Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ከመግለጫው በስተጀርባ

$
0
0

(ጌታቸው ሺፈራው)

የትህዴን ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ሞላ አስግዶም ከኤርትራ መውጣታቸውን ተከትሎ በህወሓት/ኢህአዴግ እና በተቃዋሚዎች በኩል ያልተጠበቁ ስሜቶች ተስተናግደዋል፡፡ ከተቃዋሚዎች በላይ ግን ራሱ ስርዓቱና ደጋፊዎች በክስተቱ ስሜታዊ ሆነው፡፡ ለዚህም በስርዓቱ ደጋፊ ሚዲያዎችና በደህንነት ተቋሙ እየተላለፉ ያሉትን መረጃዎች ማየት በቂ ነው፡፡ ያልጠበቁትን የሆነላቸው የሚመስሉት የስርዓቱ ደጋፊዎች በርካቶች በእሱ ስም በአሸባሪነት ተከሰሰው አሁንም ድረስ ፋዳቸውን የሚያዩበትን ድርጅት መሪ ‹‹ሀገር ወዳድ፣ ጀግና….›› እያሉ አሞግሰውታል፡፡ ይህ ያልተጠበቀ ‹‹ድል›› እንዳያመልጠው የፈለገው ህወሓት/ኢህአዴግም ሰውዬው ከኤርትራ የወጡት ለአንድ አመት በተደረገ ሚስጥራዊ ግንኙነት ነው ብሎ ‹‹ድሉን›› የራሱ አድርጎታል፡፡ የሻዕቢያ ተላላኪ ሲላቸው የነበሩትን ሰው በአንዴው የራሱ ተላላኪ አድርጓቸዋል፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች አሸባሪ ተደርጎ ሲቆጠር ‹‹ወደ ሀገር የገባው ትህዴን›› አሁን ሀገር ወዳድ ተደርጎም የጀግንነት አቀባበል እየተደረገለት ነው፡፡

Mola asgedom

ከደጋፊዎቹና ከሚዲያዎቹም በላይ ስርዓቱ በተቋማቱ ደረጃም ስሜታዊና ሁኔታው ድንገተኛና ያልተጠበቀ እንደነበር የሚያሳይ መግለጫ አውጥቷል፡፡ ‹‹የብሄራዊ የመረጃና የደህንነት አገልግልግሎትና ከፌደራል ፖሊስ የጋራ ፀረ ሽብር ግብረ ሃይል›› ተሰጠ የተባለው መግለጫም የሚያሳየው ይህንኑ ነው፡፡ እንደ ተቋም በተለይም እንደ መረጃ ተቋም ተከሰቱ ያላቸውን ጉዳዮች በመረጃ መግለፅ ሲገባው ከአንድ መንግስት ብቻ ሳይሆን ስርዓትን በፕሮፖጋንዳ ለማጥቃት ከሚፈልግ ጀማሪ ተቃዋሚ እንኳን ያልተሻለ የተጋነነ ፕሮፖጋንዳን በመግለጫነት አውጥቷል፡፡ ‹‹ሀገር ወዳድ፣ እጅግ አኩሪ በሆነ መንገድ፣ እናት ሃገራቸው፣ ብርሃኑ ነጋ ሳይወድ ተገዶ ወደ አስመራ እንዲገባ፣ በተላላኪዎቹ ብዙ ዳንኪራ ከተደለቀበት በኋላ፣ ወሽመጣቸው እንዲቆረጥ፣ በአንድ የሻዕቢያ ቅጥረኛ ከሃዲ አማካይነት፣ የኤርትራ መንግስት ሰራዊት ሙሉ በሙሉ በመደምሰስ፣ ……..›› የመሳሰሉት መግለጫው ውስጥ የተካተቱ ስሜታዊ አገላለፆች ከአንድ መረጃ ተቋም ብቻ ሳይሆን ከመንግስትን ጋር የፕሮፖጋንዳ ጦርነት ውስጥ የገባ ተቃዋሚ ድርጅት ቢያወጣቸው እንኳን የሚያስተዛዝቡ ናቸው፡፡
ከዚህ ባሻገር አብዛኛው የመግለጫው ‹‹የሀገሪቱን ሰላም የማይፈልግ፣ ተላላኪ፣ አሸባሪ፣ ፀረ ሰላም….›› ይለው የነበረውን ቡድንና ግለሰብ የሚያሞካሽ ነው፡፡ መግለጫው ‹‹ታጣቂ ሀይሉ የሻዕብያ ቅጥረኛና የኢትዮጵያ ፀረ ሰላም ሃይል የሆነው አሸባሪው ግንቦት 7 ኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረውን የጥፋት ሴራ ባለመቀበል ነው ወደ እናት ሀገሩ የተመለሰው።›› ሲል አሞካሽቶታል፡፡ (በዚህ ‹‹እናት ሀገር›› የሚልን አገላለፅ እንደ ትምክት በሚያይ ስርዓት ውስጥ ምን አልባትም ከደርግ ውድቀት በኋላ በመግለጫ ደረጃ ስለ ‹‹እናት ሀገር›› እየተወራላቸው ያሉት አቶ ሞላ አስግዶም ብቻ ይመስሉኛል፡፡)

