Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

በውንብድና የሚቆም የነፃነት ትግል አይኖርም! –በነብዩ ኃይሉ

$
0
0

ነብዩ ኃይሉ / የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ

እጥፍ ወርቅ በልስቲ በአንድነት ፓርቲ ውስጥ በተለያዩ የአመራርነት ቦታዎች ላይ ተሳትፋለች፡፡ እጥፍ ወርቅ የሰባት ወር ነብሰጡር መሆንዋ ህወሓት/ኢህአዴግ እና ምርጫ ቦርድ ብዙ ዋጋ የከፈለችበት ፓርቲ ላይ የሚያደርሱትን የማፍረስ ሴራ ተቃውማ ሰልፍ ከመውጣት አላገዳትም፡፡ በሰልፉ ላይ የገዢው ቡድን ፖሊሶችና የደህንነቶች ሲያዩዋት ደሟን ሊያፈሱ ቋመጡ፤ በአንዲት እንደ ቤተክርስቲያን ተሳላሚ ተከናንባ ቀበና መድሃኔዓለም ቤተክርስቲያንን በተደገፈች ወኪላቸውም ጥቆማ ጐትተው መሬት ላይ ጣሏት፤ አንገቷ ላይ የነበረውንም የወርቅ ሀብል በጥሰው በእጃቸው አደረጉ፡፡ ‹‹ነብሰጡር ነኝ፣ ሀላፊነቱን ትወስዳላችሁ›› እያለች ብትሟገትም ሽንጧ ላይ በጫማቸው ከመርገጥና በዱላ ጉዳት ከማድረስ አልተቆጠቡም፡፡

ጋዜጠኛ ስለሺ የተደበደበው ሰውነቱ በፋሻ ተጠቅልሎ ይታያል

ጋዜጠኛ ስለሺ የተደበደበው ሰውነቱ በፋሻ ተጠቅልሎ ይታያል

ለዘመናት በአገዛዝ ስርዓት ውስጥ ለማቀቀች እንደ ኢትዮጵያ አይነቷ ሀገር መንግስታት በዜጐቻቸው ላይ የሚወስዱት የሀይል እርምጃ አዲስ ላይሆን ይችላል፡፡ የህወሓት/ኢህአዴግ ተግባር ግን “መንግስት” ተብሎ እንዲጠራ የሚያደርገው አይደለም፡፡ ሽፍታ ለማለትም አይመጥንም፤ ሽፍታዎች ቢያንስ ለህፃናት፣ ለሴቶች እና ለአረጋውያን የርህራሄ ስሜት ያሳያሉ፡፡ ህወሓት/ኢህአዴግ ጋር ይህ አይታሰብም፤ ገዢው ቡድን ደም ማፍሰሱ የሚያረካው፣ የሚያስፎክረው፣ በማን አህሎኝነት የተወጠረ የወንበዴ ስብስብ ነው፡፡ ገዢውን ቡድን ከመንግስትነት ያስቆጠረው፣ በጭካኔ ተግባሩ ያስቀጠለው ግፍ መቀበልን የለመደው ድርቡ ቆዳችን ነው፡፡

በኢትዮጵያችን “ፖሊስ የህዝብ ነው” የሚለው አባባል ፌዝ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ፖሊሶች ህዝባዊነታቸውን ትተውና ረስተው ለስርአቱ አድረዋል፡፡ ከህግ ይልቅ ደም ለጠማቸው አዛዦቻቸው ቅድሚያ በመስጠት ደም ለማፍሰስ ሲተጉ ይታያሉ፡፡ ወንጀል ተከላክለው ሳይሆን የንፁሀንን ደም አፍስሰው የሚሰጣቸው ሹመትና ሽልማት ከፍ ያለ ነው፡፡ የገዢው ፓርቲ ፖሊሶች ባለፈው ዕሁድ ጥር 17 ከአንድነት ጽ/ቤት የወጣውን ሰልፈኛ ደም ለማፍሰስ የተጠቀሙት ህወሓት በረሃ እያለ የሚጠቀምበትን የቆረጣ ስልት ነው፡፡ ያህንን ስልት ባለፈው አመት ሰማያዊ ፓርቲ ሳውዲ ኤምባሲ አቅራቢያ ባደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ላይም ተጠቅመውበታል፡፡ ፖሊሶቹ ሰልፈኛውን ለመበተን በአንድ አቅጣጫ ብቻ መንገድ መዝጋት በቂያቸው ነበር፤ ሆኖም የደም ግብር ያለባቸውን የገዢውን ቡድን ባለስልጠናት ለማስደሰት ሲሉ ሰልፈኛውን በሁሉም አቅጣጫ ከበው የግፍ በትራቸውን አሳረፉ፤የሻቸውንም ዘረፉ፡፡

