Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Opinion & Analysis
Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

ጨክነው እንዳስጨከኑብን እንጨክን!

$
0
0

በአበራ ሽፈራው /ጀርመን/

 

security 2

ዛሬ ማምሻውን ወያኔ እንደለመደው ያው “ሰልፉ ሌላ አላማ ነበረው!!” ብሎ ይወነጅላል በሽመልስ ከማል አንደበት:: ፖሊስ አሁንም ህዝቡን በማስፈራራት ላይ ነው ::ወሎ ሰፈር በሚገኘው ሳኡድኣረቢያ ኤምባሲ የተቃውሞ ድምጾች ለማሰማት የወጡ ዜጎች በፖሊስ ተደብድበዋል:: በርካቶች ታስረዋል:: ሰልፉም በፖሊስ ቆመጥ እና አላስፈላጊ እርምጃ ተበትኗል::

የሰው ልጅ ከተወለደበት አገር እንኳን ለመሰደድ ለአንድ ቀንም ለመሄድ አይፈልግም፡፡ በተለይም የተፈጥሮ ህግጋት ፣የኑሮ ቦታ ለውጥ ፣ለንግድ፣ለጉብኝት፣ እራሱን ለማዝናናት፣ለትምህርት፣ ቤተሠቡንና ጓደኛን ለመጠየቅ ወይም በአስገዳጅ ሁኒታ ካልሆነ በስተቀር ከሀገሩ ተለይቶ ለመኖር እንደማይፈልግ የአብዛኛው የሰው ልጅ ባህሪ መሆኑ ይታወቃል፡፡ አለመታደል ሆነና በሀገራችንና በህዝቧ ላይ በተለይም በዚህ ትውልድ ላይ ትልቅ የመከራ ተራራ ወድቆበታል፡ ፡ዛሬ በህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት የፖለቲካና የማህበራዊ ኑሮ ምስቅልቅልነት የተነሳ በሀገራችን በህዝብ ላይ ከሚደርሰው መከራ አልፎ በስደት ምክንያት ያለው መከራ ፣በየበረሐው የሚደርሰው ሞት፣ የአካል መጉደልና እንግልት በየሀገራቱ እስር ቤቶች የሚደርሰው ሰቆቃ እንዲህ ቀላል አይደለም፡፡

 

ዛሬ ብዙዎቻችን ኢትዮጵያውያን በአረቡ አለም በተለይም በሳውዲ አረብያ እየደረሰብን ያለውን መከራ ስናይ የአገራችንና የህዝባችን ጉዳይ እጅግ ወደመረረና ወደለየለት ሁኔታ መድረሱን ፤ ከህዝባችን ለቅሶና ዋይታ እንዲሁም የመንግስታችንን ዝምታና ግዴለሽነት ስንመለከት ምን ያህል ኑሮአችንና ህይወታችን ጭምር ለአደጋ መጋለጡን እናያለን ።

 

ዓለም በደረሰችበት የዕድገት ደረጃ አንጻር ሲለካ ዛሬ በኢትዮጵያዊያን ላይ የተፈጠረው ውርደት፣ስደት፣ የእህቶቻችን መደፈር፣ እስራት፣ አንገታችን በስለት መቀላት ፣ ንብረትና ሃብት መነጥቀ ፣ እንደ እንስሣ መታየታችን ያሳዝናልም፣ ያስቆጫልም ፤ በውጭ ሃገራትም እንዲሁ በአገር ቤትም እንዲሁ እስከመቼ ይቀጥላል? እኛስ እስከመቼ ድረስ ውጊያችን በሰላማዊ ሰልፍ ብቻ ይሆናል? እስከመቼ የሃይል ሚዛንን መፈጠርን ሳንችል፣ አስገዳጅ ሁኔታን መፍጠር እያቃተን እንጠቃለን ? በሃገር ቤት ጥቃት! በውጭ አገር ጥቃት!

 

እንደኔ ግን ይህ ትውልድ የለውጥ ራዕይ ይዞ እነዚህን የህዝብና የሀገርን ጠላቶች ከህዝቡና ከሀገሪቱ ላይ ለማንሳት በፍጥነት ወደ ትግል መግባት ካልቻለና የራሱንና የአገሪቷን አቅጣጫ ለመቀየር ካልተነሳ ከዚህ በባሰ ሁኔታ ኢትዮጵያዊነት ውርደት እየሆነ እየቀጠለ መሆኑን አሁን ያለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ያሳየናል ። አሁን ያለንበት እውነታ የአገራችንና የህዝቦቻችን ሁኔታና የኑሮ ሰቆቃ ከማሳየቱም በላይ ዛሬ ጨክነው ያስጨከኑብን ላይ ልንጨክን መነሳት ያለብን ጊዜ አሁን መሆኑን  ከሁኔታው መረዳት ይኖርብናል።

 

