ይሄይስ አእምሮ (ከአዲስ አበባ)
ይህ ኢትዮጵያዊነት በስንት ረገድ ቁጭት ውስጥ እየከተተን እንደሆነ እናንተም አስቡት፡፡ በእጅጉ የሚገርም ሁኔታ ውስጥ እየከተተን ነው ያለ፡፡ በዚህች ሌሊት ሰባት ሰዓት ገደማ ያነበብኩት ጽሑፍ እንኳን ክፉኛ ዕንቅልፍ ነስቶኝ ከሌሊቱ አሥር ሰዓት ላይ ከሚጥመው መኝታየ ተነስቼ ይሄውና መዶግዶግ ያዝኩ – ለነገሩ ሳለ ወያኔ ምን የሚጥም መኝታ አለና!
በዚያን ሰሞን ኤርምያስ በዲ/ን ዳንኤል ላይ ያቀረበውን ጽሑፍ አንብቤያለሁ – (የቅንፍ ወሬ ደስ ይለኛል፡- እነኚህ “ዲያቆን” እና “አምባሳደር” የሚሏቸው አጠራሮች(ሹመቶች?) ግን በምን ሁኔታና እስከመቼ እንደሚሰጡ ሲገርመኝ የሚኖር መሆኑን ከዚች አጋጣሚ ውጪ የምገልጽበት ሌላ አጋጣሚ የማገኝ አይመስለኝም – ዲ/ን ዳንኤል ራሱና ሌሎች ትላልቅ ዲያቆናትን ጨምሮ ለዘመናት በዚህ ማዕረግ መጠራታቸው፣ የወያኔው ግብረ በላ አምባሳደር ተሾመ ቶጋና አምባሳደር አሃዱ ሣቡሬ እንዲሁም ሌሎች በዚህ የአንድ ወቅት ሹመት ዕድሜ ልክ መጠራታቸው … ይገርመኛል) ፡፡
ኤርምያስ በጽሑፉ ዲ/ን ዳንኤልን ተችቷል፡፡ ዲ/ን ዳንኤልም ራሱ በአቃቂር ጽሑፉ እንደገለጸው ጥቂት ዘግይቶም ቢሆን መልስ ሰጥቷል፡፡ በጽሑፍ መተቻቸታቸው ትልቅ የሥልጣኔ ምልክት መሆኑን እንደአካሄድና እንደአረዳድ በበጎ መልክ ወስጀዋለሁ፡፡ ምክንያቱም ይህ ጅምራቸው ከኩርፊያና ቅጥ ካጣ የእጅጌ መሰብሰብ እንዲሁም ከሽመል ሊላቀቅ ካልቻለው የዐመፃና የአለመቻቻል ሥር የሰደደ ባህላችን – በሁላችንም ባይሆን በአብዛኛዎቻችን ዘንድ እስካሁን እንደሚታየው ማለቴ ነው – በመጠኑም ቢሆን ወጣ ያለና በንግግር ለመግባባት የሞከሩበት ስለሆነ ነው፡፡ ቢሆንም ዕንቅልፍ ያሳጣኝ ችግር አይቼበታለሁና ሌሎቻችንን ቢጠቅመን ከሚል ቅን አሳብ ትንሽ ማለትን ወደድሁ፡፡
ሁለቱንም እወዳቸዋለሁ፤ አከብራቸዋለሁ – በዘመኑ ኤፌማዊ ቋንቋ ፍቅሬን ለመግለጽ ያህል፡፡ በተለያዩ አቋሞች ሥር የተሠለፉ ቢመስሉኝም ሁለቱም ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው በመሰላቸው መንገድና ዘዴ እያገለገሉ የሚገኙ የአንዲት እምዬ ኢትዮጵያ ውድና ብርቅዬ ልጆች ናቸው – ቢስ አይይብንና፡፡ ሁለቱም ዕድል ቢያገኙ ይህን የተገፋና የተደቆሰ ሕዝብ ወደላይ እንዲወጣና እንደሕዝብ እንዲታይ፣ ሰብኣዊ ፍጡርነቱ ተከብሮ እንደሰው እንዲቆጠርና መኖር እንደሚገባው እንዲኖር በማድረጉ ጥረት ውስጥ የበኩላቸውን በጎ አስተዋፅዖ ማበርከት የሚችሉ ምሁራን ናቸው፡፡ ሁለቱም ብዙ አወንታዊ ነገሮች የሞሉባቸው ጥሩ ጊዜ ሲመጣልን የሚጠቅሙንና በርካታ ቀዳዳዎችን የሚሸፍኑልን የጉድለታችን መሙሊያዎች ናቸው – አላበዛሁባቸውም፡፡ “አመስጋኝ አማሳኝ” እንዳትሉኝ አደራ፡፡