ባሳለፍነው እሁድ የአንድነት ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ላይ የተወሰደው ፍጹም ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት፤ ገዢው ቡድን ደም በማፍሰስ የሚረካ የወንበዴ ስብስብ እንደሆነ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ የገዢው ቡድን ፖሊሶችና ደህንነቶች፣ አንድነት የጠራውን ሰልፍ ለማጨናገፍ ያለሙ ብቻ ሳይሆኑ የሰዎችን ደም ማፍሰስንም ግባቸው ያደረጉ ነበሩ፡፡ ለዚህም ነው የሰባት ወር እርጉዝ መሬት ላይ ጥለው በጭካኔ የረገጡት፣ ለዚህ ነው የአምልኮ ስፍራን በደም በተጨማለቀ ርካሽ ማንነታቸው አርክሰው በፀሎት ላይ የነበሩ የ70 አመት አሮጊት በጭካኔ የደበደቡት፣ ለዚህ ነው እጁ ተሰብሮ የወደቀን ጋዜጠኛ ከበው እንደ እባብ የቀጠቀጡት! ለዚህ ነው በድብደባው ባለመርካት ሴት ልጅ የያዘችውን ቦርሳ ወርቅና ሞባይል ቀምተው መሬት ላይ በመጣል ልብሷን የሚቀዳድዱት፡፡ ለዚህ ነው ከሰውነት አስተሳሰብ ወርደው የአውሬን ጭካኔ የተላበሱ ኃይሎች የነፃነት ታጋዮች ላይ በጠራራ ፀሐይ ውንብድና በመፈፀም የነፃነት ትግልን ለማስቆም የሚውተረተሩት፡፡

10408950_766897883395148_5792329559256241629_n (1)

ይህ የምታዩት የስለሺ ሐጎስ የተሰበረ አጥንት ነው። እንግዲህ ይሄ እስኪሆን ድረስ ነው ይህን ሰላማዊ ወጣት የደበደቡት !!!! በአገር ዉስጥና ከአገር ዉጭ ያላችሁ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ተመልከቱ። እነዚህ አጥንቶች የተሰባበሩት ለከንቱ ነገር አይደለም። ለነጻነት ነው። ለኢትዮጵያ አንድነት ነው። ለፍትህ ነው። ለእኩልነት ነው። ሕወሃት ስጋችንን ሊበላ ፣ አጥንቶቻችን ሊሰብር ይችላል። ሆኖም መንፈሳችንን፣ ወኔያችንን፣ አንድነታችንን ሊሰብር አይችልም። አንፈራም። አናቀረቅረም። አንገታችንን አንደፋም። አናፈገፍግም። ዝም አልንም። ድምጻችንን እናሰማለን ! ከያለንበት፣ በዘር፣ በቋንቋ ም በድርጅት ሳንከፋፈል እንነሳለን። ይህ አይነት፣ ጨካኝ ስርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲወገድ እንሰራለን ! አራት ኪሎንን እና የሕወሃት ጽ/ቤትን የተቆጣጠረው፣ በሕዝባችንን ደም እየጠጣ የሚረካው አጋንንት ከአገራችን እናባረራለን። የፊታችን እሁድ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች አሉ። ለሰለፎቹ እንዘጋጅ!!!!! ዱላና ማስፈራሪያ እንደማይበግረን እናሳያቸዋለን !!!

ገዢው ቡድን፣ ባሰለፈው ሰራዊትና በመሣሪያው ብዛት ተማምኖ የሚፈፅመው የአውሬ ተግባር በየትኛውም መለኪያ የነፃነት ትግሉን እንደማይገታው የሚያረጋግጠው እንደ ህወሓት/ኢህአዴግ በአውሬነት የብዙ ንፁሃንን ደም በጠራራ ፀሐይ ያፈሰሰው የግራዚያኒ ተግባር ነው፡፡ ግራዚያኒ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ደም ቢያፈስም የነፃነት ትግሉ ግን አልቆመም፡፡ የግራዚያኒ የግፍ ተጋሪ የህወሓት/ኢህአዴግ ተግባርም ትግሉን ከማፋፋም ባለፈ እንደማያኮስሰው መሰል አምባገነኖች ታሪክ ምስክር ነው፡፡