የእኛዎቹ ዘረኞች ህወሃቶች ለ22 ዓመታት በለየለጥ ስቃይ መርተውናል።  አገሪቷን በብቃት ለመምራት የሚችሉ ሳይሆኑ የራሳቸውን ስውርና ቡድናዊ ጥቅም በሚያስጠብቁ ጥቂት ዘረኞች ጭካኔ ተሰደናል፣ ተንገላተናል፣ ተዋረደናል። የሆነው ሆኖ ግን የተሰደደው ህዝብ በሚልከው ገንዘብና ገቢ የራሳቸውን ሃብትና ምንዛሬ እየአጋበሱ የሚኖሩት ግን እነዚሁ አሳዳጆቻችን መሆናቸውና እነሱ ምናቸውም እንዳልተነካ ስመለከት በጣም አዝናለሁ ። ዛሬ ወያኔዎችና ግብረ አበሮቻቸው በኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያ ላይ የወሰዱትን ጥቃት ለመቀልበስ አሁን በፍጹም ጭካኔ ልንነሳ ይገባናል ።

 

ዛሬ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሳውዲ አረቢያ በኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ያለውን የማይሰማ እንደሌለ ግልጽ ነው፤ በጣም ያስቆጫል ፣ያቃጥላል፣ ያናድዳል። ይኽንን ነገር ለመቀየር በፍጹም ቁጭት መነሳት ያለብን ጊዜ ደግሞ አሁን ነውና ወጣቱ፣ የተማረውም ሆነ በልዩ ልዩ ሁኔታ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያለን በሙሉ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ልንነጋገር መቻል ይኖርብናል ፤መፍትሄም ማስቀመጥ ያለብን ጊዜ አሁን ነው። ዛሬ በሰልፍ ብቻ የምናስቆመው ችግር አይደለም ለዘለቄታውም ልንሰራ ያለብን ጊዜ አሁን ነው።

 

ዛሬ በአረቡ አለም እየደረሰብን ያለው ግፍ መነሻዎቹ በአገራችን ያለው የፖለቲካና የማህበራዊ ችግሮችና በኢትዮጵያዊነት ስም የህወሓቶች ጥርቅሞች በመላው ዓለም  የኢትዮጵያ ኢንባሲዎችና ቆንስላዎች በተለይም በአረቡ ዓለም ባሉ ኢንባሲዎችና ቆንስላዎች ውስጥ በህወሓት ዘረኝነት በተበከሉና በንግድ በተሰማሩ የህወሃት ባለማሎች ስብስብ የተያዙ መሆኑ ደግሞ በእንደዚህ አስቸጋሪ ወቅቶች እንኳን ለወገኖቻችን መድረስ ሳይችሉ ቀርተው የህዝቡን ጥቃት በዝምታ ማየታቸውና ኢትዮጵያዊነት በመላው ዓረብና በመላው የዓለም ሚዲያዎች እጅግ በሚያስቆጭ መልኩ  በውርደትና ወገንና ደራሽ እንደሌለው መታየቱ ደግሞ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን ብዙ የኢትዮጵያን ወገኖችና ደጋፊዎች አሳዝኗል፣ አስደንግጧል።

 

ዛሬ ኢትዮጵያን የሚመሩ ዘረኞች አስቀድሞም ቢሆን ኢትዮጵያዊነትን የካዱና አሁንም ለኢትዮጵያዊነት ዴንታ የሌላቸው በመሆኑ ይህ  ችግር ተፈጠረ አልተፈጠረ ምናቸውም አይደለምና፤ ዛሬ ከምናየው የአገራችንና የህዝባችን ውርደት በላይ ገና ብዙ መከራዎች ከፊታችን ተደቅነዋል፤ አሁን በምንችለው አቅም ከምናደረገው ትግል በላይና ለህዝቦቻችን ከምንታገለው በላይ ሁላችንም ቆም ብለን የምናስብበትና  በአረቦች ባስጨከኑብን ጨካኞች ህወሃቶች ላይ መጨከን እንዳለብን ይታየኛል።

 

 

የዛሬዎቹ ችግሮች መስፋፋት ምክንያቶቹ በሀገር ውስጥ የሚደርሰው ግርፋት ፣እንግልት፣ እስራት፣ ሞትና ሌሎች የሰብአዊ መብት ረገጣዎች እንዲሁም በመንግስት በተደራጁ ሀይሎች በሀገርና በህዝብ ላይ የሚደርሰው የሙስና ተግባር  ፣የዘር ጥቃት፣ ህዝብን ማፈናቀል፣ ሀብትና ንብረት መዝረፍ፣ የመሬት ቅሚያ፣ ሚዛናዊነት የሌለው የንግድ መድሎ  መሆናቸውን የማያውቀው ኢትዮጵያዊ የለም፡፡

 