‹‹ድሉን›› ወደ መንግስት ጥረት ለመለወጥ የጣረው ስሜታዊ መግለጫ ‹‹ሀይሉ በጉዞ ወቅት ከሻዕብያ የተሰነዘረበትን ጥቃት ተቋቁሞ በአንፃሩ የሻዕብያን ሰራዊት እየደመሰሰ ወደ እናት ሀገሩ ሊመለስ ችሏል።›› ሲልም ‹‹ጀብዱን›› አውርቶለታል፡፡ ‹‹ብዙ መስዋዕትነት በመክፈል ነው ከነሙሉ ትጥቁ እና ሎጀስቲክ መሳሪያው አገሩ የገባው።›› ሲልም አወድሶታል፡፡ የደህንነት መስሪያ ቤቱ መግለጫውን ምሽት ላይ ያስተላለፈው ቢሆንም ፋና ግን ከመግለጫው ጋር ተመሳሳይነት ያለው ዜና ትናንት መስከረም 2/2008 ዓ.ም አስተላልፏል፡፡ ይህም መግለጫውን ከአንድ ደህነንት ተቋም ነኝ ከሚል ይልቅ ከስርዓቱ የፕሮፖጋንዳ ቅርንጫፍ የወጣ ስለመሆኑ የሚጠቁም ነው፡፡

የደህንነት መስሪያ ቤቱ በመግለጫው መግቢያ ‹‹በኤርትራ መንግስት አማካኝነት ለበርካታ ዓመታት ሲደራጅ የነበረው›› ብሎ ታጣቂ ቡድኑ ግዙፍ አቅም እንደነበረው ቢገልፅም ወረድ ብሎ ‹‹በአሁኑ ወቅት ኤርትራ ውስጥ የቀሩት እና መውጣት ያልቻሉ የቡድኑ አባላት በሽተኞች፣ በየቦታው የነበሩ እስረኞች፣ የኪነት ቡድን አባላትና ሌሎች አቅመ ደካሞች ብቻ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡›› ሲል ይህ ለበርካታ አመታት የተደራጀ ቡድን አባላት 700 ብቻ ናቸው ብሎ ፕሮፖጋንዳ አይሉት ፌዝ በመግለጫነት አስተላልፎልናል፡፡

ለትህዴን ለምን?

በዚህ ደረጃ ባይሆንም በተለያዩ ጊዜያት አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ ቡድኖች አመራሮች ከስርዓቱ ጋር ታርቀው ወደ ሀገር ቤት ገብተዋል፡፡ ለዚህ ‹‹ውለታቸውም›› ቢያንስ እየተሸማቀቁም ቢሆን የቅንጦት ኑሮ መግፋት ችለዋል፡፡ እነዚህ ቡድኖች በተለይም የኦነግና የኦብነግ አመራሮች በገቡበት ወቅት ‹‹የአሸባሪ ቡድን፣ የአጥፊ ቡድን….›› አባላት እየተባሉ ከመወቀስ አልዳኑም፡፡ በቴሊቪዥን ዶክመንተሪዎችም ስርዓቱ ደግሞ ደጋግሞ ከሚወቅሳቸው በላይ ራሳቸው ቀርበው ራሳቸውን እንዲወቅሱ እየተገደዱ ነው፡፡ አቶ ሞላ አስግዶም ግን ገና ከጅምሩ፣ ገና ወደ ሀገር ቤት ሳይገቡም ጀምሮ ከዚህ የተለየ እየተደረገላቸው ነው፡፡ ምን አልባት ሞላ አስግዶም ያደረጉትን ጀኔራል ከማል ገልቹ ቢያደርጉት ከእንደዚህ አይነት ሙገሳ ይልቅ ከአሁን ቀደም ይደረግ እንደነበረው ፍረጃ ሊያመልጡ ይችላሉ ብሎ መገመት የዋህነት ይሆናል፡፡ ይህም በመሰረታዊነት ህወሓት/ኢህአዴግ ከሚከተለው ጎሰኛ ፖሊሲው እንደተቀዳ መገንዘብ አያዳግትም፡፡