በዕለቱ በፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ላይ    የደረሰው ዘግናኝ ድብደባ በአይን የሚታይ አካላዊ ጉዳት ቢያስከትልም በተቃራኒው ረቂቅ የሆነ የመንፈስ ፅናት ሰጥቷቸው አልፏል፡፡ ግፈኞች፣ በጭካኔ ተግባራቸው የህዝብን መንፈስ ለማድቀቅ ቢሞክሩም፣ በተቃራኒው በራሳቸው ላይ ቆራጦችን እየመለመሉ እንደሆነ አልተገነዘቡትም፡፡ ለዚህ አባባሌ ማሳያ የሚሆነኝ ከሁሉም በላይ አስከፊው የአካል ጉዳት የደረሰበት ወዳጄ ጋዜጠኛ ስለሺ ሃጎስ፤ እጁ ተለያይቶ፣ ፊቱ ተሰንጥቆ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የሰጠኝ አስተያየት ነው፡፡

በነገራችን ላይ ጋዜጠኛ ስለሺ ሃጐስ ለወንበዴዎቹ የግፍ በትር አዲስ አይደለም፤ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪም በአካሉም በመንፈሱም ላይ ተፈራርቆበታል፡፡ ከአራት አመታት በፊት በገዢው ቡድን አካላት ታስሮ በማዕከላዊ በርካታ የግፍ ማሰቃያ ተግባሮች ተፈፅመውበታል፡፡ ጋዜጠኛው በግሉ ከመታሰሩ፣ ግፍ ከመቀበሉም በላይ ውድ እጮኛውን ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ፤ ግማሽ  እሱነቱን ይዛ ታስራበታለች፡፡ በእሁዱ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በድብደባ እጁን ተሰብሮ በወደቀበት ከስምንት ያላነሱ የገዢ ቡድን ፖሊሶች በወደቀበት እንደ እባብ ቀጥቅጠውታል፡፡ በድብደባው በግራ ጉንጩ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ የጋዜጠኛው የትግል መንፈስ በማዕከላዊ ስቃይ እንዳልተፈታው፣ በንጹኋ እጮኛው እስር እንዳልቆመው ሁሉ እሁድ በተፈፀመበትም የግፍ ተግባርም አልተሸረሸረም፡፡

ጋዜጠኛ ስለሺ ሃጎስ፣ ለመላው የነፃነት ታጋይ የሚከተለውን መልዕክት አስተላልፏል፡፡ “በሰልፉ ላይ ስሳተፍ ከዚህ የበለጠ ጉዳት እንደሚደርስብኝ ጠብቄ ነበር፡፡ የገዢውን ቡድን አውሬነት ከማንም በላይ እገነዘበዋለሁና የደረሰብኝ ጉዳት አንድ ኢንች ከጀመርኩት ትግል አያስቆመኝም፡፡ በሚቀጥሉት ሳምንታት ፓርቲዬ በሚጠራቸው ሰልፎች ላይ እገኛለሁ፡፡ ትግሉ ይቀጥላል! ድል የህዝብ ነው!”

እኛ የምንታገለው፣ ተፈጥዊ ነፃታችንን ለማስመለስ እና እንደሰው በክብር ለመኖር ነው፡፡ እነሱ በተቃራኒው ከለውጥ ተፈጥሯዊነት ጋር የእውር ድንብራቸውን በጉልበት እየተፋለሙ ነው፡፡ እነሱን ለዛሬው ድል ካበቋቸው ነገሮች አንዱ ምናልባትም ዋነኛው የደርግ ጭካኔ የገፋቸው ብሶተኞች በገፍ ትግሉን መቀላቀላቸው እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ዛሬም ለእርጉዝ ሴት፣ ለአቅመ-ደካማ አሮጊት፣ በእጃቸው መፈክር እንጂ ዲሞትፈር ባልያዙ ወጣቶች ላይ የሚፈፅሙት ግፍ ታሪክ እራሱን እንደሚደግም የሚያስረግጥልን ነው፡፡ በርካታ አምባገነኖች፣ በውድቀታቸው ዋዜማ ጭካኔያቸው እንደሚበዛም የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በአንድ ነገር ግን እንፅናናለን የወገኖቻችን ደም በከንቱ ፈሶ አይቀርም፡፡ የነፃነት ቀን ቀርባለች ወደ አደባባዮችም ደግመን ደጋግመን እንወጣለን፡፡

 

 

The post በውንብድና የሚቆም የነፃነት ትግል አይኖርም! – በነብዩ ኃይሉ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>