Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

የኮብላዩ ሚኒስትር ወጎች –ከተመስገን ደሳለኝ (ጋዜጠኛ)

$
0
0

በዚህ ተጠየቅ ጨርፈን የምንመለከተው በኮሙኑዮኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ የነበረውና ዛሬ በስደት የሚገኘው የአቶ ኤርሚያስ ለገሰን “የመለስ ትሩፋቶች፣ ባለቤት አልባ ከተማ” የተሰኘው መጽሐፍን ነው፡፡ የመድብሉ ጻሐፊ ኤርሚያስን በግል አላውቀውም፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል ያየሁት አቶ በረከት ስምዖን እርሱን እና ሽመልስ ከማልን ምክትሎቹ አድርጐ በሚኒስቴር ዲኤታ ማዕረግ መሾሙን በግዮን ሆቴል ለጋዜጠኞች ይፋ ባደረገበት ዝግጅት ላይ ነው፡፡ ከዚህ ለጥቆ፣ በኢትዮጵያ የቀድሞው የአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ቡዝ በኤምባሲው ግቢ በሚገኝ መኖሪያ ቤታቸው ባዘጋጁት የዕራት ግብዣ ላይ (ግንቦት 19/2001 ዓ.ም) ድንገት ተገናኝተን እጅ ለእጅ ተጨባብጠን ሰላምታ ተለዋውጠናል፤ ለመጨረሻ ጊዜ የተያየነው፣ በኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ግንቦት 7 እና እነጀነራል ተፈራ ማሞን በተመለከተ መግለጫ በተሰጠበት ዕለት እንደ አፄ ኃይለሥላሴ የክብር ዘብ፣ ከሽመልስ ከማል ጋር በረከት ስምዖንን ግራና ቀኝ አጅቦ በተገኘበት ወቅት ነው፡፡ በተቀረ በመንግስት ሥልጣን ሲገለጥ ብዙም አላስተዋልኩም፡፡ ከዚህ ይልቅም ኢህአዴግነቱን ለማሳየት የሞከረበትን አንድ ገጠመኝ አስታውሳለሁ፤ ይኸውም “የፍትሕ” ጋዜጣ ስራ አስኪያጅ የነበረው እና አሁን በስደት ሀገር የሚገኘው ባልደረባዬ ማስተዋል ብርሃኑን ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ባለው ቢሮው ድረስ በመጥራት ከባድ ዛቻና ማስፈራሪያ ከሰነዘረበት በኋላ፣ ዛሬ የቀድሞ ጓዶቹ ሥራዬ ብለው እንደቀጠሉበት አይነት በጋዜጣው ላይ የሀሰት ውንጀላ ደርድሮ ሲያበቃ፣ ከኃላፊነቱ ራሱን እንዲያገል አስጠንቅቆት እንደነበር ከራሱ ከባልደረባዬ ማስተዋል አንደበት ሰምቻለሁ፡፡
temesgen-desalegn
የሆነው ሆኖ አቶ ኤርሚያስ ከላይ በተጠቀሰው መጽሐፉ በተመላኪው ሰው አመራር “ሁሉን አዋቂነት” ላይ የቆመው መንግስት ምን ያህል በጠባብ የወንዝ ልጅነት የተተበተበ እና በዘራፊ ባለሥልጣናት የተዋቀረ እንደሆነ በስፋት ተርኮልናል፡፡ በተለይም ሙስና እና የህወሓት ካድሬዎች የበላይነትን በተመለከተ በማስረጃ አስደግፎ በተዋበ ስነ-ጽሑፋዊ ቋንቋ ዘርዝሮልናል (በርግጥ “የጋዜጠኛው” አሊያም “የደራሲው ማስታወሻ” የሚያነቡ እስኪመስልዎ ድረስ የመጽሐፉን አርትኦት ተስፋዬ ገ/አብ ወይም የተስፋዬ ብዕር ተፅእኖ ያለበት ደራሲ ብዙ እንደለፋበት በግልፅ ማስታወቁን መካድ አይቻልም)፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም ዛሬም ከአገዛዙ ጋር የተሰለፉ የቀድሞ ጓዶቹ ለህሊናቸው ሲሉ በድብቅ የሚፈፀሙ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን ደፍረው እንዲያጋልጡ በጠየቀበት ብዕሩ፣ የራሱንም ጥፋቶች እና በትዕዛዝም ይሁን በግል ተነሳሽነት በደል ያደረሰባቸውን ንፁሃን በይፋ ይቅርታ ቢጠይቅ መልካም ነበር፤ አሁንም ቢሆን ለዚህ አይነቱ ቅንነትና በጎ አርአያነት ገና አልረፈደም፡፡ ርግጥ ነው የስደት ምርጫው ባደረጋት ሀገረ-አሜሪካ ባሳተመው መጽሐፉ ውስጥ ድርጅቱ ኢህአዴግ ይሰራው በነበረው ሕገ-ወጥ ድርጊትና የጭካኔ እርምጃ አልፎ አልፎ ቢሮውን ዘግቶ እንደሚያለቅስ፣ ባስ ሲልም ህሊናውን ቆጥቁጦት ታምሞ አልጋ ላይ እንደሚውል በመግለፅ የራሱን ጲላጦሳዊነት ለመስበክ መልፋቱን ስናስተውል፤ ጸሐፊው የሥርዓቱ ጋሻ-ጃግሪ በነበረበት ወቅት የበደለውን ሕዝብ ይቅርታ የመጠየቅ ዝግጁነትም ሆነ ፍላጎት (ቢያንስ በዚህ ሰዓት) የለውም ብለን ማዘናችን አይቀርም፡፡

