14.09.2015 /ሲወዘርላንድ – ዙሪክ/
እንዴት ናችሁ ወገኖቼ ደህና ናችሁ ወይ?
ዛሬ ያለንበት ወቅት የወሳኝ ዓይን ነው። ጥንካሬ የሚያንገዋልላቸው እጅግ ውስብስብ ብንታወች – ይኖራሉ። ብሄራዊ የነፃነት ትግል ለዛውም የእርስ – በእርስ ሲሆን ረቂቅና ማስተዋልን የሚጠይቁ አመክንዮች – ይኖራሉ። በፖለቲካ ህይወት ውስጥ አንጃ የተለመደ በመሆኑ የጥንካሬም የድክመት መለኪያ ሊሆን – አይችልም። ሂደቶች በራሳቸው ሊፈጥሩት – ይችላሉ።
ይህ እርምጃ ከግል ስሜት፦ ከጥላቻ፦ ከግል ኢጎ፦ ከኮፒ ራይት፦ ከበታችነት ስሜት፦ ተወጥቶ የፍላጎታችን ማዕከላዊ መዋቅር ማዬት ከተፈለገ በርግጥም የራዕያችን ጥርጊያ መንገድ ፍንትው ብሎ – ይታያል። አቅም ከፍላጎት ጋር ብቻ ሳይሆን ከዘመን ፈቃድ ጋር – ተጋብቷል። ለዚህም ነው የእንቅልፍ ክኒን ወስደው የነበሩ ብዕሮች ሁሉ አቧራቸውን አራግፈው የቂም ቋጠሮ ዳንቴሎችን ሲተረትሩ – የሚታዩት። የጠበቅነው ይዘረገፋል የተባለው ገመና የባለቤቱን ሆድእቃ ያለ ይግባኝ በቂም በቀል ተለውሶ የበለጠ እንድንመረምረው አጋጣሚ – ሸለመን። ሌት ተቀን የሚባዘንበት ምክንያት በህልም ውስጥ ለመኖር አለመቻል የፈጠረው ድቀት ይመስለኛል።
ሰማይና መሬት የተደባልቅ ያህል ጉሮ ወሸባዬ የሚባልለት አቶ ሞላ አስገዶም የአቋም ለውጥ ወሽኔ እርምጃ ሲል ጋዜጠኛ ደምስ በለጠ ኢትዮ ሚዲያ ላይ አስነብቦናል። የመልካም ምኞት መግለጫም – ተፈርሞበታል። ትግል ማለት ይሄ ነው። በሃስብ ልዩነት እየተባለ ጊዜ ማጥፋት የለብንም ያልኩትም ለዚህ ነበር። የነፃነት ትግል በተራመደ ቁጥር እንዲህ መንገድ – ይጠርጋል። ጫጫታው፦ ሁካታው ይሄው ነበር።
አቶ ሞላ አስገዶም በሚመለከት ከፈረንሳይ ጋዜጠኞች ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ ብቻ አዳምጫለሁ። ከዛ ውጪ አንድም ቀን ብዕሬም ብራናዬም ምንም ብለን አናውቅም። አሁንም ምንም አልልም። ለምን? አጀንዳዬ ስላልሆኑ። ሌላው ከእኛ በተጻራሪ ወገን ያሉት የአሸናፊነት ስሜት ያገኙ – መስሏቸዋል። አቶ ሞላ አስገዶም ምንም ሳይጽፉ በራሳቸው ሽጉጥ አለምን ቢሰናበቱ ኖሮ ዲል ያለ ድግስ ደግሰው – አታሞዋን ቢደልቁ ይችሉ ነበር። አሁን ግን ድርብ ኪሳራ ነው። የእኛ ሥነ – ልቦና ግን ገዢ መሬት ነው ያለው ማስተዋልን – ከፈቀድንለት።