በዚህ ፕሮፖጋንዳ የትግራይ ህዝብ ከህወሓት ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለው፣ የትግራይን ህዝብ ወክለናል የሚሉት ተቃዋሚዎች የስርዓቱ መጠቀሚያና ከስርዓቱ ጋር ተባብረው ሌሎች ቡድኖችን ከማጥቃት ውጭ ለተቃዋሚው ጎራ እንደማይታመኑ ማሳየት ይፈልጋል፡፡ ለዚህም መግለጫው ‹‹በዚህ አጋጣሚ ይህ ኦፐሬሽን በድል እንዲጠናቀቅ ከጅምሩ የትግራይ ክልላዊ መንግስት ከፍተኛ ተሳትፎ ነበረው›› ማለቱን በዋቢነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህ አመለካከት በህዝብ ውስጥ አለ ተብሎ ስለሚገመት አጋጣሚውን በመጠቀም ህወሓትና የትግራይን ተቃዋሚዎችን የማይጨካከኑ እንደሆኑ ለማሳየት ተፈልጓል፡፡ እውነትም በሌሎቹ ታጣቂ ቡድኖች ላይ እንደሚጨከነው እነ አቶ ሞላ ላይ አልተጨከነባቸውም፡፡

ከአዋጭነት አንፃር

ክስተቱ ለስርዓቱ ድንገተኛ እና ያልተጠበቀ እንደሆነ በዋነኝነት የሚያሳየው የደህንነቱ ተቋምን ጨምሮ ሚዲያዎቹ የግንቦት ሰባት አመራሮችን ወደ ኤርትራ መምጣትን የስርዓቱ ትልቅ ስኬት እንዲሁም የግንቦት ሰባት ትልቅ ውድቀት አስመስለው ማቅረባቸው ነው፡፡ እንደ መግለጫው ለግንቦት ሰባት ትልቅ ስኬት የነበረው፣ እንዲሁም ስርዓቱ ይጎዳ የነበረው አመራሮቹ አሜሪካን ሆነው ድርጅቱንና ቅንጅቱን/ትብብሩን በርቀት ቢመሩ ነው፡፡ በተቃራኒው ግን አመራሮቹ አሜሪካን ውስጥ ሆነው ድርጅቱን መምራታቸው ትልቅ ጫና እንደነበረባቸው የሚታወስ ነው፡፡ ወደ ኤርትራ በሄዱበት ማግስት በርካቶች ለትጥቅ ትግሉ ቆርጠው መግባታቸውን የሚያሳይ ነው ሲሉም ተደምጠዋል፡፡ የ‹‹ኦፕሬሽኑን›› ድራማ እውነት ለማስመሰል በችኮላ የወጣው መግለጫ ግን ለግንቦት ሰባት ስኬት ነው የተባለውንም የስርዓቱ ስኬት አድርጎ ገልብጠው አነብንቦታል፡፡ በችኮላ! ምን አልባትም ያልተጠበቀው ‹‹ድል›› በፈጠረላቸው ደስታ፡፡

መግለጫ ለበርካታ አመታት ሲደራጅ ነበር ያለውን ቡድን አባላት ስርዓቱ በቁጥር ከእሱ ያንሳሉ ለሚላቸው ሰላይ አድርጓቸዋል፡፡ አቶ ሞላ አስግዶምን ጨምሮ 700 የሰራዊቱ አባላት የስርዓቱ ሰላዮች ነበሩ ማለት ነው፡፡ በመግለጫው በዋነኝነት አቶ ሞላን ጨምሮ ይህ ሁሉ ሰራዊት አሳካው የተባለው ቅንጅቱ/ትብብሩ እንዳይሳካ ማድረጉን ነው፡፡ የመግለጫው ዋና አንጓ ግንቦት ሰባትን ከሌሎች ታጣቂዎች መነጠል ይመስላል፡፡ ለአንድ አመት ተደረገ ያለው ሚስጥራዊ ስራ ተሳካ ሲልም ትብብሩ እንዳይደረግ መሰናክል ሆኗል በሚል ነው፡፡