እንዲሁም ከሀገር እንዲወጣ የተገደደበት ምክንያት ተብሎ ስለተናፈሰው ወሬ ትንፍሽ አለማለቱ በበኩሌ አስተዛዛቢ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፤ በወቅቱ የስደቱ መነሾ ተደርጎ በከተማዋ በስፋት የተናኘው፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖቹ እና “የግንቦት 7 አባላት ናችሁ” የተባሉ ግለሰቦች ለእስር መዳረጋቸውን ተከትሎ ለአንድ ዓለም አቀፍ ሚዲያ “ሙከራው መፈንቅለ መንግስት ነው” የሚል መግለጫ በመስጠቱ እንደነበረ ነው፤ በዚህም እጅግ የተበሳጨው ጠ/ሚኒስትሩ፣ አለቃው በረከት ስምዖን ላይ ጭምር የጭቃ-ጅራፉን ከማወናጨፉም በላይ፣ ኤርሚያስን ያለ ሥራ እንዳንሳፈፈው መወራቱን አስታውሳለሁ፤ ይህንን መረጃ አምኖ ወደመቀበሉ የሚገፋን ደግሞ በዚያው ሰሞን መለስ ዜናዊ ራሱ በቴሌቪዥን ቀርቦ ‘…የተደረገው ነገር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፣ ከአልቃይዳና አልሸባብ ጋር ሲነፃፀሩ የእኛዎቹ አማተሪሽ (ልምድ አልባ) ናቸው’ እያለ የሚኒስትር ዴኤታውን ንግግር ለማስተባበል ሲዳክር የመስተዋሉ እውነታ
ነው፡፡ እርሱም ቢሆን ከዚህ ግልፅ ሹክሹክታ በኋላ በትምህርት ሰበብ ሀገር ለቅቆ መሰደዱ የአንድ ሰሞን የከተማ ወሬ ሆኖ ነበር፡፡ እነሆም ወንድም ኤርሚያስ ለገሰ ይህንን ጉዳይ ዳጉስ ባለው መጽሐፉ ውስጥ ሽራፊ ገፅ ሊሰጠው አለመቻሉ እዚህ ጋ በትዝብት እንዳነሳው መገደዴን በትህትና እገልፃለሁ፡፡ አሸንፈሀልና በዝብዘህ ብላ!

ህወሓት-ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ፣ በግርማ ብሩ አነጋገር “ደሀ-ዘመም” (በመጽሐፉ የተጠቀሰ) እንደሆነ ለማሳመን የሚሞክርበት ብልጠት፣ ራሱን ለሙስና ፅዩፍ አስመስሎ በማቅረብ ነው፤ ይህን አይነቱን ስሁት አመለካከት በሕዝብ ውስጥ ለማስረፅ ጥቂት የፖለቲካ መታመን-ጉድለት ጥርስ ያስነከሰባቸውን ጉምቱ ጓዶቹን “ሙሰኛ” በሚል ወንጅሎ በወህኒ የቃየል መስዋዕት ሲያደርጋቸው ተስተውሏል፤ እርምጃውንም በፓርላማው መድረክ ሳይቀር ሲኩራራበትና ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ሲያውለው ተመልክተናል (ከሩቁ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ እና መከላከያ ሚኒስትሩ ስዬ አብርሃ፤ ከቅርቡ ደግሞ የገቢዎችና ጉምሩክ ዳይሬክተር መላኩ ፈንቴ፣ የደህንነት ኃላፊው ወ/ስላሴ እና መሰል ባለሥልጣናትን እስር ልብ ይሏል)፡፡ የሚኒስትር ዴኤታው መጽሐፍ፣ መለስ እና ጓዶቹ ካደነቆሩን በግልባጩ ‘የዘረፋ መሪዎች’ የሚላቸው ሁለት የህወሓት ሰዎች፣ በባላንጣነት ተሰልፈው እንዴት የሀገር ሀብት ለመቀራመት ይሽቀዳደሙ እንደነበር አጋልጧል፤ አዜብ መስፍንን እና አርከበ እቁባይን፡፡

“እነ አርከበ ከትግራይ ወደ አዲስ አበባ ከመምጣታቸው ጥቂት ወራት በፊት በህወሓት ውስጥ መደናገጥ ተፈጥሮ ነበር፡፡ የህወሓት ዳግም መከፋፈል ምክንያት ደግሞ በወ/ሮ አዜብ እና አርከብ ቡድኖች መካከል አለመግባባቶች መፈጠራቸው ነበር፡፡ መነሻው መረን የለቀቀ የጥቅም ግጭት ሲሆን ዓላማው የህወሓት ኢንዶመንቶችን መቆጣጠር ታሳቢ ያደረገ ነበር፡፡” (ገፅ 25) ከዕለት ተዕለትም ይህ ሁኔታ የተካረረ ልዩነት ፈጥሮ፣ ፖለቲካዊ ቁመና በመላበሱ፤ አርከበ እቁባይ፣ ህወሓት መገፋቱን እና መለስ በበረከት በኩል የድርጅቱን ካድሬዎች እያስጠቃ ነው የሚል ክስ ከማጎኑም ባሻገር፤ ወደኋላ ተጉዞ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የተጠናቀቀበትን መዛግብት አቧራ በማራገፍ፣ ተጠያቂነቱን ከፍ ሲል ወደ መለስ ዜናዊ፣ ዝቅ ሲል ደግሞ ወደ በረከት ስምዖን በመወርወር ማጠቋቆሩ ያመጣውን ውጤት እንዲህ ሲል ገልፆታል፡- “በሂደት አቶ አርከበ ይዞ ብቅ ያለው መቀስቀሻ የካድሬውን እና አባሉን ቁስል የነካ በመሆኑ ተቀባይነት አገኘ፡፡ በትግራይ ፕሮፓጋንዳ እና ድርጅት ተመድበው የሚሰሩ ቁልፍ ካድሬዎች ተቀላቀሉት፡፡” (ገፅ 26)