እኔ በግሌ የመንፈስ እንቅፋት በፈቃዱ ሳይገፋ፣ እራሱን መፈንገሉ – ይታመሱ የነበሩት ግልብ ስሜቶችን ጠራርጎ አሮጌው ዓመት አቃጥሏቸዋል። ስለዚህም ደስተኛ ነኝ። ጥበብ – አይቼበታለሁ። ነገም፣ ከነገ ወዲያም፣ ከዚያ ወዲያም ማፈንገጥ – መክዳት አንጃ ሊኖር ይችላል። ብቁ አመራር መሬት ላይ ስለአለ። አብዛኛው ህዝብ ደግሞ መንፈሱን – ይጠብቃል።
ጽናት ሁልጊዜም ስንቅና ትጥቅ ሊሆን ይገባል። የነፃነት ትግል መራራ ጉዞ አረሙን ያንጠባጥባል። ፈተናን እዬጣሰ የሚሄደው ጽናት የድል ዋዜማን ያቀርባል። ሌላው ነፃነት የራበው ወገን የጠላት ጎራ ሚዲያ ሰለባ መሆን የለበትም። የጠላት መረጃ ያዳመጥኩት በሙሉ ዬዘበጠስ – ወጥ ያልሆነ – ችኩል ነበር። ስለሆነም ቀልብ ሊሰጠው አይገባም። ያልተጠበቀው ብቁ አመራር መሬት ላይ ሲገኝ እስተ ጎመራው – ፈነዳ። ቀለጦው ጠራረገው – ቀጣውም። እኛ መጠበቅ ያለብን የእኔ ከምንላቸው ሚዲያወች መሆን ይገባል። የነፃነት አርበኛው ሆነ ደጀኑ ቃናውን መጠበቅ – ይገባዋል። በዚህ ዝብርቅ – ሙርቅርቅ የሰመጠ መርከብ ትጥቅን መፍታት – አይገባም።
በጣም የገረመኝ ነገር ጥምረቱን የሚያቅልል ዕይታወች – አዳምጫለሁ። የሚፈራ ጉልበታም አቅም መኖሩ እንዲህ – ያፍረከርካል። አንድነት እንዲህ የእንፋቅቅ ያስኬዳል። ይህ የድል መንገድ ባይሆን በደቡብ ዞን ያሉት አንድ ለመሆን ምን አንደፈደፋቸው? ይህ በሀገረም በውጪ ሀገር የሚታይ አመክንዮ ነው። ሌላው ግን ከኢትዮጵያ መልስ ሰተት ብሎ የገባ አዲስ አጀንዳ አለ – የወያኔ የክብር እንግዶች። ይህን በተቃጠለ ካርቦን ፁሑፌ ገልጭው ነበር። ኮተት እያሉ ከወዳደቁበት እዬተነሱ ያሉት ጥምረቱ የትግራይን ልጆች ማግለል ይገባል ይላሉ። ኢትዮጵያን ከነችግሮቿ የመሸከም አቅም ብልህነት ነው። መውደቅን የፈቀዱ እንዲህ እንደ አቶ ሞላ ሲኖሩ ደግሞ መቃብራቸውን – ይቆፍሩ። ታጥቦ – ጭቃ።
ዛሬ ትግሉ ዬሁሉም ነው። ባለቤትነቱም የሁሉም ነው። ጥበቃውም የሁሉም ነው። እግዚአብሄርንም እንመን። የእምነት ጽናትም ይኑረን። ፈተናችን ብዙ ነው። ትእግስትና ጽናትን – ይጠይቃል። ጽላታችን ኢትዮጵያን እናድርግ። መንገዱ አቀበት፣ ዳጥ፣ ጨቀጨቅ ነው። ሆድ – አይባሳን። እሩቅ እንሰብ። ብርሃንን – እንናፍቅ። ዘመኑ እራሱ ፈተና ውስጥ ነው። ባለቤት ግን አለው። ሁሉም ለመልካም ነው። በጎ ነገሮችን ለማጣጣም መራራ ሂደቶችን መፍቀድን ይጠይቃል። እንጽና። እውነት ከእኛ ዘንድ ነው። አምላካችንም አድምጦናል። „በመከራ ጽና“ ይላል የእግዚአብሄር ቃል።
ኢትዮጵያዊነት ያሸንፋል።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።