቸዋል። የፖለቲካው መንግስት ክልሎችን ሲገናባ ኣስተዳደራዊ ኣመቺነትን እያየ የሚከፋፍል ሲሆን በመሬት ላይ የሚነበብ ክልል ይኖረዋል። ስልጣንና ፍትህ ወደ ህዝቡ በተቻለ መጠን የሚቀርብበትን ክልሎች ማቆም የፖለቲካው መንግስት ስራ ነው። ፌደራሊዝም ለትላልቅ ሃገራት ተመራጭ ይሁን እንጅ ውድነት(expensiveness) ስላለው ይህንንም ከግንዛቤ ያስገባ ፌደራሊዝም ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ ካላት የቆዳ ስፋት ኣንጻር ከኣራት የማይበልጥ ስቴቶች ቢኖሩዋትና ኣራቱም ሰሜን፣ደቡብ፣ ምስራቅና ምእራብ ኢትዮጵያ ተብለው ቢሰየሙ ጥሩ ሊሆን ይችላል። ስልጣንን ከስቴት መንግስታት ቀጥለው የሚፈጠሩ የመንግስት ሃየር ኣርኪዎች ማውረድ ኣስፈላጊ ነው።

ሌላው መንግስት ማለትም ባህላዊ መንግስት ያልነው ደግሞ በመሬት ላይ የሚነበብ ክልል ወይም ስቴት ኣይኖረውም። የኣንድ ባህላዊ በድን ኣባላት በመላው ሃገሪቱ ተሰራጭተው የሚኖሩ ከሆነ እነዚህ ኣባላት በያሉበት ባህላቸውን የሚጠብቁበት የሚንከባከቡበት ሁኔታ ነው የሚኖረው። የኦሮሞ ስቴት፣ የኣማራ ስቴት፣ የሙርሲ ስቴት ወዘተ ስንል ባህሉና ቋንቋው ነው ሊታየን የሚገባው። እነዚህ ስቴቶች ኣሳባዊ ይሆኑና ኣባላት በያሉበት የዚያ ኣሳባዊ ስቴት ኣባል ይሆናሉ የሚጠበቅባቸውንም ያደርጋሉ። ኣንዳንድ ጊዜ ባህላዊ መንግስቱ ኣስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው የመንግስትን መዋቅር ሊጠቀምበት ይችል ይሆናል።
ይህ ባህላዊ መንግስት ባለፈው ግዜ እንዳነሳነው የኣርበኞች ቤት የሚባል ካውንስል የሚያቋቁም ሲሆን ይህ ቤት የሚመሰረተው በቡድኖች ነገስታት ይሆናል። ከዚያ ስር የሚያዋቅራቸው 3 ቤቶች ይኖሩታል። ኣንደኛው የባህልና ቋንቋ ጠባቂና ተንከባካቢ ቤት፣ ሁለተኛው የኬር ቴከር ቤት፣ ሶስተኛው የሰላምና የእርቅ ግጭት ኣስወጋጅ ቤት ይሆናሉ። በባህልና ቋንቋ ጥበቃ ስር ተጨባጭና ተጨባጭ ያልሆኑ ባህሎችን የሚንከባከብ ክፍልና የብሄራዊ ሙዚየም ይኖረዋል።በኣጠቃላይ የባህላዊው መንግስት የራሱ የሆነ ሲስተም ሲኖረው ፖለቲካውም እንዲሁ በፊናው የራሱን ሲስተም ዘርግቶ በየተወሰነ ጊዜው ምርጫዎችን እያደረገ ይኖራል።

በዚህ ኣርቲክል ውስጥ በነዚህ ንኡስ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ትንታኔ ኣንሰጥም። ዋናው ኣላማ ኣጠቃላይ መዋቅሩን ማሳየት ሲሆን በዚህ ዓይነት ኣወቃቀር ሰላምን፣ ፍትህን ለማሳለጥ በኢትዮጵያ ይመረጣል ለማለት ነው። ኣጠቃላይ ቅርጹ በሚከተለው ቻርት የተገለጸ ነው።
የCCU የመንግስት ኣወቃቀር
ኣንዳንድ ፓርቲዎች ይህ ኣንገብጋቢ ጉዳይ ኣይደለም ወያኔን መጣል ነው ኣንገብጋቢው ጉዳይ የሚሉ ከሆነ ትክክል ኣይመስለኝም። የሆነ የጠራ ኣማራጭ በኣንድ እጃችን ይዘን ነው ለለውጥ መታገል ያለብን ብየ ኣምናለሁ። በመሆኑም ኣንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች ሊለውጡዋት ያሰቡዋትን ኢትዮጵያ እንዲህ የሚያዩዋት ከሆነ ፕሮግራማቸው ውስጥ ኣስገብተው ለህዝብ ቢያስተዋውቁ ጥሩ ነበር።

ለማናቸውም እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!
ኣስተያየት ካለ እነሆ ኣድራሻየ
geletawzeleke@gmail.com


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>