አሜሪካና ሌሎች ምዕራባውያን ሀገሮች በአገራችን ውስጥ ያሉትን  ችግሮች እያወቁ እንዳላወቁ እየሆኑ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለታቸውና ለነዚህ ለተደራጁ ሀገርንና ህዝብን ለሚያሸብሩ ዘረኞች በገንዘብና በቁሳቁስ በማጠናከርና በመርዳት የዚህን ትውልድ መከራ መጨመራቸው የሚያሳዝን ቢሆንም ትግላችን ከራሳችን የሀገርንና የህዝብን ስብዓዊና ቁሳዊ መብቶችን እየነጠቁ ከሚኖሩ የኢትዮጵያ መሪዎች ጋር መሆኑና የትግሉም ውጤት ተጠቃሚዎች ኢትዮጵያውያን በመሆናችን በነዚሁ የሀገራችን አንባገነኖች፣ ዘረኞችና የህዝብንና የሀገርን ጥቅም በሚሸጡ ህወሓት/ኢህአዴግ ባለስልጣናት አባላትና ደጋፊዎች ላይ ሠፊና ልዩ ልዩ የትግል ስልቶችን ተጠቅሞ ትግሉን ማቀጣጠል ከኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያውያን ይጠበቃል፡፡

 

በየትኛውም የትግል መስመር እየታገሉ ያሉ ሁሉ ትግሉን በማፋፋም ከግብ ለማድረስ አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ የዚህ ትውልድ መከራ እንዲያበቃ እመክራለሁ፡፡ ካልሆነ ግን በሃገር ውስጥ ያለውም ችግር አሁን ካለው በላይ እንደሚባባስ፣ በውጭ ያለውም በስደት እንዲኖር እንደሚገደድና  ንሮውም ከዚህ አሁን ከምናየው በላይ የከፋ እንደሚሆንና ትውልዱም የመከራ ትውልድ ሆነን እንደምንቀር ማውቅ ይገባናል ፡፡

 

በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ የሀገራችን ህዝቦች ሁሉ አሁን በትግል ላይ ያሉ እውነተኛ ፓርቲዎችንና ትግሎችን መደገፍና የትግሉ አካል መሆን  ይጠበቅብናል ፡፡

 

የአሜሪካና የምዕራብ ሀገራትም ለተወሰኑ የዲፕሎማሲና ወታደራዊ ትብብር ብለው ህዝብ ከጠላው፣ የህዝብና የሀገር ጠላት ከሆነና ህዝብን ከሚያሸብር ጋር መወገናቸውን ትተው የኢትዮጵያውያንን ትግል እንዲያግዙና በታሪክም ከተወቃሽነት እንዲያመልጡ እጠይቃለሁ፡፡

 

ዛሬ አረቦች ይህንን ለመፈጸም ምክንያት የሆናቸው የመሪዎቻችንን ወይም የህወሃቶች ሙሰኝነት፣ ግደለሽነት፣ ባንዳነትን፣ ቅጥረኝነትን የሚያገለግሉ መሆናቸውን ባይረዱ ኖሮና ለአገርና ለህዝብ የሚቆረቆሩ አለመሆናቸውን ባያውቁ ኖሮ ዛሬ ባልተደፈርን ነበረ። አረቦች በኢትዮጵያ ምድር ተከብረው እንዳልኖሩ ዛሬ ሬሳችንን ሳይቀር ለመቆራረስ መድፈራቸው ያስቆጫል ያስለቅሳል።

 

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትና ባለስልጣኑም ለኬንታው ኬንያታ እና ለሱዳኑ አልበሽር በአይሲሲ /ICC / ለሚጠብቅባቸው የፍርድ ሂደት ፍርድ እንዳይቀርቡ የተሟገተውን ያህል እንኳን  በአረቡ ዓለም በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃና ህይወትን ለመታደግ ቅድሚያ ሊሰራ የሚገባውን ሁሉ ባለመስራቱና ለሙግት ባለመነሳቱ አዝናለሁ ።

 

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትም ምንም ኢትዮጵያዊነት ስሜትም ሆነ ፈቃድ በሌላቸው የህወሓት ባለሟሎች ለ22 ዓመታት መመራቱም ሌላ ተጨማሪ መከራን አምጥቶብናልና ይህንን ለመቀየርና ለማስተካከል ሁሉም ኢትዮጵያውያን መነሳትና ባስጨከኑብን ላይ መጨከን አሁን ይኖርብናል። ትልቅ መሰዋትነትን የሚጠይቅ ትግል ከፊታችን ተደቅኖብናል። አረቦች ህወሃትን ደግፈው እዚህ ሲያደርሱት ዛሬ ይህንን ለመፈጸም እንደሚያስችላቸው ጭምር ተረድተው ነው። ከዚህ በኃላ ግን ኢትዮጵያና ህዝቦቿ የአረቦች መጫወቻ እንዳንሆንና አላማቸውንም ለማስፈጸም ተግቶ የሚሰራውን ህወሃትን ከላያችን ላይ ለማንሳት አሁን እንጨክን። ቸር ይግጠመን።

 

እግዚአብሐር ኢትዮጵያን ይባርክ!


Viewing all articles
Browse latest Browse all 1664

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>