ይሁንና ሁለቱ ሲተቻቹ በተለይም ዲያቆኑ ያሳየው ያልተገባ የመሰለኝ አቀራረብ በእጅጉ ያሳዘነኝና ለጊዜውም ቢሆን ዕንቅልፍ የነሣኝ መሆኔን በድጋሚ መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ እንተቻች፤ እንወቃቀስ፤ ነገር ግን በጨዋነት ይሁን፡፡ ማጠንጠኛዬ ይህች ነች – ጨዋነት፡፡ እርግጥ ነው – ስሜትና እውነት፣ ንዴትና እልህ እየተዛነቁብን በሚገኙበት ሁኔታ ውስጥ ሆነን ከተናገርን ወይም ከጻፍን ለትዝብት የሚዳርጉ አንዳንድ ግርምቶች እንደሚከሰቱ የታመነ ነው፤ ሰው ደግሞ በጥቅሙ ወይ በፍላጎቱ ወይ በአንዳች የማይፈልገው ነገር ሲመጡበት ድንጉጥ ነው – ያገኘውን በመወርወር መመከት ይፈልጋል፤ ሲናደድ በፈረንጅኛው አጠራር rationality, logic, reasonableness, sound judgment, ቅብጥርስ ቅብጥርስ ከኅሊና ጓዳ ይሠወራሉ፡፡ ለዚህ መፍትሔው ምናልባት በረድ ሲሉ መጻፍና ከተቻለም ጽሑፍን ደጋግሞ ማየት(ኤዲት ማድረግ)፣ ዳግመኛም ከተቻለ ለጓደኛና ለዐዋቂ ማሳየት ቢቻል ደግ ነው፡፡ አለበለዚያ ከአፍ ከወጣ አፋፍ ይባላልና የገነቡትን ዝምና ዝና በአንዴም ባይሆን ቀስ በቀስ መናድ ይከተላል፡፡ ሮም በአንድ ቀን አልተገነባችም፤ በአንድ ቀንም አልፈረሰችም፡፡ ኢትዮጵያም፡፡
ብዙዎቻችን ለዚህ ዓይነቱ ችግር የምንዳረግ መሆናችን ይታወቃል፡፡ እኔም በዚህ ረገድ ራሴን ስመለከተው ብዙውን ጊዜ አጠፋለሁ፤ ማጥፋት ደግሞ ሰውኛ ነው – የማያጠፋ(የማይሳሳት) የሞተ ብቻ ነው፡፡ መጸጸትና ንስሃ መግባት ሰውኛ ነው፡፡ ዋናው አወንታዊ ነገር ግና በስህተት ቆርቦ እስከወዲያኛው መጽናት ሣይሆን ከስህተት መመለሱና ወደስህተት የሚያመሩ መንገዶችንና መጥፎ ዕድሎችን መዝጋቱ ላይ ነው፡፡ አስቀድሜ እንዳልኳችሁ እኔም ብዙ ጊዜ እንደምሳሳት አውቃለሁ፡፡ ሆኖም የኔ ዕዳው ገብስ ነው፡፡ እኔ እንደነሱ አልታወቅምና እኔ ብሳሳት ‹አቧራ አይጤስም›፤ አለመታወቅ ለመሳሳት ዋስትና ይሆናል እያልኩ ግን አይደለም – መማርና ራሴን ማስተካከል እንዳለብኝ ይገባኛል፡፡ በነዚህ ወንድሞቼ መካከል ያለው ትግትግ ግን ከቅርብ ከሩቅም የብዙ ዜጎችን ትኩረት ይስባልል፡፡ ሁሉን ያነጋግራል፡፡ ስለዚህ አንደበትን ቆጠብ ማድረጉ አስተማሪነትም ጨዋነትም አለው፡፡ ከሁሉ በፊት እኛን ትልልቆቹን ሳይሆን የምንቀርጸውን ወጣት ትውልድ ማየት ይገባናል፤ ቦሃ ላይ ቆረቆር እንዳይሆንብን በወያኔው ምግባረ ብልሹ ሥርዓት ከሁሉም መልካም ዕሤቶች ውጪ እንዲሆን ሆን ተብሎ ግፍ እየተሠራበት የሚገኘውን የሀገራችንን ወጣት መታደግ የምንችለው ቢያንስ እኛ ትልልቆቹ በቅጡ የመነጋገርና በግልጽነት የመወያየት ባህል ስናዳብር ነው፡፡ “ምን እያስተማርነው ነው?” ብለን ራሳችንን እንጠይቅ፡፡ እያስተማርነው ያለነው አሽሙርንና ለበጣን ነው? መቻቻልንና የአብሮነትን ኑሮ ጠቀሜታ ነው? የዐዋቂነትንና በሣል አእምሮ ባለቤት መሆን የሚሰጠውን ጥቅም ነው? የመጣልንን ሁሉ በንዴትና በስሜት እሰው ላይ ብንዘረግፍ ባረጀና ባፈጀ የአስተሳሰብ ጭቅቅት እንበክለዋለን እንጂ በዘመናዊ አስተሳሰብ የተዋጀ መስተጋብራዊ ሕይወትን አላስተማርነውም፡፡ ዕድሜና ትምህርት ሊገሩንና ከደመነፍሳዊ የእንስሳነት ባሕርያት ነፃ ሊያወጡን ይገባል፡፡ ስህተትን ደግሞ በስህተት አናርመውም – እናብሰዋለን እንጂ፡፡ መጽሐፉስ “ብዔል ዘቡል በብዔል ዘቡል አይወጣም” ይል የለም? እናስ? ተሸክመነው የምንዞረው መጽሐፍ ምሥጢሩ ሳይገባን አንዳንዶቻችን በየጉያችን ከምናንጠለጥለው አሸንክታብ በምን ተለዬ?