ይህንን ተከትሎ ወትሮም በደፋር ንግግሯ የምትታወቀውና አንጋፋ ታጋዮችን ሳይቀር በቁጣ የምታስረግደው ቀዳማዊት እመቤት የሰነዘረችው የመልስ ምት በመጽሐፉ ላይ እንደሚከተለው ሰፍሯል፡- “ወ/ሮ አዜብ በበኩሏ አርከበና ቡድኖቹ በሙስና ተዘፍቀዋል የሚል ክስ ይዛ ብቅ አለች፡፡ አርከበ በሚስቱና ቤተሰቦቹ የያዘውን ንብረት በመረጃ አስደግፋ አራገበች፡፡ ላውንደሪ ቤት፣ ፋርማሲ፣ ክሊኒክ፣ ሱፐር ማርኬት፣ መስታወት ማስመጣትና መሸጥ…፡፡ በትግራይና አዲስ አበባ የተፈጠሩት አዳዲስ ባለሀብቶች የአርከበና ቡድኖቹ እንደሆኑ በስም ዘርዝራ አሳወቀች፡፡ ስዬ በታሰረበት የሌብነት ወንጀል አርከበ እጁ እንደነበረ፣ በተለይም የስዬ ወንድም ለገዛቸው በርካታ መኪናዎች ቅናሽ እንዲያገኝ ማግባባቱን የፈፀመው አርከበ መሆኑን አጋለጠች፡፡” (ገፅ 26)

እዚህ ጋ አቶ ኤርሚያስ ‹‹አርከበ በሚስቱና በቤተሰቦቹ…›› ስለያዛቸውና አዜብ መስፍን በስም እየጠራች አጋለጠች ስላላቸው የንግድ ድርጅቶች በስም አንድ በአንድ እየጠቀሰ ይፋ ቢያደርግልን ኖሮ መረጃው ምሉዕ (ከ‹ኮሪደር ሀሜት› የዘለለ) ይሆን ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡ ከሁሉም ቁጭታችንን የሚያንረው፣ ደራሲው የንግድ ተቋማቱን ባለቤቶች በስም መጥቀስ እየቻለ (አቀራረቡ ለይቶ እንደሚያውቅ ያሳብቃልና) በደፈናው ያለፈው ወንጀል (ሕገ-ወጥ ዘረፋ) ይህ ብቻ አለመሆኑ ሲገባን ነው፤ በዚሁ ገፅ ዝቅ ብሎ የሰፈረው እንዲህ ይላልና፡- “በወቅቱ ሁለቱም ቡድኖች ‹ያለ ኢኮኖሚ የበላይነት፣ የፖለቲካ የበላይነት አይመጣም› የሚል ፖሊሲ ቀርፀው የህወሓት ባለሀብቶችን ለመፍጠር ተንቀሳቅሰዋል፡፡ በዚህ ፖሊሲ ምክንያት በአንድ ሌሊት ከሹፌርነት ወደ አስመጪና ላኪነት፣ ከጋራዥ ሰራተኛነት ወደ መኪና ዕቃ መለዋወጫ አስመጪነት፣ ከታጋይነት ወደ ሪል እስቴት ባለቤትነት፣ ከወታደርነት ወደ ፋብሪካ ባለቤትነት፣ ከህወሓት ምድብተኛ ካድሬ ወደግል ባንክ ከፍተኛ አክሲዮን ባለድርሻነት የተቀየሩ ሰዎችን መስማት የተለመደ ነበር፡፡” (ገፅ 26) እነዚህ ‹‹ተላላኪ›› እና ‹‹ሹፌር›› ባለሀብቶችን በስም አለመጥቀሱ ያስቆጫል፤ በተለይም ለመረጃው ከነበረው ቅርበት አኳያ ይሄ ጉዳይ እንደተራ ነገር በደፈናው ባይታለፍ ኖሮ፣ ለተቃውሞው ስብስብ በዋናነት ሁለት ታላላቅ የፖለቲካ ትርፍ ማስገኘቱ አይቀሬ ነበር፡፡