በእርግጠኝነት የአቶ ሞላ አስግዶም ‹‹ተልዕኮ›› በስርዓቱ የተመራ ቢሆን ኖሮ ከትብብሩ ከማፈንገጥ ይልቅ ትብብሩ ውስጥ ቆይቶ እንዲሽመደመድ ማድረግን ቅድሚያ በተሰጠው ነበር፡፡ ምክንያቱም አቶ ሞላ አስግዶም ወደ ኢትዮጵያ ከመግባት ይልቅ ምክትል ሆነው ለስርዓቱ ጠቃሚ ስራን መስራት ይችሉ ስለነበር ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር የመግለጫውን (ፕሮፖጋንዳውን) ትልቅ ትኩረት የሳቡት ፕ/ር ብርሃኑና ድርጅታቸው ግንቦት ሰባት ናቸው፡፡ ፕ/ር ብርሃኑን ጨምሮ 90 በመቶ የሚሆነው የግንቦት ሰባት አመራር ኤርትራ እንደሚገኝ ተገልጾአል፡፡ ከአመራሩ መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ኤፍሬም አዴቦ ከሳምንታት በፊት ባስነበቡት ፅሁፍ አሁን ስርዓቱ የራሱ ተላላኪ አድርጎ ያቀረባቸው አቶ ሞላ አስግዶምን ጨምሮ አብዛኛውን የትህዴን ታጋይ ጋር መገናኘት ችለዋል፡፡

በመሆኑም ይህን ‹‹ኦፕሬሽን›› ስርዓቱ የመራው ቢሆን ኖሮ ‹‹አሻፈረኝ›› ብሎ ወደ ኢትዮጵያ ከመመለስ የግንቦት ሰባት አመራሮች ላይ ጉዳት ማድረስ እጅግ ትልቅ ጥቅም ይሰጠው እንደነበር መገንዘብ ቀላል ነው፡፡ በእርግጠኝነት በመግለጫው ‹‹አሸባሪው›› የተባሉት ብርሃኑ ነጋ፣ ውይክሊክስ ስርዓቱ ‹‹የጀኔራል ዘለቀን ልጅ መረጃ ማግኘት እንፈልጋለን›› እያለ እያደናቸው ነው የሚባልላቸው አቶ ንዓምን ዘለቀና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ላይ አደጋ ማድረስ ወደ ሀገር ከሚገባው 700 ይሁን 7000 የትህዲት ሰራዊት በላይ ስርዓቱ የሚቋምጥበት ነበር፡፡
የትህዴን ካምፕ ድረስ እየሄዱ ከሰራዊቱ ጋር የሚገናኙትን፣ ይህ እንኳ ባይሆን ከእነ ሞላ ጋር ተሰብስበው ሲመክሩ የነበሩትን የግንቦት ሰባት ከፍተኛ አመራሮች ላይ አደጋ መጣሉ አዋጭና ምን አልባትም የእነ ሞላ አስግዶም ጠባቂዎች የሚፈፅሙት ቀላል ተልዕኮ ነበር፡፡ ምን አልባትም ራሳቸው አቶ ሞላ አስግዶም ጭምር፡፡
ይህ ሁሉ ድንገተኝነት የሚያመለክተው አቶ ሞላ አስግዶም በትብብሩም ይሁን በሌላ ጉዳይ በነበራቸው ቅሬታ ከኤርትራ ለመውጣት ያደረጉትን ሂደት ስርዓቱ የራሱ በማድረግ እንደተጠቀመበትና እሳቸውንም ‹‹ሳይሸነፉ›› ወደ ሀገር እንዲመለሱ በችኮላ መወሰኑን ነው፡፡ አሁን እየተደረገ ያለው የችኮላ ፕሮፖጋንዳ ማንን እንደሚጠቅም እየቆየ የሚታይ ይሆናል፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>