(ለፈገግታ ያህል፡- አንዷ ሴት ወይዘሮ ባሏ እንደማይወዳት ለየጠንቋዩና መጣፍ ገላጩ ትገልጥና መፍትሔ እንዲሰጧት ትማጠን ይዛለች አሉ፡፡ ሁሉንም ሞክራ አልተሣካላትም – ባሏን መሳብ አልቻለችም፡፡ የመጨረሻው ደፍተራ የሰጣትን አሸንክታብ የቆዳ ልባሱን ተርትረው በቀይና በጥቁር ቀለማት የተጻፈውን ጠልሰም ሲያነቡት ጊዜ ወረቀቱ ከላይ እሰከታች ምን ሆነ መሰላችሁ – “ቢወድሽ ባይወድሽ እኔ ምን ቸገረኝ፣ ቢወድሽ ባይወድሽ እኔ ምን ቸገረኝ ….” የሚል ሆኖ አገኙት፡፡ ተመልከቱ – ደብተራና አባይ ጠንቋይ ሣይቀሩ የሀገራችንን የዋህ ሕዝብ እንዴት እንደሚጫወቱበት፡፡ እነመለስማ እንዴቱን ይበልጥ አይጫወቱብን! እኛ ቁልቁል ያልጋለብን ማን ይጋልብልን?)
በኤርምያስ ጽሑፍ ውስጥ እስከዚህ የሚያናድደኝ ነገር አልገጠመኝም – ካነበብኩት ራቅ ቢልም እንኳን፡፡ አሁን ትዝ እንደሚለኝ ጠንካራ ቃል ተብሎ ከተወሰደ በዲያቆኑ የሆነ ነገር – አቋም ወይም አመለካከት ሣይሆን አይቀርም – ክፉኛ መነካቱን የገለጠበት ከረር ያለ ድምፀት ነው – “አስደነገጠኝ” የምትል ቃል የተጠቀመ መሰለኝ – ያቺ ነገረኛ ቃልም ትመስለኛለች የዳኒን የክት ቃላትና የተረትና ምሣሌ ኮረጆ ቦትርፋ ምሥኪኑ ኤርምያስ ላይ የነገር ዶፍ እንዲወርድ ያደረገችው፡፡ ከዚያ ውጪ ወጣቱ የበፊት ፖለቲከኛና የአሁን አክቲቪስት ይህን ያህል ሊያናድድና ፀጉር ሊያስነጭ የሚችል ነገር የጻፈ አይመስለኝም፡፡ በነገራችን ላይ ለኤርምያስ አቦካቶ ልሆንለት አስቤና ፈልጌ ሣይሆን ለኔ እውነት ከመሰለኝ ዐምድ ተነስቼ የግል ምሥክርነቴን ለመስጠት ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሌሎቻችን ወደዚህ ዓይነት መተቻቸት ስንገባ የእውነትን ዘገር ይዘን ከከንቱና አማሳኝ ቃላትም ተቆጥበን መረጃና ማስረጃ ባላቸው እውነቶቻችን ላይ ብቻ ማተኮር እንደሚገባን ለመጠቆምም ነው – ከስብዕናዎች እንውረድ እባካችሁ፡፡ የሰውን ስም መበከል ምን ይፈይዳል? ሥራውን እንጂ ለምን ሰውን ለማርከስ እንቻኮላለን? ይሄኔ ነው ይልቁንስ ያቺን የፈረደባትን “የየጁ ደብተራ ቅኔው ቢጎድልበት ቀረርቶ ጨመረበት” ብሎ መተረት፡፡ ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት መኖሩን ደግሞ ሥነ ቃላችንም አስቀድሞ ጠቁሟልና ሰው ተሳሳተ ብለን – እኛም እንደማንሳሳት በማመን – አቅላችንን ስተን አንንዘርዘር፡፡ በርጋታ እየተያየን በእውነቱ መንገድ ብቻ በመጓዝ ካልተተቻቸን ክፍተቶች ይበልጥ እየተንቦረቀቁ፣ ከመስማማት ይልቅ ጠብና ቅራኔ እየተበራከተ ይሄድና በመጨረሻው ቡና መጠራራቱና መቀባበሩም እንዳይቀር ያሰጋል – መቀባበሯን እንኳን እናውቅባታለን – መቀባበር ደግሞ ለሀበሻ ይጥፋው! አሄሄ፡፡(በመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ቦታ ላይ እንዲህ የሚል ጥቅስ አለ – በራሴው ቃላት ላስቀምጠው፡- “ከሰዎች አንደበት በሚወጡ ቃላት ይሄን አሉኝ ብለህ የምትኮንናቸውና የምትወቅሳቸው ከሆነ አንተም በምትናገረው ውስጥ ሌሎችን የሚያስቀይም ብዙ ነገር አለበትና ጥፋቱ የሁላችሁም መሆኑን ተረዳ፡፡”በመሆኑም ወደ መግባባትና ዕርቅ እንጂ ወደባሰ ግጭት ከሚያመራ ንትርክ እንታቀብ ምዕመናን፡፡ ሁሉም ያልፋል፡፡ የማያልፈው ግን አጥንትን ሰርስሮ መቅ ድረስ የሚዘልቅ ክፉ ቃል ነው፡፡) ወደ ዳኒ ልሂድ፡፡
ዳኒ እንዴት ነህ? እንዴት ነው ነገሩ? በምን “ሙድ” ውስጥ ሆነህ ነው ይቺን ጽሐፍ የጻፍካት? እኔ አንዲት መጣጥፍ ወደ ገጸ ድሮች (ድረ ገፆች) ከላክሁ በኋላ እንደ አንባቢ በድጋሚ አነባታለሁ፡፡ እንደ አንባቢ የራሴን ትችት አወጣላታለሁ፡፡ ስሰዳት የነበረኝ “ሙድ” እና ቆይቼ እንደ አንባቢ ሳነብባት የሚኖረኝ “ሙድ” (ስሜት ብለውስ?) አዎ – ስሜት የሚለያይበት ብዙ አጋጣሚ አለ፡፡ “ይህን ባላልኩ ኖሮ፣ ይህን ብጨምር ወይም ብቀንስ ኖሮ ወዘተ.” በሚል የምቆጭባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አይደሉም፤ ጽሑፍ አስቸጋሪ ነው፤ የአርትዖት ሥራ ደግሞ እንደጨጓራ ቢያጥቡት የማይጠራ አድካሚ ሥራ ነው፤ በአንድ በኩል የምታስደስተው ሰው ይኖራል – በሌላኛው ጫፍ ደግሞ የምታስከፋው ሰው ይኖራል፤ ዓለም ሰጥቶ የመቀበል መድረክ ናት – ከአንዱ ይጎድላል – ለሌላውም ይጨመራል፤ ክፋቱ ደግሞ የጎደለበትም የተጨመረለትም የሚያዝኑበት አጋጣሚ መኖሩ ነው – የዘገነም አዘነ ያልዘገነም አዘነ እንዲሉ፡፡ በነገራችን ላይ ዳኒ – አንተስ ኤርምያስ ላይ በጻፍከው ነገር የኔን ዓይነት ስሜት ተሰምቶሃል? ቆይተህ ጽሑፍህን ስታነበው “አይ፣ ከኔ ዓይነት ማኅበረሰብን ቀራጭ የክርስቶስ ሐዋርያ ይህን የመሰለ ጎናጭና አቀራረቡ በአሉታዊነት የተሞላ ጽሑፍ መጻፍ አልነበረብኝም” ብለሃል? ብትል በወደድኩ፡፡ ለንስሃ ቀነ ገደብ የለውም፡፡ እንደገና ጽሐፉን መርምረውና በሌላ መድረክ ብቅ ብለህ ትልቅነትህን አሣውቀን፡፡
አንድ የቤተ ክህነት ሰው ይቅር ባይ ነው ወይም መሆን ይኖርበታል፡፡ ክርስቶስ ምን ነበር ያለው? አንዱ ቀርቦ “ጌታ ሆይ ጠላቴ ሰባት ጊዜ ቢበድለኝ ሰባት ጊዜ ሁሉ ይቅር ልለው ነውን?” ቢለው “ሰባት ጊዜ ሰባትም ቢሆን ይቅር በለው” አይደለምን ያለው? ለቀባሪው እያረዳሁ መሆኔን አላጣሁትም – ቢሆንም አንዳንዴ እንዲህ ቢሆንስ ምን ይለናል? የዚህን ልጅ ስህተት – ስህተትም ሠርቶ ከሆነ – በተገቢው መንገድ መጠቆምና እንዲስተካከል – ወደሳተው የእውነት መንገድም እንዲመለስ ማድረግ የሚቻለው በሽሙጥና በአግቦ ነውን? ይህ ዓይነቱ አቀራረብህ ልጁ ይበልጥ እንዲሳሳት ይገፋፋው ይሆናል እንጂ በኔ እምነት ቅንጣት አያስተምረውም ባይ ነኝ፡፡ የሚያስተምር ጽሑፍ ከመነሻው ያስታውቃል፡፡