የመጀመሪያው በጅምላ ህወሓት፣ መላው ትግሪኛ ቋንቋ ተናጋሪን ተጠቃሚ ያደረገ የሚመስለው ኢትዮጵያዊ ስህተቱን እንዲያጠራ ስለሚያስችለው፣ በድርጅቱ እና በብሔሩ መሀከል ያለውን ነጭና ጥቁር ልዩነት እንዲያስተውል ይረዳው ነበር፤ ሌላው ደግሞ እነዚህን በፖለቲካ ውሳኔ ወደሀብት ማማ የወጡትን ግለሰቦች የትላንት ማንነት አብጠርጥሮ የሚያውቀው ቤተሰብ፣ ጎረቤት፣ ዘመድ አዝማድ… የዘረፋ ወንጀላቸውን ተፀይፎ በኢኮኖሚያዊ ማግለል (ሸቀጦቻቸውን ባለመግዛትም ሆነ አገልግሎታቸውን ባለመጠቀም) በተቃውሞ ጎራ እንዲሰለፍ ገፊ-ምክንያት ይሆነው ነበር የሚለው ጭብጥ ነው፡፡ ‹‹የመለስ ትሩፋቶች›› መጽሐፍ በሀገሪቱ ውስጥ ከመጋረጃው ጀርባ ስለተፈፅሙ ህልቆ-መሳፍርት ያሌላቸው አሳፋሪ የህወሓት ሕገ-ወጥ ድርጊቶች እና እብሪቶችን ተንትኖ አስነብቦናል፡፡ ከእነዚህ መሀልም የስምንቱ ኮሎኔሎች ‹‹ጀብድ››ን እዚህ ጋ መጥቀሱ አግባብነት አለው ብዬ አምናለሁ፤ ከ268-269 ባሉ ገፆች እንደተተረከው፣ በምርጫ 97 ማግስት በአንዱ ዕለት በወታደራዊ የደንብ ልብስ የተንቆጠቆጡ ስምንት ከፍተኛ መኮንኖች በሶስት ሄሌኮፕተር ተሳፍረው አሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ ይደርሳሉ፤ በቀጥታም የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከንቲባ ወደነበረው አባተ ስጦታው ቢሮ በማምራት፣ መሬት እንደሚሰጥ መረጃ ደርሷቸው ከጦር ግንባር እንደመጡ ይነግሩታል፤ እያንዳንዳቸውም ‹‹ዘመቻ ፀሀይ ግባት የቤት ማሕበር››፣ ‹‹ኃየሎም አርአያ የቤት ማሕበር››፣ ‹‹ዛላአንበሳ የቤት ማሕበር››… የሚል እና መሰል የማህደር ስያሜ ያላቸው የአስራ ሁለት መኮንኖች ስም ዝርዝርና ፊርማ የያዘ ወረቀት ይሰጡታል፤ እንደ ብራ መብረቅ ድንገት ባጋጠመው ክስተት ክፉኛ የተረበሸው ከንቲባም እንዲህ ያለ መመሪያ እንዳልወረደ ለማስረዳት ሲሞክር፣ ለዚህ ዓይነቱ እሰጥ-ገባ ጊዜ ያልነበራቸው የጦር አበጋዞቹ አብረቅራቂ ሽጉጦቻቸውን በመምዘዝ ግንባሩ ላይ ደቅነው በወቅቱ ፋሽን በነበረው ኢህአዴጋዊ ፍረጃ ‹‹የቅንጅት ተላላኪ መሆንህን ደርሰንበታል››፣ ‹‹ኢህአዴግ እንዲሸነፍ ያደረጋችሁት እንዳንተ ያሉ ሰርጎ-ገቦች ናቸው››፣ ‹‹እዚሁ ደፍተንህ እንሄዳለን››… የሚሉ ማስፈራሪያዎችን አዥጎድጉደው በማስጠንቀቅ ነፍስ-ውጪ፣ ነፍስ ግቢ ወጥረው ይይዙታል፤ ይህን ጊዜ የህወሓት አባል የሆነው ምክትል ከንቲባው ነጋ በርሔ፣ የአባተን ቢሮ በርግዶ ሳይታሰብ ዘው በማለቱ፣ አንደኛው ኮሎኔል ያነጣጠረውን መሳሪያ ከአይን በፈጠነ ቅፅበት አዙሮ ይደቅንበታል፡፡ ሁኔታውን ከጉዳይ ያልጣፈው ነጋ በርሔም ባለሽጉጦቹን የጦር አበጋዞች በባዶ እጁ እንዲህ ሲል ተጋፈጣቸው፡-
“ነፍጥ ከእናንተ በፊት አንግበን ተራራ ደርምሰናል፡፡ የምታስፈራሩትን ሂዱና ሌላ ቦታ አስፈራሩ!”

ከፍተኛ መኮንኖቹም በድንጋጤ መሳሪያዎቻቸውን በመዘዙበት ፍጥነት ወደአፎቱ መልሰውና የምክትል ከንቲባውን የስድብ ውርጅብኝ በፀጥታ አዳምጠው ሲያበቁ፣ አባተን ይቅርታ እንዲጠይቁት ይታዘዛሉ፤ እንዲያ በጥንካሬያቸው ለማንም የሰው ልጅ የማይበገሩ መስለው ሲንጎማለሉ የነበሩት ቆፍጣናዎቹ ኮሎኔሎች ባንዴ እንደፊኛ ተንፍሰው በፍርሃት የታዘዙትን ይፈፅማሉ፤ ከዚህ በኋላም ህወሓቱ ነጋ በርሔ በተረጋጋ አንደበት ዋናው ከንቲባውም ጭምር እንዲሰማ ድምፁን አጉልቶ የሚከተለውን ‹‹ምርጥ›› ምክር ለገሳቸው፡ –
“ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ጥያቄያችሁን ብታቀርቡ ኖሮ አባተ እንኳን ቤተሰባችሁን ጥላችሁ ግንባራችሁን ለጥይት ለምትሰጡት ቀርቶ ለሌላውም አይጨክንም፡፡ ያውም ከቀናት በኋላ ጠላት (ቅንጅት) ተረክቦ ለሚዘርፋት አዲስ አበባ!” (ገፅ 255) ከንቲባውም መሬቱን ፈቀደ፤ ነጋም ወደ መቀሌ እንዲዘዋወር ተደርጎ፣ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴን እና የትግራይ ክልል ካቢኔን ተቀላቀለ፤ ከጊዜ በኋላም በበረከት ስምዖን በተመራ ግምገማ ላይ በአስቸኳይ አዲስ አበባ መጥቶ ይህንን ጉዳይ እንዲያስረዳ ቢጠየቅ አሻፈረኝ ብሎ ይቀራል፡፡ ደራሲውም ‹‹ዘመን አለፈና አዲሱ ለገሰን ለማገዝ ኢህአዴግ ቢሮ የሥልጠና ማዕከል በምክትል ሚኒስትርነት ማዕርግ ተመደበ›› ሲል የሆሊውድ ፊልምን የሚያስንቀውን ታሪክ ይደመድማል፡፡ በርግጥ አባተም ቢሆን ይህ አስፈሪ ገጠመኙ እንደድንቅ ቃለ-ተውኔት ሁሉ፣ በህወሓት መሪዎች ተደርሶ በኮሎኔሎቹ እና በነጋ የተተወነ መሆኑን ለመረዳት በርካታ ወራት እንደፈጀበት
ተጠቅሷል፡፡

በሌላ ምዕራፍ ደግሞ፤ በምርጫው ቀን እኩለ ሌሊት ተቋቁሞ፣ በአርከበ እቁባይ እና በጄነራል ታደሰ ወረደ እንዲመራ የተደረገው ‹‹የፖለቲካ ፀጥታ ጥምር ኮሚቴ››፣ ከ1978 ዓ.ም በፊት ወደ ትግል የገቡና ማዕረጋቸው ከኮሎኔል በላይ የሆነ የህወሓት መኮንኖች ቦሌ ላይ መሬት እንዲያገኙ ማመቻቸቱን አስነብቦናል፡፡ በአናቱም፣ ከኮሎኔል በታች ያሉ የህወሓት ታጋዮች በሌሎች ማስፋፊያ ከተሞች መሬት ማግኘታቸውን ተከትሎ የተፈጠረውን ሁኔታ ሚኒስትር ዴኤታው እንዲህ ያወጋናል፡- “…ወሬው ባድመና ጾረና ጦር ግንባር ድረስ ተዳረሰ፡፡ ወታደራዊ መኮንኖቹ ምሽጋቸውን እየለቀቁ በጦር ሂሊኮፕተሮች ጭምር እየተሳፈሩ አዲሳባን ወረሯት፡፡ የክፍለ ከተሞች ግቢ አቧራ በጠጣ የኮከብ ጋሻና ጦር ክምር የተሸከመ ካኪ ተጥለቀለቀ፡፡” (ገፅ 255-256) ዘመነኛው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ‹‹…አንዳንድ እንሰሳት ይበልጥ እኩል ናቸው›› በሚል ያልተፃፈ ሕግ ማደሩን ከውስጥ-አወቅ ምስክርነት የምንረዳው ከህወሓት ውጪ ያሉት ኢህአዴግን የመሰረቱ ድርጅቶች የአመራር አባላት ብቻ የወሰዷትን መሬት በግምገማ እንዲመልሱ መገደዳቸው በዚሁ መጽሐፍ መስፈሩን ስናስተውል ነው፡፡ በወቅቱም በግምገማው ፊት-አውራሪ በረከት ስምዖን የተዘጋጀ ‹‹ከምርጫው በኋላ የድርጅታችንን ስም ያጎደፉና የሕዝቡን ቅሬታ ያባባሱ ተግባራት›› የሚል ሃያ ገፅ ሰነድ የመነሻ ሃሳብ ሆኖ ቀርቦ ነበር፤ የግምገማው ውጤትም የተዘረፈ መሬት ማስመለሻ ፎርምን ህወሓት ያልሆኑ ከ600 በላይ የኢህአዴግ ካድሬዎች እንዲሞሉ አስገድዶ ተጠናቅቋል፡፡