አጀማመርህን ራሱን ተመልከተው፡፡ ልጥቀስልህ ፡-
የኤርምያስ ለገሠን ‹ግልጽ ደብዳቤ› አነበብኩት፡፡አንብቤው በሁለት ምክንያት ሳልጽፍለት ዘገየሁ፡፡በአንድ በኩል ስለኤርምያስ ከነበረኝ የዋሕ ግምት የተነሣ ኤርምያስን ያህል ሰው ይህን ያህል አይሳሳትምና በቀጣዮቹ ቀናት በስሜ የወጣ ጽሑፍ ነው እንጂ የጻፍኩት እኔ አይደለሁም ይል ይሆናል ብዬ በመገመት፡፡ ጽሑፉ እንደወጣ ብዙ ሰዎች አሁን እኔ የምነግርህን ሲገልጡት ነበርና ትሰማቸዋለህ ብዬ አስቤ ነበር፡፡ …
እርግጠኛ ሆኜ ልነግርህ የምወደው ነገር ኤርምያስ አልጻፈውም ከሚል አመክንዮ በመነሣት መልስ ለመጻፍ እንዳልዘገየህ እንኳንስ እኔ የገዛ ኅሊናህም ያውቀዋል፡፡ ይህን ያልከው የኤርምያስን አንተን የመተቸት ድፍረት አግዝፈህ በማሳየት ኃጢአቱን የተራራ ያህል ለማጉላት ይመስለኛል፤ ግምት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለኔ ከንቱነት ነው፡፡ ለዚህ ልጅ የነበረህ “የዋሕ” ግምት ደግሞ አልገባኝም፡፡ ገባኝ ብዬም ላስብና ይሄ የዋሑ ግምትህ አንተን በመተቸቱ ምክንያት ብቻ እንዴት በአንድ ቅጽበት እንደጉም ሊበን እንደጤዛም ሊረግፍ ቻለ? “የቄሣርን ለቄሣር” ትሉ የለምን? በአንድ ሰው ላይ የነበረን ግምት ምንም ይሁን ምን እኛን በተቃወመ/በነቀፈ ቁጥር የሚዋዥቅ መሆን አለበት? እስኪ ደግመህ አስበው፡፡ እንደኔ በቀላሉ “ጊዜ ስላልነበረኝ ዘገየሁ” ማለቱ በቂህ ነበር፡፡ ማንም ማንንም ቢተች ምን ክፋት አለው? ታላቁን የምድርና የሰማይ ፈጣሪንስ “ወይ ፍረድ ወይ ውረድ!” እያልን ቂጣ በቆረጠ አፋችን ስንተቸውና ስንነቅፈው እንውል የለም እንዴ? ምናልባት ከልምድ እንደተረዳሁት ራሳችንን የምናኖርበት ቆጥና የቆጡ ርዝማኔ እያስቸገረን በምን ተደፈርኩ ስሜት ድብቅ ባሕርያታችን ሊወጡብን እንደሚችሉ ማመን ይቻላል፤ ያኔ ድንገት ደርሰን ፊጋ ስንሆን ድብቁ እኛነታችን ይገለጥና ጠሓይ ይሞቀዋል፤ ፍጹም ሰው የለምና ይህ ዓይነቱ ክስተት የኮክቴል ግብዣዎችን ጨምሮ በአንዳንድ አጋጣሚዎች ብቅ እያለ የሰዎችን እውነተኛ ጠባይ ሲገልጥ ይስተዋላል፡፡ ይህ ዓይነቱ ድንገቴ በመሠረቱ መጥፎ አይደለም ፤ ምክንያቱም የማን ምንነትና ማንነት ከሚመዘንባቸው መንገዶች መካከል ይህ ዓይነቱ የEQ (Emotional Quotient) መለኪያ አንደኛው በመሆኑ፡፡ ሰው በመጠጥ ቀንና በውኃ ቀን እንደሚለያየው በንዴትና አለንዴትም በጣም ይለያያል – ሲለያይ ውሎ ሲለያይ ቢያድር ግን ይህን ያንተን ያህል መራራቅ አይኖርበትም – አንተ እኮ በብዙዎች ዘንድ ናሙና(አይከን) ነህ፤ አንተን መሰሉ የሕዝብ ሰው፣ አንተን ዓይነቱ የወጣትና ጎልማሣው አርአያሰብዕ ብዙ ጥንቃቄ ያሻዋል፤ ደጋግሞ አስቦ መናገርን፣ ደጋግሞ አስቦ መጻፍን፣ ደጋግሞ አስቦ መሆንና አለመሆንን ይጠይቃል፡፡ ብዙ የዋህ ተከታይ አለ፤ ሳያመዛዝን አንተ የምትለውን ሰምቶ ገደልም ቢሆን የሚገባ ጭፍን ጭፍራ አለ – ታውቃለህ፤ አውቃለሁ፡፡ ለዚህ ነው ብዙ ጅላጅሎች በአንተ ጽሑፍ ሥር በሰጡት አስተያየት(ኮሜንት) አንድም ተጨባጭ መሠረት የሌለው የሞገደኛ ስሜት ነፀብራቅ ልናይ የቻልነው – አየህ፡- “እምነት በሞኝነት ነው” የሚለውን ብሂል በተግባር የሚያሣየ ብዙ የዋሃን አሉ፡፡ በባህላችን ሰው በሞቅታ ወቅት አንዳች ቁም ነገር ለውይይት ሲነሣ “በውኃ ቀን እንመለስበት” የሚለው ወድዶ አይደለም፤ እንደገናም “በተናደድክ ጊዜ ልጅህን አትቅጣ” የሚባለውም አለብልሃት አይደለም፡፡ ስለሆነም ንዴትም ከስካር አንድ ስለሆነ ተናደን የምንጽፈውን ነገር ቆይተን መቃኘቱና መዳበሱም አይከፋም፡፡
በአጠቃላይ – ይቅርታ ማድረግ የሚገባው ካለ ይቅርታ ያድርግልኝና – በዚህ የዳንኤል ጽሑፍ በውነቱ በጣም ተበሳጭቻለሁ፡፡ አልተማርኩበትም፡፡ ተጀምሮ እስኪጨረስ በአሽሙር ደለል የተሞላ ነው፤ አሽሙሮቹን እዚህ መድገሙን አልፈለግሁም፤ ከክርስቶሳዊ አስተምህሮ ዐይንና ናጫ የሆነው ይህ የዳንኤል ጽሑፍ ግን ከርሱ በሳል አእምሮ የምጠብቀው አይደለም – ብዙ መሳጭና አስተማሪ ጽሑፎቹን በጉጉት አንብቤያለሁ፤ ዳኒ ለኔ የስስት ሰብኣዊ ሀብቴ ነው፡፡ ያ ጽሑፍ “ቀኝህን ቢጠፋህ ግራህን አዙርለት፣ እጀ ጠባብህን ቢፈልግ መጎናጸፊያህንም አክልለት…” የሚል ከመዓር ወሦከር የሚጥም ቃለ ሕይወት ከሚያሰማ የየዋሁ(meek) ክርስቶስ ደቀ መዝሙር አልጠብቅም፤ ክርስቶስ አፉን በምሣሌ ከፈተ እንጂ በአሽሙር አልነበረም፤ እንደሱ የዋሃን እንሁን ወይም ቢያንስ ወደእባብ የምንጠጋ አንሁን፡፡ ይህ ዓይነቱ ነገር ይቅር፡፡ በቀጥታ እንነጋገር፡፡ በሾርኒና በሥራየቤታዊ ምፀት ሰውን አናቁስል፡፡ የቆሰለ ሰውነት በቀላሉ ሊድን የሚችልባቸው ባህላዊና ዘመናዊ መንገዶች አሉ፤ የቆሰለ ኅሊና ግን በዐርባ አራቱ ጠበልም አይፈወስም፡፡ የምንለው ሁሉ እውነት ቢሆንም እንኳን ስሜት በማይጎዱ ቃላት እንግለጽ፡፡ ሰውን ጭራ በማስበቀል የሚደሰት ሰይጣን እንጂ በትክክለኛው የእግዚአብሔር መንፈስ የሚመራ ጤናማ ሰው ሊሆን አይችልም፡፡ ክርስቶስ አሁንም ድረስ ዓለምን እንደፍላጎታቸው እያሽከረከሯት የሚገኙት ሰይጣናውያን ወንድሞቹ እየገረፉት፣ በልግጫ የእሾህ አክሊል እየደፉበትና ምራቃቸውን እየተፉበት በነበረበት በዚያን የስቃይ ወቅት “የሚያደርጉትን አያውቁምና አባት ሆይ ይቅር በላቸው” ያለውን ታላቅ አስተምህሮ በዐውደ ምሕረት ብቻ ሣይሆን በዕለት ከዕለታዊ ሕይወታችንም በተግባር ማሳየት አለብን፡፡ ደግሞስ ለቦና ጥጃ ውስ ምን አነሰውና ነው ይህን ያህል የአሽሙር ዱላ በዚህ ከጨለማ ገና ትናንትና በወጣ ታዳጊ የቀድሞ ፖለቲከኛ ላይ መከመር ያስፈለገው? ምን ዓይነትስ የቦካ ቂም ቢኖር(ህ) ነው?
አንድ ነገር ይልቁናስ ትዝ አለኝ፡፡ ቀደም ባለ አንድ ወቅት ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ስለብፁዕ አባታችን ስለአባ ጳውሎስ ንዋያዊ ንጽሕና በሰጠው ምሥክርነት አንድ ሌላ ሰው ተችቶ ጽፎ ነበር – ዳኒ “ብፁዕ አባታችን ቤሣቤስቲን የሌላቸው እጃቸው ንጹሕ የሆነ (ብቸኛው) ፓትርያርክ ናቸው” ሣይል የቀረ አይመስለኝም፡፡ እኔም ያን ጽሑፍና የዲያቆኑንም የዋቢነት ቃል አመሳክሬ አንብቤ ሳበቃ የተሰማኝን ቅሬታ ልጽፍ ስል ተውኩት – በስንቱ ተንጨርጭሬ እዘልቀዋለሁ ከሚል መሰላቸት ይሆናል የተውኩት – ጊዜው ራቅ ስለሚል ለምን ሳልጽፍበት እንደተውኩት ትዝ አልልህ አለኝ፤ በርግጥም ልጻፍ ብሎ እንደኔ ሥራ ለሚፈታ ሰው በቀን ከመቶ መጣጥፍ በላይ የሚያስጥፍ ሀገራዊና ወያኔያዊ ጉዳይ ሞልቶናል፡፡ ያን አሣዛኝና አስተዛዛቢ ነገር በሰማሁ ጊዜ ታዲያ ሆድ ብሶኝ ነበር፡፡ የምወደውና የማከብረው ዳንኤል፣ በበሳል አስተማሪ ጽሑፎቹ የማውቀው ዳንኤል (በራሱ ድረ ገፅም ጭምር) ይህን ያህል ወርዶ የዐይጥ ምሥክር ድንቢጥ ሊሆን እንዴት ይቻለዋል ከሚል መዘውረ ሃሳብ የተነሣ ብዙ ዋተትኩ (አያችሁልኝ ዳኒን የምወቅስበት በሽታ እኔንም ሲነሳብኝ? ልክፍት እኮ ነው ጎበዝ! የትኛው ሐኪም ቤት ልሂድ ይሆን?)፡፡ ግን ሀገራችን የተዓምራት መገለጫ መሆኗን ከመረዳት አንጻር በዚያው ሰሞን የአንድ ወቅት መንጨርጨር አለፈልኝ፡፡ እንደፈላስፋው ዲዮጋን በገረረው ጠሐይ ትልቅ ሰው – እውነተኛ ሰው – ፍለጋ ኩራዝና ፋኖስ ይዘን በምንንከራተትበት ሶዶም ወገሞራዊ የዕልቂትና የጥፋት ዘመን ይህን መሰልና ከዚህም የከፋ የመንሸራተት ትያትር ቢገጥመን ብዙም መደነቅ እንደማይገባን በበኩሌ እረዳለሁ – እንዲያው እየመሰለን ግን እንናደዳለን፤ መናደድ መፍትሔ ያመጣ ይመስል፡፡ በዘመነ ድመት ዐይጥ የድመትን ድርሻ፣ ድመት ደግሞ የዐይጥን ድርሻ ወስደው ትራጂ-ኮሜዲ ተውኔት በሚተውኑባት ሀገራችን ውስጥ ደግሞ የማይታይ የታሪክ ብፌ የለም፡፡ አስመሳዩ፣ አታላዩ፣ ሊቁ፣ ከያኒው፣ ቄሱ፣ ጳጳሱ፣ ነጋዴው፣ ምሁሩ …. እጅግ በዝቷል፡፡ ግን ሁሉም ያው ቢከፍቱት ተልባ፡፡ በቃ – ካንጀቴን ነው የምልህ – ቢከፍቱት ተልባ ብቻ፡፡ በቋንቋ ጂዶ፣ በሣጥናኤላዊ ዕውቀት አብዶ፣ በተውህቦ ዝማሬ ቅላፄ፣ በአማላይ ስብከተ ወንጌል ውትወታ፣ በሃይማኖት አባቶች ዲያብሎሳዊ ቱማታ … ክፉኛ እየተመታ ያለ ሕዝብ የማይጠብቀው የሚጠብቀውን ቀድሞ ቢመጣና በቀቢፀ ተስፋ ቢቆዝረው፣ የማይሆነው የሚሆነውን ቀድሞ እየተከሰተ እንደግመል ሽንት የኋሊት ቢያስቀረው መጥኔ ለኢትዮጵያ፣ መጥኔ ለትውልዱ ከማለት ውጪ ለጊዜው ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ ምንም፡፡