ለአብነትም ደራሲው ‹‹ለታሪክ የተቀመጠው የይቅርታ ፎርም›› ብሎ በመጽሐፉ ያሰፈረውንና በአንድ የብአዴን አመራር የተሞላውን እንደወረደ ልጥቀሰው፡- “ለቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደር እኔ ህላዊ ዮሴፍ ድርጅቴ ኢህአዴግና መንግስት የጣለብኝን አደራና ኃላፊነት ወደጎን በመተው ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ የመሬት ወረራ ላይ በመሰማራት አንድ መሬት ወስጃለሁ፡፡ በመሆኑም ይህን ያለአግባብ የወሰድኩትን መሬት አስተዳደሩ እንዲረከበኝ በማክበር እጠይቃለሁ፡፡ ድርጅቴ ኢህአዴግና በእሱ የሚመራው መንግስትም ይቅርታ እንዲያደርግልኝና ከእንግዲህ ወዲያ በየትኛውም የድርጅቴንና የመንግስት ስም በሚያጎድፍ ተግባራት ላለመሰማራት ቃል እገባለሁ፡፡
ከሰላምታ ጋር ህላዊ ዮሴፍ
ግልባጭ
ለአዲስ አበባ ጊዜያዊ ባለአደራ አስተዳደር
ለቦሌ ክፍለ ከተማ ጊዜያዊ ባለአደራ አስተዳደር
ለኢህአዴግ ጽ/ቤት” (ገፅ 257)
የሆነው ሆነ ኤርሚያስ ለገሰ በዚህ መጽሔት ላይ እንዲህ በቀላሉ ጠቅሰን የማንጨርሳቸውን በርካታ አይን ያወጡ ድርጅታዊ እና ግለሰባዊ ዘረፋዎችን ልባችን ቀጥ እስኪል ድረስ አስነብቦናል፡፡ ሌላው ቀርቶ ዛሬ በየመድረኩ ‹ኢህአዴግ ጌታ ነው!›፣ ‹መለስ መሲህ ነው!›… አይነት ፕሮፓጋንዳ በማድመቅ ግንባር-ቀደም እየሆነ የመጣው ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ ራሱ የዘረፋው ተቋዳሽእንደነበረ እንዲህ ሲል ነግሮናል፡-

“ከሁሉም የሚያሳዝነው ሀገራችንን በዓለም መድረክ በማስጠራቱ የምንወደው ኃይሌ፣ በአስታራቂ ሽማግሌነቱ የምናመሰግነው ኃይሌ፣ በዓለም አደባባይ አልቅሶ ያስለቀሰን ኃይሌ ‹ኃይሌና አለም ሪል ስቴት› በሚል የድርጅት ስም በመስከረም 7/1998 ዓ.ም በቦሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 18 ውስጥ 50,000 ካሬ ሜትር ሕጋዊ ሰውነት በነዋሪው ድምፅ ከተገፈፈው አርከበ እቁባይ እጅ ወስዷል፡፡ መቼም ታላቁ ሯጭ እየተካሄደ ያለው ውንብድና አዲስ አበባን ማጥፋት እንደሆነ ሳይገባው ቀርቶ አይመስለኝም፡፡” (ገፅ 400-401)

…የወዶ ተሳዳጁ የኦህዴድ ካድሬ፣ ከሁለት ዓስርታት በላይ ሲነገርና ሲፃፍ የነበረውን ርዕሰ-ጉዳይ ለማጠናከር በርካታ የመጽሐፉን ገጾች ሰውቷል፡፡ ይህ የህወሓት ብቸኛ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ጠቅላይነት ትርክት፣ ገዢ የተቃውሞው መከራከሪያ መሆኑን በሚገባ የሚያውቀው ኤርሚያስ፣ በተለይም ባገለገለበት አዲስ አበባ ዙሪያ ያልተገለጡ የሚመስሉ ሁነቶችን አስተሳስሮ ለመተረክ ጥሯል፡፡ በርግጥ ለእግረ-መንገድ ያህል አንድ ጥርጣሬ ጥለን እንለፍ፤ ይህን መስመር አብዝቶ ማብራራት፣ ተደማጭነትን እና የፖለቲካ ሁለተኛ ዕድልን እንደሚሰጥ ሚኒስትሩ ከመረዳቱ አኳያ፤ የተባሉትን በምልዐት መቀበሉ ጥቂትም ቢሆን አስቸጋሪ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ አልፎም፣ የትግሪኛ ተናጋሪውን እና ህወሓትን ቀላቅሎ ወደመመልከት እንዳያሻግረን ብርቱ ጥንቃቄ ማድረጉም ሊታወስ ይገባል፡፡

(በሚቀጥለው ሳምንት ይህንኑ መጽሐፍ በማጣቀሻነት እያወሳን፣ የህወሓትን የፖለቲካ የበላይነት እና ጠቅላይነት የሚያሳዩ ወጎችን እንዳስሳለን)


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>