ብሎም ቢሆን ሌሎቻችን በዚህ አጋጣሚ ትምህርት መቅሰም ይኖርብናል፡፡ በመካከላችን ሠርፆ የአንዲት ሀገር ልጆችን እያባላንና እያናከሰን የሚገኘውን የአጋንንት መንጋ ከሀገራችን አስወግዶ የፍቅርና የመተሳሰብ አምባ የሚሆን የሕዝብ መንግሥት እንዲሰጠን ፈጣሪን እንማጸን፡፡ ይቻለዋልና ያደርገዋል፡፡ እኛ ግን ቆም ብለን እናስብና ከሚቀርበን የኅሊና ሱቅ ገብተን ጤናማ ኅሊናና አስተዋይ ልቦና እንግዛ፡፡ ይሄ በሆነ ባልሆነው መናቆር እስኪ ይብቃን፡፡ ለሆድ ማደርንም እንጸየፍ፡፡ ሆድ ከዐፈር እንደመምጣቱ ጊዜውን ጠብቆ በስባሽ ነው – ወደመጣት ወደዐፈሩ ይመለሳል፡፡ ኅሊናና መንፈስ ግን ከነፍስ ጋር ኅብረት ስላላቸው ዘላለማዊ ናቸው – ውጤታቸውም ዘመናትን ተሻግሮ ለትውልደ ትውልዶች የሚጠቅም ታሪካዊ ቅርስ ነው – ከክፉ ሥራ አሁኑኑ እንራቅ፡፡ ከሆድ ሃይማኖት በቶሎ እንውጣ፡፡ የሆድ ሃይማኖት ሰውን ከዐውሬዎች በታችም ያውላል፤ ከሃይማኖቶች ሁሉ የክፉ ክፉ አምልኮተ ሆድ ነው፤ ሁለመናን ፍጹም ያሣውራል፡፡ እውነትን የምንጨቁናት፣ ይሉኝታን የምንደፈጥጣት፣ ዘረኝነትን የምናነግሣት፣ ማተባችንን የምንበጥሳት፣ እምነታችንን ቦርጫን ውስጥ የምንደፍቃት ሆዳችን እያስገደደን ነውና ከዚህ ዘመን አመጣሽ የሆድ አምልኮት በአፋጣኝ ራሳችንን ነፃ እናውጣ፡፡ በሥጋ ብንራብና ብንጠማ አላፊ ነው፤ በራብ ብንሞት እንኳን በኅሊናና በመንፈስ የምንመተውን ያህል ብርቱ ሞት አይገጥመንም፤ የሥጋው ሞት የውሸት ሲሆን የመንፈስ ሞት ግን የምር ሞት ነው፤ ይግባኝ የሌለው የሁለት ዓለማት ሞት – በምድር የዘር ሐረጋችን የሚያፍርበት ሞት -በሰማይ ነፍሳችን ከፈጣሪዋ ተለይታ ዘላለማዊ ደይን የምትወርሰበት ሞት – ምዕመናን ከዚህ ይሠውረን፡፡ ኅሊናችንን የሥጋችን ባርያ አድርገን በሀመርም በሉት በሮልስሮይስ ብንንፈላሰስና ከርሳችንን በጮማና በዊስኪ ብንቀበትተው፣ በተንጣለለ ቪላና ፎቅ ብንኖርና ባማረ አልጋ ላይም ከፈልግነው ሰው ጋር አንሶላና ጋቢ ብንጋፈፍ ከኅሊና ወቀሣ መቼም ቢሆን ልናመልጥ አንችልም፡፡ በዕድሜም ይሁን በሌላ ጣጣ ይህን የምንንፈላሰስበትን ከምሥኪን ዜጎች ደምና አጥንት የተመዘበረ ሀብትና በጉልበት የተያዘ ሥልጣን የምናጣበት ወቅት መኖሩን ደግሞ በጭራሽ መዘንጋት የለብንም፡፡ ሁሉም ወደየመጣበት የሚሄድ መሆኑን ደግሞ ሁለቱም የሃሳባውያንና የቁሣካላውያን ጠበብተ-ነቢብ ሳይመሰክሩት የሚቀሩ አይመስለኝም፡፡ ያኔ ሁሉም ሲከዳን ኅሊናችን ግን ከኛው ጋር ሆኖ “ነግሬህ አልነበረምን? አሁንማ የፈሰሰ አይታፈስ! ቻለው እንጂ ምን ታደርገዋለህ! በጣም ረፍዶብሃል!” እያለ ያፌዝብናል፡፡ ሀገር ትድናለች፤ ዐረሞች ይጠፋሉ፤ ትክክለኛው ሰብል ተዘርቶ ሊበቅል፣ በቅሎም ሊጎመራ፣ ጎምርቶም ወደጎተራ ሊገባ ዘመኑ ደርሷል፤ የእንክርዳድና የወበሎ ክምር ሊቃጠል ጊዜው ቀርቧል፡፡ ትክክለኛው ሰንደቅ ዓላማ ሊውለበለብ ሀገርም በአዲስ መልክ ልትወለድ እመት ተፈጥሮ ምጥ ላይ ናት፤ እመብርሃን ከጎኗ ትሁን፡፡ ሩፋኤል በክንፉ ይጠብቃት፡፡ ከየት መጣ የማይባል መብረቅ አራት ኪሎንና አምስት ኪሎን ያጸዳል፡፡ የላየ ላይ በል በል ያለኝን አልኩ፤ እንዳልዋሸሁ በል የሚለኝ ያውቃል፡፡… የሰማነውን በልቦናችን ያሳድርልን እስኪ፡፡
ለማንኛውም አስተያየት yiheyisaemro@gmail.com
The post በኤርምያስ ለገሠና በዲ/ን ዳንኤል ክብረት በኩል እኛን ማዋራት አሰኘኝ appeared first on Zehabesha Amharic.